Back to Front Page


Share This Article!
Share
ይቅርታውን በተፃራሪ!!!

 

ይቅርታውን በተፃራሪ!!!

 

ተክለሚካኤል 08-02-18 Email tekle855@yahoo.com

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በየቀኑ ምክንያታዊ ባልሆነና ማንነት ላይ ያነጣጠረ በየክልሉ እየታየ ያለው ግድያና ዝርፊያ የክልሎችና ፌደራል መንግስታት የተፈለገውን መልክ ላስይዙት ስላልቻሉ ከቁጥጥር ውጭ የመሆን እድሉ እየሰፋ ይገኛል፡፡ህብረተሰቡ የአሕኣዴግ ጥልቅ ተሃድሶና ለውጡ ተሰፋ የጣለበት ቢሆንም በእኔ እይታ የተመዘገቡ ለውጦች ቀላል ባይሆኑም እንደ ተጠበቀው ሆኖ ኣላገኘሁትም፡፡

ሁላችን ልንገነዘበው የሚገባ እኛ እናውቅልሃለን የሚሉትን የፖለቲካ ሊሂቃን ካልጋረዱት ንፁሃን ዜጎችን በመግደል ፣ በማፈናቀል ፣ በመዝረፍና ሽብር በመፍጠር የሚስተካከል ችግር እንደሌለ የኢትዮጵያ ህዝብ ኣበክሮ ያውቃል፡፡ በተለይ ኮሽ ባለ ቁጥር የህወሓት እጅ ኣለበት እየተባለና የማሕበራዊ ሚዲያ ፍረጃ በመከተል በኣማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በንፁሃን የትግራይ ተወላጆች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ የተጓደለ ስብእና ካላቸው ሰዎች የሚመነጭ ቢሆንም ድርጊቱ በጠራራ ፀሓይ ሲፈፀም ዜጎች ህጋዊ ከለላ መነፈጋቸው በኣማራ ክልል መንግስት ይሁንታ እየተፈፀመ ነው ወደ ሚያሰኝ ድምዳሜ እየወሰደን ነው፡፡ እነዚህ የጥፋት ፈፃሚዎችና ኣስፈፃሚዎች የሰው ቁመና የራቃቸው ኣውሬዎች መሆናቸውን እንጂ ሰው ባልዋለበት ወንጀል ለሌላ ወንጀለኛ ማካካሻ ማድረጉ ምንኛ የዘመኑ ኣሳፋሪ መሆኑን ስለሚያውቅ በትግራይ ህዝብ በኩል በቀልን በበቀል ማወራረድ የማይታሰብና የማይታለም ሲሆን ፀረ ህዝብ ወይም ጠላትን መለየት ግን ያውቅበታል፡፡

ጥቃቱ በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም እሳቱ ለኣማረ ሰላማዊ ህዝብም በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ጉዳት ማድረሱ ኣይቀሬ ሲሆን የክልሉ መንግስትም በትግራይ ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ያለው ወንጀል ዓይቶ እንዳላየ መሆን ስለመረጠ እንጂ ሁኔታው ከቁጥጥሩ ውጭ ነው ብሎ ማመን ያስቸግራል ብቻ ሳይሆን ከባድ ዋጋ እንደ ሚያስከፍልም መገመት ጥሩ ነበር፡፡

ስለዚህ ችግር ካለ ስነ ስርዓት በጠበቀ መልኩ እንዲፈታ ማድረግ እንጂ ይህንን የመሰለ ስርዓት ኣልበኝነት ለማንም የማይበጅና የኢትዮጵያውነት እሴቶቻችንን ኣጠልሽቶ የሚያናቁረን ሊሆን እንደ ሚችል መገመት ኣያዳግትም፡፡ተንኮል ለሰሪው እሾህ ላጣሪው የሚለው የኣበው ኣባባልም ማሰቡ ጥሩ ነበር፡፡ ኣሁን ያለው ኣማራጭ መጀመሪያ የኢሕኣዴግ ኣባል ድርጅቶች የውስጥ ችግራቸው ወደ ህብረተሰቡ እንዲዛመት በማድረግ የተፈጠረ ችግር እንደሆነ መገንዘብ የኢትዮጵያ ወጣቶች ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል፡፡ችግሩ ሊፈታ ከተፈለገ ደግሞ ወጣቶች ማሕበራዊ ሚዲያውን ለሰይጣናዊ ጨዋታ ማድረግ ትተው ችግሮቹና የችግሮቹ መንስኤ በጥልቀት የሚያዩበትና የሚነጋገሩበት የጋራ ኣጀንዳ በመዘረጋትና በድርጀቶቹ ላይ ኣዎንታዊ ጫና በማሳረፍ ማሕበራዊ ሚዲያው ለኣገር ሰላም በማዋል ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡የሃይማኖት መሪዎች ፣ የኣገር ሽማግሌዎችና ምሁራንም የማስታረቅና ግንዛቤ የመፍጠር ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ይጠበቃል፡፡

