Back to Front Page


Share This Article!
Share
ኢሕኣዴግ፣ጠቅላይ ሚንስትሩና የለውጡ ሂደት

ኢሕኣዴግ፣ጠቅላይ ሚንስትሩና የለውጡ ሂደት

ተክለሚካኤል ኪ/ማርያም 07-20-18

 

ባለፉት 3 ወራት በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ ኣሕመድ የተከናወኑ ውጤታማ ሰራዎች በኣርአያነታቸው የሚጠቀሱ ሲሆን ለውጡ የኢሕኣድግ ኣቅጣጫ መሰረት ያደረገ እንደሆነይታመናል፡፡ እምነቱ የሚመነጨውም ኣገርን መምራት ከላይ እስከ ታች የተዘረጋውን የስራ መዋቅር ኣብሮ ሲራመድ ውጤቱ ያመረ ከመሆኑም በላይ የብዙዎች ይሁንታ ሲኖረው ፋይዳው የላቀ መሆኑን ስለሚታወቅ ነው፡፡

በበኩሌ ኢሕኣዴግ የጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ብሎ ምን ምን ለማከናወን እንደ ተዘጋጀ በመግለፅ ላለፈው ድክመቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ በኣደባበይ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል፡፡በተጨማሪም የኣመራር ለውጥ ለማድረግ መዘጋጀቱም ከውሳኔዎቹ ግንባር ቀደም የሚጠቀስ ሲሆን ዶ/ር ዓብይም የዚሁ ውጤት ናቸውተብሎ ይወሰዳል፡፡

በሌላ በኩል ችግሮችን መለየትና የመፍትሄ ኣቅጣጫ ማስቀመጥ ለኢሕኣዴግ ኣዲስ ባይሆንም በተቀመጠው ኣቅጣጫ መሰረት በቆራጥነት ተንቀሳቅሶ ውሳኔዎችን በብቃት ማስፈፀም ግን የክቡር ዶ/ር ዓብይ ልዩ ብቃትና ክህሎትን ያረጋገጠ ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላምን ለማስፈን ፍቅርና መደመር የሚለው መሪ ቃል እንደ ኣንድ የመረጋጋት ኣቅጣጫ የተጠቀሙበት ሲሆን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ኣገሮችም ጭምር እንደሆነ በተጨባጭ እያየን ነው፡፡

Videos From Around The World

ይህንን የክቡር ጠቐላይ ሚኒስትሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ላለፉት ሦስት ዓመታት በኣገራችን የነበረውን ኣለመረጋጋት በማስታገስ ከኣሁን በፊት የተመዘገበውን ልማት በተሻለ ፍጥነት ማስቀጠልና የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቀሚነት ማረጋገጥ ግንበር ቀደም የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት መሆኑንምኣይዘነጋም፡፡

ለታየው ለውጥምየተደበላለቀ ስሜትና ፍላጎት እየተገለፀበት ቢሆንም የህዝቡ ድጋፍ በመቀጠል ላይ ሲሆን ኣገሪቱን በመምራት ላይ ያለው የኢሕኣዴግ የውስጥ ጥንካሬ ግን ከክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር እየተጣጣመ ኣይመስልም፡፡ይኸውም

1. በኢሕኣዴግ ኣባል ድርጀቶችም ሆነ በኣጋር ድርጅቶች የሚመሩ ክልሎች በየደረጃው ያሉት ባለስልጣኖች ከየራሳቸው ፍላጎት በመነሳትና ሰበብ ኣስባብ እየፈጠሩ ህዝቡን በማጋጨት የሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት ዕለታዊ ፍፃሜ እየሆነ ይገኛል፡፡

2. በየድጋፍ ሰልፉ የሚደመጡ መፈከሮች በኢሕኣዴግ የምትመራ ኣገር እያለች በተወሰኑ የኢሕኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መፈክሮች እየተሰተዋሉ ሲሆን ይባስ ብሎ ደግሞከፍተኛ የፓርቲና የመንግስት ባለስልጠናት በኣደባበይ ሲያፀድቁላቸውና እውቅና ሲሰጡዋቸው እየተመለከትን ነው፡፡

3. ህዝቡ ከዚህ የበለጠ ልማት ሊመዘገብ ኣይችልም ነበር ብሎ ባያምንም ዋናው ጥያቄው የልማቱ ኢፍትሓዊ ክፍፍል ፣ የመልካም ኣስተዳደር ችግር ፣ የዴሞክራሲ እጦት ፣ የፍትሕ መጓደልና ከቀበሌ እስከ ከፍተኛ የመንግስት የስራ እርከን የተተበተበው የሙስና ሰንሰለት እንዲወገድለት እንጂ ልማት የለም ብሎ በጭፍን ኣልተናገረም ነበር፡፡ነገር ግን የሚዳሰስና የሚጨበጥ ልማት የሚክዱ ጨለምተኞች ተበራከተው በዓለም የተመሰከረለትን ልማት በመካድ ኢሕኣዴግ ልማት እንዳላስመዘገበ ኣድርጎ የመስበክና ህዝቡን የማደናገርድራማ ቀጣይ ስራ ሆነዋል፡፡

