Back to Front Page


Share This Article!
Share
ዲያስፖራውና የዜግነት ጥያቄ

ዲያስፖራውና የዜግነት ጥያቄ

ባይሳ ዋቅ-ወያ 09-04-18

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ ዲያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመካሄድ ላይ በሚገኘው የለውጥ ሂደት እንዲካፈሉ ጥሪ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወዳገራቸው መመላሰቸውን ሳስተውል፣ እነዚህ ተመላሾች በተለይም የፖሊቲካ ድርጅት መሪዎችና አክቲቪስቶች ከብዙ ዓመታት በኋላ በሰላም መመለሳቸውን እንጂ ከተመለሱ በኋላ በፖሊቲካው እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መሰናከል በቅጡ ያስተዋሉት ስላልመሰለኝ፣ አንዳንድ ጠቃሚ ማስታወሻዎችን ለማስቀመጥ ወሰንኩ። ይህን ሆ ብሎ የተነሳውን የፖሊቲከኞችና አክቲቪስቶችን መንጋ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል ብዬ በመገመት ሃሳቤን በአደባባይ ለማውጣት ፈራ ተባ እያልኩ ቀን በመቁጠር ላይ እያለሁ ሰሞኑን አንድ ግለሰብ በፌስቡክ ላይ ተመሳሳይ ጉዳይን አንስቶ ሰፋ ያለ ማስታወሻ አስፍሮ ካየሁ በኋላ፣ እኔም ሞራል አገኘሁና ይህንን ባብዛኛው ሕጋዊ የሆነን ጽሁፍ በተገኘው የሚዲያ መድረክ ለማሳተም ወሰንኩ። ዓላማዬ እነዚህ በገፍ በመመለስ ላይ ያሉት የፖሊቲካ ሰዎች ለብዙ ዓመታት ይኖሩበት ከነበረው የጉዲፈቻ አገሮቻቸው ነቅለው ከወጡ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በተለይም የዜግነታቸውን ጉዳይ አስመልክቶ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መሰናክል በውል የተረዱት ስላልመሰለኝ፣ የሚወስዱት ውሳኔ ሁሉ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው። ሕጋዊ መረጃዎችን ካቀረብኩ በኋላ ግን ዲያስፖራው ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪና ስለ ዛሬይቷ ኢትዮጵያ ስላላቸው የተሳሳተ ግምት የግሌን አስተያየት በማከል ጽሁፌን እደመድማለሁ።

Videos From Around The World

ወደ ዋናው ቁም ነገር ልመልሳችሁና፣

በውጭ አገር ይኖሩ በነበረበት ዘመን የኢትዮጵያዊነት ዜግነታቸውን ይዘው የቆዩት ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከቢሮኪራሲውና የኑሮ ዘይቤ ጋር መላመድ ያቅታቸው እንደሆን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ዜጋ ባገራቸው ለመኖርም ሆነ በፈለጉት መልክ ተደራጅተው ወይም ከተደራጁት ተቀላቅለው ባገሪቷ የፖሊቲካ ሂደት ለመካፈል ብሎም ለመምረጥና ለመመረጥ የሚያጋጥማቸው ችግር አይኖርም። ችግሩ ያለው፣ ፈልገውም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ተገደው የውጭ አገር ዜግነትን በወሰዱ ግለሰቦችና በተለይም የፖሊቲካ ድርጅት መሪዎችና አባላት ዘንድ ነው።

