Back to Front Page


Share This Article!
Share
ለውጥ ሁሌም ያስፈልጋል።

ለውጥ ሁሌም ያስፈልጋል።

ፀሐፊ ፣ ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ)

ወረሐ፣ ሐምሌ 2010/2018.

     በመጀመርያ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ምስጋና ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ለማስተላለፍ ተካሄዶ በነበረው ትዕይንተ ህዝብ ላይ ሀላፊነት በማይስማቸው እኩይ ሰዎች በፈፀሙት የቦምብ ፍንዳታ ምክንያት ለሞቱት ወገኖቼ ነፍሳቸው ፈጣሪ በገነት ያኖር ዘንድ የዘውትር ፀሎቴ ነው። አንዲሁም ከላይ በተጠቀሰው ዕለት አካላዊ ጉዳት ላጋጠማቸው ሁሉ ብርታቱ ይስጥልኝ እላለሁ ። ድርጊቱ ትርጉም አልባ ከመሆኑም በላይ በወገን ይፈፀማል ተብሎ የማይገመት አሳፋሪና አስነዋሪ ህዝብም ያስቆጣ ድርጊት ነበር።

     የለውጥ ይዘትና አይነት ቢለያይም ሰላማዊ ለውጥ ሁሌም ያስፈልጋል ። ለውጥ የበሰለ አስተሳሰብ ውጤት ነው። ያለለውጥ የሚኖር ማህበረሰብ የለም። ጥያቄው ምን አይንት ለውጥ የሚለው ነው። ለውጥ ሲባል የኢኮኖሚ ፣የልማት ፣የማህበረሰብ አስተሳሰብ ፣እንዲሁም የስርአት ለውጥ ሊሆን ይችላል። አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ ለበርካታ አስተያየቶች ተጋላጭ ሆነዋል ።በአንድ በኩል በበጎ ገፅታ በሌላ ጎኑ ደግሞ በቅሬታ፣ ብዥታና ጥርጣሬ የታጀበ ይመስላል ።እዚህ ላይ የግሌ እይታ የመደመርን ሃሳብ በበጎ ጎኑ ከሚያዩት ውስጥ ነኝ።ግላዊ ምክንያቶቼ በዚህ ፅሁፍ ይገለፃሉ ። አሁን በኢትዮጵያ አየመጣ ያለው ለውጥ ለኢትዮጵያ አንድነት ፣ልማትና ብልፅግና ወሳኝነት አለው። እዚህ ላይ የለውጡ ባለቤት ማን ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል።በእኔ እይታ የለውጡ ባለቤት ማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል ሲባል ምን አይነት ለውጥ የሚል ሌላ ጥያቄ ይነሳል። መልሱ ሰላማዊ ለውጥ የሚለው ይሆናል። ህዝቡ የስርአት ለውጥ አልጠየቀም። የስርአት ለውጥ መጠየቅ እና የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ጥያቄ  ትርጉማቸው ለየቅል ነው። ላለፉት 27 አመታት የኢህአዴግ መር መንግስት በርካታ መልካም የልማት ሥራዎች ሠርተዋል ።ህዝቡም መንግስት ለስራቸው ስራዎች እውቅና መቻር ብቻ ሳይሆን ያመስግናልም። ከደርግ ስርአት ድህነት የተረከበ የኢህእዲግ መንግስት በፍጥነት ከድህነት ለመውጣት የተሄዱ ሂደቶች መልካም ፍሬ አፍርተዋል ።በማህበራዊ ልማትም በተመሳሳይ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ርቀት ተሄደዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት  የ 30 ከፍተኛ ተቋማት (Universities) ባለቤት ናት። በተመሳሳይ በጤናው ዘርፍም መንግስት የስራቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች መልካም ውጤት አስገኝተዋል።

