Back to Front Page


Share This Article!
Share
አቶ በረከት: የዘመኑ የብአዴን መሪዎች የመስዋእት በግ

አቶ በረከት: የዘመኑ የብአዴን መሪዎች የመስዋእት በግ

ከታዛቢዎች 09-02-18

አቶ በረከት ስሞኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱ መሆናቸውን የሚገልፁ ዜናዎች ከሰማን ቀናት ተቆጠሩ። ለእገዳቸው መነሻዎች ናቸው ተብለው የተሰጡ ምክንያቶች ወጥነት የጎደላቸው ቢሆኑም የሚያጠነጥኑት ግን ለአማራ ህዝብ ጥቅም ሲሠሩ ያልነበሩና ጥረት ተብሎ የሚታወቀውን ድርጅት ሲመሩም ጥፋት የሰሩ በመሆናቸው ነው የሚሉ ናቸው። የእግዱንና ለእግዱ መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች ስንሰማ ለማመን እጅግ በጣም ተቸገርን።   የተቸገርነው ደግሞ ሁለቱንም በተለይ ደግሞ አቶ በረከትን በቅርበት ስለምናቀው ነው። በመጀመርያ ደረጃ አቶ በረከትን ለአማራ ህዝብ አይሰራም ብሎ ለመፈረጅ መሞከር የሞራል ልእልና ማጣት ነው ብለን እናስባለን። አቶ በረከትን እስከምናቀው ድረስ ቤቴ ልጆቼ ሳይል ሌት ተቀን ሲሰራ የነበረ ሰው እንደሆነ ነው። እንቅልፍ አጥቶ ፖሊሲዎችን ሲያረቅና የተለያዩ ፅሁፎችን ሲያዘጋጅ የነበረ መሆኑን በዙሪያው ያሉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በረቂቅ ፖሊሲዎቹና በፅሁፎቹ ላይ የተወይዩ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች አሁን ቢክዱትም አሳምረው ያውቁታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የአማራን ህዝብ ይጠቅማል በሚል የፀና እምነቱ ለምቾቱ ሳይጓጓ በየጊዜው ባህርዳርና ከዛም አልፎ በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች እየተገኘ አመራሩን ሲያግዝ እንደነድበረ ማንም የሚክደው አይመስለንም። የአማራ ህዝብ እንዲጠቀም ካለው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ እንቅልፉን አጥቶ እስከ ደረቅ ሌሊት ቁጭ ብሎ ለልማትና እድገት ጠቃሚ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን ፅሁፎች ሲፅፍ የሚያመሽባቸው ጊዝያቶች ጥቂት እንዳልነበሩ አሁን ላይ ክህደት የፈፀሙበት የብአዴን አመራሮች እንክት አድርገው ያውቁታል። የአማራን ህዝብ ይጠቅማሉ ብሎ ያስባቸው የነበሩ እንደ አፈርና ዉሃ ጥበቃ የመሳሰሉ ስራሰዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ታች ድረስ የመስክ ጉብኝት እያደረገ እገዛ ሲያደርግ የነበረ ቁርጥ ያማራ ልጅ መሆኑንም ተግባሩ የሚመሰክረው ጉዳይ ነው። ለአማራ ህዝብ እነዚህንና መሰል ተግባራትን ሲያከናውን የነበረውን አቶ በረከት ለአማራ ህዝብ ጥቅም ሲሰራ አልነበረም ብሎ መወንጀል ወደታች የምንገልፀውን ዘርዘር ያለ ድብቅ ፍላጎት ለማሟላት ከሚደርግ ሩጫ ውጭ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።

Videos From Around The World

ሌላው ከጥረት ጋ ተያይዞ የተነሳው ነገር ከአቶ በረከት ጠቅላላ ስብዕናና ባህሪያት ስንነሳ ለማመን ነው የተቸገርነው። በነገራችን ላይ አቶ በረከት ቀይ መብራት ላለማለፍ ከሚጠነቀቅባቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ሙስና ነው። ሙስና ፈፅመዋል ብሎ ያሰባቸውን ሰዎች በመታገል ረገድም ግንባር ቀደሙ የኢህአዴግ አመራር ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። ይህ በሙስና ሲያደርገው የነበረ ትግል የጀመረውም አሁን በሚስቱም ሆነ በራሱ “ቅዱስ” ለመሆን እየተፍጨረጨረ ያለውን አቶ ታምራት ላይኔን በመታገል ነው። አቶ በረከት ባልሆነ መንገድ እንዲታይና ጥርስ እንዲነከስበት ካደረጉት ነገሮችም አንዱ ይህ አይነት ጠንካራና ግንባር ቀደም ትግል ማድረጉ ነው። ስለሙስና ጉዳይ ሲነሳ አንድ ነገር ታወሰን። ባንድ ወቅት የጥረት ቀደምት ከሆኑት ድርጅቶች ውስጥ ያንዱ ድርጅት ስራ አስክያጅ የነበሩ ሰው በወቅቱ ስራ አጥ የነበረውን የአቶ በረከትን ወንድም እንደሚቀጥሩት ቃል እንደገቡለት ሄዶ ለአቶ በረከት ባሳወቀው ጊዜ "እኔ በቦርድ ሊቀመንበርነት በምመራው ድርጅት ውስጥ አንተን እንዲሁ ጠርተው ልቅጠርህ ማለታቸው ነገ እነሱ ሙስና ሲሰሩ ማስተካከል እንዳልችል አይመስልህምን? ለመሆኑስ አንተን ጠርተው ለመቅጠር የፈለጉት ምን የተለየ ችሎታና ብቃት ስላለህ ነው? ህጋዊ በሆነ መንገድ ሳትወዳደርስ እንዴት ልትቀጠር ቃል ይገባልሃል” ብሎ ከልክሎት እንደቀረና በዚህ ጉድይም ከናቱ ጋ ረዘም ላለ ጊዜ አለመግባባት ፈጥሮ እንደነበር እናስታውሳለን።

