Back to Front Page


Share This Article!
Share
የኢትዮ - ኤርትራ ግንኙነት ድሮና ዘንድሮ

የኢትዮ - ኤርትራ ግንኙነት ድሮና ዘንድሮ

ሞገስ ተ 07-20-18

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን በማስመዝገብ በለውጥ መስመር ላይ ትገኛለች። ለዚህ የለውጥ መስመር ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአመራር ልህቀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ይህ አስተዋፅኦ አገሪቱ ከገባችበት የእርስ በእርስ ግጭትና አለመረጋጋት አውጥቶ በተለያዩ ችግሮች ቆስሎ የነበረውን አገራዊ ፍቅር ወደ አንድ መስመር ያመጣ የለውጥ መሃንዲስ ነው። ይህ የስራው ጅምር ደግሞ ህዝቡ ወደ ሚፈልገው የዲሞክራሲ መንገድ እየሄደ ለመሆኑ ገና ከጅምሩ በአጋርነት ሰልፍ በመደመር ባህል አሳይቷል። በመሆኑም በአገራዊ መግባባት መርህ ላይ የተመረኮዘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕራይ ከአገራዊ መግባባት እስከ ምስራቅ አፍሪካ መረጋጋት ብሎም የአፍሪካ ኩራት የሚል ስም እየተሰጣቸው ይገኛል።

ስለዚህ ህዝቡ ይህን የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅር ባይነትና የመደመር ዕሴት ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገበዋል። ይህ ደግሞ ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም ዜጋ በአገር ፍቅር ስሜት በተግባር የተደገፈ ማለትም በሰልፍ እንዳሳየው ትክክለኛ የለውጥ ሰልፈኛ መሆኑን የሚጨበጥ ስራ ሲያከናውን ነው። እናም ወሬውን በተግባር በመለወጥ ምርታማ የሆነ ትውልድ መፍጠሪያ መሳሪያው የጥላቻ ማነቆ የሆኑትን ጥቃቅን ነገሮችን መተው ሲቻልና የጋራ አገራዊ መግባባት በይቅርታ ሲታጀብ ነው።

ለዚህም ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያለ ዕረፍት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ስለ ሰላምና ስለፍቅር እንዲሁም ስለ አንድነት ደግመው ደጋግመው የሚያወሱት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ሁናቴ ሊለካና ሊመዘን የማይችል የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ፍጡራን ሀብት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ አገር እንደ አገር ሆና ለመቀጠል አገራዊ ፍቅር ያለው፣ በምክንያትና በሀሳብ የሚያምን አርቆ አሳቢ ትውልድ ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ሲኖር በዴሞክራሲያዊ መርህ ላይ የተመረኮዘ ለአገር አላማ የሚታትር ትውልድ ሲፈጠር ዕድገት ይኖራል፡፡ ስለሆነም እየታየ ያለውን የለውጥ ጭላንጭል ግብ ይመታ ዘንድ በአገኙት አጋጣሚ የለውጥ ዘዋሪ ማሽን ወጣቱን ትውልድ ጥላቻን ትቶ ይቅርታን፣ አንድነትን፣ ይቅርባይነትንና መደመርን መርጦ ለዚች አገር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ የተማጸኑት፡፡ ይህንን ተማጽኗቸውን ደግሞ በጭብጨባ ብቻ ሳይሆን በተግባር ማሳየት የዚህ ትኩስ ኃይል ባለቤት የሆነው የወጣቱ ትዉልድ ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገርና በምስራቅ አፍሪካ ለቀጠናው መረጋጋት እያሳየ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ስራ እጅግ አገርን ብሎም አፍሪካን ሚያኮራ ተግባር መሆኑ ሁሉም የተስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በዓመታት ሳይሆን በመቶ ቀናት ውስጥ ከመቶ በላይ ስኬቶችን በማስመዝገብ ትልቅ ድል የተቀዳጁ መሪ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

