Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጤፍ ከሰጠው ምላስ የሰጠው ይበልጣል!

ጤፍ ከሰጠው ምላስ የሰጠው ይበልጣል!

 

(ከገራገር ዘበርጋ፡- 11/03/2011 ዓ.ም)

መግቢያ፡

ያገሬ ሰው በተለምዶ ጤፍ ከሰጠው ምላስ (አፍ) የሰጠው ይበልጣል! የሚል ብሂላዊ አነጋገር አለው፡፡ ይህ አባባል ሰምና ወርቅ ሳይወጣለት እንዲሁ ለመረዳት የፈለገ ሰው ብዙውን ጊዜ ጤፍ ይዞ ከቀረበው ሰው ይልቅ ምላሱን በመጠቀም ወይም ባንደበቱ አካባቢውን ጮክ ብሎ በመናገርና በማዳመቅ የቻለው ሰው ይበልጥ ተሰሚነትና ተቀባይነት ሲያገኝ ይታያል የሚል ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ያ ብዙ ድካምን አልፎ ጤፉን ይዞ የቀረበው ሰው ግን ምንም እንኳን ጤፍ ይዣለሁ! እኔ የያዝኩት ጤፍ ማንም ሊያልፈው አይችልም! ብሎ ቢያስብም ባካባቢው ያለው ሰው ስላልሰማውና ስላልታወቀለት ብቻ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ጤፉን ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲመለስ ይገደዳል የሚል አንድምታም ያለው አባባል ነው፡፡

Videos From Around The World

ባሁኑ ወቅት ባገራችን የሚስተዋለው የፖለቲካ ክንዋኔና ሂደትም ከላይ ከተጠቀሰው ብሂላዊ አነጋገር ጋር ስናያይዘውና ስናገናዝበው በተወሰነ ደረጃ ብሂላዊ አነጋገሩ አግባብነት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

