Back to Front Page


Share This Article!
Share
መርህ የተሳከረበት የኢህአዴግ መንደር

መርህ የተሳከረበት የኢህአዴግ መንደር

ከእውነቱ ይታያል 09-10-18

በተለያዩ ጊዚያት እንደሰማነው ኢህአዴግ አደረኩት ባለው 17 ቀናት የወሰደ "የጥልቅ ተሃድሶ" ግምገማ ከለያቸው ችግሮች አንዱ በግንባሩ ውስጥ መርህ አልባ ግንኙነትና አሰራር ሰፍኖ የነበረ መሆኑን ነው። ይህ አይነቱ ግንኙነት ደግሞ በሃገሪቱ ህገመንግስትም ይሁን በራሱ በኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት አሰራር በፀደቁ የድርጅት ፕሮግራምና ህገ-ደንብ ላይ የሰፈሩ መርሆዎችን የዘነጋ ወይም የጣሰ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ከፍም አለ ዝቅ ይህን መሰረታዊ ችግር ደፍሮ መለየቱና ለህዝብ መግለፁ አንድ ነገር ሆኖ አሁንስ በየድርጅቶቹ ያሉ ግንኙነቶች መርህን የተከተሉ ናቸው ወይ ብሎ መጠየቅ ደግሞ ከአንድ ነገሩ ያገባኛል ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ ነው። እንደ አለመታደል ሆነና አንዳንድ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት በግንባሩ ውስጥ ያለው ግንኙነት አሁንም መርህን መሰረት ያደረገ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻል አይመስለንም። በዚህ ረገድ እንደማሳያ የሚሆኑ የተወሰኑ ጉዳዮችን አንስቶ ማየቱ ጠቅሚ ነው።

Videos From Around The World

የመጀመሪያው ማሳያ ከዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ ጋ የተያያዘው ጉዳይ ነው። ይህ መርህ ኢህአዴግ ውስጥ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ቦታ የሚሰጠው ቁልፍ መርህ እንደሆነ ይታወቃል። በርግጥ ይህን መርህ እዚህ ላይ ማንሳት የተፈለገው መርሁ በይዘት ደረጃ ትክክል ነው ውይስ አይደለም በሚለው ጉዳይ ዙሪያ የመከራከሪያ ጭብጥ ለማስያዝ ሳይሆን መርሁ የተጣሰበት አግባብና ሂደት ስርዓትን የተከተለ ነበር ወይ የሚለውን ለማየት ነው። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የኢህአዴግ ህገ-ደንብ አካል ሊሆን የቻለው በጉባኤ ውሳኔ ነው። በመሆኑም በጉባኤው እስካልተሻረ ድረስ ሁሉም አባል ድርጅቶችና አባላቶቻቸው ሊገዙበት የሚገባ በቃልኪዳን ላይ የተመሰረተ መርህ ነው። አስፈላጊነቱ ባይታመንበት እንኳ ጉባኤው እስኪሽረው ድረስ መጣስ አልነበረበትም። ዴሞክራሲያዊ ማእክላዊነት ከሚያካትታቸው ቁምነግሮች አንዱ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ሰዎች በግንባሩም ይሁን በአባል ድርጅቶች የሚተላለፉ የጋራ የሆኑ ውሳኔዎችን ማክበርና የነዚህ ውሳኔዎች አፈፃፀም ሂደትም ይህንኑ የጋራ ሳኔ ባንፀባረቀ መንገድ መሆኑን ማረጋገጥ ነው።

