Back to Front Page


Share This Article!
Share
የቀለም አብዮት መደመር ህዝበኝነት

ቀን፦27/10/2010 ዓ/ም

የቀለም አብዮት መደመር ህዝበኝነት

ሰላምወርቅ ሁሉአገር

ከአዲስ አበባ

በኔም በሌሎችም ስለ አገርና ስለ ህዝብ ብዙ ግዜ ብዙ ለማለት ተሞከረ ቢሆንም ሰሚ የለም። ይሁንና “እጮሃለሁ” እንዳለው የማስታወቂያው ሰውየ በዜግነት በአገር ጉዳይ መጮህን አለማቆም  ይሻላል በሚል የተወሰነ ነገር ለማለት  ፈለግኩኝ።ይህንን ስል ዛሬ ዛሬ ባለው ሁኔታ የሚሰማኝ ማጣት ብቻ ሳይሆን ከኔ  ጭሆት ከፍ ያለ የተቃውሞ ጭሆት እንደሚገጥመኝ እርግጠኛ በመሆን ግን ደግሞ ይህም ያልፋልና ሁላችንም ስለ እውነት ድምፃችን ከፍ አድርገን እንጩህ ከሚል እምነት ዛሬም እንዲህ እጮሃለሁ።ከተቃውሞ በዘለለም ዘለፋና ከዛ ያለፈ እንደሚኖር የምረዳው ቢሆንም ኢህአዴግ ከቸልሲ ምን ይማራል፣ኢህአዴግና መጭው የአካል ጉዳተኝነት አዝማምያ፣የፖለቲካ ኤሊኖ በኢህአዴግና ህዝባዊነት፣ህዝበኝነትና ፀረ-ህዝብነት በሚሉ ፅሁፎቼ እንዳነበባችሁት የምፅፈው ለአገርና ለእውነት ስለሆነና ነገ የሚገኝ እውነታም በመሆኑ ነው።

በዚህ ፅሑፍ ያለው የዘመን ቀመር ስለ አገራችን በማወራበት ግዜ ያለው የዘመን አቆጣጠር በአገራችን፣ ለተሞክሮ በሚል ስለ ሌላ አለም ባሰፈርኩት ሃሳብ የተጠቀሱ ዓ/ምህረቶች በሙሉ እንደ ፈረንጅ አቆጣጠር ተደርገው እንዲነበቡልኝ ከምስጋና ጋር እጠይቃለሁ።

 በኢትዮጵያ የተደረገው ለውጥ ለውጥ ነው አይደለም ከሚል ጀምሮ ለውጡ የመጣው በቀለም አብዮት መንገድ ነው አይ እንዲሁ የህዝቡ ስሜት ለውጥ የሚፈልግ ስለነበር በህዝቡ ትግል የመጣ ለውጥ ነው በሚሉ ሃሳቦች የተከፋፈለ አቛም እንሰማለን። እንደኔ አስቀድሞ እንዲህ ነው እንድያ ነው ከማለታችን በፊት የተወሰነ ዘርዘር ያለ መነሻ ሃሳብ አቅርቤ ብናየው የሚል መረጥኩኝ።

Videos From Around The World

የቀለም አብዮት ምንድነው የሚለው በብዙዎቻችን ዘንድ አዲስ ስላልሆነ አዲስ ነገር ላልጨምር ግዜ አላጠፋም ።ለመንደርደርያነት እንዲሆን የቀለም አብዮት በውጭ መንግስታት ወይም ኃይሎች ወይም ቡድኖች ፍላጎትና ሙሉ ተሳትፎ ጥቅማችን አያሟላም ለሚሉት ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብ[የርእዮተ አለም] ልዩነት በመኖሩ ምክንያት ጥቅማችን አያስጠብቅም ለሚሉት መንግስት  የማስወገጃ መንገድ ነው። ይህ በመሰረቱ በአዲሱ ሊበራል [Neo-liberal] አቀንቃኝ በሆኑት ምዕራባያን በአብዛኛው  ደግሞ  በአሜሪካ የሚፈፀም ሲሆን ይህንን ለማሰፈፀም የመንግስት ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ጭምር በመቀናጀት ይከውኑታል።

 በመሰረቱ ከቀዝቃዛ ጦርነት ማብቃት በኃላ እየተተሰፋፋና እየታወቀ የመጣ ቢሆንም ከዛ በፊትም የተሞካከረ ጦርነት (Act of War) ነው። ሲጀምሩት ግጭት አልባው ጦርነትና የመንግስት ለውጥ ማከናወኛ የአብዮት መንገድ ተብሎ የሚታወቅ የነበረ ቢሆንም ከግዜ በኃላ ግን ሰልፈኛው ከሚጠቀመው ኃይል ባለፈ አብዮቱን የሚመሩት አካላት ራሳቸው የግድያ ቡድብ በመመልመል፣በማሰልጠንና ለዚህ የተመረጠ መሳርያ በማስታጠቅ ከመንግስት በኩልም ከሰልፈኞቹ በኩልም ታዋቂ ሰዎች እንዲገደሉ በማድርግ መንግስትም በተገደለበት ባለስልጣን ተናዶ የአፀፋ እርምጃ እንዲወስድ ሰልፈኞቹም የተገደለባቸው ታዋቂ ሰው መንግስት እንደገደለው በማመን ሁለቱም በስሜታዊነት ወደ አፀፋዊ እርምጃ ገብተው አብዮቱ ወደኃላ እንዳይመለስ የሚያደርግ ስልት ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛሉ።ይህንን የገለፅኩት በመስቀል አደባባይ በዶክተር አብይ የድጋፍ ሰልፍ የተፈፀመ የቦምብ ጥቃት አስመልክቶ ሃሳባቹና ግምታቹ ለማስቀየስ ሳይሆን በተጨባጭ በጆርጂያና ዩክሬን የነበሩ የቀለም አብዮት ታሪኮች ያረጋገጡት እውነተኛ ታሪክ ስለሆነ ነው።

 

 

በአሜሪካ ይህንን የሰው አገር መንግስት በማፍረስ አገር የመበተን ስራ የሚያከናውኑ በርካታ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች[NGOs]ስም በማቋቋምና በቢልዮን ዶላሮች ካፒታል በመመደብ የሚከናወን ተግባር ነው። ከእነዚህ መካከል United states agency for international development(USAID),National democratic institution ,Center for strategic and international study ,Freedom house ,National endowment for democracy, Albert Einstein institute እና ሌሎች የመሳሰሉ ተቋማት በማቋቋም በመረጃ፣በአደረጃጀት፣ በገንዘብ፣በእውቀት፣በስልጠና፣በቴክኒክ፣በፕሮፖጋንዳና በመሳሰሉ ጉዳዮች በሽፋንና በግልፅ ከቁጥቋጦ ጀምሮ  እስከ አውድማ ምርት መከወን ድረስ የሚመሩ ናቸው። ይህንን የበለጠ ለመረዳት የሚጠቅም ከሆነ Thierry Meyssan የተባለ የግሎባል ጥናት ፀኃፊ The CIA,NGOs and color revolution በሚል ፅሑፉ ያገኘሁትን አንድ ምስል ላጋራቹ፤

http://themillenniumreport.com/wp-content/uploads/2015/05/8536599.jpg 

በዚህ መንገድ በአለማችን በጣም ብዙ በዛፍ፣በፍራፍሬ፣በሃረግና በተለያዩ እቃዎችና የእቃ ቀለማት የተሰየሙ የተሳኩና ያልተሳኩ የቀለም አብዮቶች አካሂደዋል። የተወሰኑት ለመጥቀስ ያክል ፖርቹጋል 1974፣ፊሊፒንስ 1986፣ችኮዝላቫክያ1989፣ ዮጎዝላቭያ2000፣ ጆርጅያ 2003፣ ዩኩሬን2004፣ኢራቅ ፣ክይርጅይኪስታን፣ሊባኖስ፣ኩዌትና ኢትዮጵያ፣ ቤላሩስ፣ ማይናማር፣ኢራን ፣ቱኒዝያ፣ግብፅ፣ሶርያ በመሳሰሉና በሌሎች አገራት ተግባራዊ ሊያደርጉ ተንቀሳቅሰው በአንዳንዶቹ ሲሳካላቸው በሌሎቹ አልተሳካላቸውም ወይም ወደ ሁለተኛ የቀለም አብዮት ለመሸጋገር ተገደዋል።