Videos From Around The World

የአገር ፍቅር ስሜት የሚቀነቀነው አንድነትና ሰላም በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ሙሉ ተዳርሷል፡፡ በሁሉም ምስራቅ አፍሪካ ማለት በሚቻል መልኩ እየተዟዟሩ በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራቸው እየተጉ ለኢትዮጵያ የተዛባ ግንዛቤ ያላቸውን አገራት አስተሳሰብ በመልካም ዕይታ እንዲቀየር እንዲሁም የታሰሩ ዜጎችን በማስፈታት ወደ አገራቸው እንዲገቡ በማድረግ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል፡፡ ለዚህም ምሳሌ ሚሆነው ደግሞ በግብፅ፣ በሱዳን፣ ሶማሌና ጅቡቲ ተዘዋውረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በባህል፣ በቋንቋ እንዲሁም በተለያዩ ዕሴቶች የሚመሳሰሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሁለት አስርት ዓመታት ሞት አልባው ጦርነት እየተባለ የሚጠራውን የሁለቱን ወንድማማች አገራት የጥላቻን ግንብ በፍቅር ድልድይ እንዲናድ ከፍተኛ ስራ አከናውነዋል፡፡

ጦርነትና ሰላም ሁለት ተቃራኒ ጉዳዮችን የያዙ ናቸው፡፡ ከሰላም በዋጋ ሊተመን የማይችል ትርፍ ሲገኝ፣ ከጦርነት ግን እንኳን ትርፍ ሊገኝ ከፍተኛ ሆነ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ ከሰላም በረከት፣ ፍቅር፣ አንድነትና እድገት ሲገኝ ከጦርነት ግን ስቃይ፣ እርሃብና እርግማንን ያስከትላል፡፡ ጦርነት እህትና ወንድምን፣ ልጅና አባትን፣ እናትና ልጅን ይከፍላል። በባላንጣነትም ያሰልፋል፡፡ ሰላም በፍቅር ስሜት ሰንሰለት ያስተሳስራል። ጥላቻ ደግሞ እንደ እሳት ያቃጥላል፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ሁለቱንም ጠንቅቆ እያወቀ ፍቅሩን ትቶ በጥላቻው መንገድ ሲመላለስ ይስተዋላል፡፡ ከጦርነት ምንም አይነት ትርፍ እንደማይገኝ ሁሉም ዜጋ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ለምሳሌ ጦርነት ኮሪያን ከፍሏል፤ ጀርመንንም እንዲሁ፡፡ ወደ እራሳችን ስንመለስ ደግሞ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በደም አፋሳሽ ጦርነት ለሃያ ዓመታት የማይዘነጋ ጦርነት ውስጥ ከቷል፡፡ ይህ ክስተት ለሁለቱ ህዝቦች የልብ ቁስል ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱን አገራት ወንድማማች ህዝቦች ከሚለያዩባቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው ዕሴቶች ይበዛሉና፡፡ እነዚህ ሁለት አገራት ከ1998 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በጦርነት እንደቆዩ በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን በጊዜው መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ አሁን እነዚህ ሁለት ሀገራት ወደ ሰላም ሲመለሱ ከጦርነት ጉዳት እንጂ ትርፍ እንዳላገኙበት በትውስት አውስተዋል፡፡ ምክንያቱም በርካታ ህዝቦች ለሞትና ለስደት ብሎም ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገውበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱ አገራት ድንበር ወሰን አካባቢ በርካታ ወታደሮች ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የቆየ ሞት አልባ ጦርነት ውስጥ ገብተው ቆይተዋል፡፡ ይህ ለሃያ ዓመታት የዘለቀው ሞት አልባ ጦርነት በቃን ተብሎ ወደ ሰላም መቀየር እንደሚገባው ብዙዎች ሀሳብ ሰጥተውበት የድንበር ውሳኔው በአልጀርሱ ስምምነት ቢፈቀድም እስካሁን ድረስ መፍትሄ አላገኘም ነበር፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በባለ ሲመታቸው ወቅት በህዝብ ተወካዮች ስበሰባ ላይ ለምክር ቤት አባላት ንግግር ሲያደርጉ ከኤርትራ ጋር ያለንን ሁኔታ የአልጀርሱን ስምምነት እንተገብራለን ሲሉ ተደመጡ፡፡ ሀሳባቸውም ፍቅርና አንድነት እንዲሁም መደመር ውጤታማ ያደርጋልና በመደመር ሀሳብ ውጤታማ እንደምንሆን እርግጠኛ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ይህ በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ወደ ጎረቤት አገራት ይሻገራል የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም በዚህ ንግግራቸው የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመቀበል ለኤርትራ መንግስትም የሰላም ጥሪ አቀረቡ፡፡ ይህንን የሰላም ጥሪ ተከትሎም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገራቸው የሰማዕታት ቀን በምታከብርበት ቀን ለሰላም ጥሪው ምላሽ በመስጠትና ወደ አዲስ አበባ ልዑካን ቡድን እንደሚልኩ ገለፁ፡፡ ለዚህ የሰላም ጥሪ በጎ ምላሽ በመስጠታቸውም የኢ.ፌ.ዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ምስጋናቸውን አቀረቡላቸው፡፡ ከዚህ ምስጋና በመቀጠልም የኤርትራ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሁለቱም አገራት የልዑካን ቡድኖች ተገናኝተው የሁለትዮሽ ውይይት አካሄዱ፡፡ በውይይታቸው ወቅትም የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍፁም አረጋ ስለሁኔታው በቲውተር ገፃቸው ኤርትራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት ለሁለቱም አገራት ያለውን ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙሃን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ፋይዳ የሁለት ሀገራት አንድ ህዝቦች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ለምስራቅ አፍሪካ ብሎም ለቀጠናው አገራት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ አስነብበዋል፡፡

