Back to Front Page


Share This Article!
Share
እናንተ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች የዕርቀ-ሰላም እና የኢትዮጵዊነት አንድነት ቃል ኪዳን ሕያው ምስክር ናችሁ!!

እናንተ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች የዕርቀ-ሰላም እና የኢትዮጵዊነት አንድነት ቃል ኪዳን ሕያው ምስክር ናችሁ!!

በተረፈ ወርቁ 09-26-18

ከሰሞኑን በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩ፣ በቡራዩ ከታ፣ በአሸዋ ሜዳ፣ በአስኮና በአካባቢው በተከሰተው ኢሰብአዊ ድርጊት፣ ግድያ፣ ዝርፊያና መፈናቀል የተነሣ የታቃውሞ ድምፃቸውን ለማሰማት በአርባ ምንጭ ሰልፍ የወጡ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው በምንም መንገድ እጃቸው ለጥፋት፣ ለበቀልና ለክፋት እንዳይነሳ እንደ ጋሞ ማኅበረሰብ ባህል ለምለም ሳርና ቅጠል ይዘው ሕዝባቸውን ስለ ፍቅር፣ ስለ ምሕረትና ይቅርታ በአንድነት በጽናት ይቆሙ ዘንድ የተማጸኑ የጋሞ አባቶችና ሽማግሌዎች የኢትዮጵያዊነት አንድነትና የፍቅር ቃል ኪዳን ውል ሕያው ምስክር ናቸው፡፡ እነዚህ ስለ ፍቅር የሰበኩ፣ ይቅር ባይነት ያወጁ፣ ቂም በቀልን ያወገዙ የጋሞ አባቶች፣ የኢትዮጵያዊነትን የአንድነት ቃል ኪዳን ከፍ ያደረጉ ጀግኖቻችንና ባለውለታዎቻችን፣ የቅንነትና የበጎነት አርአያዎቻችን ናቸው፡፡

Videos From Around The World

የጋሞ ሕዝብ የግጭት አፈታትና የዕርቀ ሰላም የማውረድ ዘመን የተሻገረ ሀገራዊ እሴትን በተመለከተ፤ ‹‹A Women between Two Worlds›› የሚል መጽሐፍ ባለቤት የሆነችው የቦስተን ዩኒቨርሲቲዋ ፕሮፌሰር ጁዲዝ  ኦልምስቲድ፣ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የጥናቷ አካል አድርጋው ነበር፡፡ ጁዲዝ ለዚህ ጥናቷ በአካል በተገኘችበት በዶርዜ ማኅበረሰብ መከከል ከዶርዜ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅላ የራስዋን ቤት ሠርታ ተቀመጠች፡፡ ዶርዜዎቹ “ዶርዜ ሚሽሬ!” ይሏታል፡፡ የዶርዜ ወይዘሮ እንደማለት ነው፡፡

ጁዲዝ ኦልምስቲድ የጋሞ ማኅበረሰብን ታሪክ፣ ባህልና የግጭት አፈታት ዘዴን ለዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ አስተዋውቃለች፡፡ ጁዲዝ ከዚህ ጥናቷ በኋላም ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ተመርቃ በቦስተን ዩኒቨርስቲ (Boston University) ፕሮፌሰር ሆናለች፡፡ ከዚያ ያንን ሥራ ለቃ የራሷን የግጭት አስወጋጅ ኩባኒያ  (Conflict Resolution) ቶኮማ ዋሽንግቶን (Tokoma, Washington) አቋቋመች፡፡ የዚህ የዕርቀ ሰላምና የግጭት የማስወገዱ መንገድና ዘዴ በታወቀው በአሜሪካን  መንገድ አይደለም፡፡ ፕ/ር ኦልምስቲድ የመረጠችው የጋሞን ማኅበረሰብ የግጭት አፈታትና የዕርቀ ሰላም መንገድን ነበር፡፡

