Back to Front Page


Share This Article!
Share
ካለፈዉና እራሳችን ከፈፀምነዉ ስህተት መማር ካልቻልን ከማንም እና ከምንም ሁኔታ የመማር ብቃት አይኖረንም።

 

ካለፈዉና እራሳችን ከፈፀምነዉ ስህተት መማር ካልቻልን ከማንም እና ከምንም ሁኔታ የመማር ብቃት አይኖረንም።

ብርሃኔ በርሄ ተ. 11-03-18

በዉስጣዊ አንድነታችንና አብሮነታችን መፍረክረክ ምክንያት ከእነርሱ የምንፈልገዉን የሀገራዊ መብት ጥቅም እንዳንጠይቅ አቴንሽናችንን ወደዉስጥ የቤት ስራችን ብቻ ዳይቨርት እንድናደርግ ሲሰሩ የኖሩትና አሁንም እየሰሩ ያሉት ታሪካዊ ጠላቶቻችን መጫወቻ አንሁን! ለአማራና ትግራይ ህዝቦች!

የወልቃይትንና ራያ ህዝብን ማንነት አስመልክቶ ከሁለቱም አቅጣቻዎች እየቀረቡ ያሉትን ሰላማዊ ሰልፎች በጨረፍታ ታዝቤአለሁ። በጉዳዩ ላይ በህገመንግስታዊና አስተዳደራዊ አመክንዮዎች መሰረት ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት አልፈልግም። ከዚህ ይልቅ ሁለት ፍፃሜዎችን በማስታወስ ሁለቱም ህዝቦቻችን ከስሜታዊነት ወጥተዉ ጥያቄዎቻቸዉ በህገመንግስታዊ፣አስተዳደራዊ እና የሁለቱም ህዝቦች ለዘመናት የኖረ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካለን ፍላጎት አንፃር ብቻ ተቃኝተዉ መፍትሄ እንዲያገኙ ሁላችንም ብንሰራ ብልህነት መሆኑን መምከር እወዳለሁ።

Videos From Around The World

የነዉጥ ሀይሎች (ምናልባትም ዝንረተዓለማቸዉን የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ለማዳከም የሚሰሩት የጎረቤት አገሮች እጅ ታክሎበት) በወልቃይት ጉዳይ ላይ ባቀጣጠሉት እሳት በጥቂት ዓመታት ጥረት የማንመልሰዉን ሀብትና ንብረት እንደዚሁም እስከመቼዉም ሊመለስ የማይችለዉን የሰዉ ልጆች ህይወት ማጣታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነዉ። በወቅቱ ሁለቱም የክልል መስተዳድሮች በመመካከርና በአንድነት መንፈስ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ሰርተዉ ቢሆን ኖሮ ያ ሁሉ ኪሳራ ባልደረሰ ነበር። የዘገየ ቢሆንም ክቡር አቶ አንዳርጋቸዉ እና ክቡር አቶ አባይ ወልዱ(በሁለቱም ክልል ህዝቦች የአካባቢ ሽማግሌዎች ተነሳሽነትና ትብብር ጭምር) ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ጭምር የተደገፈ የስምምነት ሰነድ ሲለዋወጡ ስንመለከት በእጅጉ ተደስተን ነበር። በስምምነቱ መሰረትም ማንኛዉም አይነት የህዝብ ጥያቄ በህገመንግስታዊ የአፈታት ስርአትና በሰለጠነ አኳኋን ይፈታል የሚል ተስፋም አሳድረን ነበር። በዚሁም መሰረት ከእንግዲህ የሚቀርቡ ጥያቄዎች እና ሰላማዊ ሰልፎች ሊኖሩ ቢችሉ እንኳ ክቡራን የሁለቱም ህዝቦች የአገር ሽማግሌዎች፣ርእሳነ መስተዳድሮች በአጠቃላይ ደግሞ የአስተዳደር አካላት በስምምነት የጀመሩትን የሰለጠነ የችግር አፈታት ስርአት የሚያጠናክር እንጂ የሚያደፈርስ አይሆንም የሚል እምነት አሳድረን ነበር።