1.  የለውጡ ሂደት፡

የኢሕአዴግ መንግስት ላለፉት 27 ዓመታት ሲገዛ እንደቆየና (ለነገሩ አሁንም ያለው መንግስት ራሱ ኢሕአዴግ ነው) ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ደግሞ አገዛዙ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተገፋና እየተደፈረ እንደመጣ፡ በተለምዶ ስብሰባና መድረክ ሰውን አሳምኖና ብሎም አስፈራርቶ መግዛት ከማይቻልበት ደረጃ እንደደረሰ፡ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰው የወጡ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ ፈትተው በየአውራ ጎዳናውና በየመጠጥ ቤቱ የሚውሉበት ሁኔታ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት በመንግስት አሰራር ተስፋ የመቁረጥና ጥላቻን የማሳደር ስሜትንና አቅጣጫን እየያዙ ስለመጡ ወደ አመጽና ብሎም ሽብር ተግባር ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ሁኔታ እንደተፈጠረ፡ ከውጭና ከውስጥ ሆነው አገዛዙን ወይም ስርዓቱን የሚቃወሙት ኃይሎች ደግሞ ይህንኑ ሁኔታን መሰረት በማድረግ ወጣቱ በአገዛዙ ላይ እንዲነሳሳ በኢሳት፡ በቪኦኤ፡ በዶቼቬሌ፡ በኦኤምኤንና በሌሎችም ሶሻል ሚዲያዎች አማካይነት ከፍተኛ ፀረ አገዛዙ ቅስቀሳና መረጃ በማስተላለፍ ወጣቱንና ሕዝቡን ለማነሳሳት በመቻላቸውና ባንጻሩ ደግሞ ነፍጥ ይዘው መንግስቱን እንፋለማለን ብለው ከኤርትራ መሬት ሆነው ሲፎክሩ ለነበሩት ኃይሎች ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሽፋን በመስጠትና ተገቢው ማተሪያላዊ ድጋፍ ጭምር እንዲደረግላቸው በመቀስቀስ ሰፊ ስራ እየተደረገ እያለ ጩንቻውን የተማመነው የኢሕአዴግ መንግስት ግን ውስጣዊውን የወጣቶች ብሶትንና ስራ አጥነትን ለመፍታት ያከናወነው ብዙም አመርቂ ተግባር ስላልነበረ በስተመጨረሻው የወጣቶች ነውጥ ተቀነባብሮ ሲነሳበት አስቸኳይ አዋጅ ደጋግሞ በማውጣት ሁኔታውን ለማብረድ ከመሞከርና ክንዱን ለማሳየት ከመሞከር ውጭ ካንድ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቅና ስራ ፈጠራን የሚያስፋፋ ተግባር በተገቢው መንገድ ለማከናወን ባለመቻሉ ምክንያት ለውስጣዊ ፖለቲካዊ ክፍፍል እንደተጋለጠና ራሴን አሳድሻለሁ ብሎም ክፍፍሉን ሊያስቀር አለመቻሉን ለመገንዘብ እንደተቻለ፡ ኢሕአዴግ ከውስጣዊ ክፍፍሉ ለመዳን ብሎ በውስጡ ጥገናዊ ለውጥ አድርጎ እንደተለመደው አገዛዙን ለመቀጠል ቢፈልግም በውስጡ የነበረው ክፍፍል ከወጣቶች አመጽና ከተቃራኒ ኃይሎች ግብ ጋር የተሳሰረው ኃይል የድርጅቱን ሊቀመንበርነት እለቃለሁ! ካሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ ለመረከብ በተደረገው ውስጣዊ ትግል ከአራቱ ድርጅቶች መካከል ሁለቱ ባንድ ጎራ ተሰባስበው ሊቀመንበርነቱ ከሁለቱ ላንዳቸው እንዲሆን ውስጥ ውስጡን ሲሰሩ ከቆዩ በኃላ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድርጅትም በርሳቸው አስተባባሪነት በቡድን ተከፋፍሎ ከላዩ ላይ ለማንም ተመራጭ ያልወገነ በመምሰል ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፡ እንደአቋም ግን የሊቀመንበርነቱ ስልጣን ከፍተኛ የሕዝብ ውክልና ላለው ድርጅት በተለይም ለኦሮሞ እንስጠው የሚል አቋም በመያዝ በምስጢር ሲንቀሳቀስ እንደከረመና በስተመጨረሻው ሊቀመንበር ሲመረጥም የራሱን ድርጅት ተወካይ ትቶ የአቶ ኃይለማርያም ቡድን ያሁኑን ሊቀመንበር እንደመረጠ ይታወቃል፡፡

አሁን እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንግዲህ ምንመ እንኳን በኢሕአዴግ አመራር ሲነገርለትና ሲነታረኩበት እንደነበርና ለውጥን ማምጣት አለብን! ተባብለው የወጡበት ሂደት ቢሆንም የአካሄዱ ቅኝት ሲገመገም ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎትና ምኞት ብቻ እንደመጣ ተደርጎ የሚታሰብበት ወይም የሚወሰድበት አካሄድ ይታያል፡፡ ባንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስርዓቱ ውስጥ እንዳልነበሩና ለጠፋው ጥፋት ወይም ለተከሰተው ጉድለት የእሳቸው እጅ እንደሌለበት ተመስሎ እየቀረበ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በተለይም ብአዴን፡ ኦሔደድና ደኢሕዴን በተፈጸመው የኢሕአዴግ መንግስት ጥፋትና ጉድለት እጃቸው እንዳልነበረበት ተመስለው የሚቀርቡና ሚዲያውም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ትረካ ደጋግሞ በማስተላለፍ ላይ ሲገኝ ለደረሰው ጥፋትም ይሁን በደል ተጠያቂው ሕወሓት ብቻ እንደሆነ ተደርጎ የሚተረክበት ሁኔታም በግልጽ ይታያል፡፡ ሆኖም የዚህ ዓይነቱ ከደሙ ንጹሕ ነኝ ዓይነት የፖለቲካ ሸፍጥ ለኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ይሁን ለአገሪቱ መጻኢ እድል ጠቃሚ ሆኖ አይታይም፡፡ ለምን ቢባል የሚከተሉትን የቅርብ ጊዜ የኢሕአዴግ መንግስት ተግባራትን ብቻ ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ ስሕተት እየፈጸሙ መሆናቸውንና ከኃላፊነት ለማምለጥ የማይችሉባቸውን ክንዋኔዎች ብቻ በማንሳት የጋራ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ለማሳየት እንሞክር፡፡

