Back to Front Page


Share This Article!
Share
ትምህርትን የሕይወት ስንቅና ትጥቅ

ትምህርትን የሕይወት ስንቅና ትጥቅ

ይቤ ከደጃች ውቤ 10-31-18

አንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትን በመምጣት የህዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ሓይል ዕምቅ ዐቅም ነው፡፡ዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በልፅገው በሀገራቸው ልማትን በማምጣት የህዝባቸውን ተጠቃሚነት ያጎለበቱ ሀገሮች ልምድ የሚያሳየን ይህንን ሀቅ ነው፡፡ በተለይ በቅርብ ዓመታት ከነበሩት የድህነት አረን ወጥተው ከፍተኛ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት ላይ የደረሱ የደቡብኮርያ፣ ሲንጋፖርና ቻይና፣ የቪየትናምና የማሌያ ወዘተ ሀገሮችን ተሞክሮ እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡እነዚህ ሀገሮች ለትምህርትና ሥልጠና በሰጡት ትኩረት የሰው ሓይል ሀብታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማልማት ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ የህዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል፡፡ከዚህ የምንረዳው ትምህርትና ሥልጠና ብቁና በቂ የሰው ሓይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ሀሳብ የትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሐምሌ 2010 ዓም በትምህርትና ሥልጠና ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በሚል ርዕስ ለውይይት ባሳተመው ፍኖተ ካርታ ላይ እንደ መግቢያ የተጠቀመበት ነው፡፡ከያዘነው የጥቅምት ወር ሦስተኛ ሳምንት ጀምሮ የኮሌጅና የየኒቨርስቲ ተማሪዎች በየተመደቡባቸው ቦታዎች እየተጓዙ በአካባቢው በሚገኙ ነዋሪዎች አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡አቀባበል እየተደረገላቸው ያለውም በየአካባቢው የሚገኙ ማኅበረሰቦችና አስተዳደርን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ባካተተ መልኩ በመሆኑ የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው ይረዳቸዋል፡፡ተማሪዎቹ ሕዝቡ የሰጣቸውን ሰላምና ፍቅር አስበው ለአካባቢው ነዋሪዎች ትምህርታቸውን ተመርኩዘው በጎ አስተዋፅዖ ለማበርከት ወይም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ያነሳሳቸዋል፡፡

Videos From Around The World

ከደርግ ውድቀት ወዲህ ሁለት ብቻ የነበሩት ዩኒቨርሲቲዎች በአሁኑ ወቅት 46 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የደረሱ ሲሆን በግል ደረጃም 130 የሚደርሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ አዳዲስ ተመዳቢ ተማሪዎች ባሉት 46 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በኅብረተሰቡና በመንግሥት ሓላፊዎች የሚደረግላቸው አቀባበል ለውጡን ለማስቀጠል የሚረዱ ናቸው፡፡ በነዋሪዎችና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተደረገላቸው ቤተሰባዊ አቀባበል መደሰታቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለፀዋል።በዚህ ሁኔታ ደግሞ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት የላኩ ወላጆች ብሎም ዜጎች የደስታው ተካፋዮች ናቸው፡፡

ሰው በሀገሩ ሰው በወንዙ ቢበላ ሣር ቢበላ መቅመቆ

ይከበር የለም ወይ ሰውነቱ ታውቆ እንደሚለው ግጥም ዜጎች ለትምህርት ወደ ተለያዩ ክልሎች ርቀው ሲሄዱ ፍርሀትና ስጋት ሊሰማቸው አይገባም የተወሰነ ብሔርን ለይቶ ሊያጠቃ የሚችል ለዚያውም በከፍተኛ ትምህርት ማዕከላት ሊኖር አይችልም ፡፡ ከቤተሰባቸው ተነጥለው ለትምህርት የሚሄዱ ተማሪዎች ያሉት በሀገራቸው መሆኑ ማወቅ አለባቸው ፡፡ልክ ከቤታቸው ወደ ጓዳቸው እየገቡ መሆኑን እያሰቡ ወደ ትምህርት ሥፍራቸው ሊሄዱ ይገባል፡፡ ምንም ዓይነት ፍርሐትን አውልቀው መጣል አለባቸው፡፡በተለያዩ ቦታዎች ለትምህርት ሲመደቡም በየአካባቢው የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል ለማወቅ ከአካባቢው ጋር መስተጋብር ለመፍጠር ይረዳቸዋል፡፡ይህም የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ እንዲሆን ያስችላል።