በዚህ ዘመን እንኳንስ በኃያላን መንግስታት ደረጃ ይቅርና ግለሰቦች እንኳን አለምን በበጎ የመቀየርም ሆነ የማተራመስ አቅም ያላቸው መሆኑ በተለያየ አጋጣሚ አይተናል።ለዛሬ ከተነሳሁበት አላማ አንፃር አገሮችን በማፍረስ እኩይ ተግባር ተጠምደው ዝና ለማግኘት ከሞከሩ ውስጥ አንድ ሰው አይተን የአለም የፖለቲካ ጨዋታ ምን ያክል አስቀያሚና እንደ አገራችን ያሉ ያላደጉ አገሮች በግለሰቦች ኪስ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ ያሳየናል የሚል እምነት አለኝ።ከዚህ አኳያ እንደ ጆርጅ ሶሮስ የሚያክል ማግኘት አልቻልኩም።

ሰውየው ጆርጅ ሶሮስ ይባላል ሰኔ ወር 1930 በሃንጋሪ የተወለደ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ሰው ነው።እሱና አባቱ ከናዚ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ስማቸው ትተን በተለያየ የህይወት ምዕራፍ አልፎ በቢዝነሱ አለም ከተሳካላቸው የአሜሪካ ቢሊየነሮች አንዱ ነው።ሰውየው የሊበራሊዝም ደጋፊ በመሆኑ ርእዮተ አለሙን ከመደገፍና የቢዝነስ አለሙን ሞኖፖል ለማድረግ ከሞመከር ባሻገር አገርን በማፍረስ ህዝብ ያለ አገርና ያለ ህግ በማስቀረት ከሚዝናኑና ከሚረኩ ሰዎች ዋነኛው ነው። እንደ Truthwiki.com ዘገባ በሰይጣናዊ ስራው ከሚታማበት አንዱ ዶክተር ቶማስ ፍሬድን ከተባለ ሰው ጋር በመሆን በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ቫይረስ ያስፋፋ ሰው እንደሆነ ተዘግበዋል።

ጆርጅ ሶሮስ አለምን ለማተራመስ open society foundation የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ  ድርጅት በማቋቋምና በበጎ አድራጎት ስም በ70 አገሮች ቢሮ በመክፈት እንዲሁም  ለሌሎች ተቋማት ጭምር እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር በማፍሰስ በተለያዩ አህጉሮች በነበሩ የቀለም አብዮቶችና የኢኮኖሚ ቀውሶች ጀርባ ያለ ሰው ሆኖ እናገኘዋለን።በ1993 በእንግሊዝ ባንክ ሲስተም ውስጥ ገብቶ የፓውንድ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከም በማድረግ በእንግሊዝ ማህበራዊ ቀውስ የፈጠረ፣በ1997-1998 በኤስያ በነበረ የኢኮነሚ ቀውስ እጁ በማስገባት በማለዥያ፣ታይላድና ሆንግ ኮንግ ከፍተኛ ችግር እንዲፈጠር ያደረገ ሰው ነው።

በአለማችን ከነበሩ የቀለም አብዮቶች ውስጥ በሰርብያ፤ጆርጂያና በግብፅ በተካሄዱ አብዮቶች በከፍተኛ ደረጃ የተሳተፈበት ተግባር ሲሆን በቱርክ እስላሚስት ቡድን በማቋቋም ድርሻው ከፍተኛ ነበር። ሌላው ለብዙዎቻችን እንግዳ ይሆናል ያልኩት በአሜሪካ በራሷስ የቀለም አብዮት ተካሂዶ ያውቃል ወይ የሚለው ሲሆን መልሱ አዎ ነው።ሶሮስ ከቡሽ በኃላ የአሜሪካ ፖለቲካ ለመዘወር ተንቀሳቅሰዋል።ኦባማ እንዲመረጡ በማድረግና የኃላው የሂላሪ ክሊንተን ምርጫ ከ23 ሚሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ ክሊንተን እንዲያሸንፉ ጥረት ያደረገና ሌላ ቀለም አብዮት አሸንፎ ብዙዎች ባልጠበቁት ሁኔታ ዶላንድ ትራምፕ ሲመረጡ በአሜሪካ በአጭር ግዜ የተቀጣጠለው “ሐምራዊ አብዮት” የተሰየመው የቀለም አብዮት ታውጆ ከ10 ትላልቅ ከተሞች በላይ የተጠለቀለቀው የቀለም አብዮት ባለቤት አቶ ጆርጅ ሶሮስ ናቸው።

አለም በእንዲህ ያለ ሁኔታ እየተመራች ከሆነ እንደ አገራችን ያሉ በኢኮኖሚና በማህበራዊ አስተሳሰብ በዝቅተኛ ደረጃ የምንገኝ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች የተከፋፈልን ህዝቦች ሌላው ቀርቶ በባንዴራችን ሳይቀር የተከፋፈልን ሆነን ስያገኙን በቀለም አብዮት ሁለተኛ እንዳንነሳ አድርግው ቢያፈራርሱን ለምን ይገርማል።እሺ አይገርምም እንበልና ለመሆኑ በአገራችን የቀለም አብዮት ለማካሄድ ተጨባጭ ምክንያት አለ ወይ?እኛና ምዕራባውያን የሚያኮራርፈን ነገር አለ ወይ? ብለን ማየቱ አሁን በአገራችን እየሆነ ያለው ነገር የቀለም አብዮት ነው አይደለም የሚል ለማየት ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ።

የቀለም አብዮት ለማካሄድ ምክንያቶች ብለን ከላይ የገለፅናቸው ሃሳቦች አሉ።አንዱ የርእዮተ አለም ልዩነት መኖር ሲሆን ኢህአዴግ ህዝቡን በአጭር ግዜ ከድህነት የማወጣበትና ህዝቡ በየደረጃው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ ነው ብሎ ዝም አላለም። ሰርቶ በማሳየት ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ለሌላው አለም ማሳያ ሆኖ ቀረበ።ቀጥሎም አፍሪካ ካሉባት ችግሮች የምትወጣው እህንን መንገድ ስትከተል መሆኑን አስተማረ፣በርካታ አገሮችም ፈለጉን መከተል ጀመሩ።በዚህም አላበቃም ኒዮ ሊበራሊዝም የድህነት መንገድ ነው፣ሌላ የቅኝ ግዛት መንገድ ነው፣እንዳውም በአሜሪካ ህዝብ ላይም ጉዳት እያደረሰ ነው “We are 99%” ብሎ በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ሳይቀር እየተጋበዘ በመሪው አመካኝነት አስተማረ።በአሜሪካኖችም ተጨበጨበለት።

ከዚህ ከርዕዮተ አለም ልዩነት ጋር በተያያዘ ሌላው በኢህአዴግና ከምዕራባውያን ጉዳይ ጋር የሚያያዝ ነገር እስከ 1984 ዓ/ም አካባቢ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የማርኪሰ ሌኒናዊ ፓርቲ ሲሆን ይህንን አስተሳሰብና አደረጃጀት ከደርግ ውድቀት በኃላ እንደተተወ  ይገለፃል። ይሁንና በኢህአዴግ ውስጥ በግልፅ የሚታወቅ አደረጃጀትና አመራር የነበረው  ፓርቲ ስለነበር እንኳን ለቀሪው አለም ለአባላቱም ቢሆን በወቅቱ፣ በግልፅና በአዋጅ እንደተተወ ከነ ሙሉ ምክንያቱ አልተገለፀም።ስለሆነም እነዚህ ኃይሎች በጥርጣሬና በስጋት እንዲያዩት ምክንያት አላቸው።

ሌላው የቀለም አብዮት የጦርነት አዋጅ ለማወጅ ታርጌት ያደረጉት መንግስት ያለውን የተፈጥሮ ኃብትንም ሆነ ሌላ የኢንቨስትመንት (የኢኮኖሚ) ተጠቃሚነታችን የሚጠብቅ መንግስት አይደለም። ከሁሉ በላይ የሚሰማን የሚታዘዘን መንግስት አይደለም ብለው ሲያስቡ የቀለም አብዮት በማካሄድ ከተቻለ ታዛዥ መንግስት መመስረት ካልሆነ ለነሱም ሆነ ለሌላ የማጠቅም አገር አድርጎ ማፈራረስ ነው።ለዚህ ጥሩ ማሳያ በግብፅ የተካሄደ የቀለም አብዮት ነው። ወዳጃችን የሚልዋቸው ሆስኒ ሙባረክ ባህሪያቸው እየተቀየረ ጥጋብ ጥጋብ እያላቸው እንደነ ገምግመው በወቅቱ በግብፅ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ፍራንክ ዊስነር  ትእዛዝ  አይሉት ምክር  መሳይ ነገር ኃላፊነቱን ለሌላ ቢያሸጋግሩ አሏቸውና እንደማይሆንላቸው   ሲረዱ CIA,MI6,Freedom house  እና እንደ ጆርጅ ሶሮስ ያሉ ሰዎች ሃብት በማፍሰስ ጀመሩት ሙባረክ ወረዱና ወህኒ ገቡ።

