Back to Front Page


Share This Article!
Share
የሚያንስም ይሁን የሚበልጥ እንዳይኖር

የሚያንስም ይሁን የሚበልጥ እንዳይኖር

ስሜነህ 08-07-18

 

የዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታና የፍጡራን ባህሪ አገር በፍቅር እና በይቅርታ ብቻ እንደማትመራ ያጠይቃል። ለመጀመርያ ጊዜ ፍቅር ሁሉን ነገር እንደሚያሸንፍ ምሕረት ማድረግ የዕለት ተግባራችን እንዲሆን ዓለምን ያስተማረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን እሱ ያስተማራቸው ሰዎች በመሆናቸው ከሰው ባህሪ በሚመነጭ ተንኮል እሱኑ ገድለውታል፡፡ ይኼ እኛ እንድንማርበት የተፈጸመ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ይቺን ዓለም ለመምራት ከፍቅር በተጨማሪ ሥልትና በትር አስፈላጊና በሁሉም አገሮች ከፍተኛ የፀጥታ ኃይልና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አስፈላጊና  የመንግስትም ቁልፍ ተግባር ሆኗል፡፡ ሕዝብ የወደደው መንግሥት ዘላቂነት እንዲኖረውና ሕዝብ ሰላም እንዲያገኝ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የህግ የበላይነትም ግድ ይሆናል።

 

ኢትዮጵያ በሕዝብና በመንግሥት መናበብ  ከአደጋ እየራቀች ነው ብንልም፣ አሁንም ተግዳሮቶች ስላሉ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም ጌዲዮና ጉጂ፣ ሲዳማና ወላይታ የተስተዋለውም ይህንኑ የሚያመላክት ነው። ሌላው እጅግ አሳሳቢው ጉዳይ በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ያለመግባባት ከመንግሥት አመራርነት የተለዩ አባላት ያሉበት ሁኔታ በውል ያለመታወቁ ሲሆን ለውጡን ያደናቅፋሉ በሚል አሉባልታ ከመሸበር ይልቅ የህግ የበላይነትን ተግባር ላይ በማዋል ሰላማችንን ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡

 

Videos From Around The World

በማንኛውም ምክንያት በአመፅና በጦርነት ጊዜ መተማመን የለም፡፡ የትውልድም ሆነ የጋብቻ ዝምድና የለም፡፡ ባህል የለም፡፡ ስለትምህርት፣ ስለጤና አይታሰብም፡፡ የሞተ መቅበር፣ የተጎዳን መዳኘት የለም፡፡ ጥፋት እንጂ ልማት አይታይም፡፡ የሚገድል ምንጊዜም የሚታየው አለመሞት ነው፡፡ ስለሆነም የሽማግሌ ድምፅ፣ የጎሳ መሪ ድምፅ፣ የሕዝብ ድምፅ አይሰማም፡፡ ለድርድር ከቀረቡ በኋላ ወደ ጫካ መመለስ ይኖራል፡፡

  

ዛሬ የምንገኝበት የሽግግር ዘመን ከዘመናት የተለያየ አምባገነናዊ አገዛዝ ወደ አዲስ የዴሞክራሲ አቅጣጫ የሚጓዝ እንደመሆኑ መጠን፣ ከአሮጌ አስተሳባብ ወደ አዲስ አስተሳሰብ መቀየር በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ይኸው ዴሞክራሲያዊ ጮራ ካለመለመዱ የተነሳ የፀሐይን ጨረር ያህል ዓይነ ህሊናችንን ሊወጋን ይችል ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ልናስተውለው የሚገባ ዓብይ ቁም ነገር ግን ከዴሞክራሲው የሚፈነጥቀውን ጨረር ብቻ ሳይሆን፣ ጨረሩ በሕዝብ ላይ አርፎ የሚያሳየውን ክስተትም መሆን ይኖርበታል፡፡ ወትሮም ሰው የሚመለከተው ፀሐይን ሳይሆን የምታሳየውን ነው፡፡ ይኸው የዴሞክራሲ ጮራ ሁነቶችን የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የመፋቀር እሴታችን ደረጃ የት እንደሚገኝ ሊያሳየን ይገባል፡፡ 

 