አንድ ጋሞ ትላለች ፕ/ር ጁዲዝ፤ ‹‹አንድ ጋሞ ከሕፃንነቱ ጀምሮ፤ ሴት ወንድ ሳይል የማስታረቅ፣ የማቀራረብ መርህ ተክትሎ፤ ተግባራዊም ያደርጋል፡፡ ፕሮፌሰሯ A Women between Two Worlds ስለ ኢትዮጵያውያን ጋሞዎች አኩሪ ታሪክ፣ ባህል፣ የዕርቀ ሰላም ማውረድና የግጭት አፈታት ዘዴዎች ከተጻፉ ጥቂት መጽሐፍት ውስጥ ዋንኛው ነው፡፡

ይህ አፍሪካን ተሻግሮ ለአሜሪካውያን ተምሳሌት የሆነ የጋሞዎች የዕርቀ ሰላም መንገድ በእኛም ሀገር ተገቢው ክብር ተሰጥቶት በትምህርት ተቋማቶቻችን፣ በማኅበረሰባችን ውስጥ በስፋት ቢተዋወቅ፣ በትምህርት መልክ ቢሰጥ፣ እርስ በርሳችን እንደንቀራረብ፣ ከቂም በቀልና ከክፋት መንገድ ይልቅ፣ የዕርቅና፣ የሰላምን መንገድ ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዳናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዛሬም የቁርሾና የበቀል ታሪካችንን ዛሬም በፍቅርና በቅንነት ተነጋግረንና ተማምነንና በይቅርታ ዘግተን ወደፊት ለመራመድ ወደሚያስችልን መንፈስ ልእልና ላይ ገና የደረስን አይመስለኝም፡፡ ለዚህም የሚያተጉን መንፈሰ ጠንካራ፣ የዕርቅ ሰባኪያን እንደ ጋሞ አባቶች ያሉ ሽማግሌዎች፣ አስታራቂዎች በብዙ ያስፈልጉናል፡፡

የትናንትናውና የዛሬው ትውልድ ከገባበት የትናንትና የቁርሾ ታሪክ ውርዴ፣ የተተበተበበትን የዓመፃና የክፋት፣ የጥላቻና የጠላትነት እስራቱን፣ ሰንሰለቱን በጣጥሰው ነጻ የሚያወጡት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ይቅርታን የሚሰብኩ የሃይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሸማግሌዎችና ሰላም አምባሰደሮች ያስፈልጉታል፡፡ የትናንትና የአብሮነትና የአንድነት ውብ ታሪካችንን በቅጡ ፈትሸው የሚያሣዩን፣ ማፈርና መጸጸት በሚገባን የትናንትና ክፉ ታሪካችን ተጸጽተንና አፍረን ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅር ለመባባል፣ ለፍቅር፣ ለዕርቅ የጀገነ ልብ ይኖረን ዘንድ የሚያተጉን የጋሞ ማኅኅረሰብ ዓይነት የሀገር ሽማገሌዎች፣ ይቅርታ ጀግናዎች፣ የሰላም እንደራሴዎች በእጅጉ ያስፈልጉናል፡፡

ይህን የጋሞ ታሪክ አባቶችና ሽማግሌዎች ለአንድነት፣ ለፍቅርና ለይቅርታ የከፈሉትን ዋጋ፣ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ያተሙትን፣ በክፋትና በተንኮል የማይናወጽ ቅንነታቸውን፣ በጎነታቸውን፣ ሰላም ወዳድነታቸውን ብዙዎቻችን በማህበዊ ድረ-ገጾች በአድናቆትና በምስጋና ስንቀባበለው ቆይተናል፤ ይህ የጋሞ ሕዝብ መልካም የሆነ እሴት ከሦስት ዐሥርታት ዓመታት ገደማ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ የሆነ አንድ ክስተትን አስታወሰኝ፡፡ ይህ ክስተት በዚህ ጽሑፌ ላነሳው ወደድኹ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ዘረኛው የአፓርታይድ አገዛዝ በተወገደና ለ27 ዓመታት በግዞት በወኅኒ የቆዩት አፍሪካዊው ጀግና ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ/ማዲባ ከወኅኒ በወጡ ማግሥት በደቡብ አፍሪካውያን ጥቁሮች ዘንድ ዕውቅና እና ተወዳጅነት ያላቸውን የጥቁሮች መብት ታጋይ የሆኑትን ክሪሳኒን የአፓርታይድ ሥርዓት አቀንቃኞች የሆኑ ነጭ አክራሪዎች መኪናቸውን እያሽከረከሩ ሲሔዱ ሳለ በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ደብድበው ገድለዋቸው ሸሽተው ያመልጣሉ፡፡

