Back to Front Page


Share This Article!
Share
ኦሮምያ/ኤርትራ ልገንጠል ሲል የለም! አይሆንም! ትግራይ ልገንጠል ሲል እሰይ! እልም!( የግዛት አንድነት ትርክትና የትምክህተኝነት ቁርኝት)

ኦሮምያ/ኤርትራ ልገንጠል ሲል የለም! አይሆንም! ትግራይ ልገንጠል ሲል እሰይ! እልም!

( የግዛት አንድነት ትርክትና የትምክህተኝነት ቁርኝት)

 

አ/ገ

ታህሳስ 2018

 

ሰሞኑን ከትግራይ አክቲቪስቶች ጠንከር ብሎ የህ.ወ.ሃ.ት ን ከ ኢ.ህ.አ.ዲ.ግ አባል ድርጅትነት ራሱን እንዲያገልል የክልሉም መንግስት አንቀጽ 39ን በመጥቀስ የራሱን ዕድል በራሱ እሰከ መገንጠል የሚለውን መብቱን እንዲጠቀም ውተወታ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ማህበራዊ ሚድያው ላይ ሰፊ መሰረት ያለው የግዛት አንድነት አቀንቃኝ ማህበረሰብ ለዚህ እየሰጠ ያለው መልስ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ መንገድ ከኢትዪጵያ የተለየችውን ኤርትራን እና እሰከ ቅርብ ግዜ ድረስ ጥያቄ አድርጎ ያነሳ የነበረውን ኦሮሚያ ክልል ሲያነሱት የነበረው አይነት ጠንካራ ተቃውሞ ሳይሆን ይሁን ይደረግ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትግራይ ራሱዋን አትችልም፤ ትግራይ ለም መሬት ለያም ወደብ የላትም የሚል ነው፡፡ ኤርትራ አትገነጠልም ተብሎ ደም የፈሰሰበት ምክንያት በዋናነት በእርግጥ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዪጵያ መለየት የለበትም፣ ወገናችን ነው ተብሎ ሳይሆን፣ የባህር በር ያሳጣናል ከሚል መፍቀሬ ወደብ አስተሳሰብ የመነጨ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ኦሮሚያ ልገንጠል ያለች እንደሆነ አገር የሚተራመሰው በርግጥ ኦሮሞ ኢትዪጵያዊ ነው፣ ወገናችን ነው፣ ተብሎ ሳይሆን ሰፊና ለም መሬቱን ላለማጣት ነው፡፡

Videos From Around The World

የመገንጠል ጥያቄ ተራው የትግራይ ሲሆን ማጀቢያው እሰየው፣ ሂዱ፣ እልም በሉ፣ ድሮስ ምን ነበራችሁ፣ ምን አመጣችሁ፣ ሃሳባችሁን እንዳትቀይሩ የሚል ክብረ ነክና አሸማቃቂ ንግግሮች በሰፊው ይስተዋላሉ፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ትምክህትና የግዛት አንድነት አመለካከቶች ተወራራሽ ናቸው የሚያስብለው፡፡ ኢትዪጵያ የምትባለው ሃገር ጸንታ መኖር የምትችለው ህዝቦችዋ ተገቢውን ሰብዓዊ ክብር ያገኙባት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ለህዝቦች ክብር ደንታ የሌለውን ለም መሬትና የባህር በር/ወደብን ከህዝብ የሚያስቀድም የ አንድነት ትርክት ውጤቱ ብቻ መቅረት ነው፡፡

