Back to Front Page


Share This Article!
Share
ለእኛ የሚበጀን መደመር ብቻ ነውክፍል ሁለት

ለእኛ የሚበጀን መደመር ብቻ ነው

ክፍል ሁለት

አሜን ተፈሪ 07-24-18

ተፈጥሮ ምንም ነገር በከንቱ አትፈጥርም፡፡ በቋንቋ በረከት ያከበረችው ብቸኛ ፍጡር ሰው ነው፡፡ ስለዚህ የቋንቋ ብቃትን የታደለው የሰው ልጅ የቅርብ እና የሩቅ፤ ፍትሐዊ እና ኢ-ፍትሐዊውን ነገር ለመግለጽ ይችላል፡፡ የጥሩ እና የመጥፎ፤ የተገቢ እና ተገቢ ያልሆነ ነገር መለያ ዳኝነት አለው፡፡ ይህንም ብቃት የታደለው ሰው ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን መለየት እና መረዳት የሰው የብቻ ችሎታ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ነገርን መለየት እና መረዳት የሚችል ፍጡር ደግሞ እንደ ቤተሰብ እና መንግስት ያሉ ተቋማትን መመስረት ይችላል፡፡

 

ሰው ከማህበረሰብ ተነጥሎ በራሱ ብቁ ለመሆን አይችልም፡፡ በተለይ በአሁኑ ዘመን፤ ሰው ከማህበረሰብ ተነጥሎ የሚኖርበት ሁኔታ ጨርሶ የማይታሰብ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ሐኪም፣ ኢንጂነር፣ ሾፌር፣ ፓይለት ለመሆን አይችልም፡፡ በህብረት ለመኖር ችሎታ የሌለው ወይም በህብረት ለመኖር የሚያቅተው ወይም ፍላጎት የሌለው ሰው በራሱ ብቁ መሆን አለበት፡፡ በራሱ ብቁ ሊሆን የሚችለው አንድም አወሬ፤ አለያም አማልክት እንጂ ሰው አይደለም፡፡ ሰው በውስጡ የማህበራዊነት ደመ ነፍስ አለው፡፡ ስለዚህ ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው፡፡ ሆኖም የመንግስት መዋቅርን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰበ ሰው፤ የሰው ልጆች ሁሉ ባለውለታ ነው፡፡

 

Videos From Around The World

እያንዳንዱ መንግስት ወይም ሐገረ- ብሔር (ስቴት) ማህበረሰብ ነው፡፡ ህብረተሰብ ሳይሆን ማህበረሰብ ነው፡፡ በሁለቱ ሙያዊ ቃላት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ልዩነቱ የስፋት - ጥበት አይደለም፡፡ የይዘት ነው፡፡ ህብረተሰብ ውስጥ ማህበረሰብ ይካተታል፡፡ ህብረተሰብ ብዙ ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ነው፡፡ ማህበረሰብ ጠበብ ያለ ብቻ አይደለም፡፡ ከአንድ ሰው ድርጊት ጋር ተያይዞ የሚታይ ልዩ ባህርይ ያለው የሰዎች ህብረት ነው፡፡ ትስስሩ ጠንከር ያለ ነው፡፡ በዚያው መጠን በማህበረሰብ ወስጥ የምታደርገው ድርጊት የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ሰፈር እንደ ማህበረሰብ ቢሆን፤ ህብረተሰብ እንደ ከተማ ነው፡፡ አንድ ሰው በከተማ ጠጥቶ መንዘላዘል ሊደፍር ይችላል፡፡ በሰፈር ውስጥ ግን ጠጥቶ መንዘላዘልን አይደፍርም፡፡ ምክንያቱም ማህበራዊ ተጽዕኖ ያስከትልበታል፡፡ ስለዚህ ይፈራል፡፡

 

የዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ፣ የስፖርት ማህበረሰብ፣ የኪነ ጥበብ ማህበረሰብ ሲባል እንሰማለን፡፡ ማህበረሰብ ስንል ትስስሩ ጠንካራ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ አባላት ጋር የግል የሚባል ግንኙነት ያለበት ነው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ነች ስንል፤ ጠንከር ያለ ትስስር ያላቸው አባላት የሚገኙበት ህብረት መሆኑን ማመልከታችን ነው፡፡ በዚህ ስሌት ኢትዮጵያ መንደር ስትሆን ኢጋድ ከተማ ነው፡፡ ሆኖም የኢጋድ አባል ሐገራት ኢትዮጵያ ፣ ኬንያ፣ ሶማሌያ እና ኬንያ እንደ ከተማ ሊታዩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡

