Back to Front Page


Share This Article!
Share
ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች

ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች

ኢብሳ ነመራ 06-17-18

ከሃያ ዓመት በፊት ሚያዚያ 28፣ 1990 ዓ/ም ምሽት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ይሆናል ብሎ ያልገመተውን፣ አሳዛኝና አስደንጋጭ ዜና ሰማ። ዜናው  ከኢትዮጵያ ነጻ ሆኖ ከተመሰረተ አምስት ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረው የኤርትራ መንግስት ወታደራዊ ሃይል ከዚያ ቀደም በኢትዮጵያ ወሰንነት የሚታወቁትን የድንበር አካባቢዎች በወረራ መያዙ ነበር። በእለቱ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኤርትራ መንግስት የተፈጸመውን ወረራ የመመከትና ሁኔታውን ቀድሞ ወደነበረበት የመመለስ ዘመቻ አወጇል። በቅድሚያ የኢትዮጵያ ድንበር የተጣሰው በባድመና ሽራሮ አካባቢ መሆኑ ነበር የተገለጸው። ባድመ የወረራው ማጠንጠኛ እንድትሆን ያደረገው አንዱ ምክንያት ይሄው ይመስለኛል። በኋላ ግን በአብዛኛው የሰሜን ትግራይና አፋር አካባቢዎች በወረራ ስር መውደቃቸው ተሰምቷል።

ወረራውን የመቀልበስ ጦርነት መታወጁን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ በቅርብ ጊዜ ታሪክ ታይቶ በማያውቀው ሁኔታ ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ተፈጠረ። ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አባላት ወጣቶችና ጎልማሶች ጦርነቱ ላይ በተዋጊነት ለመሰለፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጽ ጀመሩ። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጦርነቱን ወጪ ለመሸፈን ባላቸው አቅም በሙሉ ድጋፍ ለማደረግ ተረባረቡ። ከተፈጠረ ገና ግማሽ አስርት ያስቆጠረውና ከነጻ ፕሬስነት ይልቅ በግልጽ ራሱን ተቃዋሚው ፕሬስ ብሎ ስርአቱን በሞቦርቦር ተግባር ላይ ተሰልፎ የነበረው የያኔው የግል ፕሬስ ጭምር  ከመንግስት (የህዝብ) መገናኛ ብዙሃን ጋር አንድ አይነት አፍ መናገር ጀመረ፤ ወረራውን መቀልበስ። በዚህ ሁኔታ ከዚያ ወዲህ ምናልባት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በታወጀበት ወቅት ብቻ የታየ ታላቅ ሃገራዊ መግባባት ተፈጠረ። ወረራውን በመቀለበስ የድንበር ሁኔታውን ቀድሞ ወደነበረበት ከመመለስ ዘመቻ ጎን ለጎን ችግሩን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ሃሳብም ይቀርብ ነበር።

Videos From Around The World

በዚህ አኳሆን ወረራውን በመቀልበስ የድንበር ሁኔታውን ቀድሞ ወደነበረበት የመመለስ ዘመቻ ‘ሀ’ ተብሎ ተጀመረ። የአውደ ጦርነት ግንባር ውሎ ዋና ዕለታዊ ዜና ለመሆን በቃ። ኢትዮጵያውያን በቀጥታ በተዋጊነት ከመሰለፍ በተጨማሪ፣ ከያሉበት ሰንጋና ሙክት እየጫኑ መከላከያ ሰራዊቱ የተሰለፈበት ጦር ግንባር ድረስ በመሄድ አርደው እያበሉ ሰራዊቱን ማበረታታቸውን ተያያዙት። የሃገሪቱ ታላላቅ ከያኒያን ጦር ግንባር ድረስ በመሄድ ሰራዊቱን በወኔ ይሞሉ ያዙ። ግንባር ላይ የተሰለፈው መከላከያ ሰራዊት ከጀረባው ሊገለጽ የማይችል ታላቅ የህዝብ ደጀን ነበረው።