ውጤቱ ግን ከፈለጉት መንገድ ወጥቶ ሌላ ሆነ። ምክንያቱም እነሱ ይህንን ሲያስቡ የቀለም አብዮቱ ሲጠናቀቅ ማን ወደ ስልጣን እንደሚመጣ አዘጋጅተው መግባት ስለነበረባቸው በዚህ ደረጃ ሙሉ ዝግጅት አድርገው ነበር።የግብፅ ፕሬዝዳንት በመሆን የአሜሪካንና እንግሊዝ ጉዳይ አስፈፃሚ እንዲሆኑ የተመረጡት የአለማቀፍ አቶሚክ መሳርያ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የበላይ የነበሩ መሐመድ አልባራዳይ ናቸው።ይህንን ለማድረግ   መጀመርያ የኢራን የኒኩለር ጉዳይ ከፍ ያለ አለማዊ አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ እሳቸውም ተደጋግሞ ስማቸው እንዲነሳ ተደረገ። ቀጥሎ እሳቸውና ኤጀንሲያቸው የሰላም ኖቬል ሽልማት እንዲወስዱና ዝናቸው ከፍ እንዲል ተደረገ በመጨረሻም ቀደም ብለው ከድርጅቱ ኃላፊነታቸው በራሳቸው እንዲለቁ ከተደረገ በኃላ የአብዮቱ መጠናቀቅ ተከትሎ አልበራዳይ ፕሬዝዳንት ለመሆን ተንቀሳቅሰው ሁኔታው አቅጣጫው እየቀየረ መሆኑ ሲገመገም ከሒደቱ ራሳቸው እንዲያገሉ ተደርጎ ለሁለተኛ አብዮት ተጋበዙ።

ስለዚህ ከዚህ አንፃር በኢህአዴግ የምትመራ ኢትዮጵያን ኢላማ ማድረጋቸው ከነሱ አንፃር አማራጭ የማይቀርብበት ጉዳይ ነው።ምክንያቱም ኢትዮጵያና ኢህአዴግ በአሜሪካና በአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች እንዲሁም ለዚህ ማስፈፀምያ ተብለው በተቋቋሙ IMF እና የአለም ባንክ በመሳሰሉ ተቋሞቻቸው በዚህ መንገድ ሂዱ በዛ መንገድ ተመለሱ የሚል ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካላቸውምና ማድረግ የነበረባቸው ማድረግ ነበር አማራጫቸው።

ሌላው ጉዳይ አገሮች የቀለም አብዮት ሰለባ የሚሆኑበት ምክንያት በአለማቀፍ የኃይል አሰላለፍ ስርአት ውስጥ ባላንጣ(ተፎካካሪ) ከሚሉት የጠበቀ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር የኃይል ሚዛኑ ያዛባል ብለው የሚያስቡት ሲሆን ነው። ኢትዮጵያና ኢህአዴግ የኤስያው በተለይ የቻይና መንገድ እንደምትከተል በአዋጅ ከመንገር አልፋ በነሱ ዘንድ  አፍሪካ ፊቷን ወደ ቻይና እንድታዞር “መጥፎ” አርአያ ናት።አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ምን ያክል እንደተጨነቀች ለመረዳት በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራክ ቴለርሰን ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች “ቻይና እየዘረፈቻቹ ነው።” ያሉትን ማስታወስ ይጠቅማል።እዚህ ላይ መለስ ለምን ሞተ የሚል ጥያቄ የጫረባቹ ሰዎች እንዳላቹ ይሰማኛል።እኔ እንጃ ? ብየ ባልፈውስ? 

ከዚህ ጋር ተያይዞ ቻይና ወደ ጅቡቲ መምጣቷ ተከትሎ አልታዘዝም ያለችና ተሰሚነትያላት  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ መኖር ሌላው ኢትዮጵያን በስጋት እንድትታይ የሚያረጋት ነው የሚል ስሜትም አለኝ።ስለሆነም ኢትዮጵያ የቀለም አብዮት ኢላማ ለመሆን ሽብርተኝነት በጋራ መዋጋት ከሚለው ውጭ ሁሉም መስፈርት አሟልታ ስለተገኘች ነው የቀለም አብዮት የተፈፀመባት ብለን በአገራችን የነበሩ ችግሮችና ለውጡ የቀለም አብዮት ነው ብለን አስረግጠን መናገር እንችላለን።

በሁሉም የቀለም አብዮት ተግባራዊ የተደረገባቸው አገሮች አፈፃፀም እንደየ አገሩ ሁኔታ፣እንደ የህዝብ ባህልና አስተሳሰብ፣እንደ አገሪቷን በመምራት ያለ መንግስት ባህሪና ጥንካሬ፣ አካባብያዊ ሁኔታ ወዘተ የተለያየ አግባብ ይከተላሉ።ተጀምሮ እስኪያልቅ ያለው የግዜ አጠቃቀምም እንደዛው የተለያየ ነው።በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ የቀለም አብዮት ሁኔታ ብናይ መሰረት ለመጣል ጉድጉድ የተጀመረው ኢህአዴግ በመጀመርያ ምርጫ አሸንፎ መንግስት ከሆነና የሚከተለው የመንግስት ባህሪ አይነት ሲጠና ግልፅ መሆን ስላልቻለ በትኩረት መከታተል የተጀመረ ሲሆን ለነሱ ያለው ጥቅምና ጉዳት እየደመሩ እየቀነሱ ቆይተው “የመጀመርያው ተሃድሶ” ከሚባለው በኃላ መንገዱ እየለየ ሲሄድ የተጠናከረ ስራ ሲሰሩ ቆይተው ለምርጫ 97 ዝግጅት አድርገው ተግባራዊ ለማድረግ ሞከሩ።ነባራዊ ሁኔታው ይህንን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የተመቸ ስላልነበረና የመንግስት ጥንካሬም ታክሎበት እንደ ኢራኑ አብዮት ከሸፈ።

ከዚህ በኃላ አዲስ ስትራቴጂ በመቀየስ ተግባራዊ ለማድረግ ይኸው 13 ዓመታት ፈጅቶ ዛሬ ተግባራዊ አደረጉት።”ጉድና ጅራት …….” እንዲሉ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ መረጃዎች አዲሱ ስትራቴጂ ቄሮ በመፍጠር የተጀመረ ስራ ሲሆን ይህንን ስራ ሙሉ በሙሉ በፀረ-ሽብር ቡድን ስም በሱማሌላንድ የተመደበ የCIA ቡድን ከብቅል ጀምሮ ሲመራው የከረመ መሆኑ የውጭ ሰዎች ሳይቀሩ በማስረጃ እያስደገፉ መፃፍ ጀምረዋል። አደረጃጀቱ ከተፈጠረ በኃላ በርካታ ወጣት ሃርጌሳ፣ ኬንያ፣ ካይሮና ጥቂት የተባሉት ደግሞ አሜሪካና አውሮፓ ሄደው ስልጠና ወስደው ተመልሰዋል።እነዚህ ሰልጥነው የመጡ ሰዎች አገር ውስጥ ለበርካታ ወጣት ስልጠና ሰጥተዋል።የሌላው አከባቢ እንደ አማራ አከባቢ ያሉ ደግሞ በተለያዩ የቅሬታ ምክንያቶች አመካኝነት እየተሰባሰበ እንዲሄድና አደረጃጀቱ ከቄሮ ጋር እንዳይቀላቀል ታስቦበት የተሰራ ሲሆን ግዜው ደርሷል ሲባል እንዲገናኝ ተደርጎ ስም ወጥቶለት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