እንዲያውም አቶ በረከትን የምናውቀው ስድስት ክንድ መሬት ለማይፈጅ የህይወት ፍፃሜ ሙስና ውስጥ መዘፈቅ የእነዚያን ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነትና ለእኩል ተጠቃሚነት ሲሉ ህይወታቸውናን አካላቸውን የገበሩ ውድና ንፁሃን ጓዶቹን እርም መብላት አድርጎ የሚቆጥር ሰው መሆኑን ነው። በዚህም ምክንያት ነው ያለምንም ግላዊ ጥቅም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ጥረትን ለማሳደግ ሲባክን የነበረው። አቶ በረከት ምንጊዜም ቢሆን የሚታየው የራሱ ግላዊ ጥቅም ሳይሆን የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ስለሆነ እያመመው እንኳን ጥረትን ለማስፋፋት ከነበረው ፅኑ ፍላጎት የተነሳ የጣናን የአሳ ሃብት በዘመናዊና ተፈጥሮን በማይጎዳ መንገድ ጥቅም ላይ ለመዋል አገር ላገር ሲንከራተት የነበረው። እንዴትና ለምንድን ነው ታዲያ አቶ በረከት በሙስና ሊወነጀል የሚችለው?

በፌዴራል መንግስቱ ደረጃም ቢሆን የአቶ በረከት አስተዋፅኦ ከማንም የኢህአዴግ አመራር ቢልቅ እንጅ የሚያንስ አይደለም። በዚህ ረገድ ብዙ የአቶ በረከትን በጎ የሆኑ ተግባራት ገልፆ መጨረስ ስለማይቻል አራት መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን በማንሳት ለማሳየት እንሞክር።

አንደኛው ከምርጫ 97 ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ምርጫ አቶ በረከት አስተባባሪ እንደነብረ ይታወቃል። በዚህም መሰረት የምርጫው ዝግጅትና አጠቃላይ ሂደት ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ቁርጠኛ አቋም በመውሰድ ተንቀሳቅሷል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዴሞክራሲያዊ የሆነ የምርጫ ማስፈፀሚያ ስነምግባር ደምብ እንዲዘጋጅ ያስቻለው አቶ በረከት ነበር። ይህ ደንብ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ገለልተኛና ተአማኒ እንዲሆን በማያሻማ መንገድ ያስቀመጠ ስነምግባር ደንብ ነበር። ይህን የስነምግባር ደንብ መነሻ አድርጎም ሁሉም የኢህአዴግ አመራርና አባላት እንዲወያዩበት ጥረት አድርጓል። በውይይቱ ወቅትም አመራሩም ይሁን አባሉ ብሎም ደጋፊው ምርጫውን በተመለከተ እንደለመደው መፈትፈት እንደሌለበትና ይልቁንም ኢህአዴግ እንደማንኛውም ፓርቲ በእኩልነት ተወዳድሮ የህዝቡን ውሳኔ መቀበል እንዳለበት የማያሻማ አቅጣጫ ስጥቷል። በዚህ ወቅት ብዙ የኢህአዴግ አመራሮችም ይሁኑ አባላት ደስተኞች ስላልነበሩ የማጉረምረም ሁኔታዎች እንደነበሩ እናስታውሳለን። ይሁንና ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ ስላልነበረ አንቀበልም ብሎ የወጣ ሃይል አልነበረም።

ከላይ በተገለፀው ሁኔታ የተካሄደው ምርጫ ደግሞ ሁላችንም እንደምናውቀው የኢህአዴግን ሽንፈት ያጋለጠ ሆኖ ተገኘ። በዚህም ምክንያት እንድንሸነፍ ያደረገን በረከት ነው በሚል በርከት ባሉ በኢህአዴግ አመራርና አባላት ከፍተኛ የሆነ ግምገማና ወቀሳ ደረሰበት። ይህን የአመራርና አባላት ግምገማና ወቀሳ ተከትሎም የረባ ስራ ላይ ሳይመደብ ለርጅም ጊዚያ ቆይቷል። በኋላ ላይ ግን እሱ ባለመኖሩ የጎደለባቸውን ሲረዱ የኢፌዴሪ የኮሙኒካሽን ጉዳዮች ፅ/ቤትን አቋቁመው እንዲሰራላቸው መደቡት። በተቃራኒው ግን ተቀዋሚዎችና የነሱ የሆኑ ሚዲያዎች ነገሩን በደንብ ባልተረዱበት ሁኔታ የምርጫውን ሂደት በዋነናነት ያበላሸው በረከት ነው የሚል ዘመቻ ህዝቡ ውስጥ እንዲሰራጭ አደረጉ። በዚህም ስሙ አግባብ ባልሆነ መንገድ እንዲነሳ ተደረገ።