4. ጥፋት የተረጋገጠባቸው ኣመራሮች ካሉ ህግና ስርዓትን ጠብቆ መጠየቅ ሲገባ ከስውር እስከ ኣደባባይ በተካሄደባቸው ዘመቻ ነባር ኣመራሮችን እስከ ማደንና ማሳደድ የደረሰ ኣንገት የሚያስደፋ እንቅስቃሴ እየታዘብ ነው፡፡ለዚህም በኣማራ ክልል ኣንዳንድ ከተሞች የታዩ ክስተቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ከዚህ ኣኳያ ጥፋተኞች ተብለው የሚፈረጁ ሰዎች ካሉምበየቦታው የማንም እጅ የሚቀሰርባቸው ከሆነ ስርዓት ኣልበኝነትን ከማንገስ ኣልፎ ግብዞቹ እንደሚሉት ዴሞክራሲሊሆነ ኣይችልም፡፡

5. እውነት እንናገር ከተባለ ብኣዴንየህዝብ ጥያቄ መመለስ ሲያቅተው ሁሉም ወደ ትግራይ እንደ ተጫነ ኣስመስሎ የተዛባ መረጃ በካድሬዎቹ በኵል ውስጥ ለውስጥ ወደ ወጣቱ እንዲሰራጭ በማድረግ በ2008 ዓ.ም በጎንደርና በሌሎች ከተሞች የተወሰኑ ወጣቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃትበመሰንዘር ኣሳፋሪ ድርጊት ተፈፅመዋል፡፡በብዙ የትግራይ ተወላጆች የደረሰው ጥፋት በቀላሉ የማይታይ ቢሆንም ከክልሉ ፀጥታ ኣካላት ያጡትን ከለላ ምንም ቢሆን ጨዋነቱ ያልተጓደለው የኣማራ ህዝብ ህይወቱን ለህልፈት ኣከሉን ለጉዳት ኣሳልፎ በመስጠት ታግሎ ተቀነባብሮ ከነበረው መጠነ ሰፊ ጥፋት ታድጎኣቸዋል፡፡

6. ኣሁንም ችግሩ ያበቃ ኣይመስልም፤ ምክንያቱ የኣማራ ኣክቲቪስቶች ከሚባሉ ጥቂቶችና በኣንዳንድ ሊሕቃን መሰል ወጣቶች በኣማራ ቴሌቪዥን እየተላለፈ ያለው ጊዜ ያለፈበት ፅንፈኛ ብሄርተኝነት ቅስቀሳ ኢህገ መንግስታዊ ከመሆኑም በላይለኣማራና ለአጎራባች ክልሎች ህዝብ ሌላ የጥፋት ድግስ የሚያዘጋጅ ኣካሄድ ስለሆነ ኣደብ ኣድርጉ ሊባሉ ይገባ ነበር፡፡

እዚህ ላይ በሚገባ መታየት ያለበት እንደ ድርጅት ለተፈፀመው ክፍተት ኢሕኣዴግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ በኣመራር ለውጥ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ግለሰዎች በኣመራር ላይ እያሉ በግላቸው የፈፀሙት ጉድለት ካለ ደግሞ ህገ መንግስታዊ በሆነ ሂደት መጠየቅ ቀርቶሁሉም እንደ ፍላጎቱ እርምጃ ይውሰድ ከተባለ መጨረሻው ምን መሆን እንደሚችል ከጅምሩ እያየን ስለሆነ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ምን እያሰቡ ይሆን?

እኔ እንደሚመስለኝለህዝቡ የሚበጅ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ የኤርትራ ሉኡካን ለመቀበል የሁሉም ክልሎች ባለ ስልጣናት በዙሪያቸው ኣሰልፈው ስነ ስርዓቱ ሕይወት እንደዘሩበት ሁሉ ለማንኛውም የለውጥ እንቅስቃሴኣቸውምበተዋረድ የሚገኙ ባለ ስልጣናት በማሳተፍና የባለቤትነት ስሜት ኣድርባቸው ድርሻቸውን በመወጣት የመደመሩ ፍልስፍና ከውስጥ ማጎልበት ግድ ይላል፡፡

በሌላ በኩልም የመደመር ምስጢር ወደ ራሳቸው የግል ፍላጎት በማዞር ኣልተደመርክም ፣ የቀን ጅብ ወዘተ በማለት የተለየ ሃሳብ እንዳይንሸራሸር ሰዎችን የማግለልና በዓይነ ቁራኛ የማየት ኣባዜ እየሰፋ ስለሆነ ዴሞክራስን አቀጭጮ ህዝቡን ዋጋ ወደ ሚያስከፍል ችግር ከመክተቱ  በፊት ፖለቲካዊ መፍትሄ ከሚሹ ዋናው ነው በማለት ሃሳቤን እደመድማሎህ፡፡

Back to Front Page