አሜሪካ በየአመቱ የአፍሪካ ወጣቶችን ወደ አገርዋ እየጋበዘች ታወያያለች። በዚህ ሽፋንም ለቀለም አብዮት ተመርጠው ለሚሄዱ ወጣቶች ይህንን የአመፅ አደረጃጀትና አመራር ስልጠና ትሰጣለች።ስሙም Young African leaders initiative ይባላል።በዚህና በሌሎች የተለያየ ስም በተሰጣቸው ሁነቶች ስንት የአገራችን ወጣቶች አሜሪካ ተጋብዘው እንደሄዱ የሚታወቅ ሲሆን ሁሉም ባይሆኑም በዚህ ሽፋን ስልጠና ወስደው የመጡ በርካታ መሆናቸው እየተሰማ ነው።ከዚህ የላቀው ቁጥር ደግሞ በኢትዮጵያ ባሉ የአሜሪካና የአውሮፓ ኤምባሲዎቻቸው በርካታ ፕሮግራም እየተዘጋጀ አእምሮ የማጠብ፣የታጠበው በአዲስ ፓኬጅ የመመገብና እየተገመገመ ወደ አደረጃጀት የመቀየር ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

ከዚህ ሌላ ከላይ ያነናቸው መንግስታዊ ያልሆኑ አለማቀፍ ድርጅቶች በማህበረሰብ ደረጃ ዘልቀው በመግባት ወጣቱንና ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ላይ አስተሳሰቡን ወደሚፈልጉት መንገድ ለመግራት በሙሉ አቅማቸው ሲሰሩ ቆይቷል።እነዚህ የተጠቀሱ NGOs የት የት ክልል አሉ የትስ የሉም ወይም ለይስሙላ ጽ/ቤት ከፍተዋል የሚሉ ጉዳዮች ልብ በሉልኝ።ኢትዮጵያ NGOs የሚተዳደሩበት ህግ ስታወጣ የነበረ አለማቀፍ ጫጫታም ማስታወሱ አይከፋም።

የዚህ የአብዮቱ ጉዞ ሌላኛው ወሳኝ አካል ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሆኑ የሚድያና የኪነ ጥበብ ስራዎችን ከረጅም ግዜ ጀምሮ በማዘጋጀት ስራውን በልክ በልኩ እያሞቁ እንዲቀጥሉና እንደየ አስፈላጊነቱ የህዝቡን ብሶት እየተንተራሱ ወደ አመፅ እያዘጋጁ መሄድ የሚለው ስትራቴጂ ነድፈው ሲንቀሳቀሱ ቆይቷል።ወደድነውም ጠላነውም ማወቅ ያለብን እውነታ ጋሼ አበራ ሞላ ገና ከመጀመርያው አዲስ አበባ አፀዳለሁ ብሎ ከውጭ መጥቶ ወጣቶችን እየሰበሰበ ፅዳት ሰርተዋል ብሎ ብር መክፈል ሲዘጅምር መጥረግያ ብቻ ይዞ አልመጣም።

በአንዳንድ አገሮች ኮሜድያን የቀለም አብዮቱ መሳርያ አድርግው ሲጠቀምባቸው እናያለን።እንኳን በሌላ በአሜሪካ purple revolution ተብሎ ትራምፕን ከነጩ ቤተ-መንግስት ለማባረር የተሞከረው የቀለም አብዮት ኮሜድያን በምን መልኩ ተዋናይ እንደነበሩ ታዝበናል።በኛም አገር አብዛኛዎቹ የሞያ ሰዎች ሲሆኑ እንደ ክበበው ገዳና መስከረም የተባሉ በግላጭ ዋናውን የአብዮቱ ኮር ሃሳብ በማስረፅ የራሳቸው ሚና ነበራቸው።ሌሎቹ አሜሪካ ደርሰው ክትባቱ ወስደው ከተመለሱ በኃላ ጨዋታ የጨመሩ ሶስት ኮሜድያንም ብዙዎቻችን የታዘብናቸው ይመስለኛል።

ከዚህ ከአርቱ ሳንወጣ ፊልሞች፣ግጥሞች፣መነባንቦችና በጥቂቱም ቢሆን የስእል ስራዎች የቀለም አብዮት ማስፈፀምያ መሳርያ ሆነው ሌላ አለም አይተናል እኛም አገር እንዲሁ።ለዚህም በቅርብ አመታት በርካታ የዚህ ቅኝት ያላቸው ፊልሞች አይተናል፣ቁጥሩና አድማጭ ተሳታፊ እያበዛ የመጣው የግጥም ምሽትና የግጥም በጃዝ ወዘተ መድረኮች መብዛት ሁላችንም ታዝበናል። ብዙም የማይደፈሩ የፖለቲካ ቅኝት ያለው ነገር ሲነግሩን ስቀናል አጨብጭበናልም። ከአመታት በፊት ሜሮን ጌትነት አሜሪካ ደርሳ የተመለሰች ግዜ በአንድ የግጥም መድረክ ያቀረበችው ግጥም አስታወሳቹ? እኔ ግን በደምብ አስታወስኩት ከነምክንያቱ።

ሌላው ለቀለም አብዮት ዋነኛ ማስፈፀምያ መሳርያ ሚድያ በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ሚድያ ከወሳኞቹ በጣም ወሳን ነው።ይህ ከፅንሰ ሃሳብ አልፎ በኛ አገር በምርጫ 97 እና የአሁኑ የቀለም አብዮቶች የሚጠበቅባቸው በተጨባጭ የከወኑ ሆነው እናገኛቸዋለን።በምርጫ 97 የህትመት ሚድያው በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን እነ ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ያመጣ የአዲሱ አብዮት ሚድያ ለረጅም ግዜ ታስቦበት በስፋት የተሰራበት ነው።ይህ ማለት ከውጭ ሚድያዎች ቢቢሲ፣ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ቪኦኤ፣የጀርመን ድምፅ ሬድዮ፣ኢሳት፣ኦኤምኤን የኤርትራ ሬድዮና ቴሌቪዥን ሁሉም አንድ ኢላማ ላይ ያነጣጠረ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።ይህ ሲባል የመንግስት ሚድያው ጨምሮ በአገር ውስጥ ያሉ ሚድያዎችም ለዚህ ለቀለም አብዮቱ ጉዞ መሳለጥ የበኩላቸው በመወጣት ረገድ ብዙም እንዳልሰነፉ ከዚህ በፊት በነበሩ ፅሁፎቼ የገለፅኩት ስለሆነ ለዛሬ ብዙ አልልም።

አንድ ነገር ግን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለኔ በሚዛናዊነትና በአገር ግንባታ ተወዳዳሪ ያጣሁለት ሚድያ የነበረ ሲሆን የአብዮቱ ግዜ እየደረሰ ሲሄድ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ጀመረና “በህይወት ፍጥነት” የሚል አዲስ መሪ ቃል አውጥቶ እየተጠቀመበት ይገኛል።ታድያ ለኔና ለአንዳንድ የተቋሙ ጋዜጠኞችም ጭምር በሚገርም ሁኔታ ልክ እንደ መሪ ቃሉ በደቂቃዎች ፍጥነት የዚህ አብዮት ማከናወኛ መሳርያ ሆኖ እየቀጠለ የሚገኝ መሆኑ ነው።

ሌሎች ከመንግስት ሚድያ እየለቀቁ ለዚህ መሳርያ የመሆን ነገርም በተግባር እያየነው የከረምን ይመስለኛል።እዚህ ላይ ሳልጠቅሰው የማላልፈው የአለምነህ ዋሴ ጉዳይ ነው።ከሚሰራበት ተቋም የለቀቀበትና ወደ ውጭ አገር ወጥቶ ግልፅ የሚባል የቀለም አብዮት የማራመድ ስራ ሲሰራ ሳይ ከረጅም ግዜ ጀምሮ በራሱ የግዜ ሰሌዳ ይንቀሳቀስ ያልነበረ መሆኑ ነው የገባኝ። ስለ ህትመት ሚድያው ምን ያክልና በምን ላይ ያተኮሩ መፃሐፍት እንቅስቃሴው ለመደፈፍ እንደታተሙና የግል በሚል የሚታወቁ ጋዜጦች በቅርብ አመታት ምን እየሰበኩ እንደነበር ህዝብ ያየውና የሰማው ነገር ስለሆነ ብዙ ለማለት አልፈለግኩም።