ሁለተኛው በፌዴራል መንግስት ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባው የበረከት ሚና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጋ ተያይዞ የተጫወተው የማይናቅ ተግባር ነው። በረከትን በኤርትራዊነቱ ሲያጥላሉትና አሁንም እያጥላሉት ላሉ የዘርኝነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የኢህአዴግም ይሁን የብአዴን አመራሮች ይህ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተጫወተው ሚና የበረከትን ለኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለአማራ ህዝብ ጥቅም በተለይ ይሰራ እንደነበር ሊያሳያቸው ካልቻለ ሌላ ምንም ሊያሳያቸው የሚችል ሃይል የለም። ነገሩ እንዲህ ነው። ኤርትራ ኢትዮጵያን ከወረረች ማግስት ጀምሮ በነበረው የሰራዊት ምልመላና ስልጠና በረከት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በየማሰልጠኛ ጣቢያው እየተገኘ የማስተባበር ስራ ይሰራ የነበረ መሆኑን በወቅቱ የነበበሩ የሰራዊቱ አዛዦች የሚዘነጉት አይመስለንም። እንዲያውም ባንድ ወቅት ለዚሁ የሰራዊት ምልመላና ስልጠና ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት የመኪና አደጋ ደርሶበት ለመስዋዕትነት ሊዳረግ እንደነበረ የሚያውቁት ያውቁታል። እንደ እድል ሆኖ ግን በእጁና በሌሎቹ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ ከደረሰበት አደጋ ውጭ ህይወቱ ሳታልፍ እስካሁን ለመኖር በቅቷል።

በኋላም ጦርነቱ መቀጠል አለበት ብለው አቋም ከወሰዱት አብዛኛዎቹ የኢህአዴግ አመራር አባላት ውስጥ አንዱ እንደነበር በተለያየ መንገድ ሲዘገብ ስለቆየ በዚህ ዙሪያ ብዙም ለማለት አንሻም። ጉዳዩን ያነሳነው የዚህንና ለሎች መስዋዕትነትን የከፈለው በረከት ለአማራ ህዝብ ጥቅም አልቆመም ተብሎ መወንጀሉ ገርሞን ነው እንጅ።

ሶስተኛው ደግሞ መሬት መሸጥ መለወጥ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ሁላችንም እንደምናውቀው ኢህአዴግ መሬት መሸጥ መለወጥ የለበትም የሚል የፀና አቋም አለው። እንዴውም በኢህአዴግ አመራርና አባላት ዘንድ አንድ የተለመደ አባባል አለ "መሬት መሸጥ መለወጥ የሚችለው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው" የሚል። አቶ በረከት ግን ከዚህ ለየት ያለ ሃሳብ ያቀርብ እንደነበር የሚያውቁት በወቅቱ የነበሩ የኢህአዴግ አመራር አባላት ብቻ ናቸው። እንደ አቶ በረከት እምነት መሬት መሸጥ መለወጥ የህዝቡን ጥቅም በማይጎዳ መንገድ የኢኮኖሚ እደገት ሊያመጣ የሚችል ከሆነ እንደአማራጭ መወሰዱ ጥቅም ይኖረዋል የሚል ነበር። ይህን ሃሳብ በማራመዱ ግን ተከፍተው የነበሩ የኢህአዴግ አመራር አባላት ቁጥርም ቀላል አልነበረም። እዚህ ላይ ለማንሳት የፈለግነው ቁምነገር መሬት መሽጥ መለወጥ ይጠቅማል ወይስ አይጥቅምም የሚለውን ጉዳይ ሳይሆን አቶ በረከት ከማንም በተሻለ የለውጥ ሰው እንደሆነ ለማሳየት ነው።

አራተኛውና በከፊልም ቢሆን ከላይ ከተገለፀው ጋ የሚገናኘው የአቶ በረከት በፌደራል መንግስት ደረጃ የነበረው ሚና ደግሞ ለለውጥ ፍልጎትና ዝግጁነት ያሳይና ለዚህም ሳይታክት ይታገል የነበረ መሆኑ ነው። አቶ በረከት ኢህአዴግ እንዲለወጥ ይፈልግ የነበረው ኢህአዴግ ነባራዊ ሁኔታዎችን እየተከተለ መሰረታዊ ፕሮግራሙን ሳይለቅ ራሱን ከነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋ እያዛመደ ካልሄደ የኢትዮጵያን ህዝብ መምራት ካለመቻልም ባሻገር ጥቅሙን ተፃሮ ሊቆም ይችላል ብሎ ያስብ ስለነበር ነው። በተለይም የኢህአዴግ አመራርና አባላት ስልጣንን እንደግል መጠቀሚያ እየወሰዱት ስለሆነ ዴሞክራሲን እያጠበቡ መጥተዋል ብሎ ባመነበት ሰዓት ሳያመነታ ታግሏል። አቶ በረከት አቶ መለስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ካለው ጊዜ ጀምሮ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ኢህአዴግ መለወጥ እንዳለበት ሳያመነታ ይታገል እንደነበር ብዙው ሰው ያውቃል። ይህን ትግል ሲያደርግ የነበረው ደግሞ በሶስት መንገዶች ነው።