ኤርትራ፤ ያመለጠ ዕድል

አጼ ሃይለስላሴ ለኤርትራ ህዝብ ተገቢውን ክብር ሰጥተውና በትዕግስት ጠብቀው ቢሆን ኖሩ ዛሬ ታሪኩ ሌላ ይሆን ነበር፡፡ በሃይል ፌዴረሽኑን አፍርሰው ያቀላቀሉዋት ኤርትራ ኋላም ደርግ ቀይ ባህር ድንበራችን ነው በሚል ከህዝብ ክብር ቁሳቁስን ባስቀደመ ፍልስፍና የተሄደበት መንገድ ውጤቱ ኤርትራን ማጣት ሆኖ ተደምድሟል፡፡ ዛሬም ድረስ ኤርትራ ሲነሳ አንድ ህዝብ ነን፣ የምንጋራው በርካታ ስነልቦና አለን ከሚለው ይልቅ የባህር በር ባለቤትነትን መልሶ ማግኝት የሚል ስለሚቀድም ለኤርትራውያን እልክና ጥንካሬን ይጨምርባቸዋል፡፡ የግዛት አንድነት ወይም የትምክህት አስተሳሰብ አራማጆች ዛሬም ከስህተት አይማሩም፡፡ ምንም እንኳን ዛሬ ኤርትራውያን የመሪያቸው በደል አንገፍግፎአቸው ወደ ኢትዪጵያ በስደት ቢመጡም መሪያቸውን እንጁ ዜግነታቸውን የመለወጥ ፍላጎት ከቶውንም አላሳዩም፡፡ እውነቱን ለመናገር ኤርትራውያንን ሊያግባባ የሚችል የህዝብን ክብር ያስቀደመ ገዢና አሳማኝ የማግባቢያ ሃሳብ ማፍለቅ አልተቻለም፡፡ ስለሆነም ሁለት አገርነታችን ይቀጥላል፡፡ የትምክህት/ የግዛት አንድነት አቀንቃኝ ከዚህ የቅርብ ግዜ ታሪክ ምንም ትምህርት መውሰድ አለመቻላቸው ትምክህት የማይድን በሽታ ነው እንድንል ያስገድደናል፡፡

ኦሮሚያ፤ የተሳካ ዕድል

የኦሮሞ ህዝብ ለነጻ ሃገርነት መታገል ሲጀምር እድሜው ከ ህ.ወ.ሃ.ት ም ይረዝማል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ትግል የተጀመረው ኦሮሞ በኢትዪጵያ ውስጥ ሁለተኛ ዜጋ ነው፤ በብሄራዊ ማንነቱ አፍሮና ተሸማቆ ነው የሚኖረው፣ ባለ ሰፊና ለም መሬት ባለቤት ሆኖ ግን የበይ ተመልካች ነው በሚል ትርክት ነው፡፡ ይህ ትርክት በፌደራል ስርዓቱ ተስፋ ማድረግ በመቻሉ ቀስ በቀስ እየከሰመ ሄዶ ዛሬ በፌደራላዊት ኢትዪጵያ ውስጥ መኖር የሚችል ሃሳብ ሆኖ ተቀይሮአል፡፡ ይህ በትክክል የፌደራል ስርዓቱ ስኬት ማሳያ ነው፡፡ እንደ ግዛት አንድነት አቀንቃኞች ቢሆን ኖሮ የኦሮሚያም ዕጣ ልክ እንደ ኤርትራ ሆኖ ይጠናቀቅ ነበር፡፡ የግዛት አንድነት ትርክት ኤርትራን ሲያሳጣን የህዝቦችን ክብር ያሰቀደመው የፌደራሊሰት ትርክት ግን ኦሮሚያን ከመገንጠል አትርፎኣታል፡፡ ዛሬ ኦሮሞ በኢትዪጵያ ውስጥ ክብር አግኝቼ መኖር እችላለው መገንጠል አያስፈልገኝም ማለት የቻለው በፊደራል ስርዓቱ ተስፋ በማድረጉ እንጂ እንደ ግዛት አንድነት አቀንቃኞ ሃሳብ ቢሆን ውጤቱ ሌላ ይሆን ነበር፡፡ ኦሮሚያ አትገነጥልም የሚሉ ሃይሎች መነሻቸው አብረን መኖር እንችላለን፤ የተከፋችሁበትን ነገር እንወቅና እናርማለን፤ የጋራ እሴቶች አሉን፤ የጋራ ታሪክ አለን የሚል ሳይሆን ለምና ሰፊ መሬት ሊሄድብን ነው ቅርጻችን ሊያንስብን ነው የሚል ነው፡፡ ለህዝብ ክብር ያለሰጠ አካሄድ መጨረሻው ክስረት ነው፡፡ የግዛት አንድነት አቀንቃኞች የሚፈልጉትን ነገር በሚያገኙበት ሳይሆን በሚያጡበት መንገድ ውስጥ መሰለፋቸውን አያስተውሉትም፡፡ ኤርትራን ፈልገው ግን በሚያጡበት መንገድ ይሄዳሉ ደግሞም አጣናት፤ ኦሮሚያንም እንዲሁ ከማድረግ የፌደራል ስርዓቱ ታድጎናል፡፡

