Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሺ ሰማንያ፡ ጉዞ ወደ ኤሪትርያ

ሺ ሰማንያ፡ ጉዞ ወደ ኤሪትርያ

ዶ/ር ዮሃንስ አበራ አየለ (ተ.ፕሮ)  11-16-18

ኤሪትርያን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት በ 1964 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነበር፤ አምሳ ዓመት ያህል መሆኑ ነው። በዛ ወቅት ኤሪትርያ በወገን ክህደት፣ በየአይነቱ የባእድ አገዛዝ፣ ወገናዊ በሆነ ንጉሳዊ የዘር ሃረግ አገዛዝ፣ እንዲሁም ህዝብን እርጋታ በሚነሱ ወታደራዊ ዘመቻዎች፡ አሰሳዎችና ወከባዎች ውስጧ የጓጎለ ቢሆንም ላይዋ ግን እያረረች የምትስቅ ያገር የባህር ማሽላ ነበረች። ከተሞችዋ ያሸበረቁና ህይወት ያላቸው ነበሩ። ህዝቡ ሲሰራ እንደ ንብ ሲዝናና እንደ እምቦሳ ነበር። ይህንን አንፃራዊ ብርሃን ችግርን ሁሉ በጉልበት ብቻ ለመፍታት ሲሞክር የነበረው ደርግ አንድያውን ድቅድቅ ጨለማ አደረግው።  በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆች ተቀጥረው ሲሰሩባቸው የነበሩትን እንደነ ቃኘው ጣብያ በመዝጋት፣ የጣልያኖች ማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን በመውረስ፣ በንግድ ሥራ የተሰማሩትን አረቦች እንዲለቁ ምክንያት በመሆን፣ ንጉሡ በካሮትና-ዱላ ስልት ሲያስተናግዱ የቆዩትን የህዝቡ ቅሬታ ወፍራም ዱላ ብቻ ይዞ ገባበት። ኢትዮጵያን ከልብ ሲያገለግሉ የነበሩትን እንደነ ጄኔራል ኣማን ዓንዶም የመስሳስሉ ምርጥ የኤሪትርያ ተወላጆችን በመግደልና  ኤሪትርያውያን ከኢትዮጵያ ጋር መቆየታቸው በውድ ሳይሆን በግድ መሆኑን በይፋ አሳወቀ። ዮኒቨርሲቲ የነበሩት የኤሪትርያ ተወላጅ ተማሪዎች በሳታየ አውቶቡሶች ተሳፍረው ከአዲስ አበባ ወደ ኤሪትርያ በርሃዎች ፈሰሱ። ምእተዓመት ለሚያክል ዘመን የሰከነ ህይወት ኖረው የማያውቁት የኤሪትርያ ህዝቦች ለከፋ የሰቆቃ ህይወት ተዳረጉ። መንደሮቻቸው ተቃጠሉ፣ ህዝቡ ተሰደደ በመላ አለም ተስራጨ፣ አቅም ያለው ብረት ጨበጠና ተዋደቀ፣ ቤተሰብ ተበተነ ስደት ባህል ሆነ። ደርግ በኤሪትርያውያን አይምሮ ላይ ሲጫወት የነበረው መረብ ማዶ ካሉት ዘመዶቻቸው ጋር የማናከስ ስራ ነበር፤ የትግራይ ተወላጆችን በስለላ ሥራ ላይ እያሰማራ። የባሰው ግን  ኤሪትርያውያን ቢደሰቱበት እንጂ ሊጠሉት ከቶ የማችሉትን ከውጭ ወራሪዎች ጋር ሲፋለሙ የስልጣን ዘመናቸውን በቤተመንግስት ሳይሆን በጦር ሜዳ ያሳለፉትን አፄ ዮሃንስና ራስ አሉላን ስም እያሞጋገሰና ሃውልት እየሰራ ከደርግ ጋር ተመሳሳይ አላማ የነበራቸው በማስመሰል ኤሪትርያውያን በትግራይ ህዝብና በመሪዎቹ ላይ ቂም እንዲቋጥር ተደርጓል። ከፌደሬሽኑ በፊትም ቢሆን ከኢትዮጽጵያ ጋር እንዋሃድ በሚለውና የተለያዩ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሲቀሰቅስ በነበረው የአንድነት ቡድን ውስጥ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ሰርገው እንዲገቡ ሲደረግ እንደነበረ ይወራል። በቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩት የኤሪትርያ ተወላጆች የነፃነት ትግላችንን ያከሸፉት ትግራዮች ናቸው የሚል ቁጭት ሲያስተናግዱ አልፎ አልፎ ከትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ጋር ግጭት ይፈጥሩ ነበር። ታሪክ ያሳየው ግን የዚህ ስሜት ተቃራኒ ነበር። ለኤሪትርያውያን ነፃነት በግምባር ቀደምትነት ጠበቃ ሆነው የቆሙት ትግራዮች ነበሩ። የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ የኤሪትርያውያንን የነፃነት ፍላጎትን የተቃወመበት ዘመን የለም፤ ለቅኝ አገዛዝ ባርነት ተላልፈው ሲሰጡም ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶታል። አሁንም ድረስ የማናከሱ ጥረት ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል። ለዚህም ኤሪትርያውያንና መሪዎቻቸው በስሜትና በአጭር ጊዜ እይታ ዘላቂ ዝምድናውን ባያባክኑት ይመረጣል።