እየታዘብን ያለነው ግን ሁኔታዎች በተቃራኒ መንገድ እየሄዱ ያሉ መሆኑን ነው። በዚህ ረገድ የዶ/ር አብይ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ምልክቶች ቸው። ለምሳሌ አሁን እየተደረገ ላለው ለውጥ መነሻው ኢህአዴግ ሳይሆን የራሳቸው ተነሳሽነትና በጎ ፈቃድ እንደሆነ አድርገው ለማሳየት እየተንቀሳቀሱ ያሉበት ሁኔታ በጣም ሰፊ ነው። በዚህም መሰረት የዴሞክራሲ ምህዳሩ እያሰፋ ያለው፣ እስረኞች እየተፈቱ ያሉትና ባጠቃላይም እየተካሄዱ ያሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች መነሻ የኢህአዴግ ውሳኔዎች ሳይሆኑ የራሳቸው የዶ/ር አብይ ውጤቶች እንደሆኑ አድርጎ በማቅረብ በህዝብ እየተወደዱ ይቀጥሉ ዘንድ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም። ከርሳቸው ውጭ ሌላ ላወድስ ብለው ካሰቡም የሚያወድሱት እርሳቸው የለውጥ አካል አድርገው ዘወትር የሚያነሱት በርሳቸውና በአቀንቅኞቻቸው አባባል የ"ቲም ለማ" ቡድን የሚባለውን ነው። አንዳንዴማ ይባስ ብለው ከኢህአዴግ እውቅና ውጭ በሆነ መንገድ እየመራኝ ያለው አቶ ለማ ነው ብለው ሲናገሩ አፋቸውን ሞልተው ነው። የሚገርመው የብአዴን ሰዎች ችግሩ እንዲስተካከል ከመጣር ይልቅ "አቤት ወዴት " እያሉ መሆናቸውን በሚያሳብቅ መንገድ የዶ/ር አብይን ስብእና በመገንባት ስራ ላይ የተጠመዱ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ኢህአዴግ ምን ያህል ከጋራ አሰራር መርህ ወጥቶ ወደ ግለሰብ አምላኪነት እየተቀየረ እንዳለ አመላካች ነው። ታዲያ ከዚህ ሌላ የመርህ ትርምስ የት ይገኛል?

ሁለተኛው ደግሞ ዶ/ር አብይ ወደስልጣን የመጡበት መንገድ ነው። በኢህአዴግ አሰራር መሰረት የኢህአዴግ ም/ቤት የግንባሩን ሊቀመንበር የሚመርጠው ብቃት አላቸው ተብለው ከሚታሰቡት ግለሰብ ተጠቋሚዎች መካከል ነው። በዚህ ሂደት የሚደረጉ የመደራጀትም ይሁን የመረባዊ ትሥሥር (Networking) እንቅስቃሴዎች በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው። ጥቆማው የሚከናወነው በግለስበ የኢህአዴግ ም/ቤት አባላት እንጅ በአባል ድርጅቶች ደረጃ ባለመሆኑ እነዚህ አባል ድርጅቶችም ቡድን ፈጥረውም ይሁን በተናጠል ምርጫው ላይ ተፀዕኖ ማሳደር አይፈቀድላቸውም። የኢህአዴግ መርህ፣ አሰራርና ባህል ይህ ሆኖ እያለ የኦህዴድ ሰዎች ግን አይን ባወጣ መንገድ ለስልጣን ራሳቸውን ስለውና ሞርደው የቀረቡበትን ሁኔታ አይተናል። ይባስ ብለውም የምርጫውን ሂደት ከእግር ኳስ የማጥቃትና የመከላከል አሰላለፍ ጋር አመሳሰሉት። በዚህ ሂደትም የብአዴን ሰዎች መርህ እንዲከበር ከመታገል ይልቅ ራሳቸውም መርህን ጥሰው ዋና ተዋናይ በመሆ የኦህዴድ ሰዎችን የስልጣን ጥም እንዲረካ አደረጉ። ይህም ታዲያ ሌላው የመርህ መሳከር ነው።

