Back to Front Page


Share This Article!
Share
መደመርና እሳቤው

መደመርና እሳቤው

                                                              እምአዕላፍ ህሩይ 07-21-18

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “መደመር” እንደሚባለው ፅንሰ ሃሳብ ያስደመመኝ ነገር የለም። ፅንሰ ሃሳቡ በተጀመረበት ወቅት ግርታ ቢጤ ፈጥሮብኝ ነበር። አሁን…አሁን ጉዳዩ እየገባኝ ሲመጣ ግን፤ የእሳቤው ጥልቀትና ምጥቀት እስከየት ድረስ እንደሚዘልቅ ለመገንዘብ ችያለሁ። በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ስለ መደመር ከተናገሩ ወዲህ፤ ነገሩ ፍንትው ብሎ ተገልፆልኛል። ገብቶኛል።

አዎ! ከመሰንበቻው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ሀገራችንን በጎበኙበት ወቅት፤ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ማብሰሪያ መድረክ ዝግጅት ላይ፤ የፍቅርና የአንድነት መሪው ዶክተር አብይ ስለ መደመር ሲናገሩ ያደመጥኳቸው እሳቤዎች፤ በጉዳዩ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ እንድይዝ አድርገውኛል። እናም “ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” እንዲሉ አበው፤ መደመርን በጥቅል እሳቤውና ከአራቱ የሂሳብ መመሪያዎች አንፃር ያለውን የላቀ እሳቤ ላስቃኛችሁ እሞክራለሁ።

የመደመር ቅኝት ነጠላ ወይም አንድ መሆንን አይቀበልም። “እኔ” የሚል አስተሳሰብን ወደ “እኛነት” የሚለውጥ ነው። በ“እኛነት” ውስጥ ያለን አብሮነትን በአያሌው የሚያበረታታ ነው። ለብቻችን ሆነን የማንፈፅመውን ነገር አንድ ላይ ስንሆንና ስንደመር ከሚፈለገው በላይ ውጤት ልናመጣ የምንችል መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ፅንሰ ሃሳቡ። በመደመር ውስጥ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ እርስዎ፣ እናንተ…ሁላችንም አለን—አልደመርም ብሎ ራሱን ከቀነሰው ውጭ። በዚህ የስሌት ቀመር ውስጥ የምንገኘው አንድ ላይ እንጂ ተነጣጥለን አይደለም። “ከአንድ ብርቱ፣ ሁለት መድሃኒቱ” እንደሚባለው ማለቴ ነው።

ርግጥም መደመር አንድነትን ይፈጥራል። በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ‘እኔ ተደምሬያለሁ፣ እርስዎስ?’ በማለት በየአደባባዩ ፍላጎቱን የሚገልፀው ወገን ከአንድነት የሚገኘውን ጥቅም ስለሚያውቅ ይመስለኛል። አንድነት አንዱ የሌለውን ከሌላኛው የሚያገኝበት፣ የድምር ውጤቱም ብዙ የሚሆንበትና የሚፈለገውን ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ማሰሪያ ልጥ ነው ማለት ይቻላል። በአንድነት የሚገኘው ለውጥ ለብቻ ቢኮን የማይሞከር፣ ነገር ግን በጋራ በመሆን ያለ ብዙ ነዋይና ጊዜ በቀላሉ እውን ልናደርገው የምንችለው ነው። ነገሩን “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው” በሚለው ይትብሃል ልንመለከተው እንችላለን።

Videos From Around The World

ይትብሃሉ መደመር በጋራ በመሆን ከምናገኘው ግብ በተጨማሪ፣ ጌጥና መድመቂያ መሆኑን ያሳየናል። ስንደመር ጎልተንና ደምቀን እንታያለን። የምንናገረው ይሰማል። የምንጠይቀው ወዲያው ምላሽ ይሰጠናል። በመደመር የተፈጠረው አንድነት፣ ጠንካራነትን ፈጥሮ የምንፈልጋቸው ሁለንተናዊ ለውጦች ሁሉ እውን ይሆናሉ። እንዳልኩት ስንደመር “እኔነትን” አሽቀንጥረን እንጥላለን። ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን የምንጥለው “እኔነት”  አንድነትን ሊያመጣ የሚችል “እኛነትን” በመውለድ፤ ችግሮች ካሉም በጋራ ተመካክረን እንድንወጣ ያደርገናል።

ስንደመር ‘የእኔ ብሔር እንዲህ ሆነ፣ የእገሌ ብሔር እንዲህ ተደረገለት’ ከሚል “የእኔነት” መንፈስ እንርቃለን። በውስጧ ከ100 ሚሊየን የሚልቅ ህዝብ የያዘችውን ትልቋን ኢትዮጵያ “በእኛነት” እንይዛለን። ርግጥ አንድ ሰው ‘ተደምሬያለሁ’ ብሎ ሲያበቃ፤ መልሶ ስለ ራሱ ግላዊ ዘውግ የሚያወራ ከሆነ፣ በእውነቱ ተደምሯል ማለት አይቻልም። አሊያም የመደመርን ምስጢር አልገባውም—የመደመር እሳቤ ሁሉንም ሀገራዊ ተግባሮች በኢትዮጵያዊ የአንድነት ስሜት መመልከት ነውና።

