Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሳይቃጠል በቅጠል(ክፍል - 2)

ሳይቃጠል በቅጠል

(ክፍል - 2)

ለአብዮታዊ ዴሞክራትሃይሎች እና ደጋፊዎች የተደረገ የትግል ጥሪ

...ከክፍል - 1 የቀጠለ

የተከበራቹ ውድ አንባብያን፣ የትምክህት እና የጠባብነት አመለካከት የተጠናወታቸው የኢህአዴግ ኮር አመራሮች ግንባር ፈጥረው እየተደጋገፉበት ያለው አንዱ አጀንዳ የቋንቋ አጀንዳ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በኦሮምያ ክልል ይሁን በሌሎች ክልሎች ያልተመለሰ መሰረታዊ በቋንቋ የመጠቀም ጥያቄ የለም፣ አሁን እየሰማነው ያለ የፌደራል የስራ ቋንቋ ተጨማሪ ይኑር፣ በትምህርት ቤቶች ተጨማሪ በቤተሰብ የሚመረጥ ቋንቋ ይኑር የሚለው ኣባባል ምንድን ነው እንድምታው? የሚለውን ትንታኔ በዚህ ክፍል ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ውድ አንባብያን ከ27 ዓመታት በፊት አገራችን ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ያሉባት የተለያዩ አገር በቀልም የውጭም እምነቶች የሚገኙባት የብዙሃነት አገር ሆና ሳለ፤ የትምክህትና የነፍጠኛው ስርዓት ግን ይህን ተፈጥሮ የለገሰንን ብዙሃነት በአደባባይ በመካድ አገራችን የወላድ መካን በማድረግ የአማርኛ ቋንቋ፣ የአማራ ወግ እና ባህል፣ የትምክህት ሃይሉ የሚያምንበት የኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣ ብቻ እውቅና ተሰጥቷቸው የአገር ኩራት መለኪያ ተደርገው ሲወሰዱ፤ ሌሎቹ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ሃይማኖቶች፣ ሁሉ እንደ ሗላቀር እና ፋራ ተደርጎ የሚወሰድበት፣ እነሱን መጠቀም ማለት እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ ተደርጎ የሚወሰድበት እና የተለያዩ መንግስታዊ ጫናዎች ይደርስበት እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

Videos From Around The World

ኢህአዴግ ለዘመናት ስር ሰዶና ተንሰራፍቶ የነበረውን የትምክህት ስርዓት እንደ ስርዓት ላይቀጥል ከገረሰሰው ቦኋላ ለዘመናት አደባባይ እንዳይወጡ ተከልክለው የነበሩ ብሄሮች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ዎጎች፣ ሃይማኖቶች እና እምነቶች ወዘተ የማንነት መገለጫዎች ሁሉም እኩልነታቸው ተረጋግጦ አደባባይ እንዲወጡ፣ አንዱ ከሌላው የማይበላለጥ እንደሆነ፣ ያለምንም ጫና የመጠቀም እና የማበልፀግ መብት ሕገመንግስታዊ ከለላ ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ቦኋላ ነበር በአገራችን ያሉ የብሄር፣ የቋንቋ፣ የእምነት ዓይነቶች እና ብዛቶች በወል የማይታወቁ የነበሩ፣ በመጥፋት ላይ የነበሩ ቀስ በቀስአደባባይ እየወጡ አሁን ከ75 በላይ ብሄሮች ያላት አገር ለመባል በቅተናል፡፡

እነዚህ የማንነት እና የብዙኋነት መለያ እና መገለጫዎች በነፍጠኛው እና በትምክህት ስርዓት እንደ ውጉዝ እና እንደ የኋላቀርነት ተምሳሌት ተደርገው ሲወሰዱ የነበሩ ባለፉት 27 ዓመታት ግን የውበታችን የጥንካሬያችን እና የአብሮነታችን ተምሳሌት፣ የመዋደዳችንና የመከባበራችን ማሳያዎች፣ እንዲሁም የአገር ልዩ ሃብታችን ተደርገው ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ አሁን እነዚህ የህዝብ ማንነት መገለጫ ዎች የሆኑ ብዙሃነታችን በጥላ-ስራቸው ያቀፉትን ህዝብ ብዛት ሳይገድብ ሁሉም እኩል መብት በማግኘታቸው በየክልላቸው እንዲበለፅጉ፣ እንዲያድጉ፣ የተረሱትን በጥናት እና ምርምር የማዳን ስራ ሲሰራባቸው ቆይተዋል፡፡ አሁን ምናልባት የትምክህ አመለካከት ያልተለያቸው ጥቂቶች በስተቀር በአብዛሀኛው ዜጎቻችን ብዙሃነታችን ማለት የፍቅር መገለጫ ሆኖው ይገኛሉ፡፡