Videos From Around The World

ጉዞየን የጀመርኩት ከአዲስ አበባ በልጅ ልጄ ታጅቤ ነበር። በአባይ ባስ የተጓዝነው የዓፈር ክልልን አቋርጦ በሚያልፈው የመቐለ መንገድ ነበር። በህግ አገር ህግና ዳኛ የጠፋበትና እንደ ጀግንነት እየተቆጠረ ባለው የአውራ መንገዶች መዝጋት ምክንያት በመደበኛው መስመር መኬድ ባለመቻሉ ነበር አማራጭ መንገዱ የተጀመረው። ጀግንነትና የወገን ፍቅር እንጂ ውንብድና የማይነካው የዓፈር ህዝብ ግን ጉዞውን እጅግ ሰላማዊ እንዲሆን አድርጎታል። መንገዱ አመቺ ከመሆኑ የተነሳ የአውሮፕላን እንጂ የመሬት ላይ ጉዞ አይመስልም። መንገዱ ከወሎው መስመር የረዘመ ቢሆንም በተመሳሳይ ወይም በተሻለ ሰዓት ይደረሳል። እንደ የዋህ የእለቱን ፓለቲካ እንጂ እንደብልጥ የአመቱን ኢኮኖሚ ያላየው መንገድ ዘጊና አዝማቾቹ ከተመላላሽ መኪኖች የሚገኘው ጥቅም ማስቀረታቸው ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ ሰላም በሌለበት የሚመጣው ቱሪስትና ኢንቬስተር ሳይሆን የጦርነት ዜና ዘጋቢ ብቻ መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው።

የዓፈር መሬት ውበቱና ብዝሃነቱ በጣም አስደናቂ ነው። ብሄራዊ ፓርኮች እንዲሁም የማርስና የጨረቃ ገፀ-መሬት የሚመስሉ አካባቢዎች ለሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልም አዘጋጆች አመቺ እንደሆኑ አሰብኩ። ክልሉ ከሆሊውድ ጋር ቢደራደርስ ብየም ተመኘሁ። በዛ ተፈጥሯዊ ሳውና ባዝ የእንግዳ ማረፍያ ቤቶች በብዛት ቢሰሩ የብርድ በሽታና የጡንቻ መተሳሰር ችግር ያለባቸው ሰዎች እዛው ሄደው በመሰንበት ፈውስ ሊያገኙ ይችላሉ። ከአስራ ሦስት ሰዓታት ጉዞ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ኮከብ ከሆነችውና በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከነበረችው መቐለ ደረስን።

"መኣዝ ክውድኦ እቱ ቅርንብ ዓይና ኩሒለ ስኢለ፣ መአዝ ከርክበሉ ሽምጢ አካላታ ዳንጋአ ኾሊለ፤

እታ ኦሪታዊት ነዊሕ መበቆላ፣ ተባሃጊ ላዛ መቐለ ወለላ፤ አለኹ ንበላ" ድምፃዊ ዳንኤል ዘርኡ

ይቺ ከተማ የትግራይ ብሄራዊ ክልል መናገሻ ስትሆን ከኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ለመሆን ስንዝር ነው የቀራት ይላሉ። እድገትዋ ግን ከውሃ አቅርቦት ጋር ባለመመጣጠኑ እንዲህ የሚል ዘፈን ተዘፍኖባታል፦ አይትፀወግለ፣ ከይርስዐኪ ከም ማይ መቐለ። ከፊል በርሃማነት የሚያመዝንበት፣ በላይም-አለት ስነምድር የተሸፈነውና ንፋስ የሚጠነክርበት መቐለና አካባቢው የገፀምድር ሆነ የከርሰምድር የውሃ ሃብቱ ውስን ነው። የህዝቡ የውሃ አጠቃቀም ባህሉ ግን ከእጥረቱ ጋር አራምባና ቆቦ ነው። ውሃው ሳምንት ቆይቶ ሲገኝም ቁጠባ የሚባል ነገር የለም። ሁሉም መኖር የሚፈልገው ልክ እንደ ባህርዳርና ሃዋሳ ህዝብ ውሃ እየተራጨ ነው። ሰኣኒኻ ክንዲ እግርኻ የሚባል የትግርኛ አባባል አለ። የጫማህን ቁጥር በእግርህ ልክ አድርግ እንደማለት ነው። መልእክቱ ጫማህ ከእግርህ ከበለጠ አረማመድህ ተወላግዶ መንገድ ላይ ልትወድቅ ትችላለህ ነው። ድሮ የነበረውና ማይ-ዚንጎ ሲባል የነበረው ከቤት ጣርያ የዝናብ ውሃ አጠራቅሞ የመጠቀም ልማድም የተረሳ ይመስላል።

