Back to Front Page


Share This Article!
Share
አሁን ኢህአዴግ የሚያዋጣው መደመር ወይስ መቀነስ?

አሁን ኢህአዴግ የሚያዋጣው መደመር ወይስ መቀነስ ?

ህዳሴ ኢትዮጵያ

መስከረም 24፣ 2011 ዓ.ም.

 

ኢህአዴግ በጥልቅ ተሃድሶው ባደረገው ግምገማ ከተለዩት ችግሮቹ አንዱ በኪራይ ሰብሳቢነት ዙርያ የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ ድርጅት እና ክልል ሳይለይ በሁሉም እንዳሉ እና ከሁሉም አከባቢ በትግል ማጥራት እንደሚያስፈልግ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የኢህአዴግ ምክርቤት አስረግጦ አስቀምጦታል፡፡ ይህ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ደግሞ ኢህአዴግ በያዘው የመንግስት ስልጣን ላይ አለአግባብ መጠቀምን፣ ስልጣን ለህዝብ አገልጋይነት ሳይሆን ለግል ክብር እና ጥቅም መዋሉ አንዱ መገለጫው ነው፡፡ አገራችን ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ አኳያ ሲታይ ኪራይ ሰብሳቢነት እንደ ተራ ወንጀል የሚታይ ሳይሆን በህብረተሰባችን እና በስርዓታችን እንደተደቀነ ከፍተኛ አደጋ ተደርጎ መወሰድ ያለበት በመሆኑ በኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች ዘንድ በቁርጠኝነት መታገል ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ሌባ ሌባ ማለት አለብን፤ ሌባን የሚፀየፍ ህብረተሰብ፣ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ እና ዜጋ መፍጠር አለብን፡፡ ይህም ሁላችን ወደ ሌላ እጅ ሳንቀስር በየጓዳችን ፈትሸን ማፅዳት አለብን፡፡ ነገር ግን በተግባር እየታየ ያለው ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል ሳይሆን በድርጅት አጥር ተንጠልጥሎ ጎራ ለይቶ እርስ በርስ መነታረክ ነው፡፡