በእርግጥም አሁን ከጥቂቶች በስተቀር የአገራችን ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ ለማወቅ የማይፈልግ የለም ማለት ይቻላል፤ የዚህም ማሳያ በየቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲቀርብ ሁሉም ሰው በጥሞና ሲከታተለው፣ በየትምህርትቤቱ እነዚህ የብዙሃነት መለያ የሆኑት ባህል ቋንቋ ወጎች ተማሪዎች በራሳቸው ወጪ በማውጣት አደባባይ ላይ ይዟቸው ሲወጡ፣ ሊያውቋቸው እና ሊያስተዋውቋቸው ጥረት ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ተግባር ነው፡፡ በየ ትምህርት ቤቱ መዝጊየዘ ጊዜ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ አለባበስ፣ ወዘተ በድራማ፣ በግጥም፣ በስነቃል፣ በስነፅሁፍ ውድድር፣ በፋሽን ሾው ወዘተ የማያስተዋውቅ ትምህርት ቤት የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ታዲያ እንዲህ ባለበት ሁኔታ አሁን፤ አገራችን ከድህነት ለመውጣት ደፋ ቀና በምትልበት ጊዜ፤ ድህነት ለማጥፋት እና ልማትን ለማበረታታት የፋይናንስ ድጋፍ እና ብድር ለማግኘት በየ ደጃፍ ያደጉ አገሮች እና ዓለምአቀፍ ተቋማት ደጅ በምትጠናበት ወቅት ይህን የቋንቋ ጥያቄ ማስነሳት የጤና ነው?

ይህ ጥያቄ በሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት የሚመኝ ዜጋ፣ በሁሉም የአገራችን ድህነት ያንገሸገሸው እና ልማትዋን እንዲቀላጠፍ የሚፈልግ ዜጋ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡

ከትምክህት እና ጠባብነት አስተሳሰብ ከተጠናዎታቸው ሃይሎች በስተቀር ማንኛውም የብሄር ቋንቋ የስራ ቋንቋ ቢሆን የሚጠላ ዜጋ የለም፣ ማንም ዜጋ ሁሉንም የአገራችን ቋንቋዎች ቢያውቅ በገንዘብ የማይመነዘር ለመለካት የማይቻል ከፍተኛ ሃብት በመሆኑ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም፡፡ በተለይ ከክልል ክልል የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከተለያዩ ቋንቋ ያላቸው ዜጎች በቀላሉ በመግባባት ያሰቡትን ማሳካት ስለሚችሉ በጣም ይጠቀማሉ፡፡ ይቅር እና የአገራችን ቋንቋ የውጭም ቢሆን ማወቁ በቀላሉ ለመግባባት ጠቃሚነት አለው፣ ለአስቶርጓሚ የምናወጣው ወጪም ይቀንሳል፡፡ ስለዚ በፍላጎት ከሆነ የተለያዩ ቋንቋ መማር ወይም ማወቅ የማይፈልግ ጤነኛ አመለካከት ያለው ዜጋ አይገኝም፡፡ ፍላጎት ለማሟላት አቅም ማየት ደግሞ ወሳኝ ነው፡፡ እንደ መንግስት ወይም እንደ ድርጅት የህዝብን ጥቅም ከማረጋገጥ አኳያ የህዝብን ፍላጎት ከማሟላት አኳያ አንድን ውሳኔ ስንወስን ዓቅምን በማገናዘብ ተገቢ ነው፡፡ ዓቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታነው እኮ ተብለዋል፡፡

ነገር ግን አሁን በድህነት እና ሗላቀርነት እየተሰቃየ ያለው ህዝባችን በየዓመቱ፣ በየመድረኩ፣ በየምርጫ ቅስቀሳችን እየጠየቀን ያለው ጥያቄ ምንድን ነው? መመለስ ያቃተን ጥያቄ ምንድን ነው? የሚል መመለስ አለብን፡፡

        ህብረተሰቡ ቋንቋ ለልማታችን እንቅፋት እየሆነ ነው፣ መግባባት አልቻልንም፣ ምርታችን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ወስደን ለመገበያየት የቋንቋ ችግር አለብን ነው እንዴ ያለን?

