Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጥላቻ የሚሸነፍበት ኢሬቻ

ጥላቻ የሚሸነፍበት ኢሬቻ

ይቤ አብርሃ ከውቤ በረሃ 10-01-18

 

ኦሮሞ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ካሉት ብሄሮች መካከል ሠፊውን የኢትዮጵያ የያዘ ማኅበረሰብ ነው።ከኩሽ ነገዶች ውስጥ የሚካተተው ኦሮሞ ከአፍሮ እስያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይመደባል።የኦሮሞ ብሔር በትውፊት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ በባህላዊው የገዳ አመራር ሥርዓት ሲተዳደርና ሲገለገል ቆይቷል። በገዳ ሥርዓት መሠረት መሪ ወይም አባ ገዳ ሆኖ የሚመረጠው ሰው በሥልጣን ላይ መቆየት የሚችለው ለስምንት ዓመታት ብቻ ነው።

Videos From Around The World

ተመራጩ የሰምንት ዓመት አመራሩ ሲያበቃ በባህሉ መሠረት ለቀጣዩ ተመራጭ መሪ ወይም አባ ገዳ ሥልጣኑን ያስረክባል።ይህም በሠለጠነው ዓለም ዲሞክራሲ ከመታሰቡ በፊት ኦሮሞ በገዳ ሥርዓት አመራሩን መርጦ ሲተዳደር እንደነበር የሚያሳይ ነው።ይህ ጥንታዊ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ከኢትዮጵያ የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ተመዝግቧል።

የያዝነው ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ከተከበረ በኋላ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ግርግር ተነስቶ የተወሰኑ ሰዎች ሕይወታቸው ቢያልፍ ገሚሶቹ ደግሞ ንብረታቸው ቢዘረፍም የፀጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት ርምጃ ችግሩን ለመቆጣጠር ተችሏል።

በዚህም ምክንያት እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ብዙ ህዝብ ተሰብስቦ የደመራን በዓል በሰላም ለማክበር ችሏል። በገጠር በዓሉን ማክበር የፈለጉ ብሔር ብሔረሰቦች ያለምንም ፀጥታ ችግርና ግርግር እንደ ባህላቸው የመስቀል በዓላቸውን ከከተሞች ወደ የቤተሰቦቻቸው አገር ቤት ሄደው አክብረዋል። ለዚህም ህዝቡና የፀጥታ አካላት የተጫወቱት ሚና ሊጎለብት የሚገባው ነው።

በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው እሁድ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሞዎች ዘንድ በጉጉትና በናፍቆት የሚጠበቀው የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በሰላምና በድምቀት ተከብሯል።ኢሬቻ ለፍቅርና ለአንድነት በሚል መሪቃል በተከበረው በዓል ላይ የሲዳማ ብሔር እና የጋሞ ብሔረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች፣ እንዲሁም የሃዲያና የኮንሶን ጨምሮ ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች በኢሬቻው የምስጋና በዓል ላይ ታዳሚ ነበሩ ።ወደ ሃምሳ የሚደርሱ ሙሽሮች በበዓሉ ላይ ተገኝተው ጋብቻቸውን ፈፅመዋል።

የመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማትም ከበዓሉ ቀደም ብሎ መስከረም 18 ተካሂዷል። በዚህም አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፣ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወአባ ማትያስ፣ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ፣ በኪነጥበብ ዘርፍ ድምፃዊ ዐሊ ቢራ እና ሙሐሙድ አህመድ፣ እንዲሁም ሰዐሊ ለማ ጉያ ተሸላሚዎች ነበሩ።በተጨማሪም የቢርመጂ ቱለማ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ሥልጣነ ገዳቸውን አጠናቀው ለአዲሱ የሜልባ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ሆሪሶ አስረክበዋል።

ይህም ከላይ ያነሳናቸው ጉዳዮች ኢሬቻ ለፍቅርና ለአንድነት በሚል መሪ ቃል መከበሩ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር የታየበት ልዩ ሆኖ ሊከበር የቻለበት በዓል ነው ማለት ይቻላል።

በቢሾፍቱ በየዓመቱ ክረምት ከወጣ በኋላ የሚከበረው ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አካልና የምሰጋናና የሰላም ቀን ነው።ከክረምቱ ጨለማ ወደ ፀደይ ብርሃናማ ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ነው። በኦሮሞ ባህል መሠረት ኢሬቻ ሲከበር ፀብና ጥላቻ ተወግዶ እርቅና ፍቅር የሚመሰረትበት ስለሆነ ጥላቻ የሚሸነፍበት ኢሬቻ ያሰኘውም ይህ በጎ አከባበሩ ነው።ባህሉም አብሮነት መሆኑን ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በተግባር በኢሬቻ በዓል ላይ ተገኝተው የመሠከሩት ሀቅ ነው።

ሀገራችን በለውጥ ጎዳና መግቧቷ ፣ የኦሮሞ ህዝብ ሲጠይቅ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦት እልባት ማግኘቱ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል።የጥምቀት ከተራ እና የአሸንዳ ጭፈራ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርትና የሳይንስና የባህል ድርጅት ቀደም ሲል በጊዚያዊነት የተመዘገቡ ሲሆን ተመሳሳይ መልኩ ኢሬቻን ለማስመዝገብ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። የኢሬቻ በዓልም የበዓሉን ትውፊት በሚያከብር ሰላም፣ ውበትና ድምቀት ባለው መልኩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በታደሙበት ሁኔታ ተከብሯል።ለዚህም የሰላምና ፀጥታ አስከባሪዎች በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

የሀገራችንን ባህል ለማስተዋወቅ ኢትዮጵያ ካላት ዕምቅ ሀብት አንፃር በማስተዋወቁና የቱሪስት መስህብ በመፍጠሩ ረገድ ብዙ ይቀረናል። ያልሠራናቸው ብዙ ባህላዊ ሥራዎችና ሀብቶች አሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል በተወሰነ መልኩ የአሸንዳ በዓልን ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ ለማሳየት ጥረት ተደርጓል።ጅምሩ ጥሩ ነው።በተለያዩ ቦታዎች ባህላዊ አከባበሮችን በማሳየት መቀጠል አለበት እንጂ በዋና መዲናዋ ብቻ መገታት የለበትም።

ከአረፋ በኋላ በትግራይ አል ነጃሺ መስጊድ የሚከበረው አሹራ፣የመስቀል ደመራ፣የጥምቀት ከተራ የመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸውን በዓላት ጨምሮ እንደ ኢሬቻ ያሉ ባህላዊ በዓላት ዜጎቻችን ይበልጥ ሊያቀራርቡ የሚችሉ የመደመር መንፈስ የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ልንከባከባቸው ይገባል።

 

 

Back to Front Page