እንደሚገባኝ ከሆነ፣ ሁላችንም በትውልድ ኢትዮጵያዊ ስለሆንን ብቻ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሌላ አገር ዜግነት እንኳ ከወሰድን በኋላ፣ የኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ለዘላለም ጥያቄ ውስጥ የማይገባና ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሆነን እንደተወለድን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሆነን የመቅረት መብት ያለን ይመስለናል። ይህን ከሕግ አንጻር ስናየው የተሳሳተ አመለካከት ነው። መነሾውም ምናልባት ዜግነት የሚባለውን እሳቤ እንደ ሰብዓዊ መብት ከመቁጠር የተነሳ ይመስለኛል። ዜግነትን የመስጠትም ሆነ የመንሳት መብት ያለው መንግሥት ስለሆነ ዜግነት የሰብዓዊ ሳይሆን የሕጋዊ መብት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል። ይህንንም በጥልቁ ለመረዳት የኛን አገር ሕገ መንግሥትና የዜግነት ሕጉን ማወቅ ያሻል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 6 እንደሚለው ወላጆቹ/ቿ ወይም ከወላጆቹ/ቿ አንደኛቸው ኢትዮጵያዊ የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው። በዚህ መሠረት ሁሉም ትውልደ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ዜጋ ነው ማለት ነው። የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግም ይህንን አንቀጽ ሰፋ አድርጎ፣ በትውልድ ምክንያት ዜጋ ከመሆን መብት ባሻገር ዜግነትን የማጣትንና መልሶ የማግኘትን ሕጋዊ መንገድ እንደሚከተለው ይተነትነዋል።

የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ በአንቀጽ 20(1) ላይ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፍላጎት የሌላ አገር ዜግነት ካገኘ (ኢትዮጵያዊ) ዜግነቱን በራሱ ፈቃድ እንደተወ ይቆጠራል ይላል። ስርዝና ቅንፍ የኔ። በራሱ ፍላጎት የሚለው አባባል በዲቪ ወይም በሌላ ሕጋዊ በሆነ ዘዴ ካገር ወጥተው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያገሪቷ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የዜግነት ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው የሌላ አገር ዜግነትን የወሰዱትን ብቻ ሳይሆን በፖሊቲካ ምክንያት ሳይፈልጉ በግድ ካገር ተሰደው በሌላ አገር ጥገኝነት ጠይቀው ያገኙና ከጊዜ ባኋላ ጥገኝነት የጠየቁበትን አገር ዜግነት የወሰዱትን ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ያጠቀልላል።

በራሳቸው ፍላጎት ሳይሆን በሌላ ምክንያት የሌላን አገር ዜግነትን ላገኙ ለምሳሌ፣ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን (ወይንም ከኢትዮጵያውያን ዜጎች) ወላጆች በአሜሪካን ምድር ላይ በመወለዳቸው ብቻ የአሜሪካን ዜግነትን ያገኙትን ግለሰቦች በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ በአንቀጽ 20(3) ላይ የሚከተለውን ያስቀምጣል።

ራሱ ጠይቆ ሳይሆን .........በማናቸውም ሌላ ምክንያት ተመሥርቶ በሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት የተነሳ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ኢትዮጵያዊ፣ ሀ) ባገኘው የሌላ አገር ዜግነት መብቶች መጠቀም ከጀመረ ወይም፣ ለ) በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ያገኘውን የሌላ አገር ዜግነት ትቶ በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ለመቀጠል መምረጡን ለባለሥልጣኑ ካላሳወቀ ዜግነቱን በፈቃዱ እንደተወ ይቆጠራል ይላል።

የዜግንት ሕግም ይህንኑ የሌላ አገር ዜግነትን የወሰዱትን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መልሶ ለማቀፍና ባገሪቷ የፖሊቲካም ሆነ ማህበራዊው ዘርፍ በሰላም እንዲሳተፉ ከማሰብ አንጻር በአንቀጽ 22 ውስጥ የሚከተለውን ቅድመ ሁኔታ አካትቷል።

አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረና በሕግ የሌላ አገር ዜግነት ያገኘ ሰው፣ ሀ) ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ መኖርያውን በኢትዮጵያ ውስጥ ከመሠረተ፣ ለ) ይዞት የነበረውን የሌላ አገር ዜግነት ከተወ እና፣ ሐ) ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለሥልጣኑ ካመለከተ የኢትዮጵያን ዜግነት መልሶ ሊያገኝ ይችላል።

ከላይ የጠቀስኳቸው የሕግ አንቀጾች በቀላሉ እንዲገባንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑም ሕጋዊ መብታቸውና ግዴታቸው ምን እንደሆነ በውል እንዲረዱት እንደሚከተለው ለማጠቃለል እሞክራለሁ፣

ሀ) በተለያየ ምክንያት የኢትዮጵያን ዜግነት ትተው የሌላ አገር ዜግነት የወሰዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟሉ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰው የኢትዮጵያዊነት ዜግነታቸውን መልሰው ለማግኘት ይችላላሉ።