 

እያንዳንዱ ስቴት ማህበረሰብ ነው፡፡ አንድ ዓይነት (መልክ፣ ገጽታ ወይም ጠባይ) ያለው ማህበረሰብ ነው፡፡ የምንመሰርተው እያንዳንዱ ማህበረሰብ የሚመሰረተውም አንድ የሆነ ጥሩ ዓላማን ለማሳካት ነው፡፡ የሰው ልጆች አንድ ነገር የሚያደርጉት ለከንቱ አይደለም፡፡ በእነርሱ እይታ ጥሩ ግምት የሚሰጠውን አንድ ጥሩ ነገር ለማግኘት ነው፡፡ ሁሉም ማህበረሰቦች አንድ የላቀ ግምት የሚሰጠውን ዓላማ ለማስፈጸም የሚሰሩ ከሆነ፤ ስቴት ወይም የፖለቲካ ማህበረሰብ የሚባለው ነገር እጅግ ከፍ ያለ ማዕረግ ያለውን አንድ ዓላማ ለማሳካት የሚመሰረት ነው፡፡ ይህ ማህበረሰብ ሌሎች ማህበረሰቦችን ሁሉ አጠቃሎ የሚይዝ በመሆኑ፤ ሊያሳካ የሚፈልገውም ዓላማ በዚሁ አንጻር እጅግ የላቀ ይሆናል፡፡ ከሌሎች ሁሉ ብልጫ ያለው እጅግ ከፍተኛ ማዕረግ የያዘ ግብን ለማሳካት የሚሰራ እና ይህን እጅግ የላቀ ግብ እውን ለማድረግ የሚነሳ ይሆናል፡፡

 

የፖለቲካ ማህበረሰብ እጅግ የላቀ ግብን እውን ለማድረግ የሚመሰረት ቢሆንም አንዳንዶች እጅግ ለወረደ ዓላማ ያውሉታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በጠበበ መልክ ይተረጉሙታል፡፡ መንግስት የምንመሰርተው በደልን ለመከላከል፣ ሰላም እና ፍትሕን ለማስፈን ነው፡፡ እኔ የምፈልገው በደል እንዲጠፋ የሚያደርግ መንግስት እንጂ የራሴን ቋንቋ እየተናገረ፤ የእኔን ቋንቋ ከማይናገሩ ሰዎች በበለጠ የሚበድለኝ ከሆነ ለውጥ የለውም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተፈጠረ የሰላም ምንጭ ያልነው ስርዓት የብጥብጥ አውድ ይሆናል፡፡ መጀመሪያም ችግሩ የሁለት ሰዎችን ግኙነት በፍትህ፣ በትክክል የሚያስተዳድር መርህ ወይም ህግ ከመጥፋት እንጂ የቋንቋ ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድን ቡድን እወክላለሁ የሚል ብሔርተኛ ቡድን የዚያን ብሔር አባል ብቻ ለመጥቀም የሚሰራ ከሆነ፤ አውክለዋለሁ ለሚለው ቡድንም ሊጠቅም አይችልም፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን (የሰው ልጆች) የሚሆን መንግስት ለመመስረት የሚጥር ቡድን የራሱንም ብሔር መብት ለማስከበር ይችላል፡፡ ለሁሉም የሰው ልጆች ለመስራት በሚያስችል መርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቡድን የራሱን ብሔር መብትም ለማስከበር ይችላል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ችግር የሚፈታው አንድን ህዝብ በድሎ ሌላውን ለመጥቀም በሚሰራ መንግስት አይደለም፡፡

 

ቀደም ሲል የጠቀስነውን የሂትለር ታሪክ እንመልከት፡፡ ለጀርመን ህዝብ በማሰብ ከሆነ ከናዚ የሚተካከል ቡድን የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ሂትለር የጀርመን ዘር ከመዳቀል መጠበቅ ያለበት ምርጥ ዘር መሆኑን የሚያምን፤ የጀርመን ህዝብ ከየትኛውም ህዝብ በላይ የከበረ ህዝብ መሆኑን የሚያምን ነው፡፡ ይህን እጅግ የሚያከብረውን ህዝብ ከመጥፎ የተፈጥሮ ክስተት ለመጠበቅ እና የዘሩን ጥራትም ለመጠበቅ፤ አንዳንድ የሐሳብ እና የአካል ጉድለት ያለባቸውን ጀርመናውያን ለማጥፋት በካምፕ በማጎር፤ በእርሱ እምነት ታላቅ አድርጎ የሚመለከተውን የጀርመን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር ሞክሯል፡፡ ስለዚህ የጀርመንን ዘር ለመጠበቅ ሲባል መጥፎ አስተሳሰብ ያላቸውን፤ አብስትራክት ስዕል በመሳል የህዝቡን መልካም ትውልድ የሚያበላሹ ሰዓሊያንን አጥፍቷል፡፡