ሌላው መቐለ ውስጥ ያስተዋልነው ክስተት ድምበር በመከፈቱ ከኤሪትርያ ወደ ከተማዋ የጎረፈው የህዝብና የመኪና ብዛት ነው። ኢአር የሚል ሰሌዳ የለጠፉ መኪናዎች በየመንገዱ ቆመው ይታያሉ። የመቐለ ህዝብ ገበያውን እየተሻሙ መሆኑንና ሌሎች አገልግሎቶች መጨናነቃቸው እየተሰማውም ቢሆን በደስታ ተቀብሎ እያስተናገዳቸው ነው። ከግማሽ ምእተ-አመት በላይ መሪዎቹን በቅኝ ገዢነት ሲፈርጁበት፣ የኤሪትርያን ነፃነትና የኢኮኖሚ እድገት ማየት የማይፈልግ የመረረ ጠላት አድርገው ሲቆጥሩት፣ ውሃ በቀጠነ ጣታቸውን ትግራይ ህዝብ ላይ እየቀሰሩ ሲወነጅሉት፣ የደርግ ሰላዮች ነበራችሁ በማለት ከሰውነት ውጪ አድርገው ከኤሪትርያ ምድር ሲጠራርጉት፣ ለራሳቸውም ቢሆን ጎጂ እንጂ ጠቃሚ ሊሆኑ ከማይችሉት ሃይሎች ጋር በማበር ደህነቱና ክብሩን ለአደጋ ሲያጋልጡ፣ አስመራ ላይ ያለው መንግስት የዓይደር ት/ቤት ህፃናት ላይ ቦምብ በማዝነብ የመቐለን እናቶች ማቅ ያስለበሰውን ድርጊት በድጋፍም በዝምታም ሲያልፉት፣ እንዲሁም በቅኝ መገዛት የሰብአዊ ክብር መገሰስ መሆኑን ዘንግተው የትግራይን ህዝብ አሳንሶ ለማየት ሲጠቀሙበት የትግራይ ህዝብ ዘላለማዊ ቂም ሊቋጥር ከቶ ግድ ይለው ነበር። ሆኖም ግን ኤሪትርያውያን ወንድሞቹና እህቶቹን በታላቅ ትእግስትና አርቆ አሳቢነት ከመንጋው እንደጠፋ በግ ቆጥሮ የክፉ ቀን መጠለያ ሆናቸው። አሁን ለትውልድ የሚዘልቅ ትምህርት ወስደዋል ብሎ ማሰብ ይቻላል። የትግራይ ህዝብ በዚህም በዛም እየተዋከበም ቢሆን ራሱን ችሎ ኤሪትርያውያንንም  ለማስተናገድ የሚችልበት አቅም ባይገነባ ኖሮ የዛ ሁሉ የሰው ጎርፍ ማረፍያው የት ይሆን ነበር?

ወደ አስመራ ለመጓዝ ንጋት ላይ መቐለ መናሃርያ ደረስን። መደበኛ ትራንስፓርት ስላልተጀመረ አስመራ! አስመራ! እያሉ የሚጠሩት የሚኒባስ ረዳት የሆኑ የመቐለ ልጆች ናቸው። ለነሱ አዲስ የእንጀራ መስመር የተከፈተላቸው ይመስላል። ሰላም የማያስገኘው ጥቅም አለን? ከመቐለ አስመራ 300 ኪ.ሜ. ሲሆን ከአዲስ አበባ-መቐለ ድረስ ያለው 780 ኪ.ሜ. መንገድ ሲደመር 1080 ይሆናል፡፡ ክፍያው በብር 350 ነው። ውድ ነው አይባልም። አንድ ሺ ብር ቢሉስ ማን ይቀራል? መንገዳችን መስፍን ኢንጅነሪንግን በቀኝ መሶቦ ስሚንቶን በግራ በኩል አልፈን የመሶቦ ሰንስለታማ ኮረብታ ዳገታማ መንገድ ተያያዝነው። ማይ መኽደን፣ አጉላዕ እያልን አነስተኛ ከተሞችን ስንቆጥር በተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ቁጥቋጦና ሳር የለበሰውን መሬትም በአግራሞት እያስተዋልነው ነበር። ውቕሮ ከተማን አቋርጠን ስናልፍ ከጎኔ የተቀመጡት አንዲት ኤሪትርያዊት እናት ይህ ከተማ ምነው አላልቅ አለ ብለው ሲጠይቁኝ  እኔም ባልናገረውም ሲሰማኝ የነበረ ስሜት ነበረና እኔንም አስገርሞኛል ብየ መለስኩላቸው። እንዲህ እያልን ህይወት የሚያድስ የአየር ፀባይ ያላትና ትግራይ ውስጥ ከመቐለ ቀጥላ ትልቅ ከተማ ከሆነችው ዓድግራት ደረስን።

"ሑመራ ነይረ ክምለስ ዓድግራት፣ አስመራ ነይረ ክምለስ ዓድግራት፤ ከመዓልኩም ደቅዓደይ ምዓራት " 

ዓድግራት ዓጋመ የሚባል እንደ ጉራጌዎች በንግድ ስራ የተካነና ከአካባቢው ርቆ በሚሄድበት ቦታ ሁሉ በጥረቱ የሚከብር ህዝብ ማእከል ናት። ተቀምጦ እንጂ ጥሮ ግሮ መክበር የማይሆንላቸው ሰዎች ክቡር የሆነውን ዓጋሜነትና ጉራጌነትን እንደስድብ ቃል ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ለኤሪትርያ ድንበር የቀረበችው ትልቋ የኢትዮጵያ ከተማ የሆነችው ዓድግራት ከድንበሩ መከፈት የላቀ ጥቅም ታገኛለች ተብሎ ይገመታል። ዓድግራት ቁምሳ ለመብላት ወረድን። ዋናው አላማ ግን ሌላ ነበር፤ ብርን ወደ ናቅፋ መቀየር። ብር ወደ ናቅፋ የሚቀየረው በመደበኛ ሳይሆን በየመንገዱ በነፃነት በሚዘዋወሩ ግለስብ ባንኮች ነው። ውድድር የለ ድርድር የለ በተባልከው ሂሳብ መቀየር ነው። ናቅፋ የብር እጥፍ ያህል ዋጋ ይኖረዋል የሚል ጥርጣሬ ግን አልነበረኝም። ለአንድ ናቅፋ ብር 1.84 ሂሳብ ከፍየ ኪሴን በግማሽ አጎደልኩ። ኤሪትርያ ውስጥ ያለው የምግብ ዋጋ ጋር ሲሰላ ኪሴ ከመጉደል አልፎ ባዶ ሊሆን መቃረቡን ሳይ ከኤቲኤም ተጨማሪ ብር አውጥቼ ለመቀየር ተገድጃለሁ። የልውውጡ ሥርአትና ተመን ጉዳይ ግን አሁን ካለው መልካም ስሜት ባሻገር ቢታሰብበት ብየ ለመንግስታቱ እተዋለሁ።