እንዲህ እንዲህ እያልን የካቲት 1991 ዓ/ም ላይ ደረስን። በዚህ ወቅት በኢትዮጵያና ኤርትራ የድንበር ጦርነት ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍ የሚቆጠር ተግባር ተከናውነ። ከጀርባው ታላቅ የህዝብ ደጀን የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በዘመቻ ጸሃይ ግባት ባድመን አስለቅቆ የአካባቢውን ድንበር ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ መመለሱ ተነገረ። ይህ በመላ ሃገሪቱ እንደታላቅ ድል ተቆጠረ፤ ታላቅነቱን በሚመጥን የድል አድራጊነትም ስሜት ተከበረ። ህጻናት በድሉ ዜና ቧረቁ፣ አዛውን ጥሪት ጉልበታቸውን አሟጠው በመጨፈር የድል አድራጊነት ስሜታቸውን ገለጹ። ይሄኔ የኢትዮጵያ ህዝብም ሰራዊቱም ወረራውን መቀልበስ እንደሚችሉ ሙሉ የእርግጠኝነት ስሜት አደረባቸው።

ጦርነቱ ቀጠለ። ግንቦት 1992 ዓ/ም ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ታላላቅ የማጥቃት ዘመቻዎችን ማካሄድ ጀመረ። በእነዚህ የማጥቃት ዘመቻዎች የኤርትራ ሰራዊት ከያዛቸው ቀደሞ በኢትዮጵያ ስር የነበሩ መሬቶች ላይ ተጠራርጎ ወጣ። ይህ የሆነው አንድ ወር እንኳን ባልፈጀ ዘመቻ ነበር። በዚህ ዘመቻ ኢትዮጵያ የድንበር ሁኔታውን ቀድሞ ወደነበረበት መለሰች። ይህ የኤርትራን ወረራ በመቀልበስ የድንበር ሁኔታውን ወደነበረበት የመመለስ ዘመቻ ታላቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት ነው። በዚህ ጦርነት መስዋዕት የሆኑ ኢትዮያውያን የሃገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተሰዉ ጀግኖች ናቸው። ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል። እንግዲህ የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ጦርነት ዝርዝር ታሪክ አንድ መጸሃፍ እንኳን እንደማይበቃው አውቃለሁ። ይሁን እንጂ ለአንድ አጭር የጋዜጣ ጽሁፍ መግቢያ ያህል በወፍ በረር እይታ ይህን ይመስላል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦርነት ከዚህ በኋላ ሌላ ገጽታ ያዘ። የድንበር ውዝግቡ በዲፕሎማሲና በህግ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ተጀምሮ የነበረው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ወደመሆን ተሸጋገረ። ሰኔ 1992 ዓ/ም ላይ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአጋሮቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት አነሳሽነት በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ሊቀመነበር የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት አብዱልአዚዝ ቡቴፍሊካ አደራዳሪነት የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራረሙ። ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለቱም ሰራዊታቸውን ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ እንዲመልሱ የሚያደርግ፣ በአዋሳኝ አካባቢው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል የሚሰፍርበትን ሁኔታም የያዘ ነበር።

በመቀጠል ታህሳስ 1993 ዓ/ም የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች በናይጄሪያ አልጀርስ የድንበር አወሳሰንና አከላለል ስምምነት (boundary delimitation and demarcation agreement) ተፈራረሙ። በዚህ ስምምነት መሰረት የሁለቱን ሃገራት ድንበር የሚወስንና የሚያካልል አምስት አባላት ያሉት የድንበር ኮሚሽን ተቋቋመ። በስምምነቱ ሁለቱ ሃገራት ዜጋቸው ያልሆኑ ሁለት ሁለት ሰዎችን የኮሚሽኑ አባል እንዲሆኑ የመመረጥ መብት ተሰጥቷቸዋል። የድንበር ኮሚሽኑ እ ኤ አ በ1900፣ በ1902 እና በ1908 ዓ/ም በኢትዮጵያን በወቅቱ የኤርትራ ቅኝ ገዢ በነበረችው ጣሊያን መሃከል የተደረጉ የድንበር ስምምነቶች እንዲሁም አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶች ላይ በመመስረት የድንበር መወሰንና ማካለል ስራውን እንዲያከናውን ሁለቱም ሃገራት ተስማምተዋል። በአልጀርሱ የድንበር አወሳሰንና አከላለል ስምምነት የድንበር ኮሚሽኑ ወሳኔ የመጨረሻና ገዢ (final and binding) እንዲሆን ሁለቱም ሃገራት ተሰማምተዋል፤ የኮሚሽኑ ወሳኔ ይግባኝ የለውም ማለት ነው።

