Back to Front Page


Share This Article!
Share
የዋሻው እስረኞች

የዋሻው እስረኞች

በዳናይት

09-01-18

1 የጓሮው ዘንዶ

ልጅነት ተመልሶ አይመጣም፡፡ አንዳንዴ ግን ትዝታው ይመላለስብሃል፡፡የልጅነት ትዝታዎቼ ውብም-አስቀያሚም ናቸው፡፡እንደያኔው ዘመን እኩዮቼ ትምህርት በፊደል ቆጠራ አልጀመርኩም፡፡ አእምሮዬን ያማሟቁኩት በፊደል ገበታ ሳይሆን በዋሻ ቆጠራ ነበር፡፡

ልጅነቴ ውብ አጋጣሚዎች ነበሩት፡፡ ዲያቆን ወይም ባህታዊ ሳልሆን ብዙ የዋሻ አብያተክርስትያናትን አይቻለሁ፡፡ ቱሪስት ሳልሆን በነፃ ጎብኝቻቸዋለሁ ፡፡ገና ከእናቴ ማህፀን እንደወጣሁ ጉብኝቴ አሀዱ ብዬ ጀመርኩኝ፡፡ክርስትና የተነሳሁት በአንዱ የዋሻ ቤተክርስተትያን ነበር-አሉኝ፡፡ ከዛም ምኑ ቀረኝ- ጠዋትና ማታ ውሎዬን በየዋሻው ሆነ፡፡

የውቅር ዋሻ አብያተክርስትያናት አሰራር አስፈሪም-ተኣምራዊ ነው፡፡ ኪነ-ህንፃዊ አሰራራቸው ውብም-ማራኪ ነው፡፡

..እንግዲህ ወደማይጠፋውና ሁሌ ወደሚመላለሰው የልጅነት ትውስታዬ ልመለስ፡፡የልጅነት ሰፈሬና መንደሬ ያለማጋነን ገነትን ትመስላለች፡፡ በእድሜ ጠገብ ዛፎችና ደኖች የተዋበች፡፡ በአራቱ ማዕዘናት ዓመቱ ሙሉ በሚፈሱ ወንዞች የተከበበች፡፡ ደኖቹ እድሜ ጠገብና ሌላ አከባቢ እምብዛ የማይገኙ፣ልምላሜዋና መኣዛዋ የሚያውድ ሰማያዊት ኤዶምን ተመስላ ምድር ላይ የተከሰተች ገነትን ትመስላለች፡፡ በጣት በሚቆጠሩ ኪሎሜትሮች ርቀት ቢያንስ አንድ ውቕር የዋሻ ቤተክርስቲያን ማይት ይችላል፡፡ በስተሰሜን ሚካኤል ባርካ፣ በስተደቡብ ሚካኤል ሞሮሮ፣ በስተምዕራብ ሚካኤል አምባ እንዲሁም በስተምስራቅ የሚካኤል ምፅዋዕን ማግኘትና ማየት ይቻላል፡፡እነዚህ በግልፅ የሚታዩ ሲሆኑ በማሃል ግን ብዙ ስውር ዋሻዎች አሉ ተብለው ይታመናሉ- በአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ፡፡

Videos From Around The World

ከዋሻው ውቅር አብያተክርስቲያን ውጪ መንደራችን ብዛት ባላቸው ህልውና የጠፋ አብያተክርስትያናትም ትታወቃለች ፡፡ የደኑ ብዛትና የቤተክርስትኑ ብዛት ተመሳሳይ ነው፡፡

መንደራችን በተራሮች የተከበበች ስፍራም ናት፡፡ ተራሮቹ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈኑ ናቸው፡፡የሰፈራችን ደኖች የሚመስል ስፍራ ኢትዮጲያ ውስጥ ያየሁት ባሌ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

መንደራችን ለምለም ብቻ አደለችም፡፡ በማዕድንም የበለፀገች ናት፡፡የከበረ ድንጋዮችም በብዛት ይገኙባታል፡፡ ታዲያ ቤታችን በጫካው መሃል ከሁሉም አቅጣጫ የምትታይ ጉበታ ነበረች፡፡ ቤተክርስትያን ባትሆንም ቆርቆሮ ደርባለች፡፡

አሁን አሁን ሳስበው ግን ሰፈራችን ከዋሻዎች በላይ በውስጧ ሌላ ዋሻ እንዳላት ነው፡፡ሩቅ ሳልሄድ ቤታችን ራሱ የቻለ ዋሻ ነው-ያውም የታሪክ ዋሻ!!

ከቦታው አቀማመጥ አንፃር አይቼ ወላጅ አባቴ ይህንን ስፍራ ለመኖሪያ መምረጡ ብልህ ሰው ነበር ማለት ነው ስል ነበር- ለዓመታት፡፡ ግን ደግሞ ስህተት ነበር፡፡ ለካስ ይህች ውብ መንደር ስፍራ አባቴ አልነበረም የቀየሳት፡፡

ያዕቆብ የሚባል ታዋቂና ጀግና ሰው ነበር፡፡ ጥቁር ይሁን ቀይ፤ ወፍራም ይሁን ቀጭን ግን አልታወቀም፡፡ጀግንነቱና ነገር አዋቂነቱ ግን አጠያያቂ አይደለም፡፡.ታዲያ ይህ ሰው ከእለታት አንድ ቀን በሆነ ጉዳይ እግሩ ይጥለዋል- ወደ ገነት መሳያዋ ስፍራ፡፡ በተፈጥሮአዊ አቀማመጥዋና በውበትዋ ይማረካል፡፡ ግራ ቀኙን ያያል፡፡ ይደመማል፡፡በመልከዓምድራዊ /በጂኦግራፊያዊ/ አቀማመጥዋና በወታደሪዊ ጠቀሜታዋ ይሁን በልምላሜዋ ተማርኮ ይሁን አይሁን ድንኳኑን ጣለባት፡፡ ትዳርም መሰረተባት፡፡ልጅም የልጅ ልጅም አየባት፡፡በፊናዋም ለወግ ለመዓረግ አደረሰችሁ፡፡ በስተመጨረሻ የሹም መዓርግም አገኘባት፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሰፈራችን ዓዲሹም ያዕቆብ ተባለች፡፡ የሹም ያዕቆብ ሀገር እንደማለት ነው፡፡ ጊዜው ቅርብ አይደለም-ሰ በአስራአራተኛው ክፍለዘመን ነው፡፡

ከሹም ያዕቆብ በኋላ ታዲያ ሌሎችም አደመቋት፡፡ገሚሶቹ ተወለዱባት፡፡ገሚሱ አስተሳሰቡ አስፋፋባት፣ ገሚሱ ድንኳኑን ለጊዜውም ቢሆን ጣለባት ሌላው ታሪኳን ዘገበላት፣ ገሚሱ ታገለላት፣ ገሚሱ ተሰዋላት ወዘተ..

ታላቁ የሃይማኖት መሪ አቡነ ሳሙኤል ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት እዚሁ መንደር ተወለደ፡፡ ሽሬ አከባቢ በሚገኘው የቆየፃ ተራራ አናት ላይ መንኖና መንኩሶ ብዙ ተከታዮችን አፈራ፡፡ ሃይማኖታዊ ትምህርቱም ዕፁብ ድንቅ ተባለ፡፡ ከሁሉም የኢትዮጲያ አከባቢዎች እሱ ዘንድ ለመማር ጎረፉ፡፡

ከአባ ሳሙኤል ተማሪዎች አንዱ አባ እስጢፋኖስ ነበር፡፡አባ እስጢፋኖስ በአባ ሳሙኤል ዘንድ ተምሮና መንኩሶ ግን ደግሞ የተለየና አዲስ አስተሳሰብን ያራመደ አባት ነበር፡፡ አባ እስጢፋኖስ ብዙ ተከታዮችም አገኘ፡፡የሱ ተከታዮችም ደቂቀ እስጢፋኖስ ይባላሉ፡፡ የደቂቀ እስጢፋኖስ አዲስ አስተሳሰብ ግን አልጋ በ አልጋ አልነበረም፡፡ አስተሳሰቡ ከሁሉም በላይ ለነገስታቱ ፈተና ነበር፡፡አፄ ዘርአያዕቆብም ደቂቀ እስጢፋኖስውያንን ለማጥፋት ተከታታይ ጥቃትና ዘመቻ ከፈተባቸው ፡፡

ደቂቀ እስጢፋኖስ ከሽረ እስከ ደብረብርሃን/ደብረኢባ/ ድረስ ከፍተኛ ተከታታይ ጥቃትና መከራ ቢደርስባቸውም በስፋት ደብቃ አስተሳሰባቸው እንዲስፋፉ ያደረጋቻቸው መንደራችን ነበረች- ዓዲ ሹም ያቆዕብ- ወንበርታ!!

የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች /ደቂቀ እስጢፋኖስ/ ብዙ አብያተክርስቲያናት ያሳነፁትና ተከታዮች ያፈሩት እዚሁ አከባቢ ነበር፡፡ ከታሪካዊው የጉንዳጉንዲ ማሪያም ባሻገር እነ አስራመቲራ ማርያም፣ዲቦ ማርያም፣ ሠረት ማርያምና ታፎይቶ ሚካኤል መገኛቸው ቤታችን አጠገብ ነው፡፡መገኛቸው ብቻ አይደለም-ብዙ ያልተነገሩና ያልወጡ የብራና መፃህፍትም በጉያቸው አቅበው እነሆ ለዛሬ ደርሳዋል፡፡

የዘመነ መሳፍንቱ አውራ ደጃዝማች ስባጋድስም ረጅም ጊዜ ሰፈራችን ውስጥ ድንኳኑን ጥሎ ሀገርን ሲያስተዳድር ነበር ይባላል፡፡ ምናልባትም ቤታችን ለአፋር ቅርብ ስለሆነች የጨው ቀረጥ የሚቀበልባት የያኔው የጉምሩክ ስፍራም ኖራ ልትሆን ትችላልች- በያን ዘመን፡፡

የስባጋድስና የወላጆቹ አስደናቂ አመጣጥ ወይም ሚይዝ (myth) የሚጀምረውም እዚሁ ስፍራ ነው፡፡መጨረሻው ደግሞ ኢሮብና አዲግራት አከባቢ ነው፡፡ የዘመነ መሳፍንቱ አውራ ስባጋድስ አንድ ታላቅ ገዳም- /የሥላሴ ደብር/ እዚሁ ሰፈር አሳንፆ አሻራውን አሳርፏል፡፡ቤተክርስትያኑ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ቤተመንግስቱ ግን ፈርሷል፡፡ደብዛውም ጠፍቷል፡፡ነበር -ነበር -አይ ነበር- የኛ ነገር!!

አፄ ዮውሃንስ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጲያ ሳይሆኑ በፊት በሽፍትነት ጊዚያቸው እዚሁ ሰፈር ተመላልሰዋል፡፡ድንኳናቸ ጥለውና ተክለው ተቀምጧል የሚል መረጃ ግን አልሰማሁም፡፡

የንጉሰ ነገስት ምንሊክ ቆይታ ግን ከነማስረጃው ነው፡፡ዳግማዊ ምንሊክ እዚሁ ሰፈር ድንኳናቸውን ተክለው ሰነባብትው ነበር፡፡እንዲያውም አየሩና አገሩ በጣም ወደውት ነበር ይባላል፡፡ይህ ነገር ለማጣፈጫ ብዬ የፈጠርኩት አይደለም፡፡የንጉሱ ፀሃፊና የቅርብ ሰው የነበሩ ደብተራ ፍሱሕ በብእራቸው ያስፈሩት ሓቅ እንጂ!!- ደብተራው ስለአከባቢውና ስለ ምንሊክ ጉዞና የስልጣን አመጣጥ ብዙ ነገር ፅፏል -ግን በትግርኛ ቋንቋ ነው፡፡ አፃፃፉ ግን ደስ ይላል፡፡

እኔ የሰማሁትን ልጨምር የያን ጊዜ የምንሊክ መድፍ ተኳሽ አልፍሬድ ኤልግም ቦታው ወዶት እነደነበረና ልዩ ፍቅር እንዳስያዘው ይነገራል፡፡ኤልግም አንድ ወቅት ወደ ንጉስ/ምንሊክ/ ጠጋ ብሎ ንጉስ ሆይ መኳንንቱ እንቀሳቀስ እያሉ ቢያስቸግሮትም ከዚህ ቦታ ንቅንቅ ማለት የለብንም-የለቦትም በማለት ንጉሱን ፈገግ አሰኝቷቸው ነበር ይባላል፡፡

ሰፈራችን በጣሊያን ወረራ ጊዜ ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል የተመታበት ስፍራም ነበር፡፡እንደነብላታ ኃይለማርያም ረዳ የመሳሰሉ አርበኞች በወራሪው ላይ ጣፋጭ ድል ያስመዘገቡበት የጦር ስፍራ ነበር-የፋጌና ጦርነት፡፡

ሰፈራችን ቀዳማይ ወያኔ የተፀነሰባትና የተስፋፋባት ስፍራም ነበረች፡፡አብዛኛዎቹ የቀዳማይ ወያኔ መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ተገኝቶባታል፡፡የፀረ ቀዳማይ ወያኔ አባላትም የዛን ያህሉ ከሰፈራችን ነበሩ- አይ መንደራችን!?

ከዚሁ የታሪክ ዋሻ የሆነው ሰፈር ሳልወጣ አንድ ነገር ልጨምር፡፡ ወያኔና ኢህአፓም ቦታው ይወዱት ነበር፡፡ በተለይ ለህወሓት ቦታውና መንደሩ ታሪካዊ ጭምርም ነው፡፡አብዛኛዎቹ የድርጅቱ መሪዎች ታግለውበታል፡፡ ለከፍተኛ ቦታም ደርሰውበታል፡፡

ህወሓት ገና እነደተመሰረተ አከባቢ ህላዌው በውጪ መንግስታት ዘንድ ለመታወቅ ይጥር ነበር፡፡ አንድ ጥሩ አጋጣሚም አገኘ፡፡ ከመቐለ ከተማ አንድ የውጪ ዜጋ በላንድሮቨር ለሽርሽር ይሁን ለስራ አገር አማን ነው ብሎ ወጣ ይላል፡፡ታዲያ ያኔ ተሓህት የሚባል ድርጅት ተፈጥሮ ነበርና በውጪ ሃገራትና መንግስታት ዘንድ እውቅና ለማግኘት ብሎ ፈረንጁን ጋማውን ይዞ አንዴ በእግሩ ሌላ ጊዜ በበቅሎ እያደረገ ወደዚህ ጫካ ያመጣዋል፡፡አዳሩንም ቤታችን ውስጥ ያደርገዋል፡፡ታጋቹም ብዙ ሳይጉላላ በጎረቤት ሀገር በኩል ይለቀቃል፡፡ተሓህትም እውቅናው በውጭ ሃገራት ዘንድ አሃዱ ብሎ ይጀምራል፡፡

አባቴም እንደ ታላቁ የሹም ያዕቆብ ያህል መንደራችንን ባይቆረቁሩትና ባያደምቃትም የራሱ የሆነ አሻራ ግን አሳርፎባታል፡፡

ከየትኛውም አከባቢ የሚታይ ህንፃ ሰርተዋል፡፡ከሰማይ ይሁን ከምድር ተለይታ የምትታይ ድንቅ ህንፃ በጫካዎች መሃል ገንብቷል፡፡የስራውንና የድካሙ ደግሞ አልከለከለችውም፡፡ ከዛች ጫካ አውጥታ አዲስ አበባ ያውም አራትኪሎ ወረወረችው፡፡ ለንጉሱ ፓርላማ አስመረጠችው፡፡የድሮ ስርዓት በተወገዘ ቁጥር በኢቲቪ/አቢሲ/ እንዲታይ አደረገችው፡፡ አባቴ በሞት ከተለየ ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም እድሜ ለቴክኖሎጂና ለመንደራችን ዛሬም ድረስ ህያው አደረገችው፡፡ በአካል የማያውቁት የልጅ ልጆቹም አቲቪ የድሮ ስርዓት ባሳየ ቁጥር አያቴ እያሉ ይመለከቱታል፡፡ ያስታውሱታል፡፡

አራትኪሎን ካነሳሁ አይቀር ሌላ መረጃ ልጨምር፡፡ የደርግ መውደቂያ እየተቃረበ ሲመጣ አዲስ አበባ እንደ ሞኖሮቪያና ሶማሊያ እንዳትሆን ይሰጋ ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን አደጋ ለመቀነስና ለማስወገድ ኢህአዴግ ዝግጅት ያደርግ ጀመር፡፡ ድርጅቱ የከተማ ኮማንዶ ውጊያ የሚያደርግ ኮማንዶ አሰልጥኖ ነበር፡፡ ይህ የኮማንዶ ሰራዊት አዲስ አበባ ውስጥ የተፈራው አይነት ውጊያ አላጋጠመውም፡፡አዲስ አበባም እንደ ሞኖሮቪያ አልሆነችም፡፡የኮማንዶ አባላቱ ስልጠና የወሰዱት ግን እዚሁ ሰፈራችንና ቤታችን አከባቢ ነበር፡፡ከዛች ጫካ /የበረሃዋ ገነት/ ቀጥ ብለው ተነስተው የት ገቡ መሰላችሁ?- አራትኪሎ ቤተመንግስት -አይ አጋጣሚ!!

የመጨረሻው የኢህአዴግ ወታደራዊ ስልጠና የተካሄደውም እዚሁ አከባቢ ነበር፡፡አከባቢውም 02 ነበር፡፡ የመጨረሻው የህውሓት ምልምሎች ስልጠናቸው የወሰዱት በዚሁ ጫካ ነበር-ታዲያ ለሰልጣኙ የሎጀስቲክስ አገልግሎት መጋዘን በመሆን ቤታችን ታሪካዊ ግልጋሎትን ሰጥታለች-በስተመጨረሻ!!

ቀደም ብዬ መንደራችን ብዙ የህውሓት ነባር ታጋዮች ያውቋታል ብዬ ነበር- አብዛኞዎቹ መሪዎች ታግለውባታል፡፡ ከጠላትም ተሸሽገውባታል፡፡ ብዙ ጊዜ ከለላ ሆና አገልግላለች፡፡ከነዚህ ታጋዮች ገሚሶቹ አሁን ለከፍተኛ ቦታ ደርሷዋል፡፡ ምንሊክ ቤተመንግሰት በቀጥታ ባይገቡም የውሃንስ ቤተመንግስት ግን ገብቷል፡፡ ከነሱ መሃል አንድ ተወዳጅ ታጋይ ግን በቦታው መስዋእትነት ከፍሎ የሹም ያዕቆብን የዘመናት ዝና ተረክቧል፡፡ አልአሚን- ቃልአሚን!!

