Back to Front Page


Share This Article!
Share
ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን ልብ አትወጣም

ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን ልብ አትወጣም

ኢብሳ ነመራ 08-04-18

ኢትዮጵያውያን ባለፉት አራት አስርት ዓመታት በከፍተኛ ቁጥር ሃገራቸውን ለቀው ተሰድደዋል። በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ የባለፉ አራት አስርት ዓመታትን ያህል ዜጎች የተሰዱበት ጊዜ የለም። የባለፉት አራት አስርት ዓመታት ስደት የሶስት ሺህ ዓመታቱን ይበልጣል። የዚህ ስደት መንስኤ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነው። ከ1960ዎቹ ማገባደጃ ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በፖለቲካ አመለካከታቸው የሚደርስባቸውን እስከ ሞት የሚደርስ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማመለጥ ተሰድደዋል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የአመለካከት ነጻነት በህገመንግስት ቢረጋገጥም፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበት እንዲሁም ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ክሶችንና እስርን ሽሽት ተስድደዋል። እነዚህ የፖለቲካ ስደተኞች በአብዛኞቹ በወጉ የተማሩ ልሂቃን ናቸው። እርግጥ አርሶ አደሮችም ጭምር በዚህ ፖለቲካዊ ሁኔታ ከተሰደዱት መሃከል ይገኙበታል።

በኢኮኖሚያዊ ምክንያት የተሰደዱም በርካቶች ናቸው። በሃገሪቱ የተንሰራፋውን የስራ አጥነት ችግር ለማምለጥ እንዲሁም የተሻለ ህይወት ፍለጋ ብዙዎች ተሰድደዋል። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለው ዋነኛ የስደት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነው። ሃገር ቤት የቀሩ ዜጎች በተለይ ወጣቶች ወደውጭ ሃገር መሄድ ያቃታቸው ናቸው ማለት ይቻላል። እድሉ ከተገኘ ሁሉም ወጣት አውሮፓና አሜሪካ መሄድ ይፈልጋል። ስራ ያላቸውና በሃገሪቱ አቅም የተሻለ ገቢ አላቸው የሚባሉት ጭምር የበለጠ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ሲሰደዱ ቆይተዋል።

Videos From Around The World

በፖለቲካዊ ሁኔታም ይሁን ስራና የተሻለ ህይወት ፍለጋ የተሰደዱት ኢትዮጵያውያን በአካል ከሃገራቸው ቢወጡም፣ በመንፈስ ግን ሃገራቸው ላይ ናቸው። ከቤተሰብና ከወዳጆቻቸው ጋር ያላቸው ትስስር አይበጠስም። አብዛኞቹ ቤተሰባቸውን በገንዘብ የደግፋሉ። ቤተሰቦቻቸውን ለአጭር ጊዜ  ጉብኝት ወዳሉበት ሃገር ይወስዳሉ። እነርሱም መጥተው ይጠይቃሉ። ለለቅሶ፣ ለሰርግ ወዘተ ሃገር ቤት ብቅ ይላሉ።

ይህ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ቤተሰባዊ ትስስር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም አለው። ኢትዮጵያ በውጭ ሃገራት ከሚኖሩ ዜጎቿና ተወላጆቿ በዓመት እስከ 4 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደምታገኝ መረጃዎች ያመለከታሉ። ይህ የውጭ ምንዛሪ ከአጠቃላይ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ መጠን ይበልጣል። የሃገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ከ2 ቢሊየን ዶላር በዙም አልዘለለም።

በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳና የአውሮፓ ሃገራት የሚኖሩቱ ሃገር ቤት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ሲነጻጸር ጠንከር ያለ የመግዛት አቅም አላቸው። በዚህ ምክንያት በተለይ አርቲስቶቻችን ዳያሰፖራውን ተደራሽ ያደረገ የጥበብ ስራ ላይ እንዲያተኩሩ ያደረገበት ሁኔታ መኖሩን ታዝበናል። አሁን ሃገሪቱ ውስጥ ባለው የኮፒ ራይት ጥበቃ ድክመት ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች (ዘፋኞችና ተዋንያን) የዳያስፖራው ገበያ በተለይ ኮንሰርት ባይኖር ኖሮ የጥበብ ስራቸውን የትርፍ ጊዜ ስራ ማደረጋቸው አይቀሬ ነበር።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በከፊል ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የተሰደዱ በመሆናቸው ባሉበት ቦታ ሁሉ በሃገራቸው ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በፍጹም የባለቤትነት ስሜት ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በውጭ ሃገራት በይፋ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ላይ አተኩረው የሚሰሩ ሲቪክ ማህበራት አደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። በአሜሪካና አውሮፓ ተደራጀተው በዚያ የሚንቀሳቀሱ፣ በጎረቤት ሃገራት የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸውም ይታወቃል። የሚኖሩባቸው ሃገራት ሃያላን መንግስታትና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ችግር እንዲሻሻል ጫና እንዲያሳድሩ፣ ማዕቀብ እንዲጥሉ ሲወተውቱ መቆየታቸውም ይታወቃል። ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውና አሁን በሃገሪቱ ያለውን የለውጥ አመራር ወደስልጣን ያመጣ እንቅስቃሴ በከፊል ውጭ ሃገር በሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶቸና ሚዲያዎች የተመራ መሆኑም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

