Back to Front Page


Share This Article!
Share
ዲያስፖራውና የመንግሥት ሚና

ዲያስፖራውና የመንግሥት ሚና

ባይሳ ዋቅ-ወያ 07-26-18

 

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱና በአሜሪካ ቆይታቸውም ከዲያስፖራው ጋር ተገናኝተው በሰፊው ለመወያየት መታቀዱን ሰምቼ ምናልባትም ከፖሊቲካው አታካራ ባልተናነሰ መልኩ እኛን ዲያስፖራውን በቀጥታ የሚመለከቱትን አራት ጉዳዮች አሜሪካ የሚገኙት ወገኖቻችን አንስተው ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር ይወያዩበታል በሚል ተስፋ ላጋራቸው ፈለግሁ።

ስለ ዲያስፖራው ሕዝብ ማንነትና ምንነት፣

በዲያስፖራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የተለያዩ የሕብረተሰባችንን አካል የሚወክልና በብሄር፣ በመጣበት ዓላማና በትምህርት ደረጃ ይለያያል። በሕጋዊ መንገድ ራሱ ፈልጎ ባገኘው ወይም በመንግሥት ስኮላርሺፕ ለከፍተኛ ትምህርት ወጥቶ የቀረ አለ፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በዲቪ የወጣ ወይም በሥራ ምክንያት ወጥቶ በዚያው የቀረም ብዙ ነው። በፖሊቲካ ምክንያት ባገሪቷ ውስጥ በሰላም መኖር አቅቶት ነፍሱን ለማዳን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ጥሶ የወጣ አለ። ሌላው ደግሞ ባገሪቷ ውስጥ ሰፍኖ በነበረው ኢዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ምክንያት የታሰረና በእስር ቤት ሥቃዩን ያየ፣ የተገረፈ ወይም ሰዎች ሲገረፉ ወይም ሲገደሉ ያየና ከፍተኛ ትራውማ ያለበት የረጅም ጊዜ የአእምሮ ሕክምና የሚያስፈልገው በመሆኑ ወደዚያ የሰቆቃ ሕይወት ለመመለስ የማይፈልግ ነው። በሳይንስ የተደገፈ ጥናት ባይኖርም በግሌ ላላፉት አርባ ዓመታት እንደተገንዘብኩት ከሆነ ከዲያስፖራው መሃል ወደ ኢትዮጵያ በየጊዜው ለዕረፍት ሂዶ ዘመድ አዝማድን ከመጎብኘት ባሻገር፣ ዛሬ ያገሪቷ ሁኔታ ቢሻሻል እንኳ ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልሎ ሊመለስ የሚችለው ከ 1% በላይ የሚሆን አይመስለኝም።