የቀለም አብዮት ያለ ማህበራዊ ሚድያ ዛፍ ያለ አየር ወይም ያለ ውሃ ወይም ያለ አፈር እንደማለት ነው። በህይወት ለመቆየት የሚቸገር።በመሆኑም ነው ምዕራባውያን አገሮች በአንድ አገር የሚያጋጥም የኢንተርኔት መቋረጥ ከሰዎች መብት ጥሰት በላይ አምርረው የሚያወግዙት።ካለፉት 15 አመታት ወደህ የተካሄዱ የቀለም አብዮቶች ዋና መሳርያቸው ማህበራዊ ሚድያ በተለይ ደግሞ ፌስቡክ እንደነበረ አይተናል።በአገራችንም ከዚህ የተለየ አልነበረም።አገራችን አሁን ወደ ደረሰችበት ችግር እንድትገባ የፌስቡክ ያክል ሚና የነበረው ኃይል አላውቅም።

ወጣቱ በአገርና በህዝብ ላይ በራሱም ጭምር የሚኖረው እንደምታ ሳይረዳ በስሜት ስልኩ ላይ እየፃፈ የሚለቀው እንዳለ ሆኖ የተመረጡ ፣የሰለጠኑ፣በኔትዎርክ እንዲተሳሰሩ የተደረጉና አጀንዳ እየተቀረፀ እየተሰጣቸው የቀለም አብዮቱን የሚያቀጣጥል ስራ የሚሰሩ ኃይሎች ወይም ቡድኖች የቀጣሪያቸው ተልእኮ ሲከውኑ ከርመዋል።ለዚህም ነው ሁላችን የምናስታውሰው ዞን-9 የተባሉ ብሎገርስ ሲታሰሩ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የአሜሪካና አንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ከሚድያቸው አልፈው በባለ ስልጣናት ደረጃ ሳይቀር የተንጫጩት።ሌላው በቅርቡ ህዝብ እያለቀና አገር እየወደመ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሲታወጅና ኢንተርኔት ሲቋረጥ የአሜሪካ መንግስት በግልፅ መግለጫ በማውጣት መቃወሙስ ለምን መሰላቹ ?

ስለ ቀለም አብዮት ሲያቅዱ የዛች አገር ውስጣዊና አካባብያዊ ሁኔታ እንደሚጠና ከላይ ለመጠቃቀስ ሞክሬለሁ። በዚህ መሰረት በአገራችን የቀለም አብዮት ለማካሄድ ቢያንስ ኤርትራንና ግብፅን  ለመጠቀም መንቀሳቀስ አማራጭ የሌለው ሃሳብ መሆኑ እሙን ነው።በዚህ ረገድ ሁለቱም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የአብረን እንስራ ጥያቄ ሲቀርብላቸው አንድ በልቶ ለማደር የተቸገረን ድሃ ሰው በገዛለት ትኬት የልዩ ሎተሪ አንደኛ እጣ ሽልማት እንደማግኘት ይቆጠራል።ለዛም ነው ሁለቱ አገራት የቀለም አብዮት ውጤት የሆነውን የአብይን መንግስት ሰርግ ለማድመቅ ከመንገዳቸው ወጥተውም ቢሆን ከበሮና በገና ይዘው ሽርጉድ ሲሉ የከረሙት።

አንዳንድ ሰዎች የኤርትራ መንግስት የልኡኳን ቡድን መላኩ እየተገረሙም ቢሆን ለሰላም ዝግጁ የሆነ የመሰላቸው አሉ።ከሁሉም በፊት ለሰላም ፍላጎት ቢኖረው ኑሮ እስካሁን ለምን ወደ ሰላም አልመጣም ? ለሁላችንም ግልፅ መሆን ያለበት ዶክተር አብይ ያመጣው እየተባለ የሚዘመርለት ትተን ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ የወሰነው በመርህ ደረጃ ብዙም ልዩነት አለው አይባልም። መለስ በነበረ ግዜ ኢህአዴግ ያለው “ብንወደውም ብንጠላውም ውሳኔው  ተቀብለነዋል።እንዴት እንደምንተገብረው ግን እንነጋገር” ነው ያለው።በኃይለማርያም ግዜ ይባስ ብሎ “ለመነጋገርና ችግሩ ለመፍታት እኔው ራሴ አስመራ ድረስ ልምጣ” ነበር ያለው።በኤርትራ በኩል የነበረው መልስ የታወቀ ነው።እንዳውም የአሁኑ ጠ/ሚኒስትራችን በቅርቡ እንደገለፁት አሁን እያደረጉት ያለው ስራ የድንበር ጉዳይ ሳይሆን ዋናው ጉዳይ የግንኙነቱ፣የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ፣የአውሮፕላኑና የባሱ መጀመር ወዘተ እንደሆነ ገልፀዋል። በኤርትራ የቀድሞ አቋም ዓይን የአሁኑ ጠ/ሚኒስትር ጉዳዩ ወደኃላ የመመለስ ያክል ነው የሚታየው።ታድያ ሻዕብያ የድንበር ጉዳይ ይቆይልን የሚል ሃሳብ ለምን ተቀበለ?ለምንስ አዲስ አበባ መጣ ? በበቂ ምክንያት ነው።

ይህ በሆነበት ሁኔታ ነው እንግዲህ ችግር የለም እኛ እንመጣለን አንተ አትድከም ብለው አ/አበባ ከች ያሉት።ሲነሱም አ/አበባ የምንሄደው ወያኔ የሞት አፋፍ መሆንዋ ስለተረዳን ነው የሚል አዋጅ ነግረው ነው የመጡት። ስለዚህ አ/አበባ የሚመጡት ወያኔ መሞቷና መቀበርዋ በማረጋገጥ ቀጥሎ ኢትዮጵያን ለማተራመስ መሃል ሸገር መገኘትን የመሰለ ነገር ስለሌለ ነው።ለነገሩ ብዙ ሰው እየተተረጎመ እንደሰማው ፕሬዝዳንቱ ወደ አዲስ አበባ የልኡኳን ቡድን እንልካለን ባሉበት መግለጫቸው “ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ እየገባች ነው ምን አይነት ለውጥ የሚለው ግን ይቆይልን” ብሏል።በግልፅ ቋንቋ ለመናገር ኢትዮጵያ ሳትበተን ኤርትራ ማደግ አትችልም በሚለው የነሱ የውጭ ፖሊሲ መሰረት “ብቻ ወያኔ አይኔ እያየ ይቀበር እንጂ የነ አብይ እንደርስበታለን የአንድ ቀን ስራ ነው።” የሚል በልባቸው የተፃፈ መሪ ቃል ይዘው ነው አዲስ አበባ የገቡት።ሻዕብያ እንዲህ እያለ ወይ ከአብይ ጋር በመመካከር የጋራ ጠላት የተባለው ህዋሃት ውጥረት ውስጥ ለማስገባት አልያም ያለውን እድል በመጠቀም ባለፈው ጦርነት የተከናነበውን ሃፍረት ያካክስልኛል በሚል ለመተንኮስ አንድ ወርም ላይጠብው ይችላል።

በአገራችን በተካሄደ የቀለም አብዮት ሌላው CIA መሳርያ አድርጎ የተጠቀመበት ኃይል የተቃዋሚው ጎራ ሲሆን በተለይ በፅንፈኝነት መንገድ የተሰለፈው ነው።አገር ቤት ያለው ፅንፈኛ አመራሮች በሶስት አመት ውስጥ ምን ያክል ግዜ አሜሪካ ደርሰው እንዲመለሱ እንደተደረጉ በግልፅ ሚድያዎች ሲነገር የቆየ ነው።በአገር ቤት በየ ኤምባሲው እየተጠሩ መሰልጠናቸው እንደተጠበቀ ነው።

በኛ አሁን የተካሄደው የቀለም አብዮት ከብዙዎች የአለማችን የቀለም አብዮቶች የሚለየውና ብዙ ታስቦበት የተሰራው ከእነዚህ ከላይ ከተገለፁት የቀለም አብዮት ሰራዊቶች በተጨማሪ የለውጥ ኃይል የሚባል ከራሱ ከገዥው ፓርቲ እንዲበቅል እና ፓርቲውን ከነ ተነሳበት ዓላማ የሚበላ ኃይል መፍጠር መቻላቸው ነው።ከገዥው ፓርቲ ኮር ኃይሉ ከተፈጠረ በኃላ በህክምና፣ በቤተስብ ጥየቃ፣ በስራ ጉብኝት፣ የክልሉ ተወላጆችን ለማነጋገር በሚልና በሌሎች ምክንያቶች  ወደ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች በመሄድ ከየመንግስታቱ በተለይ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር እየተገናኙ የስራ መመርያ እየተቀበሉ ከመመለሳቸው ባሻገር በየ አገራቱ ከሚገኙ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ኃይሎች አመራሮች ጋር በመገናኘት አሁን እያየነው ስላለን ጉዳይ ስምምነት ሲፈፅሙ ከርመዋል።ይህ አሁን ነገር ሁሉ ከሆነ በኃላ የማወራው ሳይሆን በፊት ከአንድ አመት ተኩል ገደማ  በፃፍኩት ፅሁፍ አቶ ገዱ ከአገር ወጥተው ከማን ጋር ተገናኙ የሚል ጠቋሚ ሃሳብ ጣል ማድረጌ አስታውሳለሁ።