በዚህ መሰረት የተቋቋመው የድንበር አወሳሰንና አከላለል ኮሚሽን ስራውን ጀመረ። የድንበር ኮሚሽኑ ሚያዚያ 1994 ዓ/ም የድንበር ውሳኔ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ። ይህ ሪፖርት የሁለቱን ሃገራት ወሰን በካርታ ላይ የሚያሳይ ነበር። ኢትዮጵያና ኤርትራ ይግባኝ የሌለውን ይህን ስምመነት ተቀበሉ። በዚህ የኮሚሽኑ የውሳኔ ሪፖርት የሁለቱ ሃገራት የድንበር አለመግባባትና ግጭት ማጠንጠኛ የሆነው የባድመ አካባቢ ወደኤርትራ እንዲሆን ተወስኗል። እርግጥ በሌሎች አካባቢዎች ቀደም ሲል የኤርትራ ወሰን ውስጥ እንዳሉ ይታሰቡ የነበሩ ወደኢትዮጵያ የመጡ መሬቶችም አሉ።

ኢትዮጵያ ስምምነቱን በመርህ ደረጃ ሙሉ በሙሉ መቀበሏን ገልጻ፣ አከላለሉ ላይ ግን ጥያቄ አነሳች። ይህም በካርታ ላይ የተቀመጠው ወሰን የህዝቡን አሰፋፈርና አኗኗር ከግምት ያላስገባ በመሆኑ፣ በችካል መሬት ላይ የማካለሉ ተግባር ሁለቱ ሃገራት በሚያደረጉት ውይይት እንዲከናውን የሚል ጥያቄ ነበር። ኢትዮጵያ በችካል መሬት ላይ ወሰን የማካለሉ ስራ በሁለቱ ሃገራት ውይይት እንዲከናወን የጠየቀችው፣ በካርታ ላይ የሰፈረው ወሰን አንድ መኖሪያ ቤትን፣ ቤተክርስቲያን የመቃብር ስፍራን ወዘተ ሁለት ቦታ የሚከፍል በመሆኑ መሬት ላይ የማካከለሉ ተግባር ይህን ከግምት ያስገባና በዚህ ምክንያት በህዝብ ላይ የሚፈጠረውን ጉዳትና አለመግባባት ለማስቀረት ነው። የኤርትራ መንግስት ይህን የኢትዮጵያ ወሰን የማካለል አካሄድ ጥያቄ ሳይቀበል ቀረ። የድንበር ኮሚሽኑ ወሰን የማካለል ስራም በዚሁ በእንጥልጥል ቀረ። የኤርትራ መንግስት ሁለቱ ሃገራት በአልጀርስ በገቡት የተኩስ አቁም ስምምነት መሰረት ወደድንበሩ 25 ኪሎ ሜትር  ዘልቆ እንዲሰፍር የተደረገውን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስራ በማደናቀፍ ተልዕኮውን አቋርጦ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ አደረገ። በዚህ ሁኔታ በሁለቱ ሃገራት አዋሳኝ አካባቢ ጦርነትም ሰላምም ያልሆነ (no war no peace) ሁኔታ ሰፈነ።

