Back to Front Page


Share This Article!
Share
ኢትዮጵያ እንደ ዴዝዴሞና፦ "እንደ ወደድኩሽ ገደልኩሽ፣ እንደገደልኩሽ ሞትኩልሽ"

ኢትዮጵያ እንደ ዴዝዴሞና፦ "እንደ ወደድኩሽ ገደልኩሽ፣ እንደገደልኩሽ ሞትኩልሽ"

ደ/ር ዮሃንስ አበራ አየለ 09-23-18

ከ16 አመት በፊት በጎንደር ዮኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የባህርዳርና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራን ስብሰባ ላይ ስብሰባውን ሲመሩ ለነበሩት ለአቶ ህላዌ ዮሴፍ አንድ ከተራራ የገዘፈ ጥያቄ አቀረብኩላቸው፦ " የብሄር ስሜት እየገነነ ስለመጣ ኢትዮጵያዊነት እየተሸረሸረ አይደለም ወይ ያለው?" ይህንን ሲሰሙ በአይምሯቸው ውስጥ ብዙ ነገር እንደመጣባቸው እርግጠኛ ነበርኩ።  ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን እንደ ነገር ፍለጋ ወይም የብሄር ብሄረሰቦችን መብት መፈታተን ወይም የነፍጠኛነትና የትምክህት አመለካከት ማንፀባረቅ አድርጎ በሚተረጉመው አዲስ መዝገበ ቃላት ጋር አገናዝበው አዩብኝ መሰለኝ በአስገራሚ ፈገግታ እጅበው ትክክል እንዳልሆንኩኝ ነገሩኝ። ክርክር ስለማይፈቀድ ግን ደግሞ እውነቱ ያለው እኔጋ መሆኑ ግልፅ ስለነበር መልሳቸው የጆሮየ ኩክ ይዞት ቀረ እንጂ ወደ ውስጥ አልገባም። አሁን መልሼ ያንን ጥያቄ ብጠይቃቸው ተመሳሳይ መልስ ይሰጡኝ ይሆን? አይመስለኝም፣ "ካፈርኩ አይመልሰኝ" ካልሆነ በስተቀር።

ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ ብዙ እሷን ሳያሳልፉ የሚያልፉ የማይመስሉ ቁጥራቸው የበዛ ፈተናዎችን፣ ጨለማ ዘመናትን አሳልፋለች፦ በተደጋጋሚ የውጭ ወረራዎችና የአገር ውስጥ ትርምሶች። የብዙ ኢትዮጵያውያን የአስተሳሰብ ችግር ያለው ያቺ የሚሳሱላት አገር የምትጎዳው በውስጥ ሽኩቻ ሳይሆን በውጭ ወራሪዎች ነው ብለው ማሰባቸው ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶች ድንበር ተሻጋሪ እንጂ ከጉያዋ ውስጥ ያለነው እኛ ራሳችን ልንሆን እንችላለን ብለን አናስብም። ሰው የሚሞተው ከውጭ በጥይት ተመቶ ብቻ ሳይሆን ከውስጥ በበሽታ ማቆም ነው። እገርም የምትሞተው በውጭ ወራሪ ብቻ ሳይሆን ከሃገር ይልቅ የግል የፓለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን በሚያስቀድሙ ሆድ አደሮች ተቦርቡራና ተተራምሳም ጭምር ነው። ግልፅ የሆነ የሚጨበጥ ትርጉምና ድንበር የሌለው የብሄር ልዩነት መሠረት ያደረጉ ግድያዎች እና ሌሎች ጉዳቶች በወገናቸው ላይ የሚፈፅሙ ግለሰቦችና ቡድኖች አገር በውጭ ወሪሪ ተጠቃች ሲባል ሚስቴን ልጄን ሳይሉ ለመሰዋት ወደ ድንበር ይሮጣሉ።  የውጭ ወራሪ የነበረው ጣልያን ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችንን ፈጀብን ብለን እንቆጫለን። ከውስጥ በገዛ እጃችን ስንፈጃቸው ግን ከውጭ ወረራ በከፋ ሁኔታ አገር እየተጎዳችና ለውጭ ጥቃት ተጋላጭ እየሆነች እንደሆነ ማሰብ ያቅተናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ገዳይና ተገዳይ የሚጋሩት አንድ አስተሳሰብ አላቸው፦ ኢትዮጵያ ለዘለአለም እንድትኖርላውቸው መመኘት። አንድ የሚገርም ሃቅ አለ። እርስ በርስ በመፈራረጅና በመገዳልደ ላይ ባለበት ሁኔታ ድንገት ኢትዮጵያ ነገ ትገነጣጠልና እንደፈለጋችሁ 1000 መንግስታት ፍጠሩ ቢባል እሺ የሚል አንድ ጤነኛ ኢትዮጵያዊ አይገኝም። አንደኛው ምክንያት ምንም በብሄር ተለያይቶ ቢናቆር ከውስጡ ኢትዮጵያን ይወዳል፣ ባይወድም ሌላ የተሻለ ምርጫ አይታየውም። ሁለተኛው ምክንያት ከልምድ የተገኘ ፍርሃት ነው። "ወርቂትን ያየ በእሳት አይጫወትም" የሚባል ተረት አለ። ከሰላሣ በላይ አመታት የህዝብ ኑሮ ያመሰቃቀለ የመገንጠል ጦርነት ውጤት ለኤሪትርያና ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ያመጣበትን መከራ ያየ እዋቂ ከየዋህ ስህተት ይማራል ነው።

በፍቅር ይሁን የተሻለች ምርጫ ስለሆነችብን ኢትዮጵያ እንዳትሞት የምንፈልግ ከሆነ አንድ አይን ይዘን በአፈር መጫወት የለብንም። ከውጭ ገዳይ እያዳንን "ከፍቅራችን ብዛት" የተነሳ ራሳችን ከውስጥ የምንገድላት ከሆነ ኦቴሎ ዴዝዴሞናን "እየወደዳት" እንደገደላት እና እሱም እንደ ገደላት "እንደሞተላት" እኛም እትዮጵያን ገድለን ቀጥሎ እኛም ማለቃችን ሳይታለም የተፈታ ነው።

ራሳችንን አናታልል። የኢትዮጵያ ህልውና ጠፍቶ ብትበታተን የሚጠቀም እንጂ የሚከፋ አገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ተበታትነንም በጉርብትና በሰላም አንኖርም፣ ማን እንደኖረው? ሰላም እናግኝ ተብሎ ኤሪትርያ ብትገነጠል በ30 አመት ከሞተው ሰው ብዛት በላይ በሁለት አመት ጦርነት አልቋል። ብንሰደድም ሁሉም እሳት አለበትና የሚስጠጋን ጎረቤት እንደሌለ ልቦናችን ያውቀዋል። ስለዚህ ጉዳዮ "ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ" ነው።

 

 

Back to Front Page