Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጭፍን ድጋፍም ይሁን ጭፍን ተቃውሞ ሁለቱም አጥፊ መንገዶች ናቸው

ጭፍን ድጋፍም ይሁን ጭፍን ተቃውሞ ሁለቱም አጥፊ መንገዶች ናቸው

ከእውነቱ ይታያል 10-03-18

Videos From Around The World

ማንኛውም ሰው የፈለገውን ሃሳብም ሆነ ተግባር የመደገፍ ካልሆነም የመቃወም (በህግ የተከለከለ እስካልሆነ ድረስ) መብት አለው። ቢፈልግ ቅዱሳንን ካልፈለገ ደግሞ ሃጥዓንን የመደገፍ ብቻም ሳይሆን የማምለክ ወይም የመቃወም መብቱ ተፈጥሯዊ ነው። በዚህ እሳቤም የትኛውም ሰው የፈለገውን አካል ሃሳብ የማወደስ ሳይፈልግ ሲቀር ደግሞ የመንቀፍ ፍላጎቱን እውን ማድረግ ይችላል። ትልቁ ቁም ነገር ይህ ድጋፍና ተቃውሞ በጎ ተፅእኖ ሊፈጥር የሚችለው በምን ሁኔታ ሲቸር ነው የሚለው ጥያቄ ነው። መልሱን ባጭሩ ለመግለፅ ከጭፍንነት በፀዳ መንገድ የተቸረ ድጋፍና ተቃውሞ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ነገሮችን ከማንሳቴ በፊት ስለጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ምንንነት የተወሰነ ለማለት ወደድኩ።

ጭፍን ድጋፍም ይሁን ጭፍን ተቃውሞ የሚነሱት እንደጎርፍ ከሚንዶለዶል ስሜት ነው። በዚህ አይነት ስሜት የሚነዱ ሰዎች ምንጊዜም የሚያዩት ሃሳብን፣ ርዕዮት-ዓለምን፣ የማስፈፀም ብቃትን ወይም ክህሎትን አይደለም። የድጋፋቸውም ይሁን የተቃውሟቸው ማጠንጠኛ ሃሳብ ሳይሆን ሃሳቡ የመጣው እነሱ ከሚደግፉት/ከሚቃወሙት ሰው ወይም አካል ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው። ይህን የሚደግፉትን/የሚቃወሙትን ሰው ወይም አካል የሚለኩባቸው መመዘኛዎች ደግሞ ዘር/ብሄር፣ ቋንቋ፣ ተክለ ሰውነት፣ ጎጥ፣ መንደር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ወግ፣ ልምድ እና ሌሎችም የሰው ባህሪያት ሊሆኑ ይችላሉ። ባጠቃላይም በስሜት የሚነዳ ሰው   የሚደግፈውም ይሁን የሚቃወመው በራሱ አእምሮ አገናዝቦ፣ አውጥቶና አውርዶ ሳይሆን ሃሳቡን/ድርጊቱን ያነሳውና የሰራው ማነው የሚለውን ሰምቶ ወይም አይቶ ነው። በሌላ አነጋገር የዚህ አይነት ሰዎች የሚቀላቸው እንደመንጋ መንጎድ ነው። በስሜትና በመንጋ የመንጎድ ዝንባሌና ባህሪ በግልፅ የሚያሳየው ደግሞ ሰው በተፈጥሮ የተቸረውን የማመዛዘኛ አእምሮ በሚገባ ሊጠቀምበት አለመፈለጉን ነው። ይህ ደግሞ እዛው ሳለ በራስ አለመቆምንና ለራስም ክብር ማጣትን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። 