የዚህ ናዚ አስተሳሰብ መሰረቱ ለሁሉም የሰው ልጆች የሚሆን ስርዓት መፍጠር አይደለም፡፡ ለጀርመናውን የሚመች ስርዓት ለመፍጠር ነው የታገለው፡፡ ስለዚህ ለጀርመን ህዝብ ጥቅም ሲል ሌላውን ህዝብ ለመፍጀት ተነሳ፡፡ ዓለምን በጦርትን አመሳት፡፡ ግን የጀርመን ህዝብ የሰው ፍጡር በመሆኑ፤ የጀርመንን ህዝብ ለማገልገል የሚቻለው ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን ስርዓትን በማስፈን ነበር፡፡ ለጀርመን ህዝብ አስብኩ የሚለው ሂትለር የጀርመንን ህዝብ አጠፋው፡፡ ታሪኩ የሼክስፒሩ ኦቴሎ እንዳለው፤እንደ ወደድኩሽ ገደልኩሽ ሆነ፡፡

 

የፖለቲካ መሠረቱ አብሮ ለመኖር የሚያስችል ስርዓት መፍጠር ነው፡፡ አብሮ ለመኖር የማይችል እና አብሮነቱን በፍትህ ላይ ያላጸና የሰዎች ስብስብ የፖለቲካ ማህበረሰብ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ናዚ ማጥፋት ጀመረ፡፡ ለማጥራት ማጥፋት ጀመረ፡፡ ሌሎችን ብቻ ሳይሆን ጀርመናውያንንም ለማጥፋት ተነሳ፡፡ ለሰው ልጆች ሁሉ ሊሆን የማይችል መንግስት ነበር፡፡ ስለዚህ ለጀርመኖችም ሊሆናቸው አልቻለም፡፡

 

እንዲህ ዓይነት መንግስት የራሴ የሚለውንም ብሔር ተወላጅ ለመጥቀም አይችልም፡፡ አንዱን በድሎ ለሌላው ህዝብ ለመጥቀም የሚችል መንግስት ሊኖር አይገባም፡፡ ሁሉንም ብሔሮች ለመጥቀም የሚችል መንግስት መሆን ከቻለ፤ ለአንድ ብሔር ለሚጠቅም የሚችል መንግስት ይሆናል፡፡ አንድ ብሔር ለመጥቀም የሚችል መንግስት ለመመስረት የሚቻለው ሁሉንም ብሔሮች ለመጥቀም የሚችል መንግስት በማቋቋም ነው፡፡ ሁሉንም ብሔር ለመጥቀም የሚችል መንግስት ለመመስረት የሚያስችል መርህ አለ፡፡

 

የትግራይን ህዝብ ለመጥቀም የሚሰራ መንግስት ከሆነ፤ ለአማራም ለኦሮሞም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የራሴ የሚለውን ብሔር ለመጥቀም የሚችለው ሁሉንም የሰው ልጅ ሊጠቅም በሚያስችል መርሆዎች ላይ የተመሠረተ መንግስት ነው፡፡ ይህ መንግስት አንዱን ጠቅሞ ሌለውን ሊጎዳ የሚያስችል መርህ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ይጠቅማል፡፡

 

ሁለት ሰዎችን በቀለም፣ በማህበራዊ ምንጭ እና በአቋም ለያይቶ ለማየት የማይችል መንግስት ብቻ ነው፤ እወክለዋለሁ ለሚለው ብሔር ሊጠቅም የሚችል መንግስት የሚሆነው፡፡ ለእኔ ብሔር እጠቅማለሁ ብሎ የሚሰራ መንግስት፤ የእርሱ ብሔር አባላት ያልሆኑ ሰዎች በሚገኙበት ሁኔታ እውነት መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የእርሱ ብሔር አባላት ያልሆኑ ሰዎች በማይኖሩበት አጋጣሚ፤ የእርሱን ብሔር ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ሁለት ሰዎች ከፊቱ ይቆማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ፤ ያው እንደ ለመደው የኔ የሚለው ሰው ይኖረዋል፡፡ በመንደር፣ በአብሮ መማር፣ በሐይማኖት፣ በጋብቻ፣ በትውልድ ሥፍራ ወዘተ መስፈርት አንዱን ከሌላኛው ሰው በተለየ ይቀርበዋል፡፡ በዚህ ጊዜ እንደ ለመደው ለእኔ ለሚለው ሰው ለማድላት መሄድ ነውር መስሎ አይታየውም፡፡ ስለዚህ በደሉ ይቀጥላል፡፡