በመሆኑም ኢህአዴግ ያለፈት አራት አመታት ቆዳው ብቻ ኢህአዴግ ሆኖ የውስጥ እቃው ሌላ ከሆነ ከራርሟል።ይህ ከውስጡ አለሁ እያለ ሸፍቶ የከረመው ኃይል በአሳዳሪዎቹ የተሰጠው ግዳጅ የመጀመርያው የመንግስት ስልጣኑን በመጠቀም ቃል እየገባ ግን ተግባራዊ ሳያደርግ በመቅረት፣ፍትህ እንዲጓደል በማድረግ፣የህግ የበላይነት እንዳይከበር በማድረግ፣የመልካም አገልግሎት ችግር እንዳይፈታ በማድረግ ህዝቡ እንዲሰላችና በኢህአዴግ ለውጥ መምጣት አይችልም ለውጥ ያስፈልጋል ወደሚል ድምዳሜ እንዲደርስ ሲሰራ ነበር። በዚህም የተሳካ ስራ ሰርቷል።

በጣም የሚገርመው ደግሞ በርካታ የድርጅቱ አባላት ሳይቀሩ ድርጅታቸው በብልጥ ሌባ መሰረቃቸው እስካሁን የማያውቁ መኖራቸው ነው።የአገሪቱ ህዝቦች ልማታቸውና ሰላማቸው በድምፅ አልባው ሌባ እየተነጠቁ እንደሆነ መረዳት የተሳናቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ነገር መጣልን ብለው ሲጨፍሩ ማየት ነው። “የሌባ አይነ ደረቅ……………..”እንደተባለው አሁንም “እኛ ኢህአዴጎች” እያሉ እነሱ ኢህአዴግ ሌላው ከኢህአዴግ ጋር አልሰምር ያለ አድርጎ መዘመር ለብዙ ሰው ይገርመው ይሆናል።ብዙ ሰው ደግሞ የቀለም አብዮቱ የአፈፃፀም ስልት አድርጎ ከነ ምክንያቱ ተረድቶታል።

በከዚህ ቀደም ፅሁፌ የሶርያ ጦርነት የሶርያውያን ብቻ እንዳልሆነና በዛች አገር ጦርነት የሶርያ መንግስት፣በተለያየ አገር የተፈጠሩና የሚደገፉ የተለያዩ የሶርያ ተቃዋሚዎች፣ አሜሪካ፣ ራሻ፣እስራኤል፣ሳውዲ፣ኢራን፣የተባበሩት አረብ ኢሜሬት፣ ቱርክ፣ከሊባኖስ ደግሞ ሂዝቦላህ በሶርያ ስም በሶርያ ምድር እርስ በርስ እየተዋጉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። አሁንም በኛ አገር ሁኔታ ሁሉም የውጭና የአገር ውስጥ የአብዮት ኃይሎች ታርጌታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ይቅርታ በወቅታዊ መጠርያው በወያኔ መንግስት ላይ መሆኑ ነው። ግን ደግሞ የሁሉም መጫወቻ ሜዳው ወያኔ (ህዋሃት)ይባል እንጂ የመጨረሻ የግብ ክልል ሲደርስ ደግሞ ሁሉም ኳሱ የሚለጋው ወደተለያየ አቅጣጫ ስለሆነ ትርምሱ እየደረሰ ይመስላል።ይህች ያልታደለች አገር ከክፉ ይሰውራት ብቻ ነው ማለት የሚቻለው።የቀድሞ የፖርላማ አባል አቶ ቡልቻ በፆለት ማገዝ ካለባቸው ያኔ ሳይሆን አሁን ነው።

ግብፅ እና ኤርትራ ከየራሳቸው አላማና ግብ ከአብዮቱ ጋር ተደምረዋል።የአማራው የፖለቲካ ሊህቅ ነን የሚሉና ለኛ ብቻ የተሰጠን ልእልና ኦሮሞን በመደገፍ ወያኔን ከጠረግን በኃላ ሌላው ነገር ለኛ ተዉት እያሉን ነው።ከነ አብይ ጋር የገቡት የይምሰል ቃል ትግስት እየጎደላቸው ካሉት ግዜ ቀድመው የጎል አቅጣጫውን እያመላከቱን ነው።ይህንን በባህርዳሩ ሰልፍ በደምብ ስለተገለፀ በርካታ የኦሮሞ ክልልን፣ የሁሉም ክልሎች ህዝቦችና ኤርትራውን ጭምር ነገሩ እንዴት ነው? የሚል ሁኔታ ተፈጥረዋል።ለምን ቢባል አንድም የፌደራል ባንዴራ በሰልፉ እንዳይታይ ከማድረግ ጀምሮ ኤርትራ ወደናታገሪሽ ተደመሪ፣ህግ-መንግስት የአማራ አይደለም ይቀየር፣ወልቃይት፣ራያ፣መተከል፣ሸዋ የአማራ ነው ዛሬውኑ ወደ አማራ ይደመሩ፣አፋር ወሎ ክፍለ ሃገር ነው እንዲሁም ይባስ ብሎ አብይን ለመደገፍ በሚል ሽፋን የተጠራን ሰልፍ አብይ ይውረድና የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚሉ መፈክሮች ተስተጋብተዋል።

በኦሮምያ አከባቢ ያለው ሁኔታ ደግሞ መልኩና ፍላጎቱ የተለያየ ነው።ኦነግ ኦሮምያንና ኢትዮጵያን በመደመር ሳይሆን ሶስት ተለያየ የሒሳብ ስሌት ይዞ አዲስ አበባ ገብቷል።ኦህዴድ ከኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ከኦነግም ከአዲሶቹ የኢትዮጵያ ገዥዎች የሆኑ ሊበራል ኃይሎች ወዴት እንደሆኑ ሳይለይላቸው አማርኛ ቋንቋ አጥንተህ በደምብ ካወራህ ብቻ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ይቻላል።ብያንስ ብያንስ ህዝብ የሚለውን ከኃላ እየተከታተልክ ሰምተህ እርምጃ መውሰድ ይጠይቅ ይሆናል ብሎ የሚያምን ነው።በውስጡ ደግሞ ከላይ በተገለፁ አስተሳሰቦች የተከፋፈለ አቋም ያለው ነው።ሌላው ቀርቶ ኦሮምያን እንኳን ከፀጥታ ችግር ማላቀቅ አልቻለም።የቦረናና የጉጂ አከባቢ ያለው ብቻ ነው ሰው እየሰማው ያለው።                 በዚህ ሁለት ሳምንት ብቻ በወለጋ ደምቢደሎ አከባቢ በርካታ የኦህዴድ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች በኦነግ ታጣቂዎች ተገድለዋል።በ28/10/2010 በጊምቢ የኦነግ ታጣቂዎች ገብተው የፀጥታ ሰዎች የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆችን የገደሉ ሲሆን የአንዱ ሟች እህት በሆነችው ባልደረባች ለቅሶ ሄደን እንደሰማነው በነገታው አስከሬናቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሸኝ መንገድ ላይ ጠብቀው ሬሳውና መኪናው ማቃጠላቸው በአንድ ኦሮሞ ብሔር ብቻ እንኳን ወዴት እየሄደ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።  