ከላይ ከተቀመጡት ቁምነገሮች አንፃር ሲታይ አንድ በጭፍን የሚደግፍ ሰው የተፈፀመው ድርጊት የቱንም ያህል አስከፊ ገፅታ ቢኖረው ምክንያት አፈላልጎ ከመደገፍ ወደኋላ የማይል መሆኑን ነው። ጭፍን ደጋፊ የሆነ ሰው የሚደግፈው ተራ ጥፋትን ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ከባድ የሆነን ወንጀል ሳይቀር ሊሆን ይችላል። በዚህ ረገድ ፕሬዚደንት ትራምፕ ምርጫ ውድድር ላይ በነበሩበት ወቅት ጭፍን ደጋፊዎች እንዳሏቸው ለመግለፅ እንዲህ ብለው ነበር “I could stand in the middle of 5th Avenue and shoot somebody and I wouldn’t lose voters.”  ይህ የትራምፕ አባባል ወደ አማርኛ ሲተረጎም "አምስተኛ ጎዳና መሃል ላይ ሆኘ ሰው ላይ ብተኩስ ድምፅ የሚሰጡኝ መራጮቸ እኔን ከመምረጥ ወደኋላ አይሉም" የሚል ነው። ይህ የሚያሳየን ጭፍን ድጋፍ ምን ያህል አደገኛና አጥፊ እንደሆነ ነው። ከዚሁ ተያይዞም / መላና ትራምፕ በባለቤታቸው በዓለ ሲመት ላይ ያደረጉት ንግግር ከፕሬዚደንት ኦባማ ባለቤት ከሆኑት / ሚሸል ኦባማ ኮርጀው ነው የሚል በማስረጃ የተደገፈ ክስ ሲቀርብ ድርጊቱን አውግዞ ከመቆም ይልቅ እነዚሁ የትራምፕ "ጭፍን ደጋፊዎች" ክሱን ለማጣጣል ለመካድ ያልፈነቀሉት ደንጋይና ያላቀረቡት ምክንያት እንዳልነበረ ሰምተናል፤ አንብበናልም።ዌሊንግተን ኢንተርፕራይዝ የሚል ምንጭ ፈልገው ያንብቡ። 

በጭፍን የሚቃወ ሰውም እንዲሁ የሚቃወመው ሰው/አካል ያፈለቀውን ሃሳብ ወይም ስራ ማጣጣሉ አይቀርም። በጭፍን የሚቃወም ሰው ልክ እንደጭፍን ደጋፊ ሁሉ ተቃውሞውን የሚያቀርበው የሃሳቡን ምንነት ተገንዝቦና አውቆ ሳይሆን እሱ የሚቃወመው ሰው ወይም አካል የሰራው በመሆኑ ብቻ ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች የሆነ ያልሆነ ምክንያት በመደርደር ሊሰራ የታሰበው ስራ እንዳይከናወን ወይም የተሰራው ስራ እንዲቀለበስ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የፈለቀው ሃሳብ ወይም የተሰራው ስራ በማንኛውም መመዘኛ የተሟላ እያለም ጭምር ነው።   

ኢትዮጵያ ውስጥ ስንመጣም በጭፍን የመደገፍም ይሁን የመቃወም ዝንባሌዎች በስፋት አሉ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ብዙዎቻችን ኢህአዴግን ወይም መንግስትን የምንደግፈው መልካም ነገር ሲሰራ ብቻ ሳይሆን መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ሲፈፅምም ነው። ኢህአዴግን ወይም መንግስትን የምንቃወም ከሆነ ደግሞ የሚታየን መልካም ነገር ሳይሆን መልካም ያልሆነው ብቻ ነው። ተቃዋሚዎችን ስንደግፍም ሆነ ስንቃወም በዚሁ ስሌት ነው። ለምሳሌ / አብይ ጥሩ ነገሮችን ሲሰሩ የተሰሩትን ስራዎች ደግፈው የቆሙ በርካታ ኢትዮጵያን አሉ። በዚህ መንገድ የተሰጠ ድጋፍ ምክንያታዊ እንጅ በፍፁም ጭፍን ሊሆን አይችልም። በሌላ መንገድ ግን / አብይ የህገመንግስት ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ተግባራትን ሲፈፅሙም እነዚህ ደጋፊዎች ህገመንግስታዊ ጥሰቶችን "ሆሆሆሆሆሆ" ብለው በጭፍን ደግፈዋል። በሌላ ወገን ደግሞ / አብይ ጥሩ እየሰሩ እያለም ቢሆን አሁንም "ሆሆሆ" ብለው የሚሰራውን በጎ ስራ የሚቃወሙ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።  

