Back to Front Page


Share This Article!
Share
በብሄር ስም ግጭቶችን ማስፋፋት!

በብሄር ስም ግጭቶችን ማስፋፋት!

ባይሳዋቅ-ወያ[1]

****

የሕወሓት መራሹን ግፈኛ መንግሥት ሕዝቡ ውድ ዋጋ ከፍሎበት ከገረሰሰው ባኋላ፣ ለኸያ ሰባት ዓመታት ሲናፍቀን የነበረውን ሰላምና መረጋጋትን አግኝተን ገና ሳናጣጥመው አንዴ በሶማሌ ክልል፣ አንዴ ደግሞ በቤኒሻንጉል ከዚያም በደቡብ ሕዝቦች አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለዓመታት ተከባብረው ተዋደው አብረው ይኖሩ በነበሩ የተለያየ ብሄር ተወላጆች መካከል በተነሳው ግጭት ሳቢያ በርካታ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ የተረፉት ደግሞ ለፍልሰት ተዳርገዋል። በዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ በበደኖና በጉራ ፋርዳ፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ደግሞ በጋምቤላ፣ በጉሙዝና በቤኒሻንጉል፣ በአዋሳ እና እንዲሁም ባገራችን የፍልሰት ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ካንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የኦሮሞ ሕዝብ ባንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከሶማሊያ ክልልና አካባቢው የተፈናቀለበትን ክስተት በየቴሌቪዥን መስኮታችን እየተመለከትን ከንፈራችንን መምጠጥ ከጀመርን ሰንብተናል። ፖሊስና ሐኪም ቁስል ሲያይ አይደነግጥም ይባላል፣ ፖሊስም ሐኪምም ላልሆንነው ዜጎች ግን ወገኖቻችን ከሚኖሩበት አካባቢ ከተለየ ብሄር በመወለዳቸው ብቻ መብታቸውን ተገፍፈው ለመፈናቀል ተዳርገው ስናይ፣ እንደ ፖሊስና ሓኪም ቁስላቸውን አይተን ብሶታቸውን ሰምተን አምላክ ይሁናችሁ ብለን ለመሰናበት ትንሽ ይከብዳል።

Videos From Around The World

 

በግሌ፣ የእህል ውሃ ነገር ሆኖ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በተለያዩ አገራት ስሠራ የነበረው፣ ለርስ በርስ ግጭቶች ወይም የጅምላ የመብቶች ጥሰት ሰለባ ከሆኑና ያለፍላጎታቸው ከቄያቸው ከተፈናቀሉ ሕዝቦች ጋር ቢሆንም፣ ምክንያቱን በማላውቀው ሁኔታ፣ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ፖሊሶችና ሐኪሞች ደንዳና ልብ አልፈጠረብኝም። ስለሆነም፣ የሕዝቦች መፈናቀል ምን ማለት እንደሆነ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ያየሁትና የኖርኩት ነውና የነዚህ ተፈናቃይ ወገኖቻችን ቁስል ውስጤ ድረስ ይሰማኛል። ይህንንም ስል ከፖሊቲካው አንጻር ሳይሆን፣ ማንኛውም የሰው ልጅ በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ያለፍላጎታቸው ሲፈናቀሉና ለአደጋ ሲጋለጡ አይቶ መቆርቆርና ችግሩ የሚቀረፍበትን መላ ምት መምታት የሙያ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታዬም ስለሆነ ነው። ከዚህ ሁሉ ዓመታት ተሞክሮ በኋላ ሁለት የተረዳሁትና በርግጠኝነት ልናገር የምችለው ነገር ቢኖር፣ አንደኛ፣ በሕዝቦች መካከል የትም ቦታና ምንጊዜም በማንነት ላይ የተመሠረተ ግጭት ኖሮ አያውቅም፣ ሰዎች አብረው እንደ ጎረቤት መኖር ሲጀምሩ መጀመርያ የሚያገናኛቸው ሰውነታቸው እንጂ የትውልድ ዘራቸው አይደለምና። ይህ ተፈጥሮያዊ ሕግ ነው። ሁለተኛ፣ በተለያዩ ብሄር ተወላጆች መካከል ልዩነት የሚፈጠረውና ብሎም ወደ ግጭትና መፈናቀል የሚያመራው ከውጪ ሌላ ሶስተኛ ኃይል ለሆነ ስውር ዓላማ ስኬት ሲባል ብሄር ልዩነትን መሠረት ያደረገ ቅስቀሳ ሲጀምር ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ለግጭቶችና ብሎም ለመፈናቀል ዋነኛው ምክንያት የሰዎች ከተለያየ ብሄር መወለድ ሳይሆን፣ ይህንን ከተለያየ ብሄር መወለድን ለግል ዓላማ ስኬት ለመጠቀም ከሚፈልጉ የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ ወይም የእምነት ጽንፈኞች ድርጊት ብቻ ነው።

 

ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ የጋሞ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ወገኖቻችን ከቄያቸው መፈናቀልና የሌላ ብሄር ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ መፈንቀላቸውን አስመልክተው ብሶታቸውን ከጊዜያዊ መጠለያቸው ጣቢያቸው ሲናገሩ እያየሁና እየሰማሁ ከዚህ ካለሁበት ባህር ማዶ ሆኜ ማድረግ የምችለው ሁሉ ግራ ገብቶኝ እንደተለመደው ከንፈሬን እየመጠጥኩ ለመጋደም ስሰናዳ፣ ከዚህ መፈናቀል ጋር የተያያዙ ሶስት በቅርጽም በይዘትም ተያያዥ የሆኑ ድርጊቶች ሲከሰቱ አየሁኝና ለምን ስሜቴን አምቄ እቃጠላለሁ፣ ምናልባትም ከወገኖቼ ጋር ብወያይበት አንድም ለመማማር ብሎም ለወደፊቱ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይረዳናል ብዬ ከማሰብ ሃሳቤን በዚህ ጽሁፍ አማካኝነት ላጋራችሁ ወሰንኩ። ሰው ነኝና ምናልባት አንዳንዶቹን ክስተቶች አጋንኜ ወይም በስህተት ተረድቼ ሊሆን ይችላል። ያ ከሆነ ግን፣ የድርጊቶቹ ባለቤቶች በቅንነት ቢያርሙኝና ካሳመኑኝ ለመታረም ምንጊዜም ዝግጁ መሆኔ እንዲታውቅልኝ እፈልጋለሁ።

