የምሁራን ደናቁርት

 

ምሁር ማለት ምን ማለት ነው? ፊዴል በመቁጠሩ፣ “ሀ ሁ” ስለ ማለቱ፥ ሰው ማንነቱን ካላወቀ፣ የሚያምርበትና የሚያስቀይምበትን፣ የሚያኰራውና የሚያዋርደውን ካልለየ “ምሁር” መባሉ ምንድነው? ይህ ዓይነቱ ሰው ምሁርነቱ ቀርቶ እንዲያው ሰብዓዊነቱና የአዕምሮ ጤንነቱም ለብዙ ሰው የሚያጠራጥር ነገር ሳይሆን ኣይቀርም።

 

በኣሜሪካና ኤውሮጳ የሚገኙትን ጥቂት ምሁራንን ብንመለከት በፖለቲካዊ ቅዥት ተወናብደው፣ ግራ ተጋብተው፣ ደጉና መጥፎውን ሳይለዩ፣ ለሃገር ጠቃሚውና ጎጂውን መለየት ተስኗቸው ሲወዛገቡ፣ የባዕድ መሣሪያም ሆነው ሲቅበዘበዙ እናያለን። በጣም የሚደንቅ፣ የሚያስገርምና ኣሳዛኙም ሁኔታ በእነዚህ ሰዎች ሲፈጸም፣ እነርሱ ግን ከኛ በላይ ማን ዓዋቂ ኣለ የሚል ትዕቢተኛ ኣቋም ይዘው ሲመላለሱ ይታያል።

 

መለስ ብሎ ላየውና ላሰበበት ሰው ጉዳዩ ኣጅግ ቀላልና ያልተወሳሰበ፣ ግልጽም ነው። ይህን ማየት የተሳናቸው በፖለቲካ እንካስላንትያ ግራ የተጋቡት ምሁራንና ሊቃውንቱ  ብቻ ናቸው። ይህም ድሮ ኣንድ  በታሪክና ምሳሌ የተጻፈውን ታሪክ ያስታውሰናል።

 

ሦስት ምሁራን፣ ‘ሊቃውንት’ የተባሉ ሰዎች ከኣንድ ገበሬ ጋር ሲጓዙ ብትንትን ያለ የኣንበሳ ኣጥንት ኣግኝተው፣ በድግምት ኃይል ነፍስ ሊዘሩበት ሲሉ ገበሬው፤ “ጌቶቼ ኣንዴ ስሙኝ፣ ይህ ነፍስ የምትዘሩበት ያላችሁ ፍጡር ኣንበሳ መሆኑን የዘነጋችሁት መሰለኝ፥ እባካችሁ እስኪ ሸሽቼ ከዛፍ ላይ እስክወጣ ለትንሽ ደቂቃዎች ያህል ዕድል ስጡኝና ከዚያ እንደፈለጋችሁ ኣድርጉ…” ብሎ ሸሽቶ ሲያመልጥ፣ ሊቃውንቱ ግን ራሳቸው ነፍስ የዘሩበት ኣውሬ ተነስተ እንደ ገነጣጠላቸውና እንደ በላቸው የሚነግር ታሪክ ኣለ። ታሪኩም ሲደመድም፤

“እጅግም ስለት ይቀድዳል ኣፎት

እጅግም ብልሐት ያደርሳል ከሞት!” ይላል።

 

ኣንድ ሰው ምንም ቢሳሳት እንዴት የሀገሩን ማንኛውም ሁኔታና ሉዓላዊነትን ዘንግቶ ወሳኝነቷን ለባዕድ መንግሥታት ኣሳልፎ ለመስጠት ይከጅላል? ይህ ነው ጥያቄው። ኢትዮጵያ ኣሁን ከብዙ ምእት ዓመታት ዕንቅልፍ የነቃችና፣ ለመጀመሪያ ጊዜም የዴሞክራሲ ጭላንጭል ገብቶ ብልጭ ድርግም እያለ የሚገኝባት ያለች ሃገር ናት። እንደ ማንኛው ሕፃንም ብድግ ብላ ከመሮጥዋና ከመሽቀዳደምዋ በፊት ዳዴ ብላ መዳኽና፣ እየወደቀችና እየተነሳችም መለማመድ እንዳለባት ለማንም ግልጽ ነው።

 

ምሁራኑ ይህን ሁኔታ ስተው፣ ዛሬ የምናየው ያለን ኣጉል ሕግ ኣርቃቂዎች ሆነው፣ ወደ ባዕድ ኣገር መንግሥታት እየተሯሯጡ፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ካላደረገ በእንዲህ ዓይነት እንዲቀጣ ኣድርጉልን…” እያሉ ሲሞግቱ ድንቅ ትዕይንት ስናይ፤ “በእርግጥ እነዚህ ሰዎች ኣዕምሮኣቸው ጤና ኣላቸው?” ያሰኛል። ይህንን ጉድ በኣንክሮ የተመለከተ ኣንድ ወዳጄ፤ “እነዚህ ምሁራን ልክ የኣፈ-ቄሳር፣ የነጋድራስ ኣፈወርቅ ርዝራዦች ናቸው!” ብሎ ደምድሞታል። ታሪኩን የሚያውቅ ይገባዋል።

 

ተራው የሀገራችን ገበሬ፤ “ኣንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለባዕድ መንግሥታት ኣገራችን እንዲህ ካላደረገች እርዳታ ኣትስጧት ይላሉ…” ቢባል፣ “እነዚህን ኣስሮ ዓርባ መግረፍ ይገባ ነበር!” እንደሚል ምንም ጥርጣሬ የለውም። ለዚም ነው ለሁሉም ግልጽ የሆነ፣ ለምሁራን ግን ግራ ያጋባ ሁኔታ ነው ብለን ያልነው። ምን ነካቸው!

 

በደምቡ ለሃገር ተቆርቋሪ ከሆኑ ባለው ደምብና ሕግ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መስርተው መከራከርና መረባረብ፣ ሕገ-መንግሥቱንም በድምጽ ብልጫ እስከ መለወጥ  የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ነው። ያም ኣልሠራ ሲል ከዚያ ውጭ የሆነው ታሪካዊ የጀግና ደምብ፤ ሱሪ ታጥቆ በርሃ በመግባት፣ ለሀገርና ለሕዝብ መብት መዋጋት፣  መሞት፣ ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ያለ ነው። ከዚያ ውጭ ግን በእጅ ኣዙር የባዕድን ኃይል በሃገራችን ላይ እንዲሰነዘር የሚያደርግ ማንም ሰው የኢትዮጵያ ከሓዲ ነው።

 

ሁሉም ኢትዮጵያዊና ለሃገሩ ተቆርቋሪ የሆነ ሰው ሁሉ እነዚህን ኣጉል ምሁራንና፣ የምሁራን ደናቁርትን ሊጸየፋቸውና ሊያገልላቸው ሲገባ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም በከሓዲነት ሊወነጅላቸው፣ ክስም ሊመሰርትባቸው ይገባል። ቀርበው ከተከራከሩና ከተሟገቱ ደግ፣ ካልቀረቡም በሌሉበት ተፈርዶባቸው፣ ሕጋዊ ክትትል ሊደረግባቸው፣ በደምቡም መሰረት ሊቀጡ ይገባቸዋል። የምሁራን ደናቁርት ከሓዲዎች ናቸው።

 

                                               ገ/ኢ. ጐርፉ

                                        08/04/07