2.  የፀረ-ሽብር አዋጅና ዓላማው፡

በመሰረቱ በአገሪቱ ውስጥ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በተግባር ላይ የቆየው የፀረ-ሽብር አዋጅ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት እያሉ በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት የወጣ አዋጅ ሆኖ ዓላማው በአገሪቱ ውስጥ ሊፈጸሙ ከሚችሉት የሽብር ተግባራት ለመከላከልና የአገሪቱንና የሕዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ የወጣ ሆኖ ይህም አዋጅ ከወጣ በኃላ ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጣቸው የደህንነት፡ የፖሊስና የመከላከያ ብሎም አጠቃላይ የፀጥታ አካላት ባዋጁ መሰረት ለመንቀሳቀስ በመቻላቸው ምክንያት የአገሪቱና የሕዝቡ ውስጣዊ ሰላም ባስተማማኝ መንገድ ተከብሮ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ከሽብርተኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ኃይሎችና ግለሰቦች ከውስጥም ከውጭም እየተለቀሙ ለፍርድ ይቀርቡ እንደነበርና የፀጥታው አካል ግዴታውን በቅጡ ይወጣ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ እያለ የአሁን ትረካ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መንግስት አሻባሪ ነበር! ብለው አፍ አውጥተው ሲነግሩን እንሰማለን፡፡ መንግስት አሸባሪ ከሆነ እኮ እሳቸውም የአሸባሪው መንግስት አካል ስለነበሩና አሁንም ያንኑ የኢሕአዴግ መንግስት መሪ ስለሆኑ የአሸባሪነቱ ካባ ለሌላው ተሰጥቶ ለርሳቸው ከቶም ሊቀርላቸው አይችልም፡፡ በርግጥ ነው የፀረ-ሽብር አዋጁ በተወሰነ መልኩና ድንጋጌዎቹ ሕገመንግስቱን በሚጻረር መልኩ የወጣና ተግባራዊ ሲደረግም የሚያዙትን ሰዎች ሰብአዊ መብትንና አካልን በሚጎዳ አካሄድ እንደተፈጸመ በቅርቡ ከተጎዱ ወገኖች ከሚሰማው ሮሮና ሰቆቃ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አዋጁ ሕገመንግስቱን የሚጻረሩ ድንጋጌዎች ካሉት ወይም አዋጁ ባልተፈለገ መንገድ ተተርጉሞና ተተግብሮ ከሆነ ተጠያቂው ማነው ብለን የጠየቅን እንደሆነ የተጠያቂዎች የተጠያቂነት ኃላፊነት እንደሚከተለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

n  አዋጁ ጉድለት ካለበት የመጀመሪያው ተጠያቂ አካል ሕጉን ያወጣው የተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት ስራ ላይ እንዲውል ያወጣው አዋጅ ችግር ካለበት የቅድሚያ ኃላፊነቱን ራሱን ይወስድና ሌሎች ደግሞ ከምክር ቤቱ ቀጥለው ይመጣሉ፡፡

n  በሁለተኛ ደረጃ ኃላፊነቱን የሚወስደው አካል አዋጁን በተዛባና ምናልባትም ሕገመንግስቱን በሚጻረር መልኩ ተግባራዊ ተደርጎ ከሆነ በዚህ ግድፈት ላይ ክትትል አድርጎ እርምት ያልወሰደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡

n  በተዋረድ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡

n  ከዚያ በመቀጠል ኃላፊነት የሚወስዱት የመረጃ ደህንነት፡ የፊዴራል ፖሊስ ኃላፊዎችና በተዋረድ የተቀመጡት የበታች ሹሞችና ሰራተኞች ይሆናሉ፡፡