ዛላአምበሳ ስንደርስ ምንም እንኳ ብዙ የእድሳት ጥረቶች ያሉ ቢሆንም የጦርነት ጠባሳዎች ግን በግልፅ መታየታቸው አልቀረም። በሰላም መነጋገር ሳይሳነው የሰው ልጅ ወንድሙ ላይ ሰይፍ ማንሳት ለምን እንደሚቀናው በዘመናት ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ቸኩሎ ይተላለቅና ከጊዜ በኋላ በማይመልሰው ክፉ ድርጊቱ በፀፀት ሲቃጠል ይገኛል። ዛላምበሳን አልፈን ኤሪትርያ መዳረሻ ላይ እነዛ ምሽጎች በከፊል ፈራርሰው ይታያሉ። እዚህ ላይ ነበር የኤሪትርያ ድንበር ጠባቂ ጦር አባላትን ያገኘነው። መክሳታቸውና መጎሳቆላቸውን ሳይ እምባየ ዱብ ዱብ ሊል ትንሽ ቀርቶት ነበር። ሁላችንም ከሚኒባሳችን ወርደን እልፍ ብለው ወደተተከሉት ድንኳኖች እንድናመራ ተጠየቅን። ድንኳኖቹ ውስጥ ለኢትዮጵያውያንና ለኤሪትርያውያን ለየብቻ የተዘጋጁ ባህር-መዝገቦች ላይ መታወቂያ እያሳየን ተመዘገብን። አጥብቆ መጠየቅ የለ፤ ፍተሻ የለ፣ ከአክብሮት ጋር ያልከውን  መመዝገብ ብቻ! ይህ ቀላል የሆነ የድንበር ማቋረጥ እድል ለጊዜው ቢመቸኝም ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለብኝና ውስጤን ረበሸው፤ ሁለቱን አገሮች መጉዳት የሚፈልጉ ክፉ ሰዎች ይህን ነፃነት ቢጠቀሙትስ ብየ ጉዞየን ቀጠልኩ።

ከኬላው ጀምሮ ሰንዓፈ፣ ዓድቀይሕና ደቀምሓሪ የተባሉ የኤሪትርያ ከተሞችን እያገናኘ የሚያልፈው የአስመራ መንገድ ብልሽት መኪናችን ደንገላሳ እንዲረግጥ አስገድዶት ነበር።  በመንገዱ መነኳኮር የተበጣጠሰው ወገባችን አይናችን ባየው ተጠግኗል። ግራና ቀኝ የሚታዩት ሜዳና ኮረብታዎች በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ለምለም ለብሰው ይታያሉ። እዚሁ ብቻ ሳይሆን በቀጣዮቹ ቀናት ወደ መንደፈራና ባፅዕ (ምፅዋ) ስንጓዝ በተለይ ምንጉዳ የሚባለው ረዥም ጠመዝማዛ መንገድ የሚያቋርጠው ተፋሰስ፣ እንዲሁም ዓርበ-ረቡዕ የሚባለው ከፍተኛ ተዳፋትነት ያለው ወደ ምፅዋ መውረጃ ገደላማ ተፋሰስ ችፍግ ብለው የበቀሉት እፀዋት የኤሪትርያን ከበሳ (ደጋ) ምድር ግርማ ሞገስ አጎናፅፈውታል።  ከሰሃራ-ሳሕል በርሃ ጋር የአፍና አፍንጫ ያህል የሚቀራረበው የኤሪትርያ ከበሳ በዚህ ሁኔታ ላይ መገኘቱ አስተማማኝ እንዲሆን ያደርገዋል። ለሰይጣን የስሙን ሳይሆን የእጁን ስጠው የሚለው አባባል እዚህ ላይ አስፈላጊ ነው። የህግደፍ አመራር ያለው የመልካም አስተዳደርና የሰብአዊ መብት ሬኮርድ ጥሩ አይደለም ሲባል ጨርሶ ምንም እንዳልሠራ መቁጠር ጥሩ ባህል አይደለም። ጥቁር የሚቀባውን ጥቁር እየቀባን ነጭ ሆኖ መቆየት ያለበትንም እንዳለ እየተውን መሄድ ተገቢ ነው። በመንግስት ሥራ በተለያየ የሃላፊነት እርከን ላይ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ቅን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውም ተመሳሳይ ነው። አገሪቱ የደረሰችበት ደረጃ ሰው የለፋበት ሳይሆን ከሰማይ ተምዘግዝጎ ወርዶ ኢትዮጵያ ላይ ያረፈ መና ይመስል ይህን እውን ለማድረግ የታገሉትንም፡ የታገሉለትን አላማና የሰማእታቱን አደራ ቅርጥፍ አድርገው የበሉትንም አንድ ላይ ጨፍልቆ ሁላችሁንም ሲኦል ይዋጣችሁ ብሎ ማለት ተገቢ አይደለም። ፈጣሪያችን ከሰማይ የተበላሹት ብቻ እንጂ ሁሉንም መላእክት ወደ ምድር እንዳልውረወረ መፅሃፉ ግልፅ ያደርጋል።