ሶስተኛው ማሳያ ዶ/ር አብይ ከሚያደርጓቸው የህገመንግስት መርሆዎች ጥሰቶች ጋ የተገናኘ ነው። ይህን በተመለከተ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል ግን ዶ/ር አብይ ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ባንዳንድ ክልሎች ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የተደረገውን ጣልቃ ገብነትና ትግራይ ውስጥም ፌዴራል ፖሊስን በመጠቀም የከሸፈ የጣልቃ ገብነት ሙከራን ማንሳት ይቻላል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አነሳስና የአልጄርስ ስምምነት አቀባበል ሂደቶች ዙሪያም ዶ/ር አብይ ህገመንግስቱን መጣሳቸው በተለያዩ መንገዶች ተገልፀዋል። በሌላም በኩል ፀጉረ ልውጥ፣ የቀን ጅቦችና የመሳሰሉ ኋላቀርና ያልሰለጠኑ ስሞችን በመለጠፍ ያንድ አከባቢ ማህበረሰብ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን በነፃ የመንቅሳቀስ ህገመንግስታዊ መብት ለመገደብ ጥረት እያደረጉ እንዳለም ብዙ ሰው የሚረዳው ይመስለናል። ከዚህ አልፎም አሁንም የአንድ አከባቢ ማህበረሰብ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሚያንኳስሱ እጅግ ፀረ ደሞክራሲያዊ የሆኑ ተግባራትን ሲፈፅሙ አይተናል። በዚህ ረገድ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው የነበሩ ያንድ አከባቢ ተወላጆች በተለይም ደግሞ አከብራቸዋለሁ የሚሏቸውን ሴት እህቶቻችን ጥያቄው የማን እንደሆነ እናቃለን እና የመሳሰሉ መልሶችን እየሰጡ በማጣጣል አንገታቸውን ለማስደፋት እንደሞከሩ አደባባይ የወጣ ምስጢር ነው። በዚህ ሁሉ ሂደት የብአዴን ሰዎች መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች እንዲስተካከሉ ትግል ከማድረግ ይልቅ ዶ/ር አብይ ህፀፅ የሌለባቸው ነብይ ተደርገው እንዲታዩ ነበር ጥረት ሲያደርጉ የነበረው። ከዚህ ውጭ ታዲያ ምን መርህ አልባነት አለ?

በአራተኛ ደረጃ እንደማሳያ ሊቆጠር የሚችለው ኢህአዴግ ውስጥ ታድሰናል የሚሉት ሃይሎች አልታደሱም የሚሏቸውን አመራሮች የሚያዩበት ሁኔታ ጋ የተዛመደ ነው። እነዚህ አልታደሱም የሚባሉ አመራሮች በዋናነት ደግሞ ነባሮቹ የራሳቸው በጎም ይሁን መጥፎ ተግባራት እንደፈፀሙ መካድ አይቻልም። እነሱ ተፅዕኖ ፈጣሪ በነበሩበት ወቅት ሃገር በመገንባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን በማጠናከር ረገድ የሰሯቸው በጎ ስራዎች የነበሩትን ያህል በርካታ እድሎች እንዳበላሹም የሚካድ አይደለም። በዚህም ምክንያት የስንት ንፁሃን ኢትዮጵያዊ ታጋዮች ትግል በተሟላ መንገድ ፍሬ እንዳያፈራ የበኩላቸውን አሉታዊ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ያም ሆኖ ግን እነዚሁ አመራሮች አልታደሱም ቢባሉም እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጎች የራሳቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ይሁን ማህበራዊ ሃሳቦች ማራመድ እንዳይችሉ ገደብ ሊጣልባቸው አይገባም። ሕግና ስርዓትን እስካከበሩ ድረስ እንደማንኛውም ኢትዮያዊ በነፃ የመንቀሳቀስ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል። አይደለም እነዚህ አልታደሱም ተብለው የተፈረጁ የኢህአዴግ አመራሮችና ሌሎች አባላት ቀርቶ በግልፅ ወንጀል ፈፅመው አገር ለቀው የነበሩ፣ ስንትና ስንት ሽህ ህዝብ ያላግባብ የጨፈጨፉና ንብረት ያወደሙ የደርግ ባለስልጣናትና አጋፋሪወቻቸው እንኳን ምንም ይቅርታ ሳይጠይቁ እንደፈለጉ እንዲሆኑ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል። በእርግጥ ተላልፈውት የነበረ ህግ ካለ የህግ ስርዓትን በመከተል ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው። እንደሌሎቹ ተጠርጣሪዎችና ጥፋተኞችም በቅርቡ በፀደቀው የይቅርታና የምህረት ህግ መሰረት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ከሆነም በዚሁ አግባብ ሊስተናገዱ ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን በጅምላ አንገታቸውን እንዲደፉና መፈናፈኛ እንዲያጡ ማድረግ ህገ-ህገመንግስታዊ መርሆዎችን ይጥሳል ብቻም ሳይሆን የሞራል ዋጋም ሊያሳጣ የሚችል ተግባር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