Videos From Around The World

     ባለፉት 27 አመታት የኢህአዴግ መር መንግስት መልካም የልማት ውጤት እንዳስመዘገበ ሁሉ በርካታ ክፍተቶችም ነበሩት። አብዛኛዎቹ ችግሮች ከድርጅቱ ዲሞክራሲያዊ መርሆች (Democratic principles) የሚመነጩ ነበሩ። በተለይ የኢህአዴግ አስተዳደር ግንባር ለማመን የሚከብዱ የስብአዊ መብት ጥሰቶች በህዝቡ ላይ ፈፅመዋል። ከድርግ ስርአት በቅጡ መማር ያልቻለ ይህ ድርጅት ባሳየው የዲሞክራሲ ክፍተት እንዲሁም የስብአዊ መብት እፈና በህዝቡ አይን ውስጥ ዘልቆ ገባ።የህዝቡ ቁጣም ናረ ። የዲሞክራሲ እጦት፣የስብአዊ መብት ርግጠት ለኢህአዴግ ስርአት ከባድ የመንግስት ሥራ ሆኖ ዘልቀዋል።የመልካም አስተዳደር ችግር የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ያለመኖር ችግር ነው።

 መብት ሳይከበር እውነተኛና ዘላቂነት ያለው ልማት አይኖርም። ሄዶ ሄዶ የታየውም ይህ ሐቅ ነው።የኢህአዴግ ስርአት ያጋጠሙት ችግሮች ለመፍታት ተደጋጋሚ ተሀድሶች ቢያደርግም ችግሮች ከመቀነስ ይልቅ እየጨመሩ እንዲሁም የችግሮች ጥልቀት መንግስት መቆጣጠር ከማይችለው ደረጃ ደረሱ። በሶስት አመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ በመንግስት አስቸኳይ አዋጅ ስር ወድቃ ነበር። በሁኔታው አብዛኛው ህዝብ አዝኖ ነበር ።ችግሩን ለመንቀስ ችግር የሌለበት ኢህአዴግ በራሱ መዋቅራዊ ችግሮች ተጠለፈ።መልካም አስተዳደር ማስፈን ተሳነው ።የዲሞክራሲና የፍትህ ተቋማት ማጠናከር ተሳነው። ዜጎች ከክልል ክልል ተዟዝሮ መስራትና መኖር ተሳናቸው። የህዝቦች ህገ መንግስታዊ ከለላዎችና መብቶች ተጣሱ። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጣዊ ጥንካሬና መተማመን እየላላ ሄደ። ሌላ ቀርቶ የህ.ወ.ሓ.ት የበላይነት ስፍነዋል ተብሎ በተከታታይ ለ27 አመታት ሲነገር እንኳ በድርጅታዊ ትብብር ጉዳዩን መመከት ብሎም ማስቆም አልተቻለም። የኢህአዴግ ስርአት ዘር ተኮር ስርአት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አገራዊ መግባባት ላይ ብዙ ትኩረት ሳይስጠው ቆይተዋል።ይህ በሂደት አገራዊ ጋሬጣ(National crises) አስከትለዋል።አሁን እየታየ ያለው ለውጥ ቀድሞ መስራት ነበረበት።በተለይ ከአንጋፋው የህ.ወ.ሓ.ት. ድርጅት በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ዙርያ ብዙ አበርክቶዎች እንዲፈፀም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ይጠበቅ ነበር።ግን አልተሳካም። ህ.ወ.ሓ.ት የትግራይ ህዝብ ተልዕኮ ማስፈፀም ላይ ድክመት አሳይተዋል።ስላም፣ልማትና ዲሞክራሲ የትግራይ ህዝብ የምንግዜም እምነቶች ናቸው። ህ.ወ.ሓ.ት. እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ የህዝብ ፍላጎቶች ተግቶ በማስፈፀም ረገድ አቅም አልነበረውም ።ከእንግዲህም አይኖረውም ።የትግራይ ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅሙን እንጂ የመልካም አስተዳደር ችግር ያላቸው ሹመኞች የሚሽከም ትከሻ የለውም ። ይህ ህዝብ አሁን እየታየ ያለ ከፍትኛ የህዝብ ለውጥ ፍላጎት እውን እንዲሆን ይመኝ የነበረ ዋጋም የከፈለ ክቡርና ታላቅ ህዝብ ነው።ለማህበረ ኢኮኖሚ ጥቅሙ አንድነቱ ማጠናከር ይገበዋል።አኩሪ ታሪኩና ኢትዮጵያዊነቱ በብልጣ ብልጥ ካድሬዎች መነጠቅ የለበትም። ከመደመር የተሻለ አማራጭ የለም ካለም መለየት ብቻ ነው።There are no better options rather than be part of the public interest for change and facilitate the change for good.

      ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የህዝቡ ብሶትና ግለት (public disparate) ገንፍሎ አሁን ያለንበት የለውጥ ጫፍ ደርስዋል።ከኢህአዴግ ውስጥ የመደመር ፅንስ ሀሳብ አንግቦ ድርጅቱ ለማዳን፣ ህዝብ ለማቀራረብ የጠቅላይ ሚኒስተርነት ወንበር የተረከቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ላለፉት 27 አመታት ያልታዩ፣ያልተስሙ ፣እንዲሁም ያልተነገሩ ግሩምና ድንቅ ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን  ችለዋል።በክልሎች የሰራ ጉብኝት በማድረግ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚገባውን ክብር ሰጥተዋል ። የትግራይ ህዝብ ለፈፀመው አኩሪ ድልም በወርቅ መስሎ አመስግነዋል ።ለሌሎች ብሄር ብሄረስቦችም እንደዚያው። የዶ/ር አብይ ራዕይ ማንንም ቢጠቅም እንጂ ማንንም አይጎዳም። የእንደመር ራዕይ ከፓለቲካ አንፃር ካየነው ስህተት ውስጥ ይዘፍቀናል።የመደመር ሃሳብ ማየት ያለብን ከአገራቸን አንድነትና ደህንነት ጋር አዛምደን መሆን አለበት።በእንደመር ውስጥ አሸናፊም ተሽናፊም የለም።ሁሉም ከማሽነፍም በላይ አሽናፊ ነው። አገራዊ መግባባት መፍጠር አሸናፊነት ነው። ይቅርታና ፍቅር አሸናፊነት ነው። መከባበርና አንድነት አሸናፊነት ነው።የህግ በላይነት ማስከበር አሸናፊነት ነው። ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል መኖሩ አሸናፊነት ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ ከክልል ክልል ተዟዝሮ የመኖርና የመስራት መብት መከበር አሸናፊነት ነው።የህዝቡ ሰላማዊ የለውጥ ፍላጎት ያለመደገፍ ተሽናፈነት ነው።የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ማደናቀፍ የመሽነፍ ምልክት ነው። የለውጡ መመዘኛ መሆን ያለበት ለውጡ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም የሚለው መርህ አዘል ጥያቄ  ነው። የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ የለውጥ ሃሳብ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ብቸኛ  መፍትሔ ነው።በአንድነት ውስጥ ፍትሀዊነት ይኖራል ።  ኢትዮጵያኖች ከመደመር ውጭ የተሻለ አማራጭ የላቸውም ። የትግራይ ህዝብ ላለፉት በርካታ አመታት በአንዳንድ ሃላፊነት የጎደላቸው ሀይሎች ከህ.ወ.ሓ.ት. ድርጅት ጋር አብሮ ሲወቀጥ ኖረዋል። ይህ ፍትሀዊ ያልሆነ ፍረጃ ለትግራይ ህዝብ የሚገባው አልነበረም።ህ.ወ.ሓ.ትም ቢሆን የህዝቡን ማህበረ የኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በማስከበር ረገድ ብዙ ክፍተቶች ነበሩት። አሁን አሁን በምንም መልኪያ የዶ/ር አብይ አህመድ የለውጥ ራዕይ ለትግራይ ህዝብ ከህ.ወ.ሓ.ት በበለጠ ይጠቅመዋል። ሰለዚህ የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጽያ ወንድም ህዝብ የለውጡ አካል መሆን አለበት እላለሁ ።የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ የህዝብ ጠላት የለውም ።ወቅታዊ ባልሆኑና በተሳሳቱ ድርጅታዊ ትንተናዎች ህዝቡ መደናበር የለበትም። ታሪካዊ ጠላቶችህ ተነሱብህ የሚለው አስተሳስብ ያረጀ ምክንያት ነው። ህ.ወ.ሓ.ት. ከፈረስ የትግራይ ህዝብ ይጎዳል የሚል ህሳቤም መቆም አለበት። ህ.ወ.ሓ.ት. የህዝብ ዋስትና ሳይሆን ወኪል ነው ሊሆን የሚችለው። የትግራይ ህዝብ ብሎም የኢትዮጵያ ህዝብ ዋስትናው ህገ መንግስቱና ራሱ ህዝቡ ብቻ ነው። አሁን አየመጣ ያለው የዲሞክራሲ ፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ፣ የመከባበርና የአንድነት መንፈስ የሁሉም ህዝቦች ፍላጎት ነው። የሁሉም ህዝቦች ፍላጎት ያላካተተ ለውጥ ዘላቂነት የለውም። ጥላቻ በእጅጉ ጎድቶናል፣አክስሮናልም።