 

ትግራይ፤ ያልለየለት ፈተና

 

ዛሬ ተራው የትግራይ ነው፡፡ ፈተናው በትግራይ በኩል መጥቶእል፡፡ የትግራይ ህዝብ በህ.ወ.ሃ.ት መሪነት ከማንም በላይ ግን ደግሞ ከሌሎች ኢትዪጵያውያን ወገኖች ጋር በመሆን አስከፊውን የደርግ ስርዓት ገርስሶ በመጣል የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተ፤ ህ.ወ.ሃ.ት ደግሞ ከቅንና ሃገር ወዳድ ህዝቦች ጋር በመሆን ሃገሪቱና ባለፈው 27 አመት ከነድክመቶችም ቢሆን በኢኮኖሚ፣ በመሰረተ ልማት፣ በዲፕሎማሲና በጸጥታ መልካም ስምን ያጎናጸፋት ሆኖ ሲያበቃ ዛሬ አብረው በነበሩ መራሮች ክህደት ሊባል በሚችል መንገድ ለውጥ እየተሰበከ የትግራይ ህዝብ ክብር እየተዋረደ፤ ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድና ግምገማ በማካሄድ 27ቱ አመት ጨለማ፤ የችግሮች ሁሉ እናት ወያኔ፣ ትግራዋይ ሁሉ ሌባ የሚል ክብረ ነክ ዘመቻ በመንግስት ሚዲያና በጠ/ሚ ጠብ ጫሪ ንግግሮች እየተቀናበረ ሲካሄድበት አይቶ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ቢቃወምም ችግሩ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ትግራዋይ አንቀጽ 39ን መጠቃቀስ ጀምሮአል፡፡ የግዛት አንድነት ፊት አውራሪዎች ግብረ መልስም ልክ እንደከዚህ በፊቱ የህዝብን ክብር ሳይሆን መሬትና ቁሳቅስ ተኮር ነው፡፡ ቁልቋላም፣ የድንጋይ ሃገር፣ ምን ኣላችሁ፣ ጥርግ በሉ፤ በሚል ንቀት የተሞላ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ይህን አንዴት እንደሚያልፈው ወደፊት የምናየው ሆኖ ከዚህ በፊት የታዩት ልምዶችን በማየት ግን ትግራይ የኤርትራን መንገድ የምትሄድ ሳያደርጋት አይቀርም፡፡ ምክንያቱን አሁን በስልጣን ላይ ያለው ሃይል አሃዳዊ የግዛት አንድነት ቅኝት ያለው ስለሆነና የትግራይ ህዝብ ደግሞ በብሄራዊ ማንነቱ ተሸማቆ መኖርን የማይቀበል በመሆኑ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ በህ.ወ.ሃ.ት መሪነት ለነጻነት ታግሎ በከፈለው መስዋዕትነት ምክንያትና የፊደራል ስርዓቱ መስራችና ጠባቂ እንደመሆኑ መጠና የራሱን ሃገር የመመስረት የሞራልም ሆነ የህግ ልዕልና አለው፡፡

 

 

Back to Front Page