አምስተኛው ማሳያ የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች ህወሓትን እየገፉ ያሉበት ሁኔታ ነው። ከመነሻው ህወሃት ከኦህዴድና ከብአዴን ብሎም ከደኢህዴን የተለየ ፕሮግራም የለውም። የሁሉም ድርጅቶች ፕሮግራሞች ካርቦን ኮፒ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ይህ ከሆነ ታዲያ ኦህዴድና ብአዴን ለምን ህወሓትን እንደድርጅት መግፋት አስፈለጋቸው ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው። ህወሃት እንደድርጅትም ሆነ አመራሩና አባላቱ እንደግለሰብ የፈጠሩት ችግር ካለ በግንባሩ መርሆዎችና ሀገደንብ መሰረት መፍትሄ ሊፈለግላቸው ይገባል። ከዚህ አልፎም በህግ ተጠያቂ የሚሆን ሰውም ሆነ አካል ካለ ህጋዊ ስነ-ስራቶችን ተከትሎ ህግ ፊት ማቅረብ ተቀባይነት ያለው አሰራር ነው። ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ ግን ከመርህ ያፈነገጠና ፈር የሳተ መንገድ ነው የሚሆነው።

እነዚህ መርህ እየጣሱና ፈር እየሳቱ ያሉት ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች ናቸው። አሁን ላይ የነዚህ የሁለቱ ድርጅቶች ሰዎች በዋነኛነት የሚያስጨንቃቸው ህገመንግስታዊና ድርጅታዊ መርሆዎች ሳይሆኑ የህዝበኝነት ሱስ እንደሆነ ለመረዳት ከባድ አይደለም። ። በነሱ እምነት ህወሓት የሚባል ድርጅት በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠልቷል የሚል አመለካከት እንዳሳደሩ ከእንቅስቃሴያቸው መረዳት ይቻላል። አሁንም በነሱ እምነት ከንደዚህ አይነት ድርጅት ጋ መቀጠል ደግሞ የክብርም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዋጋ ያስከፍለናል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። ከዚህ ባሻገርም ህወሓት ጥያቄ ያነሳባቸው ግን ደግሞ ኦህዴድ በፅናት እያራመዳቸው ያሉ የኦሮሚያ በአዲስ አበባ አለው የሚባለው የተለየ ጥቅምና ኦሮምኛን የፌዴራል መንግስት ቋንቋ የማድረግ ፍላጎት ለህወሓት መገፋት አይነተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው መገንዘብ ከባድ አይሆንም። ከዚህ ባለፈም ኦህዴድና ብአዴን መርህ ላይ ያልተመሰረተ ቡድን ፈጥረው ትግራይ ውስጥ ህወሃትን ተክቶ የኢህአዴግ አባል ወይም አጋር የሚሆን አሻንጉሊት ፓርቲ እንዲፈጠር ለመንቀሳቀስ አያስቡም ማለት አይቻልም።

ከላይ የተገለፀውን ጉዳይ በተመለከተ አንድ ተጨባጭ ነገር እናንሳ። ይሄውም በቅርቡ ከትህዴን (TPDM) ጋ ለመደራደር በጀኔራል አደም ሞሃመድ የተመራ የልኡካን ቡድን አስመራ ሄዶ የነበረ መሆኑን ያስታዉሷል። በዚሁ ድርድር ላይ አቶ ተፈራ ደርበውንም ያየናቸው ይመስላናል። በሌላ በኩል ኦነግ (OLF) ጋ ለመደራደር አስመራ ሄደው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ነበሩ። ከአማራው ተቃዋሚ ጋ ለመደራደር አስመራ ገብተው የነበሩትም እነ አቶ ንጉሱ ናቸው። ይህ ከሆነ ታዲያ ከትህዴን ጋ ለመደራደርስ ዶ/ር ደብረጽዮን ወይም የርሳቸው ወኪሎች ለምን አስመራ አልሄዱም? መቸም ከትህዴን (TPDM) ጋ ለመደራደር የብአዴን ሰዎች አስመራ የሄዱት ህወሓት ውስጥ ለድርድር ብቁ የሆነ ሰው ጠፍቶ ነው የሚል የጅል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል ብለን አናስብም። ሌላ የተደበቀ አጀንዳ እንዳይኖር መስጋት ግን የሚጠበቅ ነው። በዚህም አለ በዚያ ይህ አይነት የቡድነኝነት አካሄድ በኢህአዴግ መርሆዎች የተወገዘ ተግባር ነው።