አሁን ደግሞ አስቲ ከላይ ከጠቀስኳቸው ጥቅል እሳቤዎች ወጣ እንበልና፣ መደመርን ከመሰረታዊ የሂሳብ ገዥ መመሪያ አንፃር እንመልከተው። እንደሚታወቀው የሂሳብ ገዥ መመሪያ የ“BODMAS”ን “ቦዲማስ”ን (B=ብራኬት፣O=of፣ D= ማካፈል፣ M=ማባዛት፣ A= መደመር እና S= መቀነስ) አሰራርን የሚከተል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ማብሰሪያ መድረክ ላይ እንዳሉት፤ የመደመር እሳቤ ከዚህ የሂሳብ ገዥ መመሪያ (ቦዲማስ) የላቀ ነው።

“በቦዲማስ” መመሪያ መሰረት አንድን ስሌት ለመፈፀም የመጀመሪያው ህግ “ብራኬቱን” ማፍረስ ነው። የእኛ መደመር ግን የጥላቻንና የቁርሾን ግንብ የሚደረምስ ነው። ርግጥ ለመደመር የሚፈልግ ሰው፤ ወደ መደመር ጎዳና እንዳይሄድ የሚያግደውን የጥላቻንና የቁርሾን “አጥር” ማስወገድ ይኖርበታል። አጥሩ ደንቃራ መሆን የለበትም። ታዲያ ይህን አባባል ከኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት አኳያ ስንመለከተው፤ በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ጥላቻና ፀብ ወይም የተካለለው ድንበር በፍቅርና በአንድነት መተካት ይኖርበታል ማለት ነው። ለዚህም ይመስለኛል—ዶክተር አብይ አህመድ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ድንበር በፍቅር ድልድይ መፍረሱን ሲናገሩ የነበሩት።

በሂሳብ መመሪያ መሰረት አንድ ሲደመር አንድ ሁለት መሆኑ ርግጥ ነው። በእኛ የመደመር እሳቤ ግን፤ እኔ እና የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ስንደመር ሁለት አንሆንም። ልንሆን የምንችለው “እኛ” ነው። ዶክተር አብይ ነገሩን በምሳሌ ሲያስረዱ፤ “እኔ እና ኢሳይያስ ስንደመር እኛ እንሆናለን” ያሉትም ከዚህ ሃቅ ተነስተው ይመስለኛል።

ይህ የ“እኛ” ፅንሰ ሃሳብ ሁለትና ከዚያ በላይ ሰዎችን የሚወክል ነው ማለት ይቻላል። ከሁለት ግለሰቦች እስከ በሚሊዩን የሚቆጠሩ የሀገር ህዝቦችም ይደርሳል። ምክንያቱም የመደመሩ አካሄድ የተደመሩ ግለሰቦችን የሚያባዛ ስለሆነ ነው። የሁለት ሰዎች መደመር ተባዝቶ ሚሊዮኖችን ይፈጥራል። ከፍ ሲልም እልፍ አዕላፎች መፍጠሩ አይቀሬ ነው። የብዜቱ ልኬታ እጅግ ብዙ ነው። ታዲያ ይህን እውነታ ለመገንዘብ ሁለት ቀጥተኛ መስመሮች የሚገናኙበትን ቦታ ለመፈለግ እስከ አፅናፍ ድረስ መጓዝ አይጠበቅብንም። ተደምሮ መመልከቱ ብቻ እውነታው ቦታ ላይ ወስዶ ያስቀምጠናል።

የመደመር ፅንሰ ሃሳብ መቀነስም ያለው ነው። የሚቀንሰው ግን እንደ ሂሳብ መመሪያው ቁጥሮችን አይደለም— ለመደመር እንቅፋት የሆኑ በአሜኬላ እሾህ የታጠሩ አስተሳሰቦችን እንጂ። እነዚህ አሜኬላዎች፤ በሀገር አለመውደድ፣ በዘራፊነት፣ በቂም በቀለኝነት፣ በተንኮል፣ በክፋት፣ በምቀኝነት፣ በበደል፣ በጥላቻ፣ በስንፍና...ወይም በሌሎች ተግባሮች ሊገለፁ ይችላሉ። እነዚህ ተግባሮች ለመደመር የሚፈይዱት አንዳችም እርባና ስለሌለ፤ በእኛ የመደመር ቅናሽ ውስጥ መግባታቸው ተገቢና ትክከል ይመስለኛል። ማህበረሰቡም ቢሆን ተግባሮቹን በህይወት ስንክሳር መዝገቡ ላይ በእኩይ ምግባርነታቸው ፈርጆ ያሰፈራቸው ናቸው። የእኩይ ምግባር ባለቤቶቹንም ከስርዓተ-ህይወት ዑደቱ ውስጥ ቀንሶ በአሉታዊ ምልከታ የሚያያቸው ናቸው።

