Back to Front Page


Share This Article!
Share
“በእሳተ ገሞራ ውስጥ ያንቀላፋች ሀገር”

“በእሳተ ገሞራ ውስጥ ያንቀላፋች ሀገር”

 

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ 09-05-18

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

 

ለውጥ በሰው ልጅ ያለፈ፣ ያለና የሚኖር ኹለንተናዊ ሂደት ውስጥ ባሕሪያዊና ጠባያዊ ነው፡፡ ሰው በባህሪውና በጠባያቱ ለውጥን ይሻል፡፡ በሌላ በኩል በኹኔታዎች አስገዳጅነት ኹለንተናዊ እምነቱን፣ እውቀቱንና ድርጊቱን ከአኗኗሩ አንጻር ይለውጣል፡፡

   በሀገራችን ለውጥና ከለውጥ ጋር የተያያዙ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎች በተለያየ መንገድ ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በሂደቱም በርካታ አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች ያሏቸው በተለያየ አተያይ የተለያየ መልክና ትርጓሜ የተሰጣቸውና የሚሰጣቸው ክንውኖች እንመለከታለን፡፡

   ከወቅታዊ የሀገራችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኹነቶች አንጻር ነገሮችን ስንመለከት በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሣ ግድ ከሚሉን ውስጥ አንዱና ዋነኛው “ዕውን የኢትዮጵያ ጠላት ማን ነው?” የሚል ይኾናል፡፡ ዕውን ኢትዮጵያ ዛሬ ጠላት አላት? የሚል ጥያቄን እናገኛለን፡፡

እንደሀገር በተለያዩ ገለጻዎች፣ ትንታኔዎችና ጽሑፎች ኢትዮጵያ ጠላት እንደነበራትና እንዳላት ሰምተናል፡፡ እንዲሁም በርካታ ጽሑፎችን አንብበናል፡፡ በተለያዩ ክስተቶች ላይ ሲጠቀስም በደንብ እናውቃለን፡፡ ዕውን ግን ኢትዮጵያ ጠላት አላት? የሚል ጥያቄን ለምን እናነሣለን? ከምንስ አንጻር ነውእያነሣን ያለነው?

Videos From Around The World

ጠላትነት ሁለትዮሽ ነው፡፡ ጠላት ተደራጊና አድራጊ፤ጠይና ተጠይ አለበት፡፡ጠላትነት ውስጥ ትግል አንዱና ዋነኛው መገለጫ ነው፡፡ እንደየጠላትነቱ ዓይነት፣ ይዘትና አድማስ መስዋዕትነቱም እንዲሁ ኹለንተናዊ ነው፡፡ ጠላት ያለው አካል አያንቀላፋም፡፡

ስለኾነም እስኪ የኢትዮጵያ ጠላት ማን ነው? የሚለውን ከጠላትነት የትርጓሜ አድማስ አንጻር በመጠይቅ ቅርጽ እንመልከተው፡፡

አንደኛ፡- ጠላት ያለው አካል አያንቀላፋም፡፡ ጠላት ያለው አካል ራሱን ለማጠናከር የሚተጋውን ያክል ጠላቱን ለማዳከም ቀን ከለሊት ይተጋል፡፡

v  ታድያ እኛ ኢትዮጵያውያን የማናንቀላፋበት ምን አለን? ቀን ከለሊት የምንተጋበትስ ምን ኹለንተናዊ ነገር አለን? ራሳችንንስ ለማጠናከር ከጠላት አንጻር ምን እናደርጋለን? ጠላታችንንስ ለማዳከም ምን እየሰራን ነው?

ሁለተኛ፡- ጠላትነት ውስጥ በባላንጣነት መተያየት አለ፡፡

v  እኛ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት በባላንጣነት የምናየው ማንን ነው?

ሶስተኛ፡- ጠላትነት ውስጥ ቁጭት፣ እልህና ማንባት አለ፡፡

v  እኛ ኢትዮጵያውያን ከጠላታችን አንጻር ወደ ታች የቀረንበትና ኃላ ቀር በኾንበት ቁጭትና እልህ የፈጠርንበት፤ እንደሀገርስ የምናነባበት ምን አለን? ሃያ አራት ሰዓታት የሚተጋ ከጸጥታ መዋቅር ውጭ ምን አለን?

አራተኛ፡- የጠላት መኖር አካልን አንድ ያደርጋል፡፡ ልዩነት እንኳ ቢኖር ከልዩነት በላይ በሕብረትና በአንድነት የመቆምን ነገር ያመጣል፡፡ አልፎ ተርፎ ጠላትነት ሳይነጋገሩ የመሰማማትን፣ ሳይገናኙ እንደሚገናኝ አካል መናበብን ከኹሉ በላይ በመንፈስ መግባባት እንዲኖር ያስችላል፡፡

v  እኛ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት የምንቆምበት ነገር ምን አለን? ከኹለንተናዊ ልዩነቶቻችን በላይ በመንፈስ የሚያግባባን፣ ሳንነጋገር መግባባትና ሳንገናኝ መናበብን እንደዜጋ የፈጠርንበት ምን አለን?

አምስተኛ፡- ጠላትነት ጠላቴ የሚሉት አካል ወደ ራስ ቦታ እንዳይገባ መከልከልና በተቻለ መጠን ወዳጅ በሚባሉ ቦታዎች እንዳይገኙ ጫና ማድረግ አንዱ - ዋነኛ የመጠቀሚያ ስልትና ስትራቴጂ ነው፡፡

v  ኢትዮጵያውያን እንዳይገቡ የሚከለከሉበት ምን ቦታ አለ?በዐይነ ቁራኛስየሚታዩበትስ ቦታ የታለ? በወዳጆች ቦታስ እንዳይገኙ የት የት ይደረጋል?