Videos From Around The World

አሁን እኛ ካለንበት ሁኔታ፣የለውጥ ሀዋርያ መሆን ማለት የራስን ጉድፍ ሳታይ የሌላን ጉድፍ ማየት አይደለም፡፡ የለውጥ ሀዋርያ ማለት መጀመሪያ የራስን ጉድፍ በማፅዳት ሌላውን ማገዝ ማለት እንጂ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢዎች የሁሉም ህዝቦች የእድገት ፀር እና በሁሉም ህዝቦች ተሰግስገው የሚገኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በዚህ ጉባኤው በኪራይ ሰብሳቢነት የማያዳግም ትክክለኛ ውሳኔ መወሰን አለበት፡፡ ያለንበት ሁኔታ አሳሳቢ የሚያደርገው ኪራይ ሰብሳቢዎች በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ተሰግስገው ብሄር ከብሄር፣ ክልል ከክልል፣ ብሄራዊ ድርጅት ከብሄራዊ ድርጅት በማጣላት እና በማጋጨት ዕድሚያቸውን በማራዘም ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡ ይህም ውስብስብ ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልግ ያለፉት 5 እና 6 ወራት የአገራችን ሁኔታ ማየቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ባለፉት 5 እና 6 ወራት አገራችን ኢትዮጵያ አይታው የማታውቅ የእርስ በርስ ግጭት እና መፈናቀል አጋጥሟታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በሶማሌ ክልል እና በኦሮሞ ክልል፣ በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልል፣ በአማራ እና በቤንሻንጉል ክልል፣ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ በአዲስ አበባ የተከሰቱ ግጭቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የነዚህ ሁሉ ክስተት መነሻ በአመራሩ እየታዩ የነበሩ የዝቅጠት እና የመበስበስ ብልሽቶች በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መቀረፍ ባለመቻላቸው ስር እየሰደዱ በመምጣት ወደ ህዝቡ ሰርስሮ በመግባት ህጋዊ እና ክልላዊ መልክ በመያዝ ወደ ተደራጀ ግጭት እና ስርዓት አልበኝነት እንዲገባ ስለተደረገ ነው፡፡ በሁሉም አከባቢ የታዩ ግጭቶች የጋራ መገለጫቸው ሁሉም ብሄር ተኮር ግጭቶች መስተዋላቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ አንድን ብሄር ለሌላው ብሄር ጠላት የሚሆንበት ወይም ችግር የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም፤ ከአሁን በፊትም ሆኖ ኣያውቅም ለወደፊትም የሚሆን አይደለም፡፡ ግጭቶቹ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር እላፊ ጥቅም ስለወሰደም አይደለም፤ እንኳን አሁን ሁሉም የየራሱ ክልል እያስተዳደረ እና በፌደራል መንግስት ፍትሃፊ ተሳትፎ እያለው ይቅር፣ በትምክህት እና በነፍጠኛው ስርዓት ጊዜው አንዱን ህዝብ ከሌላው ህዝብ እላፊ ጥቅም የወሰደበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በቀጣይም የፈለገው ፀረ ዴሞክራሲና ፀረ ህዝብ ስርዓት ቢመጣም አንዱን ህዝብ በመጥቀም ሌላ ህዝብ የሚጎዳ ስርዓት ሊመጣ አይችልም፣ ሊመጣ የሚያስቸል ተፈጥሯዊ ሁኔታም የለም፡፡ ምክንያቱ ፀረህዝቦች ከራሳቸው ውጭ የሚጠቅሙት ህዝብ ስለሌለ፡፡ ለዚህ ነው ፀረ ህዝቦች ለተፈጠሩበት ብሄር ወይም ህዝብም ቢሆን የባሱ ፀረህዝቦች ናቸው የሚባለው፡፡

ታድያ ምንድን ነው ችግሩ ምንድን ነው?

ችግሩ ህዝባዊ ወገንተኝነት ማጣት ወይም መሸርሸር ነው፡፡ ህዝባዊ ወገንተኝነት የሌለው ወይም የተሸረሸረበት አመራር ወይም ስርዓት ደግሞ የስም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር እኛ በተግባር ከምናውቀው ከትምክህቱ ወይም ከነፍጠኛው ስርዓት የሚለየው ነገር የለም፡፡ ህዝባዊ ዓላማና ውግንና ይዞ የተነሳ ድርጅት የዝቅጠት እና የመበስበስ መንገድ ከያዘ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ወደ ትምክህተኛው ወይም ነፍጠኛው ጎራ መቀየሩ አይቀርም፡፡ የትምክህት እና የነፍጠኛ ስርዓት በሚባልበት ጊዜ የአንድን ብሄር ወይም ህዝብ መገለጫ አይደለም፤ የጥቂቶች የፀረ ህዝብ እና የፀረ ዴሞክራሲ መገለጫ እንጂ፡፡

አሁን በአገራችን እያየነው ያለው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ በአገራችን በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለዘመን ይንፀባረቅ የነበረው የትምክህት የፀረ ህዝብ እና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት አሁን ዘመናዊእና ኋሏቀር መንገዶች እየተደባለቁ በ21ኛው ክፍለዘመን ሲንፀባረቁ ይታያል፡፡ የዚህ ሁሉ ምንጭ የአመራር ዝቅጠት ነው፡፡ የዝቅጠቱ አደጋ ምን ያክል ከፍተኛ ደረጃ እንደደረሰ የሚያሳየው ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲና ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢ ጎራዎች ተደበላልቆ እርስ በርሳቸው መናቆር መጀመራቸው ነው፡፡ ለማመን እስከሚቸግር ድረስ በአንድ በኩል አንድን የኢህአዴግ እህት ድርጅት ሌላውን በጠላትነት ሲተያይ (ለምሳሌ ብአዴን እና ህወሓት) በሌላ በኩል ደግሞ አንድን የኢህአዴግ እህት ድርጅት ከሌላው ለይቶ (ለምሳሌ ብአዴን እና ኦህዴድ) በልዩ ፍቅር ሲወዳደሱ ስታይ ምን ብለህ ትገልፀዋለህ? መልሱ ለአንባብያን እተወዋለሁ፡፡