ይህ አስደንጋጭና አሰቃቂ ዜና በደቡብ አፍሪካ ምድር በተሰማ ቅጽበት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በታላቅ ቁጣና በቀል ቆንጨራ፣ ቢላዋ፣ መጠረቢያ፣ ዱላ፣ ሰይፍና ብቻ በቤታቸው ያገኙትን የነፍስ ወከፍ መሳሪያቸውን ይዘው በመውጣት፤ "የነጻነት ታጋያችን የክሪሳኒ ደም በብዙ ሺዎች ነጭ ሰፋሪዎች ደም ይመለሳል!" በሚል ቁጭት እልክና ቁጣ በነጮች ላይ የበቀል ርምጃቸውን ለመውሰድ ተንቀሳቀሱ፡፡

ሀገሪቱ የጭንቀት ምጥ ውስጥ የገባች መሰለች፡፡ ፍርሃት፣ በቀል፣ የእርስ በርስ እልቂት ዜና ምድሪቱን ክፉኛ አናወጣት፡፡ መልአከ ሞት የጥፋት፣ የእልቂት ሰይፋቸውን መዘው በምድሪቱ አራቱ መዓዘን በተጠንቀቅ የቆሙ መሰሉ፡፡ የፃረ ሞት ድባብ አየሩን ሁሉ ሞላው፡፡ የብዙዎች ልብ በፍርሃት ራደ፡፡ የጥፋት፣ የሞት ደመና በምድሪቱ ላይ አንዣበበ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ምድር በጭንቀት ተያዘች፡፡ በርካታ ነጮች የቻሉት ወደ አውሮፓ ሌሎች ደግሞ ነፍሴን አውጭኝ በሚል ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመሸሽ ጓዛቸውን በፍጥነት መሸከፍ ጀመሩ፡፡

በዚህ የምጥ የጣርና የጭንቀት ወቅት የፀረ-አፓርታይድ ታጋዩ ጀግናው ኔልሰን ማንዴላና የትግል ጓዳቸው አቡነ ዴዝሞን ቱቱ በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው እንዲህ ሲሉ ለሕዝባቸው መልእክታቸውን አስተላለፉ፡፡

"... የሀገሬ ሕዝቦች ሆይ ጥፋትን በጥፋት፣ በደልን በበደል፣ ክፋትን በክፋት ማሸነፍ አይቻልም፡፡ የዘረኝነት ክፉ፣ ብካይ ዘር በልባቸው የተዘራ ክፉዎች፣ ዘረኞች በትግል አጋራችን፤ ወንድማችን ላይ የወሰዱት የጥፋት ርምጃ የነጻነታችንን ጎሕ ፈጽሞ ሊቀለብሰው አይችልም። በልባችን ውስጥ ምንም ዓይነት የክፋት ኃይል ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የፍቅር ኃይል፣ ብርታትና የአሸናፊነት ጽኑ ጉልበት አለ፡፡

ወገኖቼ ሕዝቦቼ ሆይ እለምናችኋለሁ እባካችሁ ለበቀል የተመዘዙ ሰይፎች ወደ ሰገባቸው ይመልሱ። በቀል በቀልን ነው የሚወልደው... ለዚህች ቀን እንድንበቃ አብራችሁኝ ለ27 ዓመታት ያህል የታገላችሁ ጓዶችና ሕዝቦቼ ከአሁን ወዲህ ጥቁሮች፣ ነጮች፣ ህንዶች፣ ሁሉም የሰው ልጆች በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በወንድማማችነት መንፈስ የሚኖሩባትን አዲሲቷን ደቡብ አፍሪካ ለመገንባት፣ ዕውን ለማድረግ በፍቅር እጅ ለእጅ እንያያዝ! ይህችን ከፈጣሪ የተሰጠችን ውብ ምድራችን ዳግም የሰው ልጆች በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ግፍና በደል እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ቃል ኪዳን እንግባ፡፡

በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የበቀል ርምጃ  ሊወስድብን ነው በሚል ፍርሃት ወደ ሀገራቸውና ወደ ጎረቤት ሀገር የሸሹና በመሸሽ ላይ ያሉ ነጭ ወንድሞቻችን የአዲሲቷን ደቡብ አፍሪካ ለመመስረት አብረውን ይቆሙ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ይህችን ውብ ምድር ሰፊ ናት፤ ለሁላችንም ትበቃናለች፡፡ እግዚአብሔር ደቡብ አፍሪካን ይባርክ!"

ከዚህ ከማንዴላ/ከማዲባ ታላቅ ንግግር በኋላ አቡነ ዴዝሞን ቱቱ በግፍ ለተሰዉት የትግል አጋራቸው ሞት ኀዘናቸውን በእንባ ጭምር ከገለጹ በኋላ ለመላው ሕዝባቸው እንዲህ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላለፉ፡፡

"ውድ የሀገራችን ሕዝቦች በምድራችን ላይ ያንዣበበው የጥፋት የእልቂት ደመና ተገፎ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት ይሰፍን ዘንድ ሁሉም እንደየ እምነቱ ለሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት/ሱባኤ እንዲያደርግ፤" ሲሉ መንፈሳዊ መልእክታቸውን አስተላለፉ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብም የአቡነ ዴዝሞን ቱቱን ቃል አክብሮና ተቀብሎ ሁሉም እንደ የሃይማኖቱ ለሦስት ቀናት ያህል በደቡብ አፍሪካ ምድር ከቤተ እምነቶች ውጪ ማንኛውም ዓይነት ሥራና እንቅስቃሴ ተገቶ ሁሉም በንስሓ ልብ የፈጣሪን ምሕረትና ይቅርታ መማጸን ያዘ፡፡ የነነዌን ሕዝብ ንስሓ፣ ከልብ መጸጸትና መመለስ ተቀብሎ ምድሪቱን በምሕረት፣ በይቅርታና በበረከት የጎበኘ አምላክም ደቡብ አፍሪካን በምሕረት፤ በይቅርታ አሰባት፡

በዛች ውብ ምድር በቂምና በበቀል ፈንታ ሰላምና ዕርቅ ነገሡ፡፡ ልባቸው ለይቅርታ፣ ለፍቅር፣ ለሰላም የጨከኑ እንደ ማንዴላ ያሉ በሳልና ብልህ ፖለቲከኞች ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ከጥፋት ታድገው ምድራቸው የሁሉም ሰዎች መኖሪያ "the Rainbow Nation" የሚል የክብር ስም እንድትጎናጸፍ አበቋት፡፡ በሀገሪቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ እንደ አቡነ ዴዝሞን ቱቱ ያሉ መንፈሳዊ አባቶችም ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን አስተባብረው በምሕረት አምላክ ፊት ራሳቸውን በማዋረድ በፍቅር፣ በንስሓና በእንባ የምድራቸውን የግፍና የመከራ ታሪክ በሰላምና በዕርቅ እንዲታደስ አደረጉ፡፡ ፈጣሪም የደቡብ አፍሪካውያንን የንስሓ ጩኸት እንባ ሰምቶ ከጥፋት፣ ከእልቂት ታደጋቸው፡፡ ሰላምና ዕረፍት ለምድሪቱ ታወጀላት፡፡ በመጨረሻም ቂም በቀል በፍቅር ተሸነፈ፣ ክፋት በበጎነት፣ በመልካምነት ድል ተነሡ!!

