Back to Front Page


Share This Article!
Share
የለዉጥ ሂደት ህግ የመጣስ መብትን አያጎናፅፍም!

የለዉጥ ሂደት ህግ የመጣስ መብትን አያጎናፅፍም!

ከእገሌ(የህወሓት አባል)

09-21-18

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎች ታሪክ እንደሚያስረዳን ስራ ላይ የዋለዉን የኢፈደሪ ህገመንግስትና ህገመንግስቱን መሰረት አድርገዉ የወጡትን ህግጋት አᎂልቶ ያለመተግበር ጉዳይ አባል የሆንኩበትን ህወሓት/ኢህአዴግ መሰረታዊ ያለመተግበር ችግር እንደሆነ በመግለፅ ሲያብጠለጥሉ የኖሩበት አጀንዳ ነዉ። ዳሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለመብቶች መከበርና ስለፖለቲካ ምህዳር መጥበብ አጥብቀዉ ሲያወግዙ የኖሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸዉ ሲያሰሙ የኖሩትን ወቀሳ እና ስህተት ኢህአዴግ ከመጠን በላይ ለጥጦ በሰጣቸዉ በራሱ ሜዳ ጭምር ገብተዉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሀገርንና ህዝብን ለብጥብጥና ለህልፈት ሲደርጓት ማስተዋል ጀምረናል። ከሚገባዉ በላይ ቸር ሆኖ ምህዳሩን ያሰፋላቸዉን ኢህአዴግን በህይወት እንደሌለ ወይንም ህግና ስርአት የማስከበር አቅም እንደሌለዉ ቆጥረዉ ጉዳት የማድረሳቸዉ ጉዳይ ሶስተኛ ዙር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድናዉጅ ከማስገደዱ በፊት ሊታሰብበት ስለሚገባዉ የማስጠንቀቂያ ደወል ያስፈልገዋል። ህገመንግስታዊ ስርአትን፣ ህዝብንና የአገር ክብርን የማዋረድ የመጨረሻ ግብ የአንድነታችንንና የአብሮነታችንን መሰረት ከስር መሰረቱ መናድ ስለሚሆን እየተፈፀሙ ያሉትን የስርአት አልበኝነት ተግባራት ከህገመንግስታችንና ሌሎች መሰረታዊ ህግጋት አንፃር ታይተዉ ገደብ ሊበጅላቸዉ ይገባል።

 

1. እራስን በራስ የማስተዳደር መብት መሰረታዊ ትርጉም-ከእነ ሙሉ መብቱና ግዴታዉ ነዉ"

ኢህአዴግ የተጋለለትና ከኢፌዴሪ ህገመንግስት የማእዘን ድንጋዮች አንዱ የሆነዉ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት መሰረታዊ ትርጓሜ ሁለት ገፅታ አለዉ። አንደኛዉ ገፅታ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ማጎልበትና እያጠናከሩ መሄድ ነዉ። ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን እያጠናከሩ መሄድ ሲባል፦

የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት፣ቋንቋ፣ባህልና ታሪክ የማረጋገጥና የማሳደግ መብት

Videos From Around The World

ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር መሆኗን አምኖ መቀበልና ማክበር

ከሌሎች ብሄር በሄረሰቦች ጋር በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በእኩልነት የመሳተፍ እና የዉክልና መብትን ማረጋገጥ

በኢፌዴሪ ህገመንግስት መሰረት በሚፈጠሩ ክልላዊ የአስተዳደር ስርአቶች የምንወክለዉን ህብረተሰብ ከድህነት እና እርዛት ለማዉጣት ምርታማነትን ማሳደግ፣ የሀብትና የምርት ተጠቃሚ መሆነን እና ፍትህንና ዲሞክራሲን ማረጋገጥ የሚልቱን በቁንፅሉም ቢሆን ያካትታል።