ይህ ጦርነትም ሰላምም ያልሆነ ሁኔታ እስካሁን ቀጥሏል። ሁኔታው በሁለቱ ሃገራት መሃከል መደበኛ ጦርነትን ቢያስቀርም አልፎ አልፎ በሰርጎ ገቦች አማካኝነት የሚፈጸሙ ትንኮሳዎችንና የአጸፋ እርምጃዎችን አላሰቀረም። በድንበር አካባቢ የሚሰማ የተኩስ ድምጽም አልቀረም። በአግባቡ ካልተጠበቀ በማንኛውም ጊዜ በሃይል ለመያዝ የተጋለጠውን የድንበር አካባቢ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሌት ተቀን ሳያሸልብ ሲጠብቅ ቆይቷል፤ አሁንም እየጠበቀ ነው። ለዚህ ተግባር ያለማቋረጥ የመከላከያ ሰራዊት ይመለመላል፣ ይሰለጥናል፣ ይሰማራል፣ ወቅቱ የሚጠይቀው ትጥቅና የሰራዊቱ ስንቅ ይቀርባል ወዘተ። ይህ  ያለማቋረጥ ከፍተኛ የመከላከያ ባጀት መመደብን የግድ ያለ ሁኔታን አስከትሏል።

ይህ ብቻ አይደለም። በድንበር አቅራቢያ የሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ከተሞች ምንም አይነት የልማት ስራዎች የማይከናወንባቸው ባድማ ሆነው እንዲቀሩ አድርጓል። ከተቀረው የኢትዮጵያ አካባቢዎች እጅግ በተለየ ሁኔታ ምንም አይነት የመንግስት የመሰረተ ልማትና ማህበራዊ ልማት ስራዎች አይከናወኑበትም። በማንኛውም ጊዜ አውዳሚ ጥቃት ሊሰነዘርበትና ግጭት ሊቀሰቀስባቸው በሚችሉባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ባለሃብቶች ሃብታቸውን ኢንቨስት የማድረግ ድፍረት በማጣታቸው ከተሞቹ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በነበሩት የፈራረሰ ገጽታቸው ቀርተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ህይወት አንቀላፍታለች። የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ የለም። የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ከሞቱት በላይ፣ ከሚኖሩት በታች የሆነ ተስፋ ቢስ ህይወት እንዲገፉ አድርጓል።

በዚህ ምክንያት በድንበር ኣካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይህ ጦርነትም ሰላምም ያልሆነ ለአስከፊ ኑሮ የዳረጋቸው ሁኔታ እንዲቀየር ለመንግስት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ ምን አይነት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አማራጭ ባያቀርቡም። በቅርቡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደመቀሌ ተጉዘው ከተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎች ተወካዮች ጋር ውይይት ባካሄዱበት ውቅትም ይህ ጥያቄ ተነስቷል።

እንግዲህ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ የሚያዚያ 1994ቱን የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ለመቀበል የወሰነው ይህን ጦርነትም ሰላምም አልባ የሆነ ሁኔታ በማስቀረት፣ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያን ከሞቱት በላይ ከሚኖሩት በታች የሆነ ተስፋ ቢስ ህይወት እንዲገፉ ያስገደደን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየር ነው። ይህን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስማማ ይመስለኛል። ሃገር ህዝብ እንጂ ባዶ መሬት እንዳልሆነ የሚገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት የዜጎቹን መብቶችና ነጻነቶች፣ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ለአደጋ የሚያጋልጥ ውሳኔ ያሳልፋል፤ ተግባራዊም ያደርጋል የሚል ግምትም የለም።

በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይ በኢትዮጵየና በኤርትራ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሁን የሚገኙበትን ከሞቱት በላይ፣ ከሚኖሩት በታች የሆነ ተስፋ ቢስ ህይወታቸው ሊቀየር የሚችልበትን ተጨባጭ ሁኔታ በሰከነ መንፈስ ቢያቀርቡና በጉዳዩ ላይ ቢመክሩ መልካም ነው፤ ከሞቱት በታች፣ ከኖሩት በታች የሆነው ህይወት መቀየር አለበትና።   

 

Back to Front Page