የኔ ዘውድ
ለዛ አንደበትሽን ሰምቶ ያ ጠበቃ
ብዕር፣ ወረቀቱን ሌላም ውድ ዕቃ
ሰብስቦ አመጣና ውሰድልኝ ብሎ
ገዳም ገባ አሉኝ ተገዝቶ ምሎ
አይታው ባለ ሞያ ትዕግስትሽ ማሩን
ጠጅ ጥላ አመጣች የምጠጣውን
ጠጥቼ እንድረካ፣ ደግሞም እንድተኛ
ነይና ከጐኔ ገደም በይልኛ!
ክቱ ገላሽን፣ ሽንጥ፣ ዳሌሽን
አርኪቴክቶች አይተው ያን ቁመናሽን
ማመን ቢያቅታቸው ሲያዩኝ ካንቺ ’ጋ
ወፈፍ አድርጓቸው ዓበዱ በመንጋ
ወርቁን አመልሽን ቢያየው አንጠረኛ
አጊጦ፣ አሳምሮ፣ ሸላልሞ ሰጠኛ!
ይዤው ልዙር ይሆን አጥልቄው ካንገቴ
ወይ እንደ ቀለበት ላድርገው ከጣቴ!
ጥርስሽ ንቅሳቱን አይቶ መሃንዲሱ
መላ-ቅጥ ቢጠፋው፣ ቢታወክ መንፈሱ
ኮምፕዩተሩን ጭምር ወረወረውና
ደብረ ዳሞ ገዳም ገባ ለምነና
ዕንቍ ዓንሽን አይቶ ኮከብ ቆጣሪው
ግራ ግብት ብሎት፣ ጥንቆላም ጠፋው
ታድያ ተመካክሮ ከአልማዝ ሠራተኛ
እንካ ድፋው ብሎ ዘውድ አመጣልኛ
አሁን እምቢ ብለው ይቀየመኝ ይሆን
አባይ ውሃ ልግባ፣ ሃይቅ፣ ወይስ ግዮን
አረ ምን ይሻለኝ፣ ወይ ጉዴ! ወይ ጉዴ!
ምናችውም ይቅር፣ ለኔ አንቺ ነሽ ዘውዴ።
ገ/ኢ. ጐርፉ።