 

የመጀመርያው፣ የወገኖቻችንን ሰቆቃ ለግል የፖሊቲካ ዓላማ ስኬት ማዋል የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክት ነው። ከቡራዩ በግፍ የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ገና እንደተፈናቀሉ ለሚዲያው ማህበረሰብ ይገልጹ የነበሩ ቅሬታዎቻቸውና ጥያቄያቸው፣ መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው፣ የተዘረፈው ንብረታቸው እንዲመለስላቸውና እነሱም ወደ ቄዬያቸው ተመልሰው በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ እንዲያበጃጅላቸው ነበር በጋሞኛ አማርኛ ሲያቀርቡ የነበረው። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የተፈናቃዮቹ ወጣቱ ክፍል ከሌሎች ቀደም ተብሎ ለድጋፍ ሰልፍ እንዲወጡ ከታዘዙት አዲስ አበቤዎች ጋር በመሆን በመስቀል አደባባይ ያሰማ የነበረው መፈክር ግን በቅርጽም በይዘትም ለየት ያሉ ነበሩ። በኔ ግምት፣ ይህ መስቀል አደባባይ ላይ በተቀላጠፈ አማርኛ የተሰማው መፈክር፣ ፌዴራሊዝም ይውደም፣ ክልሎች ይፍረሱ፣ አዲስ አበባ የኛ ናት፣ የሽግግር መንግሥት መንግሥት ይቋቋም፣ ምክትል ከንቲባው ሥልጣኑን ይልቀቅ፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ይውጣ፣ ኦነግ አልሸባብ ነው፣ጃዋር አሸባሪ ነው ወዘተ የሚሉት በማንኛውም መልኩ ከተፈናቃዮቹ ወቅታዊ ችግር ጋር ያልተያያዙና ለመፈናቀሉም መንስዔም መፍትሔም ሊሆን የማይችሉ፣ የሆነ የፖሊቲካ ቡድን አጄንዳ የሚመስል ነበር። ወንጀሉ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ሆኖ ሳለ፣ የአዲስ አበባን ከንቲባ ሥልጣን እንዲለቅ መጠየቅ፣ ወይም ፊዴራሊዝም ሥርዓቱና ክልሎች እንዲፈርስ መጠየቅ፣ ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን አንዳችም መፍትሄ የማይሰጥ ሌላ ራሱን የቻለ የፖሊቲካ አጄንዳ ይመስለኛል።

በኔ ግምት፣ ወጣቱን ያላግባብ የራሳቸው ያልሆነውን መፈክር አስነግበን ለራሳችን የሥልጣን ጥም ማርኪያ ሲባል ብቻ ሊመክቱት የማይችሉትን የመንግሥትን የታጠቀና የተደራጀ ኃይል እንዲጋፈጥ መገፋፋት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በስድሳዎቹ ያካሄድነውና ሳይሳካልን መቅረቱ ብቻ ሳይሆን ያገሪቷን የተማረውን ክፍል ለደርግ ሰይፍ የዳረግነው እንዲህ እንዲያ እያልን ነበርና ካለፈው ተምረን ያልተጓዝነው አዲስ መንገድ ፈልጎ መሞከር የሚሻል ይመስለኛል። አንዳችም ዓይነት መሻሻል ሳይደረግበት ያንኑ ስህተት እየደጋገሙ ስኬትን መጠበቅ ደግሞ ዕብደት ነው ይላሉ ፈረንጆች። በተለይም ስሕተቱ የሰው ልጆችን ነፍስ መጥፋት የሚያካትት ከሆነ!

 

ሁለተኛው፣ የነዚህ ወገኖቻችንን መፈናቀል ለሆነ የፖሊቲካ ዓላም ስኬት ማዋል የሚፈልጉ ቡድኖች እየተጠቀሙበት ነው ለማለት ያስደፈረኝ፣ ከሁለት ቀናት በፊት አንድ ሁሌም በሙያው የማደንቀው ዲያስፖራ ጋዜጤኛ፣ በቀጥታ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ በዓለም አካባቢ ያሉትን አዲስ አበቤዎችንና ደጋፊዎቻቸውን የተጣሰባቸውን መብታቸውን በራሳቸው ትግል ለማስመለስ መደራጀት እንዳለባቸውና፣ የድርጅቱም ዓላማ ከሞላ ጎደል፣ አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች እንጂ ኦሮሞዎች ምንም እንደማያገባቸው ስለሆነም የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ እንዲወጣ መንግሥት ደግሞ መብታቸውን ሊያስጠብቅላቸው ስላልቻለ አዲስ አበቤዎች መብታቸውን በራሳቸው ለማስጠበቅ መደራጀት እንዳለባቸው በማግሥቱ ደግሞ በሰልፍ ወደ ኦኤሜን ቢሮ ሄደው ባስቸኳይ እንዲዘጋ እንዲጠይቁ እና ሌሎች ምክንያቶችንም እየዘረዘረ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ መሆኑን በማስረዳት ሕዝቡን ለአመጽ ሲያዘጋጅ መስማቴ ነበር። በዚህ ከሁለት ሰዓት በላይ በፈጀው ዓለም አቀፋዊ የቅስቀሳ ዘመቻ በቀጥታ የስልክ መስመር ሲሳተፉ የነበሩ ወገኖቻችንም ሲያሰሙ የነበረው ቁጭት የተሞላበት ንግግር ምንኛ አደገኛ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ይህ በንዲህ እንዳለ፣ በጎን ደግሞ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ጠቢባን ከጥቂት ዓመታት በፊት የቦኮ ሃራም ጽንፈኞች ጡቷን የቆረጧትን ናይጄሪያዊት ዜጋ ፎቶግራፍ እየለጠፉ፣ በቡራዩ አካባቢ ኦሮሞዎች በጋሞ ብሄር ተወላጆች ላይ የፈጸሙት ወንጀል ነው እያሉ ያለ ኃፍረት አስተያየት እየሰጡና የኦሮሞዎችን ክፋት ለዓለም ሲያሳውቁ ነበር። ደግነቱ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ፎቶግራፎችን ቆርጦ ለመቀጠል ብቻ ሳይሆን ፎቶዎችም ከየት ተቆርጠው እንደተቀጠሉም ስለሚያሳይ እውነቱን ለመረዳት ሕዝቡ ጊዜ አልፈጀበትም። እውነተኛው የመረጃው ምንጭ ይፋ እስኪሆን ድረስ ግን የፎቶግራፉ አሰቃቂነት ስንቱን ኢትዮጵያዊ እንዳሳዘነና ድርጊቱን ፈጽመዋል በተባለው ሕዝብ ላይ አሉታዊ ግምት እንዲኖረው እንደሚገፋፋ መገመት አያቅትም። ግን ለምን አስፈለገ? የዚህ ድርጊት ተጠቃሚስ ማን ነው?

