Back to Front Page


Share This Article!
Share
ትንኝም ለሆዱ ዝሆንም ለሆዱ እኩል ወንዝ ወረዱ

ትንኝም ለሆዱ ዝሆንም ለሆዱ እኩል ወንዝ ወረዱ

ይቤ ከደጃች ውቤ 10-24-18

በቅርቡ የተመሠረተ አንድ ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበርና የሰጠው መግለጫ ፈገግ አስደረገኝ።ፓርቲው ገና ከመቋቋሙ የሰጠው መግለጫለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፋፋት የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለንየሚል ነበር ።እኔም ይሄ ፓርቲ ስሙ አዲስ ነው፤ ከመቼ ጀምሮ ነው ሲታገል የቆየው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፤ምናልባት መግለጫ የሰጡት የፓርቲው አባላት በሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ ውስጥ ያደረጉትን እንቅስቃሴ የአዲሱ ፓርቲ አካል እንቅስቃሴ አድርገውት ሊሆን ይችላል አልያም በምናባቸውና በህልማቸው ያሰቡትንና ያለሙትን የትግሉ አካል አድርገው ቆጥረውት ሊሆን ይችላል ብዬ ለራሴ ደመደምኩ ።

በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥራቸው እንደ አሸን የፈላ ነው።የአባላቶቻቸው ብዛት አንድ ጭብጦ የማይሞሉ ናቸው።ከፊሎቹ ለይስሙላ የተቋቋሙ በመሆናቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ጠብ ያደረጉት ነገር የለም። ገዢው ፓርቲ አመራሩን ለረጅም ጊዜ ተቆጣጠረ ይላሉ እነርሱ ግን በፓርቲያቸው ውስጥ የአመራር ለውጥ አድርገው ሲያሳዩ አልታየም።

Videos From Around The World

የፖለቲካ አመራሮቻቸው የዕድሜ ልክ ሆነውና የአመራር ለውጥ ሳያሳዩ እነርሱ ግን ገዢው ፓርቲን አምባገነን ነው፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አያውቅም ፣የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ እያሉ እሮሮ ሲያሰሙ ይስተዋላል ።ለራሳቸው ምንም ዓይነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሳይኖራቸው ወይም የኢህአዴግን ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመተቸት የሚያስችል ግንዛቤ ሳይጨብጡ መንግሥትን ሲያብጠለጥሉ ይሰማሉ ።

የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሊቀመንበር አመራር ከሆነ የሥልጣን ዘመኑ የዕድሜ ልክ ነው ማለት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ ተፎካካሪ ፓርቲዎቻችን በአሸዋ ላይ እንደተሠራ ቤት ቶሎ የሚፈርሱና የሚደረመሱ፣ በአመራሮች ጥቅማ ጥቅም የሚወቃቀሱ፣ በሥልጣን ሽኩቻ የሚቆራቆሱ፣ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸው ተሰሚነትና ተቀባይነት የአብዛኞቹ የሞተና በትዝታ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑ፣ ብሔራዊ ስሜትን ወደ ጎን ጥለው ጎሰኝነትን አንጠልጥለው የሚዳክሩ እንዲሁም ያረጀ ያፈጀውን19 60ዎቹን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አሁን ለመተግበር የሚጥሩ ናቸው ።

ከፊሎቹ በሀገር ውስጥ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ አሻንኩሊት ወይም ተለጣፊ ሆነው የተበጃጁ ድርጎ ሲቆረጥላቸው የነበሩ መሆኑን የፖለቲካ ልሂቃን ይናገራሉ።አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን እንደ ፓርቲ አመራር አድርገው ሲያቀርቡ ዜጎች ይገረማሉ ።አንዳንድ ሰዎች የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር መስለው በቴሌቪዢን መስኮት ሲታዩ፣ በሬዲዩ ሲደመጡ፣ በጋዜጣ ሲወጡ ማንም ሊያቅብን የሚችል ሰው የለም ብለው ቢያስቡም ቅሉ፤ እውነታው ግን ሌላ ነው። ህዝቦቻችን እንኳን በዚህ የመረጃ ዘመን ይቅርና መረጃ እንደ ልብ በማይዳረስበት ዘመንም እንኳን ይቺንና የዝንብ ጠንጋራ እናውቃለን ( ጠንካራ አላልኩም) እያሉ ያወጉ ነበር ።

ብላቴና ሳለሁ የማውቃቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አሁን የማውቃቸው አመራር ሆነው ነው።የሥልጣን ሽግሽግና ሽግግርን አያውቁትም ማለት ይቻላል።አመራር ቀይረው አልያም ተሸጋሽገው ልምዳቸውንና ድጋፋቸውን ለፓርቲያቸውና ለአመራራቸው መስጠት እየቻሉ ያደረጉት ነገር የለም። ስለ ዴሞክራሲ ለህዝቡ ሲያወሩና አውራውን ፓርቲ ሲተቹ የራሳቸውን ውስጠ ዴሞክራሲ እያሳዩና እያፀኑ ቢሆን ሸጋ ነበር። ገሚሶቹም በርዕዮተ ዓለም እና አመራር ሽኩቻ እየተቆራቆዙና እየተከፋፋሉ በየፊናቸው ፓርቲ ሲያቋቋሙ ዐይተናል ሰምተናል።

