Back to Front Page


Share This Article!
Share
አዲስ አበባ ዘረኝነት እያጠቃት ነው

አዲስ አበባ ዘረኝነት እያጠቃት ነው

ከእውነቱ ይታያል 09-14-18

በአለም ላይ ያለው ልምድ እንደሚያሳየው አንድ ሃገር ሲመሰረት ሃገሩን የሚያስተዳድረው መንግስት አማክሎ ሊመራ ይችል ዘንድ አመች የሆነ ዋና ከተማ የሚያቋቁም መሆኑን ነው። በኢትዮጵያም የሆነው ከዚህ የተለየ አይደለም። በጊዜው የነበሩ ነገስታት ኢትዮጵያ የሚል ሃገር በመሰረቱበት ወቅት ላስተዳደራቸው የሚመች ዋና ከተማ መሰየማቸው አልቀረም። በዚህም መሰረት አዲስ አበባ ዋና ከተማ ሆና ተመረጠች። አዲስ አበባ በዋና ከተማነት ለመመረጧ የተሰጠ ግልፅ የሆነ ምክንያት ባይኖርም አንዳንዶቹ ሁለት መላምቶችን ያስቀምጣሉ። አንደኛው የአዲስ አበባ የአየር ፀባይ ለመኖር የሚመች መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእንጦጦ ከፍተኛ ቦታ ፀጥታ ለማስከበር ጠቀሜታው የጎላ ሆኖ መገኘቱ ነው የሚል ነው። ለኔ ደግሞ አንድ ተጨማሪ ምክንያት ይታየኛል። ይህም አዲስ አበባ አማካይ ከሆኑ ቦታዎች አንዷ ስለሆነች ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ።

Videos From Around The World

ያም ሆነ ይህ ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው እነዚህ ንጉሶች አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አድርገው ሲሰይሙ ከምቾት (comfort) ባለፈ ሆን ብለው ኦሮሚያንና ኦርሞን ለመበደል ያደረጉት ነው ለማለት ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። በወቅቱ የተመረጠችው አዲስ አበባ ባትሆንም ሌላ ቦታ ዋና ከተማ መሆኑ አይቀርም ነበርና። ይህ ሲባል ግን ንጉሶቹ የኦሮሞን ይሁን ሌላውን ህዝብ በሌላ መንገድ አልበደሉም ለማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል።

አዲስ አበባ ዋና ከተማ ሆና የተመረጠችበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን በወቅቱ የነበሩት ንጉሶች በጊዜው በነበራቸው የንቃተ-ህሊና ደረጃ "አንድ ኢትዮጵያ፤ አንድ ህዝብ" በሚል ጠንካራ አቋም ላይ የተመሰረተ ስለነበር አዲስ አበባ በማንም ተፀዕኖ ስር ትወድቃለች ብለው ሊያስቡ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም። በዚህም መሰረት አዲስ አበባ ካንድ ምእተ-አመት በላይ በገለልተኛነት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና አገልግላለች። ኢህአዴግ ሃገሪቱን ከተቆጣተረ በኋላ ግን የድሮው ትርክት ቀረና "ብዙ ብሄሮች፣ ብሄርሰቦችና ህዝቦች ከዛም ኢትዮጵያ" ወደሚል ትርክት ተገባ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የየራሳቸውን ክልላዊ ወሰን መያዝ ጀመሩ። አዲስ አበባን በተመለከተም ከተማዋ ራሷን የቻለች አስተዳደር ሆና ግን ደግሞ የኦሮሚያ የተለየ ጥቅም ሊከበርባት እንደሚገባ በህገመንግስቱ ተደነገገ። በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦሮሞ ተዋላጆች ደግሞ የተለየ ጥቅም ከሚለው አልፎ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት የሚል ሃሳብ ማቀንቀን ጀመሩ። እነዚህ የኦሮሚያ ተወላጆች ይህን የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳታቸው ውሃ ይቋጥራል ወይስ አይቋጥርም የሚለውን ፍሬ ነገር በሌላ ጊዜ የምመጣበት ሆኖ ከላይ በርእሱ እንደተገለፀው አዲስ አበባ ዘርኝነት እያጠቃት ነው የምልባቸውን ምክንያቶች እንደሚከተለው ላብራራ።