 

ሶስተኛው ክስተት፣ እንደዚሁ ያንድ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰና ለዘመናት በጽኑ አቋሙ የማደንቀው አክቲቪስት የጋሞ ወገኖቻችንን ጊዜያዊ መጠለያ ሲጎበኝ ማየቴ ነበር። አክቲቪስቱ ሁሌም እንደሚያደርገው ሕዝቡን ረጋ ባለና ኃዘን በተሞላበት አኳኋን እየዞረ ካነጋገረ በኋላ፣ የመሰነባበቻ ንግግር አድርጎ በዕንባ ሲሰናበታቸው አይቼ ይህ ዜጋ፣ ሁሌም እንደማስበው ትሁትና ለወገን አሳቢ መሆኑን አረጋገጥኩና ጋደም ብዬ የሃሳብ ፈረሴን ጭኜ ማለቂያ የሌለውን የዘወትር ጉዞ ልጀምር ስል፣ አክቲቪስቱ ከተናገራቸው ውስጥ ሁለት አረፍተ ነገሮች ጎልተው ታዩኝና ምን ማለቱ ነበር ብዬ ከራሴ ጋር ሙግት ጀመርኩ። እንዲህ ማለቱ ነው? አአአይ አይደርገውም፣ ሊሆን አይችልም፣ ምናልባት በተሰሳተ መንገድ ገብቶኝ ይሆናል ብዬ ለብዙ ደቂቃዎች ከራሴ ጋር ከተሟገትኩ በኋላ፣ የለም አልተሳሳትኩም እንዲህ ማለቱ ነው ብዬ ደመደምኩ። ለምን ይህን ማለት እንዳስፈለገው ግን አሁንም ያልገባኝ ስለሆነ፣ እስቲ ያለውን ልድገምና እናንተ ከኔ በተለየ መንገድ ገብቷችሁ ከሆነ ደግሞ አብራሩልኝ። ከንግግሮቹ መካከል፤ ቀልቤን የሳበውና በኔ ግምት ትክክለኛ አይደለም ብዬ የደመደምኩት የአክቲቪስቱ ሶስት አረፍተ ነገሮች ቃል በቃል እነዚህ ናቸው፣ በኢትዮጵያዊነታችሁ የተጠቃችሁ ወገኖቼዛሬ ኢትዮጵያዊነት የተፈተነበት ቀን ነው ኢትዮጵያዊነታችንን ያገዙንን የአዲስ አበባ ልጆችን እናመሰግናለን የሚሉ ነበሩ። ቪዲዮውን ደግሜ ደጋግሜ አየሁት አዳመጥኩት፣ ግን የነዚህን ዓረፍተ ነገሮች አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ገጻቸውን በጭራሽ ለማየት አልቻልኩም። እነዚህ የጋሞ ብሄረሰብ ተወላጆች ለደረሰባቸው ጥቃት ዋነኛው ምክንያት ኢትዮጵያዊ መሆናቸውና፣በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ መጠቃታቸውን አይተው ከጎረቤት ክልል የደረሱላቸው ደግሞ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበቤዎች መሆናቸው ስሰማ፣ እነዚህ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት ያደረሱና ከቤታቸው ያፈናቀሏቸው ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ የጎረቤት አገር ዜጋ ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ቡራዩ ድረስ ዘልቀው ገብተው ይህንን ወንጀል ፈጸሙ ማለት ነው ብዬ ደመደምኩ። መቼም ያካባቢውን ኗሪዎች የኦሮሞን ሕዝብ ኢትዮጵያውያን አይደሉም ለማለት አይደፍርምና! ከኔ በተለየ መልኩ የገባችሁ ካላችሁ ደግሞ በጥሞና ካስረዳችሁኝ አቋሜን ለመቀየር ዝግጁ ነኝ። እነዚህን ሶስት ክስትቶች ሳገናኝ፣ ከዚህ በፊት አስቤ በማላውቀው መልኩ ብዙ ብዙ አንድነታችንን የሚያናጉና አጥፊ የሆኑ አደጋዎች ታይተውኝ፣ እንደ ወትሮው ከንፈሬን መጥጬ ከመተው አካፋን አካፋ ብዬ ይህንን ከፋፋይና ጎጂ የሆነ ኋላ ቀር አስተሳሰብን ከእንጭጩ ለመቅጨት ይረዳል ብዬ ከማሰብ ይህንን ጽሁፍ ከናንተ ጋር ለማጋራት ወሰንኩ።