Videos From Around The World

በመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ እንደተነገረን ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሶስት ሚሊዮን በላይ ነው። በአኃዙ መሰረት ፌዴራል ኢትዮጵያን ከሚመሰርቱት ዘጠኝ ክልሎች ሕዝቦች ጋር ብናወዳድር ዲያስፖራው ስድስተኛ ደረጃን ይይዛል ማለት ነው። ከሌሎቹ የፌዴራሉ የክልል መንግሥታት በተለየ መልኩ ግን፣ ያላንዳች የመንግሥት በጀት፣ ቢሮክራሲያዊ የሰው ኃይል አገልግሎትና ድጎማ ይህ የዲያስፖራ አካል በ 2017 ዓ/ም በሕጋዊ መንገድ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው ጥሬ ገንዘብ 4.6 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የመንግሥት መረጃዎች ያረጋግጣሉ። መንግሥት ያላንዳች ጥረት ይህን ያህል ጥሬ ገንዘብ በውጪ ምንዛሪ አገኘ ማለት ነው። ስለዚህ ዲያስፖራን አስረኛው የፌዴራሉ አካል ነው ብንል ስህተት አይመስለኝም። ያ ሁሉ ሆኖ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም ከደርግ ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ስለዲያስፖራ ያለውን አመለካከት ብንገመግም፣ ትውልደ ኢትዮጵውያኑ ወዳገራቸው እንዲመለሱ የሚያበረታታ ሆኖ አናገኘውም። በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት በዓዋጅ የተደነገገው የትውልደ ኢትዮጵያውያን ሕግም መጠነኛ የኢሚግሬሺን ፎርማሊቲዎችን ከማቃለሉ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም አላስገኘም። ያላቸውን የውጪ ምንዛሪ ሃብት አፍስሰው ኢንቬስት ለማድረግ ወደ እናት አገራቸው ከተመለሱት ብዙዎቹ የሚያመች አሰራር ባላመኖሩ ለኪሳራ ተዳርገዋል። ያገሪቷ ሕግም ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ንግድ ተቋማት ለምሳሌ በባንኮችና ኢንሹራንሶች ውስጥ ሼር መግዛት ስለማይፈቅድ፣ ዲያስፖራው ያን ያህል ንጹህ የውጪ ምንዛሪ በያመቱ ማስገባቱ እየታወቀ፣ ከቢጫው ካርድ ሌላ ለምን አንዳች ዓይነት አስተያየት አላደረገም የሚለው ጥያቄ ሁሌም እንደተነሳ ነው። በኔ ግምት፣ ዓይነተኛውን የኢትዮጵያዊነት እሴታችን የሆነውን ምቀኝነትን ወደ ጎን ብንተው፣ ዋነኛው ምክንያቱ፣ ዲያስፖራዎች በተለምዶ ከባሕር ማዶ ሆነው መንግሥትን የሚቃወሙና የተቃውሞ ትግሉን ይመራሉ ተብለው ስለሚታሰቡ ይመስለኛል። ስለዚህም መንግሥት ሁሌም በክፉ ዓይን እንዳያቸው ነው። እንደ አንድ ተራማጅ ድርጊት የታየው የትውልደ ኢትዮጵያውያን ቢጫ መታወቂያ ወረቀት እንኳ ማደሻ ቀኑ ከተላለፈ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለያንዳንዱ ሳይታደስ ላለፈበት ቀን በውጪ ምንዛሪ ቅጣት ያስከፍላሉ። ዛሬ ግን የዶ/ር ዓቢይ ቡድን ለዲያስፖራ ያለው ግምት ከሌሎቹ ጊዜ የተሻለ መስሎ ይታየኛል። ለዚህም ነው በቀን የአንድ ዶላር መዋጮ ጥሪያቸው ወዲያውኑ አዎንታዊ መልስ ያገኘው። ግን ይህ የሙሽርነት ጊዜ አልፎ ዛሬ ያለው ተነሳሽነት እንዳይቀዘቅዝ ከተፈለገ፣ መንግሥት ባስቸኳይ የሚከተሉትን ዲያስፖራውን ብቻ የሚመለከት እርምጃዎች ቢወስድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጠቃሚ ይሆናሉ ባይ ነኝ።

መንግሥት ማድረግ ያለበት፣

አንደኛ፣ መንግሥት የጀመረው ትራስት ፈንድ ዜና በጣም አስደሳች የሆነውን ያህል፣ ገና በሕዳሴ ቦንድ ምክንያት ከደረሰብን መዋዠቅ ሳናገግም አሁንም ፈንዱን ማን እንደሚያስተዳድር በውል ሳይታወቅ በንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ተከፍቷልና በየቀኑ ለአንድ ማኪያቶ ከምታወጡት አንድ አንድ ዶላር ቆጥቡና ወደ አካውንቱ አዛውሩ ማለት ብቻ በቂ አይመስለኝም። ከዚህ

በፊት ለሕዳሴ ግድብ ከንጹህ ያገር ፍቅር የተነሳ በብዙ ሺህ ዶላር ቦንድ የገዙ ግለሰቦች ዛሬ ድረስ ገንዘባቸው የት እንዳለ እንኳ ለማወቅ አልቻሉም። ስለዚህ መተማመን እንዲኖር ከዲያስፖራው መካከል ዕውቅናና ተዓማኒነት ካላቸው ግለሰቦች የተውጣጣ የትረስት ፈንድ ቦርድ ማቋቋምና የአባላቱን ማንነት ለሕዝብ በአደባባይ መግለጽ፣ የአካውንቱን ድረ ገጽ መክፈትና እያንዳንዱ አዋጪ ግለሰብ በፈለገበት ሰዓት የገንዘቡን እንቅስቃሴ እንዲከታተል ቢደረግ ጥሩ ነው። የቦርዱ ተቀዳሚ ተግባር ደግሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የልማት ፕሮጄክት ዕቅዶችን የሚያወጣና በቅደም ተከተል አተገባበራቸውን የሚቆጣጠር ይሆናል። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ግን፣ ዛሬ በአገር ፍቅር ስሜት ተገፋፍቶ ያላንዳች ጥያቄ ማዋጣት የሚጀምረው ግለሰብ ከዓመት በኋላ የጥረቱን ውጤት ማወቅ ሲፈልግ አጥጋቢ መረጃ ካላገኘ መዋጮውን እንደሚያቁርጥ ካሁኑ መታወቅ አለበት። ቅድመ ሁኔታዎቹ ከተሟሉ ግን፣ ከማኪያቶው ቀንሶ በቀን አንድ ብር ብቻ ማዋጣት ሳይሆን፣ የአንድ ሙሉ ማኪያቶ ዋጋን ለማዋጣት ወደ ኋላ የማይል አገር ወዳድ ሕዝብ ነው።

