Back to Front Page


Share This Article!
Share
እድገቱ ይቀጠል ወይስ ይብቃን?

እድገቱ ይቀጠል ወይስ ይብቃን?

ለሚ ዋቄ 06-25-18

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች በከፊልና በሙሉ ወደግል ይዞታነት እንዲሸጋገሩ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል። በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ፤ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ ነው የተወሰነው

Videos From Around The World

የኢፌዴሪ መንግስት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመንስት ይዞታ ስር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን በሽያጭ ወደ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ሲያዞር መቆየቱ ይታወቃል። የሰሞኑም ውሳኔ የዚህ ቀጣይ ነው። ምናልባት በሰሞኑን ውሳኔ ልዩ የሚያደርገው፣ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ይዞታ ስር አይወጡም ተብለው የሚገመቱት ኢትዮ ቴሌኮምና የሃይል ማመንጫዎች በከፊልም ቢሆን ወደግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ መወሰኑ ነው። ሌላው ልዩ ነገር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው የኢትዮጵያን ሰንድቅ ዓላማ ይዞ በመላው ዓለም የሚዞረውና የኢትዮጵያውያን ሃገራዊ ኮራት ተደርጎ የሚቆጠረው፣ ይህም ለኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚያዊ ያልሆነ የማይጨበት ሃብት (intangible asset) ተደርጎ የሚወሰደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፊል እንዲዘዋወር መወሰኑ ነው። በመሰረቱ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደግል ይዞታ አይዘዋወርም ተብሎ አያውቅም። በመሆኑም በአጠቃላይ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ያልተጠበቀ ተደረጎ የሚወሰድ አይደለም።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ወገኖች ውሳኔውን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እስካሁን ሲከተለው ከቆየው የልማታዋ መንግስት ፖለሲ እንዳፈነገጠ አድርገው የወሰዱበትን ሁኔታ ታዝበናል። አንዳንድ ዜጎች ደግሞ በሃገሪቱ ኢኮኖሚና በዜጎች የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮ ቴኮምና የሃይል ማመንጫዎች ወደግል ይዞታ መዞር ከዋጋና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ አሉታዊ ተዕእኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

እንግዲህ፤ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ያለፉ ዓመታት የልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል። ይህ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይ ባለፉ አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ገደማ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ አስችሏል። በመሆኑም በርካታ ኢትዮጵያውያን ፖሊሲውን በበጎነት ይመለከቱታል። ከሃያ ሰባት ዓዐመታት በፊትም ሃገሪቱ በእዝ ኢኮኖሚ ስር ስለቆየችና አብዛኞቹ የሃገሪቱ የልማት ድርጅቶች በመንግስት ሲተዳደሩ የቆዩ በመሆናቸው የልማት ድርጅቶች ወደግል መዞር ወደማያውቁት ዓለም የመግባት ያህል ስጋት የሚፈጥርባቸው ዜጎችም ቁጥር ቀላል አይደለም። በተለይ በግል ይዞታ ስር ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚገመተውን የስራ ዋስትና የማጣት ስጋት ብዙዎች ይጋሩታል። እነዚህ ሁኔታዎች ተዳምረው ህዝቡ የልማት ድርጅቶች በተለይ የግዙፎቹ ወደግል ይዞታነት መዞር ስጋት ያሳድብተል።

በመሰረቱ ልማታዊ ፖሊሲ መንግስት የልማት ድርጅቶችን በባለቤትነት ይዞ ከሚያስተዳድርበት የእዝ ኢኮኖሚ ስርአት ፍጹም የተለየ ነው። የልማታዊ መንግስት ግብ የግል ባለሃብቱ ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረበት ገበያ መር የካፒታሊስት ኢኮኖሚ መገንባት ነው። የእድገት ጉዟቸውን ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያደረጉ ታዳጊ ሃገራትም ግብ ይሄው ገበያ መር የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ መገንባት ነው። ከመድረሻ ግብ አኳያ የልማታዊ መንግስትና ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመሳሳዮች ናቸው። ልማታዊ መንግስትን ከሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚለየው አካሄድ ነው። ልማታዊ መንግስት በተለይ የግሉ ዘርፍ ባላደገባቸውና የካፒታል አቅም ያላቸው ባለሃብቶች በሌሉበት የታዳጊ ሃገራት ኢኮኖሚ ውስጥ መንግስት በተመረጡ ዘርፎች ጣልቃ በመግባት የኢኮኖሚ ተሳትፎ የሚያደርግበት ነው። በተለይ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁ፣ የትርፍ ጊዜያቸው ረጅም የሆኑና በኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው የግል ባለሃብቱ የማይደፍራቸው ዘርፎች ላይ መንግስት የካፒታል በጀት በመመደብ ይሳተፋል።

ይሁን እንጂ፤ ልማታዊ መንግስት የግል ባለሃበቶች በቁጥርና በካፒታል አቅም እየበዙና እየጎለበቱ ሲመጡ ደረጃ በደረጃ ከኢኮኖሚው ውስጥ እየወጣ፣ በወጣበት ልክ የግሉን ድርሻ እያሳደገ ይዘልቃል። በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ይህ ሲደረግ ቆይቷል። ከሁለት አስርት ዓመታትና አሁን መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ በየዘርፉ ያለውን ድርሻ መመለከት ለዚህ በቂ አሰረጂ ነው። ከአስር ዓመት በፊት የሃገሪቱ የቢራ ምርት ሙሉ በሙሉ በመንግስት የተያዘ ነበር። አሁን ግን አንድም በመንግስት የተያዘ የቢራ ፋብሪካ የለም።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው አሁንም ከልማታዊ መንግስት ፖሊሲ ያላፈነገጠ መሆኑን እንረዳለን። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ በልማታዊ መንግስት ፖሊሲ አተገባበር መሰረት መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ እየቀነሰ፣ በሌላ በኩል የግሉ ዘርፍ ድርሻ እያደገ የሚሄድ መሆኑን ያመለክታል። ስራ አስፈጻሚው ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ፣ አፈፃፀሙ የልማታዊ መንግስትን ባህሪያት በሚያስጠበቅ፣ የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ እድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፒሊን ተግባራዊ እንደሚደረግ አሳውቋል።