ስድስተኛ፡- ጠላትነት ውስጥ ኹለንተናዊ ፉክክር አለ፡፡

v  እኛ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከነማን ጋር እየተፎካከርን ነው?

ሰባተኛ፡- ጠላትነት በተለይ እንደሀገር ሲኾን በሀገር ግንባታ (Nation Building) እና ሕብረተሰብን በማነጽ (Reshaping Society) ሂደቶች ውስጥ ኹሉ በግለሰብ፣ በቡድንና በተቋም ደረጃ ትርጉም ባለው መንገድ በዜጎች እምነት (አስተሳሰብና አመለካከት)፣ እውቀት (ስልትና ስትራቴጂ) እና በተግባር (በድርጊት ደረጃ) በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ይሰራበታል፡፡

ይበልጥ በሥነ - ጽሑፋዊ ጥበቦች (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ የኾኑ ማንነቶቹ የሚገለጹባቸው ድርሰቶች (ልብ ወለዶችና ኢ ልቦለዶች)፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ ሥነ ቃሎች፣ መነባንቦች - - - ወዘተ)፤ እይታዊ ጥበቦች (የሥዕል፣ የፎቶ ግራፍ፣ የምልክት ሥራዎች፣ የፊልም፣ የድራማ፣ የጭውውት፣ የኪነ - ህንጻ ሥራዎች፣ የፋሽን፣ የዲዛይን፣ - - - ወዘተ)፤ ትዕይንታዊ ጥበቦች (የሙዚቃ፣ የትያትር፣  የውዝዋዜ፣ የጭፈራ፣ ባሕላዊ የሐዘንና የደስታ መገለጫዎች የኾኑ ተግባራት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ የሃይማኖት በዓላት መገለጫዎች)፤ የዕደ ጥበብ ሞያ (የእንጨትና የቆዳ ሥራ፣ የሽመና ሥራ ፣ የጌጣ ጌጥ ሥራ - - - ወዘተ) ሥራዎች ውስጥኹሉ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ ነገሩ ጎልቶ ይታያል፡፡ዕውን እኛ ጋር ይህን ያክል ሰፊ፣ ትርጉም ያለውና አርቆ ማሰብ የታከለበት ሥራ ይሰራልን?

ጠላት ቢኖረን ከኹለንተናዊ ልዩነቶቻችን በላይ ሕብረትና አንድነት ይኖረን፤ በመንፈስስ እንግባባ አልነበርን? ማንቀላፋትስ ይወገድ አልነበረምን? በጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች የተዋጡ ስብሰባዎች ትርጉም ያላቸው ይኾኑስ አልነበርን?ከውጭያዊ ንትርክና እሰጣ ገባ ይልቅ የውስጡ እጅጉን በአዘቅጥ ውስጥ የኾነውስ በዚህ ምክንያት አይደለምን? በኢኮኖሚ መለኪያዎችና በፖለቲካ ምህዳር ማነጻጸሪያዎች እጅግ የወረደ ደረጃ ላይ መኾናችንስ ቁጭትና እልህ ያልፈጠረብን በዚህ የተነሣ አይደለምን?

ጠላትና ጠላትነት ሕልውናን የሚፈታተን፣ መቆጣጠርን ግድ የሚልና ማዳከምን እንደስልትና ስትራቴጂ እንደሚጠቀሙ ይታወቃል፡፡

ዛሬ ዛሬ “ጠላቶቻችን”፣ “ዕድገታችንን ማይመኙ”፣ “ተላላኪዎችን የፈጠሩ”  - - - ወዘተ ሲባሉና በተግባርም በተጨባጭ እንደሚንቀሳቀሱ የሚታወቁ ሀገራት ዛሬ “ወዳጆች”፣ “ደጋፊዎች” እንደኾኑ እየተነገረን ነው፡፡ ዕውን ምን አግኝተው ነው? ‘ታሪካዊ ጠላት’ የተባሉ አካላት ዛሬ ወዳጆቻችን የኾኑት ዕውን በዓለም ላይ ጠላት የሌለው፣ ተቀናቃኝ የሌለው ሀገር ኖሮ ነውን?

ዕውን ከኹሉ ጋር ወዳጅ መኾን ይቻላል? ማይቻል ከኾነስ እንደምን ከኹሉ ጋር ሰላም ኾን ተባለ? “እስከ ዛሬ ተሰርቶ ማያውቅ” ሲባል ዕውን ምን የተለየ ነገር ተሰጥቷቸው ነው? ምን አግኝተው ነው? እኛስ ምን አግኝተን ነው?

የዓለም ፖለቲካ በኃይል ሚዛን፣ በሴራና በጥቅም ላይ የተመሠረተ ስለመኾኑ የፖለቲካ ሀ፣ ሁ፣ - - የሚያውቅ ኹሉ በቀላሉ የሚረዳው ነገር ነውና ፖለቲካችን በምን እየተመራ ነው? አንዳንድ በተለየ አቋማቸው በደንብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ተቋማትና ሀገራት ድጋፍ እየሰጡ ነው - ይሰጣሉም እየተባለ ነው፡፡ እነሱ ምን አግኝተው? እኛስ ምን ሰጥተን ነው? በመስጠትና በመቀበል መሐከል ያለው ነገር ምን ይመስላል? ግልጽ መኾን ለምን አልቻለም?

በጃንዋሪ 27, 1848Alexis De Tocqueville በምክር ቤት ውስጥ ንግግር ሲያቀርብ ማጠቃለያውን ‘I believe we are sleeping on a volcano’ እንዳለው የሀገራችን ወቅታዊ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ እንደዛ በእሳተ ገሞራ ውስጥ እንዳንቀላፋን አስተውላለሁ፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

 

 

Back to Front Page