Back to Front Page


Share This Article!
Share
የዘጠና ቀናት ትሩፋቶች

የዘጠና ቀናት ትሩፋቶች

ወንድይራድ ኃብተየስ 06-30-18

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ቦታዎች ባደረጓቸው ንግግሮች ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያስብል ደረጃ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል። ከአገር ቤት ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንም "በርታ፣ ተበራታ ከጎንህ ነን" በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል። ከቃላት ባለፈም በሠላማዊ ሠልፍ ጭምር ድጋፋቸውን ገልጸዋል። እየገለጹም ይገኛሉ። በቃላት በሚገለጽ ንግግር ብቻ አይደለም። ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአካል ተገናኝተው ሲመክሩም ተስተውሏል።

 

ሕዝቡም የዓመታት ችግሮቹን አነሳስቶ በግልጽ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ጠይቋል። ከአገሩ ኢትዮጵያ በላይ ምንም የሚያስቀድመው ነገር እንደሌለ በማረጋገጥ ጭምር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን ኩሩና ታታሪ ሕዝብ በመምራት ታላቅ ተግባር መከወን እንደሚቻል አረጋግጠዋል በንግግሮቻቸው።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክቶቻቸው አጽንኦት የሰጡት ነገር ቢኖር ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በሰከነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል ነው። ይህም ጉዳይ በእምነት ተይዟል። የጋራ መግባባት ላይም ተደርሷል።

 

በተለይ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ወገኖች ትልቅ ሥራ ሊከውን የሚችለውን የሰው ኃይል አባክነዋል፤ መልካም አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙባቸው እንዲሁ እንደዋዛ አልፈዋል። ዛሬ ከዚያ አስተሳሰብ ተላቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በተጀመረው የለውጥ ጎዳና ላይ የራስን ድርሻ ለማበርከት መነሳሳት አሳይተዋልና ሊደገፉ ይገባል። በእርግጥም መንግሥት በዚህ ረገድ ትልቅ ርምጃ ወስዷልና ያስመሰግነዋል።

Videos From Around The World

 

የዚህች የጋራ አገራችን የዓመታት ችግሮች የሚቀረፉትና ወደተሻለ ደረጃ መሸጋገር የሚቻለው በቀና መንፈስ የለውጥ ኃይል ሆኖ መደመር ሲቻል ነው። እዚህ ላይ የሁሉም ችግሮች መፍትሄ የሚገኘው ከአንድ ግለሰብ ነው ብሎ መጠበቅም፤ ማሰብም አይገባም። ተጠቃሚ መሆንም አይቻልም። የዜጎች ኑሮ ተለውጦ የአገር ዕድገትና ብልጽግና የሚመጣው ኢትዮጵያውያን በጋራ ተባብረው ለአንድነት ሲተጉ ብቻ ነው፡፡ ምርጫቸውም ይኸው ነውና።

 

ዶክተር አብይ አህመድ ዘጠና ቀናት ባልሞላው የጠቅላይ ሚኒስትርነት የኃላፊነት ጊዜያቸው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከሕዝብ ጋር መክረዋል። ይህ ሁኔታ በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖም አልቀረም። በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በሣውዲ አረቢያ፣ በኤምሬትስ፣ በኡጋንዳ፣ በግብጽና በሶማሊያ የሥራ ጉብኝቶች አድርገዋል። ጉብኝቶቹም ለኢትዮጵያ ታላቅ ጠቀሜታን አስገኝተዋል። ኢትዮጵያ ከተተበተቡባት ችግሮች ተላቃ በጋራ ጥቅም ላይ ወደተመሠረተ ብልጽግና ለመሸጋገር ጽኑ አቋም እንዳላት ለዓለም ያሳየችበት አጋጣሚ ነበር። ኤርትራን ጨምሮ ከጎረቤት አገራት ጋር የመተማመን መንፈስ ለመፍጠር አስችሏታል። ትብብሮችን በበለጠ ደረጃ ለማስቀጠል መሠረት ተጥሎበታል።

ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩ ሠላምና የምጣኔ ሀብት ትስስር መጎልበት ዛሬም የፀና አቋም እንዳላት ለዓለም ያሳየችበት መልካም አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ኢትዮጵያ የወደብ ልማትን ከጎረቤት አገራት ጋር በመሆን በትብብር ለማካሄድና ለማስተዳደር መስማማቷ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉብኝታቸው ትሩፋቶች መካከል ተጠቃሹ ነው። በእነዚህ አገራት ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መብቶቻቸው እንዲከበሩም የጉብኝቱ ሌላው ጠቀሜታ ነው። በእነዚህ አገራት ውስጥ ለረዥም ዓመታት በእሥር ሲማቅቁ የኖሩ ዜጎች ከእሥር ተፈተው ወደ አገራቸው የተመለሱትም በዚሁ ወቅት ነው።

ቀጠናውን በመሠረተ ልማት በማስተሰሰር አገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ለማስቻል የኢትዮጵያ ቁርጠኛ አቋም ለዓለም ሕዝብ የተገለፀበት ነበር። ከኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገው ምክክር በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘ ድል ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል።

በተለይ ጂቡቲ የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚስተናገድባት አገር ናት። ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር መስመር የተሳሰረች ናት። ወደቧን በጋራ ለማልማት ከስምምነት ተደርሷል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመሪዎቻቸው በኩል የደረሱት የመሠረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት ኢትዮጵያን በጅቡቲ የወደብጅቡቲንም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ባለ ድርሻ የሚያደርጋቸው ይሆናል።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ ከወደብ አልፈው በእርሻና በመንገድ ልማቶች ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመሥራትም ተስማምተዋል። ይህ ሁኔታ ለኢትዮ - ጅቡቲ ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን ታምኖበታል -ሌላው የጉብኝቱ ትሩፋት።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት የተፈራረሙት ስምምነት ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን ለብቻዋ የምትጠቀምበትን ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከስምምነት ላይ ያደረሳት ነው።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያም ሁለቱ አገራት የጋራ አቋም ይዘዋል። ሱዳን ግድቡን በገንዘብ እስከ መደገፍ የሚያደርስ ትብብር ለማድረግ ቁርጠኛነቷን አሳይታለች። አዲስ አበባን ከካርቱም በባቡር መስመር ለማስተሳሰር ከስምምነት ተደርሷል። የንግድና የኢንቨስትመንት ልውውጡ እንዲጠናከር ቁርጥ አቋም ተይዟል። እነዚህ ጉዳዮች ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይታመናል።

በኬንያ ጉብኝት ያደረጉት ዶክተር አብይ በምጣኔ ሀብትናፀጥታ ጉዳዮች፣ በላሙ ወደብ ልማትና ኬንያ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ባሰበችው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ አተገባበር ዙሪያም ከአገሪቱ መሪ ጋር መክረዋል። ይህ ብቻም አይደለም! የኢትዮጵያና ኬንያ ሞያሌን የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስናንግድ ማዕከል እንድትሆን በጋራ ለማልማት ከስምምነት ተደርሷል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ጆሞ ኬንያታ የጀመሯቸው የልማት ትብብርና የህብረት ራዕይን ለማሳካት የሁለቱ አገራት መሪዎች ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን መሠረት ያደረገ ሁለቱ አገሮች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ በቱሪዝም መስክ ለመተባበር ተስማምተዋል። አገራቱውኃ ሐብት አጠቃቀም፣ በፀረ ሽብር ዘመቻ በሶማሊያ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ከስምምነት ደርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጅቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ ባደረጓቸው የሥራ ጉብኝቶች የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ተግባራትን አከናውነዋል። በዚህም "ከጉብኝቶቹ ምን አተረፍን?" ቢባል "ትሩፋቶቹ ከዚህም የላቁ ናቸው" ምላሹ ይሆናል። በሣውዲ አረቢያ፣ በኤምሬትስ፣ በኡጋንዳ፣ በግብጽና በሶማሊያ ካደረጓቸው የሥራ ጉብኝቶችስ ምን አተረፍን? በሌላ ጊዜ የዳሰሳ ጽሁፌ እመለስበታለሁ።

 

 

 

Back to Front Page