የመንደራችን የዘመናት ስም ከአዲሹም ያዕቆብ ወደ አልአሚን ተቀይሯል፡፡ስፍራችን ለስማእቱም ለህልውም ውለታው ይከፍላል፡፡የመንደራችን ስያሜ ከአዲሹም ያዕቆብ ወደ ቃልአሚን በፍላጎት ቢቀየርም ልምላሜውና ወዘናው ግን ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡

ከዚህ ዋሻ ሳልወጣ አንድ ነገር ልጨምር ፡፡ አራትኪሎ ፡፡አራትኪሎ ብሔራዊ ሙዚየም፡፡ አንድ የቅደመ አክሱም የድንጋይ ጥርብ የሴት ምስል ትገኛለች-ሙዝየሙ ውስጥ፡፡ ታዲያ ይህች ጉዑዝ በንጉሱ ዘመን ከመንደራችን የመጣች እንደሆነች ብነግሮትስ-አይገርሞትም፡፡

አንዳንዴ ሳስበው ይሄ ያዕቆብ የተባለ ሰውእግዚአብሔር እንዴት ይወደዋል የአንተን ምድርና ሰፈር የረገጠ ሁሉ ይነግሳል ወይ ደግሞ ስሙ ይነሳል ተብሎ ቃልኪዳን የተገባለት ይመስል ሁሉም እዛ ሰፈር የረገጠ ሰው በዚህም ባዛም ባለታሪክ ሆኗል፡፡

ያችው ከሁሉም አቅጣጫ የምትታይና በባህላዊና ዘመናዊ መንገድ የታነፀች መኖሪያ ቤታችን ግን ለሌላ ታሪክና ዜና የተዘጋጀች ትመስላለች፡፡ በንጉስ ዘመን ይሁን በደርግ ዘመን እዛው አከባቢ ካሉት የህድሞ ቤቶች በተለየ የቆርቆሮ ቤት እሷ ብቻ ነበረች፡፡ ባለሁለት ፎቅም ነበረች-ያውም በጫካና በገጠር፡፡ከሩቅ ስትታይ የግለሰብ መኖሪያ ቤት አትመስልም -ቤተክርስትያን ትመስላለች፡፡ከሩቅ ላያት ሁላ ታሳስታለች-ሁሉንም ግን ስባ ታመጣለች፡፡ንቦችንም ሳይቀር፡፡

መስከረም ወር ሲሆን ከተለያየ አቅጣጫ ንቦች መጥተው ያርፉባታል- መንጋውን ለማግኘት ባዶ ቆፎ መስቀል ብቻ በቂ ነው፡፡ ሌላ ነገር አይጠበቅብህም፡፡

መንገደኛውም፣ሽፍታውም፣ንጉሱም፣ባህታዊውም፣የነፃነት ታጋዩንም ወታደሩንም ለዘመናት እየተፈራረቁ የጎበኟት ቤታችን ዛሬ ዛሬ እርጅና የተጫጫናት ትመስላለች፡፡

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ያደኩባትን መንደርና ቤት ለመጎብኘት እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ቤታችን በግማሽ ገፅታዋ ፈራርሷል፡፡ ግንቡ ተገንጥሎ ሄዷል፡፡ ቆርቆሮውና መሰረቱ ግን አልተናጋም፡፡ ከጓሮ በኩል ቤታችን ውስጥ ከጫካውና ከወንዙ አከባቢ የመጣ ዘንዶ ሰፍሮበታል፡፡ ቤታችን ምድር ቤት ሥር ዘንዶ ገብቶበታል ተብሏል፡፡በቤቱ ላይ ግን ሰው ይኖርበታል፡፡ዘንዶና ሰው አንድ ላይ!!-አይ ጊዜ፡፡አይ ዘመን!!

ያደኩበትና የልጅነት ዘመን ቤቴን ለመግባትና ለማየት እጅጉን ፈለግኩኝ-ግን ደግሞ ፈራሁኝ፡፡ ዘንዶው ድንገት ተነስቶ ቢውጠኝስ ምን አገባኝ አልኩኝ፡፡ ለህይወትህ ዋጋ ስጥ ተብሎ የለ፡፡ ግን ማን ያውቃል? ቤታችን ውስጥ የመሸገውን ዘንዶ ሰይጣን ይሁን መላአክ ገና አልለየም፡፡ማንነቱ ጊዜ ይፈተዋል፡፡ ቤታችንም ትታደስ ይሆናል፡፡ማን ያውቃል?!ወይ በያዕቆብ ስም ወይም ደግሞ በሰማእቱ ቃልአሚን ስም ዘንዶውን እንዳይቀሳቀስ ገዝቼ ከገባበት ጉድጓድ አወጠዋለሁ፡፡ የልጅነት ቤቴም አድሳታለሁ፡፡አምላክ ብቻ ይርዳኝ፡፡ የጓሮው ዘንዶ አውጣው ቤትህንም አድስ ይበለኝ፡፡

2 የፋሪስ ዋሻ

አሁን ደግሞ ከሰፈሬ ወጥቼ ወደሌላኛው የታሪክ ዋሻ ከአንባቢያን ጋራ ላዝግም፡፡ አክሱም፡፡ አክሱም የታሪካችንና ማንነታችን መግቢያ በር ናት ልንላት እንችላለን፡፡ ድንቅ ከተማ ናት፡፡ከውጭ ላያት ሀውልቶቿ፣የነገስታት መገበያያ ገንዘቦችዋ፣ መንፈሳዊ ታሪኳ ፅዮን ማርያምን ጨምሮ ታይቶ የማያልቅ መስብ አላት፡፡የአክሱምን ከተማ በደንብ ላያትና ላስተዋላት ግን አንድም ሦስትም ናት ይላሉ፡፡

አንደኛው ገፅታ ውጫዊ ሲሆን ማንም ፍጡር የሚያየውና የሚዳስሰው ነው፡፡ ሁለተኛውና ሦሰተኛው ከተማ ግን እስካአሁን ድረስ በከፊል አሊያም ሙሉበሙሉ ስውር ነው-ሌላኛው ገራሚ ዋሻ!!

ከሃውልቶቹ አከባቢ ከምድር ስር ተቆፍረው በከፊል የተገኙ መካነመቃብሮች አሉ፡፡ከነዚህ የምድር ውስጥ አስደናቂ ነገሮች አንዱ የነገስታቱ መቃብር ነው፡፡ የነገስታቱ መቃብር ሁለት ዋሻዎች አሉት፡፡ አንደኛው ዋሻ መቃብሩ የተቀመጠበት ቤትና ግንብ ሲሆን እጅ ስራውና ኪነህንፃው ባለብዙ ትርጉም ነው፡፡

ራሱ የነገስታቱ መቃብርም ሌላኛው ተአምራዊ ዋሻ ነው፡፡ ከአንድ ድንጋይ የተስራ መቃብር-ወጥ መቃብር!! መግቢያውና መዝጊያው በውል አይታወቅም፡፡ ቅርፅ ያለው ወጥ ድንጋይ ነው፡፡ውስጡ ክፍት እንደሆነ ውስጡ የተቀመጠው አስክሬንና ሌላው ነገር ድምፅ ያሰማል፡፡ አስከሬኑና የከበረ ማእድናቱ ወደ ውስጥ እንዴት ብለው እነደገቡ ግን አይታወቅም፡፡ በሳይንስም በሌላ ነገርም አልተደረሰበትም፡፡ መቃብሩ አፍ የለው ምን የለው ነው፡፡ እንቆቅልሽ ይሉታል የዚሁ ዓይነት ዋሻ ሚስጥር አይደል?!

ሦስተኛው ከተማ ግን እስካሁን ማንም ሰው የማየት እድል አልገጠመውም፡፡ጥቂት ተመራማሪዎች ግን ፍንጭ አግኝተናል ይላሉ፡፡ለማንኛውም እዚሁ ውስጥ ምን እንደሚገኝ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡ሁሉንም ለማየት መቆየት ብሎ የለ ዘፋኙ!

ከአክሱም ሳልወጣ ሌላ ታሪክና የዋሻ ሚስጥር ልጨምር፡፡ ይህ ዋሻ መነሻውና መጨረሻው በውል አይታወቅም፡፡ በተረት ግን ይታወቃል፡፡ መነሻው አክሱም መድረሻው ቀይ ባህር፡፡ ትልቅ የምድር ሥር ታናል ነው፡፡ ረዠም የምድር ውስጥ ታናል ወይም ደግሞ ዋሻ ነው፡፡ በጥንት ጊዜ በዘመነ አክሱም ነገስታቱ በዚሁ ዋሻ ውስጥ ለውስጥ ነበር ለዘመቻ ወደ ውጭ ሃገራት የሚመላለሱት፡፡ ባቡር ባልነበረበት ዘመን-የባቡር ታናል እንደማለት ነው፡፡