ሁለተኛ፣ ይህ አገሪቷን ካለችበት የኤኮኖሚና ማህበረሰባዊ ቀውስ ለመታደግ የእንተባበር ጥሪ የታለመውን ግብ እንዲመታ፣ ይህንን ከብዙ ያገሪቱ ክልሎች በላይ በያመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠረውን ንጹህ ዶላር የሚያስገባውን ዲያስፖራ፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ያስፈልጋል። እንደ ክልሎች ፕሬዚዴንትና በሺዎች የሚቆጠሩ የቢሮክራሲ ባላሥልጣናት ይመደቡላቸው ለማለት ሳይሆን፣ የነሱን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል ከማንም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ነጻ የሆነና ተጠያቂነቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ብቻ የሆነ፣ ለማንኛውም የዲያስፖራ ጥያቄ ያላንዳች ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድና እንግልት ተገቢውን እርዳታ ወይም መልስ ሊሰጥ የሚችል ከፍተኛ የዲያስፖራ ኮሚሽኔር ማቋቋም ያስፈልጋል። ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ኮሚሽኔር ከቀን ተቀን አገልግሎት መስጠት ባሻገር፣ ዲያስፖራው ዜጋን እንዴት አድርጎ ወዳገር ቤት እንደሚመለሱ፣ ከተመለሱ በኋላም እንዴት ተደርጎ ያካበቱትን ልምድና ሃብት ላገሪቷ ጥቅም ለማዋል የሚችሉበትን ዘዴ የሚቀይስ ዘመናዊ ተቋም መሆን አለበት። ይህ፣ ራሱን በራሱ ከዲያስፖራው በሚመጣው ገቢና ያላንዳች ተጨማሪ የመንግሥት ድጎማ ሊንቀሳቀስ የሚችል የዲያስፖራ ኮሚሽኔር፣ ከሌሎች ለምሳሌ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ልምድ በመቅሰም፣ ወዳገራቸው ተመልሰው ያስተማራቸውን ሕዝብ መልሶ ለማስተማር ወይም በሙያቸውና በሃብታቸው በመርዳት ማህበረሰባዊ ግዴታቸውን ለመወጣት እየተመኙ በቢሮክራሲው ምክንያት ሳይሳካላቸው የቀረውን የብዙ ሺ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሕልም ዕውን ያደርጋል የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ።

ሶስተኛ፣ ብዙውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳስበው ጉዳይ ደግሞ የጣምራ ዜግነት አለመፈቀድ ነው።

ጣምራ ዜግነት ማለት አንድ ግለሰብ ባንድ ጊዜ የሁለት አገሮች ዜግነት ባለቤት ሲሆን ማለት ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ የራሱ ዜጋ በተመሳሳይ ወቅት የሌላ አገር ዜጋ እንዲሆን የሚፈቅድ መንግሥት አልነበረም ማለት ይቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ ዓለም እየጠበበች ስትመጣና የሰው ልጆች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር አመቺነት እየጨመረ መጥቶ ዜጎች ወደ ሌላ አገር ሄደው ከመኖርም አልፈው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የአዲሱ አገራቸው ዜጋ ቢሆኑም፣ ከቀድሞ አገራቸው መለየት ስለማይችሉ፣ ብዙ አገራት ጣምራ ዜግነትን ፈቅደው ዜጎችን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመሳብ ሙከራ ማድረግ ጀመሩ። ራቅ ብለን ሳንሄድ እዚሁ በአፍሪካችን፣ ጋና፣ ናይጄርያ፣ ሴራሊዮን፣ ኬንያ፣ ዚምባብዌና ዩጋንዳ፣ አይቮሪ ኮስትና ቤኒን፣ ናምቢያና ደቡብ አፍሪካ፣ ቡሩንዲና ሞሮኮ የመሳሰሉ አገራት፣ ከዘር ግንዳቸው የወረሱትን ደማችንን ይዘው ይዘዋወራሉ የሚሏቸውን ሰዎች በሙሉ፣ ከጊዜ በኋላ የተጎናጸፉትን ዜግነት እንደያዙ፣ ያላንዳች ሕጋዊ ሂደትና ማመልከቻ የትውልድ አገራቸውን ዜግነት እንዲጎናጸፉ የሚፈቅዱ የጣምራ ዜግንት ሕጎችን ደንግገዋል።