በእያንዳንዱ ክልል የሚከናወኑት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና የፍትህ ጉዳዮች ከላይ በተጠቆሙት የዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መነፅር የተቃኙ ከሆኑ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጌዴታዎችንም ያካተተ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ እና ህገመንግስታዊ ስርአትም ሆነ በድርጅታችን ኢህአዴግ አስተሳሰብ እራስን በራስ የማስተዳደር መርሆ መብትን ብቻ ሳይሆን ግዴታዎችንም አጣምሮ የያዘ ነዉ። ስንተረጉመዉ ..ከእነ ሙሉ መብቱና ግዴታዉ. በሚል እንጂ መብቱን ብቻ በመቆንፀል ሊሆን አይገባም። መብቱን እያጣጣሙ ከግዴታዉ መሸሽ ማለት በኢፌዴሪ ህገመንግስት የሰፈረዉን አንድ የኢኪኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባት ዘላቂ ግብን ለመተግበር ዝግጁ አለመሆን ማለት ነዉ። በዚህ መነፅር ተመልክተን ከተገበርነዉ የብሄራዊ መግባባት እንደዚሁም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር መርሃችንና ራእያችን የተሳካ ይሆናል።ስለሆነም በሽግግሩ ወቅት በአንዳንድ ፅንፈኛ ብሄርተኞች አማካኝነት ተስተዉሎ የነበረዉ በተወሰኑ ብሄረሰቦች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በአሁኑ ጊዜ ተቃዋሚ ሀይሎችን ወደሀገር እንዲገቡ እየተገበርነዉ ያለነዉን የለዉጥ ሂደት ተከትሎ እየተደገመ ይመስላል። ቀደም ያሉትን ጥቃቶች ለጊዜዉ እናቆያቸዉና ሁለተኛዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካነሳንበት ጊዜ ጀምሮ እንኳ የኦሮሚያን እና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች የፅንፈኛ ብሄርተኞች ጥቃቶች ሲፈፀሙ ተስተዉለዋል። የሰዉ ህይወትና ሀብትና ንብረት ወድᎂል።የእነዚህ ጥቃቶች መነሻና ተልእኮም ከዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ያፈነገጠ አስተሳሰብ አራማጆች መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። እንዲህ አይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙም እራሳቸዉን በራሳቸዉ እንዲያስተዳድሩ ሉአላዊ ስልጣንና መብት ያላቸዉ የክልል መስተዳድሮች እና በምርጫ የህዝብ ይሁንታ ያገኙ መሪ ድርጅቶች ግዴታቸዉን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። በዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ፅንሰሃሳብ መሰረት በክልሎች የሚፈጠሩ ልማቶች የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆኑት ክልሎቹን የሚወክሉት ብሄረሰቦችና አስተዳደሮች እንደመሆናቸዉ ሁሉ በሚያስተዳድሩትና ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት በሆኑበት ክልል ብሄር ተኮር ጥቃት እንዳይደርስ የመከላከልም ሆነ ተፈፅሞ ሲገኝ እርምጃ የመዉሰድ ሀላፊነትና ግዴታ የክልሎቹ መስተዳደሮች እና መሪ ድርጅቶች መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነዉ። በክልሎች የሚኖሩ መጤም ሆኑ ኢንዲጂኒየስ ብሄር ብሄረሰቦች ከሁሉም በፊት እንደከለላና