 

ከነዚህ ሶስት ክስተቶች ሌላ ሁሌም የማይጥመኝና ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብዬ የደመደምኩት አንድ የእኛ ውጭ አገር ያለነውን ተቆርቋሪ ዲያስፖራውን የሚመለከተን ዓቢይ ጉዳይ አለ። በመጀመርያ ደረጃ፣ ተፈጽመዋል እያልን የምናስተጋባቸውን ክስተቶች በውል መፈጸማቸውን ሳናረጋግጥ (ለምሳሌ በቅርቡ ከአርባ በላይ ሰዎች በተለያዩ አዲስ አበባ ክፍሎች ተገድለዋል ብሎ አንድ አክቲቪስት ያወራው ዓይነት) ይኸኛው ብሄር ያኛውን ገደለ፣ ይህን ያህል ሕዝብ ሞተ፣ አንገቱን ተሰላ፣ ይህን ያህል ሴቶች ተደፈሩ ይህን ያህሉ ሴት ደግሞ በገጀራ ጡታቸውን ተቆረጡ እያልን አንዳችም አስተማማኝ መረጃ ሳይኖረንና የተውሶ ምስሎችን ሳይቀር ለማስረጃነት በሚዲያው ገጽ ላይ በመለጠፍ ህዝብን ለበቀል ለማነሳሳት መሞከር በእሳት ላይ ውሃ መጨመር ካልሆነ በስተቀር፣ ለተፈናቃዮቹም ሆነ ለሕዝባችን አንዳችም ዓይነት ፋይዳ የማይሰጥ ድርጊት ነው። አዎ! ባገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ከባድ መሆኑን ጠንቅቄ ባውቅም፣ በጥቂቱም ቢሆን ተበዳዩ ሕዝብ በሚሰጠን መረጃ ላይ ብቻ ከማተኮር፣ (ከዘመናት ልምዴ እንደተገነዘብኩት፣ የተበደለ ሕዝብ ስለበደሉ ሲያወራ በዓይኑ ያየውን ብቻ ሳይሆን በጆሮው የሰማውንም ልክ በዓይኑ እንዳየ አድርጎ አጋንኖ ያወራልና) ይህን ያህል ሕዝብ ተገደለ፣ ታረደ ተደበደበ ተፈናቀለ እያልን ልክ በቦታው እንደነበርን አስመስለን መዘገብ የሕዝብን ስሜት ብቻ ቀስቅሶ ችግሩን ወደ ባሰ ቀውስ ለመምራት ካልሆነ በስተቀር ለችግሩ አንዳችም መፍትሄ አይሰጥም።

 

ሌላኛው ችግራችን ደግሞ፣ በወገኖቻችን ላይ ለሚፈጸሙት ጥቃቶች የምናሳየው መቆርቆር በጣም ወገናዊ ይመስለኛል። የሕዝባችን መፈናቀል አርዕስተ ዜና ሆኖ መቅረብ ከጀመረ ዓመታት አስቆጥሯል፣ አማሮች ወገኖቻችን በተለያዩ ክልሎች ከአማራ ብሄር በመወለዳቸው ብቻ ለመፈናቀል ሰለባ መሆን ከጀመሩ ዘመን የለውም። ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ በተቀነባበረ ዘመቻ ከሶማልያ ክልል ሲፈናቀልና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ በተጠለሉበት ቦታ ሳይቀር እንደ በግ ሲታረዱ አይተናል ሰምተናል። ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ የወላይታ ሕዝብ የወላይታ ብሄር ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ ከአዋሳ መኖርያ ቤታቸው ሲፈናቀሉ ያየነው ከጥቂት ወራት በፊት ነበር። ታዲያ ይ ሁሉ ሲሆን አንድም ቀን በመስቀል አደባባይ ይቅርና በየቀበሌያችን ተሰብስበን ለተፈናቃዮቹ መብት መከበር ይቅርና ሰብዓዊ እርዳታ እንኳ ልናደርግላቸው የምንችልበትን መንገድ ከመፈልግና አልፎም መንግሥት ቀድሞ እንዲደርስላቸውና ወንጀለኞቹን ለፍርድ አቅርቦ ተፈናቃዮቹን ደግሞ ወደየቤታቸው ባስቸኳይ እንዲመልስ በሰልፍ ወጥተን አንዳችም ዓይነት ጥያቄ ያላቀረብን ሰዎች፣ ዛሬ ቡራዩ ውስጥ በጋሞ ብሄር ተወላጆች ላይ በተፈጸመው የማፈናቀል ወንጀል ሳቢያ፣ አዲስ አበቤ ተነስ፣ ተደራጅ ለመብትህ ታገል፣ ወዘተ ብሎ የፖሊቲካ አጄንዳ ይዞ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ስውር የፖሊቲካ አጄንዳን ከማራመድ ባሻገር ወገናዊነትን የሚያሳይ ድርጊት ይመስለኛል። ከሚሊዮን በላይ የሆነው የአማራው፣ የኦሮሞና የወላይታው መፈናቀል ተደምሮ ያላገኘውን ትኩረት የቡራዩው ወገኖቻችን መፈናቀል እንዴት ባጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል የአዲስ አበቤዎችን ትኩረት ሊስብ እንደቻለ ለማንኛችንም በቀላሉ የሚገባን አይመስለኝም። ምናልባት የቡራዩው መፈናቀል ይህን ያህል ትኩረት ሊስብ የቻለው የወንጀሉ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን የተጠለሉበት ጊዜያዊ መጠለያ ለዋናው ከተማችን ካለበው ቅርበት የተነሳ ነው እንዳይባል፣ ከሶማሊያ ከተፈናቀለው በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠረው የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ እዚሁ አዲስ አበባ አካባቢ በጊዜያዊ መጠለያ መኖር ከጀመረ ወራት ቢያልፈውም አዲስ አበቤው ወጣት አንድም ቀን በጎዳና ወጥቶ ለነዚህ ዜጎች ፍትህን ሲጠይቅ ወይም ሰብዓዊ እርዳታ ሲያሰባስብና ሲያከፋፍል አላየንም። የተፈናቀሉት የጋሞው ወገኖቻችን ቁጥር አናሳ በመሆኑ መቆርቆር አይገባንም ማለቴ እንዳልሆነ ይገባችኋል። የሰው ልጆች መብት ጥሰት በቁጥር ብዛት አይለካምና! ለማለት የፈለግሁት፣ እዚሁ አዲስ አካባቢ የሁለት የተለያዩ ክስተቶች ሰለባ የሆኑ ተፈናቃይ ወገኖቻችን መኖራቸው እየታወቀ፣ ያንደኛው ወገን አበሳ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ በአደባባይ ስናውጅና ሌላውን እኩል ተበዳዩን ተፈናቃይ ወገን ግን ችላ ማለት፣ ከመልሱ ይልቅ ጥያቄው የጎላ ይሆናልና በጥልቅ እናስብበት ለማለት ያህል ነው።