ብዙዎቹ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ካገራቸው ያለፍላጎታቸው ተገፍተው ወደ ሌላ አገር በመኮብለል የሌላ አገር ዜግነትን የወሰዱት ተገደው እንጂ ኢትዮጵያውነታቸውን ጠልተውት እንዳልሆነ ትውልደ ማንነታቸውን (identity) ላለመቀየር ከሚያደርጉት የቀን ተቀን ጥረት መገምገም ይቻላል። አብዛኞቹ የውጪ ዜጋ መሆናቸውን የሚያስታውሱትም ድንበር ሲያቋርጡ ብቻ ነው። በተረፈ ግን እንኳን ራሳቸው ይቅርና ልጆቻቸውም ሳይቀሩ በተቻለ መጠን ኢትዮጵያዊ ሆነው እንዲያድጉላቸው ሲጥሩ ይገኛሉ። በአንጻሩ ደግሞ ዲያስፖራው የተመኘውን ያህል በትውልድ አገሩ የፖሊቲካና ማህበረሰባዊ ሕይወት እንደልቡ ተካፍሎ ማህበረሰባዊ ግዴታውን እንዳይወጣ የሚያደርግ ያገራችን የዜግነት ሕግ ጣምራ ዜግነትን አይፈቅድም። ስለሆነም፣ ይህ ትውልድ አገሩን ከልቡ የሚወድና አቅሙ እንደፈቀደለት አገሪቷን ከተዘፈቀችበት ቀውስ አንሰራርታ ወደ ዕድገት ጎዳና እንዲታመራ በሚድረገው ርብርቦሽ ሙሉ ተካፋይ እንዲሆን፣ መንግሥት ጣምራ ዜግነትን መፍቀዱ አግባብ ያለው ይመስለኛል። ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውምና! በመንግሥት በኩል ያለው ኪሳራ ፓስፖርትና መታወቂያ ወረቀቶችን ለማተም የሚያወጣው ወጪ ብቻ ሲሆን እሱንም ደግሞ አመልካቾቹን ማስከፈል ይቻላል።

አራተኛ፣ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ደርግ እስኪያከስመው ድረስ በአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት መካከል ቁጥራቸው መጠነኛ የሆኑትን አሜሪካውያን መምህራንን የሰላም ቡድኖች (peace corps) በሚባለው ፕሮግራም መሰረት ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ባገሪቷ የነበረውን የመምህራንን እጥረት እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ለመሸፈን ተችሎ ነበር። በፕሮግራሙ በስተጀርባ ያለውን የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም (national interest) ጉዳይ ወደ ጎን ብንተው፣ ዛሬ ይህንን ፕሮግራም ለኢትዮጵያ ብቻ እንዲመች ተደርጎ እንዲያንሰራራ ቢደረግ ብዙ ጥቅም እናገኝበታለን ባይ ነኝ። በኔ ግምት፣ የአሜሪካ መንግሥትም በፕሮግራሙ

መንሰራራት የሚደሰት ይመስለኛል። ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ እንዲመች በሚለው ሃሳብ ላይ ወሳኝ ድርድር ያስፈልጋል። ለማለት የፈለግሁት፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚላኩት የሰላም ቡድኖች መምህራን ሌሎች አሜሪካውያን ሳይሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን ዜጎች ብቻ መሆን አለባቸው ማለቴ ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው ሁለተኛ ትውልድ ከምንላቸው ልጆቻችን መካከል ብዙዎቹ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ጨርሰው በተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች ተሠራጭተው በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ልጆቻችንን ነው ወደ ኢትዮጵያ በ ሰላም ቡድኖች ፕሮግራም ሥር እንደ አሜሪካዊ ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ያስተምሩ የምለው። ለአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹ እስከሆኑ ድረስ እነዚህን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ብቻ መርጦ ወደ ኢትዮጵያ መላኩ ብሔራዊ ችግርን የሚያስከትል አይመስለኝም። ላገራችን ግን ነጻ መምህራንን ከማግኘት ባሻገር ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ከወላጆቻቸው እናት አገር ጋር ስለሚያቀራርብ ትርፉ ሁለትዮሽ ነው። የነዚህ የትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በሰላም ቡድን ፕሮግራም ሥር ወደ ኢትዮጵያ መመለስ፣ ለሚጦሯቸው ወላጆቻቸውም ወዳገራቸው ተመልሰው ላገራቸው አፈር የሚበቁበትን መስመር ያመቻችላቸዋል። ስለዚህ መንግሥታችን ይህንን ጉዳይ በጥብቅ አስቦበት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ኦፊሲኤላዊ ውይይት ቢጀምር ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ውይይቱ ከሰመረ ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መግደል የምንለው አባባል ተግባራዊ ሆነ ማለት ነው።