መከታ የሚቆጥሩትና ተማምነዉበት የሚኖሩት ሉአላዊ ስልጣን የተሰጠዉን ክልላዊ መስተዳድር እና መሪ ድርጅት እንጂ በሁለተኛ ደረጃ ያለዉንና በሁሉም ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የመግባት ህገመንግስታዊ ስልጣን ያልተሰጠዉን የፌዴራል መንግስት አይደለም። መጤ ብሄረሰቦች የተወለዱባቸዉ ሌሎች ክልሎች የመስተዳድር አካላትም ቢሆኑ ድርጊቱ እንዲታረም ከማዉገዝና ከማሳሰብ ዉጭ በክልሎች ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት መብት የላቸዉም። ስለሆነም ጥቃት የደረሰባቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ችግሮቻቸዉን ለክልላዊ መስተዳድሮች ከለላና ጥበቃ እንዲደረግላቸዉ በተለያዩ አግባቦች የመጠየቅና ለደረሰባቸዉ ጉዳት ካሳ የማግኘት ህጋዊና ህገመንግስታዊ የመጠየቅ መብታቸዉ ሊረጋገጥላቸዉ ይገባል። የክልሎች መንግስትና መሪ ድርጅትም ቢሆን የፌዴራል መንግስትንም ሆነ የሌሎች ክልሎችንና መሪ ድርጅቶችን ማሳሰቢያና ወቀሳ ሳይጠብቁ የክልሉ ብሄር ተወላጅ በሆኑትም ሆነ ባልሆኑት ነዋሪዎቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሚያስችል ተከታታይ እና የተደራጀ ፖለቲካዊ ስራ መስራት እና ተፈፅሞ ሲገኝም ለወደፊት እንዳይደገም ትምህርት የሚሰጥ እርምጃ የመዉሰድ ግዴታ አለባቸዉ። ይህን ማድረግ ያልቻለ ክልላዊ መስተዳድር እና መሪ ድርጅት ከእነ ሙሉ መብቱ እና ግዴታዉ. የሚለዉን እራስን በራስ የማስተዳደር መርህ አᎂልቶ እንዳልፈፀመ ይቆጠራል። የዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መርህን እየተገበረ እንዳልሆነም ያስቆጥረዋል። ከመጀመሪያዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ጀምሮ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እየገባ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ላደረጋቸዉ ጥረቶች በጠባብ እና ፅንፈኛ ብሄርተኞች ዘንድ በጣልቃገብነት ስም ሲወገዙ የተስተዋሉበት አንዱና መሰረታዊ መንስኤም የክልል መስተዳድሮችና መሪ ድርጅቶች እራስን በራስ በማስተዳደር ስልጣን ክልል ዉስጥ ሆነዉ ብሄር ብሄረሰቦች በመረጡት ክልል በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ የመኖር እና ሀብት የማፍራት መብታቸዉ እንዳይጣስ የመከላከል ግዴታቸዉን አᎂልተዉ መወጣት ባለመቻላቸዉ ነዉ። ስለሆነም በእርግጥም በአዲሲቷ ፌዴራላዊትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን አስተሳሰብ ያᎂላ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የቆረጥን እስከሆንን ድረስ ክልሎችና መሪ ድርጅቶች የፌዴራሊዝም ስርአታችንን ከእነ ሙሉ መብቱና ግዴታዉ ተቀብለዉ የመተግበር ሀላፊነታቸዉን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ሲሳናቸዉ በህገመንግስቱና ህገመንግስቱን መሰረት አድርጎ በወጣዉ አዋጅ ጣልቃ የመግባት ስልጣን መሰረት የፌዴራል መንግስት ፌዴራላዊ ስርአቱን እና የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለመታደግ ሲባል የሚያደርገዉን ጣልቃ ገብነት በመደገፍ የጠባብና ፅንፈኛ ብሄርተኞችና ጥቃት ከማዉገዝ ባለፈ እርምጃ መዉሰድ ይጠበቅበታል።