በዚች አገር ፍትሕ፣  ሰላምና አንድነት ተከብረው እንዲቆዩ ማንኛቸውም የፖለቲካ ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ለሕዝብ የሚበጅ አስተዳደር ይዤያለሁ ብለው ከፊታችን ከቆሙ፣ በበጎም ሆነ በመጥፎ ትምህርት ሊገኝበት እንደሚችል አውቀን በትዕግሥት ሁኔታዎችን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያ ለአንዱ እናት ለሌላው እንጀራ እናት ሆና ከቆየችበት ዘመን ልትላቀቅ የምትችለው ሕዝብ በፍቅር ዓይን መተያየት ሲጀመርና ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነቱን ሲያጠናክር ነው፡፡ ሰዎች በፈለጉት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ኑሮ መስክ ሊራመዱ የሚችሉትም አንድ እምነት ሲኖራቸው እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ስለአንድነታችንና ልዩነታችን ለማስንዘብ በየፊናችን ስንሰማራ ደግሞ የብዙ ዘመናት የብሔር ብሔረሰብ ጭቆናን አስወግደን ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ አስተደደር ለመመሥረት ባለን ዓላማ እንጂ በአሜሪካ ያሉት ሞንጎሎይድ፣ ካውካሶይድና ኔግሮይድ እንደ አሜሪካዊ ሁሉ አንድ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን በመዘንጋት አይደለም፡፡  ከዚህ በላይ የሆነውን ግን ማሽሞንሞን ዋጋ የሚያስከፍልና አገርን በሁለት እግሯ የሚያቆመውን የህግ የበላይነትን መዘንጋት ነው።

 

እስከዛሬ ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ የከተቱንን ችግሮች ለቅመን ብናስተውላቸው  ምንጫቸው የህግ የበላይነት ካለመኖሩ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የለም ማለት ደግሞ ፍትህ የለም ማለት ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ይህቺን አገር ያስተዳደሩና የገዙ መንግስታት አንዱ ትልቁ ችግራቸውና ድክመታቸው እንዲሁም ሊወቀሡበት የሚገባቸው ከፓርቲና ከመንግስት ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን አለመፍጠራቸው ነው፡፡ አሁንም እነዚህ የሉም። ምናልባት ሙከራዎች ሊደረጉ ይችላሉ እንጂ ነፃ ተቋማት የሉም፡፡

ከዚህ በመነሣት ነው የአገራችን ችግር የህግ የበላይነት አለመኖር ነው የምለው፡፡ የህግ የበላይነት የሌለው ደግሞ የፍትህ ተቋማት ከፖለቲካ ነፃ ሆነው መስራት ባለመቻላቸው ነው፡፡  

 

የህግ የበላይነት በአንድ አገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ከህግ በታች መሆናቸውንና በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያመላክት ፅንሠ ሀሳብ ነው። ይሄን ስርአት መገንባት ዜጎች በሃይለኞች በተለይ ከምንም በላይ ሃይል ባለው መንግስት እንዳይጠቁ ዋስትና ይሠጣል፡፡ ያለ ህግ የበላይነት ዘመናዊ የመንግስት ስርአት አይገነባም። የህግ የበላይነት ከሌለ ዘመናዊ መንግስት የለም፡፡ በየትኛውም አገር የመንግስት አሰራር በህግ ካልተገደበም ብቻ ሳይሆን አተገባበሩ የላላ ከሆነ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ የፈላጭ ቆራጭ ምንጩም ይሄው ነው። ስለዚህ የህግ የበላይነት ማለት ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡

 

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ደግሞ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ አንዱ ፍ/ቤት ነው፣ ከፍ/ቤት ጋር ደግሞ አቃቤቢ ህግ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት፣ ጠበቆች እንዲሁም ሚዲያ መኖር አለባቸው፡፡ ዜጎች በህግ የበላይነት እስካልተመሩ ድረስ ማንኛውም ዓይነት አዋጅ፣ ህግና ደንብ እንዲሁም መመሪያ ሊተገበር እንደማይችል ይገነዘባሉ። መብትና ግዴታቸውንም ሊያስፈፅሙና ሊፈፅሙ እንደማይችሉም እንዲሁ።

 

