ፕሪስ ሪሊዝ
ጥቅምት 20 ቀን 2000 ዓ.ም
ማስታወቂያ ሚኒስቴር
የድንበር ውዝግቡን በሰላማዊ ዉይይት መፍታት የኢትዮጵያ
ፅኑ ዓላማ ሆኖ ይቀጥላል
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ በሰላም ለመፍታት የማያወላዳ አቋም ይዛ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ባላት ፅኑ ፍላጎት መሠረት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ባለአምስት ነጥብ አዲስ የሰላም ሃሳብ ማውጣቷ የሚታወስ ሲሆን ይህም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት፣ በአውሮፓና በአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም በቀጣናው ባሉት አገሮች ጭምር ድጋፍ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡
አገሪቱ ውዝግቡን በዉይይትና በድርድር ለመፍታት አቋም የወሰደችውም ድህነትንና ኋላቀርነትን የመዋጋት ጥረቷን ለማሳካትና በቀጣናውም ዘላቂ ሰላም የማስፈን ፅኑ ፍላጎቷንና ዝግጁነቷን ከዳር ለማድረስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የልማት እንቅስቃሴ እንዲገታ ዘወትር የጠብ አጫሪነት ትንኮሰዎችን ከማራመድ ተቆጥቦ የማያውቀው የኤርትራ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ልትወረኝ በዝግጅት ላይ ነች በማለት በፈጠራ ላይ የተመሰረተ ክስ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ኤርትራ በሀገር ውስጥና በወጪ አገራት ለገጠማት ቀውስ የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር የቀየሰችው ዘዴ መሆኑ ከዓለም ሕብረተሰብ የተሰወረ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ሙሉ አቅማቸውንና ትኩረታቸውን ወደልማት በማዞር ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ድህነትንም ከአገሪቱ ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ ጦርነት ለማካሄድ እንደማትፈልግና ወደዚያ የሚያመሩ ማናቸውንም ድርጊቶች እንደማትፈጽም በተደጋጋሚ ስትገልጽና ይህንኑም በተግባር ስታረጋግጥ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት የተቀበለችና ድንበር የማካለሉ ጉዳይም በውይይት እንዲፈታ ሃሳብ ስታቀርብ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን በተቃራኒው በሰላም አስከባሪው ኃይል /አንሚ/ ላይ በተደጋጋሚ ችግር ሲፈጥር ከመቆየቱም በላይ ጊዜያዊ የፀጥታ ቀጣናውን በማንአለብኝነት በመጣሱ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይልና ከባድ የጦር መሣሪያዎችን በፀጥታ ቀጣና አከማችቷል፡፡ ኢትዮጵያን ፊት ለፊት ለመውረር ምኞቱ ቢኖረውም በተግባር ማድረግ ባልቻለበት ሁኔታ በተላላኪዎቹ በኦነግና በአብነግ እንዲሁም በሶማሊያ አሸባሪዎችና በሌሎችም አማካይነት የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የለየላቸው አሸባሪዎችን በማሰልጠንና የተለያዩ ድጋፎች በመስጠት የምስራቅ አፍሪካን ቀንድ ሰላም በማወክና በመንግሥት ደረጃ የአሸባሪነትን ጎራ የተቀላቀለው የኤርትራ መንግሥት አሁንም ከጠብ አጫሪነት ድርጊቱ ሊቆጠብ አልቻለም፡፡
በአሁኑ ወቅት በኤርትራ በተከሰተው ቀውስ ሳቢያ በባለሥልጣናቱ መካከል እስከ መገዳደል የደረሰ የቡድን ክፍፍል ከመፈጠሩም በተጨማሪ ሙስና በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቷል፡፡ ሕብረተሰቡም ለከፍተኛ የኑሮ ችግር በመጋለጡ በዚያች አገር ያለው ሁኔታ በእጅጉ አስከፊ እየሆነ መጥቷል፡፡ አስከፊውን ሥርዓት በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገራት የሚኮበልሉ ወጣቶችና ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህን የሕዝብ ብሶት አቅጣጫ ለማስቀየርና ውስጣዊ ገበናውን ለመሸፈን የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት በህዳር ወር ወረራ ለመጀመር ተዘጋጅቷል በማለት ማወጅ ጀምሯል፡፡
ኢትዮÉያ ከአሁን በፊት ስትገልጽ እንደቆየችው ሁሉ የድንበር ውዝግቡ በዲፕሎማሲያዊ ዉይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ሊፈታ እንደሚችል ስለምታምን ማናቸውንም ወደ ጦርነትና ግጭት የሚወስዱ እርምጃዎችን በፅኑ ትቃወማለች፡፡ የጦርነት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ስጋቶችን ከማስቀረት ውጭ በምንም ዓይነት መልኩ ኢትዮጵያ የጦርነት መንስዔ ልትሆን እንደማትችል መላው ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ይገነዘቡታል፡፡
የኤርትራ መንግሥት የድንበር ውዝግቡ በዉይይትና በድርድር እንዲፈታ በተደጋጋሚ የቀረበለትን ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ መርገጡም ኪሣራ እንጂ ትርፍ እንደማያስገኝለት አሁንም ሊገነዘብ ይገባል፡፡
ማስታወቂያ ሚኒስቴር አዲስ አበባ
# # #