አንድ ወቅት ንጉሱ ሰራዊቱን ይዞ ድንገት ከአክሱም ወደ ቀይ ባህር አከባቢ ይሄዳል፡፡ የንጉሱ ሰራዊት አባላት ግን ለዋሻው እንግዶች ነበሩ፡፡ ዋሻው ውስጥ ምን ዓይነት ቁስ መኖሩ አያውቁም፡፡ጨለማ ነው-ረዠሙ ታናል፡፡ሰራዊቱ ሁሌም ዝግጁ ነበር፡፡ እንኳንስ በታናል ውስጥ ለውስጥ በሌላ መንገድም የመንና ግብፅ ድረስ ተመላልሷል፡፡ ዘመቻ አለ ሲባል ተነስቶ ይሄዳል፡፡ንጉሱ ሰራዊቱ መርቶ ዋሻው ውስጥ ለውስጥ አቋርጦ ቀይ ባህር ይደርሳል- መርከቦችና ጀልባዎች ይቀበሉታል፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በዚሁ መንገድ የዘመቻ ክተት ይታወጃል፡፡ከዘማች ሰራዊቱ ውስጥ ገሚሶቹ የዋሻው ርዝመት እያደነቁ ፤ ገሚሶቹ ደግሞ ይህ የጨለማ ዋሻ መቼ ነው የምንጨርሰው ቶሎ ብለን በተገላገልን እያሉ ከአክሱም ተነስተው ቀይ ባህር ይደርሳሉ፡፡ ጥቅቶች ግን ለማንኛውም ብለው የጉዞ ማስታወሻ እንደማለት ያህል ከሚረግጡት የጨለማ ዋሻ/ታናል/ ውስጥ በእጃቸው ዘገን ዘገን አድርገው ይወጣሉ፡፡ወዲያውኑ ፀሐይ ማየት ሲጀምሩ ለናሙና የያዙት ድንጋይ ጠጠር ወርቅ ሆኖ ያገኙታል፡፡በጣም ይደነቃሉ -ያዝናሉም፡፡ ባዶ እጃቸው የወጡትም ወይኔ ትንሽ በያዝን ብሎው ይቆጫሉ፡፡ትንሽ ዘግነው የወጡት ደግሞ በጨመርን ብሎው ከህሊናቸው ጋር ይጨቃጨቃሉ፡፡

ታዲያ ምን ተባለ መሰላቹሁ? የዘገነም አዘነ ያልዘገነም አዘነ ተባለላችሁ፡፡

ይሄ ዋሻ ህላዌው ተሰውሯል፡፡ ታሪኩ ግን ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ብዙ ምሽጎች ግራ ቀኙ ተቆፍሯል፡፡ ድንገት እንኳ አንድ ቦታ ላይ የታናሉ ድኳ አልተገኘም፡፡የሁለቱ አገራት ድንበር በወታደሮቸ ታጥሯል፡፡የሥውሩ ዋሻ/ታናል/በሮች ግን ያለጠባቂ ዛሬም ድረስ ተሰውሯል፡፡

አከባቢው የወርቅና የሳፋየር መዕድናት ቦታ ስለማሆኑ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው እውነታ በቂ ምስክር ነው፡፡በኤርትራም በኢትዮጲያም በኩል የከበሩ ማዕድናት ክምችት አለ፡፡ ታዲያ ዋሻው የወርቅ ታናል ይሁን? ጊዜ ይነገር ይሆን? ማን ያውቃል፡፡ ሁለት ወንድማሞች ከላይ ሆነው ይጋጫሉ ከውስጥ ያለው የጋራ ፀጋቸው ግን ዛሬም ድረስ ካልታረቃችሁ አልከፈትም ያለ ይመስል ተሰውሯል፡፡

የወንድማሞች ነገር ካነሳሁ አይቀር ከአክሱም ሳልወጣ ሌላ ገራሚ ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡ የአክሱም ቅርሶች በተደጋጋሚ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ከዘመነ ዮዲት ጉዲት ጀምሮ ብዙዎቹ በከፊል ወይም ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ጉዳት ካጋጠመው ቅርስ አንዱ የፅዮን ቤተክርስትያን ነበር፡፡ ታዲያ አፄ ፋሲል ነው አሉ አክሱምን ይጎበኝና ይቆጫል፡፡ የፈረሰውን የፅዮን ቤተክርስትያን በአስቸኳይ ይሰራ ብሎ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

በአፄ ፋሲል ዘመን ጊዜ አንድ ፋሪስ የሚባል ወጣት ትግራይ ውስጥ ነበር፡፡ይህ ሰው ጠንካራና ታታሪ ነው፡፡ ራሱን ለማስተዳደርም ወደ ጎንደር አፄ ፋሲል ቤተመንግስት በግብርና ሙያ ለማገልገል ይሄዳል፡፡ከነበሩት ገበሬዎች መሃልም ጎላ ብሎ መውጣት ይጀምራል፡፡ቤተመንግስቱም አከባቢም ተልዕኮ ይሰጠዋል፡፡ ተልዕኮውም በብቃት መወጣት ይጀምራል፡፡ እያለም እያለም አፄ ፋሲል አይን ውስጥ ይገባል፡፡ አፄ ፋሲልም ፋሪስን ጠርቶ አንድ ተልዕኮ ይሰጠዋል፡፡ የአክሱም ፅዮን ቤተክርስትያን በአጭር ጊዜና በጥንቃቄ ገንብቶና አሳድሶ እነዲጨርስ ተልዕኮ ይሰጠዋል፡፡ ፋሪስም ተልዕኮውን በሚገባ ይወጣል፡፡ከዚህ ተልዕኮ በኋላ ደግሞ ከተራ ገበሬነት ወጥቶ የደጃዝማችነትና የራስነት ማዕረግን ይደርባል፡፡በፋሲል ዘንድ ታላቁን ሞገስ ይጎናፀፋል፡፡

ራስ ፋሪስም ትዳር መስርቶ ልጆች ይወልዳል፡፡ካራ፣ገለቡ፣ወ/ሮ ሰንበልተን፣አክሎም፣ ማርያም ስና ኪሂለሃይማኖትና እትየለቱ ወዘተ የተባሉ ልጆች ይወልዳል፡፡ወ/ሮ ሰንበልተ ፋሪስ የአቤቶ ያዕቆብ የልጅ ልጅ የሆነውን የስግወቃል የሆነው አቤቶ ወረዳቃልን አገባች፡፡ ወደ ሸዋም ተዛመደች፡፡ ከአቤቶም ወረደቃልም ነጋሲን ወለደች፡፡ ነጋሲም ለስብስቴ ወለደ፡፡ ስብስቴ ደግሞ አብቶ ኣብዩን ወለደች፡፡ ኣብቶ ደግሞ አምሃኢየሱስን ወለደ፡፡አምሃኢየሱስ ደግሞ አዝማች አስፋወሰንን ወለደ፡፡አስፋወሰን ደግሞ ለንጉስ ሳህለሥላሴ ወለደ፡፡ሳህለሥላሴ ደግሞ ኃይለመለኮትን ወለደ፡፡ ኃይለመለኮት ደግሞ ዳግማዊ ምንሊክን ወለደ፡፡

ወ/ሮ ገለቡ ፋሪስ ደግሞ ወደ ወሎ ተዛመዱ፡፡ከሴሩ ጓንጉል ቤተሰብ ጋር ተጋባች፡፡ እነ ራስ ዓሊም ተወለዱ፡፡ ራሰ ዓሊም እነ ራስ ወሌን ወለዱ፡፡ ራስ ወሌ ደግሞ የዳግማዊ ምንሊክ ሚስት እቴጌ ጣይቱ ያመጡ ሲሆን ገለቡ የወለደቻቸው የወረሸክ ቤተሰቦች ይገኙበታል፡፡

ወ/ሮ ማርያም ስና ፋሪስ ደግሞ ለጋብቻ ወደ ሽሬ ሄደች፡፡ እዛውም ደጃዝማች ዮውሃንስ ወለደች፡፡ ዮውሃንስም ፋሲልን ወለደ፡፡ ፋሲል ደግሞ የራስ ሚካኤል ሱሑል ልጅ ወ/ሮ ገሊላዊነትን አግብቶ ወርቀሃን ወለደ፡፡ ወርቅሃ ደግሞ ሹም ተምቤን ምርጫን ወለደች፡፡ ሹም ተምቤን ምርጫም አፄ ዮውሃንስን ወለዱ፡፡

ሰደጃዝማች ካራ ፋሪስም ኤርትራ ውስጥ ይሁን ትግራይ ውስጥ ብዙ ተዋልዷል፡፡ጎጃም ውስጥ ይሁን ሸዋ ውስጥም የልጅ ልጆች አይቷል፡፡ አዝማች አክሎም ፋሪስም ኤርትራ፣ትግራይ፣ወሎ፣ጎንደር፣ሸዋ፣ጎጃም ዘሩን አጥለቅልቆታል፡፡

ኤርትራና ኢትዮጲያ፣ ትግሬና አማራ፣ አማራና ኦሮሞ ወዘተ እያልን የምንለያይ ለካስ የአንድ አባት ልጆች ኖረናል?-ያውም ሩቅ ሳንሄድ የፋሪስ፡፡ አይ የፋሪስ ዋሻ ምኑ አሳየኸኝ? ንጉሰ ነገስት አፄ ዮውሃንስ፣አፄ ምንሊክ፣ እቴጌ ጣይቱ-ሁሉም የአንድ ማህፀን የአንድ ሽንት ልጆች፡፡ የፋሪስ ዋሻ ልጆች፡፡

3.መዝባዕ

በተለምዶ የሰው ልጅ የስሜት ህዋሳት አምስት ናቸው እንላለን፡፡ ቁሳዊ ነገር መኖሩንና አለመኖሩን በነዚህ የህዋስ ስሜቶቻችን አማካኝነት ህላዌያቸው እናረጋግጣለን፡፡ አንዳንዴ ግን በነኚህ የስሜት ህዋሳት በኩል ለማረጋገጥ የሚያስቸግር እውን ነገር እናገኛለን፡፡ የምር ስድስተኛው የስሜት ህዋስ ይኖረን ይሆን ብለንም ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡

እንኳንስ ስድስተኛ ተጨምሮ አምስቱ የስሜት ህዋሶቻችን የሚያቀርቡልንን መረጃ እውነት ይሁን ውሸት የሚጠራጠሩም አልጠፋም፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ አይደል?! ታላቁ የፈረንሳይ ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት መጀመሪያ የስሜት ህዋሳቶቹ የሚመጡለትን መረጃዎችን መጠራጠር ጀመረ፡፡ቀጥሎም ፈጣሪውን መጠራጠር ጀመረ በስተመጨረሻ ግን እንደምንም ብሎ ፈጣሪ መኖሩን አረጋገጠ፡፡ በፈጣሪ የተሰራ አናሳ ፍጡር መሆኑ የፈጣሪ ማህተም በልቡ አገኘ፡፡ ኢትዮጲያዊው ፈላስፋ ዘርአያዕቆብም ይህንን የሜዲቴሽንና የጥርጣሬ መንገድን በአመክንያዊነት ዘዴ መከተሉን ይነገራል፡፡

የጥርጣሬንና የእውነት ነገር፤ የሚታይና የማይታይ ነገር ስለማይዳሰስና ስለተሰወረ ነገር በተነሳ ቁጥር ሁሌም የአንድ አከባቢ የማውቀውን ነገር ትዝ እያለ ያስቸግረኛል፡፡

የሚታይ ቤተክርስትያን በአቅራቢያው ሳይኖር የቅዳሴ መንፈሳዊ ዜማ ይሰመሃል፡፡ዝናብና ውሃ ሳይኖር እርጥበት ይሰማሃል፡፡ እጣን ሳይጨስ ያውድሃል፡፡ ከየት መጣ ሳይባል መንፈስህን ገነት ውስጥ ያስገበሃል፡፡ ይህ ቦታ ሰማይ ላይ አይደለም፡፡ ምድር ላይ እንጂ!!

እንዲህ ዓይነት ፀጥ ያለ መንፈሳዊ ቦታ ሲታሰብ ቀድሞ የሚታወሰን ቦታ ቢኖር ዋልድባ ገዳም ነው፡፡ ይህ ቦታ ግን የዋልድባ ገዳም አይደለም፡፡ እንደ ዋልድባ ገዳም ብዙ አልተባለለትም፡፡ አልተፃፈለትም፡፡ ይህ ስፍራ ዋሻ የለውም፡፡ከየት ልጀምር? ከአፋር፡፡

የአፋር ክልል ነገር ሲነሳ ቀደም ብሎ የሚታየን የዳሎል መልክዓምድር፣ የአዋሽ ወንዝ ዳርቻዎች የነ ሉሲ ሰፈር ወዘተ ነው፡፡ ከታሪክ ጉዞ አንፃር ደግሞ የአሞሌ ጨው ቦታው ረገድን ነው፡፡

በተለምዶ የትግራይ ደጋማ አከባቢዎች የሚያዋስነው የዳሎልና የረገድ የአፋር አከባቢባሕሪ (ባህር እንደ ማለት ነው) ተብሎ ይጠራል፡፡ከዚህ ቦታ ቀጥሎ ቀይ ባሕር ስለሚገኝ ይሆናል፡፡

ባሕሪ በሙቀቱ የሚታወቅ-የደን ሽፋን የሌለበት፣ ውሃም እነደልብ የማይገኝበት እጅጉ አስቸጋሪ አከባቢ ነው፡፡በዚህ አከባቢ ለቀናት ተዘጋጅተው የሚጓዙ የጨው ነጋዴዎች ካልሆኑ በስተቀር ቋሚ ኑሮ መስርቶ ለመኖር ቦታው አሰቸጋሪ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አልፎ አልፎ ግን እንደ በራሕለይና ሸኸት የመሳሰሉ የጥንት መንደሮችና ከተሞች ይገኙበታል፡፡

ከሸኸት ከተማ እንነሳ፡፡ የሸኸት ከተማ ለመቐለ ከተማ ቅርብ ናት፡፡ከ40ኪሎሜትር ርቀት ላይ ብትገኝ ነው፡፡ በከተማዋ በስተምዕራብ በኩል ባለው ከፍተኛ ኮረብታ ተጠግተን ትንሽ እንጓዝ- የሐሩሩ ነገር አስቸጋሪ ቢሆንም ከዚህ አከባቢ ተሁኖ ወደላይ አንጋጦ የሚታየው ከፍተኛ ቦታ መውጫና መግቢያ ያለው አይመስልም፡፡እንኳንስ ለሰው ልጅ ለዝንጀሮዎችም ይፈትናል፡፡ገደሉን ለማየት እንኳን ይታክታል፡፡

አሁንም ዳገቱን ትንሽ እያደኸየንና እየተንፋቆቅን እንቀጥል፡፡ከብዙ ወጣ ወረድ በኃላ ትንሽና አንዲት ቀጭን መንገድ እናገኛለን፡፡እንደደብረዳሞ ገዳም ገደሉ በገመድ ተጎትተህ አትወጣውም፡፡በመከራና በዘዴ ግን የተለየ መንገድ አለው፡፡

ዳገቱ አሁንም እንደምንም ብለህ ታጋምሰዋለህ፡፡የአፋርና የደርጋዓጀን እረኞች እንዳጋጣሚ ካገኘህ ደግሞ መንገዱ ትንሽ ቀለል ያደርግለሃል፡፡አሁን ከሐሩሩ የአፋር አከባቢ እየወጣን ወደ ደጋው የትግራይ አከባቢ እየደረስን ነው-አሰቸጋሪ ጉዞ፡፡ውሃ የሚባል ነገር በአከባቢው ጭራሽ የለም፡፡መንደር የሚባልም ጭምር፡፡

ከሰዓታት አስቸጋሪ ጉዞ በኃላ ከፊት ለፊታችን ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ማግኘት እንጀምራለን፡፡የዴስኣ የደን ጫካ የመጨረሻው ክፍል ማለት ነው፡፡የዴስኣ የደን ይዞታ የኦሮሚያ ባሌ በተለይ ደግሞ የዲንሾን አከባቢ ይመስላል፡፡

ይህ ቦታ መዝባዕ ይባላል፡፡ መዝባዕ መንፈሳዊ ቦታ ነው፡፡ሆኖም ግን በአጠገቡ የሚታይ ቤተክርስትያን የለም፡፡መዝባዕ በስተደቡብ አፋር በስተሰሜን ዴስኣ በስተምስራቅ ደርጋዓጀን በስተድቡብ ደግሞ የመቐለ ከተማ በቅርበት ያዋሱኑታል፡፡

ይህ መንፈሳዊ ቦታ በወጣህበት የማይገባበት፣በገባህበት የማይወጣበት ስፍራ ነው፡፡ወደዚሁ ቦታ ለመግባትና ለመውጣት በጣም አስቸጋሪና ጠባብ መንገዶችን በዳዴ መሄድን ይጠይቃል፡፡ለየት ያለ መንፈሳዊ ስፍራ ነው፡፡ የቅርቡ- ሩቅ-መዝባዕ!!

መዝባዕ ለመቐለና አከባቢው እጅግ ቅርብ ቢሆንም ከነዋሪዎች መካከል ስለቦታው የሚያውቁ ግን እጅግ በጣም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡መዝባዕ ተራ የአከባቢ ነዋሪዎች እንኳን ዝር አይሉበትም፡፡እጅግ የተከበረ ቅዱስ ስፍራ ነው፡፡

ታሪኩ ረጅም ነው፡፡ከ500 ዓመታት በፊት የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች/ደቂቀ እስጢፋኖስ/ እንደመሰረቱት የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ፡፡ ታዲያ በዛን ጊዜ በንጉስ ዘርአያዕቆብና በደቂቀ እስጢፋኖስ መካከል በነበረው መሳሳብና ውዝግብ ምክንያት በርከት ያሉ የደቂቀ እስጢፋኖስ አብያተክርስትያናት እንደተቃጠሉና በወታደሮቹ ዱኳቸው እንዲጠፋ መደረጉ የያኔው ጊዜ ድርሳናት መዝግበውታል፡፡የዚሁ ዕጣ ፈንታ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት መካከል አንዱም መዝባዕ ነበር፡፡

መዝባዕ እንደ ጉንዳጉንዲ ማርያም መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ድርሳናት ለታሪክ አልተውልንም፡፡ ነገር ግን የእውነተኛ መንፈሳውያን አባቶች መናሃሪያ ለመኖሩ ግን ዛሬም ድረስ አሻራው በግልፅ ያስታውቃል፡፡

መዝባዕ ጥቅጥቅ ያለ ደን ያለበት ጫካ ቢሆንም የሚላስ የሚቀመስ ነገር የለውም፡፡ ቦታው በተፈጥሮ ለምለም ቢመስልም ጥብ የምትል ውሃ አትገኝበትም፡፡ዝር የሚል የዱር አራዊት ለአይን አይታይበትም፡፡ከላይ የተሸፈነም ነገር የለውም፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጠህ ስታይ ሁሉም ነገር ግልፅ ብሎ ይታየሃል፡፡ የሚሸፍንህ ነገር የለወም፡፡መግቢያው በአፋር በኩል ሲሆን መውጫው ደግሞ በደርጋዓጀን/መቐለ/በኩል ነው፡፡ ይህ ስፈራ ማንም ሰው ዝር አይልበትም፡፡ ሽፍታም የለውም-ጠባቂም የለውም፡፡ራሱ በራሱ የከበረና የታፈረ ስፍራ ማለት መዝባዕ አይደል?!