አሁን የምናየው የተጠያቂነት ጉዳይ ግን አንዳንዶቹ አካላትና ኃላፊዎች ከደሙ ንጹሕ ነን ለማለት ሲቃጣቸውና ሲሞክሩ የሚታዩ ሲሆን ይባስ ብሎም አዋጁን እንደማያውቁትና በምክር ቤት ቁጭ ብለው መክረው እንዳላወጡት ተመስለው መቅረብ፡ አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን ብለው አገር እንዳልመሩና እንዳልነበሩ ተመስለው ለመቅረብ ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡ ምንም እንኳን ሟችን መክሰስ ስለማይቻል አቶ መለስን አይጠየቁም ብንልም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን ከ2004 ዓ.ም ጀምረው ጠቅላይ ሚኒስትር ስለነበሩና እያንዳንዷን የፀረ-ሽብር እንቅስቃሴና ውጤት በጠረጴዛቸው በኩል ስታልፍ ስለነበርና ማናቸውንም የደህንነትና የመረጃ ስራ ይመሩት ስለነበር አሁን ስልጣን ስለለቁና በክብር ስለተሸኙ ብቻ ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ እንዲያውም አብዛኛው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ጉድለት በሳቸው ዘመን የተፈጸመ ስለሆነ የአንበሳው ድርሻ ተጠያቂነት መውሰድ ያለባቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡

ያሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርም አዋጁ ሲወጣ የፓርላማ አባል ከመኖራቸውም በላይ እስከ ሚኒስትርነት ደረጃ በአቶ ኃይለማርያም መንግስት ስር ያገለገሉ፡ የደህንነት አባል ሆነው የሰሩ በመሆናቸው ምንም እንኳን እኔም ከውስጥ ትግል እያደረግኩ ነበር ብለው ሊሸነግሉን እንደሚሞክሩ ቢገመትም የስርዓቱ አካል ሆነው ስለመቀጠላቸው ግን ሊካድ አይቻልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተገኝተው ስለመንግስታቸው የስራ አፈጻጸምን አስመልክተው ማብራሪያ እንዲሰጡ በተደረገበት በ2010 ዓ.ም መገባደጃ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢሕአዴግ መንግስት አሻባሪ እንደነበርና ዜጎችን አለአግባብ እንዳሰረና እንደበደለ ገልጸው ሲያበቁ በይፋም ሕዝቡን ይቅርታ እንደሚጠይቁ በመግለጽ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ ይቅርታውና ለሕዝቡ ያላቸው ትሕትና ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ይቅርታ ሲጠይቁ በመንግስታቸው ስም ሆነው ለተፈጸመው ድርጊት ሕዝቡ ይቅር እንዲልላቸው ሲጠይቁ የሕዝቡ ይቅርታ ከራሳቸው ጀምሮ የቀድሞ አለቃቸውን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝንና አቶ ደመቀ መኮንንን፡ እንዲሁም ካቢኔውንና ከስሩ የሚገኙትን የፀጥታ መዋቅሮችንና ኃላፊዎቹንና ሰራተኞችንም ያጣቃለለ መስሎን ነበር እንጂ እሳቸው ያሁኑ አለቃ በመሆናቸው ከይቅርታው ተቋድሰው ሲያበቁ ሌሎች አለቆቻቸውም እሳቸው እስካልመሩት ድረስ የማይጠየቁ በሚመስል ትርጉም ሊገባን አልቻለም ነበር፡፡ በዋልን ባደርን ቁጥር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደሙ ንጹሕ ሆነው ራሳቸውን ነጻ ካደረጉ በኃላ በሂደት ግን ሊያጠቁዋቸው የፈለጉትን የቀድሞ አለቆቻቸውንና የስራ ባለደረቦቻቸውን በሰብአዊ መብት ጥሰትና ረገጣ እስር ቤት ሲያስገቡዋቸው ይታያሉ፡፡ ይህች ናት የፖለቲካ ጨዋታ ማለት፡፡