 

ወገኖቼ አንሳሳት! አንዳንዶቻችን ለኢትዮጵያ ኅልውናና ለባንዲራዋ ከማንም በላይ ተሟጋች ነን እያልን በአደባባይ ስንናገር፣ ሌላውን ከኔ እኩል ኢትዮጵያዊ አይደለህም ማለታችንን ማስተዋል አለብን። ይህ የተሳሳተ ግምት ነው። እናት ልጆቿን እኩል ነው የምትወደው። የሰማዩን አናውቅም እንጂ በምድራዊው ሕግ፣ እናት ልጆቿን እኩል እንዲታፈቅራቸው ባያስገድድም እንድታበላልጥ ግን አይፈቅድም። ልጆቿ ግን ለናታቸው ያላቸው ፍቅር እንደ መመዘኛ ሳይቀርብ እሷንና ቅርሷንም እኩል እንዲካፈሉ ሕጉ ይደነግጋል። የናት ሆድ ደግሞ ዥጉርጉር ነውና ልጆቿ ሁሉም አንድ ዓይነት አይሆኑም። ፈሪ ወይም ጀግና፣ ቆንጆና መልከ ጥፉ፣ አጭር ወይም ረጅም ኃብታም ወይም ደሃ፣ የሚያዋርዳትም የሚያከብራትም በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ልጆቿ ናቸው። የኢትዮጵያችን 85 ልጆቿ (ብሄሮቿ) በሙሉ እኩል ልጆቿ ናቸው ማለት ነው። በመሆኑም የማንም ብሄር ከማንም ብሄር የበለጠ የኢትዮጵያ ልጅ አይሆንም፣ የማንም ብሄር ባሕል ወይም ቋንቋ ከማንም ብሄር ባሕል ወይም ቋንቋ አይበልጥም። ለዚች እናት አገር ደግሞ ማንም ከማንም በላይ የሞተላትም የለም፣ በመሆኑም ማንም ብሄር ከማን ብሄር በላይ ለግዛት አንድነቷ ወይም ለባንዲራዋ ጠበቃና ዋስ ነኝ ሊል አይችልም። አራት ነጥብ! ማንኛችንም ወድደን ወይም በግል ጥረት የዚህ ወይም የዚያ ብሄር ተወላጅ አልሆንንም። ስለዚህ ካንድ ብሄር መወለድ አያኮራምም አያሳፍርምም። የሚያሳፍረው፣ በጥረታችን ሳይሆን ባጋጣሚ ተፈጥሮ ያጎናጸፈንን ማንነት ለበጎ ተግባር ማዋል ሳንችል ስንቀር ብቻ ነው።

 

አይፈረድብንም! ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የነበረው ያ የፊውዳል ማህበረሰብ ባህሪያችንን፣ ይህን ብሄር ቡዳ ያኛውን ደግሞ ፉጋ፣ ይኸኛውን አጭበርባሪ ያንን ደግሞ ልቡ የማይገኝ፣ ይህንን ጨካኝ ያንን ሞኝ ወዘተ እያልን የኖርነውን፣ በዘመናዊ ትምህርት ሳሙናም አጥበነው ልንጸዳ አልቻልንም። ዛሬም፣ የኔ ብሄር ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ ኅልውና የታገለ ስለሆነ ለግዛቷ አንድነትና ለባንዲራዋ ተቀዳሚ ተጠሪ ነው ሲል፣ ሌላው ደግሞ ያንተ ብሄር ለዓመታት ጨቁኖኝ ስለነበረ ብሄርህ ከኃጢያቱ እስካልጸዳ ድረስ ካንተ ጋር በቅንነት ስላገራችን የወደፊት ዕጣ ለማውራት አልችልም ብሎ እርፍ ይላል። ይኸኛውም ሆነ ያኛው ወገን የረሱት ነገር ቢኖር፣ የሰው እንጂ የሕዝብ መጥፎ እንደሌለ ነው። ዛሬ ቄሮ አልሻባብ ነው ጃዋር አሸባሪ ነው እያልን በአደባባዩ ስንፎክርና ጃዋር ካገር እንዲባረርና የኦኤሜን ቢሮ ይዘጋ ብለን ለሰልፍ ስንወጣ፣ በቁጥር ከኛ የማያንሱ ደግሞ ቄሮ ታማኝና ለሕዝቡ ነጻነት የቆመና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ነው ጃዋር የቁርጥ ቀን ልጃችንና ወንድማችን ነው የሚሉ ወገኖቻችን እንዳሉ ደግሞ ማወቅ ይኖርብናል። ታዲያ ይህ ሁሉ እየታወቀ፣ ለምንድነው እነዚህን ያንድ እናት ልጆችን ለግጭት የምንጋብዛቸው? ከግጭቱስ የምናገኘው ትርፍ ከመገዳደል ሌላ ምንድነው? መቼ ነው የርስ በርስ ግጭት ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ እንደሌለው የምንረዳው?