ጭፍን ድጋፍን በተመለከተ አንድ በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ የተፈፀመን ጉዳይ አንስቸ የችግሩን ክብደት ላሳይ። እንደሚታወቀው ቡራዩ ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋና መፈናቀል ተከትሎ ቡራዩ ላይም ሆነ አዲስ አበባ ላይ በርካታ ሰዎች እንደታሰሩ በተለያዩ መንገዶች ሰምተናል። ቡራዩ ውስጥ የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ብንሰማም ሰዎች እየታፈሱ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንደገቡ የተዘገበ ነገር አልሰማንም። አዲስ አበባ ላይ ደግሞ በተቃራኒው ወጣቶች እየታፈሱ ለፀባይ ማረሚያ ስልጠና ጦላይ ወታደራዊ ካምፕ እንደገቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በልበ ሙልነት ገልፀዋል። ይህ አሰራር በየትኛውም የህግ መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አይደለም። በኢትዮጵያ ህግ ማንኛውም ሰው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካልታወጀ በስተቀር የእስር፣ የእገታ፣ የማህበራዊ ግልጋሎት ብሎም የፀባይ ማረምያ ስልጠናና የመሳሰሉ ቅጣቶች እንዲሁም የእርምት እርምጃዎች ሊወሰኑ የሚችሉት በፍርድ ቤትና በፍርድ ቤት ብቻ ነው። በዚህ ሂደት ፖሊስ የተሰጠው አንዱ ስልጣን የፍርድ ቤት ትእዛዝ በማውጣት እስር መፈፀምና 48 ሰዓታት ውስጥ የወንጀል ሁኔታውን አጣርቶ ፍርድ ቤት ማቅረብ ነው። ሌላው የፖሊስ ህጋዊ ስልጣን የፍርድ ቤት ትእዛዝ ባይኖረውም ወንጀል ለመከላከል አስፈላጊ ነው ብሎ በተጠራጠረበት ወቅት ተጠርጣሪውን ማሰር ነው። ፖሊስ በዚህ ሁኔታ ያሰረውን ተጠርጣሪ አሁንም 48 ሰአት ውስጥ ፍርድ ቤት ማቅረብ ግዴታ አለበት። ከዚህ ውጭ ፖሊስ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ካልሆነ በስተቀር ሰውን 48 ሰዓት በላይ ለሆነ ጊዜ የፀባይ ማረሚያ ስልጠና እሰጣለሁ ብሎ መንቀሳቀስ ህግመንግስታዊዉን የሰዎች በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ከመጣሱም አልፎ አጉራ ዘለልነቱን በግልፅ ያሳየበት ድርጊት ነው።

ይህን ጉዳይ እዚህ ላይ ያነሳሁት ፖሊስ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የፈፀመውን በጅምላ የማጎርና ብሎም የፀባይ ማረሚያ ስልጠና እሰጣለሁ የሚል እንቅስቃሴ በራሱ ህገመንግስታዊ አይደለም ብየ ለመከራከር ሳይሆን ይህን ህገመንግስት የጣሰ ድርጊት በርካታ ሰዎች በጭፍን እየደገፉ ያሉ መሆናቸውን ለማሳየት ነው። በዚህም መሰረት እጎራው ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ እስካሁ ድረስ በዶ/ አብይ አስተዳደር የሚመራው የአዲስ አበባ ፖሊስ የሄደበት መንገድ ትክክል ነው ብለው የሚጮሁ ጭፍን የመገናኛ ብዙሃን አካላትና የፌስቡክ ሰራዊት አባላት ቁጥር ቀላል አይደለም። አንዳንዶቹም ድርጊቱ ህገመንግስቱን የጣሰ መሆኑን ቢቀበሉም / አብይን በጭፍን ስለሚደግፉ ብቻ ይሄው ህገመንግስታዊ ጥሰት በለውጥ ሂደት የተፈፀመ ስለሆነ ተቃውሞ ሊገጥመው አይገባም ብለው ይከራከራሉ። እነዚህ ጭፍን የሆኑ ደጋፊዎች ያልተረዱት ግን አሁን / አብይ እየመሩት ያለው አስተዳደር ወደስልጣን የመጣው ህግና ህገመንግስት አልተከበረም በሚል ሽፋን የነበረ መሆኑን ነው።  ሌላው ያልተረዱት ነገር ደግሞ ሕግና ህገመንግስት አልተከበሩም ብሎ ለለውጥ የተነሳ ነው የሚባለው ይሄው ሃይል ራሱ ሲጥሳቸው ግፋበት ብሎ ጭፍን ድጋፍ መስጠት አምባገነንነትን የሚያደልብ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ነው።

ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ተለውጠናል እያሉ እያደነቁሩን ያሉት የድሮ ስርዓት ወቃሽ የሆኑት አብዛኞቹ የኢትዮጵያ መንግስት የሚዲያ አካላት ጉዳይ ነው። እነዚህ የሚዲያ አካላት አሁንም የህዝብ መሆናቸውን ዘንግተው በዶ/ አብይ የሚመራው የአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የወሰደው የጅምላ ማጎርና ስልጠና የመስጠት እንቅስቃሴ ትክክል መሆን አለመሆኑን ባለሙያዎችን አነጋግረው ዘገባ ማቅረብ ሲገባቸው ዝምታን መርጠዋል። እንዲህ አይነቱ ዝምታ ደግሞ ከአድርባይነት፣ ሙያዊ ስነምግባርን ቅርጥፍ አድርጎ ከመብላት፣ ህሊናን ከመሸጥና ጭፍን ድጋፍ ከመስጠት የዘለለ እንደምታ አይኖረውም። ይህ በሙያ ስነምግባር አለመገዛት ባህሪያቸው በዚህ ክስተት ብቻ ሳይሆን በሌሎች እንቅስቃሴዎቻቸውም ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ይህንን ብዛት ያላቸውን የኢትዮጵያ መንግስት የሚዲያ አካላት ለሙያ ስነምግባር አለመገዛት፣  አላማ ቢስነትና ለህዝብ ያለመወገን ድርጊት የታዘበው የአሶሽዬትድ ፕሬስ (Associated Press) ዘጋቢ ኢሊያስ መሰረት ትዝብቱን በፌስቡክ ገፁ ላይ  በሚከተለው መንገድ ነበር ያስቀመጠው፡

“(አብዛኞቹ) የመንግስት ሚድያዎች ሰው ሲሞት እና ሲሰደድ ዝም ብለው ነገሩ የተረጋጋ ሲመስላቸው "የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው" እና "የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ጎበኙ" የሚሉት ዘገባቸው ይገርማል። ብጥብጥ እንዳይባባስ በመስጋት ወይስ ለመንግስት ዘብ የቆሙ መስሏቸው? ይህን መሰል ዘገባዎች በግል እና ውጪ ሚድያዎች ቢኖርም በመንግስት የዜና አውታሮች ግን ይብሳል። 

በነገራችን ላይ ይህ የፖሊስ እንቅስቃሴ ህጋዊ የመሆኑንና ያለመሆኑን ጉዳይ በተመለከተ ከነዚህ በድሮው ስርዓት ላይ አንበሳ ነን እያሉ ያዙን ልቀቁን ከሚሉ የመንግስት የሚዲያ አካላት ይልቅ የውጭዎቹ ሚዲያዎች በተለይም የቢቢሲ (BBC) የአማርኛ ዘጋቢዎች እያከናወኑት ያለው ተግባር ምስጋና ሊቸረው የሚገባ መሆኑን ለመግለፅ እፈልጋለሁ።