        አሁን የኦሮምኛ ቋንቋ የስራ ቋንቋ ቢሆን የኦሮሞ አርሶ አደር አንገብጋቢ ጥያቄ ይመልስለታል?

        አሁን ያለንን ሃብት ተጠቅመን ሁሉም የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዉም አርሶአደሩም ሁሉንም የአገራችን ቋንቋዎች ቢማር ቢያውቅ አንገብጋቢው የህዝብ ጥያቄ ይመለሳል? ድህነት እና ሗላቀርነት ይቀረፋል?

        የትግርኛ ቋንቋ የፌደራል ቋንቋ ቢሆን የትግራይ አርሶአደር ምን ይጠቀማል?

        በአጋጣሚ የአማርኛ ቋንቋ በሁሉም የአገሪቱ ቋንቋ ይነገራል፣ ባለፉት 27 ዓመታት የአማርኛ ቋንቋ የፌደራል የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል በህገመንግስት ሰፍሮ ተግባራዊ ሆኖዋል፤ እንዲህ መሆኑ ለአማራ ክልል ምንድን ነው ጥቅሙ? የአማራ አርሶአደር ከዚህ የተጠቀመው ምንድን ነው? የአማራ ብሄር ተወላጅ አማርኛ የስራቋንቋ በመሆኑ ያገኘው ልዩ ጥቅም ምን አለ?

        ህዝባችን እና አመራሩ በቋንቋ መግባባት ስላልቻሉ ነው እንዴ የህዝባችን የልማት ጥማት፣ የመሰረተ ልማት ጥማት ማሟላት ያቀተን?

        ውድ አንባቢያን እስኪ በተረጋጋ እና በሰከነ አእምሮ እናስበው፣ ራሳችን ጠያቂ ራሳችን መላሽ ሆነን እስኪ በአእሙሯችን ሙጉት እንፍጠር፣

እኔ ይህን ጥያቄ ስጠይቅ ምንም ጥቅም የለውም ከሚል በመነሳት አይደለም፤ ጥቅም አለው እላይም ለመጥቀስ ተሞክረዋል፡፡ ነገር ግን እዚህ ለማስገንዘብ የፈለኩት ካለንበት የድህነት፣ የኋላቀርነት የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎቻችን በመነሳት ቅድሚያ መስጠት ያለብን ምንድነው ለማለት ነው?