መዝባዕ ግን የሚመላለሱበት እውነተኛ ሰዎች አሉት፡፡ መናንያን- ባህታዊያን፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ ዋልድባ ገዳም እንኳ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ አይታዩም፡፡ ዋልድባ ገዳም ውስጥ አብረንታንት መድኀኔዓለም ቤተክርስትያን አለ፡፡ መዝባዕ ውስጥ ግን ለአይን የሚታይ ቤተክርስትያን የለም፡፡ ዋልድባ ገዳም ውስጥ የገዳሙ ስርዓት ተከትሎ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡እዚህ መዝባዕ ውስጥ ግን የተለየ ነው፡፡

መናንያኑ ለፀሎትና ለሱባኤ አንድ የተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ከገቡ በኃላ የሱባኤ ጊዜው ሳያልቅ አይነቃነቁም፡፡ የሱባኤውና የፆሙ ጊዜ ደግሞ አጭር አይደለም -ወራት እንጂ!!

በሱባኤው ወቅትም ቀለባቸው ሽንብራ ነው አሉ፡፡ጥሬ ሽንብራው ደግሞ እንደልብ አይገኝም፡፡ ትንሽ ሕይወት ለማቆያ ካልሆነ በስተቀር፡፡መናንያኑ ምግባቸው መንፈሳዊ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

መናንያኑ ከየት እንደመጡና የት እንደሚሄዱ የሚያውቅ የለም፡፡ሲገቡም በጨለማ ነው፡፡ ሲወጡም በጨለማ ነው፡፡ ወደዚሁ ስፍራ ግምጃ/ምንጣፍ/፤ጧፍም ሆነ ሻማ ተይዞ አይኬድም፡፡ቦታው ፀጥ ያለ ቦታ ነው፡፡ከመዝባዕ በስተቀር ፀጥ ያለ መንፈሳዊ ቦታ ይኖር ይሆን? እኔእንጃ-አይመስለኝም፡፡የቅርብ ሩቅ-ምድራዊት ገነት-መዝባዕ!!

የመዝባዕ መናንያን እጅጉ ይደንቁኛል፡፡ ቤተክርስትያን በሌለበት ለወራት ሱባኤ ይገባሉ፡፡ይፀልያሉ፡፡ ዓላማቸው አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ንፁህ ፀሎት፡፡ ግንኙነታቸው ከአንድ ጋር ነው-ከፈጣሪ!! አጠገብ ለአጠገብ ፀሎት የሚያደርጉ መናንያን እንኳ እርስበራሳቸው አይነጋገሩም-በመንፈስ ግን ይገናኛሉ፡፡ለወራት አንዴ ጉድጓድ ውስጥ ከገቡ በኃላ ፀሃይን እንኳን ቀና ብለው አያዪም-አቤት መንፈሳዊ ፅናት!!

መዝባዕ ገራሚ ስፍራ ነው፡፡በከተሞች ተከቦ የማይታይ፤ ከመንደሮች አጠገብ ሆኖ የማይጎበኝ፡፡ከበረሃና ሃሩር አከባቢ አጠገብ ሆኖ -ለምለም፡፡ ደንበኞቹ ንፁሃንና ፈጣሪን የሚለምኑ መናንያን ብቻ ናቸው፡፡መናንያኑ ለወራት ይሰወርበታል፡፡ በገቡበት አይወጡም በወጡበት አይገቡም፡፡ከየት አከባቢ እንደመጡ አይታወቅም፡፡የት እንደሚደርሱም አይታወቅም፡፡ስፍራው ግን ውጧቸው አይቀርም፡፡መዝባዕ ግልፅ ሆኖ እያለ ራሱ በራሱ ዋሻ አድርጎ የቆየ ሚስጥራዊ ስፍራ ነው፡፡

4 የዋሻ እስረኞች

አሁን ደግሞ የገጠር ዋሻዎች ትውውቃችንን ለጊዜው እናጠናቅቅና ወደ ከተማ ዋሻ ጉብኝት በምናባችን እንግባ፡፡የከተማ ኑሮ በራሱ ዋሻ አይደል?-አዲስ አበባ ደግሞ ትልቁ የሃገሪቱ ዋሻ፡፡ይህ ዋሻ በዓይነቱና በይዘቱ ፍፁም የተለየ ነው፡፡ እንደ መጀመሪያዎቹ የልጅነት ትዝታዎቼ ዋሻዎች አይደለም፡፡ውቅር አብያተክርስትያናት የሉትም፡፡ይህ ነው የሚባል ታሪክም የለውም::እንደ አክሱም ተኣምራዊ የነገስታት የድንጋይ ውስጥ መቃብር ተቆፍሮ አልተገኘም፡፡ በትንሹ ግን የመመሳሰል ባህሪያት አሉት፡፡እንደ ረጅሙና ስውሩ የምድር ውስጥ ታናል/ዋሻም/ አይደለም-ደብዛው አልጠፋም፡፡ታዲያ እንደ መዝባዕ ይሆን?-ይሄ አይታሰብም፡፡ያውም አዲስ አበባ ከተማ -ይታያችሁ፡፡ ግን ደግሞ በትንሹም ቢሆን መመሳሰል አይቼበታለሁ፡፡

..አንድ ትልቅ ዋሻ ነው፡፡ከብረት ይሁን ከድንጋይ በምን እንደተሰራ አይታወቅም፡፡መግቢያና መውጪያ በርም የለውም፡፡ የበርም የመስኮትም ምልክት አይታይበትም፡፡ኪነ-ህንፃው መተለቁ ካልሆነ በስተቀር የአክሱምን የነገስታት መቃብር ይመስላል፡፡ የነገስታቱ መቃብር የአልጋ ያህል ስፋት ቢኖረውም ይሄኛው ግን መካከለኛ አዳራሽን ያክላል-ግዙፍ ዋሻ!!

የአክሱሙ የነገስታት መቃብር በውስጡ አቅፎ ለዘመናት የዘለቀው የነገስታት አስከሬንና የከበሩ ማዕድናትን ነው፡፡የአዲስ አበባው ዋሻ ግን በውስጡ ዘግቶ የያዘው ግዑዝ ነገር ሳይሆን የሚንቀሳቀሱና የሚናገሩ ሰዎችን ነው፡፡

የአዲስ አበባው ዋሻ ከመዝባዕ ጋርም ይመሳሰላል፡፡ ዋሻው ውስጥ የተዘጉ ሰዎች ማን እንደሆኑ መቼ እንደገቡ አብዛኛው ሰው አያውቅም፡፡መናንያን ግን አይደሉም-ዓለማውያን ናቸው፡፡ሰዎቹ መቼ እንደገቡና ማን እንዳስገባቸው በውል አይታወቅም፡፡ ግራ ያጋባል-ለጊዜው፡፡የሚናገሩት ንግግር ግን በደንብ ይሰማል፡፡ከዋሻው ውጭ ያለው ሰው በደንብ ይሰማዋል፡፡ጠጋና ረጋ ብለህ ስትሰማቸው ልክ የሬድዮ ድራማ የማዳመጥ ያህል ይሰማሃል፡፡

ከዋሻው ሰዎች ውስጥ አንዳዶቹ ስለሃገራችን ወቅታዊሁኔታዎች ይናገራሉ፡፡ ገሚሶቹ የአምስት ዓመት የሃገሪቱ ዕቅድ አፈፃፀምና ውጤቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ይሄ ጉዳይ ሳያልቅ ሌላ ድምፅ ይሰማል-ከዋሻው አንደኛው ጥግ፡፡ ጭፈራ ይሁን እርግጫ አልለየም፡፡ በአይን ካልታየ በምን ይታወቃል? ከአንደኛው የዋሻ ጥግ ደግሞ ስለ መልካም አስተዳደር ንግግር ይሰማል፡፡ከመሐል ደግሞ ቅዳሴና ፀሎት መሰል ድምፅ ይሰማል፡፡

ትኩር ብዬ አየሁት-ገርሞኝ!፡፡ በእጆቼ ዳበስኩት፡፡ጠጣር ነገር ነው፡፡ የስንዝር ያህል እንኳን ስንጥቅና ቀዳዳ የለውም-ልሙጥ ነው፡፡ የጠጠር ያክል ቀዳዳ የለበትም-ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፡፡ወደ ውስጥ ሆኖ ከውጭ አየር እንዴት እንደሚገባና እንደሚወጣ የታወቀ ነገር የለም-እግዚያብሔር ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡በሪሞት ኮንትሮል የሚዘጋና የሚከፈት በርና መስኮት ይኖረው ይሆን ወይ ብዬ እንዳላስብ ደግሞ ዋሻው አውሮፓ ወይም አሜሪካ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ ነው-ግራ የሚያጋባ ዋሻ!!

