Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሳይቃጠል በቅጠል

ሳይቃጠል በቅጠል

(ክፍል - 1)

ለአብዮታዊ ዴሞክራትሃይሎች እና ደጋፊዎች የተደረገ የትግል ጥሪ

የተከበራቹውድ አንባብያን፣ የተከበራቹ የኢህአዴግ አባላት እና ደጋፊዎች ሰሞኑ እያየነው ያለውን የአገራችን ሁኔታ በጣም አሳሳቢ በሆነ ጊዜ ላይ ደርሳ ትገኛለች፡፡ ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ብሎ በ2009 ዓ.ም. በሎኮሰው ግምገማ እስከ አሁን ድረስ በታሪኩ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሁለት ዓመት ኣስቆጥሮ ግን ደግሞ የከሸፈ ጥልቅ ተሃድሶው ሆኖ አገራችን ወደ ትርምስ አስገብቷት ይገኛል፡፡በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ትምክህት እና ጠባብነት ገንግኖ በጊራይ ሰብሳቢነት ሴራ የኢህአዴግ አመራር ወይም ስልጣን በጥገኞች እጅ እንዲወድቅ በማድረጉ ምክንያት ኢህአዴግ የፈጠራቸውን ተቋማት በማፈራረስ ወይም ሽባ በማድረጉ ምክንያት እነሆ የአገራችን ሰላም እና መረጋጋት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስርዓት አልበኝነት ነግሶ ዜጎች መውጫና መግብያ አጥተው ንብረታቸው በጠራራ ፀሃይ እየተዘረፈ፣ እየተቃጠለ የመንግስት ያለ እያሉ ይገኛሉ፡፡ በትግራይ ተወላጆች ላይ አነጣጥሮ ይፈፀም የነበረው ብሄር ተኮር ጥቃት እና መፈናቀል እየተስፋፋ በመሄዱ በሁሉም ብሄሮች እና ብሄረሰቦች እየደረሰ ይገኛል፡፡

አሁን ወደ ስልጣን ከመጡት ውስጥ በትምክህት እና በጠባብነት የተለከፉ ጥገኛ ሃይሎች ያደራጃቸው ቄሮ፣ ፋኖ፣ ሄጎ፣ ወዘተ የሚባሉ ፀረ ሰላም ሃይሎች የህገወጥ ተግባራቸውን በማስፋፋት መንግስት ሊቆጣጠራቸው ስላልቻለ የህግ የበላይነት ማክበር ተስኖት እነሆ ዜጎቻችን የህግ ያለ፣ የስርዓት ያለ እያሉ ባሉበት ጊዜ፤ ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንደሚባለው ብአዴን ላይ የነቆጠው የጥገኛ ሃይል አብዮታዊ ዴሞክራት የተባሉ አመራርን በማሳደድ ተግባር ላይ ተጠምዶ ሰበር ዜናዎች እያሰማን ይገኛል፡፡ ከዚህ እኩይ የጥገኞች ተግባር በመነሳት ይህን የትግል ጥሪ ለማስተላለፍ ይህ ፅሁፍ በተጋጋለ የትግል ስሜት ለመፃህ አነሳስቶኛል፡፡

ውድ አንባብያን !

ኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር አንግቦ የአገራችን ጭቁን ህዝቦች በማቀናጀት እና ግንባር በመፍጠር በአገራችን ኢትዮጵያ ለመቶ አመታት ተንሰራፍቶ የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ደመኛ ጠላት የሆነው የትምክህት ስርዓት በመደምሰስ፣ በምትኩ የህዝቦች እኩልነት እና ዴሞክራሲያዊ አንድነት የተረጋገጠበት ህዝባዊ ስርዓት በመፍጠሩ አገራችን ከአሃዳዊ ስርዓት ወደ ፌደራላዊ ስርዓት በመሸጋገር እነሆ ያለፉት 27 ዓመታት በልማት እና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አመርቂ ውጤት ተመዝግቦ ህዝባችን ከድህነት የሚያወጣ የህዳሴ ጉዞ ጀምሮ መሀል መንገድ ላይ ይገኛል፡፡