Videos From Around The World

ሌላው የኣማራ መገናኛ ብዙኃንና ኢቢሲ በእስር ቤት ቆይታቸው ድብደባና ኢሰብኣዊ በደል የደረሰባቸው ወገኖችን ችግር ለህዝብ ማስተላለፋቸው ዳግም እንዳይፈፀም ለማስተማርያ ታስቦ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡ነገር ግን የብኣደንና የኣማራ ክልል መንግስት እጅ እንደሌለበትና በኣማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንደ ተካሄደ ኣስመስሎ ማቅረብ እየተፈጠረ ላለው ግድያና ዝርፊያ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ይሁንና የተፈፀመው በደል ሁሉ የህወሓት ባለ ስልጣናት እጅ ብቻ እንደ ነበር ኣስመስሎ እየቀረበ ያለውን ይሁንላችሁ ቢባል እንኳን ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚያገናኘው የቱ ላይ ነው? የትግራይ ተወላጆች እንደወትሮው የኣማራ ወንድም ህዝብ ኣለን ብለው ኑሯቸውን ለማሸነፍ በክልሉ ደፋ ቀና በሚሉበት ጊዜ የበቀል መወጣጫ ማድረጉ በምን መስፈርት ቢለካ ነው? መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች እየተከሰቱ ቢሆንም የግጦሽ ፣ የወሰን ፣ ይእርሻ ፣ የግለ ሰዎች ጠብ ወዘተ የመሳሰሉ የተለያዩ ፍላጎቶች እንደ መነሻ ምክንያት መሆናቸውን ሲነገር እንሰማለን፡፡

በኣማራ ክልል ኣንዳንድ ቦታዎች ግን የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ ህይወታቸው የጠፋ ፣ ንብረት የተዘረፈባቸውና የተቃጠለባቸው ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ በታሪክ እንደምንከታተለው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው በመላ ኣገሪቱ ሰርተው የመኖር ችግር እንዳልነበረ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡በተለይ የትግራይ ተወላጆች በጎንደር መኖር ኣዲስ ሳይሆን ከጎንደር ዘመነ መንግስት ጀምሮ በስፋት የሚታወቅ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ ኣሳፋሪ ድርጊት ግን ታይቶም ተሰምቶም ኣይታወቅም፡፡

መንግስት ባለበት ኣገር ሰው እንደ ኣወሬ ተቀጥቅጦ ሲገደል በህዝቡ ላይ የሚፈጥረው ስቃይ ላንዳንድ ግብዞች ባይገባቸውም ለሰፊው የጎንደር ህዝብ ግን ስቃዩ ከምንገምተው በላይ እንደ ሆነ ይሰማኛል፡፡ይኸውም በደርግ ጊዜ በጎንደር ወጣቶች ላይ የተፈፀመው ግፍ ከጎንደር እናቶችና ከጎንደር ህዝብ ህሊና በቀላሉ የሚወጣ ኣይደለምና፡፡

ከ1969 እስከ 1971 ዓ.ም ከወላጆቻቸው እቅፍ እየተነጠቁ በጠራራ ፀሓይ መንገድ ላይ የተገደሉ ወጣቶች ምን ግዜም ቢሆን ከህሊና ኣይጠፋም ብቻ ሳይሆን ከልቅሶና ፀሎት በዘለለ ኣንጀት የሚበላ የህዝቡ እንጉርጉሮ እስከ ኣሁን ድረስ የስንቱን ህሊና እያናጋ የሚኖር ሲሆን ሳይሆንላቸው ቀርቶ እንጂ እየተደረገ ያለው ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ ለጎንደር ወላጆች ጠፍቷቸው ኣይደለም፡፡ከማስታውሳቸው ጥቂቶቹ እንጉርጉሮዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

በ1969 ዓ.ም ሕዳር ወር ወጣቶችና ተማሪዎች ፒያሳ ላይ ሲጨፈጨፉ የተባለው

የዝና ታደሰ ኣልሞተች ተገኘች

ማኸል ፒያሳ ላይ በደም እየዋኘች

የተማሪ ደብተር ኣልጨፋም ተገኘ

ማኸል ፒያሳ ላይ በደም እየዋኘ

ጭፍጨፋው በቀይ ሽብር ሲቀጥልም የሚከተለውን ይባል ነበር

ሻለቃ መልኣኩ የእግዚኣብሄር ታናሽ ወንድም

ለዛሬ ማርልኝ ከንግዲህ ኣልወልድም

የደርጉ መኪና ሸራ የለበሰው

የጎንደሩ ወጣት ወዴት ኣደረሰው

ስለዚህ እንደዚህ የመሳሰሉ ጠባሳ ትዝታዎች እየተደገመ እንዳይሆን ቆም ብለን ማሰብ ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡

እስኪ በዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ በጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት በጠራራ ፀሓይ ኣደባባይ ለይ እንደ እባብ ተቀጥቅጠው የተገደሉ ይትገራይ ተወላጅ ወጣቶች የህይወት ኣድን ከለላ ባያገኙም ኣስከሬናቸው ሙሉውን ቀን በወደቁበት ተጥሎ መዋሉ መንግስት ኣለ ለማለት ያስደፈራል? በመጨረሻ እግዚኣብሔር ለሁለችንም ኣስተዋይ ህሊና ሰጥቶ ሰላሙን ይስጠን፡፡ ኣሜን!

 

Back to Front Page