     የዶ/ር አብይ የለውጥ ሃሳብ ለድርጅታቸው ኢህአዴግ የህልውና ብትር ነው።በመሆኑም የኢህአዴግ አባልም ሆኑ አጋር ድርጅቶች የለውጡ ተዋናይ መሆን የግድ የሚሆንበት ወቅት ላይ ነን። ህዝቦች ሊያቀራርብ የሚችል ብቸኛ መሳሪያ ይቅርታ ፣ፍቅርና አንድነት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ የኢትዮጵያ ህዝብ የማቀራረብያ መንገድ ሁሉ ዝግ ነው። የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀስ ማንም ይሁን ማን የስልጣን ህርፈት አልያም የመልካም አስተዳደር ችግር ያለበት አልያም ሁለቱም ችግሮች ያለበት አካል ከመሆን አያልፍም ።ይቅርታ ፣ፍቅርና አንድነት ይስፈን ያለ መሪ እንዴት ሊወቀስ ይችላል?። አስመሳይ ሳይሆን ሐቀኛ የህዝብ መሪ እንዴት የህዝብ ጠላት ይባላል?።ጥላቻ ይወገድ ያለ መሪ እንዴት ይወቀሳል?። የሚስነዘሩ አንዳንድ ስሜት አዘል አስተያየቶች አሁን ካለው ተጨባጭ አገራዊ ትንተና ጋር የሚቃረኑ ሆኖ አግኝቻቸዋለሁ። በስሜትና ቁጭት ሳይሆን በሀሳብ ልዕልና የለውጡ እንቅስቃሴ መከታተል አለብን። መልካሙን ማየት ከተሳነን መልካም ያልሆነው መለየት አንችልም። የህዝቡ የለውጥ ሂደት መደገፍና መጠናክር ይገበዋል።ለውጡ ሁሉም ያካተተ ነው።ህዝብ የበደሉም በዚህ የይቅርታ ማቀፍ ተካተዋል ።መገዳደልና መበዳደል የቁም። እያፈረሱ ከዜሮ መጀመር ይቁም ።ቀድሞ ለተስሩት የልማት ስራዎች አክብሮትና እውቅና እንስጥ። አስፈፅሚዎችም እናመስግን።ዘለፋውና መወነጃጀሉ ስለማይጠቅመን ይቁም ።መከባበርና መደማመጥ ይስፈን።

     መደመር ሲባል ያለብንን ክፍተት መሙላት ማለት ነው።የነበረን ክፍተት ደግሞ ግልፅ ነው። አገራዊ መግባባት አልነበረም ።የአንድነት ስሜት አልነበረም ።ጥላቻ በነገሰበት አገር ተደምረን ነበርን ማለት ከእውነታ ውጭ ነው።ብንደመር ኖሮ የህዝብ መፈንቅል ባልነበረ ነበር። ለመደመር ይቅርታና ስላም መቅደም አለበት።ለመደመር አገራዊ መግባባትና መከባበር መቅደም አለበት።

     በመጨረሻ ጥላቻ ለመስበር፣ብሄራዊ አንድነት ለማስፈን፣ የህግ የበላይነት ለማክበር፣ ዲሞክራሲ ለማጎልበት፣ በስላም ለመኖር ፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃ ለመሆን ፣አንዲሁም ድህነትና ኃላ ቀር አስተሳሰብ ለመቅረፍ የጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ብስለት የተላበሱ የመፍትኄ ሃሳቦች ላይ በአሸናፊነት መንፈስ ሁሉም ዜጋ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ወሳኝ ጥሪ ነው።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።

 

     

 

Back to Front Page