በእውነቱ እንነጋገር ከተባለ

በህወሓት እና በብአዴን የአሁኑ አዴፓ ያለው ግንኝነት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ላይ የተመሰረተ ነውን?

ፈፅሞ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ለብአዴን የአሁኑ አዴፓ ከህወሓት ይልቅ ግንቦት 7 እና አርበኞች ይመቸዋል፤ አሁንም ለብአዴን ከህወሓት ይልቅ የኢሳያስ አፈወርቂ ሻዕብያን ይመቸዋል፤ ለህወሓት ከትግል አጋሩ ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ይልቅ ኦነግን ይመቸዋል፡፡ ለምን ? ሁለቱም ድርጅቶች ማለትም ብአዴን እና ህወሓት እንታገልለታለን ብለው ያነገቡት በሰነዳቸው ላይ ያለው ፕሮግራም፣ ዓላማ፣ ራኢይ እና ግቦች ከተፃፉበት የቋንቋ ልዩነት (አንዱ በአማርኛ ሌላው በትግርኛ) በስተቀር ምንም ልዩነት የለውም፡፡ አንድ የአማራ ተወላጅ በህወሓት ተደራጅቶ ቢታገል፣ ወይም አንድ የትግራይ ተወላጅ በብአዴን ተደራጅቶ ቢታገል፣ የተወለደበት ብሄር ወይም ህዝብ ጥቅም ብቻ ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም ያስከብራል፤ ኢህአዴግ የሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ፍልስፍና የሚለው ይህ ነው፡፡ 

ታድያ ለምንድን ነው ከዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ርቆ መሄድ ያስፈለገ ? የትግል ተሞክሮ ማነስ ነው?

መልሱ አሁንም ጥልቅ ተሃድሶው በመክሸፉ ኢህአዴግ በመበስበስ መንገድ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ጎበዝ ነቃ እንበል እንጂ፡፡ አሁን በህወሓት እና በአዴፓ ላይ ያለው ግንኝነት የጠላትነት አንዱን ሌላውን የሚጠረጥርበት፣ አንዱ ሌላውን ሊወረኝ ነው፣ ጦርነት ሊከፍትብኝ ነው በሚል አመለካከት የተሰለቡ በጠላትነት የሚተያዩ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ወደድንም ጠላንም ሀቁ ይህ ነው፡፡ ለህዝብ ጥቅም አንተ ትብስ አንተ ትብስ ተባብሎ የታገሉ ድርጅቶች፤ አብረው መስዋእት የከፈሉ እና ታጋዮቻቸው አንድ ጉድጓድ ላይ የቀበሩ ድርጅቶች እንዲህ በጠላትነት እና በጥርጣሬ ዓይን መተያየት ከጀመሩ እውነትም እነዚህ ድርጅቶች ወደ ለየለት ፀረ ህዝብ እና ፀረ ዴሞክራሲ ጎራ ተደበላልቋል ቢባል ሓቁን መናገር እንጂ መወስለት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፡-

በኦህዴድ የአሁኑ ኦዴፓ እና በብአዴን የአሁኑ አዴፓ ያለው ግንኝነት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ላይ የተመሰረተ ነውን?