በጣም እጅግ በጣም የሚገርመኝ ነገር የአገራችን ችግር መንስኤው ምን እንደሆነ እየታወቀ ወደዛ መፍትሄ እንደመሄድ አሁንም የትግራይ ህዝብና ህዋሃት ከአፋችን አለመውጣታቸው ነው።ከዚህ በፊትም እንደገለፅኩት የጠበቀው ምርት ሳያገኝ ሲቀር ትግሬ፣አንድ ሰነፍ ተማሪ ለምን ወደቅክ ሲባል ትግሬ፣ባልና ሚስት ተጣሉ ህዋሀት የሚለው መዝሙር እስከመቸ ያቆየናል? ዛሬም ይህንን ለማንሳት ምክንያት የሆነኝ ህዋሀት ክልሌ ቅድምያ እሰጣለሁ ብሎ ቅልሎ በሚባል ደረጃ ትግራይ ከገባ በኃላም ደቡብ የተነሳው ግጭት አመራሩ ተጠያቂዎች እኛ ነን ሲል አይ ተሳስተሃል ግጭቱ የቀሰቀሰው ህዋሀት ነው ተባለ።በቤንሻንጉልስ ሲባል ሌላ ማን አለ እሱ ነዋ ተብሎ ስም እስከመጥቀስ ሄድን።

ሌላው ገራሚ ነገር በመስቀል አደባባይ ቦምብ ፈነዳ ተባለ ያለ ምንም ማመዛዘን አምስት ደቂቃ እንኳን ግዜ ሳናባክን ሃላፊነቱ ለህዋሃትና ለትግራይ ህዝብ ተሰጠ።ጉዳዩ ከሌላ ጋር እየተያያዘ እንዳለ በግልፅ እየታወቀ እያለም ይህ ወሬ እንዲበርድ አይፈለግም። እኔ እንደ ታዘብኩት ማንም ሰው ህወሃት ለአብይ አልሞ ተኩሶ ሌላ ሊገድል አይችልም የሚል ሰው እንኳን አልሰማሁም። ለምን ቢባል ቢያንስ ኢላማ እንደማይስት ታሪካችን ነግሮናልና ነው።ህዋሃት ቢፈልግ ከአግአዚም በሉት ከሌላ አንድ አልሞ ተኳሽ ኮማንዶ አምጥቶ ጨዋታው ያጠናቅቀው እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። ህዋሃት ሂደቱ ባይጥመውም ለአገራዊ መግባባትና ለሰላም ብሎና ህገ-መንግስቱ ለማክበር ብሎ ሳሞራ ታንክና ቢኤም እንዲሁም ተዋጊ አውሮፕላኖች አስረክቦ በሰላም ከተሸኘ በኃላญญญ  አንዲት ቦምብ ይዞ መስቀል አደባባይ የሚገኝበት ሁኔታ እስኪ አስቡት። እኔ አሁን አሁን ህዋሀት የተባለ ድርጅት ይህን ያክል ተፅእኖ ፈጣሪ እንደነበር ማሰብ የጀመርኩት ገና አሁን ነው።ደርግ በመደምሰስ የበላይ እንደነበር ያኔ እነ ገዱም ሳይቀር ይነግሩን ስለነበር ማወቅ ብችልም ከዛ በኃላ የመጣው የአዲስ አገር ግንባታ፣እድገት፣ሰላምና ጅምር ዴሞክራሲ ሁላችንም እኩል ድርሻ እንዳልነበረን ነው አሁን እየተረዳሁ ያለሁት።

እሱ ብቻ አይደለም ህዋሃት የምርጫው ጉዞ ጤነኛ እንዳልሆነ ከመረዳትም አልፎ በግልፅ በመድረክ አንስቶ መወያየቱን ኦህዴዶች ነግረውናል።የአገር ግንባታ ሂደቱ እንዲበላሽ ቢፈልጉ የምርጫ ሂደቱን በማደናቀፍ መከላከያ ጣልቃ እንዲገባ አድርገው ጨዋታው መቀየር ይችሉ ነበር።ይህንን አላደረጉም።ሌላው የአፍሪካ መከላከያ ኃይል እንኳን ምክንያት አግኝቶ ምክንያት ፈልጎም ቢሆን ምን እንደሚያደርግ የምናውቀው ነው።በሳሞራ የሚመራ መከላከያችን ግን ህገ-መንግስቱ አደጋ ላይ ወድቆ  እያለና አገር ከአንድ ወር በላይ ያለ መሪ በነበረችበት ሁኔታ እንኳን ጣልቃ ለመግባት አላሰበም።ሳሞራን ማመስገንና ማድነቅ ይገባን ነበር።ተቃዋሚ ኃይሎችም ጭምር።ይህንን አልሰማንም።ለምን ትግራይ ነው።ለምን ህዋሀት ነው።በርካታ ሰው የሚድያ ሰዎችም ጭምር ደብረፅዮን በምርጫ ሁለት አመጣ ብለው ሲተርቡት አሁንም ድረስ አሉ።ግን ህዋሃት እኳ በስብሰባው ከ40 ያላነሰ ቁጥር ነበረው።ሁሉም ለደብረፅዮን ድምፅ መስጠት ይችል ነበር።አላደረገውም።በተሃድሶ የታየበት ችግር ለመቅረፍ ቆርጦ መነሳቱንና ከኔነት አልፎ ለመርህ ድምፅ ሰጥቷል ማለት ነው።እንዲህ በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባ ነበር ባይ ነኝ።ህዋሀት አሸባሪ ተብሎ በየቤቱ የሚዘመርበት ግዜ መመስገን ነበረበት ስል ከእብደት የምትቆጥሩት ወይም ዘሬ ወደ መቁጠር የምትሄዱ ትኖራላቹ።ሁሉም የማወራው በእምነትና በእውነት ነው።የማንንም ብሔር አባል እንሁን እውነትን ግን በዚህ ደረጃ ነው መጋፈጥ ያለብን።

ከመጀመርያው ግዜ ጀምሮ በሁሉም ፅሁፎቼ ደጋግሜ ያልኩት ነገር አገር እየጠፋች ስለሆነ አገር ከመፍረስ የሚያድን መጥፎ መንግስትም ቢሆን ይኑረን የሚል ነው።የዶክተር አብይ መንግስት ስለ አፈጣጠሩ ትተን ያገኘው አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ተሻለ የመውሰድ እድል አግኝቶ ነበር።እኔም አገር እንዲኖረኝ ምንም ይሁን ምን መንግስት የሚባል አካል ይኑረኝ በሚል ሒሳብና አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ በኃላ በተወሰዱ እርምጃዎች አንዳንዶቹ የምደግፋቸው ስለ ነበርኩ የአብይን መንግስት ከነ ስጋቱ በበጎ አጋጣሚ ተቀብየው ነበር። የተቀበልኩት ግን በኦሮ+ማራ ሒሳብ አይደለም ።ሳትበተን ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትኖረኝ ከመፈለግ ከነበረው ሁኔታ አንፃር በመልካም አጋጣሚ ስላየሁት ነው።የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የድጋፍ ሰልፍና ጩኽትም ከዚህ ተስፋ የተለየ አይደለም።

አሁን ወደ ባሰ ጭንቀት እየወሰደኝ ያለው  “የደህንነታችን ስጋት የሆነውን ወያኔ አብረን እናጥፋ” በሚል የተሰባሰበው ኃይል እርስ በርሱ የሚባላበት ግዜ እየቀረበ መምጣቱ እያየሁ ስለሆነ ነው።ለኔ የውጭ ኃይሎችን ትተን በነገው የኦሮ+ማራ ግንኙነት እየመጣ ያለው አደጋ ነው አገር ወደከፋ ችግር የሚያስገባት። ኦሮማራ ማለት የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ማለት አይደለም።የቀለም አብዮት መሃንዲሶች አገር ለመበተን የተጠቀሙበት በውግያ ስልት የተደራጀ የነውጥ ኃይል ብቻ ነው።ይህ ኃይል የየራሱ አጀንዳ ይዞ የተደራጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወያኔ ወደ ትግራይ ከሸኘን በኃላ ወዴት? የሚል ጥያቄ የየራሱ ገነ በጣም ተቃራኒ መልስ በውስጡ ይዞ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። መልሱ ደግሞ በኦሮሞ በኩል በአዲስ አበባ ዙርያ ወጣቶቹና በነቀምት ሰልፍ የተገለፀ ሲሆን ኦህዴድም በሃሳብ እየደገፋቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ለማድረግ ቀስ እያለ  መሰረት መጣል ጀምረዋል።የአማራው የባህርዳሩ ሰልፍ ግልፅ ያለ መልስ ሰጥቷል። የብአዴን አመራርም ድጋፉ የገለፀበት መንገድ ሁላችንም ሰምተነዋል።ዶክተር አብይ በሰነፍ ክር የተሰፋው ቡቱቶ እንዳይፈታ በመፍራት ግን ደግሞ ስጋት ውስጥ በመግባት የባህርዳሩ ሰልፍ ፀረ-መደመር ነው ብሎ ላለመናገር በሚድያ ቀርቦ በአናሳ  ክልሎች ግጭት የሚቀሰቅስ ኃይል ስላለ ተጠንቀቁ በሚል ከዚህ ቀደም ያስተላለፈው መልእክት በመድገም ቀስ አድርጎ የድጋፍ ሰልፉ ይቅር ብሎናል።እኔ አሁን ያለው የኦሮማራ ጥምረት ወደየመንገዱ ለመለያየትና በዚህ ውስጥ የሚፈጠር ትርምስ ኢትዮጵያ ትጎዳለች።ይህ ለመሆን ያለው ግዜ ከወራት የበለጠ አይመስልም።   