 

2. ሰንደቅዓላማ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንፃር

ኢህአዴግ እና የኢፌዴሪ መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሀይል ለማፍረስ ተሰልፈዉ የነበሩትንና ህዝብንና አገርን ሲያደሙ የኖሩትን ይቅርታ በመጠየቅ ወደሀገር ቤት እንዲገቡ ጋብዟል። ይህም በፍርድቤት ዉሳኔ በኢትዮጵያ የምርጫ ስርአት ተሳታፊ እንዳይሆን እገዳ የተጣለበትን የፖለቲካ ድርጅትና አባላትንም ያካትታል። ይህ የለዉጥ ሂደት በህግ እና ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች መርህና አስተሳሰብ መሰረት ብቻ ይፈፀም ቢባል ኖሮ የበደሉትን አገርና ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ የነበረባቸዉ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ ተሰልፈዉ የነበሩት ወገኖች ናቸዉ። ሆኖም ግን ኢህአዴግና መንግስታችን እነርሱ ሊያደርጉት ይገባ የነበረዉን ይቅርታ የመጠየቅ የህግ ግዴታ በመፈፀም ግማሽ መንገድ ሳይሆን በተጠለሉበት ሀገር ድርስ ጭምር ሙሉ መንገድ ተጉዞ ተቀብሏቸዋል። ይህን ተግባር በይሁንታ ልናልፈዉ ብንችልም እንኳ ወደሀገር ቤት ከገቡ በኋላ እየፈፀሙ ያሉትን ህገመንግስቱንና ህገመንግስቱን መሰረት አድረገዉ የወጡትን ህግጋት የመጣስ ተግባር በዝምታ አናልፈዉም። አንድ በትጥቅ ትግል ህገመንግስታዊ ስርአትን ለማፍረስ ተሰማርቶ የነበረ የፖለቲካ ፓርቲ እና አባላቱ በተደረገለት ይቅርታ ወደሀገር ቤት ሲገባ ቀድሞ ለብሶት የነበረዉን የፖለቲካ ተልእኮ መጠሪያና መገለጫ አዉልቆ መጣል ይጠበቅበታል። ቀደም ሲል ለተሰማሩበት ዓላማ ሲጠቀሙበት የነበረዉን ሰንደቅ ዓላማ፣አርማ፣የፖርቲ ስያሜ እና ሌሎች ነባር ሁኔታዎችን ያለመጠቀም ግዴታን ከአዋጅ ቁጥር 573/2002 አንፃር ብንቃኘዉ ተገቢ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ግንቦት 7 የተሰኘ የፖለቲካ ድርጅት በተደረገልኝ ይቅርታ ምክንያት ከእንግዲህ የትጥቅ ትግል አቁሜአለሁ. ብሎ ካወጀ ለትጥቅ ትግል ዓላማ ሲጠቀምበት የኖረዉን የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜ፣ ሰንደቅዓላማ እና አርማ እንዳይጠቀም ህገመንግስትም አዋጅ ቁጥር 573/2002 ያስገድደዋል። እንዴት ለሚለዉ ጉዳይ የሚከተለዉን ድንጋጌ መመልከቱ በቂ ይሆናል። በአዋጅ ቁጥር 573/2002 አንቀፅ 27/2/ // መሰረት የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አርማ እና ሰንደቅዓላማ ከሌሎች ፓርቲዎች አርማና ሰንደቅዓላማ ጋር የማይመሳሰል እና የጦረኝነት ወይንም ሌላ ህገወጥ ድርጊት መልእክት የማያስተላልፍ መሆን ይኖርበታል። ስለሆነም ግንቦት 7 የተሰኘዉን የፓርቲ ስያሜ እና ይህን ፓርቲ የሚወክለዉን አርማና ሰንደቅዓላማ በህዝብ የተመረጠ መንግስት በሚያስተዳድራቸዉ ከተሞችና አጠቃላይ የሀገሪቱ ክፍሎች ለቅስቀሳና ሌሎች ፖለቲካዊ ተልእኮዎች እንዲዉል መፍቀድ ፓርቲዉ የቀድሞዉን ህገወጥ ተልእኮ በሀገር ዉስጥ ገብቶ እንዲፈፅም እንደተፈቀደለት ይቆጠራል። ይህ እንዲሆን የመፈቀዱ እና በመሆኑም የሚከተለዉ አደጋና ጉዳት ደግሞ ተጠያቂ የሚያደርገዉ የፖለቲካ ፓርቲዉን ብቻ ሳይሆን ህጋዊ ስልጣን የያዘዉን መንግስትና መሪ ድርጅት ጭምር ነዉ። ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ የተቋቋመ መንግስት ህገመንግስታዊ ስርአቱን እና የአገሪቷን ህግጋት የማስከበር ተቀዳሚ ሀላፊነት ተጥሎበታል። ይህን አመክንዮ ይበልጥ ለማጠናከርም የአዋጁን አንቀፅ 10/4/ ድንጋጌ መመልከጹ ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ያወጀ የፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ የማይችል መሆኑን ነዉ። ግንቦት 7 ደግሞ በቀድሞ አርማዉ፣ሰንደቅዓላማዉ እና ስያሜዉ ሊመዘገብም ሆነ ወደሀገር ቤት ከገባ በኋላ ሊጠቀምበት የሚያስችል ህጋዊ መሰረት የለዉም። ከዚህ በተጨማሪም ማንኛዉም የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ዉስጥ መንቀሳቀስ የሚችለዉ በአዋጅ ቁጥር 573/2002 አንቀፅ 7 መሰረት በቦርዱ ተመዝግቦ የህጋዊ ሰዉነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሲያገኝ ብቻ ነዉ

የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጅ ለምዝገባ ሂደት በመስፈርትነት ካስቀመጣቸዉ ተጨማሪ መስፈርቶችና ጌዴታዎች ዉስጥ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከአባልነት እስከአመራርነት ለሚይኖረዉ የሰዉ ሀይል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለዉ መሆኑን የተረጋገጠ ግዴታ ነዉ። ከዚህ አኳያ አሁንም ግንቦት 7 የተሰኘዉን የቀድሞዉን የትጥቅ ትግል አዋጅ ነጋሪ ቡድን እንደምሳሌ እንዉሰድና ስያሜዉን ቀይሮ በፖለቲካ ፓርቲነት ልመዝገብ ቢል እንኳ አባላቱና አመራሮቹ የኢትዮጵያዊ ዜግነት ባለመብት መሆናቸዉን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል(አንቀፅ 11/4)

ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የአዋጅ ቁጥር 573/2002 ከልካይ እና አስገዳጅ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ቀደም ሲል የትጥቅ ትግል አዉጀዉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸዉ ወደሀገር ከገቡ በኋላ በህገመንግስትና በአዋጅ እዉቅና ያገኘዉን የኢፌዴሪ ሰንደቅዓላማ እዉቅና የሚነፍግ የራሳቸዉን ሰንደቅዓላማ ይዘዉ በሰላማዊ ሰልፎች እና ሌሎች እንቅስቃሴዎቻቸዉ በይፋ ሲያዉለበልቡ መታየት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደማለት ነዉ። የኢፌዴሪ ህገመንግስት እና የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ስለኢፌዴሪ ሰንደቅዓላማ ይዘት እና አጠቃቀም ደንግገዋል። ከድንጋጌዉ ይዘት የኢፌዴሪ ሰንደቅዓላማ አርማ እንደሚኖረዉና ይህም መከበር እንዳለበት እንደዚሁም ከሰንደቃላማዉ ይዘትና አጠቃቀም ጋር ተፃራሪ የሆኑ ተግባራት ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ በግልፅ ይደነግጋሉ። ግንቦት 7 ጨምሮ በአሜሪካ ለኖሩት ተቃዋሚ ሀይሎች በነበሩበት ሀገር ለሰንደቅዓላማ የሚሰጠዉን ክብር ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪዉ ማርዳት ይሆናል። አሁን የምንነጋገረዉ ሰንደቅዓላማዉን ስለመዉደድና አለመዉደድ አይደለም። የሚያነጋግረን ጉዳይ ህገመንግስታዊ ስርአት ስለመጠበቅና አለመጠበቅ ጉዳይ ነዉ። የነበሩበትን አገር የአሜሪካን ሰንደቅዓላማ እንዲከበር ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ለህግመንግስታዊ ስርአታቸዉ መከበር ያላቸዉ ቀናኢነት ነዉ። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች መቼም ቢሆን ሊሳካላቸዉ ያልቻለዉ ጉዳይ በአንድ በኩል ስለሰዉ ልጆች መብቶች እና ስለህግና ህገመንግስታዊ ስርአት መከበር እያማረሩ በሌላ በኩል ዋነኛዉ የህግ ጥሰት ፈፃሚዎች እነርሱ ሆነዉ የመገኘታቸዉ ጉዳይ ነዉ። ስለሆነም ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ካርድን ሳይዙ እና ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የኖሩትን የትጥቅ ትግል ካባ ማዉለቃቸዉን በህጋዊ መንገድ ሳያረጋግጡ ወደኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ሰንደቅዓላማችንን የሚያዋርድ እና የሚያንቋሽሽ ወይንም ደግሞ ያልተቀበሉት መሆናቸዉን የሚቀሰቅስ ሌላ አይነት ሰንደቅዓላማ በአደባባይ ማዉለብለብ እና በተለያዩ ሁኔታዎች መጠቀም በስህተት ላይ ስህተት መፈፀም ነዉ። ይህ ተግባራቸዉ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኞችን ወደስጋት እየከተተ ከዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ወደ ጠባብ/ፅንፈኛ ብሄርተኝነት ሊያሸጋግራቸዉ ይችላል። የኢፌዴሪ ሰንደቅዓላማችንን እዉቅና የሚነፍጉ ተግባራትን በይፋ መፈፀም ማለት ህገመንግስታዊ መሰረት ያለዉን ፌዴራላዊ ስርአታችንን የማፍረስ አንዱ ተግባር ተደርጎ ይቆጠራል። ማንኛዉም የፖለቲካ ድርጅት በኢትጵያ ዉስጥ ማምጣት የሚፈልገዉ ህገመንግስታዊና መዋቅራዊ ለዉጥ ካለ ሊፈፀም የሚችለዉ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ተከትሎ ብቻ ነዉ። ከዚህ ዉጭ የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች እና የማነሳሳት ተግባራት ከዲሞክራሲያዊ ብሄርተኞች የአፀፋ እርምጃ ይገጥማቸዋል። በአንዳንድ ክልሎች የተስተዋሉት የሰላምና መረጋጋት እጦቶች አንዱ ምክንያትም ፌዴራላዊ ስርአታችንን ለማፍረስ የሚከተሉ ሀይሎች ያመጡብን ጦስ እና ይህቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም በሚል ብሂል ስርአቱን ለመከላከል የተወሰዱ ስጋት የወለዳቸዉ አፀፋዊ ግብረመልሶች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ከባድ አይሆንም።