አስመራ ስንደርስ መኪናችን ሰተት ብሎ ወደ ዕዳጋ ሓሙስ አልሄደም። በከተማዋ የደቡብ ዳርቻ ላይ የሚገኘው ጎዳይፍ ተብሎ ከሚጠራው ሰፈር ነበር የጉዟችን መጨረሻ የሆነው። ቢጫ ታክሲዎች ተኮልኩለው ወደሚጠብቁበት ቦታ በመሄድ የአስመራ ልጆች "ሹቕ" ብለው ወደሚጠሩት የከተማዋ እምብርት ጉዟችንን ተያያዝነው።

"ጓል አስመራይ፣ ጓል አስመራይ፣ ጓል አስመራይ መአረይ ሽኮሪናየ" ድምፃዊ አያሌው መስፍን።

ኮምቢሽታቶ እየተባለ ወደሚታወቀው ትልቁ ጎዳና ስንገሰግስ የከተማዋን በርካታ ሰፈሮች የመመልከት እድል አገኘን። በመንገዳችን ላይ የህንፃዎቹንና የመንገዶቹ ሁኔታ ስንመለከት፣ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በከተማው ውስጥ ስንዘዋወር የታዘብነው ነገር አይምሮን የሚነካ ነበር። ከተማዋ በ1960ዎቹ የተነሳና በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት የጠቆረና ቀለሙ በከፊል የለቀቀ ፎቶግራፍ ትመስላለች። ጨቋኝ ነው ሲባል የነበረው ንጉሣዊ አገዛዝ ዘመን እንኳ ስታብረቀርቅ የነበረችው አስመራ ከነህዝቧ ሱባኤ የገባች እንጂ በነፃነት ጥማት ተቃጥላ 30 አመት የጦርነት አውድማ ሆና የራስዋን እድል በራስዋ የመወሰን እድል ካገኘች እንኳና 27 አንድ አመት የቆየችም አትመስልም። ይህ ሁኔታ እንደ መንደፈራ፣ ደቀምሓረ፣ ዓድቀይህ፣ ባፅዕ (ምፅዋ)፣ ሰንዓፈ የመሳስሉት ሌሎች አነስተኛና መካከለኛ ከተሞችን ይመለከታል።

"ተላብዮምኻ ኢሎም ሓደራ፣ ወርቂ ክትለብስ ዓባይ ኤሪትራ" ድምፃዊ ወዲ ትኹል

የተፈጠረው ችግር ምን እንደሆነ አልገባኝም። አስመራ የዩኔስኮ ቅርስ ስለሆነች አትነካም ያሉኝም አሉ። የዩኔስኮ ቅርስ መሆን ማለት ይህ ከሆነ ባፍንጫየ ይውጣ። እኛ ዘንድስ ለዩኔስኮ ሲባል መስቀል ወደ ካርኒብቫል ተቀይሮ፣ አሸንዳ እንደ አውደ ጥናት በባለስልጣን ንግግር እየተከፈተ የግብታዊነት ጣእሙን አጥቶ የለ? ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚስቅ የለ፣ ህፃናት መንገድ ላይ አይሯሯጡ፣ ወጣት ሴቶች ፋሽን ለብስውና ፀጉር አክለው መንገድ ላይ አይታዩ፣ ብቻ ባጠቃላይ ቀዝቃዛ ህብረተሰብ ሆኗል።  በክፍለሃገር ትራንስፓርት አቅርቦት በኩል ያለው ሁኔታ የሞባይል ቻርጀር ያላቸውና መቀመጫ ወንበራቸው ለቀናት ቢቀመጡበት የማይጎረብጠው፣ ወርፋ ሳያስፈልግ በባንክ ቲኬት የሚቆረጥባቸው ምቹ ባሶች ካሉበት አገር ወደ ኤሪትርያ የተጓዘ ሰው አስቸጋሪ እንደሚሆንበት አያጠያይቅም። አውቶቡሶቹ ሁሉም ማለት ይቻላል የእድሜ ባለፀጋዎች መሆናቸውን ለማወቅ የኦርቢስ ምርመራ አያስፈልጋቸውም። ከ50 አመት በፊት በጎንደርና በደሴ መስመሮች ከአስመራ አዲስ አበባ ህዝብ ሲያመላልሱ የነበሩት "ሳታየ" አውቶቡሶች አሁንም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አንዱን አውቶቡስ ዕዳጋ ሐሙስ መናሃርያ ውስጥ በማየት አረጋግጫለሁ።

