Back to Front Page


Share This Article!
Share
ከጅቡቲ ነፃ የንግድ ቀጠና በስተጀርባ የባቡሩ ስኬት ማማ

ከጅቡቲ ነፃ የንግድ ቀጠና በስተጀርባ የባቡሩ ስኬት ማማ

ሞገስ ተ 07-20-18

ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጋርነት ካሉት የቀጠናው አገራት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቁርኝት አለው፡፡ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ያላቸው ባህል፣ ቋንቋና ዕምነት ተመሳሳይ ዕሴትን የሚጋሩ በመሆናቸው ግንኙነታቸው የጠበቀ እንዲሆን አስችሏቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የጅቡቲ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ጅቡቲ በመንቀሳቀስ ሥራቸውን እያከነወኑ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ጅቡቲ ብቸኛዋ የኢትዮጵያ የወደብ በር ሆና ቁልፍ የሆነ ሁለንተናዊ ሚና ስትጫወት ቆይታለች፡፡ በዚህም የሁለቱ አገራት ግንኙነት እጅና ጓንት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ለዚህ የጠነከረ ግንኙታቸው ደግሞ ሁለቱ አገራት ያላቸው የግንኙነት ፖሊሲ ምቹ መሆን መሰረታዊ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብቸኛው የባቡር መስመር አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋር በማገናኘት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ በዚህ ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነታቸው ደግሞ ሁለቱም አገራት በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ይህ የባቡር መስመር የተዘረጋው በወቅቱ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ዋነኛ የመውጫ በር ትሆናለች ተብሎ ታስቦ ነው፡፡

ሁለቱ አገሮች በቋንቋም ሆነ በባህል አንድ የሆኑ ህዝቦች ይገኙባቸዋል፡፡ ወደቡ ለኢትዮጵያ አገልግሎት እንዲሰጥ ተመቻችቶ የተረመሰረት መሆኑና ለብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች የቀረበ ስለሆነ ትልቅ ጥቅም እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ ወደብ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ለኢትዮጵያም እስካሁን ድረስ ብቸኛው የወደብ ምንጭ በመሆን ጅቡቲ ቀዳሚ አገር ናት፡፡ ይህ ሁኔታ ሁለቱን አገሮች እንደ ሰንሰለት ያሰተሳሰረ የረጅም ጊዜ የንግድ መረብ እንዲኖራቸው ያስችላል፡፡

Videos From Around The World

ጅቡቲ በሰኔ ወር ከቻይና ጋር በመተባበር የአፍሪካ ነፃ የንግድ ማከል በመገንባት ለአፍሪካውያን አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ከፈተች፡፡ ይህ የንግድ ማዕከል በ240 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ትልቅ ነፃ የንግድ ቦታ ነው፡፡ ይህ የንግድ ማዕከል በ340 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገነባ ነው፡፡ በዚህም 60 በመቶ ጅቡቲ እና 40 በመቶ ቻይና ድርሻ አላቸው፡፡ የዚህ ማዕከል መከፈት ደግሞ በዋናነት ለምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ ነፃ የንግድ ማዕከል ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን በተደረገበት ወቅት በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የአፈሪካ አገራት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ከነዚህ አገራት መካከልም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የሯንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ፣ የሱዳን፣ የኡጋንዳ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳፋኪን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች መገኘታቸው የተቋሙን ሁለንተናዊ ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ጅቡቲም ለቀጠናው አገራት ምቹና ተፈላጊ ስትራቴጅክ ቦታ መሆኗ ልዩ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በዚህ የምረቃ ስነስርዓት ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የንግድ ማዕከሉን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ተደመጡ፤

የጅቡቲ ፕሬዝዳንትና ህዝብ በቀጠናችን አዳዲስ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመጀመርና የአፍሪካን ትስስር በማፋጠን ረገድ ግንባር ቀደም ተግባር እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ሁላችንም ወንድም የአፍሪካ አገራት እናመሰግናችኋለን፡፡ ጅቡቲም ለኢትዮጵያ ሁለተኛ አገር እንደመሆኗ መጠን ይህ የንግድ ቀጠና መከፈቱ የኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ብሎም ለመላ አፍሪካ አንድ የኢኮኖሚ መረብ በመዘርጋት ለአህጉሩ የክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ወደር የለሽ የገበያ ቀጠና እንዲሆን ያስችላል፡፡ ይህን ትልቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ እንደራሷ ነው እምትቆጥረው፡፡ ሁላችንም ወንድም የአፍሪካ አገራት ለምታደርጉት ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ከጎናችሁ ነን፡፡ ይህ ነፃ ዓለም አቀፍ የንግድ ቀጠና የሱዳን፣ የኤርትራ፣ የሱማሌ፣ የኡጋንዳ ብሎም የሁላችን የአፍሪካውያን ሀብት ነው፡፡ ለቀጠናው አገራትም የጋራ ሀብት ነው ብለውታል፡፡

ይህ ፕሮጀክቱ ለቀጠናው የንግድ ትስስር ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው አመላካች ነው፡፡ ይህ የንግድ ማዕከል ለአህጉሪቱ የሚያበረክተው የምጣኔ ሀብት አንፃር የአፍሪካ አገራት በኢኮኖሚው መረብ እንዲተሳሰሩ ያደርጋል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና በዋናነት በአካባቢው ጅቡቲ ዋነኛ ስትራቴጅክ አገር ያደርጋታል፡፡ በተለይም ህንድ ውቅያኖስንና አትላንቲክ ውቅያኖስን በማገናኘት የዓለም 50 በመቶ የሚሆነው የመርከቦችና የነዳጅ ምልልስ የሚካሄድበት አፍሪካን፣ ኤስያንና አውሮፓን በሚያገናኘው የባቢን መንዲብ የባህር ወሽመጥ የሚገኝባትም እንደመሆኗ መጠን የዓለም ትኩረትን በመሳብ ላይ ትገኛለች፡፡ኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነውን የንግድ እንቅስቃሴ የምታከናውነው በጅቡቲ በኩል መሆኑ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሁሉን አቀፍ ሚና አለው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱም አገራት በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ማለትም በመንገድና በባቡር ተቆራኝተው የየዕለት እንቅስቃሴያቸውን እያከነወኑ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ይህ ነፃ የንግድ ማዕከል መከፈት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋገረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ የዓለም አገራት የሚመጡ ሸቀጦችን በማስተናገድ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ይኖረዋል እየተባለ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በቅርቡ በአዲስ ምዕራፍ ትራንስፖርቱን የጀመረው የኢተዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ለዚህ የንግድ እንቅስቃሱ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የሥራ ዕድል ከመፍጠርም ባሻገር የቴክኖሎጅ ሽግግር በማድረግ የአካባቢው አገራት ተሞክሮ ይወስዱበታል፡፡ ከነዚህ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም በመሆን በሁሉም መስክ የላቀ ጠቀሜታ ይኖራታል፡፡ ስለዚህ በሚከናወነው የንግድ እንቅስቃሴ ሁሉ ቀዳሚ ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡ የባቡር መስመሩም ከፍተኛ የሆነ ሸቀጠ በማጓጓዝ ረገድ ሰፊ ድርሻ ስለሚኖው ኢኮኖሚው እንዲያድግና እንዲሻሻል ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ቀጠና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የንግድ እንቅስቃሴ የማይተካ ሚና በመጫወት የኢኮኖሚ ዕድገቷን ያፋጥናል ተበሎ ይታመናል፡፡

Back to Front Page