Back to Front Page


Share This Article!
Share
ትምክህት እና ጠባብነት የመመከት ጉዳይ የአገር አንድነት የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፤

ትምክህት እና ጠባብነት የመመከት ጉዳይ የአገር አንድነት የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፤

ትምክህት ወይም ጠባብነት ሲባል አብዛኛውም ጊዜ በማህበራዊ ሚዲያ የተዛባ ትርጉም በመስጠት ሲያከራክር ይታያል፤ ትምክህት ሲባል የአማራ ህዝብ መለያ ተደርጎ ሲወሰድ፣ ጠባብነት ሲባል የትግራይ፣ የኦሮሞ እና የደቡብ ህዝቦች መለያ ተደርጎ ሲወሰድ ይታያሉ፡፡ ትምክህትም ጠባብነትም ለማንም ህዝብ አይወክልም የማንም ህዝብ መለያ ሊሆን አይችልም፡፡ በትምክህት እና በጠባብነት ህዝብን እንደ ህዝብ የሚፈርጅ ካለ፣ ከጅምሩ የተሳሳተው እሱ ነው፡፡ትምክህት እና ጠባብነት የግለሰቦች እና የፖለቲካ ድርጅቶች አመለካከት እንጂ ህዝብን አይወክልም፡፡ ትምክህት እና ጠባብነት ኢህአዴግ የፈጠረው፣ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚውል ፋሽኑ ያለፈበት ፍረጃ ነው ብሎ የሚወስዱም አሉ፡፡ ይህም የተሳሳተ ነው፡፡ ትምክህት እና ጠባብነት ለአንድ መድረክ ተብሎ በአንድ ድርጅት የሚሰየም ፍረጃም አይደለም፤ ታድያ ትክክለኛ ፖለቲካዊ ትርጉሙ ምንድን ነው፤

ትምክህት

ትምክህት ማለት የብሄር ህልውና የሚክድ፣ የህዝቦች የማንነት ልዩነት የማይቀበል፣ አንድ አገር-አንድ ህዝብ የሚል፣ የብሄር ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥያቄ የማይቀበል ነው፡፡ ማንኛውም ብሄራዊ የዴሞክራሲ ጥያቄ በአገር ህልውና የተጋረጠ አደጋ አድርጎ በመውሰድ ይጨፈልቀዋል፡፡ ትምክህት የብሄር እና የህዝቦች ህልውና የሚክድ ቢሆንም የአንዲት ኢትዮጵያ-አንድ ህዝብ መገለጫ አድርጎ የሚወስደው ግን ቋንቋው አማርኛ፣ ባህሉ እና ወጉ የአማራ ሆኖ ሳለ አማራ የሚባል ብሄር የለም፣ ይላል፡፡ እነዚህ ቋንቋ፣ ባህልና ወጎች የማን ናቸው ሲባል የማንም ብሄር ሳይሆን የኢትዮጵያ ነው በማለት ተፈጥሯዊ የህዝቦች ልዩነት በአደባባይ ይክዳል፡፡

Videos From Around The World

የትምክህት ነገር ሲታይ እልም ያለ ዘረኛ ነው፡፡ የራሱ ዘር የካደ መስሎ፣ የራሱ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ በሌሎች ላይ በመጫን፣ የሌሎች ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ በማንቋሸሽና በማሸማቀቅ ከምድረገፅ ድራሻቸው እንዲጠፉ ይሰራል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ቀላል የማይባሉ ቋንቋዎች ባህሎች እና ዎጎች የጠፉና በመጥፋት ላይ ያሉ አሉ፡፡ በ21ኛው ክ/ዘ ከትምክህት ጋር አብሮ መኖር አይቻልም፡፡ ምክንያቱ ማንም ብሄር ወይም ህዝብ ማንነቱ እንዲረገጥ እና እንዲዋረድ ስለማይፈልግ፡፡

በአጠቃላይ ትምክህት በታሪክ አጋጣሚ ከአማራ ህዝብ አብራክ የወጡ ጥቂት ገዢዎች ስልጣናቸውን ለማቆየት የተከተሉት ፀረ ህዝብ እና ፀረ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካዊ አስተሳሰብ በመሆኑ ለአማራ ህዝብ የማይወክል ግን ደግሞ አማራን እንወክላለን ብለው ለተነሱ የፀረ ህዝብ እና የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት የያዙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሚወክል ፖለቲካዊ ፍረጃ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ድህነት አጥፍተን ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እስክንሰለፍ ድረስ ይህ አስተሳሰብ እየተመናመነም ቢሆን አብሮን ይቀጥላል፡፡