አስመራ ከተማ አየርዋ ጤናማ የሆነ ደጋማ ስፍራ ናት። ወቅቱ የዝናብ ወቅት ነው። ከእስያ ወደ ደቡባዊ አፍሪካ አቅጣጫ የሚነፍሰው መደበኛ አህጉራዊ ንፋስ ከቀይ ባህር መጠነኛ የሆነ እርጥበት በማንሳት ለኤሪትርያ ደጋማ አካባቢዎች ዝናብ ይሰጣል። በህንፃዎቹና በጎዳናዎቹ ማርጀት ብንከፋም የአስመራ ፅዳትና የህዝቡ ዲሲፕሊን መንፈሳዊ ቅናት ያጭራል። በአዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች የሚታየው የማሽከርከር፣ የማህበራዊ ግንኙነት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርአት አልበኝነት ጋር ሲያስተያዩት አገርን እስከመጥላት የሚያደርስ መጥፎ ስሜት ይፈጥራል። ይህ የአስመራ ህዝብ ዲሲፕሊን መሠረታዊና ውስጣዊ መሆኑን ስላስተዋልኩ የፓለቲካ አመራሩ ተፅእኖ የፈጠረው ነው ብየ ለማሰብ ተቸግሬአለሁ። የፓለቲካ አመራሩ ጫና የፈጠረው ቢሆንም መቸም ከዲምክራቲክ ሥርአት አልበኝነት መቶ እጅ ይሻላል። አስመራ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ከተሞችም እንኳን የተከመረ የወደቀ አነስተኛ ቆሻሻም ለአይን አይታይም። አትክልት ተራው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችም ጭምር ከጥሩ የአትክልትና ፍራፍሬ መዓዛ በስተቀር አፍንጫን የሚሰረስር ክርፋት የላቸውም። አስመራን ጨመሮ ባየናቸው ከተሞች ሁሉ ፌስታል የሚባለ ነገር የለም፡፡ የሚጠቀሙት ካኪ ወረቀትና የማዳበርያ ዘምቢል ነው፡፡ ፅዳት መጠበቅ ድሮም ቢሆን የህዝቡ አኩሪ ባህል መሆኑን ስለማውቅ ባየሁት ብዙም አልተደነቅሁም።

አስመራን እንዲህ ጎርጉሬ ካየኋት በኋላ ቀጣዩ ጉዞየ ወደ መንደፈራ ሠራየ ሆነ። መንደፈራ ከአስመራ 50 ኪ.ሜ. ያህል ርቀት ላይ በደቡብ ምእራብ አቅጣጫ ወደ ዓድዋ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ የምትገኝ መካከለኛ ከተማ ናት። ዓዲ ውግሪ የሚል ሌላ ስምም አላት። ወደዚች ከተማ ያመራሁት በንጉሱ ዘመን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩባትና "ማትሪክ በጥሼ" ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዮኒቨርሲቲ የገባሁባት ባለ ውለታየ የሆነችውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ት/ቤት (ሳን ጂዮርጂዮ)ን ለመጎብኘት ነበር። ከአስመራ ስንወጣ ውብና ስፋት ያለውን የሰምበል ሜዳ እያየና እያደነቅን ነበር። የአስመራን አውሮፕላን ማረፍያ በቀኝ በኩል እያለፍን የዘንድሮን ጥሩ አዝመራ የሚያመለክቱ የሰብል ክምሮች እያየን ወደ መንደፈራ አቀናን። በመንገዳችን ላይ የምትገኘውን ጥንታዊትዋን የድባሩባ ከተማንም አይተን አለፍን። መንደፈራ ከተማ ለመድረስ 5 ኪ.ሜ. ያህል ሲቀረን አይናችንን የሳበውን መዝናኛ ስፍራ ለመጎብኘት ከአውቶቡሱ ወረድን። የመዝናኛ ስፍራውን የሚያስተዳድሩት ጠንካራ ግን በእድሜ ገፋ ያሉ ሰው ናቸው። አብረውን እንዲቀመጡ ከጋበዝኳቸው በኋላ ብዙ ነገር አወጋን። ደርግ ስልጣን እንደያዘ ወድያውኑ ህዝባዊ ግንባርን የተቀላቀሉ ነባር ተጋዳላይ መሆናቸውን አጫወቱኝ። በ1983 አዲስ አበባ ድረስ መሄዳቸውንም ነግረውኛል። የባህርዳር ፓሊቴክኒክ የቅየሳ ምሩቅ የሆኑት እኒህ ሰው ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ባሉበት የመቐለ መሰቦን መንገድ እንደቀየሱ ሲነግሩኝ ልዑሉን በታታሪነታቸውና በትህትናቸው እያደነቁ ነበር። በንጉሱ ዘመን በደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ በተሰሩ መንገዶች ላይ እንደተሳተፉም አውግተውኛል። የባድመው ጦርነት ጭራሽ መሞከር እንዳልነበረበት በአፅንኦት ሲናገሩ የሰጡኝ ምክንያት አዲስ አበባ እያሉ የሰሙት፣ ያስደነገጣቸውና ያበሳጫቸው ነገር ጋር የተያያዘ መሆኑ ነበር። ነገሩ ለኔ አዲስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አሳማኝነትም ነበረው። የትግራይ ህዝብ በራሱ ላይ የተሸረበውን ሴራ ግምባር ቀደም አስፈፃሚ ሆኖ መገኘቱ ሰውየውን ግራ አጋብቷቸዋል።