እንደ የቄስ ዮውሃንስ ሃገር የታሪክ ደብዳቤ /ፕሪስተር ጆንኦፍኢንድስ/ ዓይነት ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩኝ፡፡ የዛን ዘመን ኢትዮጲያውያን ሊቃውንት አባቶችና የአሁኑ ዘመን አመዛዘንኩኝ፡፡ የአሁኑ ይሄንን ነገር ሊያደርጉ አይችሉም ብዬ ደመደምኩ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ ዓለምን ጉድ ያሰኘ ዜና ሰምቼና ተከታትዬ እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ፍፃሜው በምድር ደቡብ አሜሪካ ቺሊ ውስጥ ነበር፡፡ አንድ የማዕድን ቁፋሮ የሚካሄድበት ጥልቅ ጉድጓድ ድንገት ይደረመሳል፡፡ እንደ አጋጣሚ ጉድጓድ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች መግቢያና መውጫ ያጣሉ፡፡

ይህን ተከትሎም የዓለም ታዋቂ ሳይንቲስቶችና ባለሙያዎች የሰዎቹን ሕይወት ለመታደግ ብዙ መላምትን ያወጣሉ-ያወርዳሉ፡፡በስተመጨረሻም የሬድዮ ሞገደኞችና የናሳ የስፔስ ቁሳቁሶች በመጠቀም ከወራት ቆይታ በኋላ ዓለምን ጉድ ባሰኘና ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ሰዎችን ከተደፈኑበት ጉድጓድ ወይንም ዋሻ በሰላም እንዳወጣቸው ነው፡፡ይህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ እኛ ሃገር ቢኖር ሰዎች በቀላሉ ይወጡ ነበር ይሆን? ደግሞ ቴክኖሎጂውስ ይሄንን ዋሻ ይበሳው ይሁን-አይመስለኝም፡፡ ይሄኛው ዋሻ ደግሞ እንደ ቺሊው ከምድር ስር የተደረመሰ አይደለም-ከምድር በላይ ጉብ ብሎ የተቀመጠ እንጂ፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂውን መሞከር ከንቱ ልፋት ነው፡፡

የአዲስ አበባው ዋሻ ሁኔታ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ከከተማው አልፎ ዜናውና ወሬው በመላው ሃገሪቱ ተሰራጭቷል፡፡ ሰዎቹ ቀድመው ወደ ዋሻው እንዴት ገቡ? ማነውስ ያስገባቸው? ማነውስ የቆለፈባቸው? እውነትስ ተቆልፏል ወይ? በርና መስኮት በሌለበት እንዴት ተቆለፈ ሊባል ይችላል? ምን ዓይነት ሰዎችስ ናቸው?እዛው ዋሻው ውስጥ የሚነገረው ድምፅስ ምን ዓይነት መልእክቶች አሉት? ሰዎችስ ለመውጣት ሙከራ ያደርጋሉ ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ጀምረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋሻው አከባቢ ከውጭ ሆነው ዋሻውን የሚዞሩና ሰዎቹን ለማውጣት የሚሞክሩም አሉ፡፡ከሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ታዋቂዎች ናቸው፡፡አይዞኣችሁ ከዋሻው እንዴት እንደምትወጡ እርስ በራሳቹህ ተገማገሙ፡፡ያኔ በሩ የዘጋባችሁ ሰውና ከውስጥ የቆለፋባችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ እያሉ ምክር ቢጤ ይለግሳሉ፡፡ በመሃል አንድ ድምፅ ከዋሻ ውስጥ ሰማሁ፡፡ሎሬት ዶክተር ከውጭ መልዕክት መጥቶልናል አድምጠህ ንገረን ቀጥሎ ደግሞ ሌላ ድምፅ አስፈላጊ አይደለምየሚል ቃልም ከዋሻው ውስጥ ሰዎች መሃል ሰማሁ፡፡አሁን ከውጭም ከውስጥም የተለያዩ ድምፆችና መልዕክቶች ይሰማሉ፡፡በደንብ አጢነህ ካላደመጥከው ድምፁ የማን መሆኑን በቀላሉ ለመለየት ያዳግታል፡፡

አንድ ታዋቂ ሰው አሁን ከአንድ የዋሻው ውጫዊ ጥግ ሆኖ እናንተ የዋሻ ሰዎች ሆይ!-አይዞኣችሁ፡፡ ለቁርባን ተዘጋጁ፡፡እግዚያብሔር ያኔ ይራራላችኋልና በሩን ይከፈትላኋል፡፡አንኳንኩ-ይከፈትላችኋል ተብሎ የለ በመፅሃፉሲል አዳመጥኩት፡፡አሁንም ከዋሻው ውስጥ ሰዎች መሃል አፀፌታውዊ ምላሽ መጣ-ተሰማ፡፡

ሁላችንም ንሰሃ ሳንገባ እንዴት ለቁርባን እንዘጋጃለን?ይልቁንስ ሌላ መውጪያ ነገር አፈላልግልን የዋሻው ኑሮ መሮናልይላል፡፡

ሌላ ድምፅ-ከዋሻው ውጭ አይዞኣችሁ ጭስና ጀግና መውጪያ አያጣም ይባል የለ፡፡ በመሬት ስርም ቢሆን እንደ ፍልፈል መሬቱን ቆፍራችሁ ለመውጣት ሞክሩ- ተስፋ አትቁረጡይላል፡፡ወዲያውኑ ሌላ ድምፅ -ከዋሻው ውስጥ- ፊሽካ!! ደውል፡፡ቅጡ ያጣ የተምታታ ድምፅ፡፡ ተመችቶኛል አቦ! አታስቸግሩን፡፡ ዞር በሉልን፡፡እንኑርበት ይላል፡፡

እኔም የዋሻውን ዙርያ ተመላለስኩበት፡፡ አንዳንዴ ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚሰነዘሩት ድምፆችና ምልልሶች እንግዳ አልሆነብኝም፡፡የማውቃቸው ሰዎች ድምፅ መስለው ተሰሙኝ፡፡ ከውጭ ሆነው አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችንም ቢሆን መልካቸውን በደንብ ባልለየውም የከተማ ባህታውያን መሆናቸውን ልብ ብያቸዋለሁ፡፡ ከዋሻው ጀርባ ግን ጥቂት ሰዎች ተክዘውና አዝነው አየሁ፡፡የዋሻው ውስጥ ሆነ ዋሻው ውጪ የሚደረገው የቃላት ምልልስ የሚሰሙ ይመስላሉ፡፡ ምላሽ ግን አይሰጡም፡፡ ጋዜጠኞችም አይደሉም-አይቀርፁም-አይጠይቁም፡፡

ወንዶችም ሴቶችም ይገኙበታል፡፡ጠጋ ብዬ አንዷቸውን ምንድን ነው ነገሩ?ምንድንናቸው እነዚህ ዋሻ ውስጥ የታሰሩ ሰዎች?እነማንስ ናቸው አልኳቸው፡፡ ፈገግ ብለው አዩኝ፡፡ መነኩሴ ናቸው፡፡እማሆይ አልኳቸው፡፡ ቅድስተ ማርያም መስለው ታዩኝ፡፡ የዋሻው እስረኞች ናቸውም አሉኝ፡፡

ና ወደ ዋሻው ጠጋ በልና ታሪኩን ላጫውትህ አሉኝ፡፡ ተከትያቸው ሄድኩኝ፡፡ ረዥሙና አዝናችን የዋሻው እስረኞችን ታሪክ እንዲህ ሲሉ አጫወቱኝ፡፡

... መጀመሪያ ብዙ ሰዎች ነበርን፡፡ስፖርት እንሰራ ነበርን፡፡ ከዛ ጥቂቶች ሆነን ለቀጣይ ትምህርት ወደ ዋሻ ውስጥ ገባን፡፡እዚሁ ዋሻ ውስጥ ገባን፡፡ እዚሁ ዋሻ ውስጥ አስተማሪያችን ብዙ ትምህርት አስተምሮናል፡፡ፀሀይ ሳናይ በጨለማ ብዙ ተምረናል፡፡ትምህርቱም ማራኪ ነበር፡፡ ዋሻው እንደአሁኑ ዝግ አልነበረም፡፡በርና መስኮት ነበረው፡፡ በተወሰነው መልኩም ቢሆን የብርሃን ወጋገን ይገባበት ነበር፡፡

አንዳዶቹ ከውጭ የሚገባው ወጋገን አይናቸው ያቃጥላቸው ነበርና ጥቁር መነፀራቸውን አድርገው ከዋሻው ብዙም ሳይቆዩ ሸሽተው ወጡ፡፡ቀስ በቀስም ትምህርቱ ላይ ፍቅር አጡ፡፡ ተበላሹ፡፡የዋሻው ውስጥ ትምህርት መቋቋም አቅቶአቸው የተወሰኑ ተማሪዎች መውጣትና መሸሸን ተመልክቶ አስተማሪያችን ቀሪዎቻችን ይገመግመንና ያስተካክለን ነበርከዛስ አልኳቸው-እማሆይን?

ከዛማ

ለቀጣዩ ትምህርት እኔን ጨምሮ እዛ ከዋሻው ጀርባ ተክዘው የማይናገሩትን ያሉት ሰዎች ታያቸዋለሁ አይደል እነሱንና እኔን ከዋሻው ወጥተን ደጅ መማር ጀመረን ነበር፡፡ ምን ዓይነት ትምህርት አልኳቸው፡፡

ረቀቅ ያለና ጠለቅ ያለ

ትምህርቱ ከዋሻው ውስጥ ይልቅ ይሄ ረቀቅ ያለ ነበር፡፡ ዋሻው ውስጥ ግን አሁን ታስረው ያሉት ሰዎች ቀሩ፡፡ የዋሻው በር እንዴት እንደሚዘጋና እንደሚከፈት የምናውቀው ነገር የለም፡፡ አስተማሪችን ግን በቀላሉ በየጊዜው ይከፈተውና ይዘጋው ነበር፡፡ አንድ ቀን እኔና እነዛ የቆሙት ሰዎች ደጅ እየተማርን ሳለን የዋሻው በር መክፈቻና መዝጊያ እንዴት ነው ብዬ ጠይቄው ነበር፡፡በሩ በፓስወርድ/በይለፍ ቃል/ እንደሚዘጋና እንደሚከፈት ነግሮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ታዲያ ፓስወርዱን/የይለፍ ቃሉን/ አልያዛችሁትም?

ሳቅ አሉ እማሆይ፡፡ በጥያቄ አላጣደፍኳቸውም፡፡ ከዛስ- አልኳቸው?