3. ፖለቲካ በርእዮተዓለም እንጂ በማህበራዊ ግንኙነት አይመራም!

በመንግስታችንና መሪ ድርጅታችን ግንባር ቀደም ተነሳሽነት በሀገራችን ብሀር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል የተጠናከረ አንድነት እንዲሰፍን የተጀመረዉ የለዉጥ መንፈስ የሚደገፍ ነዉ። በዚህ ሂደት የሚወደሱም ሆነ የሚወቀሱ ቢኖሩ የብሄራዊ ድርጅቶች ግንባር የሆነዉ ኢህአዴግ እንጂ ግለሰቦች አይደሉም። ግለሰቦች የመሪነት ሚና እንዳላቸዉ ቢታወቅም እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ የተፈፀሙት ተግባራት በድርጅታችን ዉስጥ በመሪነት ደረጃም ሆነ በአባልነት ደረጃ ያሉ ግለሰቦች ስለፈለጉ ብቻ የተፈፀሙ አይደሉም። ድርጅታችን ከምንም በላይ በጋራ ሀላፊነት እና የዉሳኔ አሰጣጥ ስርአት የሚያምንና የሚመራ ነዉ። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ የትጥቅ ትግል አዉጀዉ የነበሩ ሀይሎች ኢህአዴግ የተመረጠበት ፖሊሲና ፕሮግራም የጠፋ እስኪመስለን ድረስ የድርጅታችንን መጫወቻ ሜዳ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረዉ በመስራች ብሄራዊ ድርጅቶች መካከል የመናቆር ተልእኮአቸዉን በመፈፀም ሂደት ላይ ናቸዉ። የአሁኑን ኢህአዴግ ወይንም አመራር እንደ መልአክ የቀድሞዉን/የቀድሞዎቹን/ ደግሞ እንደሰይጣን ወይንም ወንጀለኞች የሚቆጠሩበት ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ ተጠምደዋል። ሁሉም ነገር በአንድ ግለሰብ ወይንም ግለሰቦች ይሁንታ ብቻ እንደተከናወነ ተቆጥሮ ነባር እና አዲስ በሚል ፈሊየጥ የማጥላላት ዘመቻ እንዲፈጠር ያደረግነዉ ከብዙሃን መገናኛዎቻችን ጀምሮ እኛዉ እራሳችን በመሆናችን በህዝብ ግንኙነት ስርአታችን ላይ የማስተካከያ እርምጃ መዉሰድ ይጠበቅብናል።