ለምሳሌ አገራችን ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለችውን የኤኮኖሚ ፖሊሲ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ነው፡፡ አንድን በኦሮሚያ ክልል በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅቶ ከድህነት ለመውጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ወገን፤ እንቅስቃሴዉን በድል ለመወጣት በተሰማራበት የስራ መስክ በጥራትና በፍጥነት ማቅረብ እንዲችል የሙያ እና የቢዝነስ ትምህርትና ስልጠና የሚያስፈልገው ሲሆን ከፍ እያለ እያደገ ሲሄድ ሙያውን በቴክኖሎጂ እያስደገፈ እንዲሄድ፣ ቢዝነሱም በዛው ልክ ዘመናዊነት እያሳደገ እንዲሄድ ድጋፍ ይፈልጋል፤ ምርቱ ከኦሮሚያ ክልል አልፎ ወደ አጎራባች ክልሎች የሚልክ ሲሆን የፌደራሉ የስራ ቋንቋ የግድ ማወቅ ይለዋል ምክንያቱ ከአማራ፣ ከደቡብ፣ ከሶማሌ እና ከሌሎች ሲገናች ሲገበያይ መግባቢያ ስለሚያስፈልገው፣ ከዛ ምርቱ እና ገበያው እያስፋፋ ከፍ እያለ ሲሄድም ቋንቋውም እንቅፋት ስለሚሆንበት የምርቱ ተገልጓዮች ቋንቋ ማወቅ፣ ባህልና ወግ ማወቅ የግድ ይለዋል ለምን ቢባል ምርቱን ከህብረተሰቡ ባህል በማጣጣም ገበያውን ለማጧጧፍ፡፡ ወደ አለም ዓቀፍ ገበያ በሚሄድበት ጊዜም እንደዛው የዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች እና የዓለም አቀፍ የምርት ስታንዳርድ ማወቅ እና ማሟላት ይጠበቅበታል ካልሆነ መንገድላይ መቅረቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ይህ የቢዝነስ ሰው ቢዝነሱ ሲጀምር የግድ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማሟላት አለብኝ ብሎ ማሰብ የለበትም ግን ደረጃ በደረጃ የደረሰበትን ሁኔታ እያየ ሁልንም ሟሟላት እንዳለበት ግን ያውቃል፡፡ ስለሆነም ቢዝነሱ ሲጀምር መጀመሪያ ማወቅ ያለብኝ ምንድን ነው? ከሙያ አንፃር፣ ከቢዝነስ አንፃር፣ ከቋንቋ አንፃር ወዘተ በመገምገም ያለውን ውሱን ሃብት እና ብድርም በመጠቀም ችግሮቹን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ተግባራዊ ካደረገ ውጤታማ ይሆናል፡፡ በድፍን በፍላጎት በቃ የቋንቋ እውቀት ከሌለኝ ቢዝነስ መስራት ስለማልችል ብሎ ሁሉም ቋንቋዎች (ሊደርሳቸው ያሰበ ክልሎች ቋንቋ፣ ሊደርሳቸው የፈለገ አለምዓቀፍ ቋንቋዎች) በመማር ገንዘቡና ጊዜው ከጨረሰ የትም ሳይደርስ ከስሮ ቁጭ ነው የሚሆነው፡፡

ስለዚ አሁን በአገራችን ላይ እየታሰበ ያለው ነገር ቆም ብለን እናስብ፤ አገርን ከድህነት የማውጣት እንቅስቃሴም ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የመንግስት ሚና በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ግን ደግሞ መንግስት ይህን ከፍተኛ ሃላፊነት ለመወጣት የገንዘብ ዓቅሙ ይወስነዋል፡፡ ስለዚህ ያለው ኣማራጭ ከዚህ ድህነት እና ኋላቀርነት በተቻለ ፍጥነት በመውጣት ወደ በለፀጉ አገሮች ለመሰለፍ ያለህን ውሱን ሃብት ችግሮችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ መድቦ መጠቀም ነው፡፡ ስለዚ የአገራችን ቀንደኛ ችግር፣ መፈታት ያለበት ችግር፣ ጊዜ የማይሰጥ ችግር ብሎ በመለየት ያለውን ውስን ሃብት መድቦ መንቀሳቀስ ቁርጠኛ መንግስት ያስፈልጋል፡፡

የሚገርመው ነገር በአሁኑ ሰዓት በጠባብነት የተዋጠው የኢህአዴግ ኮር አመራር እና በትምክህተኝነት የተለከፈው አሁንም የኢህአዴግ ኮር አመራር ለማመን በሚገርም ነገር ከ27 ዓመታት ቦኋላ በቋንቋ ጉዳይ፣ በማንነት ጥያቄ ጉዳይ እንዲሁም በድንበር አካለል ጉዳይ የህዝበኝነትና የሆይ-ሆይ ድጋፍ ለማግኘት ሲቀባበሉበት፣ ሲተጋገዙበት እያየን ነው፡፡ እስኪ አሁን በእውነቱ እንነጋገር ከተባለ የአማራ አርሶ አደር ጥያቄ የኦሮምኛ/ሶማልኛ/ትግርኛ ወይም የአፋርኛ እና የሌሎች ቋንቋዎች ትምህርት ይከፈትልኝ ነው? አይመስለኝም፡፡ ቋንቋ እኮ መግባቢያ ነው፣ የማንግባባበት ከሆነ አሁን መማሩ ምን ትርጉም አለው? አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 30 ሚልዮን ዜጎች በትምህርት ገበታ ይገኛሉ፣ እነዚህ ዜጎች የማይጠቀሙበት ቋንቃ ከሚማሩ በአከባቢያቸው ወይም አብዛኛው (ከ90% በላይ) ከሚንቀሳቀስበት አከባቢ የሚጠቀሙበት ቋንቋ እንዲማሩ በማድረግ ከነዚህ ዜጎች ውስጥ ጥቂቶቹ በተሰማሩት የስራ መስክ ወይም በሌላ ምክንያት ከሁለት እና ከዛ በላይ ቋንቋ የሚያስፈልጓቸው ከሆነ፣ በግላቸው እንዲማሩ ቢመቻች እና እንደ የአገር ትምህርት ፖሊሲ ግን አንድን ብሄራዊ ቋንቋ ለሁሉም እንደ ግዴታ የትምህርት ካሪኩለም በማስገባት ቢነደፍ ወጪ በመቀነስ ወይም በመቆጠብ በሌላ አንገብጋቢ የህዝብ ጥቅም ማዋል ብልህነት ነው፣ ህዝባዊነትም ነው፡፡