 

ስለዚህ አንድ መንግስት ለሰው ልጆች ሁሉ ጠቃሚ በሆነ መርህ የሚመራ ከሆነ፤ በምንም ዓይነት ሚዛን በዜጎች መካከል ልዩነት ማድረግ አይፈልግም፡፡ ይህ መንግስት እወክለዋለሁ ለሚለው ሰው ይጠቅማል፡፡ ሰው ለሆነ ፍጡር ሁሉ ይጠቅማል፡፡ የአማራ ገዢ መደብ ወይም የትግሬ ገዢ መደብ የሚባል የፖለቲካ ኃይል አይኖርም፡፡ ትግሬን በድሎ አማራን መጥቀም የሚችል መንግስት ሊኖር አይችልም፡፡፡ አንድም ሁለቱንም ይጠቅማል ወይም ሁለቱንም ይበድላል፡፡ አሁን የምናያቸው ችግሮች ሁሉ ምንጫቸው ከዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት ነው፡፡

 

ቋንቋው እና ባህልን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ አንድ ሰው ብን በሁሉም አካባቢ የሚነገሩ ቋንቋዎችን ሊያውቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ ያልተማከለ አስተዳደር ከመፍጠር እና አካባቢውን በሚያውቅ ሰው ለማስተዳደር መመከር ከውጤታማነት አንጻር ተመራጭ ይሆናል፡፡ ሥልጣን ባልተማከለ ሁኔታ መደራጀቱ ለአስተዳደር ቅልጥፍና ወይም ውጤታማነት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ አካባቢውን ወይም ባህሉን የሚያውቅ አመራር የተሻለ ውጤታነማነት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን አካባቢውን ወይም የህዝብን ፍላጎት ለማወቅ የሚቻለው ቋንቋውን በማወቅ ብቻ አይደለም፡፡ ቋንቋውን አውቆ ህዝብን ሳያማክር ከሚሰራ ሰው ይልቅ ቋንቋውን ሳያውቅ በአስተርጓሚም ቢሆን ህዝቡን አማክሮ የሚሰራ ሰው የህዝቡን ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ ያውቃል፡፡ ነገሩ ቋንቋውን የማወቅ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የህዝብን ፍላጎት የማክበር የሞራል ወይም የፖለቲካ አቋም ጉዳይ ጭምር ነው፡፡

 

አሁን እንደሚታየው ኢህአዴግ በብሔር የተደራጀ መንግስት በመመስረቱ የወቅቱን አንገብጋቢ ጥያቄ ቢፈታም በርካታ አዳዲስ ቅራኔዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ እነዚህን አዳዲስ ቅራኔዎች ለመፍታት ለሰው ልጆች የሚሆን መንግስት የመመስረት ፕሮጀክት ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ሁሉም ወደ ብሔር ጎጆው ከገባ በኋላ የፖለቲካ አስተዳደሩ በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ጉዳይ ይሆናል፡፡ በሰዎች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ ይህን ሰብአዊ ግንኙነት ለማስተዳደር የሚያስችል መርህ መከተል አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መድረሻችን በሰብአዊነት ላይ የተመሰረት አስተዳደር ማጽናት እንጂ የብሔር መዝሙር እየዘመሩ መኖር አይደለም፡፡

 

ከራሳችን ተጨባጭ ልምድ መማር እንችላለን፡፡ ኤርትራ ጉዳይ ከእኛ ተገንጥላ በመሄዷ ብቻ ሰላም እንዳልተገኘ፤ የብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ህዝቦች መብትን በማክበር ብቻ ዘላቂ ሰላም ማግኘት አልተቻለም፡፡ ሁሉም ብሔሮች የየራሳቸውን አስተዳደር መስርተው በመኖራቸው፤ የራሳቸውን ቋንቋ መናገር በመቻላቸው ነገሩ ፍጻሜ አላገኘም፡፡ ነገሩ የራስ ቋንቋ ተናጋሪ በሆነ መሪ በመተዳደር የሚያበቃ ጥያቄ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ በልዩነት ስሌት የራሴ ሰው ይግደለኝ ሊባል ይችላል፡፡ ሆኖም ሁላችንም በየክልላችን ከገባን በኋላ፤ ጉዳዩ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ የሁለት ሰዎች ግንኙት ጉዳይ ይሆናል፡፡ በዚህ ውስጥ የእኔን ቋንቋ እየተናገረ የሚበድለኝ ከሆነ፤ ፍትሕን የሚዛባ ከሆነ፤ በአድሎ የሚሰራብኝ ከሆነ፤ ይህ መንግስት የእኔን ቋንቋ የሚናገር ጨቋኝ መንግስት ነው፡፡