አንደኛው አመራሮችን በግል በማወያየት ነበር።  በተለይ ከአንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ሰፊና ተደጋጋሚ ውይይት ያደርግ እንደነበረና በውይይታቸው የተስማሙባቸው ቁምነገሮችም ተግባራዊ ይደረጉ ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት ያደርግ እንደነበር የሚመሰክሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በተመሳሳይ መንገድም አቶ ሃይለማሪያም ባግባቡ እየመሩ እንዳልነበርና የመወሰን ችግር እንደነበረባቸው ለነዚሁ ጉዳዩ በቅርብ ይመለከታቸዋል ብሎ ላሰባቸው አመራሮች ያነሳላቸው እንደነበር ይታወቃል።

ሁለተኛው የመታገያ መንገዱ ደግሞ የአባላትና የህዝብ ኮንፈረንሶች እንዲጠሩ በመወትወት ነበር። በነዚህ ኮንፈረንሶችና ህዝባዊ መድረኮች ለህዝብ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሃሳቦች ከማራመድ አይቆጠብም። ጥፋት አለበት ብሎ የሚያስበውን ግለሰብም ይሁን ቡድን ከመታገል ወደኋላ የማይል ግንባር ቀደም ታጋይ እንደሆነ አሳይቷል።

ሶስተኛው የአቶ በረከት የመታገያ መንገድ የተለያዩ ፅሁፎችን በማዘጋጀት ነበር። በግልና በኮንፈረንሶች የሚያደርጋቸው ትግሎች በቂ ናቸው ብሎ ያስብ ስላልነበር የረፍት ጊዜውን ሁሉ እየተሻማ የተለያዩ የተሃድሶ ፅሁፎችን እያዘጋጀ ያቀርብ እንደነበር የኢህአዴግና በተለይም የብአዴን አመራር ያውቃል። ፅሁፎቹ በዋነናነት የሚያተኩሩት የዴሞክራሲ ምህዳርን ማስፋት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና ይህን በማድርገም የህቡን በተለይም የወጣቱን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ ላይ ነበር። አለመታደል ሆኖ ግን ይህ የአቶ በረከት የለውጥ ሃሳብ በአብዛኛው የኢህአዴግ አመራር ሊገዛ አልቻለም ነበር። ይህ በመሆኑም አገሪቷና ህዝቦቿ ሊከፍሉት ይገባቸው ያልነበሩ ዋጋዎችን ከፍለዋል። ለማንኛውም ግን እነዚህ በበረከት ይዘጋጁ የነበሩ እና በፃፈው መፅሃፍ ውስጥ ያልተካተቱ የኢህአዴግ ይለወጥና ይታደስ ፅሁፎች ጊዜያቸውን ጠብቀው ለህዝብ ይፋ ይሆናሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

እዚህ ላይ አቶ በረከት ለአማራም ሆነ ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም መከበር ከላይ በተገለፁት መንገዶች ይንቀሳቀስ ከነበረ ለምንድን ነው ታዲያ ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች አማራ ክልል ውስጥም ይሁን ከዛ ባለፈ ለተፈጠረው ችገር ሁሉ አቶ በረከትን ዋነኛ ተጠያቂ አድርገው ሊያዩ የቻሉት ሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።  ከዚሁ ጋ ተያይዞም ለምንስ ነው የብአዴን አመራር ያውም ደግሞ ጉባኤ ሊካሄድ ሶስት ሳምንታት ሲቀሩት አቶ በረከት ከማዕከላዊ ኮሚቴነእንዲታገድ ያደረገው ብሎ መጠየቅም አግባብነት አለው። በእኛ እምነት አቶ በረከት ሌት ተቀን ሲሰራ እንደማንኛውም ሰው ሊሳሳት የሚችል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዋነኛ ተጠያቂ ተደርጎ እንዲታይ ያደረጉትና እነሱንም መነሻ አድርጎ የብአዴን አመራር ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያገደው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው እንላለን።