እኛ ጥቂቶች ከዋሻው ውጭ ለተወሰነ ጊዜ ትምህርት እየተከታተልን ሳለን የዋሻው በር ለመክፈትና ለመዝጋት ግን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በቀላሉ የሚከፈትና የሚዘጋ ይመስላል-እባካችሁ ተጠንቀቁ ብሎን ነበር

አስታውሳለሁ ከዛች ቀን ጀምሮ ወደ ዋሻው ውስጥ በአካል ለማስተመር አልሄደም፡፡ ዋሻው ውስጥ የቀሩትን ተማሪዎች በአካል ሳይሁን በፕላዝማ ነበር የሚያስተምራቸው አሉኝ፡፡

አስተማሪያችሁ ታዲያ አሁን መጥቶ ዋሻው አይከፍተውም? ስል እማሆይን ጠየቅኩኝ

እሱ አይደለም ችግሩ፡፡ አስተማሪያችን እኛን ደጅ ትቶ ተማሪዎቹ ዋሻ ውስጥ እንዳሉ ድንገት ተሰውሯል አሉኝ እማሆይና ሌሎች ተክዘው የነበሩት ጓደኞቻቸው በጋራ፡፡

አሁን ከእማሆይ በተጨማሪ ሌሎችም ከእሳቸው ጎን ቆመው መናገር ጀምረዋል፡፡ለሁሉም አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ሰነዘርኩላቸው፡፡ አስተማሪያችሁ ማን ነበር ብዬ ጠየቁኳቸው?

በአንድ ቃል ረቡኒ ብለውኝ ቻው ብለው ወደፊት መንገዳቸው ቀጠሉ፡፡

ረቡኒ ደግሞ ምንድነው? አልኳቸው

እማሆይ ዞር ብለው ፈላስፋው ንጉስ ብለውኝ ጉዞቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ቀጠሉ፡፡ ከዋሻው አከባቢም ተሰወሩ፡፡

እማሆይና ጓደኞቻቸው ብቻ አይደለም ተሰላችተው ከአከባቢው የተሰወሩ፡፡ የከተማ ባህታዊያኑም ከስፍራው ባይሰወሩም ድምፃቸው ግን አጥፍተዋል፡፡ የዋሻው ውስጥ ሰዎች ግን አጥፍተዋል፡፡ የዋሻው ውስጥ ሰዎች ግን የተዘበራረቀ ድምፅ ማሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተለየ ነገር ባለመኖሩም እኔም ብሆን ስለፈላስፋው ንጉስ እያሰብኩኝ ዋሻውን ለደቂቃዎችም ቢሆን ተሰናበትኩኝ፡፡

-------------------------

የልጅነት ሰፈሬ እኔንም ቢሆን ከጫካው ገነት አስወጥታ በብሔራዊ ሙዚየምና በቤተመንግስቱ አከባቢ ኑሬዬን እንድመሰርት አድርጋኛለች፡፡ የአዲስ አበባ ዋሻም ከመኖሪያ ቤቴ ብዙም አይርቅም፡፡ቤቴ ገብቼ ልረፍ ወይስ ፈላስፋው ንጉስ ፈልጌ የዋሻውን ሚስጥር ላፈላልግ እያልኩኝ ሳስብ ከዋሻው አጠገብ ባለው ቤተክርስትያን ቅጥር ግቢ አንዱን ጥግ ይዤ ፀሎቴን ጀመርኩኝ፡፡

ድካሙንና የዋሻው ጨኸት ስልችት ብሎኝ ስለነበር ወዲያውኑ እንደሰመመን አይነት ሃሳብ ውስጥ ገባሁ፡፡ፈላስፋው ንጉስ የሚለው ቃል ስሰማው የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡የዛሬ 30-40 ዓመት የሰማሁትና የማውቀው ይመስለኛል፡፡የታላቁ ግሪካዊ ፈላስፋ ፕሌቶ ዘ ሪፐብሊክ በሚለው መፅሃፍ ውስጥ ስለዋሻው እስረኞች እንዲሁም ስለፈላስፋው ንጉስ የሚያወራ መፅሃፍን አንብቤአለሁ፡፡ የፕሌቶ ሪፐብሊክና ፈላስፋው ንጉስ ግን የአምሳያ/ስሙሌሽን/ ነው፡፡

ፈላስፋው ንጉስ ማንነህ? እባክህን ስማኝ መንገድህን ወዴት ነው?በየት በኩልስ ነው የተሰወርከው እያልኩኝ ተመስጬ ማውጠንጠን ጀመርኩኝ፡፡

የሆነ ድምፅ ተሰማኝ፡፡ሓይለኛ መብራት አየሁ፡፡የፀሐይ ጨረር ይመስላል፡፡ ፈላስፋው ንጉስ ማየት አልቻልኩም፡፡ የሆነ ሰው ግን ድምፁን እያሰማ አትልፋ ፈላስፋው ንጉስ እኔ ነኝ! ከኔ ምንድነው የምትፈልገው አለኝ

ስለዋሻው እስረኖች ልጠይቅህ ነው? ሰዎቹ ኮ ዋሻው ተዘግቶባቸዋል?ለምን አልኩት፡፡

ሁሉም እዛ ውስጥ እንዳሉ ተቆለፈባቸው? መክፈት አልቻሉም ብሎ በግርምት ተመልሶ ጠየቀኝ

አዎ ግን ደግሞ እማሆይና ጥቂት ሰዎች ግን ከዋሻው እንደወጡ በአይኔ አይቻለሁ አልኩት፡፡

እንግዲህ እድሜ ልኬን ደጋግሜ አስተምሪያቸዋለሁ፡፡የይለፍ ቃሉ አስቸጋሪ መሆኑን ቀደም ብዬ ተናግሬአለሁ፡፡ካልነፁ በቫይረስ ስታክ ያደርጋል፡፡ስለዚህ ንፅህና ቢኖራቸው ይከፈትላቸው ነበር፡፡ ተወው ይህ የራሳቸው ጉዳይ ነው አለኝ፡፡

እረ እባክሀ አትጨክንባቸው ባይሆን የይለፍ ቃሉን ስጠንና እንንገራቸው፡፡የሰው ልጅ እንዴት ዋሻ ውስጥ ይበሰብሳል፡፡ትንሽ አታስብም እንዴ?አልኩት፡፡

ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡በል ይሄን የምልህ በጥሞና አድምጥ አለኝ፡፡ ከግራዝማች እስከ ደጃዝማችነት ማዓርግ ይዘህ ሂድና ዋሻው ላይ በትነው፡፡እስረኞቹ ማዓርጉን ለመከፋፈል ሲሉ ዋሻውን ሰንጥቀው ይወጣሉ አለኝ፡፡

ይህ ማዓርግ ምን ያደርግላቸዋል፡፡ጠጋ ብዬ ስሰማኮ ዋሻ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሎሬትም ሆነ የዶክተርነት መጣሪያ መዓርግ አላቸው፡፡ ይህ አሁን በትንላቸው ያልከኝ መዓረግ ምን ያደርግላቸዋል አልኩት፡፡

ግድ የለህም ሁለት ወዶ የሚባል ነገር የለም ታየዋለህ አለኝ፡፡ ማዓረጋቸው ካገኙ በኋላ ደግሞ ወደፈልጉበት ይሄዳሉ፡፡ህዝቡም ማንነታቸው በገሃድ ያውቃቸዋል፡፡ዋሻውም ለዘላዓለሙ ይከፈታል፡፡ባይሆን እቺን ብራና መፅሃፍ ለነ እማሆይ ስጥልኝ ብሎ ብራናውን ወረወረልኝ፡፡

ግን እኮ ዋሻው ውስጥ የንሰሃ ጊዜ ደርሳለች ተዘጋጁ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ አልኩት

ሁለት ወዶ ቁርባን የለምበልልኝ አለኝ፡፡

በመጨረሻም ፋላስፋው ንጉስ እንዳለኝ የሹመት መዓረጎችን ይዤ ወደ ዋሻው ተጠጋሁ፡፡

የምስራች ዜና ለዋሻው እስረኞች፡፡ ይህ የምስራች ቀጥታ የተላከላችህ ከፈላስፋው ንጉስ ነው፡፡ አልኳቸው፡፡በድንገት ዋሻው ውስጥ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ያን ሁሉ ጩኸትና ርግጫ በአንዴ ቆመ፡፡ ገረመኝ፡፡ ጊዜ ሳላቃጥል ከግራዝማችነት እስከ ደጃዝማችነት ማዓረግ በተንኩላቸው፡፡ከዋሻው ውጭ ለነበሩ ሰዎችም የባላምባራስነት መዓርግ እንደ ሰርግ ከረሜላ በተንኩላቸው፡፡

ዋሻው ድንገት ተከፈተ፡፡ እስረኞችም የተላከላቸው መዓርግ ተከፋፍለው ወደየ ቤታቸው አመሩ፡፡የውጪዎቹም የባላምባራስነት መዓርግ ተቀበሉ፡፡

ድፍን የአዲስ አበባ ህዝብ በነዚህ የዋሻ እስረኞች ጉዳይ ላይ መነጋገር ጀመረ፡፡ጉድና ጅራት ወደኋላ እያለ ወደ ዋሻው መትመም ጀመረ፡፡

እማሆይና ጓደኞቻቸውን ፍለጋ ቀጠልኩኝ፡፡ድንገት ከቤተክርስትያኑ ጀርባ አገኘኋቸው፡፡ ብራናውን ሰጥቼ ፊቴን መለስ ሳደርግ ብራቮ!እንዳለኝ ከህልሜ ነቃሁኝ፡፡ ለካስ ይሄ ሁሉ ቅዠት ህልም ነበር አልኩኝ፡፡በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ-ሰዓሊነ ለማሪያም፡፡

 

Back to Front Page