በሁለተኛ ደረጃ በቅርቡ ክቡር አቶ ጌታቸዉ ረዳ በብአዴን ኮንፍረንስ ወቅት ተገኝተዉ ያደረጉትን የሁለቱን ህዝቦች ታሪካዊ ትስስርና ወንድማማችነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ካለ ዉስጣዊ እምነትና መርህ የመነጨ ንግግር ላዳመጥን ዜጎች በእርግጥም በክቡር አቶ ገዱ እንዳርጋቸዉ እና አቶ አባይ ወልዱ የተደረሰዉን የአብሮነት ስምምነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን በመገንዘብ ዉስጣዊ ደስታ የፈጠረልን ነበር። የእኛ ፍሎጎት ይህ ቢሆንም ቅሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መታየት የጀመሩት እጅግ ያፈነገጡ አስተሳሰቦችና የሰላማዊ ሰልፍ መልእክቶች ብልህነት የጎደላቸዉ እና እንድነታችንን ለማላላትና ለማዳከም ሁሌም ሲሰሩ ለኖሩት የዉጭ ሀይሎች መጠቀሚያ እንዳያደርጉን በጥሞና እና በአርቆ አስተዋይነት ብንገመግማቸዉ የተሻለ ይሆናል። የማንነት፣ የመብትም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች የማቅረብ መብታችን እንደተጠበቀ ቢሆንም በሰከነ እና ለሌሎች ከፋፋዮቻችን በመሳሪያነት በማያጋልጠን መልኩ ይቅረብ የሚል ምክራችንን መለገስ እንወዳለን። የአፈታት ስርአቱም ቢሆን ከተዘረጋዉ የህገመንግስታዊ ስርአት ዉጭ እንዳያፈነግጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል። ካለፈዉና እራሳችን ከፈፀምነዉ ስህተት መማር ካልቻልን ከማንም እና ከምንም ሁኔታ የመማር ብቃት አይኖረንም። በመሆኑም ለምንም አንበቃም። አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀስ ያህል የራያና የወልቃይት ማንነት ጥያቄን መንግስት ባፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ ባፈሙዝ እንመልሰዋለን(በክላሽ የተደገፈ) የሚል መፈክር ከእነርሱ ለማስመለስ የምንፈልገዉን ሀገራዊ፣ ታሪካዊ እና ህጋዊ ጥቅምና የባለቤትነት መብት በዉስጥና በእርስበርስ ችግራችን ተሸብበን ረስተነዉ እንድንኖር ሌት ተቀን የሚሰሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ለአማራና ለትግራይ ህዝብ የሚፈይደዉ ነገር አይኖርም። በአንድነት እጦት ምክንያት አቴንሽናችንን ከእነሱ ዳይቨርት እንድናደርግና ከእነርሱ የምንፈልገዉን የሀገራዊ መብትና ባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት እንዳንችል በዉስጥ የቤት ስራ ተጠምደን እንድንኖር አጀንዳ ከሚያቀብሉን ሀይሎች መጠንቀቅና ችግሩን በብልሃት መያዝ ካልቻልን እንደሀገርና እንደ ህዝብ ዋጋ አይኖረንም።

ስለሆነም ችግሩን በብልሃትና በብልህነት እንያዘዉ፤ እንፍታዉ። ሁለቱም ክልሎችና የአስተዳደር መሪዎች ቀደም ሲል የጀመሩትን የአፈታት ስርአት አጠናክረን እንቀጥል እንጂ አናፍርሰዉ። እንደዚያ ካልሆነ የሁለቱንም ህዝቦችና ክልሎች አንድነት ለማላላትና ለማፍረክረክ የሚጥሩት የዉጭ ሀይሎች መሳቂያና መሳለቂያ ሆነን መቀጠላችን አይቀርም። ልብ ያለዉ ልብ ይበል። በብልህነትና ሰፋ እድርገን ማሰብ እንጀምር።

 

Back to Front Page