ለ) ይህ ማለት ግን ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ እንደው በግብታዊነት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነኝና ወደ ትውልድ አገሬ ተመልሼ ወዲያውኑ ባገሪቷ የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እኩል ተሰልፌ አስተዋጽዮዬን አበረክታለሁ ማለት አይደለም። ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ሕግ ጣምራ ዜግነትን ስለማይፈቅድ፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ሕጉን ተከትለው፣ የውጪ ዜግነቱን አስረክበውና፣ ማስረከባቸውንም የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከማመልከቻቸው ጋር አያይዘው ለኢትዮጵያ የደህንነት የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን ማስረከብ አለባቸው ማለት ነው።

ሐ) ባለሥልጣኑ ጉዳዩን ለኮሚቴ አቅርቦ እስኪያስጸድቅላቸው ድረስ ግን፣ እንደ ትውልደ ኢትዮጵያ በሕግ በተሰጣቸው መብት መሠረት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖርና ከፖሊቲካ ውጭ በሆነ ማንኛውም የሥራ መስክ ተሰማርተው አገራቸውን ማገልገል ይችላሉ። የቢሮክራሲው ውጣ ውረድ ያስቸግራቸው እንደሁ እንጂ ሕጉ አንዳችም ገደብ ስለማያስቀምጥ፣ ባመቻቸው ጊዜ ወዳገራቸው ተመልሰው ያላንዳች ችግር ከመሥራት የሚያግዳቸው የለም።

እነዚህን የሕግ ቃላት ዛሬ በገፍ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላይ ካሉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የወደፊት የኢትዮጵያ ቆይታቸውና ብሎም በኢትዮጵያ ፖሊቲካ ውስጥ ሊኖራቸው ከሚችለው ዕውኔታ ጋር ለማጣጣም፣ እንደገና ወደ ዜግነት ሕጋችን መመለሱ ግድ ይላል። የትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ኢትዮጵያ መጉረፍ ተፈጥሮያዊ የመሆኑን ያህል፣ ሕጋዊ መብታቸውን ጠንቅቀው ሳይረዱ ሕጋዊ አገራቸውን ለቅቀው በግብታዊነት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መወሰናቸው ግን የተሳሳተ ይመስለኛል። የምንኖረው በዚህ ምድር ላይ እስከሆነ ድረስ የምንተዳደረውም በዚሁ በምድራዊ ሕግ መሆኑን ሁላችንም ማወቅ ያለብን ጉዳይ ነው። እነዚህን ምድራዊ ሕጎች ደግሞ መንግሥታት ካገራቸው ሁኔታ ጋር አጣጥመው የሚያወጡት በመሆኑ ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ መተቸት ወይም መጥፎ ስለሆነ እንጣሰው ብሎ ሙከራ ማድረግ ሕግን መጣስ ነው። ስለሆነም፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን በተለይም በፖሊቲካው መስክ ተሰልፈው ላገራችን አስተዋጽዎ ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ፣ ሕጉ ምን ይላል ብለው አስቀድመው መጠየቅ አግባብ አለው ባይ ነኝ።

መደምደምያና የግሌ አስተያየት፣

እንደደሚገባኝ ከሆነ ዶ/ር ዓቢይ ዲያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ያቀረቡት ጥሪ በመጀመርያ ደረጃ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከወሰደ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ካገር ወጥተው ሊመለሱ ያልቻሉትን ግለሰቦች በሰላም ወዳገራቸው እንዲመለሱ ከማሰብ እንጂ፣ የፖሊቲካ ድርጅት መሪዎችን ወይም አክቲቪስቶችን ወዳገር ቤት ተመልሰው ባገሪቷ የፖሊቲካ ሕይወት ንቁ ተካፋይ እንዲሆኑ ታስቦ አይመስለኝም። መሆንም የለበትም። የሳቸው ጥሪ ዲያስፖራው ወዳገር ቤት ተመልሶ ገንዘብ ያለው በኢንቬስትሜንት፣ ሌሎች ደግሞ በሙያቸው ለምሳሌ ሐኪሞች በየሆስፒታሉና በየክሊኒኩ፣ የማስተማር ሙያ ያላቸው ደግሞ በየትምህርት ቤቱና በየኮሌጆቹ እየሄዱ እንዲያስተምሩ፣ በሰብዓዊ ድርጅቶች በኩል የማህበረሰቡ አቅመ ደካሞች ዜጎቻችን ጎን