ነባር ታጋዩ አዛውንት ኤሪትርያዊ በነገሩኝ ነገር እየተገረምኩ ወደ ሳን ጂዮርጂዮ ት/ቤት አቀናሁ። የት/ቤቱ ርእሰ መምህርና አስተዳዳሪው በደስታ ተቀብለው አስተናገዱኝ። ት/ቤቱ እንደ ተውኩት ነው ያገኘሁት። ካስቀመጡት የሚገኝ ወዳጅና ገንዘብ ሲሆን ደስ ይላል። ለልማት ወሳኝ የሆነ መሠረተ ልማት ግን ለአስርት አመታት ያህል ደንዝዞ ሲቆይ ልብ ይሰብራል። ይህ ት/ቤት በሺዎች የሚቆጠሩና በያሉበት አገር ከፍተኛ የልማት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ሊቃውንት የፈሩበት ነው። ትምህርት ቤቱን ለማደስና ለማሟላት ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም። ይህ ነው አንዱና ዋነኛው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርያ መንገድ። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አላማ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላቂ መሆን አለበት። ዘላቂነት ከወደፊት ትውልድ ጋር የተያያዘ ነው። የወደፊት ትውልድ ማለት ደግሞ አሁን ት/ቤት ውስጥ ያሉት የወደፊት አገር መሪዎች ናቸው። እነሱ ላይ ትኩረትና ቅድሚያ ሰጥቶ የተሰራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በአለት እንደተሰራ ግምብ ይሆናል። በመላ ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ የሚገኙ ት/ቤቶችና ዮኒቨርሲቲዎች በተቀነባበረ መንገድ የመፃህፍት፣የትምህርት ቁሳቁስ፣ በእረፍት ጊዜ እዛው ድረስ ሄዶ በማስተማር፣ በጋራ የምርምርና ስልጠና ስራዎች በመስራት ለግንኙነቱ ጠንካራ መሠረት መጣል ይቻላል። በርግጥ ለዚህ በጎ ተግባር የመንግስታቱ በጎ ፈቃድ ወሳኝ ሚና አለው። አሁን አየሩን የሞላው ስሜታዊ የፓለቲካ ዲስኩር፣ ታሪክን እያስተካከሉ ወይንም እያዛቡ ማቅረብ፣ የዘፈንና የኮንሰርት ጋጋታ፤ የከፍተኛ የስልጣን አካላት መጎበኘኛኘትና ሞቅ ያለ መወዳጀት አጭርና ውሽንፍራም ዝናብ ያመጣው ጎርፍ ሆኖ እንዳይቀር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እንዲህ ያለን አጋጣሚ ተጨባጭ በሆኑ፣ ግልፅነት ባልጎደላቸው፣ ህዝብንና መሬትን በነኩ እርምጃዎች መደገፍ አለባቸው። ከላይ ብቻ የሚሠራው ስራ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ የታየና አስደስቶ ያስለቀሰ ነው።

"ሹም ንሹም ይኳለሱ፡ ድኻ ንድኻ ይላቐሱ" የትግርኛ አባባል  (ሹምና ሹም ሲጎራረሱ፤ ድሃና ድሃ ይላቀሱ)

 

አስመራ ተመልሰን ካደርን በኋላ በማግስቱ ከአስመራ 100 ኪ.ሜ. ያህል ወደምትርቀው ባፅዕ (ምፅዋ) ተጓዝን። በ100 ኪ.ሜ. ርቀት ከባህር ጠለል 2300 ሜትር ከፍታ ካላት አስመራ ከባህር ጠለል 5 ሜትር ብቻ ከፍታ ወዳላት ምፅዋ መውረድ ማለት 7500 ጫማ ከፍታ ላይ ከሚበር አውሮፕላን በፓራሹት የመውረድ ያህል ነው። ይህን አደገኛ አወራረድ የሚያስተናግደው መንገድ ግን ሰፊ፣ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል አስፋልት የለበሰ ምቹ መንገድ ነው። በዚህ መንገድ አዘውትሮ መመላለስ ያስመኛል። የመንገዱ ስፋትና ልስላሴ ብቻ አይደለም አስደሳች የሆነው፣ የአካባቢው ልምላሜና በዚህ ልምላሜ ላይ ጣል ጣል የተደረጉ ፈርጦች የሚመስሉት የነፋሲት፣ የእምባትካላና የጊንዳዕ የከተማ ቤቶችም ጭምር ናቸው። በዚህ መንገድ ላይ ያየኋቸው የትራፊክ አገልግሎት ሰጪ ትልቅ ክብ ኮንቬክስ መስተዋቶች የኤሪትሪያውያን የፈጠራ ችሎታ ህያው ምስክሮች ናቸው። እነዚህ መስተዋቶች ጠመዝማዛው መንገድ ተጀምሮ እስከሚያበቃበት ያለው ረዥም መንገድ በየመታጠፍያው ላይ የተተከሉ ናቸው። ቁልቁለት ወራጅ መኪና ወደቀኝ ሲታጠፍ ዳገት ወጪ መኪና ወደ ግራ ሲታጠፍ ስለማይተያዩ ግጭት ይፈጠር ነበር። መታጠፍያው ዳር ላይ ተማክሎ የተተከለው መስተዋት ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡት መኪኖች ፊት ለፊት እንዲተያዩ ይረዳቸዋል። ከተረጋጋ አነዳዳቸው ላይ ተጨምሮ ህይወት የሚታደግ ቴክኖሎጂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እነዚህን በጣም ውድ የሚመስሉ መስተዋቶች የሚነካ ሰው የለም። ከቴክኖሎጂ ሃርድዌር ጋር የሰው ባህርይ (ሶፍትዌር)ሲገጣጠም አገር ያድጋል ይገሰግሳል። ከዘመድና ከስራ ጋር የሚያገናኘው የቴሌ ገመድ እየተበጣጠሰ በሚወሰድበት ህብረተሰብ ውስጥ ስልጣኔ በቀላሉ ይደላደላል ብሎ ማሰብ ከባድ ሥራ ነው። ለይህ ነው እንጂ እነዚህ መስተዋቶች ሊማሊሞ፣ ግራ ካሕሱ፣ ደንገጎ፣ ሃረጎ፣ አላጀ፣ አባይ ሸለቆ፣ ጣርማ በር፣ ምጉላት፣ ጣራ ገዳም፣ አለም ሳጋ ላይ ቢተከሉ የስንት ሰው ነፍስ ከየቤትዋ ታድር ነበር።

