Back to Front Page


Share This Article!
Share
የነቃ ብርሌና የኢህአዴግ ጥምረት

የነቃ ብርሌና የኢህአዴግ ጥምረት

ከእውነቱ ይታያል 10-08-18

ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ ይላሉ ያገራችን እናትና አባቶች ከተጨባጭ የህይወት ልምዳቸው ተነስተው። እውነትም ደግሞ ብርሌ አንዴ ከነቃ ለጊዜው መልኩን አሳምሮ ይቀመጥ እንደሆነ ነው እንጅ የተሰራበትን አላማ በሚገባ ሊያሳካ አይችልም። ጥቅም ላይ ይዋል ቢባል እንኳን ትንሽ ጠበቅ አድረግው ሲይዙት ፍርክስክስ ማለቱ አይቀርም። ከፈራረሰ በኋላም ልጠግንህ ቢሉት በጅ የሚል የቤት እቃ አይደለም። እዩኝ ያለ ባለሙያ ጋ ቢቀርብ እንኳን ወደነበረበት ተመልሶ አግግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የሚቻል አይደለም። ሙጫና፣ ማስቲሽ ይዞ የነቃ ብርሌን ለመጠገን ሙከራ ማድረግም ትርፉ ድካም እንጅ ብርሌን ጠግነው አገልግሎት እንዲውል ያደርጉታል ማለት ዘበት ነው። አይደለም ተራ ማስቲሽና ሙጫ ቀርቶ ልእለ ማስቲሽ (Super Glue) የሚባለው የማስቲሾች ሁሉ ማስቲሽ እንኳ የነቃ ብርሌን ለመጠገን አቅሙ ያለው አይመስልም። ብረትን ያህል ነገር ጠግኖ አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚያደርግ ብየዳን ተጠቅሞም ቢሆን የነቃ ብርሌን ጠግኖ ወደነበረበት ቦታ መመለስ የሚቻል አይደለም።

Videos From Around The World

ከዚህ በላይ ያለውን የፅሁፌን ክፍል ስታዩ ታዲያ የነቃ ብርሌን መጠገን የማይቻል መሆኑ ከኢህአዴግ ጋ ምን አገናኘው የሚል ጥያቄ ልታነሱ ትችላላችሁ። ጥያቄያችሁ ትክክል ቢሆንም እንዴት ሊገናኝ እንደሚችል ግን ከዚህ በታች ባለው የፅሁፌ ክፍሎች ለማብራራት እሞክራለሁ። ኢህአዴግ እንድብርሌ ሁሉ ሰዎች ቀርፀው የፈጠሩት አካል ነው። ይህ አካል የተፈጠረው ልክ እንደብርሌው ሁሉ የተለያዩ ክፍሎች ተሳክተው ነው። በዚህ መልክ ተሳክተው ኢህአዴግን የፈጠሩ ክፍሎች ደግሞ ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን ናቸው።

እነዚህ አራት ድርጅቶች ኢህአዴግን ሲፈጥሩ እኩል ቁመና አልነበራቸውም። ሁላችንም እንደምንገነዘበው ህወሓት በትግል ልምድም ይሁን በሰው ሃይል ብቃት ከሁሉም የበለጠ ቁመና ያዳበረ ድርጅት ነው። ከህወሃት ቀጥሎ ደግሞ በተነፃፃሪነት ብአዴን ከዛም ኦህዴድ ብሎም ደኢህዴን እንደየቅደም ተከተላቸው ቁመናቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኝ ድርጅቶች ናቸው። ታዲያ እነዚህ የኢህአዴግ መሰረት የሆኑ ድርጅቶች በእኩል ቁመና ላይ ያልነበሩ በመሆኑ የኢህአዴግ ቁመናም የተንጋደደ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል። ከዚህ ስንነሳ ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ትፅእኖ የነበረው ህወሃት እንደሆነ ለመገንዘብ የግድ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም። ይህ በመሆኑም ሌሎቹ ሶስቱ ድርጅቶች ማለትም ብአዴን፣ ኦህዴድና ደኢህዴን ህወሃትን ያዩት የነበረው ልክ እንደፈጣሪያቸው ነበር። እነዚህ ድርጅቶች በፍርሃትም ይሁን በአቅም ማነስ ወይም በአክብሮት እንደህወሃት የሚያመልኩት ሃይል አልነበረም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በርካታ የህወሃት አመራሮችና አባላት ራሳቸውን አግዝፈውና አይነኬ እንደሆኑ ቆጥረው ያሻቸውን እንዲያደርጉ በር ከፍቶላቸዋል፤ በጀብድም እንዲወጠሩና የሚነገራቸውን መስማት እንዳይችሉ አድርጓቸው ቆይቷል።