ከተቃዋሚ ሀይሎች ጋር አብሮና ተባብሮ መስራት እና የድርጅቱን መጫወቻ ሜዳ በሌሎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ቸል ብሎ መመልከት ለየቅል ናቸዉ። በአንድ በኩል የትጥቅ ትግል ያወጀ፣ፌዴራላዊንና ህገመንግስታዊ ስርአትን የማፍረስ ፖሊሲና ፕሮግራም በሌላ በኩል ደግሞ በህዝብ ይሁንታ ስልጣን የያዘ መሪ ድርጅት ፖሊሲና ፕሮግራም ተደበላልቀዉ ሊፈፀሙ አይችሉም። ምክንያቱም እሳትና ጭድ በእንድ አልጋ ሊተኙ ስለማይችሉ ነዉ። ተቃዋሚ ሀይሎች ላለፉት ዓመታት ዲሞክራሲያ ብሄርተኞችን ከዉጭ ሆነዉ ለማፈራረስ ያደረጉት ሙከራ ህዝባዊ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በአሁኑ ጊዜ አዲስ ህይወት የሚገኘዉ ከዉስጥ ወደዉጭ በሚፈጠር የግፊት ሀይል ወይንም መፈረካከስ ነዉ የተሰኘዉን የእንቁላል ብሂል እየተከተሉ ስለሆነ ከወዲሁ መስመራችንን የማጥራት ግዴታና ሀላፊነት አለብን። ይህ ሀላፊነት የእኛዉ የኢህአዴጎች እንጂ ቀድሞዉንም ህልዉናችንን የማይፈልጉት ተቃዋሚ ሀይሎች ሊሆን አይችልም። ጨዉ ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነዉ ብለዉ ይጥሉሃል እንደሚባለዉ የቀድሞ አንድነታችንን አጠንክረን ለማስቀጠል መጣፈጥና ከአፍራሽ ግብረሀይሎች ጋር የሚኖረንን የግንኙነትና አብሮ የመስራት ድንበር በአግባቡ ማበጀት ያለብን እኛዉ ራሳችን ነን። የኢህአዴግን/ የብሄራዊ ድርጅቶችን ፕሮግራምና ፖሊሲ የሚወድ ካለ ምርጫዉ በፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ መስፈርቶች መሰረት ከኢህአዴግ ብሄራዊ ድርጅት ጋር በህጋዊ መንገድ መዋሃድ ብቻ ነዉ። ከዚህ በመለስ ስራ ላይ በዋለዉ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የመመካከሪያ የጋራ መድረክ አማካኝነት በጋራ መስራት ይቻላል። አንድም ዉህደት መፈፀም ነዉ አለያም የየራሳችንን ርእዮተዓለም አስጠብቀን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እየተመካከሩ ለሀገር ልማት እና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ስራ ላይ የዋለዉን የጋራ መድረክ አጠናክሮ ማስቀጠል ነዉ። ለሁሉም አይነት ግንኙነቶች ስርአትና ህግ ተበጅቶለት ሳለ የብሄራዊ ድርጅት/የኢህአዴግ አባልነትን፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን እና የልማታዊ መንገስት አስተሳሰብን በይፋ መናገር እንደፀያፍ/ታቡ/ እስኪያስቆጥርብን ድረስ የመጫወቻ መድረኩን ለአጥፊዎቻችን አሳልፎ መስጠት ግን እራስን በራስ የማጥፋት ወንጀል እንደሆነ ልንገነዘበዉ ይገባል። ፖለቲካ በአይዲዮሎጂ እንጂ በማህበራዊ ግንኙነት አይመራም። በመጠፋፋት ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ርእዮተዓለም ተከታዮች ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸዉ ብቻ በአንድ አልጋ ላይ እንዲተኙ ማድረግ አይቻልም። ለምሳሌ በአንድ በኩል የአሀዳዊ አወቃቀር ወይንም ፕሬዚደንታዊ ስርአተ መንግስት አራማጅ በሌላ በኩል የፌዴራላዊ አወቃቀር ወይንም ፓርላመንታዊ ስርአተመንግስት አይዲዮሎጂ አራማጅ በህዝብ ምርጫ ከተሸናነፉ በኋላ የአሸናፊ ድርጅቱን ፖሊሲና ፕሮግራም ለማስፈፀም በአንድ የመንግስትነት አልጋ ላይ እንዲተኙ የምናደርግ ከሆነ ቀድሞዉንም የብዙሃን ፓርቲዎች ህልዉና እና የዉድድር ስርአት ባላስፈለገን ነበር። በዚህ ሁኔታ በሚፈፀም የድመራ ስራ ዉጤቱ ኔጌሽን ኦፍ ኔጌሽን ኢዝ ኔጌሽን የሚሰኘዉን የሂሳብ ቀመር የሚሰጥ ይሆናል። በዉስጣችን አሁን ያለዉን የፖለቲካ አይዲዮሎጂና ፖሊሲ የማይደግፍ ቢኖር እንኳ የሚኖረዉ አማራጭ ከድርጅቱ ወጥቶ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት ብቻ ነዉ።