በጋሞ አባቶች የሰላም እንደራሴነትና ከዚህም ጋር አያይዤ በደቡብ አፍሪካ ተፈጸመውን የዕርቀ ሰላም ታሪክ በመልካም ተምሳሌነቱ ስናነሳ በተቃራኒው ደግሞ፤ እንደሚታወቀው ሀገራችን እየሔደችበት ባለበት የለውጥ ጎዳና ላይ፤ ሰላማችን የሚያደፈርሱ፣ እርስ በርስ በጠላትነት እንድንተያይ፣ እንድንለያይና እንድንነጣጠል የሚያነሳሱን በርካታ እንቅፋቶች እየተከሰቱ ናቸው፡፡ ከሐሰት ፕሮፓጋንዳና የፈጠራ ታሪክን ከማሰራጨት ጀምሮ ክቡር የሰው ልጅን ወልዶ ከሳመበት፣ ዘርቶ ከቃመበት ሀገሩ፣ ከቀዬውና ከመንደሩ በማፈናቀልና ኢሰብአዊ በሆነ ጭካኔ ገድሎ ቁልቁል እስከ መስቀል ድረስ የጫካኔያቸውን፣ የኢሰብአዊነታቸውን ጥግ ያሳዩን ቡኩኖችን፣ ሰነፎችን እያየን ነው፡፡

እነዚህ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት የታሪክ መሠረት ውሉ እጅግ ጥልቅና ምጡቅ መሆኑ ያልገባቸው፣ ወይም እንዲገባቸው የማይፈልጉ፤ ኢትዮጵያዊነት ዋልታና ማገሩ በደምና በአጥንት የቆመ፣ የሰው ልጆች የታሪክና የሥልጣኔ መነሻ፣ ሰው የመሆን ክብርና የላቀና የመንፈስ ልእልና ሕያው አሻራና መገለጫ መሆኑ መቀበል የከበዳቸው ሰዎችና ቡድኖች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የቆመበትን የፍቅር፣ የአንድነት መሠረት ለመናድና ለማፍረስ ታች ላይ ቢሉም ይህ የቀን ሕልማቸው/ቅዠታቸው መቼም የማይሳካ እውነት መሆኑን ደፍረን ልንነግራቸው፣ ልናሳስባቸው እንወዳለን፡፡

እነዚህ ጥቅማቸው የተነካባቸው የጥፋት፣ የክፋት ኃይሎች፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የሰላም ጠላቶች ያለ የሌለ ኃይላቸውን አስተባብረው በክፋትና በጥፋት መንገድ ላይ እየነጎዱ ቢሆኑም መቼውንም አሸናፊ እንደማይሆኑ ሊያውቁ ይገባቸዋል፡፡ የሀገራችን ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም ይህኑን እውነት ለውስጥ ለውጭም ጠላቶቻችን ደግመው ደጋግመው አስረግጠው ነግረዋቸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም!!››

ሁላችንም እንደምናውቀው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ታሪክ ሥልጣን የጨበጠ ወገን ተቀናቃኞቹን መግደልና የተረፉትንም ከሀገር ማባረር ወይም እንዲሰደዱ ማድረግ የሥልጣን ማጠናከሪያ አንድ መንገድ ሆኖ ቆይቶ ነበር፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሀገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ሥልጣን የሕዝብ ማገልገያ ነው ብለው ደፋ ቀና የሚሉ ፍቅርን፣ በጎነትንና ቅንነትን የተላበሱ መሪዎችን እያየን ነው፡፡ እጃችን ከደም ይፅዳ በቀል በኛ ይብቃ፣ ሞት ከንግዲህ ይቁም ከይቅርታ በላይ የተበደለ ሕዝብን መካሻ መንገድ የለም፤ ለቀጣዩ ትውልድ ልማትንና ሰላምን እናውርስ ብለው ለበርካታ አመታት የተበላሹ ነገሮችን ለማስተካከል ያለመሠልቸት ደፋ ቀና እያሉ ያሉ፣ ከኢትዮጵያ አልፈው ለአኅጉራችን አፍሪካ ጭምር መልካም የሆነ ራእይን የሰነቁ ባለ ራእይ መሪዎችን እያየን ነው፡፡