አንደኛው አዲስ አበባ   ለኦሮሞ ተወላጆች የተለየ ጥቅም እንድትሰጥ መሞሸሯ ነው። ይህ የተለየ ጥቅም ደግሞ ህገመንግስታዊ እውቅና ተችሮታል። ነገር ግን አዲስ አበባን ሁላችንም እንደምናቃት ከአራቱም የኢትዮጵያ ማእዘናት የመጡ ህዝቦች የሚገኙባት ከተማ ነች። በዚህም መሰረት የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ የተለያየ ቀለማት ያላቸው ህዝቦች የሰፈሩባት፣ የተለያዩ ባህሎች የሚንፀባረቁባት፣ የተለያዩ ምግቦች የሚቀርቡባት ባጠቃላይም የማህበረሰብ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያዊያን ትንሿ የማጃመያ/የመቀየጫ እንስራ (Melting Pot) ነች ብትባል ማጋነን አይሆንም። ታዲያ በምን ሂሳብ ነው በንደዚህ አይነት የህዝቦች ጥንቅር ውስጥ የምትገኝ ከተማ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ለይቸ ልዩ ተጠቃሚ ላድርግ ብላ የተነሳችው፤ ዘረኛ ካልሆነች በስተቀር።

ሁለተኛ አዲስ አበባ ብዙውን ጊዜ እንዲመረጥላት የምትፈልገው ከንቲባ የኦሮም ተወላጅ የሆነ ሰው ነው። ይህን ሁኔታ የሚያጠናክረው ደግሞ በቅርቡ የተካሄደው የከንቲባ ምደባ ነው። እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ያፈራቻቸው እልፍ አእላፍ ልጆች አሏት። እነዚህ ልጆቿ በትምህርት ዝግጅትም ይሁን በሌሎች ክህሎቶች ከሌላው ቢበልጡ እንጅ የሚያንሱ አይመስለኝም። ይህ በሆነበት ሁኔታ አዲስ አበባ ዘረኛ ሆና በአድሎ የኦሮሞ ደም ያለበት ሰው በአጉሊ መነፀር አንዲፈለግ አድርጋ ያውም ያለህዝብ ምርጫ በከንቲባነት እንዲመደብላት ማድረጓ ዘረኝነቷን ያሳብቅ እንደሆነ እንጅ ፍትሃዊነቷን አያመለክትም።

ሶስተኛ አዲስ አበባ አቀማመጧን ያስተካከለችው ለኦሮሚያ ሃይሎች የተለየ ጥቅም ልትሰጥ እንድትችል ሆና ነው። ይህን ከተለያየ አቅጣጫ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያውን ጉዳይ ከልማት ጋ አያይዘን እንመልከተው። አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስቱ ዋና ከተማ በመሆኗ የውስጥም ይሁን የውጭ ባለህብቶች በዙሪያዋ መዋእለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የተለያዩ ከልማትት ጋ የተያያዙ ስራወችን ለማከናወን ማሰባቸው አይቀርም፤ በተጨባጭም እየሆነ ያለው እሱ ነው። ይህ ደግሞ እዛው ሳለ የስራ እድልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች መፍጠሩ ይቀርም። በዚህ ረገድ ደግሞ በወሳኝነት የሚጠቀሙት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው።  ይህም ቢሆን ምንም እንኳን በጎላ መንገድ ባይሆንም አዲስ አበባ ላንድ ወገን የምታሳየውን ውግንና ማሳበቁ አይቀርም።