በፍፁም አይደለም፡፡ ፍቅሩ ለይስሙላ ወይም ፌክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በጣም ብዙ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያሉባት አገር፣ የግለሰቦች የጥገኛነት ፍላጎት እንጂ በህዝቦች መካከል የጥቅም ግጭት የሌለባት አገር፣ በህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር አንዱን ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች አብልጦ ለሌላ ህዝብ ልዩ ፍቅር እንዳለው አድርጎ ማየት፣ አንዱን ህዝብ በሁለት ህዝቦች መካከል ገብቶ ማጋጨት እንደሚፈልግ አድርጎ በመውሰድ በአደባባይ መናገር፣ ኦሮማራ ማለት ምንድን ነው? ኦሮማራ የሚል ስም አውጥቶ መንቀሳቀስ ለዛውም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም አራማጅ በሚባል ድርጅት እንዲህ ብሎ ፕሮፖጋንዳ መንዛት መበስበስ ነው፡፡

ብአዴን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር እየተመራ ሲታገል ለምን ለአማራ ህዝብ ጥቅም ብቻ፣ ለምን ለትግራይ ህዝብ መብት አይቆምም? ለምን ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር አይቆመም? ለምን ለሶማሌና ነቤንሻንጉል ጉምዝ ህዝብ ጥቅም መረጋገጥ አይቆምም?

ኦህዴድ ለምን ከአማራ ህዝብ ብቻ ልዩ ፍቅር አደረው? ለምን ከሶማሌ ህዝብ ጋር እንደ ኦሮማራ አልመሰረተም? ለምን ከቤንሻንጉል ጉምዝ እንደ ኦሮማራ አልመሰረተም? ለምን ከደቡብ ህዝቦች እና ከትግራይ ህዝብ ጋር እንደ ኦሮማራ አልመሰረተም? ሁሉም የአገራችን ህዝቦች እኩል አይደሉም እንዴ? ደኢህዴን እና ህወሓት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አይደሉም እንዴ? በድንበር ስለማይገናኙ ነው እንዴ? መልሱ አይደለም፡፡ እነዚህ የአገራችን ህዝቦች ፈፅሞ አንዱ የሌላው ጠላት ሆኖ አያውቁም፤ ወይም አንዱ የሌላው ብቻ ልዩ ወዳጅ ሆኖ አያውቁም፤ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች እኩል ናቸው፣ ሁሉም በጋራ ያለምንም ልዩነት በገዢዎች ሲጮቆኑ ኑሮዋል፣ ሁሉም በተናጠልም በተደራጀም ለመብታቸው ሲታገሉ ኖሮዋል፡፡ ታድያ ለምን ተጣልተው የነበሩ ይመስል፣ አሁን በኦህዴድ እና በብአዴን ሽምግልና የታረቁ ይመስል ኦሮማራ የሚል ስያሜ መስጠት ምን አመጣው?

አሁን እያየነው ያለውን ኦሮማራ ወይም ቲም-ለማ የሚል እንቅስቃሴ፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እይታ አንፃር ሲታይ የጥቂት የኦህዴድ እና የብአዴን አመራሮች የጥፋት አደረጃጀትና ቁርኝት እንጂ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ አይደለም፣ የዝቅጠት እና የጥፋት ምልክት ነው፡፡ የመበስበስ ምልክት ነው፡፡ የአማራ ህዝብ እና የኦሮሞ ህዝብ መቼም ጠላት ሆኖ አያውቅም፣ ተጣልቶም አያውቅም፡፡ ማንም ግለሰብ ይሁን የፖለቲካ ድርጅት ሁለትን ህዝብ ማጣላት አይችልም፡፡ ሙከራዎች ቢኖሩም ሁሌም እንደከሸፈ ነው፣ ይህም ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በደንብ ያውቁታል፡፡ሚኒሊክ በኦሮሞ ህዝብ እና በሌሎች ህዝቦች የፈፀመው ግፍ ሚሊሊክ እና መዋቅሩ ይጠየቁበታል እንጂ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ወይም ጤነኛ አመለካከት ያለው ድርጅት ሚኒሊክ የወጣበትን የአማራ ህዝብ አይወቅስም፤ የደርግ ሊቀመንበር መንግስቱ ኋ/ማርያም በተከተለው ፀረ ህዝብ እና ፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ከግማሽ ሚልዮን በላይ ዜጎች በቀይሽብር እንዲያልቁ በማድረጉ መንግስቱ ኋ/ማርያም ከነ መዋቅሩ ይጠየቃል እንጂ እሱ የወጣበት ብሄር ወይም ህዝብ ተጠያቂ ማድረግ ከሱ ተለይቶ አይታይም፡፡በአሁኑ ፌደራላዊ ስርዓትም ከህወሓት፣ ወይም ከኦህዴድ ወይም ከብአዴን ወይም ከደኢህዴን ወይም ከሁሉም የወጡ ጥቂት አመራሮች በኪራይ ሰብሳቢነት ህዝብን ሲያሰቃዩ የነበሩ ራሳቸው እና ግብረ አበሮቻቸው ይጠየቃሉ እንጂ፣ እነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች የወጡበትን ብሄር ወይም ህዝብ እንደ ህዝብ ፈርጆ ማሸማቀቅ የቀን ጅቦች ብሎ መሳደብ የጤነኛ አእምሮ ወይም የጤኔኛ ድርጅት መገለጫ አይደለም፡፡