ሌላው ማሳያ ደግሞ ኢህአዴግ አሰላለፉ የት እንዳለ የጠፋበት ሁኔታ ላይ ያለ መሆኑ ነው። አሁን ያለው የኢህአደግ ረዕዮተ-ዓለም (Ideology) አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይሁን ሶሻል ዴሞክራሲ ወይም ለዘብተኛ ዴሞክራሲ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። በሌላ በኩል ኢህአዴግ ውግንናው ከማን ጋ እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ የሆነ ወቅት ተደርሷል። ባጠቃላይ ኢህአዴግ ራሱ አሉኝ በሚላቸው ህዝባዊ መርህዎቹ ላይ ግራ ተጋብቶ ሌላውንም ግራ እያጋባ ይገኛል። ለዚህም ይመስላል ከመርሆዎቹ ማፈንገጥ ብች ሳይሆን ከነዚህ መርሆዎች በተቃራኒ የቆሙ ግለሰቦችና ሃይሎች፣ የማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች ፅንፈኛ የመገናኛ ዘዴዎች በሚያቀነቅኗቸው ሃሳቦች እየነጎደና እየተመራ ያለው። በዚህም ምክንያት ገና ከመነሻው የስርዓቱ አደጋዎች ናቸው ተብለው የተለዩት ትምክህትና ጠባብነት እግር አውጥተው እየተራመዱ ክንፍ አውጥተው እየበረሩ ኢህአዴግን ከወዲያ ወዲህ እያላጉት ይገኛሉ። በዚህ ዙሪያ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል። እንደሚታወቀው ሁሉም የተለያየ ሃሳብ የሚያራምዱ ግለሰቦችም ይሁኑ ሃይሎች ሃገር ውስጥ ገብተው በነፃ እንዲንቀሳቀሱ በተደረገው ጥሪ መሰረት በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች አገር ውስጥ ገብተዋል። ይህ ድርጊት የዴሞክራሲውን ምህዳር በማስፋት ህዝቦች የተለያዩ አማራጮች እንዲኖሯቸው ስለሚያደርግ በጣም የሚበረታታ እርምጃ ነው። ከዚህ አልፎ ግን የኢህአዴግ ከፍተኛ የሰራ ሃላፊዎች ባንድ ወገን ትምክህት በሌላ ወገን ደግሞ ጠባብነት በነገሰባቸው ያቀባበል ስንስርዓቶች እየተገኙ ትምክህትና ጠባብነት ለሚያቀነቅኑት ሰዎች ወርቅና የመኪና ቁልፍ ማስረከብ ብሎም ካባ መደረብ የኢህአዴግን መርህ ይጥሳል። እነዚህና መሰል ድርጊቶች የሚያሳዩት ደግሞ ኢህአዴግ በስሜት በሚነዳው ሃይል እየተጎተተ እንደሆነ ነው። ይህ ደግሞ ራሱን ኢህአዴግን ከመሪነት ጎዳና አውጥቶ ተመሪ የሚያደርገው አሳፋሪ ተግባር ነው። እነዚህ የስራ ሃላፊዎች ይህን የሚያደርጉት ህዝቡን በመምሰል ስህተቶችን ለመታገል ነው እንዳይሉ አንድም የማረሚያና የማስተካከያ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልታዩም፡ እንዲያውም ያየናቸው ሲያጨበጭቡና ሲያሽቃብጡ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ የመርህ መተራመስ ከወዴት ይመጣል?

የውግንና ጉዳይ ሲነሳ አንድ ነገር ታወሰን። ይሄውም በኦህዴድና በብአዴን ሰዎች የሚዘወረው ቡድን ከኢህአዴግ መርህ የወጣ በሚመስል መንገድ የዴሞክራሲ ፅንሰ-ሃሳብ እሬት እሬት ከሚላቸውና የአለም መጨረሻው ገንዘብና በሱ የሚሸመቱ ቁሳቁሶች ከሚመስላቸው እንደ ሳኡዲ አረቢያ፣ አረብ ኢመሪቶችና በተለይም ደግሞ በሻእቢያ ከሚመራው የኤርትራ መንግስት ጋ የያዘው ሸብ ረብ ያለ ግንኙነት ነው። ምክንያቱም ከነሰሜን ኮሪያ ተርታ የሚመደበው አምባገነኑ የኤርትራ መንግስት እንኳን ለኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ጥቅም ሊቆም ለራሱ ህዝብ እንኳን ከጠላት በላይ ጠላት የሆነ ሃይል እንደሆነ አለም ያወቀው ሃቅ ስለሆ ነው። አንዳንዴማ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አቶ ኤሳያስ የታላቅ ወንድም አማካሪየ ነው ሲሉም ይደመጣሉ፤ ድንቄም አማካሪ። አቶ ኤሳያስ ያማክራሉ እንኳን ቢባል ሊቸሯቸው የሚፈቅዱት ምክረ-ሃሳቦች ኢትዮጵያን ወደገደል የሚያስገቡና የኢትዮጵያ ስም አለም ካርታ ላይ እንዲጠፋ በሚያደርግ መንገድ ሊሆን እንደሚችል በርግጠኛነት መናገር ይቻላል። በአቶ ኤሳያስ ፍላጎት ቢሆን ኖር ኢትዮጵያ የምትባል አገር ተበታትናና ሃይሏ ተዳክሞ እርሳቸው የምስራቅ ብሎም የመላው አፍሪካ ሃያል መሪ ሆነው መገኘት ነው።