የሁለቱ አገራት የግንኑነት ምዕራፍ በር ከፋች የነበረው የሐምሌ 7 የኤርትራው ፕሬዝዳንት ክቡር ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ የገቡበት ዕለት ነበር፡፡ በዚህ ቀን ከቦሌ አለም አቀፍ አየር መንገድ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ድረስ ያለው የህዝብ አቀባበል የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እየተቀባበሉ በድህረ ገፆቻቸው የሁለቱን አገራት የመደመር ፈይዳ ዘገቡ፡፡ ለዚህ መነጋገሪያ እርዕስ ደግሞ በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ የሚነበቡ ፅሁፎች ልዩ ድምቀት ነበሩ፡፡ ከነዚህም መካከል በጣም ያኮራኛል ኢትዮጵያዊነቴ የአገሬ ፍቅር ጠልቆ በስሜቴ፣ ለበጎ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ ጎረቤት ወዳድነን እንግዳ ተቀባይ የሚሉ ህብረ ዜማዎች በማቅረብ እጅግ በሚያስደምም አቀባበል በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በህዝብ ዝማሬ በመታጅብ ተቀብለዋቸዋል።

በዚህ ደማቅ ያቀባበል ስነስርዓት የህዝቡ ስሜትና እልልታን ጠቅላይ ሚኒስተር ዶር አብይ አህመድ በደስታ ስሜት የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም አዲስ አበባና የአካባቢው ህዝብ 24 ሰዓት ብንሰራለት፤ደማችን ብናፈስለት፤በምንም ዋጋ ልንከፍል የማንችለውን ፍቅር በተግባር አሳይቶናል፡፡ ሳናገለግለው፣ ሳንሰራለት ያከበረን ህዝብ ብዙ መናገር ብፈልግም እንኳ በዚህ ስሜት ውስጥ ሁኜ መናገር ስለማልፈልግ እጅግ የተወደድክና የተከበርክ በኢትዮጵያ ህዝብ የተናፈክ የአገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ወደ መድረክ መጥተህ ለህዝብህ መልዕክት እንድታስተላልፍ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ በማለት ከመድረኩ ፈቀቅ ብለው በሳቅና በፈገግታ ጋበዙት፡፡ ይህንን ያሉት በሚሊኒም አዳራሽ የሁለቱ አገራት የሰላም ማብሰሪ መድረክ ላይ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም መድረክ ላይ ቆመው ንግግራቸውን በአማርኛ እንዲህ ሲሉ ተደመጡ ተዘጋጅቶ የመጣ ብዙ መናገር ይችላል፡፡ እኔ ፊታችሁ ላይ ቆሜ የሚሰማኝን በእውነትና በልቤ ውስጥ ያለውን የደስታ ስሜት ለመግለፅ በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ እየታየ ያለው ሂደት ታሪክ እየተሰራ ነው፡፡ የኤርትራ ህዝብ ፍቅር፣ የኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ዶ/ር አብይ የመጣ ዕለት ዕድል ስለሰጠን በዓለም አደባባይ ፊት ስሜቱን ለመግለፅ የኤርትራ ህዝብ እኔ መናገር የምፈልገውን ሁሉ ገልፀውታል፡፡ እኛ ከህዝብ በስተጀርባ ነን፡፡ ስለዚህ ከህዝቡ በላይ እኛ ለመግለፅ አንችልም አሉ፡፡ ቀጥለውም ስለተደረገልን አቀባበል ከልብ እናመሰግናለን አሉ፡፡ ይህ የሁለቱ ሀገራት ጥምረት በጠንካራና በሳል የዲፕሎማሲ ስራ በመስራት በቀጠናው ያላቸውን ተሰሚነት ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