Videos From Around The World

ይሁንና ኢህአዴግ ውስጥ አብዮታዊ ዴሞክራት መስለው ድርጅቱን በመምራት ላይ የነበሩ ጥቂት የድርጅቱ ኮር አመራር የየክልላቸው ልማት እና ህዝቡን በትክክለኛ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት መምራት ሲያቅታቸው፤ የክልሉን የልማት ጥማት (የተፈጠረውን ሞጓች ህብረተሰብ - Demanding Society) ማርካት ሲያቅታቸው፤ ህዝቡ ከጎናቸው ማሰለፍ ሲያቅታቸው፤ በሃላቀር አስተሳሰብ ለማሰለፍ እና ከሌሎች የአገራችን ብሄር ብሄረሶቦች ዳግም ወደ ጦርነት ለማስገባ የታለመ እርኩስ ዓላማ ይዘው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ የድርጅታችን ኢህአዴግ የትግል ታሪክ እና የስልጠና ሰነዶቻችን እንደሚያሳዩት ሁሌም ፀረ ህዝቦች በልማት ጎዳና ለውጥ ማምጣት ሲቸገሩ ወደ ትምክህት እና ወደ ጠባብነት እንደሚገቡ የታወቀ ነው፡፡

የብአዴን አመራር አሁን እያደረገው ያለ ነገር ስንመለከት እላይ ላዩ የኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ለማስመሰል በመጣር ውስጥ ውስጡን ግን የነ አፄ ሚኒሊክአይነቱ የትምክህተኞች እና አስመሳዮች ተንኮል እና ሴራ በማሴር ፀረ ሕገመንግስት መጓዝ ጀምሯል፡፡

እንደ አብነት መግለፅ የሚቻለው አንዱ የወልቃይት የትምክህት የመስፋፋት ጉዳይ ነው፡፡ በህገመንግስቱ መሰረት አንድን ይገባኛል ወይም የማንነት ጥያቄ መቅረብ ያለበት ግልፅ አሰራር እያለ የበሰበሰው የብአዴን ኮር አመራር ግን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት ርቆ የወጣ በመሆኑ፤ በትምክህት አመለካከት የተሰለበው ሃይል ጎንደር እና ባህርዳር ሆኖ ስለ ትግራይ/ወልቃይት መወሰን እየከጀለው ፈራ ተባ እያለ ይገኛል፡፡

ማንም እንደሚያውቀው የወልቃይት ህዝብ ብሄሩ፣ ቋንቋው፣ ማንነቱ እና ሁለመናው ትግራይ መሆኑ ይታወቃል፤ ታድያ ምንድን ነው ጥያቄው ከወልቃይት ከራሱ ሳይነሳ ከጎንደር እና ባህርዳር እየሰማነው ያለ? ብሎ ብሎ በብአዴን የበሰበሱ ኮር አመራሮች አንደበት መነሳት ጀምሯል፡፡ መልሱ ቀላል ነው፣ የግዛት መስፋፋት ነው፣ የነሚኒሊክ እና የነ አፄ ሃይለስላሴ የመስፋፋት ጥያቄ ማስቀጠያ ነው፡፡ የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ሳይሆን የድሮ ግዛት ጥያቄ ነው፤ የወልቃይት ጉዳይ የወልቃይት ብቻ አይደለም፤ በወልቃይት ብቻ የሚቆም ሳይሆን በአፋር፣ በአዲስ አበባ፣ በቤንሻንጉል እና በኦሮሚያ የሚቀጥል ጥያቄ ሆኖ በአጠቃላይ በፌደራል ስርዓቱ የተቃጣ አደገኛ የነፍጠኛ፣ የትምክህት እና የሚኒሊካዊ የመስፋፋት ሴራ መሆኑ ታውቆ ማንም የኢህአዴግ ኣባል ድርጅት በትኩረት ሊከታተለው እና ሊታገለው ይገባል፡፡ አንድን አብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት ማራመድ ላይ የነበረ ሃይል የትምክህት አመለካከት ማሞካሸት እና ማባባል ከጀመረ፣በቃ ከነፍጠኛነቱ ስለማያልፍ ወደ ባሰ እልቂት ከመገባቱ በፊት በጊዜው እንዲቆም መደረግ አለበት፡፡