ከኢፌዴሪ ህገመንግስት ስራ ላይ መዋል በኋላ ቅይጥ የተሰኘ የፖለቲካ ድርጅት ህጋዊ ሰዉነት አግኝቶ ነበር። በወቅቱ ከነበሩት አባላት አንዱን የፓርቲዉን መመስረት ምክንያት፣ስያሜ እና ዓላማ ምን እንደሆነ ጠየቅኩት። አባላቶቹ በኢትዮጵያ ካሉት ከሁለት ብሄረሰቦች ወላጆች የተወለዱ በመሆናቸዉ እንደሆነ ነገረኝ። ማለትም ፓርቲዉ በፖለቲካ ርእዮተዓለም እና የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የተፈጠረ ሳይሆን በተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ ተራክቦ ፍላጎት ላይ አተኩሮ የተመሰረተ ነዉ። የሀገርንና የብዙሃን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ያለፉ አገዛዞች የዉድቀት ምክንያት እና ለሀገር ልማትና ብልፅግና በሚኖዉ የፖለቲካ ርእዮተዓም ፋይዳ ላይ የማይመሰረት አስተሳሰብና ድርጅት ብዙ ርቀት አይጓዝም። ቅይጥ የተሰኘዉ የፖለቲካ ፓርቲ ከሌሎቹ ህጋዊያን ፓርቲዎች ቀድሞ የጠፋበት ምክንያትም ረጅም ርቀትና ለዉጥ በሚያመጣ ርእዮተዓለም ሳይሆን እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ በማህበራዊ ግንኙነት/በድመራ ዉጤት/ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነዉ። ከዚህ አኳያ በኢህአዴግ ዉስጥ ኢህአዴግን በርእዮተዓለም ሳይሆን በጣም ጠባብ በሆነ የማህበራዊ ግንኙነት አስተሳሰብ እንዲመራ የሚፈልጉ ቢኖሩ የእነርሱ መድረክ ኢህአዴግ ሳይሆን ቅይጥ የተሰኘዉን የፖለቲካ ድርጅት ህይወት እንዲዘራ በማድረግ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲን በማስመዝገብ የሚገኝ መሆን አለበት ።ፖለቲካ በርእዮተዓለም ላይ በተመሰረተ ፅኑ እምነት እንጂ ግለሰቦች ባላቸዉ ጠባብ የሆነ ማህበራዊ ግንኙነት ምክንያት ሊመራም ሆነ ሊለወጥ አይችልም።

Back to Front Page