Back to Front Page


Share This Article!
Share
ቀን የጨለመባቸው...

ቀን የጨለመባቸው...

ገናናው በቀለ 08-01-18

በአገራችን አንዳንዴ የሚታዮት ግጭቶች መንስዔዎች የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ የከሰሩ ኮንትሮባንዲስቶችና የቀን ጅቦች እንዲሁም ከጀርባ ሆነው ጥቂቶችን በገንዘብ በመደለል ሁከት የሚፈጥሩ የጥቂት መሰሪ ተግባር ፈፃሚዎች መገለጫ ነው። ሆኖም ይህ እኩይ ዓላማቸው የማይሳካ መሆኑ በተግባር ታይቷል። ለአብነት ያህልም፤ በአማራና በኦሮሞ፣ በሲዳማና በወላይታ፣ በጉራጌና በቀቤና ወዘተ. ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ጤናማ ግንኙነት በማደፍረስ እንጠቀማለን ብለው ያሰቡ ጥቂት የቀን ጅቦች ፍላጎታቸው ያልተሳካላቸውና ወደፊትም የማይሳካላቸው መሆኑን በተግባር ታይቷል።

እነዚህ ጥቂት አካላት ዓላማቸው በአገሪቱ የተጀመረውን የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ጉዞ ማደናቀፍ ብቻ ነው። የፖለቲካ ነጋዴዎች ስለሆኑም ፍላጎታቸው ይህንኑ ንግዳቸውን ማጧጧፍ ነው። ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ይህን ሴራ ጠንቅቆ በማወቅ የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ሚና ለማክሸፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

Videos From Around The World

ምናልባት ችግሮች ቢኖሩ እንኳ በተያያዝነው የመደመር ጉዞ በፍቅር፣ በመወያየትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚችልበት አውድ በአገራችን እውን ስለሆነ፣ ከዚህ ውጪ የሚካሄድ ማንኛውም እርምጃ የሚጠቅመው የቀን ጅቦችንና ኮንትሮባንዲስቶችን ብቻ በመሆኑ ህብረተሰቡ እነዚህ በለውጡ ቀን የጨለመባቸው መሰሪዎችን ለመመከት ሁሌም መትጋት ይኖርበታል።

ያም ሆኖ ጊዜያዊ ግጭቶች የህዝቦችን ፍላጎት የሚወክሉ አይደሉም። ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኦኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጣ ውረዶችን አብሮ ያሳለፈ ህዝብ ለጊዜያዊ ሁኔታ ብሎ የሚጋጭበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።

እናም ህዝቦች በወሰን መካለል ጉዳይ ሊጋጩ የሚችሉበት ነባራዊ ሁኔታ እዚህ ሀገር ውስጥ ሊፈጠር አይችልም። በመቻቻል፣ በመከባበርና አንደኛው ህዝብ የሌላኛውን በሚያከብርበት አገር ውስጥ ህዝቦች በጊዜያዊ ሁነት ሊጋጩ አይችሉም። ያለፈው ታሪካቸውና አብሮነታቸው ይከለክላቸዋል።

ሆኖም በተነሱት ግጭቶች ሳቢያ አንዳንዶች ዘረፋን የመሳሰሉ ህገ ወጥ አካሄዶችን የሚከተሉ ናቸው። ይህን ለማመቻቸት ሲሉም ደጋፊዎችን በማብዛት የጥቃት ዱላቸውን ሊሰነዝሩ ስለሚችሉ ህዝቡ ጥንቃቄ ከማድረግ በላይ እነዚህን አካላት ወደ ህግ ማቅረብ ይኖርበታል።

የትኛውም የህበረተሰብ ክፍል ከሚፈጠረው ግጭት ተጠቃሚ አይሆንም። የሚያስከፍለው ዋጋም ከባድ ነው። ግጭት በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግሥት መሪነት በልማት ላይ ሌት ተቀን በመሳተፍ ህይወቱን ለመለወጥ የሚያስበውን የየክልሎቹን ህዝቦች የሥራ ሞራል የሚሰልብ ነው። ኢንቨስትመንታቸው የውጭ ባለሃብቶችን እንዳይስብም ማነቆ ይሆናል።

የአገራችንን ልማት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ክልሎቹ ሊወጡት የሚገባቸውን የተናጠልና የአብሮነት ሚናን ያቀጭጫል። በሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ላይም እንቅፋት ይሆናል። ተደምረን እናመጣለን ለምንለው ሂደት ማነቆ ስለሚሆኑም እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶችን ማስወገድ ይገባል።

የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ግጭት አራጋቢዎች ሁሌም በክልሉ ላይ በማተኮርና በሽብርተኝነት ከተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በጸረ ሰላም ሚዲያዎች የሀሰት ወሬ በመንዛት ሁከት ለመፍጠር እየሞከሩ ነው። የሚሳካለቸው ግን አይደለም።

እነዚህ የከሰሩ ፖለቲከኞች ቀደም ባሉት ጊዜያት በፈጠሩት እኩይ ሴራ አንድም ስንዝር መራመድ ያቃታቸው ናቸው። በዘመናት የትስስር ድር የተጋመዱት ህዝቦች የአእምሮ ዕድገትና የፈጠራ ክህሎት እንዳይዳብር፣ ተወዳዳሪነታቸው እንዲደናቀፍና ድህነትና ኋላቀርነት በክልሉ ስር ሰዶ እንዲቆይ ያላቸውን ክፉ ምኞት ለመተግበር ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ይሁን እንጂ አልተሳካላቸውም።

በአገራችን ሁሉም አካባቢዎች እየታየ ያለው የመደመር ጉዞ የሚያሳብዳቸው እነዚህ የከሰሩ ፖለቲከኞች የልማቱን ግስጋሴ ባዩ የከሰሩ አቋሞቻቸው ከመቃብር በታች ይውሉብናል በሚል ስጋት ችግር መፍጠራቸው የማይቀር ቢሆንም፤ የሁለቱም ክልል ህዝቦች የእነዚህን እኩይ ሃይሎች ትክክለኛ ፍላጎት በመገንዘብ ሴራቸውን ዛሬም እንደ ትናንቱ ሊያመክኑት ይገባል።

የከሰሩ ፖለቲከኞች የህዝቡ ፍላጎት ያልሆነን አጀንዳ በመምዘዝ በሁለቱም ክልሎ ውስጥ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል። አንዳንዴም የገቢ የሆኑ የህዝቦችን ጥያቄዎች ከመጠን በላይ በማጎንና ለግጭት መንስኤ እንዲሆን በማድረግ እኩይ ሴራቸውን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል። ያም ሆኖ ግጭትን ማራገብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ እነዚህ ሃይሎች ሊገነዘቡ ይገባል።

ይሁን እንጂ ዛሬ የህግ የበላይነት የነገሰበት ወቅት በመሆኑ የትኛውም አካል ግጭትን በማራገብ ተግባር ላይ ተሳትፎ እስከተገኘ ድረስ ከተጠያቂነት አያመልጥም። በመሆኑም በውጭም ይሁን በውስጥ የሚገኙ ግጭት አቀጣጣዩች ተግባራቸው መልሶ ራሳቸውን እንደሚያስጠይቃቸው ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦች ከግጭት የሚሰንቁት ምንም ዓይነት ተስፋ የላቸም። ተስፋቸው የተመሠረተው ከፍቅር፣ ከመደመር፣ ከይቅርታና ከአብሮነት ነው። ከግጭት የሚጠቀም ህዝብ ባለመኖሩም እነዚህን ተስፋዎች በማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት ላይ ለማኖር አስተማማኝ ሰላም መፍጠር የግድ ነው።

በመሆኑም ለበርካታ ዓመታት በሠላም የኖሩት ህዝቦችም ጥቅማቸው ያለው ከመደመርና አብሮ ከመኖር እንጂ ከግጭት አይደለም። ስለሆነም በየትኛውም ህዝብ መካከል ግጭት የሚፈጠርበት መሠረታዊ ሁኔታ ሊኖር አይችልም።

የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ከሚፈጠረው ግጭት ተጠቃሚ አይሆንም። የሚያስከፍለው ዋጋም ከባድ ነው። ግጭት የህብረተሰብን የሥራ ሞራል የሚሰልብ ተግባር ነው።

ግጭት አገራችን በመደመር መንፈስ አንድነቷንና ልማቷን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሂደት ያቀጭጫል። በሁለንተናዊ አገራዊ ለውጥ ላይም እንቅፋት ይሆናል። ስለሆነም የህዝብ ለህዝብ ዘላቂ ጥቅሞችን የሚያኮሰምኑ ግጭቶችን አቅም በፈቀደ መጠን በዘላቂነት መፍታት ይገባል። በተለይም ህብረተሰቡ በለውጡ ምክንያት ቀን የጨለመባቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች ለግጭት የሚከፍቷቸውን አጀንዳዎች በመድፈቅ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል።

 

Back to Front Page