 

ታዲያ እኮ መቼ ነው እኛ ከዚህ የእንስሳ ባህርያችን ተላቅቀን እንደሰው ልጅ አምላክ የሰጠንን ጭንቅላት ተጠቅመን ከታቃራኒዎቻችን ጋር ቁጭ ብለን ተወያይተን በሰላማዊ መንገድ ቅራኔዎቻችንን ለመፍታት ሙከራ የምናደርገው? መቼ ነው እኛ ሁላችንም እኩል የኢትዮጵያ ልጆች እንደሆንና ማንም ከማንም ይበልጥ ልጇ እንዳልሆነ ተረድተን፣ በእኩልነት መንፈስ ለናት አገራችን ዕድገት በጋራ የምንጥረው? መቼ ነው እኛ፣ ኦሮሞም ሆነ አማራ፣ ትግሬም ሆነ ወላይታ፣ አገውም ሆነ ሶማሌ እኩል ከኢትዮጵያ ማዕድ ተቋዳሽ መሆናችንን ተገንዝበን፣ እርስ በርስ መዋጋቱን በመተው እንድ አንድ እናት ልጆች አንተ ትብስ እኔ ልብስ ተባብለን፣ በጋራ ረሃብና ድንቁርናን የምንታገለው? መቼ ነው እኛ ለችግራችን መፍትሄ ለማግኘት መንገድ ላይ ወጥቶ መጮህ ብቻ ሳይሆን ቁጭ ብሎ በመወያየት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል የምንረዳው? መቼ ነው ከመንጋና የመንገድ ፖሊቲካ ከፍ ብለን ታይተን ችግሮቻችንን በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ወይም በዋርካ ሥር ቁጭ ብለን የምንፈታው? ቀኑ እየራቀ አስቸገረኝ። በኔ ዕድሜ ዕውን ይሆናል ብዬ ገምቼ ባላውቅም ዛሬ ዛሬ ግን ይበልጥ የሚያሳስበኝ፣ በኔ ዕድሜ አለመሳካቱ ሳይሆን በልጆቻችንም ዕድሜ መሳካቱ እያጠራጠረኝ መምጣቱ ነው። ሟርተኛ ነህ አትበሉኝና አሁን አዲስ አበቤዎች የሚያካሄዱትን የፖሊቲካ ቅስቀሳ ሳስብ የሆነ የስድሳ ስድስቱን አብዮት ተከትሎ የመጣውን የድርጅቶች ፍትጊያ ዓይነት መጥፎ መጥፎ ሽታ ይሰማኛል። እባብ ያየ በልጥ በረየ የሚሉት ተረት ይሁንልኝ ብዬ ራሴን ለማጽናናት ብሞክርም፣ ያኔ በምሁራን መካከል፣ መሆን በነበረበትና ሳይሆን በቀረው ልዩነትን አቻችሎ አብሮ ለመኖር ያለመቻል ክስተት መልኩን እንኳ ሳይቀየር እንዳለ ጥሬው ዛሬ በመስቀል አደባባይ ሲቀርብልን የሚያስከትለው ጥፋት እየታየኝ ነው። መንግሥት ሊያስከብርልኝ ያልቻለውን መብቴን ራሴ ተደራጅቼ አስከብራለሁ ማለት ደግሞ ለመብቴ ጥሰትም ሆነ ለትግሌ አለመሳካት ዕንቅፋት የሚሆነውን ሁሉ የማስወገድ መብት አለኝ ወደሚለው አስነዋሪ የግድያ አዟሪት ውስጥ የሚከተን ይመስለኛል።

 

ከዚህ ተነስቼ ነው ወጣቱን ትውልድ ያላግባብ፣ የራሳቸው ያልሆነውን መፈክር አስነግበን ለራሳችን የፖሊቲካ የሥልጣን ጥም ማርኪያ ሲባል ብቻ ሊመክቱት የማይችሉትን የመንግሥትን የታጠቀና የተደራጀ ኃይል እንዲጋፈጥ መገፋፋት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በስድሳዎቹ ያካሄድነውና ሳይሳካልን መቅረቱ ብቻ ሳይሆን ያገሪቷን የተማረውን ክፍል ለደርግ ሰይፍ የዳረግነው እንዲህ እንዲያ እያልን ነበርና ካለፈው ተምረን ያልተጓዝነው አዲስ መንገድ ፈልጎ መሞከር የሚሻል ይመስለኛል። አንዳችም ዓይነት መሻሻል ሳይደረግበት ያንኑ ስህተት እየደጋገሙ ስኬትን መጠበቅ ደግሞ ዕብደት ነው ይላሉ ፈረንጆች። በተለይም ስሕተቱ የሰው ልጆችን ነፍስ መጥፋት የሚያካትት ከሆነ!