እነዚህ በዘመናችን እያየናቸው ያሉ የፖለቲካ መሪዎች በቅርብ የታሪካችን ዘመን፤ ምናልባትም የኢትዮጵያ ሕዝብ እምዬ እያለ እንደ እናት ከሚጠራቸው ከዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በኋላ ካየናቸው የሀገር መሪዎች የተሻለ የሀገር ፍቅር ያላቸው፣ ፍቅርና ምሕረት ከአንደበታቸው የማይጠፋ፣ የተማሩና የድሆች አባቶች ተብለው ሊወደሱ የሚገባቸው የ21ኛው ክ/ዘመን የለውጥ መሪዎች ናቸው ማለት ያስደፍራል፡፡ እነዚህን ሰዎች እንደ ሀገር መሪነታቸው ለሕዝቡ የተናገሩት፣ ቀን ከሌት አንድነታችን እንዲጠነክር በወሬ ሳይሆን በተግባር ያሳዩትን እኛም  ብንሰማቸውና ለራሳችን ሰላም ስንል ብናግዛቸው ከበቂ በላይ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሕፃናት በደቦ ሲደፈሩ፣ ድሃ ከጎጆው ሲባረር ሰው በተኛበት ሲታረድ የለውጡ ሞተር የሆኑት መሪዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ በተፈጠረው ሰላም ልዩነቶቻቸውን ወደጎን ትተው ደጋፊ ሕዝባቸውን ከጎናቸው በማሰለፍ ለዚች አገር እድገትና ሰላም አብረን ሀገር እንዳትፈርስ ከመንግስት ጎን ሆነን  እንሰራለን፣ የሕግ የበላይነት ይከበር  ብለው የጋራ መግለጫ እየሰጡ ከሚገኙ በቅርቡ ወደ አገራቸው ከገቡ አመራሮች  በላይ በዚህ አረመኔያዊ ተግባር ማን ሊበግን ይችላል፡፡  ይህንን ሕገ ወጥነት ለማስቆም ከጎናቸው ሆነን በሰከነ መንገድ ካላገዝናቸው በመጀመሪያ በጣም የምንጎዳው እኛው ስንሆን በመቀጠል የሚጎዱትና የሚያሳዝኑት ትላንት አጨብጭበን አይዞአችሁ ከጎናችሁ ነን በርቱ ያልናቸው በተግባር ግን የሚረዳቸው ሕዝብ  ያጡ ባለ ራእይ መሪዎቻችን ናቸው፡፡

ስለሆነም ሀገራችን የጀመረችው የለውጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን የሁላችንም ጥረትና በጎ አስተዋጽኦ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ጋሞ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች የሰላም አምባሳደር በመሆን በመካከላችን ጠብን፣ መለያየትን የሚዘሩ የክፋትና ጥፋት ኃይሎችን ማሳፈር ይገባናል፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለነፃነት፣ ለሰው ልጅ ክቡር ማንነት በተከፈለ የፍቅር መሥዋዕትነት ላይ የተገነባ ማንነት እንጂ ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው በአሸዋ ላይ የተመሠረተ በክፉዎች ምክርና ሤራ፣ የጥፋት ዐውሎና ወጀብ የሚናወጽ፣ የሚፈርስ ደካማ ማንነት አይደለም፡፡

ለዚህም ትልቅ ተምሳሌቶቻችን፣ ማሳያዎቻችን ከሰሞኑን በመዲናችን በሆነው አሳዛኝ ክስትት የክፋትን፣ የመለያየትን እኩይ ዘር በመዝራት፣ የቂም ድገስ የደገሱ የክፉዎችን ምክር፣ በዕርቀ-ሰላም መንገድ- ክፋትን በመልካምነት፣ ጥላቻን በፍቅር ያሸነፉ፣ የጋሞ ብሔረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች ናቸው፡፡ በእውነትም እናንተ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች/አባቶች የዕርቀ-ሰላም እና የኢትዮጵዊነት አንድነት የፍቅር ቃል ኪዳን ሕያው ምስክር ናችሁና ልናመስገናችሁ፣ ልናከብራችሁ እንወዳለን!!

ሰላም!!

 

 

 

 

Back to Front Page