ፕሬስ ሪሊዝ

ጥቅምት 2ዐ ቀን 2ዐዐዐ

የኢፌዴሪ ማስታወቂያ ሚኒስቴር

 

 

የሲፒጄ ውንጀላ ሃሰተኛና መሰረተ ቢስ ነው

 

      በአንድ ሃገር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ሁኔታዎች መካከል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አንዱ ነው፡፡ ይህ መብት በተሟላ መልኩ ሊከበር የሚችለው የፕሬስ ነፃነት መብት ሲረጋገጥ ነው፡፡

 

      የፕሬስ ነፃነት ከብዙ ውጣ ውረድና መስዋዕትነት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ዕውን የሆነው ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ መሆኑም ግልፅ ነው፡፡ ቀደም ባሉት መንግሥትት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተነፍጓቸው የኖረ ከመሆኑም በላይ የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ሂደትን ያላለፈ የፕሬስ ውጤት ሊታተም የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ዜጐች ባደረጉት መራራ ትግል በላያቸው ላይ ተንሰራፍተው የነበሩ አገዛዝ ሥርዓቶችን በማስወገድ ከ1983 በኋላ የፕሬስ ነፃነት መብታቸውን አስከብረዋል፡፡

 

      ከደርግ ውድቀት በኋላ ዜጐች የፕሬስ ነፃነት መብታቸው ተጠቃሚ መሆን ስለነበረባቸው በሽግግር ወቅት ቻርተርና ይህን ተከትሎም በወጣው የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ህግ  ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡ የፕሬስ ውጤቶች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታም በኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋት ችለዋል፡፡  ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው የአገሪቱ ህገመንግሥት ህገመንግሥታዊ ዋስትና አግኝተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የፕሬስ ነፃነት መብት ተጠቃሚነት የበለጠ እየጐለበተ እንዲሄድም አስችሏል፡፡

 

      ይህን ህገመንግሥታዊ መብት በመጠቀም ባለፉት 17 ዓመታት የተለያየ ይዘትና ስያሜ ያላቸው በርካታ ጋዜጦችና መጽሄቶች ለህትመትና ስርጭት በቅተዋል በመስከረም ወር 2ዐዐዐ ዓ.ም. አገራዊ ስርጭት ከነበራቸው ፕሬሶች መካከል ስልሳ ስልሳ አንድ ጋዜጦችና አሥራ አምስት መጽሔቶች በድምሩ ሰባ ስድስት የፕሬስ ውጤቶች በስርጭት ላይ ይገኛሉ፡፡  ከዚህ ውስጥ ስልሳ ያህሉ የግል ይዞታነት ያላቸው ሲሆኑ አሥራ አንድ ያህሉ በፖለቲካና በሃይማኖት ድርጅቶች አንደዚሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ባለቤትነት የሚመሩ ናቸው፡፡ አምስት ያህሉ መንግሥታዊ ናቸው፡፡

 

      ከእነዚህ ውስጥ 27 ጋዜጦች በፖለቲካ፣  ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ ከቀሪዎቹ ውስጥ 1ዐ ያህሉ በስፖርት፣ 9 ደግሞ በንግድና ማስታወቂያ፣ 7 ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡  ይህ መረጃ የአገሪቱን የፌዴራላዊ ሥርዓት ተከትለው በተደራጁት ክልሎች ያለውን የፕሬስ ሥራ አያካትትም፡፡

 

      በኢትዮጵያ የህትመት ውጤቶች ብቻ ሳይሆን የብሮድካስት አግልግሎት የማስፋፋት ሥራም ተጠናክሮ እየተካሄደ ነው፡፡ በአገሪቱ ያሉትን የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት የማስፋፋት ጥረት አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ሬዲዮ በስምንት የአገር ውስጥ ( አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግረኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አኝዋክ፣ ንዌርና ሃረሪ) እንደዚሁም በሦስት የውጭ ቋንቋዎች ( እንግሊዝኛ፣ አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ)  ስርጭት እያካሄደ ሲሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 2 ቻናሎች በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግሪኛና ሶማሊኛ እንደዚሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ስርጭት እያካሄዱ ነው፡፡ ጣቢያዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስርጭት ሰዓታቸውንም እያሰፉ ናቸው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የክልል መንግሥታትም የሬዲዮ ጣቢያዎችን በስፋት እያቋቋሙ ናቸው፡፡  ከዚህ ውስጥ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልሎች የብሮድካስት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