በተጨባጭ ህዝባችን እየጠየቀን ያለ ስራ ፍጠሩልኝ፣ ከድህነት ለመውጣት መሰረተ ልማት ይገነባልኝ፣ ምርታማነት የሚጨምር ቴክኖሎጂ አምጡልኝ ነው እያለን ያለው፤ ውሃ ጥማት ሞትኩኝ ነው እያለን ያለው፤ እናቶች አምቡላንስ አጥተው መንገድ ላይ እየሞቱ ነው ነው ያለው፣ መሰረተ ልማት አነሰብኝ ነው እያለን ያለው፡፡ ያለውን ውስን ሃብት/ባጀት በነዚህ ቁልፍ ችግሮች አውሉሉኝ ነው እያለ ያለው፣ በሙስና እየተበላ ያለው ገንዘብ ወደ ልማት ይዙርልኝ ነው እያለ ያለው፡፡ ዋና የለውጡ ቀስቃሽ ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው እንጂ የማንነት ጥያቄ፣ የቋንቋ ጥያቄ፣ የድንበር ጥያቄ አይደሉም፡፡

ለኢትዮጵያ ብዙ የስራ ቋንቋ ያስፈልጋልን?

በህገመንግስታችን መሰረት ቋንቋ እና ባህል የማልማት ጉዳይ የፌደራል ጉዳይ ሳይሆን የክልል ጉዳይ ነው፡፡ አንድን ቋንቋ የማልማት የማሳደግ እና የማስፋፋት ጉዳይ የየክልሉ እንጂ የፌደራል አይደለም፤ ፌደራል መንግስት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ክልሎች ቋንቋቸውን በማልማት ረገድ የሚያደርጕት እንቅስቃሴ ሊደግፍ ይችላል፡፡

የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠ/ሚ ዶ/ር አብዪ ጨምሮ ብዙ የፌደራል የስራ ቋንቋ ይኑር ብለው የሚደግፉ ዜጎች የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ሲታይ እንደሚከተለው ሲሉ ይደመጣሉ፡-

"ይህ ጉዳይ አዲስ በኛ የተጀመረ አይደለም፣ በብዙ አገራት ሁለት ሶስት የስራ ቋንቋ አላቸው ለምሳሌ ኤርትራ ከወሰድን ትግርኛ እና ዓረብኛ አላት፣ ኬንያ ከወሰድን ሱሃሊኛ፣ ፈረንሳይ፣ ኢንግሊዝኛ፣ ወዘተ ብዙ አገሮች ሁለት ሶስት የስራ ቋንቋ አላቸው ስለዚ ለኛ አገርም ይህ ታሳቢ በማድረግ ለምን አይሆንም"

ብለው ይከራከራሉ፡፡ ጥሬ ሀቁን ካየን ትክክል ነው ብዙ አገሮች እንደተባለው ሁለት እና ሶስት ወይም ከዛ በላይ የስራ ቋንቋ አላቸው፡፡ ምክንያታቸው ግን ብዙ ቋንቋ ስለተፈለገ ሳይሆን አስገዳጅ ምክንያት ስላለበት ይመስለኛል፡፡