አንደኛው ምክንያት አቶ በረከት ኤርትራዊ በመሆኑ ነው። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው በተለይም ኢህአዴግ መሃል አገር ከገባ በኋላ ትግሉን የተቀላቀሉ አመራሮችም ይሁኑ አባላት የአቶ በረከትን የደም ሀረግ ብቻ በማየት የዘረኝነት አስተሳሰብ በግልፅም ባይሆን ውስጥ ለውስጥ ያናፍሱ እንደነብር ይታወቃል። በዚህ ምክንያትም ነው ብአዴን ውስጥ ካሉ አመራሮች ውስጥ የተሻለ ብቃትና ችሎታ እንዳለው ቢታወቅም በአንድ ወቅት ምክትል ሊቀመንበር ከመሆኑ ውጭ ለሊቀመንበርነት ታስቦ የማያውቀው። ለነገሩ ይህን የሊቀመንበርነትና የም/ል ሊቀመንበርነት ሃላፊነት እሱም ቢሆን ይቀበለው እንዳልነበር እናውቃለን።  ይህም ሆኖ ግን ያን ጊዜ ቆርጠው ሊጥሉት አልፈለጉም። ምክንያቱም ደም ተፍቶ እንደሚሰራላቸው በሚገባ ይረዱት ስለነበረ ነው። አሁን ላይ ደግሞ በሌላ መርህ አልባና ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የፖለቲካ ትርፍ እናገኝበታለን ብለው ሲያስቡ ሃሳቡን እንኳን ለመስማት ሳይፈቅዱ ገፍትረው ለመጣል ጊዜ አልፈጀባቸውም።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በግንባር ቀደምነት የሚጋፈጥ መሆኑ ነው። ይህንን እውነታ ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሰብራል እንዲሉ ሊያጣጥለው የፈለገው አቶ ንጉሱ እንኳን ሊክደው አልደፈረም። አቶ በረከት ሁሉም የብአዴን አመራርም ይሁን አባላት እንደሚያውቁት የመሰለውን ሃሳብ ይዞ ከመታገል ወደኋላ የማይል የጦር ሜዳ ብቻም ሳይሆን የአስተሳሰብ ግንባር ቀደም ታጋይ ነው። አቶ በረከት ሲታገል ሰውም ይሁን ቡድን መርጦ አይደለም። በእሱ እምነት ጥፋት ፈፅሟል ብሎ የሚያስበውን ሃይል ሁሉ ሳያወላውል ይታገላል። ለምሳሌ ባህርዳርና አዲስ አበባ ከተገባ ጊዜ ጀምሮ አቶ በረከት ቢሮክራሲው ሲፈጥራቸው የነበሩ ምስቅልቅሎችን ለመጋፈጥ ወደኋላ የማይል ጀግና ታጋይ የነበረ መሆኑ ነው። ከዚህ ጋ በተያያዘ ባንድ በኩል መብራት ጠፋ ሲባል፣ በሌላ በኩል ስልክ ተበላሸ ሲባል እንዲሁም የውሃ ችግር ሲያጋጥም ለምን ህዝቡ በቢሮክራሲው ይሰቃያል የሚል የፀና ህዝባዊነት ስላለው ችግሮችን ለማስተካከል ዘው ብሎ የሚገባው እሱ ነበር። ሌላው በርከት ያለ አመራር ግን ከቢሮክራሲው ጋር እየተጋፈጠ ችግሩን ራሱ መፍታት ሲገባው አብዛኛውን የህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ አሳልፎ የሚሰጠው ለአቶ በረከት ነበር። ይህም ሌላው የአቶ በረከት ስም ያላግባብ እንዲነሳ ያደረገ ሂደት ነበር።

እንዲሁም ከበረሃ ጀምሮ በብዙዎቹ የያኔው የኢህዴን አመራሮች እንደፍፁም ይታዩ የነበሩትን የህወሃት ሰዎች ሳይቅር በፖሊሲና በአመለካከት ልዩነት ሲሞግቱ ከነብሩት በጣት ከሚቆጠሩ ታጋዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው እሱ ነበር። በዚህ ረገድ በረሃ ላይ ከህወሃት ጋር በነበረው የመስመር ልዩነት ምን ያህል እንደታገለ በየመድረኮቹ የነበረ ታጋይና አመራር ሁሉ የሚያስታውሰው ሀቅ ነው። ለዛም ይመስለናል በወቅቱ የኢህዴን መስራችና ሊቀመንበር የነበረው አቶ ያሬድ ጥበቡ (ጀቤሳ) ብዙ ጊዜ ስለአቶ በረከት ጥሩ እንጂ መጥፎ ነገር ለማለት የማይደፍረው። አቶ ያሬድ አለውም አላለውም ግን የአቶ በረከት ታጋይነት ኢህአዴግ ወደመሃል አገር ሲገባም ተጠናክሮ ቀጠለ እንጅ አልቀዘቀዘም።  በሁሉም ጊዜያት የህወሃት ሰዎች አጥፍተዋል ብሎ ሲያምን እነሱን ከመታገል ቦዝኖ አያቅም።

ይሁንና አቶ በረከት የማያደርገውና ትክክልም የሆነው ነገር ግን አለ። ብዙዎቹ የህወሃት አመራሮች ወይም ግለሰቦች በሚያጠፉት ጥፋት ህወሃትን እንደድርጅት መኮነን የለብንም ብሎ ያምናል። ምክንያቱ ደግሞ ህወሃት እንደድርጅት የበላይ መሆን አለብኝ ወይም እኔ የወጣሁበት ማህበረሰብ ተጠቃሚና የበላይ መሆን አለበት የሚል ፕሮግራምም ይሁን ፖሊሲ የሌለው በመሆኑ ነው። ይልቁንም የህወሃት ፕሮግራም ከብአዴንም ይሁን ከኦህዴድ ብሎም ከደኢህዴን ፕሮግራሞች ጋር ተመሳሳይ ወይም አንድ አይነት በመሆኑ ህወሃትን እንደ ድርጅት ማጥላላት የራሱ የሆነውን ደርጅት ብአዴን/ኢህአዴግን እንደ ማጥላላት አድርጎ ስለሚያየው ነው። በዚህ ረገድ አቶ በረከት ከሌሎች ብዛት ካላቸው የኢህአዴግ አመራር አባላት የተለየ አቋም አለው ብሎ መናገር ይቻላል። የማን አቋም ትክክል እንደሆነ ለመርዳት ደግሞ የሚጠይቀው መመዝኛ የሚያመዛዝን አእምሮ ይዞ መገኘት ብቻ ይመስለናል።