 

      በአገሪቱ የብሮካስት አዋጅ የማርቀቅና ማጽደቅ ሥራ ተከናውኖ የግል የብሮድካስት ሬዲዮ ጣቢያ የማቋቋም ስራም ተጀምሯል፡፡ መንግሥት ለሦስት የግልና ለንግድ ዓላማ ለተቋቋሙ ተቋማት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ ከአንድ ዓመት በፊት ሰጥቷል፡፡ ተቋማቱ የሙከራና መደበኛ ሰርጭት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የኮሙኒቲ ሬዲዮ የማቋቋምና ስራ ማስጀመር ሁኔታም ይታያል፡፡ የእነዚህ ሚዲያ ተቋማት መስፋፋት የተለያዩ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች እንዲንሸራሸሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ጥረቱም ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው፡፡

 

      የውጭ አገር ዜና ወኪሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተዘረጋው ቀልጣፋ የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት በቋሚነትም ሆነ ለጊዜያዊ ሥራ የሚመጡ ወኪሎች ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት 42 የውጭ አገር ቋሚ የዜና ወኪሎች ፈቃድ አግኝተው እየሠሩም ይገኛሉ፡፡

 

      መንግሥት እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠሩና በየጊዜውም እያጠናከረ በመሄዱ በአገሪቱ ፕሬስ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህ የፕሬስ መስፋፋት ደግሞ ከማንም በላይ የኢትዮጵያን ህዝቦች ለልማትና ብልፅግና የሚያደርጉትን ትግል በብዙ እጅ እያገዘና ለውጤት እያበቃቸው ነው፡፡ ልማት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በእጅጉ እየተፋጠኑ ናቸው፡፡ የተረጋጋ ሰላምና ኢኮኖሚ እንደዚሁም ባለፉት አራት አመታት በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገባቸው ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

 

      በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ታዳጊ ዴሞክራሲ የመገንባት እንደመሆኑ ችግሮች አይኖሩም ለማለት አይቻልም፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያና ሥነ - ምግባር ባልዳበረበት፣ የዴሞክራሲ ባህል ሀሁ በተጀመረበትና እያደገ ባለበት፣ ጐታች የሆኑና ከአለፉት ስርዓቶች የተወረሱ ውስብስብ የአስተሳሰብ ችግሮች ባሉበት አገር መንገዱ አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ችግሮችን እየፈቱና ተሞክሮ እየወሰዱ በጐውን በማጐልበት መጥፎውን በማስቀረት ወደፊት መጓዝ መቻሉ ላይ ነው፡፡

 

      በመሠረቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በ1997 የተካሄደውን ምርጫ የግል ተከትሎ ፕሬሱ የህግ የበላይነትን መርህ የጣሰ አካሄድ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ሙያዊ ሥነምግባርን ያልተከተለ፣ ግላዊ የገንዘብና ፖለቲካ  ጥቅምን መሠረት ያደረገና ስሜታዊነት የተጫጫነው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ውስጥ ወድቆም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ከሲፒጄም ሆነ ከማንም ኢትዮጵያዊና በመስኩ ዕውቀት ያላቸው ምሁራንና አለም አቀፍ ተቋማት የተሠወረ አልነበረም፡፡ የታዳጊ ዴሞክራሲያችን ባህርይም ሁኔታውን አባብሶት በዚህ መንሥኤ የአገሪቱ የወደፊት እርምጃ ላይ እክል ፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ዘላቂ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለመገንባት ቆርጦ የተነሳ አገርና ህዝብ ከዚህ ራዕይ የሚያሰናክለውን ሁኔታ ዝም ብሎ ሊመለከተው አይገባም ነበር፡፡ ተገቢውን ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በመከተል ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች ጥፋተኛነታቸው እስከተረጋገጠ ድረስ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