መደምደምያ፣

የጠቅላይ ሚኒስትራችንን አባባል ትንሽ አጣምሜ ብጠቀምበት፣ ዲያስፖራው ከኢትዮጵያ ይወጣል እንጂ ኢትዮጵያ ከዲያስፖራው አትወጣም። በተግባር በራሴና በልጆቼ ደርሶ ስላየሁ ይህ አባባል ትክክለኛ ነው በሙሉ ልቤ እሞግታለሁ። ሆኖም ግን፣ ከያንዳንዷ የኢትዮጵያ ጉዞዬ መልስ ሁለተኛ ወደዚያች አገር ብዬ ያላማረርኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። እዚህ ባለሁበት አገር በዘርና በኃይማኖት እንዲሁም በባሕልና በኑሮ ዘይቤ ከማይመስሉኝ ነጮች ጋር የዜግነት መብቴ ያላንዳች መድልዖ እየተጠበቀልኝ፣ ተወልጄ ባደግሁበት አገር ግን ወደ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሄድኩ ቁጥር የሚያንገላቱኝን ሳስብ፣ ያባት የእናቴ ባልሆነውና ባልተውለድኩበት አገር፣ አንድ አፍሪካዊ ባርያ ያን ያህል ተከብሬ ስኖር፣ ተወልጄ ባደግኩበት ያባት የናቴ አገር ግን ያን ያክል ስንገላታ፣ መማረሬ የተጋነነ አይሆንብኝም ብዬ እገምታለሁ። መንግሥት ይህንን አሉታዊ ድባብ ለማጥፋት እርምጃ መውሰድ አለበት። ወዳገሩ ለአጭር ጊዜ ዕረፍትም ሆነ ለሌላ ጉዳይ የሚመለስ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም አንጻር ብናጤነው፣ አገሪቷን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም። ለፍቶ ያጠራቀማትን ዶላር ወደ ሌላ ታዋቂ የዕረፍት ቦታዎች ሄዶ በማጥፋትና የባዕድ አገርን ኤኮኖሚ ከመደጎም ይልቅ፣ ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ የትውልድ አገሩን ኤኮኖሚ መደጎም የሚመርጥ ሕዝብ ስለሆነ ልዩ ትኩረት ቢሰጠው አግባብ ያለው ይመስለኛል።

ስለዚህ ዲያስፖራው ላንድ ማኪያቶ ከሚከፍለው በቀን አንድ ዶላር እየቀነሰ ለአገሪቷ ዕድገት ከማዋጣት በጣም የላቀ አስተዋጽዎ ሊያደርግ የሚችል ከብዙ የፌዴራሉ ክልል መንግሥታት የተሻለ አካል መሆኑ ታውቆ፣ መንግሥት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ባገሪቱ የንግድ ተቋማት ውስጥ ሼር እንዳይገዙ የማይፈቅዱትን ደንቦች መሰረዝ፣ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባገሪቷ ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ሕይወት እንዲካፈሉ የሚያስችል ጣምራ ዜግነትን የሚፈቅድ ሕግ ማውጣትና፣ የዲያስፖራን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል ራሱን የቻለ ነጻ ተቋም (ኮሚሽኔር) ማቋቋም ከዶ/ር ዓቢይ የቤት ሥራዎች መካከል በመጀመርያ ተርታ መሰለፍ ያለበት አገራዊ ጉዳይ ይመስለኛል።

******

ጄኔቫ፣ 24 July 2018 ዓ/ም wakwoya2016@gmail.com


 

Back to Front Page