እንዲቆሙ እና ሌሎችም እንዲሁ በየሙያቸው የትውልድ አገራቸውን በነጻ እንዲያገለግሉ

ነበር። አገራችንን እንወዳለን ለምንለው የዲያስፖራ ማህበረሰብም ከዚህ የተሻለ ዕድል መጠበቅ ወይም የተለየ እንክብካቤ መጠየቅ ቅንነት የጎደለው ይመስለኛል። በርግጥ ዲያስፖራው ከዚህም በፊት ደጋግሜ ስል እንደነበረው፣ የኤኮኖሚ አስተዋጽዎው ከብዙዎቹ ክልሎች የላቀ በመሆኑ፣ ቢያንስ ቢያንስ ባገሪቷ የንግድ ተቋማት ለምሳሌ በባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ቴሌ፣ መብራት ኃይልና አየር መንገድን በመሳሰሉት ውስጥ ሼር እንዲገዛ ቢፈቀድለት አግባብ ያለው ጉዳይ ነው። ያ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው።

በግሌ የማልደግፈውና መሆንም የለበትም የምለው፣ በገዛ ፈቃዳችን የትውልድ አገራችንን ዜግነት ትተን፣ በውጭ አገር ባንዲራ ሥር ተንበርክከንና እጃችንን ደረታችን ላይ ጭነን ላገሪቷ ሕገ መንግሥት ብቻ ታማኝነታችን በአደባባይ ቃል እየገባን፣ ዛሬ ሁኔታው ተመቻችቶ ስናገኘው ወዳገር ቤት ተመልሰንና የተውነውን ዜግነታችንን እንኳ መልሰን ለማግኘት ሕጋዊ እርምጃ ሳንወስድ፣ ባገሪቷ ሕግ ለውጪ ዜጎች ክልክል በሆነው የፖሊቲካ ሥራ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር በእኩልነት እንሰለፍ ማለት አንድም ካለማወቅ አለያም ከማን አለብኝነት የመነጨ መሆኑን ነው።

ከዳር ሆኜ ካየሁትና ካስተዋልኩት ተነስቼ በርግጠኝነት የሚከተለውን ለማለት እችላለሁ፣ ሀ) አገራችን ኢትዮጵያ የፖሊቲከኞች ወይም የፖሊቲካ ድርጅቶች እጥረት የለባትም። እንዲያውም ከሚያስፈልጋት በላይ ስለሆነ በጣም መቀነስ አለባቸው።

ለ) ቄሮና ፋኖ እንዲሁም ሌሎች ለውጥ ፈላጊ ወገኖቻችን ያላንዳች የውጪ ቀጥተኛ ድጋፍ ራሳቸውን አደራጅተው፣ የአግዓዚን ገዳይ ጦር የተጋፈጡና፣ ለለውጡ መሳካት ከመታሰርና ከመሰቃየት አልፎ ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል። ስለዚህ እነዚህ የለውጥ ጀግኖችና ለውጡም ያፈሯቸው መሪዎቻቸው ይህንን ውድ ዋጋ ከፍለው ያገኙትን ድል ለመንከባከብና ከታለመለትም ግብ ለማድረስ የሚያቅታቸው አይመስለኝም። ስለዚህም የዲያስፖራው ሚና እጅግ በጣም ውስን መሆኑ መታወቅ አለበት።