አቀባበል የተደረገላቸው እምነት፣ ቋንቋ ወይም የብሔር ልዩነትን ባተኮረ መልኩ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ባህል ወግና ልማድ መሠረት መሆኑን ከየዩኒቨርስቲዎቹ ለአዲስ ተማሪዎች እየተደረጉ የአቀባበል ሂደቶች ያሳያሉ፡፡በ2011 የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እየተቀላቀሉ ያሉ አዲስ ተማሪዎችም ዓላማ እንዳለው ሠራዊት ተሰልፈው ትምህርታቸውን አጠናቀውና ተመርቀው በመውጣት ግባቸውን ሊያሳኩ ይገባል ፡፡ በያዝነው የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡ አዲስ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጤናማና ውጤታማ ህይወት መምራት እንዲችሉ የሚረዳ ሥልጠና መስጠቱ ተማሪዎች እንዳይቸገሩ እንግዳ እንዳይሆኑ የሚረዳቸው በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ተማሪዎችን በብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች አልባሳትና ጭፈራዎች ለመቀበል የተደረገው ዝግጅትም በአብዛኛው ስኬታማ ነው፡፡

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቃሊተ ካምፓስ ተማሪዎች ከአቻዎቻቸው በሃያ ትልልቅ ፌስታሎች ጫማና ልብስ ይዘው ወደ መርካቶ ጎጃም በረንዳ አካባቢ መጥተው እርዳተ ሰጥተው ነበር፡፡በዚህም 110 የሚሆኑ ነዳያንን (ችግረኞችን) ገላ አጥበው፣ ልብስና ጫማ አድለው ወደ ትምህርት ማዕከላቸው ተመልሰዋል፡፡ይህ በጎ ተግባር በመሆኑ የሚወደስ ነው፤ በየዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ተማሪዎች ህዝቡ በባህሉና በወጉ አቀባበል ሲያደርግላቸው ያየሁት ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ እንኮራበታለን ለወደፊትም መቀጠል ያለበት ነው ፡፡ከላይ ያነሳናቸው ነጥቦች ህዝቡ እርስ በርሱ ለመደጋገፍ እና በመደመርን መንፈስ ለመራመድ ዝግጁ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችም ለአዳዲስ ገቢ ተማሪዎች በስነ ልቦና፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በኤች አይ ቪ ዙርያ በሌሎችም ርዕሶች ዙርያ እና በሀገራችንን እየታየ ካለው ለውጥ ጋር በተያያዘ ግንዛቤ መሥጠት ችግሮችና ግርግሮች ቢፈጠሩ እንኳ በሰላም ለመፍታት መሞከር አልያም ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ይገባል፡፡ችግር ሲከሰት ደግሞ አስቀድሞ ለመከላከል፣ ተማሪዎች እንደገቡ ይህንን መሰል ሥልጠናዎችን በመስጠት የህይወት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳል ፡፡ይህ ሲሆን ደግሞ የቤተሰቦቻቸውና የመምህሮቻቸው ልፋት ከንቱ ሆኖ አይቀርም፡፡ከዚሁ ጎን ለጎን ተማሪዎች ከጎሰኝነት ሽኩቻ መራቅ፣ ራስን ከሴሰኝነትና ከሱሰኝነት መጠበቅ ፣ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንዲሁም ትምህርትን እንደ ሕይወት ስንቅና ትጥቅ አድርጎ መታጠቅ ያስፈልጋል ለዚህም ሲባል ጊዜያቸውን ለትምህርታቸው መሰዋት አለባቸው፡፡

 