ከፊሎቹ ፓርቲዎች ደግሞ በብሔር ደረጃ ተመሥርተው ርስ በርስ ከአቻ ተፎካካሪ ፓርቲ ጋር የሚጎሻሸሙ ናቸው።ቀጣዩ የምርጫ ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ልዩነታቸውን አስወግደው አንድ ለመሆን የሚችሉበት መንገድ ካልዘየዱ ከገዢው ፓርቲ ጋር በሚያደርጉት የምርጫ ፉክክር ያለ ድምፅ ማጭበርበር ይሸነፋሉ ። በሚያደርጉት የምርጫ ውድድር አንድ ርምጃ መሻገር የሚችሉ አይመስለኝም።የምርጫ ውድድሩን ሳስበው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተበታትነው ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚያደርጉት የምርጫ ውድድር ለኔ በጥንቸልና በኤሊ መካከል የሚደረግ ሩጫ ይመስለኛል። ይሀ ደግሞ በብሂላችን ትንኝም ለሆዱ ዝሆንም ለሆዱ እኩል ወንዝ ወረዱ እንደሚባለው ይሆናል።

ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በርግጥም ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን የቤት ሥራቸውን መሥራት ያለባቸው አሁን ይመስለኛል።የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት በወሰደው ርምጃ ከውጪ የመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ለዜጎች ምሳሌ ሆነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማጎልበት መጣር አለባቸው።እኔ ነኝ ህጋዊ ፓርቲ እያሉ ርስ በርስ መጎሻሸም የለባቸውም ችግርም ካለ በምርጫ ቦርድ በኩል ተመዝግበው ራሳቸውን ማጥራት አለባቸው።ከፊሎቹም ከነ ትጥቃቸው ገብተው ሠራዊቶቻቸው በህዝቡ ዘንድ ችግር እየፈጠሩ ለሰላማዊ ትግል ነው የገባነው ማለትም ፌዝ ስለሚመስል ለችግሩ እልባት መስጠት አለባቸው።አመራሮቹ በዴሞክራሲ ከሚመሩ ሀገሮች መጥተው ልምዳቸውን ለፓርቲያቸው አባላት ማሳየትና የሰላም ተምሳሌት መሆን ካልቻሉ ተቀባይነት ያለው አመራር መሆን አይችሉም።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በሕዝቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት እየጎለበተ ነው።የሕዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጠ፣ መፍትሔ እየሰጠ፣ በለውጥ ጎዳና እየሮጠ ነው።ዜጎችም የኢህአዴግ ርምጃ ተስፋ እየፈነጠቀላቸው በየዕለቱ የሚከናወኑ ሥራዎችን በጉጉትና በስስት እያዩት ለመሆኑ ጥናትና ምርምር የማያሻው ዕውነታ ነው።

ምክንያቱም ኢህአዴግ ቀደም ሲል የህዝቡን የልብ ትርታ ከማዳመጥ ይልቅ እየደፈጠጠ፣ ከመነጋገር ይልቅ በመቃቃር የዜጎችን እንባ ማበስ ተስኖት ሲያባብስ የቆየበትን ሂደት በአመራር ለውጥ ቀይሮት በጎ ጅማሬዎችን እያሳየን መሆኑ ይታወቃል።ይህንን አጠናክሮ ለመቀጠል ውስጠ ዴሞክራሲን ማጠናከር፣ ሰሞኑን እንደተመረቀው የስኳር ፋብሪካ ዓይነት ለዜጎች የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ፣የውጪ ባለሀብቶችን መሳብ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር፣ በየቦታው የሚታዩ የሚታዩ ሁከቶችን መቅረፍ፣ ግብር የማይከፍሉ ዜጎችን ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲካተቱ ማድረግ ይጠበቅበታል።

እንደ አዲስ አበባ በመሳሰሉ ከተሞች የሚታዩ የመኖሪያ ቤቶችና የትራንስፖርት ንረትንና እጥረት ለመቅረፍ መጣር የተደቀነበት ሥራ ነው።ኢህአዴግ በትንንሽ ሥራዎች ሲኮራ የነበረ ድርጅት ነው። ይሄ ደግሞ ብዙ ሥራ ይጠብቀኛል እንዳይል አድርጎታል። በአዲስ አበባ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያለውን የቤት ፍላጎት በሩብ እንኳን መቅረፍ ያልቻሉ ለመሆኑ በአደባባይ የምናየው እውነታ ነው።

ዘወትር ሲነገረን የነበረው ኪራይ ሰብሳቢነት ለመዋጋት በተደረገው ሩጫ ከሚዲያ ፍጆታ ውጪ የተሠራ ሥራ አልነበረም ማለት ይቻላል።ምናልባት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት በተደረገው ሩጫ የተወሰደ ርምጃ ቢኖር የኪቤአድን ማለትም የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅትን ስያሜ ወደ ቤቶች ኤጀንሲ መቀየሩ ነበር ብዬ ነው የማስበው ።

ያም ሆነ ይህ ግን በየቦታው የሚሰሙ ሁከቶችን በማስወገድ ለሰላም ዋጋ መስጠት የመንግሥት ዋነኛ ሓላፊነት ቢሆንም ሚዲያዎች ለችግሮቹ እልባት የሚሰጡ ዘገባዎችን በማቅረብ የጎሳ መሪዎች የእምነት አባቶች አረጋውያን ሁሉም ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ።

Back to Front Page