ሐ) ላለፉት አራት ዓመታት ሲካሄድ በነበረው ሕዝባዊ ዓመጽ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቷ በፌዴራሊዝም ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች ጀምሮ፣ አገራችን በክልሎች በመከፋፈሏ ወይም ክልሎች በፈለጉት ቋንቋ በመጠቀማቸው ወይም ክልሎቹ የየራሳቸውን ባንዲራ በማውለበለባቸው በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረ ቅራኔ አልተስተዋለም። ብዙውን ጊዜ የኢትዮጵያን መከፋፈል የምንሰማው እዚህ ውጭ አገር ከምንኖረው በተለይም ካንጋፋው ትውልድ ዲያስፖራ ነው። የሚያሳስበኝ ነገር ቢኖር፣ ይህንን ባንድ መንፈስ ተነሳስቶ ወያኔ መራሹን የግፍ አገዛዝ ያስወገደውን ትውልድ፣ ዛሬ ከውጪ ተመልሰን፣ ስለ ፌዴራሊዝምና ብሎም ስለ ክልል መዋቅሩ መጥፎነት እየሰበክን ሌላ ዓይነት አስተዳደራዊ መዋቅርን ለፖሊቲካ ገበያ ማቅረብ፣ ይህንን ጥሩ መሠረት ላይ የቆመውን የሕዝቦቻችንን አንድነት የሚያናጋ ይመስለኛል። ፌዴራሊዝሙ ወይም የክልል መዋቅሩ እንከን የለውም ብዬ ለመሞገት ሳይሆን፣ ጉድለቱን ይህን ለውጥ ያመጣው ትውልድ ራሱ በራሱ አነሳሽነትና በራሱ ጊዜ ሊፈታው ይችላልና እኛ ዲያስፖራዎች ጥጋችንን ይዘን አስፈላጊውን ድጋፍ ብቻ እንስጥ ባይ ነኝ።

መ) ቄሮና ፋኖ፣ ሌሎቻችን በተለይም አንጋፋው ትውልድ ዲያስፖራ ካላወካቸው በስተቀር በመካሄድ ላይ ያለውን ለውጥ ከግቡ እንደሚያደርሱ አንዳች ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም። ብዙዎቻችን መታሰርንና መሰቃየትን ፈርተን በተገኘው ቀዳዳ ተጠቅመን ካገር በመውጣትና በውጭ አገር ኑሮአችንን አደላድለን በትርፍ ጊዜአችን ብቻ ስለ ኢትዮጵያ በሶሻል ሚዲያና አልፎ አልፎም ሰላማዊ ሰልፍ እያዘጋጀን የታሰሩት የፈቱ ወያኔ ይውደም ብለን ስንጮህ፣ እነ በቀለ ገርባ፣ መረራ ጉዲና፣ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌን የመሳሰሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ግን ካገሪቷ ርቀው ከተደላደለ ጥግ በትርፍ ጊዜያቸው እንደኛ ከመጮህ ይልቅ እዚያው በሕዝቡ መሃል ሆነው መታገል፣ ብሎም መታሰርና መሰቃየትን መርጠዋል። እነዚህ በእሳት የተፈተኑ እውነተኛ ታጋይችና የፖሊቲካ መሪዎች ስለሆኑ ውድ ዋጋ ከፍለውበት ያገኙትን ድል ከግብ ለማድረስ እንደሚችሉ ሁላችንም አምነን መቀበል አለብን።

ሠ) ብዙዎቻችን፣ በተለይም የኔው ያንጋፋው ትውልድ አባላት ኢትዮጵያ ያኔ ጥለናት እንደወጣን ከቦታዋ ሳትንቀሳቀስ እንዳለች የምትጠብቀን ይመስለናል። በመሆኑም ያኔ በስድሳዎቹና በሰባዎቹ መጀመርያ ላይ ከውጪ አገር ሆነን የተማሪውን እንቅስቃሴ እንመራ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም አገሪቷ ውስጥ የኛን ያህል ዕውቀትም ሆነ ልምድ ያለው ባለመኖሩ ተመልሰን አመራር ለመስጠት ኃላፊነት የተጣለብን አድርገን እየወሰድን ነው። ይህ በጣም ስህተት ነው። በነጻ አገር በመኖራችን ብቻ ዲሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን ያበረከትነውን አስተዋጽዖ፣ አገር ቤት በሕገ ወጥ መንገድ ራሳቸውን አደራጅተውና መስዋዕትነት ከፍለው ለውጡን ያስገኙትን ዜጎቻችንንና ከውስጥም የበሰበሰውን ኢህአዴግን በመቃወም ቁርጠኛ እርምጃ ከወሰዱት የኦቦ ለማ ቡድን ታሪካዊ ድርጊት ጋር ማወዳደር ቅንነት የጎደለው ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም።