ሌላም ምሳሌ ልጨምር። ሁላችንም እንደምናቀው ሰኔ 16 ቀን 2010 . በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተፈፅሞ ለነበረው ጥቃት / አብይ ጣታቸውን አንድ ቡድን ላይ ሲቀስሩ ደጋፊ ጭፍን መንጋቸውም "ግርርርርርርርርር፣" ብሎ እሳቸውን በመደገፍ ጣቱን በህወሃት ዙሪያ ያሉ ሰዎች ላይ ቀሰረ። ይሁንና አቃቤ ህግ ከሳምንት በፊት በተጠርጣሪ አሸባሪዎቹ ላይ ያደረገው ክስ በህወሃት ዙሪያ ያሉ ሰዎችን የሚነካ ሆኖ አልተገኝም። ይህ ሆኖ እያለም ሁኔታውን በተመለከተ / አብይ አንዳችም ነገር አላሉም። በመሆኑም ጭፍን ደጋፊ የሆነው መንጋ አሁንም ጣቱን ከቀሰረበት አካል ላይ ያነሳ አይመስልም። በዚህ ወቅት የጠቅላይ አቃቤ ህግ ቃል አቀባይ የሆኑት  አቶ ታየ ደንደአ በበኩላቸው ጭፍን የሆነው ደጋፊ ጣቱን ከቀሰረበት አካል ላይ እንዳያነሳ የማሳሰብና የማበረታታት እንደምታ ያለው መልእክት በፌስቡካቸው ገፅ ላይ ለጥፈው የነበረ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ነው።   በቅርቡ ደግሞ በዶ/ አብይ የቅርብ ሰው የሚመራው ጠቅላይ አቃቢ ህግ ጥቃቱን ያቀናበሩትንና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን መለየቱንና መግለጫም በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚሰጥ አስታውቋል። ይህ የአቀናባሪዎችና የገንዘብ ድጋፍ አድራጊዎች ማንነት ደግሞ / አብይ አሜሪካ በነበሩበት ወቅት ከሰዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ከሰጡት መልስ ተመሳሳይ ነው። ከዚህ ስንነሳ መረዳት የሚቻለው ዋናው ፍላጎት በተጨባጭ በድርጊቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን የመለየትና ለህግ የማቅረብ ሳይሆን የተደበቀ የፖለቲካ አጀንዳ ለመፈፀም መደላድል መፍጠርን ይመስላል። በመሆኑም በሚቀጥለው ሳምንት የሚሰጠው የአቃቢ ህግ መግለጫ ድሮውንም ቢሆን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ተበይኖ ጣት በተቀሰረባቸው አካላት ላይ ላይሆን እንደሚችል እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ይህ ሁሉ የሚያሳየው በጭፍን ደጋፊ የተከበበ ሰውም ይሁን አካል በፍርድ ቤት  ሳይረጋገጥ እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር (Presumption of Innocence) የሚለውን የህግ መርህ ይቅርና የፈጣሪን ቃልን ጥሶም ቢሆን  ያሻውን ከማድረግ የሚከለክለው አንዳችም ነገር እንደሌለ አድርጎ የሚቆጥር መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው ሌላው የጭፍንነት አስከፊ ገፅታ ደግሞ ጭፍን ተቃውሞንና ጭፍን ድጋፍን የሚቃወሙ ቅን፣ ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊና ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችን ጭምር የሚበላ አረመኔያዊ የሰዎች ባህሪ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ አቶ ልደቱ አያሌው ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደሚታወቀው አቶ ልደቱ የተቀዋሚ ፓርቲ መሪ ሆነው ለረጅም አመታት ሰርተዋል። በነዚህ ጊዚያት አቶ ልደቱ የኢህአዴግን ጥፋቶች ያለምንም መደራደርና ርህራሄ እያብጠረጠሩ እያወጡ በአደባባይ አሳይተዋል። በአንፃሩ ኢህአዴግ ጥሩ ሰርቷል ብለው ባመኑብቸው ሁኔታዎች ላይ ደግሞ ግልፅ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። ይህ የአቶ ልደቱ አካሄድ በአለም ላይ አሉ ከሚባሉ ስልጡን የፖለቲካ ሂደቶች የሚመደብ ነው ብሎ መናገር አያሳፍርም። ይሁንና የአቶ ልደቱ ምክንያታዊ አካሄድ ያስከፋቸው ጭፍን ተቀዋሚዎች ረቂቅ በሆነ መንገድ በመዶለት አቶ ልደቱ  ለጊዜውም ቢሆን ከፖለቲካ እንዲርቁ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ለኔ የአቶ ልደቱ አያሌው ለጊዜውም ቢሆን ከፖለቲካ የመራቅ ውሳኔ የሚያሳየኝ ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሚዛናዊ የሆነ ፖለቲካ እንዳይፈጠር እያሳደሩት ያለውን እጂግ በጣም ከፍተኛ የሆነ አደገኛና አጥፊ ተፅእኖ ነው።

በአጠቃላይ ጭፍን ድጋፎችና ተቃውሞዎች ምክንያታዊ ያልሆኑና በስሜት የሚነዱ ዝንባሌዎች ናቸው።  የሚመሩትም በሚያመዛዝን አእምሮ ሳይሆን ልቅ በሆነ የመንጋ (Herd/Mob) ህግ ነው። መነሻቸው ሃሳብ ሳይሆን ተክለ ሰውነት፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጎጥ፣ ዝምድናና የመሳሰሉት ጉድዮች ናቸው። ይህም ማለት ጭፍን ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች  የሚነጉዱት ማን አነሳውና ከየት ተነሳ ብለው እንጅ የተነሳው ሃሳብ ወይም የተሰራው ስራ መጥፎ ወይም ጥሩ መሆንና አለመሆኑን አመዛዝነው አይደለም። ይህን አይነት መንገድ መከተል ደግሞ እጂግ በጣም ሲበዛ ክብረ ነክ ነው። ባጭሩ ጭፍንነት ክብረነክ ከመሆን አልፎ  ደጋፊውንም፣ ተደጋፊውንም፣ ተቃዋሚውንም ሆነ ተቃውሞው የሚዝንብበትን አካል በጥቅሉም አገርንና ህዝብን የሚያመሳቅል አጥፊ መንገድ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። 

 

በተረፈ በሚቀጥለው ጊዜ "የኢህአዴግ ጥምረትና የነቃ ብርሌ" የሚል ፅሁፍ የዤ ብቅ እንደምል እየገለፅኩ መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

 

ቸር እንሰንብት!

 

Back to Front Page