ይቅር እና ኪራይ ሰብሳቢዎች በሰረቁት ሀብት ምክንያት የብሄራቸውን ህዝብ ተጠያቂ በማድረግ መፈረጅ፤ ኪራይ ሰብሳቢዎች የተደራጁበት የኢህአዴግ እህት ድርጅት ወይም ኢህአዴግ ራሱም እንደፈፀመው አድርጎ መውሰድም ተገቢ አይደለም ምክንያቱ የኢህአዴግ ፕሮግራም እና ዓላማ ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው፣ በተግባርም አገርና ህዝብን የቀየረና በተከታታይ የህዝብ ይሁንታ/ድጋፍ ያገኘ በመሆኑ፡፡ ስለዚ ተጠያቂ የሚሆኑት፣ በቀን ጅብነት የሚፈረጁት ራሳቸው የኪራይ ሰብሳቢነት አዘቅት ውስጥ የተዘፈቁት እንጂ ንፁህ ዜጋ ማሸማቀቅ ትክክል አይደለም፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት ሲባል የመንግስት ስልጣንን ተገን በማድረግ የህዝብ ሃብት መዝረፍ እና/ወይም ማዘረፍ ማለት ነው፡፡ በኢህአዴግ አሰራር እና አደረጃጀት መሰረት የኢህአዴግ አመራር ሰጪ አካል የሆነው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የኢህአዴግ ምክርቤት፣ ከአራቱም እህት ድርጅቶች በእኩል ኮታ በተውጣጡ አመራሮች የተዋቀረ ሲሆን አራቱም ድርጅቶች እኩል ተሳትፎና ተጠያቂነት አላቸው፡፡ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠው የመንግስት ስልጣን በተመለከተ (የተወካዮች ምክርቤት እና የሚኒስትሮች ምክርቤት) ግን አራቱ እህት ድርጅቶች የወከሉትን የህዝብ ብዛት መሰረት ባደረገ ኮታ በተውጣጡ አመራሮች የተዋቀረ ነው፡፡በዚህ መሰረት ህወሓት በፌደራል መንግስት ያላትን ቦታ ሲታይ ከ8% የማይበልጥ ሲሆን፣ ደኢህዴን ከ20% የማይበልጥ፣ ኦህዴድ ከ30% የማይበልጥ፣ ብአዴን ከ28% የማይበልጥ ሲሆን የተቀሩት አጋር ድርጅቶች ደግሞ ከ14% አይበልጥም፡፡ በእውነቱ እንነጋገር ከተባለ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት የተናጠው የኢህአዴግ መንግስት የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራት የሚፈፅሙ ሙሰኞች ይጋለጡ ቢባል ከየድርጅቱ እንደየ የተሳትፎ ብዛት እንደሚኖሩ ምንም አያጠራጥርም፡፡ እንደ ስርዓት ኢህአዴግ በኪራይ ሰብሳቢነት ተለክፏል ከተባለ የቀን ጅብ የሚለው ፍረጃ እንዴት 30% እና 28% የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠሩት የኦህዴድ እና የብአዴን አመራሮች ሳይፈረጁ፣ 8% የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው የህወሓት አመራር ይፈረጃል? ከሁሉም ነገር የሚገርመው ደግሞ ፈራጂው ሁለቱም ማለትም 58% የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው ከኪራይ ሰብሳቢነት ነፃ ያልሆነው አመራር መሆኑ ነው፡፡