ጠባብነት

ጠባብነት የትምክህት ጭቆና የፈጠረው ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ያነገበ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጠባብነት እንደ ትምክህት የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ህልውና ባይክድምአንዱ የበላይ ሌላው የበታች ነው ብሎ ግን ያምናል፡፡ የኔ ብሄር ወይም ህዝብ በቁጥርም፣ በተፈጥሮውም ልዩ ነው፣ በተፈጥሮ ሃብትም የተካነ ነው፤ ስለዚ የኔ ብሄር የበላይ ሆኖ መቀጠል አለበት፣ ካልሆነ ደግሞ ነፃነታችን ማወጅ ብሎ የሚያምን ነው፡፡ የጠባብነት ችግር የህዝቦች እኩልነት የማያምን፣ የራሱ የበላይነት ከተረጋገጠ ለሌላው ደንታ የሌለው፤ በተራው የትምክህት ቦታ በመውሰድ የፀረ-ህዝብ ተግባር መፈፀም ነው፡፡ ጠባብነት አንድነት ያምናል ተብሎ አይታመንም፡፡ ምክንያቱ ማንም ብሄር ወይም ህዝብ አንድ የበላይ ሌላው የበታች ነው ብሎ የሚቀበል ስለሌለ ከጠባብ አመለካከት ጋር አብሮ መኖር አይቻልም፡፡ ጠባብ አስተሳሰብ ያለው ድርጅት የኔ የበላይነት ካልተቀበላቹ ነፃነቴን እመርጣሎ ስለሚል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንድነት አይቀበልም ማለት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ ጠባብነት ብሄራዊ ጭቆና ከደረሳቸው ህዝቦች የሚፈልቅ ቢሆንም ለፀረ ዴሞክራሲ አገዛዝ በሌላ ፀረ ዴሞክራሲ አገዛዝ ለመተካት፣ ገዢዎች እና ገዢዎች የፈለቁበት ህዝብ ለያይቶ የማያይ፣ አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ በጠላትነት የሚፈርጅ እና ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥቃት ወይም ለማጥፋት የሚተጋ በመሆኑ፣ ይህም እንደ ትምክህት አንድን ህዝብ አይወክልም፡፡ ጠባብነት የሚወክለው ብሄራዊ ጭቆና የደረሰባቸው ህዝቦች እንወክላለን ብለው ለተነሱ የፀረ ህዝብ እና የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት የያዙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሚወክል ፖለቲካዊ ፍረጃ ነው፡፡ ይህ አጥፊ አስተሳሰብም ልክ እንደ ትምክህቱ ወደድንም ጠላንም ድህነት አጥፍተን ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እስክንሰለፍ ድረስ ይህ አስተሳሰብ እየተመናመነም ቢሆን አብሮን ይቀጥላል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ማለት፣ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ተፈጥሯዊ ልዩነት በመቀበል ህልውናቸውን በማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ግንኝነት እንዲኖር የሚፈልግ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቡች እኩል መብት አላቸው ብሎ ያምናል፡፡ የፈለገው የቁጥር ልዩነት ቢኖርም፣ የተፈጥሮ ሃብት ልዩነት ቢኖርም፣ የባህል፣ የቋንቋ እና የወግ ልዩነት ቢኖርም ሁሉም እኩል መብት እና እውቅና ይኖራቸዋል ብሎ ያምናል፡፡ ስለሆነም ሁሉም የየራሱ ቋንቋ እንዲጠቀም፣ ባህሉ ወጉ እንዲያሳድግ እኩል መብት እንዲኖረው በህገመንግስት እንዲካተት ያደርጋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች፣ ህገመንግስታዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተዳደራዊ ወሰን እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በእኩል ዓይን ያያል፤ የሌሎች መብት መከበር ልክ እንደ የራሱ መብት መከበር ያያል፡፡ የሌሎች መብት ከተረገጠም ልክ እንደ የራሱ መብት የተረገጠ አድርጎ ያያል፡፡

በኢትዮጵያ 21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን አንድነት ማስጠበቅ የሚችል ብቸኛ አስተሳሰብ ይህ ነው፡፡ ምክንያቱ በ21ኛ ክ/ዘ ማንም ህዝብ የበታች መሆን አይፈልግምና፣ ማንም ህዝብ በቋንቋው፣ በባህሉ፣ በወጉ እንዲዋረድ እና እንዲሸማቀቅ አይፈልግም፤ ስለዚ ትክክለኛው የህዝቦች ፍላጎት በትክክል አስማምቶና አቻችሎ መውሰድ የሚችለው ጠባብ ወይም ትምክህት አመለካከቶች ሳይሆኑ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ብቻ እና ብቻ ነው፡፡

ማጠቃለያ

ትምክህት እና ጠባብነት የአንድ ወቅት ክስተቶች ሳይሆኑ፤ ወይም ደግሞ አንድን ፖለቲካዊ ድርጅት ለራሱ ጥቅም ብሎ ያወጣቸው ፍረጃዎች ሳይሆኑ፤ በህዝቦች መካከል መቃቃርን የሚፈጥሩ፣ አንዱን ህዝብ ሌላውን ህዝብ በጥርጣሬ ዓይን እንዲተያዩ የሚያደርጉ፣ አንዱን ባለቤት ሌላውን ዳተኛ የሚያደርጉ፣ በአጠቃላይ ይህዝቦች እኩልነት፣ አንድነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማያምኑ ፀረ ህዝብ እና ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ ሁለቱም ይአገራችን አንድነት አደጋ ናቸው፡፡ ስለዚ እነዚህ አፍራሽ አመለካከቶች በድህነት አረንቋ እስካለን ድረስ፣ ከኋላቀርነት አስተሳሰብ እስካልተላቀቅን ድረስ መልካቸው እየቀየሩ የሚመጡና ሳንታክት ልንታገላቸው የሚገቡ ዋነኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠላቶች ናቸው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ህዝብን አደናግሮ ወደ ስልጣን ከመጡ በአገራችን የማታቧራ ግጭት ማስከተላቸው የማይቀር በመሆኑ፣ ይህን በውል ተገንዝበን፣ በሰከነ አእምሮ በማሰብ ከስሜት ወጥተን በመርህ ልንታገለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ትምክህት እና ጠባብነት የመታገል ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የአገር አንድነት የማስጠበቅ እና ያለማስጠበቅ ጉዳይ ነው፤ የአገራችን ሰላም እና መረጋጋት የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፤ የአገራችን የህዳሴ ጉዞ የማስቀጠል ወይም የማስቆም ጉዳይ ነው፡፡

 

 

ህዳሴ ኢትዮጵያ

hidaseethiopia@yahoo.com  ;hidaseethiopiaa@gmail.com

ጥቅምት 19፣ 2011 ዓ.ም.

 

Back to Front Page