ረ) ከላይም እንዳልኩት፣ አገር ቤት ያለው የለውጥ ትውልድ (ያገሪቷ 80% ሕዝብ የዚህ ትውልድ አባል መሆኑን ልብ ይሏል) በተለያዩ ሎጂስቲክ ምክንያቶች ከዳር እስከ ዳር ባንድ ጊዜ አይነሳ እንጂ፣ ሁላቸውም በያሉበት እየተናበቡ ይሰሩ እንደነበር የተረጋጋጠ ነው። በዲያስፖራው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖሊቲካ ድርጅቶች የመተባበር ታሪክ ግን የዚህ ተቃራኒ ነበር። እንኳን አንድ ላይ ሆነው በሚያስማማቸው ላይ ተስማምተው ለመሥራት ይቅርና በማይስማሙበት ነጥብ ላይ እንኳ ላለመስማማት መስማማት አቅቷቸው የየግላቸውን ድርጅት ይመሩ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። ታዲያ ትልቁ ስጋቴ፣ እነዚህ በነጻ አገር እየኖሩና የዲሞክራሲን ጥቅም ባይናቸው እያዩ መግባባት የተሳናቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ወዳገር ቤት ተመልሰው የለመዱትን የመከፋፈል መርዝ፣ ተስማማቶ ባንድ ላይ ለውጡን ከግብ ለማድረስ በሚተጋው ማህበረስባችን መሃል እንዳይረጩና እንዳይከፋፍሏቸው ነው። በኔ ግምት፣ ለሩብ ምዕተ ዓመት ልዩነቱን አቻችሎ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ባንድ ላይ የተሰለፈውን፣ ሕዝብ ዛሬ ከውጪ ተመልሰን ያልቸገራቸውን እንደቸገራቸው በማቅረብ ክልሎች ይጥፉ፣ ፌዴራሊዝም ይወገድ፣ ይኸኛው ሐውልት ይፍረስ ይኸኛው ይገንባ፣ አንድ ቋንቋ አንድ ሕዝብ ወዘተ እያልን ሕዝቡን ባንከፋፍል ጥሩ ይመስለኛል። ለወደፊት ኑሮውን የሚኖሩት እነሱ ናቸውና እናት አገራቸውን እንዳመቻቸው እንዲገነቧት ይህንን የሥራ ድርሻ የትግሉ ባላቤት ለሆነው ለወጣቱ ትውልድ እንተወው ማለቴ ነው።

ሰ) ብዙዎቻን የዲያስፖራ አባላት፣ አገር ቤት ካሉት ወገኖቻችን የተሻለ ዕውቀት ወይም ልምድ ያለን ይመስለናል። የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የተወለደ ልጅ ዛሬ ፒኤች ድግሪ እንዳለው እንኳ ለማሰብም አንሞክርም። የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትም ወድቋል ተብሎ ስለታመነበት አገሪቷ ከኛ ባኋላ ምሁር ያፈራችም አይመስለንም። ይህም የተሳሳተ ግምት ነው። ኢትዮጵያ ብዙ የተማረና የተመራመረ ዜጋ አላት። ያገሪቷ ዋና እጥረት የተሳሳተው የመንግሥት ፖሊቲካ ያስከተለው የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመኖር ነው። እሱን ደግሞ ራሱ ሕዝቡ በሂደት እያስተካከለው ነው። ስለዚህ በማህበራዊው ሚዲያ ላይ ብቅ እያልን ራሳችንን ስላስተዋወቅንና የተሻለ እንግሊዝኛ በማውራታችን ብቻ ከነዚህ አገር በቀል የፖሊቲካ መሪዎችና ምሁራን የተሻልን ነን ብለን ራሳችንን መሸንገሉን ብናቆም የተሻለ ይመስለኛል።