ወደ ምፅዋ ስንቃረብ የአካባቢው ሰዎች "ዶጎሊ" ብለው የሚጠሩትና በኢትዮጵያውያን ዘንድ "ዶጓዓሊ" ወይም "ዶጋሊ" በሚል ስም የሚታወቀው ስፍራ ደረስን። ይህ ስፍራ የእንግሊዝ መንግስት በአፄ ዮሃንስ ላይ ክህደት በመፈፀም ከማህዲስቶች ጋር አጣልቶ የጣልያን ጦር ምፅዋ ላይ ካሰፈረባቸው በኋላ ወደር አልባው ራስ ኣሉላ የጣልያንን ጦር ያሸነፉበት ግንባር ነው። ይህ ድል ከአድዋ በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ መንግስት አፍሪካ ውስጥ የተዋረደበት አኩሪ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ኤሪትርያውያንም ሊኮሩበት የሚገባ ድል በተቃራኒው የሚያዝኑበት ሆኖ ማየቴ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። በጤነኛ አይምሮ ቅኝ ሊገዛው የመጣን ሃይል  ወገኑ የሆነ ጦር ሞቶና ቆስሎ ጠላቱን ቢያባርርለት ባለውለታ እንጂ ጠላት ይሆናል? በዚህ ስፍራ ወደላይ ሾጠጥ ብላ በወጣች ኮረብታ አናት ላይ ረዥም አንቴና የሚመስል ሃውልት አለ። "መቓብር ጥልያን" ነው አለኝ ከጎኔ የተቀመጠው ተሳፋሪ። ለ 30 ዓመት ትግልና መስዋእትነት አንድ ድንጋይ እንኳ ሳይቆምለት ምነው? ብየ በሆዴ አጉረመረምኩ። ይህን አሳቤን ሳልጨርስ ሃወልቱን ተጠግተው የኢጣልያና የኤሪትርያ ባንዴራዎች ጎን ለጎን ሲውለበለቡ አየሁ። ይህ አስደማሚ ድርጊት ቅኝ አገዛዝን አምርሮ ለተዋጋው የታዳጊው አለም ህዝብ ምን አይነት መልእክት ሊያስተላልፍ እንደሚችል የኤሪትርያ ህዝብ በቅጡ ተገንዝቦት ይሆን? ብየ ራሴን ጠየቅሁ። መቸም ቅኝ አገዛዝ ለኤሪትርያውያን ብቻ መልካም የሚሆንበት ምክንያት አይኖርም። ኤሪትርያውያን 30 ዓመት ሙሉ በዱር በገደሉ የተዋደቁት ከኢትዮጵያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አልነበር? ቅኝ ገዢን ለመውደድና ለመጥላት የቆዳው ቀለም ወሳኝ የሚሆንበት መመዘኛ አለ ይሆን?   ራስ ኣሉላ ተመሳሳይ ሥራ ሰርተው ባንዱ ወንጀለኛ በሌላኛው ጀግና የሆኑበት ስሌትስ ከየት የተወሰደ ነው? ዶጋሊ ላይ ያሸነፉት የጣልያን ወራሪዎችን ነበር፤ አድዋ ላይም እንዲሁ። የዶጋሊ ድል ወንጀል ሲሆንባቸውና ሲወገዙበት በአድዋ ድል ግን ስማቸው በወርቅ ቀለም ተፅፏል። በዚህ አካሄድ አንድ ሰው ጀግና ወይንም ወንጀለኛ የሚሆነው ማንን ወጋ ሳይሆን ከየትኛው ንጉስ ስር ሆኖ ነው የወጋ በሚል ተገምግሞ መሆኑ ነው። ታሪክ በሰው ሳይሆን በራሱ እጅ ራሱን የሚፅፍ ቢሆን አለም የተሻለች ስፍራ ትሆን ነበር።

ምፅዋ ከተማ ውስጥ ካደርን በኋላ በማግስቱ ጥዋት ወደ ጉርጉስም የባህር ዳርቻ መዝናኛ በታክሲ የ12 ኪሎሜትር ጉዞ አደረግን።

"ምፅዋዕ ኬድኪ ተናፈሲ፣ ጉርጉስም አብ ባሕሪ ሓምሲ" ድምፃዊ በረከት መንግስተአብ።

በረከት እንዳለው ድንቅ ከሆነው የቀይ ባህር ውሃ ውስጥ ገብተን ስንዝናና ውሃው ውስጥ እንደተነከርን መዋልና ማደርን ተመኘን። ወደ አስመራ ለመመለስ ታክሲው ድርሶ ሲጠብቀን ከኔ ጋር አብሮ የሚጓዘው የልጅ ልጄ "አልሄድም እዚህ ነው የምቆየው" ብሎ ከምሩ አስቸግሮኝ ነበር። እኔም በውስጤ የሱን ስሜት እንደተጋራሁ ግን አልነገርኩትም።

 

Back to Front Page