ይህን የሸብ ረብ ግንኙነት እጅግ በጣም የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ህወሃትንና የትግራይን ህዝብ ያገለለ በሚመስል መንገድ እየተከናወነ ያለ መሆኑ ነው፤ ትሻልን ሰድጀ ትብስን እንዲሉ ይነት ነገር።ይህ መንገድ የማያዛልቅና የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል የጥፋት መንገድ ነው። በመሆኑም ከላይ ከተገለፁት መንግስታት ባጠቃልይና በተለይ ደግሞ ከኤርትራ መንግስት ጋ የሚደረግ ግንኙነት በመሰረቱ የሚደገፍ ቢሆንም አጀማመሩ ግን በጣም አስጊ ስለሆነ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ጥቅም ሳይሸራርፍ መሆን እንደሚገባው ፅኑ እምነት ሊያዝበት ይገባል።

ተጠቃሎ ሲታይ ኢህአዴግ ባሁኑ ወቅት የመርህ መሳከር ገጥሞት እየተወላገደ ያለ ግንባር ሆኗል። ይህ በመሆኑ ደግሞ የተለያዩ ሃይሎች ፍላጎት ተገዥ የመሆን ዝንባሌ እያሳየ መጥቷል። ለዚህም ነው አንዱ ተነስቶ እኔ ሁለተኛ መንግስት ነኝና እኔ ያልኩትን ካልፈፀምክ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት አውጥቸ ጎዳና ላይ እጥልሃለሁ ሲለው እሱኑ ሰምቶ የተባለውን ለመፈፀም ደፋ ቀና ሲል የሚታየው። በሌላ ወገን ሌላው ተነስቶ "አንድ ህዝብ አንድ ኢትዮጵያ" ብሎ ሲውረገረግ አጃቢና አሸርጋጅ በመሆን ታዛዥነቱን ባደባባይ እያስመሰከረ ይገኛል። ኢህአዴግ በተለይም ኦህዴድና ብአዴን ይህን በማድረጋቸው ህዝባዊነትን በተላበሰ መንገድ እየመራን ነው ብለው እያሰቡ እንደሆነ ለመገንዘብ ከባድ አይሆንም። እውነታው ግን የዚህ አይነት ፓርቲ እየተመራ እንጅ እየመራ አለመሆኑ ነው። አንድ ፓርቲ መሪ ነው ሊባል የሚችለው ህዝቡ መረጠውም አልመረጠውም ለህዝቡ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሃሳቦች በፕሮግራም ደረጃ ቀርፆ መያዙና እሱንም ህዝብ ሊገዛው እንዲችል ማድረጉ ነው። ከዚህ ውጭ ህዝብ ምን ሊፈልግ ይችላል እያሉ በህዝብ ስሜት መነዳትና አደናግሮ ድጋፍ ለመሰብሰብ መንቀሳቀስ የግል ጥቅምን ማሳደድ እንጅ የህዝብ ግንባር ቀደም መሪ ፓርቲ ሊያደርግ አይችልም። ለዚህም ነው ኢህአዴግ በቅርቡ ሊያካሂደው ባቀደው ጉባኤው ላይ ውስጥ ለውስጥ የሚያደርገውን ቡድናዊ መናቆር አስወግዶና የተሳከሩትን መርሆዎች አስተካክሎ መሪነቱን የሚያረጋግጥ ግንባር ሆኖ መውጣት የሚጠበቅበት።

 

መልካም ዘመን!

Back to Front Page