ይህም በአገር ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ አሉታዊ ጫናን ይፈጥራል። እናም ሁሉም ዜጋ የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር አገራዊ ሃላፊነቱን መከወን የእለት ተእለት ተግባሩ ሊያደርገው ይገባል። የአገራችንን ሰላም፣ የልማት ጉዞ እንዲሁም  የዴሞክራሲ ግንባታ መጠንከር እና የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስኬታማ ሆኖ መዝለቅ  የሚችለው የህግ የበላይነትን በማስፈን ብቻ ነው። ለውጡን ለማስቀጠል እና ከዳር ለማድረስ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ዜጎች ድጋፍቸውንም ይሁን ተቃውሟቸውን ሲገልጹ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ መሆን የሚችለው ለህግ የበላይነት ዋጋ ሲሰጠው ነው። እንዳስተዋልነውም ከዚያ ውጭ እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎች መቋጫቸው ሥርዓተ አልበኝነት ነው።

በአንዳንድ አካባቢዎች በድጋፍ ሥም የሚካሄዱ ሰልፎችን ተገን በማድረግ በአመራሮችና ህጋዊ ተቋማት ላይ ጥቃት የመፈፀም፣ መንገዶችን መዝጋት፣ የግለሰቦችን እና የመንግሥት ንብረቶችን እንዲሁም የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የማውደም ተግባራት ሲፈጸሙ ተስተውለዋል፡፡ ይህን መሰሉ ተግባር ለውጡን የሚያደናቅፍ ቢሆን እንጂ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ለመመለስም ይሁን እየተካሄደ ያለውን አገራዊ ለውጥ የሚያግዝ አይደለም።

 

ሥርዓተ አልበኝነት የጥፋት መንገድ ነው። ድጋፍም ይሁን ተቃውሞ መቅረብ ያለበት ህግና ሥርዓትን ባከበረ መልኩ መሆን እንዳለበት በተለይ ወጣቱ  ሊገነዘብ ይገባል።  በህግ ካልተደነገገ በስተቀር በየትኛውም አገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ሥርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። የመኖር ዋስትና በሌለበት አገር ውስጥ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋና እንደ ሰው ለመንቀሳቀስ የማይቻልበት ክፉ አጋጣሚ ይፈጠራል። ያኔ መብት ሰጪና ነሺ በጉልበታቸው የሚተማመኑ ኃይሎች ይሆናሉ። ዜጎችን ቀርቶ፣ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ የሚተጉ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሎችን ጭምር በአጉራ ዘለልነት እስከመግደል ሊደርሱ ይችላሉ። ለዚህም የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ህገ ወጦች ፖሊስንና የፀጥታ ሃይሎችን መግደላቸውን የኢፌዴሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለፓርላማ ካቀረበው ሪፖርት መገንዘባችንን እናስታውሳለን።

 

እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል። መንግስት ባለበት አገር ውስጥ ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም መንግስት የህግ የበላይነትን ከማስከበር መንገድ መውጣት የለበትም።መንግስት መብትም፣ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ያለበት አካል በመሆኑ በህጉ አግባብ መሰረት ተጠርጣሪዎችን ህግ ፊት በማቅረብ ተገቢውን ትምህርት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር የተጎጂዎችን እምባ ማበስ ይኖርበታል። ይህን ካላደረገ ህዝቡንም ይሁን በህዝቡ የተመሰረተውን ስርዓት በአግባቡ ሊጠብቅ አይችልም።

 

የህግ የበላይነትን የሚያፀና ሥርዓትን ዕውን ማድረግ ሴረኞችን በጩኸት፣ በህገ-ወጥነትና በሴራ የምትናጋ ሃገር  አለመሆኗን እንዲያውቁ ያደርጋል።

 

ኢትዮጵያ የጀመረችው አዲስ የለውጥ እና የመደመር እንዲሁም የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው።ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የግድና የግድ ይላታል።

 

የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ የምናውዳቸውን የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ሊሆኑ አይችሉም። ህግ ለድርድር ሳይቀርብ ሲቀር ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንስተናገዳለን። የሚያንስም ይሁን የሚበልጥ አይኖርም። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገራችንን ህገ መንግስት አክብረን እናስከብራለን።

 

 

 

Back to Front Page