አቶ በረከት የሃሳብ ትግልና ሙግት ሲያደርግ ደግሞ ጀርባየን ልከላከል የሚል አመለካከት የለውም። ሌላም ሰው አላግባብ እንዲከላከለው አይፈቅድም።  ለዚህም ነው መረብ (Network) ያልዘረጋውና ተራ ጓድኝነት በመመስረት የማይታወቀው። በሌላ አነጋገር ብዙው አመራር እንደሚያደርገው አቶ በረከት ተክለሰውነቱን ለመገንባት ተራ የሆነ ሽርክና ፈጥሮ አያውቅም። ለዚህም ነው ያብዛኛው አመራር ስብዕና ተራ በሆነ ሽርክና ሲገነባ የአቶ በረከት ስብዕና ግን ሲጥላላ የሚስተዋለው። የሚገርመው በድርጅት ጉባኤዎችም ይሁን በሌሎች መድረኮች የሚያደርጋቸው ያልተለሳለሱና መርህን መሰረት ያደረጉ ትግሎች በበርካታ የብአዴን አመራሮችና አባላት ሌላ ትርጉም እየተሰጣቸው የሱን ስብዕና በሚያጠለሽ መንገድ ህዝብ ውስጥ ሲሰራጩ ኖረዋል። አሁን አሁን ደግሞ ይህ የተቀናጀ የሚመስል የስም ማጠልሸት ስራ በፌስቡክ ሰራዊቱና የሚጮሁት ሌሎች የማህበራዊም ይሁን መደበኛ የሆኑ የመገናኛ ዘዴዎች ዋነኛ ተልእኮ ሆኗል። በዛ ላይ ይዞት የነበረው የማስታወቂያ ሚንስትርነት ሃላፊነት ህዝብ ፊት እንዲቀርብ ስለሚያደርገው የኢህአዴግ አመራርን ሃጢያት ሁሉ እሱ ብቻውን እንዲሸከም አድርጎታል። ከዚህ ስንነሳ ከላይ በተገለፀው መንገድ በአቶ በረከት ላይ የደረሰው ነገር ሁሉ ቀንዲትን እንጅ ጎዲትን እንዲሉ አይነት ሁኔታን የፈጠረ ይመስላል።

ሶስተኛው ምክንያት አቶ በረከት ትምክህትን አምርሮ የሚታገል መሆኑ ነው።  እንደሚታውቀው ኢህአዴግ ትምክህትና ጠባብነትን የኢትዮጵያ ህዝብ ብሎም የስርአቱ ዋነኛነት ጠላት የሆኑ አስተሳስቦች ናቸው ብሎ ፕሮግራሙ ላይ በግልፅ አስቀምጧል። ስለዚህም በረከት “ትምክህትና ጠባብነትን ማስወገድ የእኛ የኢህአዴግ አራቱም ድርጅቶች መሪዎችና አባላት ሃላፊነትና ግዴታ ነው ብሎ ያምናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ትምክህት የአማራን ጥቅም የሚፃረር አድሃሪሃና አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን አጥብቆ ይረዳል። ምክያቱም ትምክህት የአማራን ህዝብ ከሌሎች ወግኖቹ ጋር ተዋዶና ተከባብሮ እንዳይኖር ብሎም በጥርጣሬ አይን እንዲታይ እንደሚያደርግው ከማንም በላይ ስለሚገነዘብ ነው። ለዚህም ነው ትምክህት ነው ብሎ ያስበውን ማንኛውንም አመለካክት ከማንም ይሁን ከማን ሲሰማ የሚያንገሸግሸውና አምርሮ የሚቃወመው።

ትግል ከራስ ይጀምራል የሚል እምነትም ስላለው እኛ ብአዴኖች በውስጣችን ያለውን የትምክህት አስተሳስብ ሳናስወግድ የሌሎችን የጠባብነት አስተሳስብ ለማውገዝ ሞራል አይኖረንም ብቻ ሳይሆን ሰሚም አናግኝም፤ ብዙም ያስከፍለናል” ብሎ ስለሚያምንም ነው “መጀመሪያ ከዚህ ፀረ-ህዝብ የሆነ አስተሳሰብ ራሳችንን እናፅዳና የሌሎችን ችግር በልበ-ሙሉነት ለመታገል አቅም እናገኛለን” በሚል እሳቤ ለዚህ በጎ እምነቱ በቁርጠኝነት ይተጋ የነበረው።

ይህ በጎ እምነቱ ግን ባልሆነ መንገድ ተጣሞ ሲተረጎም አይተናል። ይህም የሆነው አንዳንዶች በግንዛቤ እጥረት፤ ሌሎች ለመረዳት ባለመፈለግ፤ ገሚሶች ደግሞ እውነታውን እያወቁ ሆን ብለው ለማጣመም በመፈለግ ሲሆን የተቅሩት ደግሞ ስም አጥፊዎች በሚነዙት አሉባልታ ተደናግረው ነው።

እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ማየት ጠቃሚ ነው ብለን እናስባለን። አቶ በረከት ትምክህትንም ይሁን ሙስናን ወይም ኪራይ ሰብሳቢነትን ብሎም ስራ ላይ ማልመጥንና የመሳሰሉ ጥፋቶችን አምርሮ የሚታገል ቢሆንም የትግል አግባቡ ላይ ችግሮች እንደነበሩበት ራሱም ይረዳል ብለን እንገምታለን። ይህን ስንል አቶ በረከት የሃሳብ ትግል የሚያደርገው ሰዎችን ለመጉዳት አስቦ ነው ከሚል መነሻ ሳይሆን ከላይ የተገለፁ ችግሮችን አምርሮ በሚታገልበት ወቅት የሰዎችን አቅምና ችሎታ ሳያገናዝብ ነው ማለታችን ነው። ይህም በራሱ የፈጠረው ቅሬታ ስለነበረ ጥቂት በማይባሉ የብአዴን አመራርና አባላት አማካኝነት ከደም ሃረጉጋ እየተያያዘ አማራውን ለመጉዳት የሚያደርገው ነው ተብሎ ተዛብቶ በድብቅ ህዝብ ውስጥ እንዲሰራጭ ይደረግ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

በነገራችን ላይ አቶ በረከት የአማራን ህዝብ ፍትሃዊ ጥቅም መሰረት አድርጎ በሚያካሂደው ትግል አጠቃን ብለው የሚያስቡ በርካታ የብአዴን አመራርና አባላት አማካኝነት ባልሆነ መንገድ ወደህብረተሰቡ የተናፈሰው ወሬ ሄዶ ሄዶ በተላያዩ ሚዲያዎች አድጎና ገዝፎ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። ውሸት ሲደጋግም እውነት ይመስላል እንዲሉ ነውና አቶ በረከትን በጥልቀት ለማያቀው የህብረተስብ ክፍል ይቅርና አበጥርጥረው ለሚያቁት ሳይቀር ያልሆነውን ነው ብለው እንዲያምኑ ሶሻል ሚዲያዎችና ጯሂ መደበኛ የመገናኛ ዘዴዎች ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ባሉባልታው የተደናገረ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የማህበረሰብ ክፍል በተለይም ወጣቱ በበረከት ላይ ቂም እንዲቋጥርና ጥርስ እንዲነክስ አድርጎታል።

አሁን አሁንማ ስለሚናገሩት ነገር ሁሉ ራሳቸው ሊያፍሩ የሚገባቸው ሰዎችና አካላት አቶ በረከትን ለማጥቃት ስራየ ብለው የያዙት ይመስላል። አንዳንዶቹ ከላይ እንደተገለፀው ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሰብራል እንዲሉ በሙስና ተከሰው ፍርዳቸውን ጨርሰው የወጡ ወይም በይቅርታ የተፈቱ፣ የሴት ጓደኞች ማፈራረቅንና ስልጣንን ተገን አድርገው የባለትዳር ሚስቶችን መንንጠቅ እንድጀብዱ አድርገው የሚንጠባረሩና የመሸታ ቤት ጀግና የሆኑ ሰዎች ጊዜ አገኘን ብለው ለህዝብ ጥቅም ሲል መስዋእትነት የከፈለውን ታጋይ በረከትን ለመዘርጠጥ እየተውተረተሩ እንዳለ ስናይ ከግርምትም በላይ ግርምት ፈጥሮብናል። በሌላ በኩል ያለአግባብ ለመጠቀም በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አይሆንም ብሎ ጉሮሯቸው ላይ የቆመባቸው አንዳንድ አካላት ደግሞ አሁንም መጣልን ያሉትን ጊዜ ተጠቅመው አቶ በረከትን ለማጥቃት እላይ እታችህ ሲኳትኑ እየተመለከትን ነው።  ያም ሆኖ እውነታው ወደፊት እየተገለጠ ሲሄድና ህብረተሰቡ ሁሉንም ነገር በሰከነና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማየት ሲጀምር ግን ማን ትክክል ማን አጥፊ እንደነበር መግባባት ላይ ይደረሳል ብለን እናምናለን።

ከላይ በተገለፁት ዋና ዋና ምክንያቶች በተፈጠረ መደናገር እና ተያይዘው በተከሰቱ ጉዳዮች ላይ ተመስርተው አሁን ያሉት ጥቂት የማይባሉ የብአዴን አመራሮች አቶ በረከት በህዝብ ተተፍቷል የሚል አቋም ላይ የደረሱ መሆኑ የምያጠራጥር አይደለም። በዚህም ምክንያት አቶ በረከትን ቆርጠው በመጣል ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሊያገኙ እንድሚችሉ የተገነዝቡ ይመስላል።  እየሰሩት ባለው ስራማ ህዝቡ ከልቡ እየደገፋቸው እንዳልሆነ በሚገባ ያውቁታል። በክልሉ ውስጥ መልካም አስተዳደር እየተዳከመ ሰው እንደ የዱር እስንሳ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሳይቀር ተጨፍጭፎ እየተገደለ፣ ንብረት በማናለብኝነት እየተዘረፈ፣ የልማት ስራዎች እያደር እያሽቆለቆሉ በሄዱበት ሁኔታ ችግሩ ሊላከክበት የሚችል ከሌላ የዘር ሀረግ የፈለቀ እንደ አቶ በረከት ያለ ለእርድ የተዘጋጀ በግ ማግኘታቸውን እንደመልካም አጋጥሚ ቆጥረውታል። ምክንያቱ ይህ ካልሆነ ታዲያ በምን ሂሳብ ነው አቶ በረከት የድርጅቱ ዋና መሪ ባልሆነበት እንዲሁም ክልሉን ለአንዴም አንኳን በበላይነት ባልመራበት ሁኔታ ጥፋቱ ሁሉ እሱ ላይ የሚራገፈው? በርግጥ ይህ የክህደት ተግባራቸው እንዳሰቡት የተወሰነ ጊዜያዊ ድጋፍ ሊያስግኝላቸው ይችል ይሆናል፤ ዘላቂ ግን ሊሆን አይችልም። ምክኒያቱም ሰንቅና ውሸት እያደር ይቀላል እንዲሉ የብአዴን አመራር በአቶ በረከት ላይ የፈፀመው ግፍና የሸር ተግባር ውሎ አድሮ ገሀድ መሆኑ የማይቀር ስለሆነ ነው።