የአሜሪካ መንግስት ደግሞ እንደ ባለ ድርሻ ብቻ ሳይሆን እንደ የአብዮቱ ጠንሳሽና መሃንዲስ በዚህ ውስጥ የራሱ አጀንዳ ለማስፈፀም እየተነቀሳቀሰ መሆኑ ሌላ ምርመራና ጥናት ሳያስፈልግ የETV ዜናና ፕሮግራም ማየት ብቻ በቂ ሆኗል።እሱም በበኩሉ ጥቅሜን ለቻይና አሳልፎ የሰጠ “ስውር ሶሻሊት” የሚለው ወያኔን ለማዳክምና ከጨዋታ ውጭ የማድረግ ስራ በድል እንዲጠናቀቅና የውጭም የውስጡም ፀረ-ወያኔ ኃይል በማቀናጀት በመሃንዲሶች ቋንቋ ፍኒሽንግ ላይ ደርሷል።ይሁን እንጂ “ወያኔ አይናችን እያየን ሞቶ ቢቀበር እንኳን አናምነውም ማታ ወደየቤታችን ይመጣል” የሚለው የአገራችን ፖለቲከኞች አባባል CIAም ያለ የመሰለኝ ነገር ሰርግና ምላሹ እንዲሳካለት የቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሆነ እያየነው ነው።በዩክሬን አልሞ ተኳሾች አስገብቶ ሁለቱም ወደ ከባድ መቃቃርና የብቀላ ስሜት እንዲገቡ ራሱ ካደራጃቸው ተቃዋሚዎች አመራርና ከመንግስት አካላት እንዲገደሉ ማድረጉ ሳስብ የመስቀል አደባባዩ ቦምብ ነገር እያሰብኩ እያለ በዚህ ጉዳይ የተምታታ ዜና መተላለፉ ስሰማ ጭንቀትም አግራሞትም ነው የፈጠረብኝ።

እስኪ እንየው ቅዳሜ ፍንዳታው ተፈፀመ፣እሁድ በአንድ ምክትል ሚኒስትር የሚመራ የአሜሪካ መንግስት ልኡካን ቡድን አዲሰ አበባ ገብቶ ሰኞ ከዶክተር ወርቅነህ ጋር መገናኘቱንና የቅዳሜውን ጥቃት አውግዞ አሜሪካ ምርመራውን ለማገዝ ከFBI አንድ ቡድን መላክ እንደምትችል ገልፀው ለመንግስት ጥያቄ አቀረቡ። በዚሁ ቀን ማለትም በሰአታት ልዩነት ውስጥ የFBI የምርመራ ቡድን አባላት ስራ መጀመራቸው ተነገረን።ይህ ሁሉ የተነገረን በአንድ ETV ሲሆን ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በድርጊቱና በዜናው መካከል የአንድ እሁድ ብቻ ልዩነት እንዳለው አስቡት ። ከአሜሪካ አዲስ አበባ በአውሮፕላን  የ16 ስአታት እንደሚፈጅ  ልብ በልሉኝ።በዚህ ላይ አብዛኛው የኛ የምርመራ ባለሞያዎች እንዳይሳተፉ ተብሏል። ለምን የሚለው ግልጥ ያለ መልስ ነው ያለው።አሁን ከዚህ የምርመራ ውጤት የምንጠብቀው እውነት ሳይሆን የቀለም አብዮት ሰርግና ምላሽ አድማቂ እንደሚሆን ከግምት በላይ መሆኑ አየን።                                                                                                                                                                                                                                     

አሁን የተመሰረተው የአብይ መንግስት በቀለም አብዮት መንገድ መምጣቱ አንድ ችግር ሲሆን ሌላው ግን ሌላ ችግር መደመሩ ነው።አለምን በተለይ የአውሮፓ አገራትን ወደ ከባድ ችግር እያስገባ ያለው የህዝበኝነት መንግስት መበራከት ነው።በአውሮፓ በርእሰ መንግስት፣በህግ አውጪ አካል እንዲሁም በቅርቡ በጣልያን አገር እንደሆነው በጥምር መንግስት የህዝበኝነት አቀንቃኞች በያዙት ቦታ የአውሮፓ ህብረት የመበተን አደጋ ተጋርጦበታል። በኛም አገር የህዝበኝነት አደጋ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ እኔም ከኔ በተሻለ ደግሞ ሌሎች ገልፀውታል። ከዚህ በፊት ህዝባዊነት፣ህዝበኝነትና ፀረ-ህዘብነት በሚል በሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እስካሁን ባሉት ማለቴ ነው የህዝበኝነት ባህሪ እንደወረራቸውና አንዳንዴም ፀረ-ህዝብነት የሚገለፅበት ሁኔታ መኖሩ ገልጨ በዋነኝነት ግን አሁን አገር ለማስተዳደር እድል ያገኘው የአብይ ኦህዴድ ላይ እንደሚጎላ ከነ መገለጫዎቹ ለማቅረብ ሞክሬ ነበር።ይኸው አሁን ደግሞ ባለ ውለታቸውን ህዝበኝነትን ይዘው አራት ኪሎ ገቡ።ስለዚህ ህዝበኝነት አለም እያሰጋ ያለና አገራችን ለማጥፋት ብዙ መንገድ የተጓዘ መሆኑ እየታየ ስለሆነ ዜጎች ሁላችን የመንግስታችን ባህሪ ተረድተን ከቻልን ለማረም ካልቻልን መሳርያ ባለመሆን አገራችንና የእያንዳንዳችን ቤት እንጠብቅ ባይ ነኝ።

ለማጠቃለል ይህ አሁን ያለው መንግስት የኢህአዴግ መንግስት እንዳልሆነ የማያጠያይቅ ሆኖ አገር ማቆየት የሚችል ቢሆን መቀበሉና ደግፎ ማቆየቱ ችግር አልነበረውም።ከዚህ መርህ አንፃር እኔም መተንፈሻ የሚሆን መፍትሔ መጣ ብዮ ከነስጋቴም ቢሆን ደጋግፎም ቢሆን መንግስት ይኑረን የሚል ሃሳብ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ እንደነበርኩ የምታውቁኝና በጋራ የምናወራ ሰዎች የምታውቁት እውነታ ነው።አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከመቸውም ግዜ በላይ አስፈሪና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባታችን እንደ ንጋት ፀሐይ ጎላ ጎላ እያለ እያየነው እንገኛለን።ምክንያቱም በአዲሱ የአካውንቲንግ አሰራራችን መሰረት የተለያየ አቋም ያለው ኦነግ፣ደርግ፣የተሰነጣጠቀ ኢህአዴግ፣በርካታ የመገንጠል ኃይሎች፣በርካታ ኤርትራን ጨምሮ የአንዲት ኢትዮጵያ አራማጅ ኃይሎች፣የኤርትራ መንግስት፣ግብፅና CIAን ደምሮ አንድ መንግስት መፍጠር ስለማይቻል ነው።ይህ ሁሉ ወደ አንድ ቋት አስገብተን አንድ ምርት ለማግኘት ብትፈጨው ውጤቱ ዲዲት እንጂ የስንዴ ዱቄት ሊሆን አይችልም።ስለዚህ ሁል ግዜ እንደምለው ወደኃላ መቁጠር የጀመረ የፈንጅ ደቂቃ ላይ ሆነን መጠበቅ የለብንም።

ለሁሉም አይነት አስተያየት በተለመዱት መስመሮቼ ፤

ኢሜይል agerawiguday@gmail.com    

Facebook selamwerq huluager እንገናኝ።

 

Back to Front Page