ርግጥም ለሀገሩ ደንታ የሌለውን፣ ህዝብን የሚዘርፈውን፣ የተንኮልና የክፋት ጎሬ የሆነውን፣ ምቀኝነትና በደል የተጠናወተውን እንዲሁም በውስጡ ጥላቻ የሞላውንና የስንፍና ቋት የሆነውን ዜጋ የሚፈልግ ማህበረሰብ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ ማንነቱና ምግባሩ ከእኩይነቱ የሚቀዳ ዜጋ፤ ከማህበረሰቡ የአንድነትና የእኛነት ድመራ ውስጥ ቢቀነስ፤ ከመደመር እሳቤው የሚያጎድለው አንዲትም ሰበዝ የሚኖር አይመስለኝም—ራሱን እንደ ደሴት ነጥሎ በጥፋት አረንቋ ውስጥ ከማዳከር በስተቀር። ያም ሆኖ ተቀናሹ በጥፋት መዘውር ውስጥ ሲንከላወስ እንዲኖር አይፈቀድለትም። የተደማሪዎቹ ዓላማ በማግለል ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ፣ የእኩይ ተግባሩን ባለቤት በይቅርታ፣ በምህረት፣ በፍቅርና በደግነት ማንፃት የግድ ይላቸዋል። ታዲያ ያኔ እርሱ ከነበረበት “የእኔነት” አረንቋ ወጥቶ የድምሩ አካል በመሆን “እኛ”ነትን ይሆናል።

የመደመሩ እሳቤ ማካፈልንም የሚያካትት ነው። የማካፈሉ እሳቤ ግን እንደ ሂሳብ መመሪያው ዓይነት አይደለም። የሚካፈሉት አራት ብርትኳኖች ለሁለት ሰዎች እንደሚባለው ዓይነት አይደለም። መደመሩ መከፋፈልን አይወክልም። በእሳቤው መሰረት የሚካፈሉት በማሀበረሰቡ ውስጥ ያሉት አዎንታዊ የዘመናት እሴቶች ናቸው። እነዚህ እሴቶች መልካም ቃል፣ ጥበብ፣ ፍቅር፣ ነዋይ…ሊሆኑ ይችላሉ። እሴቶቹ መልካምነትንና ተደምሮ መኖርን የሚያስተምሩ ናቸው። ለዚህም ነው—ዶክተር አብይ በሚሌኒሙ ዝግጅት ላይ “…ከኢሱ (ኢሳይያስ አፈወርቂን ማለታቸው ነው) ጋር የምንካፈለው አሰብን ይሆናል” በማለት የተናገሩት።

እንዳልኩት መደመር አንዱ የሌለውን ከሌላው ማግኘት በመሆኑ፣ እኛ ከኤርትራ ጋር አሰብን “ስንካፈል” (ስንከፋፈል ማለት አይደለም) ኤርትራ ደግሞ በምላሹ ሰፊ ገበያ ባላት ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ትስስር የመፍጠር እንዲሁም ሌሎች የምትጠቀምባቸውን ጉዳዩች ማግኘቷ ግልፅ ነው። ታዲያ በዚህ “የመካፈል” እሳቤ ውስጥ መልካም የሆኑ ነገሮችን አብቃቅቶ መካፈል፤ መከፋፈል ሳይሆን መደመር መሆኑን መገንዘብ ይገባል። መከፋፈል ለየግል መውሰድን እንጂ፤ መደመርን አያመላክትም።

መከፋፈል “እኔነትን” እንጂ፤ “እኛነትን” ስለማይገፅ የመደመር ወገን ሆኖ ሊቆጠር አይችልም። በጥቅሉ ከላይ ያነሳኋቸው የመደመር እሳቤዎች፤ በሀገራዊም ይሁን በቀጣናዊ ጉዳዩች ውስጥ ተደምሮ በእኛነት ለመዝለቅ የሚያስችሉን ሃቆች ናቸው። እናም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም እንዲሉ አበው፤ ‘ተደምሬያለሁ’ የሚል ማንኛውም ዜጋ፤ የመደመሩ እውነታዎች የጠቀስኳቸውን ሃቆች በውስጣቸው አምቀው የያዙ መሆናቸውን ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም። ሃቆቹን በሚገባ አለማወቅ፤ በትክክል ወይም ጭርሱኑ አለመደመር ይመስለኛል። እናም ሃቆቹን ከራሱ ጋር በማዋሃድ ‘እኛነትን እውን ለማድረግ ከእኔ ምን ይጠበቃል?’ ብሎ ራሱን በመጠየቅ፤ ለተግባራዊ ምላሹ ከወዲሁ መዘጋጀት ወቅቱ የሚጠይቀው ሁነኛ ጉዳይ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።     

 

Back to Front Page