እቺ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በዴሞክራሲ፣ በእኩልነት እና በመቻቻል እየገነባናት ያለችው ውዷ አገራችን ወደ ሗላ የመመለስ አባዜ ኢህአዴግ ኮር አመራራችን ላይ ይታያል፤ ኮር አመራራችን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት ወጥቶ ሩቅ ተጉዟል፣ በየክልሉ መመለስ የሚገባው ጥቃቅን የአስተዳደር ወይም የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል ጥያቄዎች ካልሆነ በስተቀር አሁን በአገራችን ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ያልተመለሰ መሰረታዊ በቋንቋ የመጠቀም ጥያቄ የለም፡፡ ነገር ግን አመራራችን የህዝብ ጥያቄ መመለስ አቅቶት ከህዝብ እየራቀ ሲሄድ፣ የህብረሰተሰቡን የልማት ጥማት ማርካት ሲያቅተው ስሜት ኮርኳሪ ጥያቄዎች፣ የጠባብነት ጥያቄዎች፣ የትምክህት ጥያቄዎች በራሱ ጊዜ እየቀሰቀሰ የሆይሆይ ህዝበኝነትን ድጋፍ ማሰባሰቢያ አድርጎ ተያይዞታል፡፡

ውድ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር ቀደሞች

እናንተ ባደረጋችሁት ከፍተኛ ተጋድሎ አገራችን ኢትዮጵያ ከነበረው ኣስከፊ ስርዓት በመላቀቅ በምትኩ ህዝባዊ መንግስት ተመስርቶ የአገራችን ህዝቦች የነበራቸውን የማንነት ጥያቄ መልስ አግኝቶ እነሆ በትግላችን ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፌደራላዊ ስርዓት መስርተን አገራችን ከድህነት ተርታ በማውጣት ወደ ከፍታ ለማድረስ ግማሽ መንገድ ተጉዘናል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከዘመናት የሃልዮሽ ጉዞ ተላቋ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዘገቡ ከሚባሉት አገሮች አንዷ ለመሆን አብቅተናታል፡፡ ይህ ከፍተኛ ዕድገት የአንድ ዓመት ብቻ ሳይሆን ላለፉት 17 ዓመታት ሳይቆራረጥ የተመዘገበ በመሆኑ ሁሉም የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡ ባለፈው ወር የተከበሩ የድርጅታችን ኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አሕመድ በአሜሪካ ለተሰብሳቢዎች ባደረጉት ንግግር 27 ዓመት የጨለማ እና የቆሻሻ ዓመታት እንደነበር ገልፆዋል የሚል ዜና በሰማንበት የመንግስት ሚድያ በንጋቱ የዓለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው አገራችን ኢትዮጵያ በዓለማችን ፈጣን እና ተከታታይነት ያለው ልማት ካስመዘገቡት አገራት ውስጥ ከቻይና እና በይናማር ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የምትጠቀስ አገር ሆናለች የሚል ዜና ሰማን፡፡ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሃቅ መውጣቱ አይቀርም ውሸት ተንኮል እና ሴራ መጋለጣቸው አይቀርም፡፡ ስለዚ መነሻችን አይተን አሁን የደረስንበትን ሁኔታ ስንገመግም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያስመዘገበው ድል ማንም ሊያንቋሽሸው የሚችል ወይም ማንም ሊሸፍነው የሚችል አይደለም እንደ ፀሃይ ብርሃን ፈንጥቆ ይወጣል ይታያል፡፡ ስለዚህ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስር ሆነን መታገላችን ልንኮራና ልንደሰት ይገባል፡፡