የድሮ የደህንነት አለቆቻቸውና የስራ ባለደረቦችን ለማሰርና ለማሳደድ ከተነሱ ዘንዳ እሳቸውም ተጠያቂ መሆናቸውን ሊያውቁት ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አሁን በመከሰስና በመሳደድ ላይ የሚገኙት አንዳንድ የደህንነት ሰራተኞች ምንም እንኳን የፈጸሙት የሰብአዊ መብት ረገጣ አይኖርም ባይባልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸውን ወክለው በፓርላማ ፊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት ይቅርታና ትሩፋቱ ለራሳቸውና ሊጎዱዋቸው ላልፈለጉት ደጋፊዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ትሩፋቱ ለሁሉም የፀጥታ ኃላፊዎችና ሰራተኞችም ጭምር የሚተርፍ መሆን ነበረበት፡፡ ምክንያቱም ይቅርታው ለግማሹ የሚሰራ ለግማሹ ደግሞ የማያዳረስ ሆኖ ሊወሰድ አይገባውምና፡፡ በደቡብ አፍሪቃ የተካሄደው ሁሉንም ወገኖች ጉዳት ባደረሱትንም ባላደረሱትንም ላይ ተግባራዊ የሆነ ሂደት እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ሂደት ነው፡፡ አገራችን ውስጥ ግን የይቅርታው ሂደት ለእናት ልጅና ለእንጀራ ልጅ በሚል ተለይቶ ሲሰራበት እያየን ነው፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ ቂምንና በቀልን ቋጥሮ ለሌላ ጊዜ በይደር የሚተላለፍ እንጂ ለአገሪቱ መጻኢ ፍትሕን የማስፈን ተግባር የሚጠቅም ሆኖ አይታይም፡፡

 

3.  የሙስና ተግባርና የቀን ጅብነት መፈክር፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መንግስት በሙስና ተግባርና በቀን ጅብነት ፍረጃ እየተከተለው ያለው መንገድም ሚዛናዊነት የጎደለውና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ተብሎ የሚሰራ ይመስላል፡፡

3.1.     የቀን ጅብነት፡

ይህ ሐረግ ወይም ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሚዲያ የተወረወረው በሰኔ 16/2010 ዓ.ም የመስቀል አደባባይ ላይ የቦንብ ጥቃት ከደረሰ በኃላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አድራጊዎቹን ለማፈላለግና ሕዝቡም ቃሉን ተቀብሎ ወደ አንድ አቅጣጫ ወይም ብሄር አተኩሮ እንዲመለከት ለማድረግ የተቀየሰ አነጋገር ይመስላል፡፡ እንደተጠበቀውም የቀን ጅቦቹ ስያሜ በትግራይ ተወላጅ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ስለተዘመረ ሕዝቡም ይህንኑ አባባል ተቀብሎ ትኩረቱን ወደ ትግራይ ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን በትግራይ ተወላጆች ባጠቃለይ ያነጣጠረ እንዲሆን አድርጎ በመተርጎም በአዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች ላይ በሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ላይ አንዳንዴ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፡ ሌላ ጊዜም የመግደል፡ በሌላ ጊዜም ከሚኖሩበት ማባረር ወይም እንዲወጡ ማድረግ፡ ሕዝብን እንደሕዝብ መተያያትና መከባበር ቀርቶ የማንጓጠጥ፡ የመስደብ፡ ወዘተ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ከርሟል፡፡ በመሰረቱ ይህ ያልተገባ ስያሜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ለመወርወር እንደፈለጉ ምክንያቱን ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት፡፡ ሆኖም በትግራይ ተወላጆች ላይ ያሳደረው ተጽእኖና አንገትን የመድፋት ሁኔታ ግን ምን ያህል ስሜትን እንደሚጎዳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገነዘቡት ቢሆን መልካም ነው፡፡ ውሻ በከፈተው እንደሚባለው ሆነና ባሁኑ ወቅት ባዲስ አበባ ውስጥ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ሲኖሩ የነበሩት በርካታ የትግራይ ተወላጆች በየመደብሮቻቸው በርና ባካባቢው መንገዶች አርማ የሌለው ባንዴራ እየተውለበለበባቸውና የቀን ጅብ የሚል ስያሜም እየተወረወረባቸው በሰቀቀንና በስጋት አካባቢውን እየለቀቁ መሄዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መረጃ ቢደርሳቸው ምን ስሜት ሊኖራቸው እንደሚችል ለማወቅ ቢቻል መልካም ነበር፡፡ ይህ ስያሜ በየትም ቦታ ሲነሳ ባሁኑ ጊዜ ስያሜው ማንን ለመጥቀስ ተፈልጎ እንደሚነሳ ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ካንድ ያገር መሪ እንደዋዛ ተወርውሮ ያንድ ኩሩና ጠንካራ ሕዝብ መለያ እንዲሆን የተደረገበት አካሄድ ሲሰላሰል የዚህ ዓይነቱ አካሄድ አገርን የሚጠቅም አለመሆኑን በመጥቀስ ብቻ ብናልፈው በቂ ነው፡፡