 

 

ሰላም የሚገኘው ከትክክለኛ ፖሊሲ ነው፡፡ የሰላም ምንጭ ትክክለኛ የፖለቲካ እና የኢከኖሚ ፖሊሲ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የዕድገት ምንጭ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ይህን እንደ አግዚየም መውሰድ ይቻላል፡፡ ግን ሌላ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል ነገር ይነሳል፡፡ ይህን ጥያቄ በሁለት ወገን ከፍዬ አየዋለሁ፡፡ በፖሊሲ እና በአፈጻጸም ደረጃ ከፍየ አየዋለሁ፡፡

 

በእኔ እምነት በፖለሲ ደረጃ የሐብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ፖሊሲ መኖሩን እቀበላለሁ፡፡ ግን ይህን ተመልክተን ዝም ካልን እንሳሳታለን፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት የበጀት አመዳደቡን መሠረት አድርገው ድሃ ተኮር ነው፤ የሐብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ነው በማለት ሙግት ያነሳሉ፡፡ የመንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ 85 በመቶ ለሆነው አርሶ እና አርብቶ አደር ህብረተሰብ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ የሐብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ጥሩ ፖሊሲ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ግን አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችለው ፕሮጀክት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ካልተጠናቀቀ፤ ተጠቃሚ የሚያደረገውን የህብረሰተብ ክፍል ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡ ፕሮጀክቱ ከተመደበለት ገንዘብ በሁለት እና በሦስት እጥፍ የሚወስድ ከሆነም ያው ነው፡፡ ፕሮጀክቱ፤ ለጨረታ ሲቀርብ የግልጽነት እና የተጠያቂነት አሰራርን ባልተከተለ መንገድ ኩባንያ አሸናፊ የሚደረግ ከሆነ፤ ውጤቱ ዜሮ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ጥገኛውን የሚያጠናክር ከሆነ ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚያደፋፍር ከሆነ፤ ውጤቱ ያው ዜሮ ነው፡፡

 

የአነስተኛ እና ጥቃቅን ብድር ተቋማት አሰራር ጤነኛ ነው ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ፤ መልሱ አይደለም ከሆነ፤ ውጤቱ ያው ዜሮ ነው፡፡ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል መሬት የመንግስት እና የህዝብ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ከተደረገ በኋላ ይህን ሐብት በተለያየ አግባብ እንዲዘረፍ ከተደረገ የሐብት ክፍፍል ጥያቄ አይመለስም፡፡ በእርግጥ አዲስ አባባ ውስጥ መሬት ለመግኘት የማይችሉ ወጣቶች ወይም ሴቶች መሬት ማግኘታቸውን እናያለን፡፡ ግን ይህ ዕድል የፖለቲካ አቋም ወይም ሌላ ነገር ሚዛን ውስጥ ሳይገባ የሚሰጥ ነው? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ችግር ካለ ውጤቱ ዜሮ ነው፡፡ በትክክል ተፈጽሞ ሲያበቃ፤ መሬቱን ለልማት ሥራ የወሰዱት የተደራጁ ወጣቶች ተመልሰው ኪራይ የሚሰበስቡበት ሁኔታ ከተፈጠረ ያው ዜሮ ነው፡፡ የራሱን ቤተሰቦች መዝግቦ ማህበር አደራጀሁ እያለ ለመጣ ሰው ቦታ የሚሰጥ ከሆነ፤ የሐብት ክፍፍል የለም፡፡ ሐብቱ ወደ አንድ ቤተሰብ ይሄዳል እንጂ ክፍፍል የለም፡፡ ጥያቄው ይህ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታየው ቀውስ ሁሉ የመጣው ከነበሩብን ተጨባጭ ችግሮች ነው፡፡ መንግስት ችግሮቹን ተቀብሎ ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ መፍትሔውም፤ ፍቅር፣ ይቅርታ እና መደመር ነው፡፡ ለእኛ የሚበጀን መደመር ብቻ ነው፡፡

 

 

Back to Front Page