ይሁንና ሁሉም መንገዳችን አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲያችን ሊያጋጥሙ ይችላሉ በማለት አስቀድሞ ለይቶ ያስቀመጣቸው የስርዓታችን አደጋ ማለትም ኪራይ ሰብሳቢነት በሚገባ ባለመታገላችን በተለይ ኮር አመራሩ ይህን አደጋ በመታገል ረገድ ባሳየው ዳተኝነት ችግሩ በኮር አመራሩ ገንግኖ ኢህአዴግን ለማፍረስ ቆርጦ በመነሳት የትንቅንቅ ትግል ላይ እንገኛለን፡፡

ከሁሉም ነገር ኣሳሳቢ የሚያደርገው በስንት መስዋእትነት የተገነባው ድርጅታችን ኢህአዴግ፤ ሰፊው አርሶአደር እና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰፊው የከተማ ኖዋሪ ያካተተ የ8 ሚልዮን ግንባርቀደሞች ያቀፈ የህዝብ ድርጅት ኢህአዴግ፣ በጥቂት ኮር አመራር ሴራ ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጣም በጣም ያስቆጫል፡፡ ድርጅታችን እየፈረሰ፣ አገራችን የሰራላት ቀርቶ ያውደለደለ የሚኩራራባት፣ ማንም አሸባሪ የፈጠርነውን ሰላም እና መረጋጋት እንደ ፈለገው የሚያደፈርሳት አገር እየሆነች ነው፡፡ እኛ አብዮታዊ ዴሞክራቶች በኢህአዴግ ስር ሆነን ለመታገል ድርጅቱን ስንቀላቀል ልዩ ጥቅም ፈልገን አይደለም፤ የድርጅታችን ዓላማ ስላማለለን እንጂ፤ በድርጅታችን መስመር የህዝባችን ኑሮ ይቀየራል ብለን እንጂ፤ ለህዝባችን እና አገራችን ሰላም መረጋጋት ልማት እና ዴሞክራሲ ስንል እልፍ መስዋእትነት ለመክፈል እንጂ፡፡ ይሁንና ድርጅታችን የተቀላቀለ ሁሉ ይህን ዓላማ ታጥቆ ነው ማለትግን አይደለም፤ ይኸው በኮር አመራሩ ሳይቀር ከትምክህት እና ጠባቡ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችን እርቅ ፈፅሞ ድርጅታችን ለማፍረስ ላይ ታች ሲል ይታያል፡፡

ይህም የኛ የኣባሎች ችግር ነው፣ በእንጭጩ መታገል እና አባሎቻችን ከዚህ አስነዋሪ የጎራ መደበላለቅ ማዳን ስንችል፣ ሳናድን ቆይተን አሁን የብተና አደጋ አንዣብቦብን ስጋት ላይ ወድቀናል፡፡ ስለዚ አሁን በጊዜ የለም መንፈስ ድርጅታችን የምናድነበት ጊዜ አሁን ነው፡፡

ድርጅታችን ለግማሽ ምእተ ዓመት የገነባነውን መስመር ዓደጋላይ ወድቋል፣ በፍጥነት በጊዜ የለም መንፈስ የማዳን ስራ ካልሰራን ትግላችን፣ ያስመዘገብነው ውጤት፣ የከፈልነው መስዋእትነት ሁሉ ደመ-ከልብ ሆኖተረት ተረት ሆኖ ይቀራል፡፡ አገራችን ወደ ትርምስ እየገባች ነው፣ ትርምሱ ተጀምሯል፤ በትላልቅ ክልሎቻችን ኦሮሚያ እና አማራ ስርዓት አልበኝነት ነግሷል፡፡ በያለፍክበት የዘረፋና የጥቃት ማዘዣ ኬላዎች ተፈጥሯል ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ አሁን ይህን ጉዳይ ካልተቆጣጠርነው አደጋው የከፋ ነው፡፡