 

የዛሬው ትውልድ ወገኖቼ! እስቲ ወደ ኋላ ልመልሳችሁና ከጥቂት ዓመታት በፊት በኔ ትውልድ ዘመን በመኢሶንና ኢሕአፓ መካከል የተፈጸመውን ግጭት ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን ላስታውሳችሁ። እነዚህ ሁለት በታሪካችን አንጋፋና የአገሪቷን ምርጥ ምሁራንን ያቀፉ ድርጅቶች፣ በጽንፈ ሃሳብ ደረጃ ያጠኑትን ዲሞክራሲያዊ እሴት በተግባር አውለው በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ቁጭ ብለው ተወያይተው በሚስማሙበት ላይ ተስማማተው በማይስማሙበት ላይ ደግሞ ላለመስማማት ተስማማተው በአብዮቱ ውስጥ እኩል ተካፋይ ሆነው ሕዝባችንን ለድል ለማብቃት ባለመቻላቸው ያንድን ትውልድ ምሁር እንዳለ ለደርግ ሰይፍ ዳረጉ። ይህ በምድራችን ላይ ያሉ ዩኒቬርሲቲዎች ከሚሰጡት በላይ ጥሩ ትምህርት በሰጠን ነበር። ሳይድለን ቀርቶ፣ ዛሬም እዚያው ከአርባ ዓመት በፊት እነበርንበት ቦታ መገኘታችን እጅጉን ያሳዝናል። የሰው ልጅ እኮ ከእንስሳ የሚለየው አምላክ የሰጠውን አእምሮ ተጠቅሞ ካለፈው ስህተት በመማር፣ ለወደፊት ጉዞው ካለፈው የተለየና የተሻለ ዕቅድ አውጥቶ ራሱንና ኅብረተሰቡን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የመቻል ስጦታው ነው። የእኛ ሰውነት ግን እያጠራጠረኝ መጥቷል። የሶስት ሺህ ዓመት ታሪካችንም ከዚህ ካውሬነት ባህርይ በላይ ከፍ ሊያደርገን አልቻለም። ምናልባትም እንደሚወራው ልዩ ሕዝቦች እንሆን እንዴ?

 

ስለዚህ ወገኖቼ፣ እስቲ ሰከን ብለን እኛ ሰማንያ አምስት ያንድ እናት ልጆች ባንድ ዋርካ ሥር ተሰባስበን፣ ድሮ ድሮ አባቶቻችን ያደርጉ እንደነበረው ሁሉ፣ በመካከላችን የተፈጠረውን አለመግባባት በቤተሰብ መካከል የሚደረግና የተለመደ ጊዜያዊ ግጭት መሆኑን አምነንና ተቀብለን፣ ለጋራ እናታችን ኅልውናና ጤንነት በጋራ ሆነን የምንሠራበትን ዘዴ እንቀይስ። የግድ ሰማንያ አምስታችንም ባንድ ሃሳብ ላይ መስማማት የለብንም፣ ሁላችንም ግን የሚሰማንን የመናገርና ሌሎችን የማሳመን መብት እንዳለንና ከኛ የተሻለና አብላጫው የቤተሰቡ አባላት የተስማማበትን ሃሳብ ደግሞ ባንስማማበትም እንደራሳችን ሃሳብ አድርገን በመቀበል ለአፈጻጸሙ የምንተባበርበትን ሁኔታ እንፍጠር። ከውጪ ወራሪ ኃይል ጋር በሚደረግ ውጊያ እንጂ፣ በርስ በርስ ግጭት ምንጊዜም አሸናፊ ኖሮ አያውቅም። በሌላ አነጋገር በብሄሮች መካከል በሚደረገው ግጭት ሁላችንም ተሸናፊ ነው የምንሆነው። የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ እንደሚሉት ነገር ይሆኖብንና፣ ማን ግቢ የሃዘን ድንኳን ተክለን፣ የትኛውን ገዳይ ኮንነን ለየትኛው ሟች እንድምናዝን ግራ ይገባናልና በጥብቅ እናስብበት። ሁሉም ቤት ሃዘን!

 

ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ግን በአጠቃላይ ለሚዲያ ተቋማት፣ አባላት እና ጋዜጤኞች በተለይ ደግሞ ከውጭ አገር በቅርብ ወደ ኢትዮጵያ ለተመለሱት ሚዲያ ተቁማት የሚከተለውን አጭርና ከልብ የመነጨ ልመና ወይም ማሳሰቢያ ላስተላልፍ እሻለሁ። ላገራችን ልማትና የወገኖቻችን የመጻፍ፣ የመናገርና የአስተሳሰብ ተፈጥሮያዊ መብትን ለማስፈንና ለማረጋገጥ ስታደርጉ የነበረውና ዛሬም እያደረጋችሁ ያላችሁ እንቅስቃሴ በሁላችንም ዘንድ እንድትከበሩና እንድትውደዱ አድርጎአችኋል። ላለፉት ኸያ ሰባት ዓመታት ባገራችን ሰፍኖ በነበረው ሥርዓት የመጻፍና የመናገር መብት ታፍኖ በነበረበት ዘመን፣ የሕዝባችን ዓይንና ጆሮ በመሆን ያላንዳች መታከት ታስተላልፉ የነበረው ወቅታዊ ፕሮግራም ለሕዝባችን ወሳኝ የመረጃ ምንጭ ነበር። ለዚህም ታሪክ ተገቢውን ቦታና ክብር ይሰጣችኋል። ዛሬ ግን ያ አፋኙ ሥርዓት ከሥሩም ባይሆን እየተገረሰሰ ባለበት ሰዓት አገር ቤት ገብታችሁ በማስተላለፍ ላይ ያላችሁት ፕሮግራም፣ ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ ከማድረስ ባሻገር መረጃዎችን በወገንተኝነት ስታቀርቡ እየተስተዋላችሁ ነው። የሚጥማችሁን መረጃ ብቻ በመምረጥ ለፈለጋችሁት ዓላም እንዲጥም አመቻችታችሁ ስታቀርቡልን ቅር እየተሰኘን በመመገብ ላይ ነን፣ ከዚያም በላይ አውቃችሁም ሆነ ሳታውቁ በየገጻችሁ ላይ የምትለጥፏቸው አንዳንድ ምስሎች ዘግናኝ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ አንዱ ወገን ሌላውን በጥላቻ ዓይን እንዲያየው ብሎም አንደኛው በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚያደርግ መሆኑን ለመመዘን አለመቻላችሁ በጣም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ሙያችሁ በመሠረቱ ከወገንተኝነት ነጻ የሆነና የምታገለግሉት ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ ያላንዳች አድልዖ እንዲያገኝ ነው። አንዳንዶቻችሁ ግን ኢ-ወገንተኛ መሆን የተሳናችሁ ወይም የረሳችሁ ይመስለኛል።

