በኢትዮ-ሶማልያ ጉዳይ ላይ የዋሽንግተን ሜትሮ አከባቢ ኢትዮጵያውያን የአቋም መግለጫ

 

እኛ በሰሜን አሜሪካ ማለትም በቨርጂንያ፣በሜሪላንድና በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ኗሪ የሆንን ኢትዮጵያዊያን በወቅቱ የሃገራችን ጉዳይ ላይ ግልፅና ጠለቅ ያለ ውይይት አካሂደናል፡፡

 

ኢትዮጵያ ሃገራችን ራሷን ለመከላከል በቅድሚያ እልህ አስጨራሽ ሁሉን ዳሰስ የሰላምና የዲፕሎማሲ ጥረት ያለመታከት መውሰዷን አጢነናል፡፡የሰላሙና የዲፕሎማሲው ጥረት ተሟጦ ሉዓላዊነታችን ላይ አደጋ በመጋረጡ ሕጋዊ የመከላከል እርምጃ በመውሰድ ጀግናው ሰራዊታችን ለወገን አስመኪ ለቀሪው የዓለም ህብረተሰብ እጅግ አስደናቂና ቅፅበታዊ ድል መጎናፀፉንም የተከታተልነው በታላቅ የሃገርና የወገን ፍቅርና ወኔ ነው፡፡በመሆኑም በዛሬው ዕለት ጃንዋሪ 21 ቀን 2007 በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ የሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ባካሄድነው ስብሰባ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

 

1.     ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በሶማልያ እስላማዊ ሸንጎ አክራሪና ፅንፈኛ አመራር፣በዓለም አቀፍ ሽብርተኞችና በሃገር ውስጥ ጋሻጃግሬዎቻቸው፣በሻዕቢያ አስተባባሪነትና በአይዞህ ባዮቻቸው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በሃገራችን ላይ ያንዣበበውን የአደጋ ዳመና በመበተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን ባስደነቀ መብረቃዊ ፍጥነት በ “አርእድ ወአስደምም” (Shock and Awe) ጀብዱ የጠላትን አከርካሪ በመስበር ያስመዘገበውን ነጎድጓዳማና ኣሸብራቂ ድል የኛን የኢትዮጵያውያንን የቆየ የአትንኩን ባይነት ቅርስን ያደሰና የአዲሱን ትውልድ የዴሞክራሲያዊ አንድነት ቁርጠኝነትን ያጎላ አኩሪ ታሪካዊ ክንውን እጅግ በመርካታችን ፍፁም አጋርነታችንንና አለኝነታችንን በጥልቅ ኢትዮጵያዊ ወኔና ግዙፍ መንፈሳዊ ኩራት እንገልፃለን፣

 

2.     ሰራዊታችን ካስመዘገበው ተአምራዊ ድል ሌላ ሃገራችን ይህ ቀረሽ የማይባል ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድል በመቀዳጀት ዛሬ የዓለም ተምሳሌት ተብላ ተጠቃሽ የመሆንዋ ሚስጢር የመንግስታችን የሰከነ፣ብልህና ጠቢብ አመራርና የህዝባችን በሳል፣ንቁና ወደር የለሽ አጋርነትና ደጀንነት ቀጥተኛ ውጤት መሆኑን በመገንዘብ በመሪዎቻችንና በህዝባችን ልዩ ኩራት የተሰማን መሆኑን በሙሉ ልብ እንገልፃለን፣

 

 

3.     በተፈጠረው አመቺ አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያና የሶማልያ ህዝቦች ትስስር ከምንጊዜም በላይ ይጠነክር ዘንድ ዘርፈ ብዙ መንግስታዊና ህዝባዊ የመቀራረብ እርምጃዎችን በማያባራ መልኩ በመውሰድ ለዘለቄታው አስተማማኝ መደላድል መፈጠር ጥረቱ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናስተጋባለን፣

 

4.     መፃኢውን አዲሱን ሚልየነም በአዲስ ራእይ እንቀበለው እያልን በሃገራችን በሳል የፖለቲካ ባህል፣አካታችና አቀራራቢ፣የፖለቲካ ውይይትና መቻቻል አብቦ ለህግ የበላይነትና ለህገ መንግስታዊ ስርዓት ተገዥነት አንዱ እሴታችን ሆኖ እንዲያጎመራ በበኩላችን የተቻለንን ተግባራዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁነታችንን እንገልፃለን፣

 

 

5.     ከእንግዲህ አገራችን ከኋላቀርነት፣ከድንቁርናና ካለችበት የድህነት አረንቋ ወጥታ የህዝቦቿ የተሻለ ኑሮና የወደፊት ተስፋ ይለመልም ዘንድ ባለን ሁለንተናዊ አቅም፣በኢንቨስትመንት፣በንግድ፣በማህበራዊና በሌሎችም ዘርፎች የነቃ ተሳትፎ ለማበርከት እንረባረባለን፣

 

6.     እኛ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተጠለልንባቸው አገሮች ዘንድ የሃገራችን ገፅታ አዎንታዊነት እንዲጎላ፣አገራችን ለልማትዋ፣ለሰላምዋ፣ለዴሞክራሲያዊ ትልሟና ለመልካም አስተዳደር ራእይዋ አጋዥና ምርኩዝ የሚሆናት ድጋፍ እንድታገኝ ሁለገብ ጥረትና ትግል እናካሂዳለን፣

 

 

7.     የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረ-ሰቦች ፍትሃዊ እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በአንድ በኩል ብሄራዊ ኢትዮጵያዊነት የትስስር መንፈስ በሌላ በኩል ተጣጥመውና ተመጋግበው አዲሲቱ ኢትዮጵያ በፍቅር፣በመቻቻል፣በመደጋገፍና በመተሳሰብ በህዝቦቿ ቅን ጥረት ትገነባ ዘንድ የበኩላችንን አበርክቶ ለማድረግ በትክክለኛው የሃገር ፍቅር ስሜት መነሳሳታችን አበክረን እንገልፃለን፡፡

 

8.     እኛ ኢትዮጵያውያን “በሃገር ጉዳይ ላይ አንለያይም” በሚል እምነት ለቀጣዩም ሃገራዊ ጥቅማችንን በሚያስቀድሙ፣የህዝባችንን አንድነት፣ደህንነት፣ዕድገት፣ልማትና ሰላም በሚያሳኩ እንዲሁም የሃገራችንን ሉዓላዊነት በሚመለከቱ የጋራ ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን አብረን ለመጓዝ ቃል እየገባን ለዚሁም ጥረታችን ስምረትና ስኬት ይረዳን ዘንድ “Ethiopian National Interest Promotion Network” “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጉዳይ አራማጅ ኔትወርክ” የተሰኘውን መድረክ መመስረታችንን በአንድ ድምፅ እየገለፅን በዚህ መድረክ አስተባባሪነት ሃገራዊ ግዴታችንንና ሃላፊነታችንን እንደምንወጣ በዚህ ቅዱስ ዓላማ መሳካት በዓለም ዙርያ ያሉትን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለማነሳሳት ቃል ኪዳናችንን እናድሳለን!!

 

    የስብሰባው ስፖንሰሮች

 

··        Ethio-American Group

··        Ethiopian Consensus Forum

··        Ethiopian Public Affairs Committee

··        Union of Tigreans in North America / U.T.N.A/

··        Hager Fekir Radio

 

 

                                       የኢትዮጵያውያን ሲቪክ ማህበራት

                                               አስተባባሪ ኮሚቴ

 

                                       January 21,2007

                                       Washington, DC