ከዚህ የኢህአዴግ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የተነሳው ሌላው ጉዳይ የህዝብን ተጠቃሚነትና የአገልግሎት ዋጋ የሚመለከት ነው። በቅድሚያ በተለይ በህዝቡ ኑሮ ላይ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ቴሌኮምና ሃይል ማመንጫ የመሳሰሉት ዘርፎች ወደግል የሚዘዋወሩት ሙሉ በሙሉ አይደለም። አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት አብላጫውን ድርሻ ይዞ አናሳውን ነው ወደግል የሚያዞረው። በመሆኑም የኩባንያ ውሳኔ አሰጣጥ ላይ መንግስት የወሳኝነት አቅም ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የግል ኩባንያ ሁሌ ዋጋን እንደፈለገው የመወሰን የሞኖፖሊ አቅም እንዳለው ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በተለይ ቴሌ ኮምን የመሳሰሉ ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎት ስርአት ስለሚዳኙ ዋጋን እንደፈለጉ የመወሰን አቅም አይኖራቸውም። የአገልግሎት ዋጋ በጨመረ መጠን ውድደሩ እየከበደው ይሄዳል። በተጨማሪ ዋጋ የሚገኘውን ትርፍ የሚሻሙ ተፎካካሪዎች ወደአገልግሎቱ ስለሚገቡ የአገልግሎት ዋጋው መሆን ከሚገባው በላይ ሊሆን አይችልም።

ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዜጎች የልማት ድርጅቶቹን ይዞታ በከፊልና በሙሉ ወደግል ማዞር በዚህ ወቅት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ተደምጧል። በዚህ ጉዳይ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውበታል። እነዚህ አስተያየቶች ጠቅለል አድርገን እንመልከታቸው።

የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በወጭ ንግድ መዳከምና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ አደጋ ውስጥ መግባቱ ለውሳኔው ምክንያት ሆኗል። ባለፉት ጥቂት አመታት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ በአማካይ ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ላይ ሲቆም፣ ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ ከ16 እስከ 17 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የኢትዮጵያ የብድር ምጣኔ የአጠቃላይ አመታዊ ምርቷን 59 በመቶ መያዙን፣  የብድር ጫናውም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ የብድር ጫና መሸጋገሩን አሳውቋል። አሁን ባለው ሁኔታ ሃገሪቱ ወደ ከፍተኛ የብድር ጫና ውስጥ እየገባች መሆኑን መንግስትም እየተቀበለ ነው። በዚህ ሁኔታ ሃገሪቱ ተጨማሪ የካፒታል ብድር ማግኘት አትችልም። የሃገሪቱ የብድር ጫናአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት አኳያ ሲታይ የውጭ ባለሀብቶች ወደሃገር ውስጥ እንዲመጡ የሚያበረታታም አይደለም። ይህ ሁኔታ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ የሚያስችል ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን አስፈላጊ አድርጓል።  ይህ ደግሞ በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን በከፊልና በሙሉ ወደግል ይዞታ (ለውጭ ባለሃብቶች) ማዞሩን አስፈላጊ አድርጎታል።

በሌላ በኩል፤ ሀገሪቱ ለቀጣይ ሁለት አመታት ብድር ለመክፈል ስድስት ቢሊየን እንዲሁም፣ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ለሁለት አመታት ለማስፈጸም ሰባት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ያስፈልጋታል። እንደ ስኳር ላሉ ፕሮጀክቶች የተወሰደው ብድር ደግሞ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ወደ ምርት ሳይገቡ እዳ መክፈያው ጊዜያቸው ደርሷል። ነዳጅና ሌሎች የፍጆታ ሸቀጦችን ማስገቢያ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እጅጉን ከፍ እያለ ነው የሚሄደው። ይህም የልማት ድርጅቶችን ይዞታ ወደውጭ ባለሃብቶች ለማዞር የተላለፈው ውሳኔ መነሻ ምክንያት ነው።

በአጠቃላይ አሁን በሃገሪቱ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወደፊት መጓዝ የሚያስችል አይደለም። አዲስ የልማት ስራዎችን ማከናወን፣ የተጀመሩትን የማስጨረስና ከውጭ የሚገቡ የፍጆታ ምርቶችን ወጪ መሸፈን የሚያስችል አቅም የለም። ተጨማሪ ካፒታል ወደኢኮኖሚው እንዲገባ ካልተደረገ አሁን ባለው ሁኔታ ላለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት በተከታታይ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል አይቻልም። ኢኮኖሚው ካላደገ ሃገሪቱ ውስጥ ፖለቲካ ቀውስ የመፍጠር አቅም ላለው ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር የስራ እድል መፍጠር አይቻልም። የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ውሳኔ መነሻዎች እነዚህ ናቸው። ውሳኔው የሃገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት የማስቀጠል ወይም እድገትና የእድገት ፋይዳዎች ይብቁን በሎ የማቆም ጉዳይ ነው። የኢኮኖሚ እድገት መቆም የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ግን ሃገሪቱ ልትሸከመው የሚቻላት አይደለም።

 

 

Back to Front Page