Back to Front Page

Share
የቆዳው ፋይዳ ተዘንግቶ አገር እንዳይጎዳ

የቆዳው ፋይዳ ተዘንግቶ አገር እንዳይጎዳ

በሰላማዊት ራያ 09-25-18

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች የታደለች ሀገር ስትሆን የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ እድሜም ከዘጠና በላይ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ሀገራችን 58 ሚሊየን የሚደርስ ከብቶች ያላት ሲሆን በአፍሪካ አንደኛ በዓለም ስምንተኛ ሆና ተመዝግባለች፡፡ ከሚሊየን በላይ ቢሆኑ በጎች ደግሞ በአፍሪካ ሦስተኛ በዓለም አስረኛ ደረጃ ላይ ስትሆን በ29 ነጥብ 7 ሚሊየን የፍየል ሀብቷም በተመሳሳይ በአፍሪካ ሦስተኛ በዓለም አስረኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በየዓመቱ ወደ ቆዳ ማልፊያና ማለስለሻ ፋብሪካዎች ከሚቀርቡት ቆዳ እና ሌጦ ውስጥ 1.4 ሚሊየን የከብቶች፣ 20 ሚሊየን የፍየሎች፣ 13.2 ሚሊየን የበጎች ነው፡፡

Videos From Around The World

ካለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንፃር የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ማምረቻ ኢንደስትሪዎች አንዱ ነው፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪዎች ልማትና ሽግግርን በማፋጠን ኢንዱስትሪዎቹ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ፈጣን ልማት እንዲያስመዘግቡ ማብቃትን ዓላማ አድርጐ የተቋቋመ የምርምር ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱ የዘርፉ ኢንዱስትሪን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ የዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ፣ የቴክኒክ፣ የግብይት፣ የሥራ አመራርና ሌሎች እንደ አስፈላጊነቱ የሚያግዙ ተግባር ተኮር ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ የምርምርና ስርጸት፣ የምክርና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የቆዳ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ በዐላት አከባበር ከእርድ ጋር ያላቸው ቁርኝት ጥብቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ለስጋው እንጂ ለቆዳው አይደለም፡፡ በ2011 በጀት ዓመት ከ133 ሚሊዮን ካሬ ጫማ ቆዳና ሌጦ በማልፋትና በማለስለስ ያለቀለት ቆዳን ማምረት የሚችሉ ከ32 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች ቢኖሩም ለፋብሪካዎቹ የሚቀርቡት ቆዳና ሌጦዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የጥራት ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ አገራችን ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ከዘርፉ በማግኘት ላይ አይደለችም፡፡ ይህም በተለይ በእርድ ወቅትና ከእርድ በኋላ በሚፈጠር ሰው ሠራሽ ችግር የተነሳ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት በእርድ ወቅት፣ ከእርድ በኋላ እና በቆዳ ሰብሳቢዎችና ነጋዴዎች መወሰድ የሚገቡ ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ቆዳና ሌጦ በጥንቃቄ ጉድለት በቶሎ የመበላሸት ባህሪ ያለው ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የእንስሳት እርድ የሚፈጽሙ አካላት ቆዳ በቢላ ሳይበሳ፣ ሳይቀደድ እና ሳይተፈተፍ ያለምንም ሰው ሠራሽ እንከን መግፈፍ፣ በዕርድ ወቅት አንገት ከተቆረጠ ወይም ከተባረከ በኋላ እንስሳውን መሬት ላይ አለመጎተት፤ ዘመናዊ ቄራዎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በእንስሳት እርድ በቂ ልምድና ሙያ ባላቸው ሰዎች እርድ ማካሄድ፤ ከቆዳው መወገድ ያለባቸውን እንደ ኮቴ፣ ጆሮ እና የመሳሰሉትን ማስወገድ፣ ሥጋን እና አጥንትን በቆዳው ላይ አለመከትከት፣ በተቻለ ፍጥነት በአቅራቢያ ለሚገኙ ቆዳ ሰብሳቢዎች በሽያጭ ማቅረብ፤ በየአካባቢው ቆዳና ሌጦ የሚሰበስቡ ነጋዴዎች የተረከቡትን ቆዳና ሌጦ በጨው በማጀል በጥንቃቄ መያዝ፣ ጨው ማግኘት ካልተቻለ ቆዳ እንዳይበሰብስ ዘረጋግቶ አየር እንዲያገኝ በማድረግ ለቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ወይም ለፋብሪካዎች በሽያጭ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጨው ያልተቀባን ቆዳ የቆዳውን 40 በመቶ ክብደት በሚመዝን ንፁህ ጨው በአግባቡ ሁሉንም የቆዳ ክፍል መቀባት፤ ጨው የተቀባውን ቆዳ መደርደሪያ በርብራብ መልክ ከመሬት ከፍ ያለ ሆኖ እንዲዘጋጅ በማድረግ ከቆዳው የሚወጣውን ደምና ፈሳሽ የሚንጠፈጠፍበት ክፍተት ማዘጋጀት፤ ጨው የተቀባውን ቆዳ የውስጠኛው/የስጋውን ክፍል በማገናኘት ቀዝቃዛና ነፋሻማ መጋዘን ውስጥ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ጨው የተቀባውን ቆዳ በመደርደሪያው ላይ በደንቡ መሠረት ሲቀመጥ የድርድሩ ከፍታ አንድ ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡

ቆዳና ሌጦን በማልፋትና በማለስለስ ከመጫሚያዎች፣ ከቆዳ ዕቃዎችና አልባሳት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ከሚውሉ ጓንቶች በተጨማሪ የመኪና ወንበርና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት ጥቅም ላይ ስለሚውል በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ስለሆነ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች የሚከናወን ንግድ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከጥሬ ቆዳና ሌጦ ንግድ ጀምሮ እስከ ያለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ሂደት በርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንዲያገኙ ስለሚያስችል ጠቀሜታውን ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል፡፡

በመሆኑም ቆዳና ኢንዱስትሪ ካለው ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጠቀሜታ አንፃር ኅብረተሰቡ ለቆዳ የሚያደርገው ጥንቃቄ ከእንስሳት እርባታ እስከ አለቀለት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ግብይት ድረስ ባሉት የግብይት ሰንሰለቶች፣ ቆዳና ሌጦ እንዳይባክን ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡

ያለንበት ወቅት የአዲስ ዓመት መባቻ ተያይዞም የመስቀል በዓል ሳምንት እንደመሆኑ በርካታ እርድ ይከናወንበታል፡፡በገጠር ቆዳ የሚገዛ ባይኖር እንኳ ገበሬዎች እና አርብቶ አደሮች ለተለያዩ አገልግሎቶች ይጠቀሙበታል፡፡ እንደ አጎበር (መቀመጫ) ፣ የመኝታ ቁርበት፣ስልቻ የመሳሰሉ ነገሮች በመሥራት ይገለገሉበታል እንጂ ቆዳና ሌጦ ከእርድ በኋላ እንደ አልባሌ ዕቃ ሊጣል አይችልም፡፡

እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች በዚሁ በል ወቅት የታረዱ ከብቶች ቆዳ ሌጦ የሽያጭ ዋጋ ወርዶ እንዳልባሌ ዕቃ በየቦታውና በቆሻሻ መጣያ ገንዳዎች ሲጣሉ ለመታዘብ ችለናል፡፡ትኩረት ያልተሰጠው ሀብታችን ሆኗል ፡፡ስለዚህ ቆዳው ለውጪ ምንዛሪም ሆነ ለኢንዱስትሪዎቻችን በግብዓትነት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ መታሰብ አለበት፡፡ስለዚህ ቆዳ የሚሰጠው ፋይዳ እንዳይዘነጋና ሀገር እንዳይጎዳ የሚመለከታቸው ኢንዱስትሪዎችና አካላትም ለገበያው ትኩረት ሊሠጡት ይገባል፡፡ በከተሞቻችን በየቦታው የእርድ ቆዳዎች ቢጣሉ የጤና ጠንቅ ያመጣሉ እንጂ የሚፈይዱት ነገር የለም፡፡ነጋዴዎች ለቆዳ ተገቢውን ዋጋ ቢሰጡ ዜጎች ቆዳውን በመሸጥ ይጠቀማሉ አካባቢያቸውንም ከመበከል ይጠነቀቃሉ ፡፡

የቆዳ ፋብሪካዎችና የሚመለከታቸው አካላት ለዚህ ችግር በጊዜ ዕልባት የሚሰጡበትን መንገድ ቢያመቻቹ መልካም ነው፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ የሚከበረው የመስቀል በዐልና የሠርግና ምላሽ ባህላዊ ዝግጅቶችም ብዙ እርድ የሚፈፀምባቸው ናቸው፡፡ በተለይም በደቡብ ኢትዮዽያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቢያንስ ለአንድ ሳምንት የሚያስቆይ የበዐልና የጋብቻ ዝግጅቶች ስላሉ የውጪ ምንዛሪ የሚያመነጨውን ቆዳና ሌጦ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንረባረብበት፡፡

በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር

 

 

Back to Front Page