የተከበርክ የአማራ ህዝብ

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት አንድነቷን አስጠብቃ የኖረች አገር ብትሆንም በዚህ የአንድነት ታሪኳ እየተፈራረቁ ወይም እየተቀባበሉ የመጡ ገዢዎቻችን በተወለዱበት ብሄር ስም እየነገዱ፣ የተወለዱበት ብሄር ሳይቀር ሁሉንም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በመጨቆን አገራችን ከዓለማችን ቀደምት ስልጣኔዎች ከሚጠሩ አንዷ እንዳልነበረች ሁሉ፣ በስተመጨረሻ ከዓለማችን በሃላቀርነት እና ድህነት የመጀመሪያ ተጠቃሽ አገር ለመሆን ደርሳለች፡፡ በተለይ ባለፉት 100 ዓመታት የነፍጠኛው እና የትምክህት ስርዓት በስመ አማራ በመነገድ ከፍተኛ የሆነ ብሄራዊ ጭቆና በአገራችን አስፋፍቶ ከአማራ ውጭ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች በማንነታቸው እንዲያፍሩ፤ በቋንቋቸው እንዳይናገሩ፣ እንዳይማሩ፣ እንዳይዳኙ ሲደረጉ ነበር፡፡ ከኣማራ ውጭ ባሉ ብሄሮች እና ህዝቦች እንዲህ ዓይነት ግፍ በመደረጉ የአማራ ህዝብ ጉዳት እንጂ ምንም ያገኘው ጥቅም አልነበረም፡ብሄራዊ ጭቆና ምክንያት የሚጠቀም አንድም ህዝብ የለም፡፡

በመሆኑም የአማራ ህዝብ ይህንን በመረዳት ከሌሎች ወንድም እና እህት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ ግንባር በመፍጠር፣ በድሮው ኢህዴን በዛሬው ብአዴን ስር ተሰልፈህ በግፈኛው የትምክህት ስርዓት ክንድህን በማሳረፍ የትምክህት ስርዓት ተገርስሶ ዳግም ላይመለስ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለሃል፡፡ በከፈልከው መስዋእትነትም የአገራችን ህዝቦች እኩልነታቸው አረጋግጠህ የነበረውን የአብሮነታችን እና አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር እና እርስ በርሳችን እንድንተማመን ያደረገ የፌደራል ስርዓት ተገንብቶ ሁሉም እንደየ ጥረቱ ተጠቃሚ ሆኖዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄረ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጥዋቸው አመራሮች እየተመሩ እነሆ 5 ተከታታይ አገራዊ ምርጫ ተካሂዶ ሁሉም ክልሉን በመምራት በህዳሴ ጉዞ ይገኛል፡፡

ነገር ግን ባረጋገጥነው ልማት ልክ የመልካም ኣስተዳደር የማስፈን ኣቅሙ ባለመገንባት፣ ኣመራሩ ዓላማውን ስቶ ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት በመግባቱ ድርጅትህ ብአዴን ወደ ዝቕጠት ገብቶ በፀረ ዴሞክራሲና ኪራይ ሰብሳቢነት አዘቅት መዋኘት ጀምሯል፡፡ አመራሩ በክልሉ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲያቅተው፤ የክልሉን የልማት ጥማት ማርካት ሲያቅተው እየቀለደ በስልጣን ላይ ለመቆየት በመከጀል፤ የችግሮች ሁሉ መንስኤ ፌደራል ስርዓት ነው፣ የትግራይ/ህወሓት የበላይነት ነው፣ የሚል ምክንያት በማምጣት ከወንድም የትግራይ ህዝብ ለማጣላት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ አሁን ደግሞ የወልቃይት ጥያቄ ከህገመንግስታዊ አካሄድ ውጭ በመቀስቀስ ወደ ግጭት ለማስገባት "የወልቃይት ነገር ልንተወው ብንፈልግም የማይተው ሆኖብናል"በሚል አነጋገር ከወንድም የትግራይ ህዝብ ሊያጋጩህ ሲንቀሳቀስ ይታያል፡፡ ስለዚህ ይህን አፍራሽ የትምክህት እና የነፍጠኛው ስርዓት ናፋቂዎች እንቅስቃሴ በደንብ በመከታተል ፀረ ህዝቦቹ አደብ እንዲያደርጉ ልታደርግ ይገባል፡፡

አገራችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ በተደረገው በትጥቅ ትግል ይሁን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል መድረክ የአማራ ህዝብ ትልቅ ሚና እንደነበረው ማንም የሚያውቀው ሓቅ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም አገራችን አጋጥሟት ካለው የመበታተን የእርስበርስ ግጭት አደጋ በማውጣት በኩል የአማራ ህዝብ እንደ ቀድሞው ድርጅትህን ብአዴን በማስተካከል ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ አለብህ፡፡

የተከበራቹ የብአዴን አባላት

ብአዴን ራሱን በራሱ የማጥፋት ሂደት ውስጥ ገብቶ ህይወት ውጪ ህይወት ግቢ የሞት ሲቃ እያሰማ ያለ ድርጅት ነው፡፡ በአገራችን እየተፈጠረ ያለው ለውጥ ወይም በመደመር ምክንያት የተለያዩ አመለካከት የነበራቸው ድርጅቶች እና ግለሰቦችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል እንዲያደርጉ፣ የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የትግል ምህዳሩ ለማስፋት እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሚደነቅ ቢሆንም የብአዴን አመራር ግን ለፍትህ ለሰላምና ለዴሞክራሲ ብለው መስዋእት የሆኑትን ብርቅየ የአማራ ሰማእታት ደም ደመ-ከልብ ለማድረግ፤ በክልሉ ያሉትን የትግሉ አሻራዎች በማጥፋት በምትኩ የትምክህት ወይም የነፍጠኛው ስርዓት አሻራዎች እንደሚተካ በአደባባይ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው ብአዴን በሂወት ግቢ ህይወት ውጪ ሲቃ ይገኛል የሚባለው፡፡

ብአዴን እየወሰደው ያለ ራስን በራስ የማጥፋት እርምጃ አንዱ ለዚህ ተግባራ እንቅፋት ይሆኑኛል ያላቸውን የብአዴን መስራች እና ነባር አመራሮች፣ ከዴሞክራሲያዊና ኢህአዴጋዊ አሰራር ውጭ፣ በሚኒሊካዊ ተንኮል እየታደኑ ከድርጅቱ እንዲታገዱ እና በብአዴን አባላት ውስጥ የፖለቲካ ስራ እንዳይሰሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ይህ እልም ያለ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ነው፡፡ የዚህ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተንኮል መገለጫም በጓድ በረከት ስምኦን የተወሰደ እርምጃ ማውሳቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ ጓድ በረከት በለጋ እድሜው ጀምሮ እስከ ህይወት መስዋእትነት ለመክፈል የተታገለለትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር፣ የአማራ ህዝብ ከወንድም እና እህት የኢትዮጵያ ብሄር እና ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በመቻቻል፣ በዴሞክራሲያዊ አንድነት በልማት ጎዳና እንዲጓዝ ያደረገውን መስመር ወግኖ በመታገሉ፤ በትምክህት በታወሩ የብአዴን ኮር አመራር ካሳደገው ድርጅት እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

ጓድ በረከት ስምኦን በሁሉም አብዮታዊ ዴሞክራት ግንባር ቀደሞች እይታ ከመለስ ቀጥሎ አለን ብለን የምንመካበት ዋናው አሰልጣኛችን መምህራችን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን ከመካከለኛ አመራር እስከ ከፍተኛና ኮር አመራር ደረጃ ያለው የኢህአዴግ አባል በጓድ በረከት ስምኦን አስተምህሮ ያላለፈ የለም፡፡ አሁን ግን ይህ መሪያችንየአብዮታዊ ዴሞክራሲ አባት ብለን የምንጠራው ብርቅየ የትግል አባታችን በተልካሻ ምክንያት ከትግል ማገዱ በጣም አስቆጥቶናል፡፡