ለነገሩ ይህን የቁጥር ማነፃፀሪያ ያመጣሁት አንዱን ትንሽ ስርቆት ስለፈፀመ ችግር የለውም፣ ሌላው ትልቅ ስርቆት ስለፈፀመ ወንጀለኛ ነው ለማለት ሳይሆን፣ ወይም ትንሽ ተሳትፎ ያለው ኪራይ ሰብሳቢነቱ ትንሽ ነው ሰፊ ተሳትፎ ያለው ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነቱ ሰፊ ነው ለማለት አይደለም፡፡ እንዲህ ከሆነ ከኪራይ ሰብሳቢነት መደራደር ማለት ነው፡፡እኔ ለማለት የፈለኩት አሁን ኢህአዴግ ላይ እያየነው ያለውን ነገር የጤነኛ አካሄድ አይደለም፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ የተከተለ አይደለም፣ ሪፎርሙ ወይም ተሃድሶው ስም ብቻ በመያዝ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት በዝቅጠት ጎዳና እየተጓዘ ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ግንባር የኪራይ ሰብሳቢዎች መፋለሚያ ድርጅት እየሆነ ነው፡፡ እዚህም እዛም በእህት ድርጅቶች ውስጥ ስልጣን ተቆጣጥረው ያሉት ኪራይ ሰብሳቢዎች በሚያደርጉት አፍራሽ ፕሮፖጋንዳና ፍልሚያዎች ምክንያት ህዝቡ ሰላም እና መረጋጋት አጥቷል፣ ብሄር ተኮር ጥቃቶች ተጧጥፏል፡፡ ስለዚህ ይህን ጉዳይ ኢህአዴግ ቆም ብሎ በሰከነ አእምሮ፣ ከስሜታዊነት በመውጣት፣ ያለፉትን የትግሉ ሰማእታት በማስታወስ፣ የህዝብ ፍላጎት እና የሆይሆይ ነውጠኛ ፍላጎት በመለየት፣ ለፍትህ፣ ለሰላም፣ ለህዝብ፣ ለአገር አንድነት መስዋእት ለመክፈል በመዘጋጀት ሊፈታው ይገባል፡፡

ይህን ለማድረግ ኢህአዴግ ለያንዳንዱ እህት ድርጅቶች የቤት ስራ መስጠት አለበት፡፡ እሱም በየብሄራዊ ድርጅቶች ተሰግስገው ያሉ አመራሮችን ማጥራት ነው፡፡ መደመር የሚለው ፍልስፍና የማይገባው ሰው ይሁን ድርጅት አለ ብየ አላምንም፡፡ መነሻው ቅዱስ ነው፣ መነሻው ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ነው፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ለማስፋት ነው፣ ሁሉም ዜጋ ባለችው ብቸኛ አገሩ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ትግል ለማድረግ እና በአገሩ እጣፈንታ የመወሰን መብት እንዲሰጠው ነው፣ የህግ የበላይነት ተከብሮ ዜጎች ሁሉም በእኩል መብት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ነው፣ ስልጣን ለህዝብ መገልገያ ብቻ እንዲሆን እና ከዚህ ውጭ የሚደረግ በስልጣን መባለግ በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲገታ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን በተግባር እያየነው ያለውን እንቅስቃሴ የሚያሳየው በስመ መደመር ጤነኛውም ልክፍቱም አንድ ላይ ተደባልቆ ጎራ ለይቶ የሞት ሽረት ትግል ሲያደርግ ነው፡፡ በመደመር ስም ኪራይ ሰብሳቢው እና ንፁሁ ተደባልቆ የሚደረገው ትግል ህዝባዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ሳይሆን በህዝቦች መካከል መቃቃር እና ግጭትን በመፍጠር የግልን የስልጣን ጥማት ማርካት ነው፡፡ በዚህ መሀል ግን የግጭቱ ገፈት ቀማሽ እየሆነ ያለው ሚስኪን ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ዜጋ እንዲሁም ወጣቱ ነው፡፡