የግል አስተያየቴን እንድሰነዝር ቢፈቀድልኝ፣

የጣምራ ዜግነት ሕግን የሚያጠና ቡድን በቅርቡ ሥራውን እንደሚጀምር ዶ/ር ዓቢይ ተናግረዋል፣ ጥሩ ጅማሬ ነው። ያ በተግባር እስኪተረጎም ድረስ ግን ከፖሊቲካ ሥራ ውጪ በሙያችንና ባካበትነው ልምድ አገራችንን ለማገልገል ለምንፈልግ የዲያስፖራ አባላት፣ ሥራ ላይ ያለው ሕግ አንዳችም መሰናክል ስለማያስቀምጥ፣ የውጪ ዜግነታችንን እንደያዝን ወዳገራችን ተመልሰን በየሙያችን ተሰልፈን በነጻ ማገልገል እንችላለን። ችግሩ ያለው የኢትዮጵያ ዜግነት ሳይኖራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በትውልደ ኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ባገሪቷ ፖሊቲካ ሕይወት ለመሳተፍ ወይም አመራር ለመስጠት/ለመውሰድ በሚያስቡት ፖሊቲከኞችና የፖሊቲካ ድርጅት መሪዎች ዘንድ ነው። ለነሱ ደግሞ አንድ ወንድማዊ ምክር አለኝ፣ በ መ ጀ መ ር ያ ደ ረ ጃ ፣ የኢትዮጵያ ዜጋ ስላልሆናችሁ በሰው አገር ፖሊቲካ ውስጥ ገብታችሁ አትፈትፍቱ። በግድ መሳተፍ አለብን የምትሉ ከሆነ ደግሞ የውጪ ዜግነታችሁን አስረክቡና የኢትዮጵያ ዜግነትን መልሶ ለመውሰድ በሕጉ መሠረት ማማልከቻ አስገቡ። በ ሁ ለ ተ ኛ ደረጃ፣ እዚህ ዲሞክራሲ በነገሰበት አገር ስንኖር የፖሊቲካ መሪዎች የሥራ ዘመናቸውን ጨርሰው በሰላም ለሚቀጥለው ትውልድ ሥልጣንን አስረክበው መሄዳቸውን በመገንዘባችን፣ ያገራችን መሪዎች ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ መቆየታቸውን ስናወግዝ ኖረናል። ብዙዎቻችን ግን ራሳችንን ብቸኛ መሪ አድርገን ከመቁጠር የተነሳ፣ ለብዙ ዓመታት የየድርጅታችን መሪ በመሆን እያገለገልን ነው። ባገሪቷ ውስጥ በተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴና ለውጡን ከግቡ ለማድረስ ያበረከትነው አስተዋጽዎ እንዳለ ሆኖ፣ ይህንን የለውጥ ትውልድ ራሱን እኛ ነን ኮትኩተን አሳድገን ከዚህ ያደረስነው ብለን ራሳችንን እናጽናና። ያባት ሕልም እኮ ልጆቹ አድገውለት ከሱ በልጠው እሱ ከሰራው በላይ ሰርተው ጎልተው እንዲታዩና ስሙን እንዲያስከብሩ ነውና፣ እኛም የዛሬውን ትውልድ ኮትኩተን አሳድገን እዚህ ደረጃ ላይ በማድረሳችን የሚገባንን ምሥጋና እንውሰድና፣ አመራሩን ለወጣቱ ትውልድ አስረክበን በክብር ከፖሊቲካ መድረክ እንሰናበት። ያካበትነው ልምድ ካለና ለማህበረሰቡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እነዚህ ለክብር ያደረስናቸው ልጆቻችን ለምክር መምጣታቸው አይቀርምና፣ ለዚያ እንዘጋጅ። በተረፈ ግን፣ በሕይወት ዘመናችን በፈጸምናቸው በጎ ሥራና ባበረክተነው አስተዋጽዎ እየተኩራራን ማድረግ ያለብንን ፈጽመናል ብለን በደስታ ወደሚቀጥለው ሕይወት ለመሻገር አስፈላጊውን ዝግጅት እናድርግ። ለዚህም ፈጣሪ አስተውሎትን በርከት አድርጎ ይስጠን።

 

 

**** ጸሃፊው ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባላሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው። ጄኔቫ፣ ነሓሴ 3 ቀን 2018 ዓ/ም wakwoya2016@gmail.com

Back to Front Page