በጓድ በረከት እና በጓድ ታደሰ ጥንቅሽ የመታገድ ምክንያት እንደ ቀረበው ከሆነ በጥረት ባደረጉት ጉድለት ነው የሚለው፡፡ ጥረት ሌላ ፖለቲካ ድርጅት ማእከላይ ኮሚቴነት ሌላ፡፡ በእርግጥ በኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ከሆነ ችግር የለውም፣ ማንም ከመስመር በላይ ስላልሆነ መጠየቅ አለበት፡፡ ይህም በድርጅቱ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እና እሰዮ የሚያስብል ነው፡፡ ነገር ግን የብአዴን የጥልቅ ተሃድሶ አካሄድ ሲታይ ከኢህአዴግ አሰራር ውጭ የጠባብነት እና የትምክህት ህቡእ ቡድን በድብቅ በመመስረት ከኦህዴድ መሰል ቡድን ጋር በመሆን የኢህአዴግ ስልጣን በሚኒሊካዊ ተንኮል፣ የኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ተጠቅሞ ስልጣን በመረከብ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት በመፈፀም ላይ ያለ ድርጅት በመሆኑ አሁን የብአዴን ኮር አመራር አብዮታዊ ዴሞክራት ሆኖ ጓድ በረከት እና ጓድ ታደሰ በኪራይ ሰብሳቢነት አገደ ማለት የማይታመን እና የሚኒሊካዊ የትምክህት ተንኮል ነው፡፡ ምክንያቱ እስካሁን እየወሰዳቸው ያለ እርምጃዎች እና ፕሮፖጋንዳዎች አፍራሽ እና ህዝበኝነት ተኮር በመሆናቸው፡፡

ይህ የብአዴን ኮር አመራር ምንኛ በዝቅጠት ጎዳና ረጅም ርቀት የተጓዘ መሆኑ የሚያሳየው፤ ባለ ኮከቡ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ባንዴራ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያለፈውን የትምክህት እና የነፍጠኛ ስርዓት፣ በብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ላይ ያሳረፈው ጠባሳ በመርሳት፣ የአብሮነታችን የእኩልነታችን ምልክት በመጨመር በየክልላችን እናውለበልበዋለን በማለት አረንጓዴ ብጫ ቀይ የፌደራል ስርዓታችን ሰንደቅ ዓላማ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አሁን ግን ብአዴን የክልሉ ባንዲራ በልሙጥ አረንጓዴ ብጫ ቀይ እቀይረዋሎ፣ የነፍጠኛና የትምክህት ስርዓት ታሪክ በአደባባይ ጎልቶ መውጣት አለበት፤ ጠባሳ ምናምን እያልን የጀግንነት ታሪካችን አንረሳም እያለ ነው፡፡

የዚህ እንድምታ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት የሚፃረር በመሆኑ በአገራችን ተፈጥሮ የነበረውን ሰላምና መረጋጋት፣ መቻቻል እና አብሮ የመኖር ፍላጎት አደጋላይ የሚጥል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ የአማራን ህዝብ ከወንድሞቹ ብሄር ብሄረሰብ እንዲጋጭ እና ወደ ጦርነት እንዲገባ የሚያደርግ፤ የተስፋ ቆራጮች የመጨረሻ ራስን በራስ የማጥፋት የፀረ ህዝቦች ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እያየነው ያለውን የብአዴን የመበስበስ አደጋ ከክልሉ አልፎ ሌሎች ክልሎችም የሚነካ በመሆኑ ዳግም የነፍጠኛ ስርዓት እንዳይ መለስ ሁሉም በተለይ የብአዴን አባላትቆቅ ሆኖ ፌደራል ስርዓቱ የመጠበቅ ሃላፊነታቹ ልትወጡ ይገባል ይወጣ፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የህዝብ መስመር ሁሌም ፈተና ይገጥመዋል፤ ሁሌም ከፈተናው ፈንጥቆ የመውጣት ብቃትም አለው

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ነሓሴ 21፣ 2010 ዓ.ም.

 

አስተያየትዎን በሚከተለው የኢሜል አድራሻ ማድረስ ይቻላል

hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com

Back to Front Page