የኢትዮ-ኤርትራ መልካም ግንኙነት ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት መፍጠር በጎረቤት አገራት ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያስክትላል፡፡ ስለሆነም አገራቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ የቀረበ ትስስር ከመኖራቸው የተነሳ ለሌሎች አገራት የሚያደርጉት አስተዋፅኦ የጎላ ነው፡፡ በዚህ መልካም የሆነ ግንኙነት ግንባር ቀደም ተጠቃሚ የሚሆኑት በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በተለይም ደግሞ የትግራይና አፋር ክልል ህዝቦች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ድሮም በጦርነት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎጅ የነበሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ባላቸው የባህል፣ የቋንቋና የተለያዩ ዕሴቶቻቸው አንፃር ተሳስረው የሚኖሩ ህዝቦች ከመሆናቸው አኳያ ባላቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተጠቃሚነታቸው የጎላ ነው፡፡ ምክንያቱም አገራቱ በዋናነት ያላቸውን ወደብ በጋራ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት ተከትሎ በሚደረገው የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይጠቀማሉ፡፡

የኤርትራ ወደቦች ለኢትዮጵያ የወደብ አማራጮችን እንደሚያሳድግና ተወዳዳሪነትንም እንደሚፈጥርላት፤ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ለወደብ አገልግሎት ትከፍል እንደነበር ይታወሳል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ከኤርትራ ጋር የወሰደችው ስምምነት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬን ስለሚቀንስ ለምታደርገው ዕድገት አስተዋፅኦ አለው፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞም የትራንስፖርት አገልግሎት የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች በረራ እንደሚጀምሩና የኢትዮጵያ አየር መንገድም 20 በመቶ የሚሆነውን የኤርትራ አየር መንገድ ለመግዛት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 465 መንገደኞችን በመያዝ በ11/11/2010 ዓ.ም ወደ ኤርትራ በረራ አድርጓል፡፡ የሁለቱ አገራት ኢምባሲዎችም በአዲስ አበባና በአስመራ እንዲከፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሶ በኢትዮጵያ የኤርትራ ኢምባሲ ከ20 ዓመት በኋላ በሁለቱ አገራት መሪዎች ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

 

Back to Front Page