በዚህ ሂደት ከላይ የተገለፀው የኢህአዴግ መንጋደድ አሳስቦናል ያሉ ብአዴን ውስጥ ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው አባላትና የተወሰኑ አመራሮች የኢህአዴግ መሰረት ተስተካክሎ መደላድል መፈጠር አለበት የሚል ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ። ይህን ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩትን ሃይሎች በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው ሃይል ያነሳ የነበረው ሃሳብ ከቅንነት የመነጨ ሲሆን ሃሳቡም ያለመመጣጠኑ ተወግዶ ኢህአዴግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለመ ነበር። ሁለተኛው ሃይል ደግሞ ድሮውንም ቢሆን አለመመጣጠኑ የተፈጠረው በህወሃት ፍላጎት ነው ከሚል በትምክህት አመለካከት የተሸፈነ እምነት ተነስቶ ከህወሃት ጋ ያለው ጥምረት እንዲፈርስ ጭምር የራሱ የሆነ መረብ (Network) ዘርግቶ የሚንቀሳቀስ ሃይል ነው። በነገራችን ይ በየመድረኩ ጎልቶ የሚሰማው ድምፅ የዚሁ የሁለተኛው ሃይል ድምፅ ነው። እንዲያውም በዚህ ዙሪያ የተሰባሰበው የአባላትና የአመራር ሃይል ማእከላዊ ኮሚቴ ሆኖ ለመመረጥና በየመድረኩ ሻምፒዮን ሆኖ ለመውጣት ህወሓትን መቃወም እንደመመዘኛ አድርጎ የወሰደ ነው ቢባል አባይ አያሰኝም። ይህ ሃይል ከዚህ የህወሃት ሰዎችን ከመጥላት አባዜ አልፎ ብአዴን ውስጥ ያሉ የትግራይ ደም አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ ግን ደግሞ ለአማራ ህዝብ ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ ነባር የኢህዴታግዮችን ሳይቀር ጠልቶ በማስጠላት ረገድ ያደርገው የነበረ እንቅስቃሴም በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ይህ አደገኛ የሆነ የትምክህት አስተሳሰብ እየገነገነ ቢሄድም ችግሩን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ደግሞ የራሱ የሆነ እጅግ በጣም ከፍተኛ ውሱንነት ነበረበት። ይህን ችግር ለመፍታት መደረግ የነበረበት በትምክህት አመለካክት አደገኝነትና በዴሞክራሲያዊ ብሄርተንነት አስፈላጊነት ላይ የፅንሰ ሃሳብና የተግባር ቅንነት የተሞላበት ቀጣይ የሆነ ውይይት በማድረግ በአባላትና በአመራሩ ውስጥ የአመለካከት አንድነት እንዲፈጠር ማስቻል ነበር። ከዚህ ይልቅ ብአዴን የተከተለው አማራጭ በድፍኑ ትምክህት ነው የሚል የፍረጃ መንገድን ነበር። ይህ መንገድ ለጊዜው ሃሳቡን ያነሱ የነበሩ አባላትንና አመራሮችን አስመስለው እንዲኖሩ አደረጋቸው እንጅ ዘለቄታዊ የሆነ መፍትሄ አላመጣም። ይልቁንም እነዚህ ሰዎች ሃሳቡን ውስጥ ለውስጥ እያብላሉና በህዝቡ በተለይም በወጣቱ ውስጥ እያሰራጩ የተመቻቸ መድረክ እስኪፈጠርላቸው እንዲቆዩ ነበር ያደረገው።