 

      ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ነኝ የሚለው ሲፒጄ በቅርቡ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የማይወክል ዘገባ ማውጣቱን ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ  ውስጥ የፕሬስ ቅድመ ምርመራ /ሴንሰርሽፕ/ እንዳልተወገደ፣ የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማኀበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ የፕሬስ ውጤቶች እንዳሌሉ፣ በአጠቃላይ የፕሬስ ነፃነት እንደሌለ በማስመሰል መግለጫ ሲያወጣ ይስተዋላል፡፡  ይህን እውነት ለማስመሰልም የአንዳንድ ጋዜጠኞችን ስም በመጥቀስ ለማሳመን ጥረት እያደረገ ነው፡፡

 

      የፕሬስ ነፃነት የህግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ መሆኑ ለሲፒጄ የተሰወረ አይደለም፡፡ በየትኛውም ዓለም ፕሬስ የበለጠ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የህግ ጥበቃ ሲደረግለት ነው፡፡ ሆኖም ሲፒጄ በማንኛውም አገር እንደሚደረገው ከህግ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ጋዜጠኞችን ለማስተካከል የሚወሰድን የህግ ማስከበር ሥራ የጋዜጠኞችን መብት እንደመጋፋት አድርጐም እያቀረበ ነው፡፡ ፕሬስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሳየውን እድገት ሚዛናዊ ሆኖ መመልከትም ተስኖት ይገኛል፡፡

 

      ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት አሁንም የተረጋገጠ ነው፡፡ የፕሬስ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ የፕሬስ ተቋማት ቁጥር በማደግ ላይ ነው፡፡ የመረጃ አቅርቦትን ለማስፋት ተጨባጭ ጥረት እየተደረገ ነው ጋዜጠኞች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ህትመት ከገቡት የግል ፕሬሶች ውስጥ ከህጋዊ ሥርዓቱ ውጭ በጣልቃ ገብነት ሥራ እንዲያቆም የተደረገ ፕሬስ ውጤት የለም፡፡ ሲፒጄም ሆኑ ሌሎች ይህን በሚገባ ተረድተው በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትችት ቢያቀርቡ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ከዚህ በተፃራሪና ስሜታዊ የሆኑ ዘገባዎችን መቀበል የሚቻልበት ሁኔታ ፈጽሞ የሚታሰብ አይሆንም፡፡

 

      ይህ ብቻ ሳይሆን ሲፒጄ እውነታውን ሳያጣራ ወይም ሆን ብሎ ኃላፊነትና ሚዛናዊነት የጐደለው ሀሰተኛ ውንጀላ ውስጥ በተደጋጋሚ መግባቱ ድርጅቱ ለማንና ለምን አላማ እንደቆመም አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ሲፒጄ ራሱንና ውስጡን መርምሮ ይልቁንም ሙያዊ ሥነ- ምግባርና የህግ የበላይነት መርህን ሳይጠብቁ አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ ፕሬሶችን ለማስተካከል በሚያስችል አቅጣጫ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ ለፕሬስ መጐልበት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

 

      ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝቦች ራዕያቸውን ለማሳካት የጀመሩትን ልማትን የማፋጠንና ዴሞክራሲን የመገንባት ጥረት ይቀጥላሉ፡፡ ለብሔራዊ ጥቅማቸው ደግሞ ከራሳቸው በላይ ማንም ዘብ ሊቆምላቸው እንደማይችል ጠንቅቀው ይረዳሉ፡፡ ፕሬስ በኢትዮጵያ እንዲጐለብት የማድረግ ጥረታቸው የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደረገውም በራሳቸውና ለራሳቸው ተፈላጊ በመሆኑ እንጂ ማንንም ለማስደሰት ብለው እንዳልሆነ ሲፒጄም ሆነ ሌላው ሊገነዘበው ይገባል፡፡

                                               

                                                ማስታወቂያ ሚኒስቴር

                                                አዲስ አበባ