እላይ የተጠቀሱት አገሮች ሁሉ ታሪካቸው ከኛ ይለያል፤ ለበርካታ አመታት በቅኝ ግዛት በመገዛተቸው ምክንያት የጋራ መግባቢያ ቋንቋቸው የባዕድ ቋንቋ ነበር የሚጠቀሙበት፡፡ ነፃነታቸው ሲጎናፀፉ ግን ሁለት ወይም ከዛ በላይ ቋንቋ መጠቀም የግድ አላቸው ምክንያቱ ለማግባቢያነት ሁሉንም ቋንቋ ተናጋሪ የሚግባቡባቸው የባዕዱ ቋንቋ ሲሆን፤ የማንነት እና የሉዓላዊነት መገለጫም ካለው አገር በቀል ቋንቋ የግድ መምረጥ ስላለባቸው በህዝብ ብዛት ወይም በተናጋሪ ብዛት ቋንቋዎች ሲመርጡ ሁለት ወይም ከዛበላይ አገር በቀል ቋንቋ መረጡ፡፡ የኛጉዳይ ሲታይ ታሪካችን ለየት ያለ ነው፡፡ ሁሌም የኩራታችን ምንጭ የሆነው አንዱ ለውጭ ጠላት ያለመንበርከክ ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ነፃነትዋ አስከብራ የቆየች ሁለተኛ አገር የምትባል፡፡ በዚህ መሰረት ላለፉ ከመቶ ዓመት በላይ አገራችን ኢትዮጵያ በትምክህቱ ወይም በነፍጠኛው ስርዓት ስትገዛ መቆየትዋ ይታወሳል፡፡ ይህ ስርዓት በአገራችን ብሄራዊ ጭቆና አንሰራፍቶ መቆየቱ ሁሉም የሚያውቀው ሓቅ ነው፡፡ በመሆኑም ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በውድም በግድም የአገራችን ህዝቦች ሁሉም የአማርኛ ቋንቋ እና ወጎች መጠቀም የግድ የነበረ በመሆኑ አሁን በአገራችን የባዕድ ቋንቋ ሳያስፈልግ በዚህ አጋጣሚ የአገር በቀል ቋንቋ የማግባቢያ ሆኖ ቆይተዋል፡፡ ደርግ ተገርስሶ ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲመጣ ይህ ቋንቋ እንደ የፌደራል ስራ ቋንቋ በመመረጡ እነሆ ያለምንም ተጨማሪ ወጪ ወይም ጫና እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡ በዚህ እኛ እድለኞች ነን፡፡

እንደ ኤርትራ እና ኬንያ በባዕድ የተገዛን ቢሆን ኖሮ፣ ያኔ አንድ የባዕድ ቋንቋ እና ሌላ ካሉን ከ80 በላይ ቋንቋዎች ሁለት ወይም ሶስት ወይም ከዛ በላይ አገር በቀል የሉአላዊነታችን መገለጫ ቋንቋ እንመርጥ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ይህን ዕድል መጠቀም ትችል ነበር ማለትም አማርኛ እንደ የስራ ቋንቋ በመጠቀም ሌሎች ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ሳያስፈልጋት ወደ ድህነት ቅነሳ መግባት ትችል ነበር፡፡ ነገር ግን ጥላቻና ቂም ስለነበረ ጠቅላላ አማርኛ የሚባል በማጥፋት በሱ ፋንታ ዓረብኛ መረጠች፡፡

ስለዚ ትምክህት በሌላ በኩል ሁሌም እንደሚገለፀው ጨቋኝ እና አስከፊ ስርዓት የነበረ ቢሆንም በዚህ በቋንቋ ረገድ ግን ትልቅ ጥቅም ሰጥቶናል፡፡ቢያንስ አማርኛ ቋንቋ እንደዚህ ተስፋፍቶ ባይ ቆይ ኖሮ ወይ የባዕድ ቋንቋ እንጠቀም ነበር ወይም ደግሞ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በርካታ አገር በቀል ቋንቋዎች እንጠቀም ነበር ስለዚ ለድህነት ቅነሳ የምናውለው ገንዘብ ይጎድል ነበር ማለት ነው፡፡

 

 

ታድያ አሁን ለምን ይህ አጀንዳ ሆነ?