ሌላውና ዋነኛው አዲስ አበባን ዘረኛ የሚያሰኛት ተግባሯ ደግሞ አሁንም ተፈጥሯዊ አቀማመጧን ተጠቅማ የኦሮሞ ሃይሎች በፌዴራል መንግስቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የበኩሏን የማይናቅ አስተዋፅኦ እያደረገች ያለች ከተማ መሆኗ ነው።  ይህን ጉዳይ ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የተከሰቱትን አለመግባባቶች፣ አመፆችና ግጭቶች በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግ ሲፈፅማቸው የነበሩ አያሌ ስህተቶችን እንዲያስተካክል ረዘም ላለ ጊዜ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲጮህ ኖሯል። ባለፉት ሶስትና አራት አመታት ደግሞ ጩኽቱ ወደ አመፅ ተቀይሮ ከኢህአዴግ ቁጥጥር ውጭ በማፈትለክ የሃገራችን አንድነት አደጋ ላይ ጥሎት የነበረ መሆኑን ሁላችንም የምንረዳው ጉዳይ ነው። በዚህ የአመፅ እንቅስቃሴ ወቅት ደግሞ ቄሮና ፋኖ በሚል ራሳቸውን የሰየሙ ቡድኖች ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። በተለይ ቄሮ የተሰኘው ቡድን የአዲስ አበባን ተፈጥሯዊ አቀማመጥ በሚገባ ተጠቅሞ ትግሉን ጫፍ ላይ አድርሶት የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በዚህም መሰረት ይህ ቡድን የአዲሳባባን ዙሪያ አጥሮ በመያዝ ከምግብ ሸቀጥሸቀጦች ጀምሮ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴወች ወደ አዲስ አበባም ይሁን ከአዲስ አበባ እንዳይገቡና እንዳይወጡ በማድረግ ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በተለየ መንገድ በፌዴራል መንግስቱ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ እንደነበር ለማንም ግልፅ ነው። በዚህም ምክንያት ሁኔታውን ለማብረድ በሚል እሳቤ አብላጫ ድምፅ ያላቸው የኢህአዴግ አመራሮች በተለይም የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች ከድርጅታቸው ግልፅ መርህ በማፈንገጥ በመቧደንና ቀድመው ተደራጅተው አቋም በመያዝ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚንስትር ከኦህዴድ የፈለቀ ሰው እንዲሆን የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ ተሳክቶላቸዋልም። እንደ ኢህአዴግ መርህ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ሳይውል ሳያድር ከድርጅት ሊያባርር የሚችል ተግባር ነበር።

ጠቅለል ባለ መንገድ ሲታይ የዚህ አይነት የመርህ መዘበራረቅ እንዲፈጠር ያደረገው አንዱና ዋነኛው ጉዳይ አዲስ አበባ ውግንናዋን ለቄሮዎች ወይም በሌላ አነጋገር ለኦሮሞ ሃይሎች በማያሻማ መንገድ የቸረች ስለነበረ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል።  በርግጥ እዚህ ላይ አዲስ አበባ ያሳየችው ውግንና ፍትሃዊ ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ምክኒያቱ ደግሞ ቄሮ ከታገለላቸው ዋነኛ ጥያቄወች ውስጥ ዴሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ እኩል ጠቃሚነትና ነፃነት ይካተቱ ስለነበር ነው። ይሁንና ሌሎች ከላይ የተገለፁና ወደፊትም ቢሆን አዲስ አበባን የከበቧት የኦሮሞ ሃይሎች ፍትሃዊ ያልሆነ ጥያቄ በማንሳት እንቅስቃሴ ቢያደርጉ አዲስ አበባ በአድሎ ላይ በተመሰረተና ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ከነእሱ ጋ ወግና ፌዴራል መንግስቱን የማሽመድመድ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ ብሎም ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን ወደኋላ የምትል ከተማ አትመስልም። በዚህ ላይ ደግሞ አዲስ አበባ የቅርብ ተደራሽነቷ ከሌሎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይልቅ ሰፊ ቁጥር ላለው የኦሮሞ ህዝብ በመሆኑ ከዚህ ህዝብ የሚፈልቅ ሃይል የፌዴራል መንግስቱን እጅ ለመጠምዘዝ እንዲችል አዲስ አበባ ሁኔታዎችን ያመቻቸች ከተማ ሆናለች። ከዚህ ስንነሳ አዲስ አበባ በዘር ላይ ለተመሰረተው "የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስርዓተ መንግስት" ዋና ከተማ/መናገሻ  የመሆን ብቃቷ ያከተመላት ይመስላል። ስለዚህ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት በሚሳተፉበት መድረክ ነፃና ግልፅ ውይይት ተደርጎ በአድሎም ይሁን በዘረኝነት ወይም በሌላ ምክንያት በፌዴራል መንግስቱ ላይ ጫና ሊያሳርፍ የማይችል  ወይም ጫናው በጣም እዚህ ግባ የማይባል ገለልተኛ ዋና ከተማ ሊመሰርቱ ይገባል። ካለበለዚያ በአዲስ አበባ ገለልተኛ ያልሆነና ዘረኝነት የተጠናወተው ጣልቃ ገብነት ምክንያት የሃገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ሊጠገን የማይችል ከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።

 

Back to Front Page