ከዚህ አልፎም አዲስ የተቋቋመው አብን (ANM) የሚባል ድርጅትና ሌሎች እየገቡ ያሉ የአማራን ህዝብ እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚቀጥለው ምርጫ ተቀናቃኝ እንደሆኑ የብአዴን መሪዎች ያቃሉ። ታዲያ የምርጫ ካርዱን ለመውስድ ያላቸው አንዱ አማራጭ ራሳቸውን ከደሙ ንፁህ በማስመስል ለሁሉም በክልሉ ውስጥ ለጠፉ ጥፋቶች ሁሉ አቶ በረከትን ዋነኛ ተጠያቂ በማድረግ እንደምስዋእት በግ ለመጠቀም መሞከርን አማራጭ እንዳደረጉ መገመት አይከብድም።

ይህ ባይሆን ኖሮ የድርጅቱ ባህልና ህገ-ደንብ በማይፈቅደው አኳኋን አቶ በረከት በሌለበትና የሱ ሃሳብ ባልተሰማበት ኢ-ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከድርጅቱት ማዕከላዊ ኮሚቴነት ለማገድ አይጣደፉም ነበር። በርግጥ መነሻው የአቶ በረከት ጥፋት ቢሆን ኖሮ ከሶስት ሳምንታት በኋላ የሚካሄደውን ጉባኤ ላለመጠበቅ የሚያደርጋቸው ምክንያት ነበረ ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው። አቶ በረከት ላይ ያላቸውን መርህ አልባ የጥላቻ ዳርቻ የሚያሳየው ሌላውጉዳይ ደግሞ በሱ ላይ የተወሰነውን ውሳኔ እንዲሰማ ያደረጉት እንደሌላው ሰው በሚድያ መሆኑ ነበር። የሚገርመው ደግሞ ውሳኔውን በሌለበት ያሳለፉት ስብሰባው ላይ ያልተገኘበትን ሁኔታ በሚገባ እያወቁ ነው። እዚህ ላይ አንድ የሚያሳዝንና የሚያስተዛዝብ ነገር እናንሳ። የብአዴን ፅ/ቤት ከጋዜጠኛ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባይሆንም አቶ በረከት ስብሰባው ላይ መገኘት ነበረበት ምክኒያቱም ታጋይ መስዋእትነት መፍራት የለበትምና” የሚል ነው። ታጋይ የሚከፍለው መስዋእትነትስ ቢሆን አጓጉል መሆን ያለበት በየትኛው መመዘኛ ይሆን? ብአዴን ውስጥ የተፈጠረ አዲስ ግኝት ካልሆነ በስተቀር። መቸም ትክክለኛና በቅንነት የሚያስብ ሰው ይሄን መልስ ይስጣል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም እንኳን በአካል ሄዶ ሳይሄድ ገና ለገና ደብረማርቆስ ላይ ነበረ ተብሎ ምን ያህል ጉዳትና ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበረና ባንድ ጊዜ አምስትና ስድስት ቦታዎች ታይቷል ተብሎ ረብሻ ለመፍጠር ዝግጅት የሚደረግበት ክልል እንደሆነ የሚያውያቅ ሰው የዚህ አይነት መልስ መስጠት በእጃዙር የሞት ፍርድ መፍረድን እንጅ ሌላን አያመላክትም።

በመጨረሻም ከስልጣንና ከግላዊ ጥቅም ውጭ ሌላ የማይታያቸው ጥቂት የማይባሉ የብአዴን መሪዎች መረብ (Network) ዘርግተው የሌላ ዘር የደም ሃረግ አላቸው ብለው የሚያስቧቸውን ለአማራ ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከልጅነት እስከ እውቀት የታገሉትን እንደ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ የመሳሰሉ ታጋዮችንና ከነሱ አልፎም ሌሎች አማራ ቢሆኑም ጥቅማችንን ይፃረራሉ ብለው የሚገምቷቸውን ምርጥ ታጋዮች ለማጥቃት እየተውተረተሩ ባሉበት ሁኔታ ብአዴን ስህተቱን አርሞ ፍትሃዊ ለሆነ የህዝብ ጥቅም መቆም እንደሚችል ካላረጋገጠ በስተቀር ሰፊውን የአማራ ህዝብ አታግሎ ተጠቃሚ ያደርጋል ብሎ ማሰብ ከዝንብ ማር እንደመጠበቅ ያስቆጥራል።

 

 

Back to Front Page