3.2.     የሙስና ጉዳይ፡

የኢሕአዴግ መንግስት አልተሳካለትም እንጂ ሙስናን እዋጋለሁ! ብሎ መፎከር ከጀመረ ከአስር ዓመት በላይ ይሆነዋል፡፡ በኢሕአዴግ ቤት ሙስና የሚዋጋው ላንድ ሳምንት ቢበዛም ላንድ ወር ብቻ ነው፡፡ በሙስና ሳምንቱ ወይም ወሩ በሚድያ ሁሉም ይለፈልፍና የሚያዘውና የማይያዘውንም ወደ እስር ቤት ወርውሮ ሙስናን እንደተዋጋ ተመስሎ ይቀርባል፡፡ ይህ ቅጥ ያጣና ምናልባት አንዳንዴም የፖለቲካ ወይም የጥቅም መበቀያ ሆኖ ሲሰራበት የቆየው የፀረ-ሙስና አካሄድ ለኢሕአዴግ መንግስት ብዙም የረባ ውጤት እንዳላስገኘለት በሂደት ስናይ መጥተናል፡፡ በርካታ ባለስልጠናት በሙስና ታስረውና በሚዲያ ብዙ አዋራጅ ስም ተሰጥቶዋቸው በእስር ቤት ለበርካታ ዓመታት ከከረሙ በኃላ አብዛኞቹ በነጻ ሲወጡ አይተናል፡፡ በርካታ ነጋዴዎች ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ከነቤተሰቦቻቸው በሚዲያ እንዲዋረዱና ንብረታቸው ታግዶ እንዳይንቀሳቀሱ ከተደረጉ በኃላ ምንም የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለ በፍርድ ቤት ተረጋግጦ ከበርካታ የእስር ዓመታት በኃላ በነጻ ሲወጡ አይተናል፡፡

ነገር ግን አንድ እርግጠኛ ሆነን የምንነጋገርበት ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያ ውስጥ የሙስና ድርጊት ስር የሰደደና በየትኛውም የስራ ዘርፍ ተንሰራፍቶ የከረመና አሁንም ገና ከስሩ ያልተመነገለ ድርጊት መሆኑን ግን ያደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ከሰሞኑን የሜቴክ ሙስና አገር ፈረሰ፡ አገር ተናደ፡ አገር ጠፋ ወዘተ እየተባልን ነው፡፡ ምናልባት የሜቴኩ ጉዳይ በአጀንዳ መልክ ከፊት ከመገኘቱ ጋር በተያያዘ አገር እንደፈረሰ ተደርጎ እየቀረበልን ይገኛል እንጂ ሙስና መረቡን ዘርግቶ በየመስሪያ ቤቱ በፌዴራልም ይሁን በክልል መስሪያ ቤቶችና የአስተዳደር እርከኖች በየጓዳው ጎድጓዳው የተንሰራፋ ስለመሆኑ ያደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ ከሰሞኑን በኤል ቲቪ ውይይት ላይ ቀርበው የነበሩት የቀድሞው የጂቡቲ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በወደቡ አካባቢ ብቻ ያስተዋሉትን አንዳንድ ክስተቶች ሲጠቁሙን እንደሰማነው፡ በመንግስት ገንዘብ ከውጭ አገር ስኳር ተገዝተዋል ተብሎ ከህንድ አገር 10ሺሕ ኩንታል አሸዋ በወደቡ ላይ እንዳዩ፡ ማዳበሪያ ተብሎ የተገዛው ዕቃ ይቅርና ለማዳበሪያነት ሊጠቅም ለማስወገዱም ተጨማሪ ወጪ የወጣበት ንብረት እንደተመለከቱ፡ በቴሌ፡ በመብራት ኃይል፡ በዕቃ ግዢ ኤጄንሲ፡ ወዘተ የሚገዙት ንብረቶች ገዢዎቹ ተወካዮች ወይም ኃላፊዎች በሄዱበት አገር ባለሰባት ኮከብ ሆቴል እየተያዘላቸው በፖስታ ታሽጎ ኮሚሽን እየተቀበሉ የተገዛው ንብረት ሳያዩና ሳያጣሩ ውጭ አገር የሚመላለሱ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ሌላም መናገርና መጠቆም ይቻላል፡፡ የተባላሸ፡ ጥራት የጎደለው፡ ጠቀሜታ የሌለው ንብረት ወዘተ እንደተገዛና ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ሁሌም ይነገራል፡ ተጠያቂ ተፈልጎ ሲቀጣ ግን አይታይም፡፡