በዩኒቨርስቲ አካባቢ ወይም ዙርያ ያሉ ነዋሪዎችና ነጋዴዎችም ተማሪዎችን ወደ ሴሰኝነትና ሱሰኝነት ከሚያመሩ ንግዶች መጠበቅ ወጣቱ በርግጥም ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆን በአመለካከቱ የጠራና በዕውቀቱ የነጠረ ዜጋ ሆኖ እንዲወጣ የድርሻቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በየአካባቢው በትምህርት ቤቶች ዙርያ ያሉ የንግድ ቤቶች ተማሪዎችን እንዳያባክኑና እንዳያመክኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መመካከር ያስፈልጋል ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት ድጋፍና አገልግሎት ቢሰጡ መልካም ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ደሴት ታጥረው ህዝቡ አገልግሎታቸውን ሳያገኝ፣ መምህራኑም ሙያዊ አስተዋፅዖዋቸውን ሳያበረክቱ የሚያሳልፉበትን ምዕራፍ መቀየር ያስፈልጋል ፡፡ የቀድሞው ዓለም ማያ ግብርና ዩኒቨርሲቲ አሁን ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሐሮ ማያ ወይም በአካባቢው የነበረው ማያ ሐይቅ ሲደርቅ መምህራኑ በሙያቸው ለዚያውም የግብርና ሙያ ልሁቃን ሆነው ሐይቁ ጠፍ እስኪሆን ታዛቢዎች ነበሩ፡፡ለመታዘብማ እኔም በአካባቢው ሄጄ ሐይቁ ጠፍ እየሆነ ሊሄድ እንደሚችል ታዝቤያለሁ መምህራኑ ታዲያ ክህሎታቸውና አስተዋፅዖዋቸው ምኑ ጋር ነው ያሰኛል፡፡

የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም ሲወረር የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ድምፁን ማሰማት፣ ለችግሩ እልባት ለመስጠት የሚያስችል መፍትሔ ማፈላለግ ፣ ባለሙያዎችን ማሰባሰብ የመሳሰሉ ግዴታዎችን መወጣት ወይም ደግሞ ከሌሎች አቻ ተቋማት ጥናትና ምርምር የሚደረግበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበት ነበር፡፡ በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከአካባቢው ነዋሪ ተነጥለው በጥራቸው ውስጥ ደሴት ሆነው የሚኖሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የአካባቢውን ችግር እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉ ከሆነ አስተዋፅዖዋቸውን ለመረዳት ህዝቡ ይቸገራል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በአጥር ተከበው ደሴት ሆነው ለከአካባቢው ነዋሪ እዚያው እያሉ እንደሌሉ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ይህ ደግሞ ዜጎች የዩኒቨርሲቲዎቻችንን ሚና በጥልቀት እንዲረዱ ይረዳቸዋል፡፡ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ሲያካሂዱ ኅብረተሰብ ተኮር ካልሆነ ያልተማረውም ሆነ የተማረው ነዋሪ ምንድነው የሚሠሩት? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ተማሪዎች በትምህርት ሥፍራዎች ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ወደ ጎን አድርገው ትምህርታቸውን በሰላም መማር አለባቸው፡፡ለትምህርት የሚሄዱት የልዩነት አጀንዳን ለማራገብ ሳይሆን ጎሳ ተኮር ሁከትን ለማርገብ ተምረው ራሳቸውን ቤተሰባችውን ብሎም ኅብረተሰቡን ለመለወጥ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ ከተሞች ለአዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በነዋሪዎች አቀባበል የተደረገላቸው ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ስለሚማሩ አለንላችሁ ስጋት አይግባችሁ በሚል ነዋሪው የሀሳብ ድጋፉን ለመግለፅ ነው፡፡ይህ ደግሞ በያዝነው መስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር እንዳይሰጉና ለትምህርታቸው እንዲተጉ ለማሳሰብ ይረዳል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይሚኒስትር እና የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር ዐብይ አህመድ በሐዋሳ ተካሂዶ በነበረው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባዔ ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ፍፁም ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን በሚቻልበት ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና ከክልል አመራሮች ጋር መወያየታቸው ለጉዳዩ የሰጡትን ትኩረት ያሳያል፡፡በዚሁ ወቅት የትምህርት ዘመኑ ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን የተማሪዎች ወላጆች መምህራን የትምህርትማህበረሰቡ አባላት የክልል አመራሮችና የፀጥታ አካላት ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡እኛም ዘመኑ መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን፡፡

Back to Front Page