የተመኙትም አልቀረ እነዚሁ ሰዎች የትምክህትን እሳት ተጠቅመው ባቀጣጠሉትና በሌሎችም ያልተመለሱ ጥያቄዎች ምክንያት ህዝቡ አሻፈረኝ ማለት ጀመረ። በዚህ ወቅት የህዝቡን አልገዛም ባይነት እንደደጀን በመጠቀም ከህወሓት ሰዎች ጋ ያላቸውን ቁርሾ ማራገብ ጀመሩ። በዚህም መሰረት የህወሃት የበላይነት አለ በሚል (አንዳንዴም የሚሉትን እውነት የሚያስመስሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህወሃት ሰዎች የሚሰሩትን ጥፋት በማንሳት) ህወሃትን እንደድርጅት መወንጀል ቀጠሉበት። ከዚህ አልፎም አብረዋቸው የሚታገሉ ነባር አመራር አባላትን ዘር እየጠቀሱ ማሸማቀቅና ህዝብ እንዲጠላቸው የማድረግ ህቡዕና ግልፅ ቅስቀሳን ስራየ ብለው ተያያዙት። ቅስቀሳ ብቻም ሳይሆን አሁን በቅርቡ እንደታየው የዘር ማፅዳት በሚመስል መንገድ የትግራይ ደም አለባቸው የሚባሉና ሌሎች ለህወሃት የቀረቡ ናቸው ተብለው የሚታሰቡትን ከፍተኛ አመራሮች የተለያየ ምክንያት ሰጥተው ከብአዴን ገለል እንዲሉ አድርገዋቸዋል።

የህወሃት ሰዎች በበኩላቸው ትክክለኛ የሆኑ ቅሬታዎችን ተቀብለው የማስተካከያ እርምጃወች ከመስውሰድና ትክክለኛ ያልሆኑትን ደግሞ በማስረጃ አስደግፈው ከማስተባበል ይልቅ ሁሉንም በጅምላ የመቃወም አባዜ ተጠናወታቸው። ይህ በብአዴን ፅንፈኛና ትምክህተኛ ሃይሎች በአንድ በኩል በህወሃት ጀብደኖችና አይነኬ ነን ባዮች በሌላ በኩል ሆኖ የመሳሳብ ትዕይንት ገሃድ ወጥቶ ችግሩ ለዘመናት ተግባብተው ለሚኖሩት የአማራና የትግራይ ህዝቦች ሳይቀር መትረፍ ጀመረ። የኋላ ኋላ ደግሞ ነገሮች እየገፉ ሄዱና ይህ ብአዴን ውስጥ ያለው ፅንፈኛና ትምክህተኛ ሃይል የድርጅቱን አመራር በበላይነት ተቆጣጠረው።