የሜቴክ ጉዳይም ብዙ ሀብት እየፈሰሰ ነው፡ ሜቴክ ግዴታውን በእቅዱ መሰረት አልተወጣም፡ የበጀት ብክነት ይታይበታል፡ ወዘተ የሚሉ ቅሬታዎች፡ ስሞታዎችና ሪፖርቶች ለተወካዮች ምክር ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ይቀርቡ እንደነበር መስማት ከጀመርን አራትና አምስት ዓመታት ይሆናል፡፡ ይህ ድርጅት ከፍተኛ ሀብት ሲያባክን፡ ከፍተኛ በጀት ሲወጣበት፡ የጀመራቸው የስኳርና የማዳበሪያ ፕሮጀክቶች በእቅዳቸውና በተወሰነላቸው ጊዜ ሳይፈጸሙ ሲቀሩ ተገቢውን እርምጃና ማስተካከያ ማድረግ ሲገባ በሚመለከተው አካል ዝምታ በመመረጡ፡ በአመራር ቦርዱና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሎም ጉዳዩን በሚከታተለው የመንግስት ልማት ድርጅትና የተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ኮሚቴ እርምጃና ማስተካከያ ማድረግ ሲገባ ኃላፊነት በጎደለው አካሄድ በዝምታና በቸልታ ማለፋቸው ለከፍተኛ የሕዝብ ሀብትና የገንዘብ ብክነት ሊዳረግ ችሏል፡፡ ስለሆነም የሜቴክ ኃላፊዎች ተጠያቂነት ሲቀጥል ሌሎች ከላይ የተዘረዘሩት የመንግስት በአካላትና ኃላፊዎችም ከተጠያቂነት ነጻ የሚሆኑበት አግባብ የለም፡፡

ጉዳዩ ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ከሆነና መጠየቅ ያለባቸው አካላትና ኃላፊዎች ሳይጠየቁ ቀርተው ሌላው ውሱን አካልና ቡድን ብቻ ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ የሚካሄድ የፍርድ ሂደት ከሆነ ግን የፍትሕ ውጤቱ ከፊሉን ፀጉር ላጭቶ ከፊሉን መተው ስለሚሆን ፍትሕ መሆኑ ይቀርና ለፍትሕ ስርዓቱ መሳለቂያና መዛበቻ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በስተመጨረሻውም የፍትሕ አዙሪቱ ጤፍ ከሰጠው ምላስ የሰጠው ይበልጣል! የሚለውን ብሂላዊ አነጋገር ባለምላሶች አሸናፊ፡ ምላስ የለሾች ተሸናፊ ይሆኑና ሚዛናዊነቱ የተጓደለ ሆኖ ይጠናቀቃል፡፡

ቸር ይግጠመን!

Back to Front Page