ስለዚህ ኢህአዴግ ለማዳን ከተፈለገ አሁንም የውስጥ ችግር በየድርጅቱ መፍታት አለበት፤ ራሱን መፈተሽ አለበት፣ እስካሁን ድረስ እያደረጋቸው ያለ የህዝብ ግንኝነት እና ፕሮፖጋንዳዎች መፈተሽ አለበት፡፡ የአሁን ኢህአዴግ ትክክለኛ ኢህአዴግ አይደለም፡፡አንድ ዓይነት ዓላማ ይዞ ግን የማይተማመኑ በጥርጥር ዓይን የሚተያዩ ድርጅቶች ለይስሙላ አንድ ነን ቢሉ ትርጉም የለዉም፡፡ አሁን ያለ ኢህአዴግ ህዝባዊ ውግንናው የረሳ ከህዝብ ሰላምና መረጋጋት ውጭ የራሱ የአመራሩ ክብር የሚጨነቅ፣ አንዱን ሌላውን ለማጥቃት ከፀረህዝቦች እና ፀረ ዴሞራሲያዊ ድርጅቶች ግንባር የሚፈጥር አድሃሪ ድርጅት ሆኖዋል፡፡ ኢህአዴግ ለራሱ ሲል ካልተስተካከለ ኢህአዴግነት ተረት ተረት ሆኖ ይቀራል፡፡

ስለዚህ የአመለካከት ማጥራት መካሄድ አለበት፤ የጎራ መደበላለቅ ሚናውን ይለይ፤ በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ ውስጡን ፈትሾ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ከውስጡ መንቅሮ ካላስወጣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ህልውና በኢህአዴግ ያከትምለታል፡፡ ስለዚህ የኢህአዴግ ህይወት ለመዝራት መደመር ሳይሆን መቀነስ ነው የሚያዋጣው፡፡ አሁን ኢህአዴግ በመደመር ስም የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋቱ የሚደነቅ ሲሆን በውስጠ ድርጅት እንቅስቃሴ ግን በመቀነስ ኪራይ ሰብሳቢዎችን መንግሎ ማውጣትና አብዮታዊ ዴሞክራሲን ማዳን ስራ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

አሁን እየተካሄደ ያለው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ይህን ጉዳይ እንደ ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ ካልተወያየበት እና ጠንካራ ውሳኔ ካላሳለፈበት ጉባኤው ትርጉም የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ አጨራረስ በጉጉት እየጠበቀው ያለውም ኢህአዴግ አሁን ከገባበት አዘቅት ውስጥ የሚያስወጣ ጠንካራ አቋም ይዞ ይወጣል በሚል ነው፤ ለዚህ ስኬት በአጠቃላይ ጉባኤተኛው በተለይ ደግሞ የሊቀመንበሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡

ህዳሴ ኢትዮጵያ

መስከረም 24፣ 2011 ዓ.ም.

አስተያየትዎ በ hidaseethiopia@yahoo.com ወይም hidaseethiopiaa@gmail.com ማድረስ ይቻላል

Back to Front Page