ይህ ህወሓት ሰዎችና ከፍተኛውን የአመራር ቦታ በተቆጣጠሩት የብአዴን ፅንፈኞች መካከል የነበረው ግንኙነት ከላይ በተገለፀው መንገድ እየተካረረ በሄደበት ወቅት ኦሮሚያ ውስጥ የተፈጠረው የህዝብ አመፅ ተባብሶ ኦህዴድን ሊውጠው ደረሰ። በዚህ ጊዜ ኦህዴድ ውስጥ የነበሩ በርካታ አባላትና አመራሮች ተደራጅተው ወደፊት በመምጣት እነሱም ሲፈፅሟቸው ለነበሩ ጥፋቶች ሁሉ ህወሃትን ተጠያቂ ማድረግ ጀመሩ። ከዚህ አልፈውም እነዚህ ሃይሎች የህዝቡ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ከማድረግ ይልቅ አንዳንዴም አሁን አሁን እየሰማን እንዳለነው ኢህአዴግን ከሚቃወሙ ፅንፈኛ ሃይሎች ጋ በድብቅ በመሻረክ የህዝቡን ሰላማዊ የሆነ ጥያቄ ወደረብሻና ስርዓት አልበኝነት ቀየሩት። በዚህም ሳቢያ ብዙ ህይወት ጠፋ፣ ንብረት ወደመ ባጠቃላይም ሰላም ታወከ። ይህን ረብሻና ስርዓት አልበኝኘት ለማቀጣጠል የተጠቀሙበት ስልት ደግሞ ዘረኝነት ሲሆን በሚገርም ሁኔታ የሚቆጣጠሯቸውን እንደ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (OBN) እና ኦሮሚያ ሚድያ ነትወርክ (OMN) የመሳሰሉ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም አንዳንዴ ቦምብ ይዞ ተገኘ በሌላ ጊዜ ደግሞ ዶላር እያሉ ዘር በመጥቀስ በህወሃት ዚሪያ ያሉ ሰዎችን መወንጀል ስራየ ብለው ተያያዙት።

ከዚህ አልፎም እነዚህ የኦህዴድ ሰዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኝኙነት በሚል ሽፋን ከኢህአዴግ አሰራር በወጣ መንገድ ብአዴን ዉስጥ ካሉ ፅንፈኞች ጋ ዘላቂነት ይኑረው አይኑረው እርግጠኛ ያልሆነ ስልታዊ የሚመስል ቡድነኝነት ፈጠሩ። ይህ የብአዴን ፅንፈኞችና የኦህዴድ ሰዎች ጥምረት ራሱን የተሃድሶ/የለውጥ ሃይል ነኝ ብሎ ካወጀ በኋላ አሁንም በለመደው የቡድነኝነት መንገዱ የኢህአዴግን የስልጣን መንበር ተቆጣጠረ። ወዲያውም በኢህአዴግ ተቃዋሚውች የወጣን ቲም ለማ የሚልን ስም በይፋ አፀደቀ። ይህ የቲም ለማ ቡድን የሚያካትተው ደግሞ በዋነኝነት የብአዴንና የኦህዴድን ጽንፈኞች ሲሆን በኋላም የደኢህዴንን ሊቀመንበር እንደሚጨምርም በይፋ ታወጀ።

በሌላ በኩል ህወሃት እንደለውጥ አደናቃፊ ተደርጎ ተወሰደ። በዚህ ላይ የርዕዮተ-አለም አንድነት የሚባል ነገር እንደሌላቸው ከሚያደርጉት የተዘበራረቀ ተግባራቸውና የተጣረሰ መግለጫቸው ግልፅ እየሆነ መጥቷል። በቅርቡ ባደረጉት ጉባኤያቸውም ቢሆን ላይ ላዩን ካልሆነ በስተቀር ውስጣዊና ልብ ለልብ የተገናኘ የሃሳብ አንድነት ይዘው ወጥተዋል ብሎ ለመናገር የሚያስችል ተጨባጭ የሆነ ነገር አላየንም። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ኢህአዴግ በሁለት ጎራ ተከፍሎ እየተናጠ ያለ ግንባር መሆኑን ነው። ይህ መናጥ የኢህአዴግን መሰረት እያናወጠው እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች እንዳሉ ለሁሉም ግልፅ እየህነ መጥቷል። የመናወጡ ቀጣይ ውጤት ደግሞ ልክ እንደብርሌው መነቃቃት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ከዚህ ሁሉ ስንነሳ የአራቱም አባል ድርጅቶች በተለይም የብአዴንና የህወሓት ሰዎች ልብ ለልብ ተገናኝተው በቅንነትና መርህን በተከተለ መንገድ ችግራቸውን ሊፈቱ የሚችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር የጊዜ ጉዳይ እንጅ የኢህአዴግ ንቃቃት ሰፍቶ ሊፈረካከስ እንደሚችል ደፍሮ መናገር ይቻላል።

 

 

Back to Front Page