በእርግጥ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እምነት ያለው አመራር ይህን ጠፍቶት አይደለም ነገር ግን ኮር አመራሮቻችን (የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች) የየክልላቸው ልማት እና ህዝቡን በትክክለኛ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አመለካከት መምራት ሲያቅታቸው፤ የክልሉን የልማት ጥማት (የተፈጠረውን ሞጓች ህብረተሰብ - Demanding Society) ማርካት ሲያቅታቸው፤ ህዝቡ ከጎናቸው ማሰለፍ ሲያቅታቸው፤ ከሌሎች የአገራችን ብሄር ብሄረሶቦች ግጭት የሚፈጥሩ ወይም በመሀከላቸው ጥርጣሬ እንዲነግስ የሚያደርግ በሃላቀር አስተሳሰብ እና በስሜት ቀስቃሽ አጀንዳዎች ከጎናቸው ለማሰለፍ እና ስልጣናቸውን ለማቆየት የታለመ ነው፡፡ የድርጅታችን ኢህአዴግ አስተምህሮዎች እንደሚያሳዩት ሁሌም ፀረ ህዝቦች በልማት ጎዳና ለውጥ ማምጣት ሲቸገሩ ወደ ትምክህት እና ወደ ጠባብነት እንደሚገቡ የታወቀ ነው፡፡ ፣ አመራሩ በዝቅጠት ጎዳና ሩቆ በመሄዶ፣ እሱ ራሱ ቀንደኛ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠላት ሆኖ ተሰልፏል፡፡ጠባብነት እና ትምክህት እሳት እና ጭድ መሆናቸው ይታወቃል፣ነገር ግን "የጠላት ጠላት ወዳጅ ነውና" የሚል የትምክህት ፈሊጥ በመከተል ጠባብነት እና ትምክህት ግንባር ፈጥረው አብዮታዊ ዴሞክራሲን ለማጥፋት ሽርጉድ እያሉ ይገኛሉ፡፡ይህ የትርምስ ስትራቴጂ መቸውም ኢትዮጵያን የሚያረጋጋ ሳይሆን ከአንድ የጦርነት ምዕራፍ ወደ ሌላ የጦርነት ምእራፍ በማሸጋገር በታሪክ ወደምናውቀው የዘመነ መሳፍንት እልቂት እና ውድመት የሚያመራ ነው፡፡

የተከበርክ የኦሮሞ ህዝብ

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት በነፍጠኛው እና የትምክህት ስርዓት አራማጅ ሃይሎች በህዝቦችዋ ጫንቃ ላይ ጭነውት የነበረ ብሄራዊ ጭቆና ስትሰቃይ የነበረች አገር ናት፡፡ የዚህ ጭቆና ገፈት ቀማሾች አንዱ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ጭቆናን አሜን ብሎ ተቀብሎ አያቅም፤ በመሆኑም ከዚህ አስከፊ የነፍጠኛ እና የትምክህት ስርዓት ጭቆና ለመላቀቅ በተደራጀም በተናጠልም ትግል ከጀመሩት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የኢትዮጵያ ህዝቦች አንዱ የኦሮሞ ህዝብ ነው፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ለበርካታ ዓመታት በተለያዪ መንገዶች ሲታገል ከቆየ ቦሃላ በስተመጨረሻ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ያነገበ፣ህዝብንና ጨቋኞችን ለይቶ የሚታገል የኦሮሞ ድርጅት (ኦህዴድ) ጥላ ስር በመሰለፍ ከወንድም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች አብሮ በመታገል ደመኛው የህዝብ ጠላት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ በምትኩ የአገራችን ህዝቦች እኩልነታቸው የተረጋገጠበት፣ አብሮነታችን እና አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር እና እርስ በርሳችን እንድንተማመን ያደረገ፣ የፌደራል ስርዓት ተገንብቶ ሁሉም እንደየ ጥረቱ ተጠቃሚ ሆኖዋል፡፡ ኦህዴድ፣ የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት ይመኘው የነበረ እና ይታገልለት የነበረን የማንነት ጥያቄ በተሟላ መልኩ በመመለስ እነሆ ባለፉት 27 ዓመታት በልማትም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታም በአገራችን ቁልፍ ተዋናይ በመሆን እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡

ይሁንና በእሳት ተፈትኖ እንደ ወርቅ ነጥሮ የወጣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ የመሰለ ወደር የማይገኝለት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረገ ህዝባዊ መስመር ጨብጠን እያለን፤ በልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግል ሂደት ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት በመሆኑ እንዲሁም መሪዎቻችን የማይሳሳቱ መላእክት ሳይሆኑ ሰዎች በመሆናቸው፣ የህዝብን ፍላጎት ማርካት ተስኗቸው ለችግሮቻቸው ሰበብ አስባብ፣ ስማስም በማውጣት ከተጠያቂነት ለመሸሽ በማሰብ ሓላፊነታቸውን መወጣት አቅቷቸው በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት ነግሶ የአገራችን ህዝቦች በማንነታቸው ጥቃት እየደረሳቸው፣ ንብረታቸው በጠራራ ፀሃይ እየተዘረፈ ወይም እየተቃጠለ ሰላም እና መረጋጋት ከራቀን ብዙ ወራት ወይም ዓመታት አልፏል፡፡

በተለይ በኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች (ኦህዴድን ጨምሮ) አሁን እየታየ ያለው ዝንባሌ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ጎን በመተው ወደ ጠባብነት እና ትምክህተኛ አመለካከት ያደላ እንቅስቃሴ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ባለፉት 27 ዓመታት ጥያቄ ቀርቦባቸው የማያውቁ ግን ደግሞ በውጭ ሃገር ሆኖው፣ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ይነሱ የነበሩ የተስፋፊነት እና የማንነት ጥያቄዎች አሁን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር እንመራለን የሚሉ ድርጅቶች አፍጥጦ እየወጣነው፡፡

የኦሮሞም ሆነ የሌላ ብሄራዊ ጭቆና ገፈት ቀማሽ ህዝብ ጥያቄ፤ የቋንቋ የማንነት የራስ አስተዳደር የራስን ባህልቋነቋ የማሳደግ እና ክልልህን የማልማት ጥያቄ በህገመንግስቱ መሰረት ተመልሶ በያንዳንዱ ክልል ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ አሁን መሰረታዊ ያልተመለሰ የማንነት ወይም የቋንቃ ጥያቄ የለም፡፡ ነገር ግን በኦህዴድ ያለው ኮር አመራር የክልሉ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መመለስ ሲያቅተው፤ ስልጣን ለህዝብ ጥቅም መሆኑ ረስቶ ለግል ክብር እና ጥቅም ማስገኛ አድርጎ በመውሰድ በስልጣን ማቆያ ብሎ ያሰበው ስልት የኦሮሞ ህዝብን በቋንቋ ፖለቲካ ስሜት መቀስቀስ እና ማነሳሳት፣ አመራሩ ራሱ የፈጠራቸው የመልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ወደ ሌላ ማላከክ፣ የትግራይ የበላይነት አለ፣ በማለት ለመሸወድ እና የልማትን ጥያቄ የጠየቀ ህዝብ የፌደራል ቋንቋ ጥያቄ በሚል ምስምስ በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ ኣታግሎ ለድል ያበቃው መስመር፤የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሙ በእኩልነት እና በኣብሮነት እንዲኖር እገዛ ያደረገ መስመርአገራችን በልማትም በዴሞክራሲ ስርዓትም በዓለማችን ተጠቃሽ ያደረጋት መስመር አደጋላይ እየወደቀ ስለሆነ የከፋ እልቂትና ብጥብጥ ከመምጣቱ በፊት፣ የተከበርክ የኦሮሞ ህዝብ ድርጅህን ኦህዴድ ትክክለኛው መንገድ እንድታስይዝ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

 

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የህዝብ መስመር ሁሌም ፈተና ይገጥመዋል፤ ሁሌም ከፈተናው ፈንጥቆ የመውጣት ብቃትም አለው !!

ህዝበኝነት ዕድሜ የለውም፤ ህዝባዊነት ሁሌም አሸናፊ ነው !!

ከህዳሴ ኢትዮጵያ

ነሓሴ 24፣ 2010 ዓ.ም.

 

አስተያየትዎን በሚከተለው የኢሜል አድራሻ ማድረስ ይቻላል

hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com

 

Back to Front Page