 

ሚዲያው የግል ሆኖ የባለቤቱን የፖሊቲካ ወይም የዕምነት ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተቋቋመ ሊሆን ይችላል፣ ይህ ደግሞ ስሕተት አይደለም። በዲሞክራሲ አገሮችም በተግባር የዋለ ነው። ግን አንድን መረጃ ለሕዝብ ስታቀርቡ ተቀዳሚ ዓላማችሁ የድርጅቱን ባላቤት የፖሊቲካ አቋም፣ አስተሳብ ወይም እምነት ለሕዝብ ለማሳወቅና ለማሳካት መሆኑን በግልጽ ለሕዝባችን አስቀድማችሁ መንገር አለባችሁ። ሕዝቡ መረጃችሁ ወገንተኛ እንደሆን እንዲያውቅ ማለት ነው። መረጃ (ኢንፎርሜሽን) የኒውክሌር ኃይል ማለት ነው። እንዳጠቃቀሙ፣ የኤሌክትሪክ ብርሃንን ሰጥቶ የሕዝብን ሕይወትን ብሩህ ሊያደርግ ይችላል፣ ቦምብ ሆኖም ትውልድን ሊያጠፋ ይችላል። ሂትለር የጀርመኖች የበላይ ዘር መሆናቸውን ለማሳመንና ብሎም ጀርመን ያልሆኑትን ለመፍጀት የተጠቀመበት ትልቅ መሳርያ ኢንፎርሜሽንን ነው። ስታሊንም፣ የሩሲያ ሕዝብ ታላቅ መሆኑን ለማሳመንና ብሎም ሂትለርን ለማንበርከክ የቻለው ሕዝቡን በኢንፎርሜሽንን አስታጠቆ ነው። ስለዚህ በተቻላችሁ መጠን የምትሰጡን መረጃ ቅራኔዎችን አጥፍቶ ሕዝቦችን የሚያፋቅርና ትውልድን በበጎ መንፈስ ለማነጽ የሚረዳ እንጂ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ሊያነሳሳ የሚችል የጥፋት ኃይል እንዳይሆን በጥብቅ አስቡበት እላለሁ።

 

በተረፈ ወገኖቼ! እስከዛሬ የተከሰቱት የወገኖቻችን መፈናቀል በጭራሽ መሆን ያልነበረባቸው ክስተቶች እንደሆኑ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። አዎ! አንድ ሕዝብ አንድ አገር አንድ ባንዲራ እያልን መወትወታችን መፈናቀሉን ሊያቆመው አልቻለም። ከፍላጎታችን ውጪና ባላሰብነው ሰዓትና ቦታ የሕዝቦች መፈናቀል እየቀጠለ ነው። የሕዝቦቻችንን መፈናቀል ማቆም ባንችልም በግብታዊነት መንፈስ ተነሳስተን፣ ይህንን ሕዝብ ያፈናቀለው ያኛው ሕዝብ ነው እያልን ከመኮነን መቆጠብ ግን መቻል አለብን። ከላይ እንዳልኩት እና ሁሌም መመርያዬ፣ የግለሰብ/ሰው እንጂ የሕዝብ መጥፎ የለም። ስለዚህ ከስሜታዊነት ነጻ በሆነ መንገድ ሰከን ብለን ክስተቶችን ለመዳሰስ እንሞክር። አቋም ለመውሰድ ወይም ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አንቸኩል። የማሕበረሰብ ድር በጣም ውስብስብና ጊዜ ወስዶ በዝግታ ካልተፍተለተለ በስተቀር የባሰውኑ ሊተበተብና ለመፍታት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ችግሮችን በጡንቻ ሳይሆን በጭንቅላት ለመፍታት መሞከር ነው። ችግሮቻችንን በጡንቻ ለመቅረፍ ብዙ ዓመት ሞክረናል ግን አልተሳካልንም። ስለዚህ ካለፉት ስህተቶቻችንና ተጓዳኝ ተሞክሮዎች ትምህርት ቀስመን፣ ሌላ አዲስ ጎዳና እንቀይስ። የኔ ትውልድ ማህበረሰባዊ ችግሮቻችንን ቢያንስ ቢያንስ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ለይቶ ማስቀመጥ ቢችልም በተግባር ግን መፍትሄ ለማቅረብ አልቻለም። ችግሮችን ለይቶ ማወቅ ራሱ ግማሽ ስኬት ነው ይላሉ ፈረንጆች! አዎ! ችግሮቻችንን ለይተን እናውቃለን፣ መፍትሄውን ለማቅረብ የሚችል አዲስ ትውልድም አለ። እነዚህን ሁለቱን ማገናኘት ደግሞ የኛ በተለይ ያንጋፋው ትውልድ ማኅበረሰባዊ ግዴታ ይመለኛል። ያን እስካደረግን ድረስ፣ በዚህ ትውልድ ዘመን ሕዝቦቿ ተከባብረውና ተፋቅረው የሚኖሩባት፣ የኤኮኖሚው ችግሯ ተቀረፎ ሕዝቦቿ ለፍልሰት የማይዳረጉ ኩሩና ራሷን ችላ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አንገቷን ቀና አድርጋ የምትታይ እናት አገር እንደምትኖረን አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም። ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛልን።

******

ጄኔቫ፣ መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ/ም

Wakwoya2016@gmail.com[1]ጸሃፊው ቀድሞ የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው።

Back to Front Page