በቀጥታ የፖለቲካ ተሳተፎ ከሚያደረጉት የዳያስፖራ አባላት በተጨማሪ ቁጥራቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ በተለያየ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሃገር ቤት ሳሉ እንደነበራቸው የአመለካካት ዝንባሌ የአንዱ ወይም የሌላው የፖለቲካ አመለካከት ወገን ደጋፊ በመሆን የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴው እንዲበረታ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የፖለቲካ ድርጅቶቹንና ሲቪክ ማህበራቱን በገንዘብ ይደግፋሉ፤ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በህዝባዊ ስብሰባ የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰማሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተላለፈ ማንኛውም ፖለቲካዊ ወሳኔ፣ ወይንም ፖለቲካዊ ሁኔታ አሜሪካ ወይም እንግሊዝ የሆነ ያህል ልዩ ትኩረት ያገኛል፤ የሞቀ ተቃውሞ ወይም ድጋፍን ያስተናግዳል። የዳያስፖራው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ሃገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ጭምር ከውጭ ሃገር የሚተላለፉ ኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩሩ ሚዲያዎችን እንደዋነኛ የመረጃ ምንጭነት ይጠቀማሉ። በውጭ ሃገር ያሉ ኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩሩ የመገናኛ ብዙሃን ሃገር ቤት ያለው የተቃውሞ ድምጽ የሚሰማባቸው ጭምር ናቸው።

እንግዲህ፣ ከላይ በአጭሩ የተነሱት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በሃገሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለው ድርሻ የዳያስፖራውን ማህበረሰብ ጉዳይ ከሃገር እንደራቁ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ችላ ማለት እንዳይቻል ያደረገዋል። ባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት ዳያስፖራውን በሃገሩ ጉዳይ በቅርበት እንዲሳተፍ ለማደረግ የዳያስፖራ ህግ ወጥቶ እንዲሁም የዳያስፖራ ቀን ተወስኖ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፣ ይህ ነው የሚባል ተጨማጭ በጎ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። ይህ የሆነው በሃገሪቱ ውስጥ ተጨባጭ  የፖለቲካ ማሻሻያ፣ የእርቅና የሃገራዊ መግባባት እርምጃዎች ሳይወሰዱ ዲያስፖራውን ለማቀረብ የተደረገ ጥረት በመሆኑ ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በአካል ከሃገሩ ቢርቅም፣ በሃገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ በንቃት ስለሚሳተፍ በሃገሪቱ ልማትና ሰላም ላይ ወሳኝ ድርሻ አለው። ዳያሰፖራውን እንደሌለ ቆጥሮ በኢትዮጵያ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ልማትን በሚፈለገው ልክ ማቀላጠፍ አይቻልም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ለዳያስፖራው ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሰጡት ለዚህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ጉብኝት ለማደረግ የወሰኑትም ለዚህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በሰሜን አሜሪካ ሶስት ከተሞች - ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጅለስና ሚኒሶታ ባደረጉት ጉብኝት ከሃያ በላይ ሁነቶች ተዘጋጅተው ከኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተዋል። በውጭ ሃገራት ከሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። በውጭ ሃገራት ለሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያ ላይ አተኩረው ለሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መገለጫ ሰጥተዋል። በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ በሃገሩ መንግስት ላይ የነበረውን አተያይ ሙሉ በሙሉ የቀየረ ታሪካዊ ነበር። ቀደም ሲል የኢፌዴሪና የክልል መንግስታት አመራሮች ለሰራ ሲሄዱ የመረረ ተቃውሞና ጥላቻ በመግለጽ የዲፕሎማሲ ስራውን አዳጋች አድርጎት የነበረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ፣ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የሚመራውን የልኡካን ቡድን እንደናፈቃቸው የስጋ ዘመዶቹ በደስታና በለቅሶ ስሜቱን እየገለጸ ነበር የተቀበላቸው። ይህ በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚከተሉት የይቅርታ፣ የምህረት፣ እርቅና መደመር አካሄድ ምክንያት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዳያስፖራው ጥሪ ብቻ ይደለም ያስተላለፉት፤ ምህረትና ይቅርታም አድርገዋል፤ የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአካል አግኝቶ የተወያየው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ በእውቀት፣ በገንዘብ ልገሳ፣ በኢንቨስትመንት በአካል ቢርቅም ከልቡ ሊያወጣት ላልቻላት ሃገሩና ወገኖቹ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል። ቀደም ሲል የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል የሚሉትን የኢፌዴሪ መንግስት እርምጃ በመቃወም፣ ከዓለም ለመነጠል ይሰሩ የነበሩ አይነ ግብ የፖለቲካ አክቲቪስቶች አሁን ወገናቸውን መርዳት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ በይፋ ቃል ገብተዋል። የሽሽት ሃገራቸውን ጥለው ወደትውልድ ሃገራቸው ለመመለስ ቃል የገቡም አሉ። በውጭ ሃገር እስከ ትጥቅ ትግል የዘለቀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያካሂዱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደሃገር ቤት በመመለስ ቀደም ሲል በተደረገው ጥሪ ከተመለሱትና ከነባሮቹ የሃገር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራም ይሁን በተናጥል ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወስነው ይህን በይፋ አሳውቀዋል።

በአጠቃለይ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲ፣ የኮኖሚና ማህበራዊ ልማት የሚደግፍ ሃይል ሆኗል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባላንጣ ሆኖ ለሃገሩ ልማት ማድረግ ይችል የነበረውን ሳያደርግ የቆየው ዳያስፖራ ማህበረሰብ ይህን ያለፈ ምእራፍ ዘግቶ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትና ጋር ተደምሯል። ኢትዮጵያውያን ከሃገራቸው በአካል ቢርቁም፣ ኢትዮጵያን ከልባቸው ውስጥ ማውጣት ሰለማይቻል፣ በልባቸው ይዘው የሚዞሯት ሃገራቸው የራሳቸው እንድትሆን ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ይህን ነው ያደረጉት።   

 

Back to Front Page