Back to Front Page


Share This Article!
Share
ካልለመድነው መላመድ ሲያቅተን!

ካልለመድነው መላመድ ሲያቅተን!

 

ባይሳዋቅወያ

08-01-18

 

የኢትዮጵያን ሕዝብ ፖሊቲካዊ ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ሥርዓትን ታሪክ በተመለከተ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት የተለያዩ አገር በቀልና ባህር ማዶ ምሁራን በርካታ ምርምር ላይ የተመሰረቱ ጥናቶችን አበርክተውልናል። እያንዳንዱ ደራሲ ደግሞ ልዩና የሱ ብቻ በሆነው ጭንቅላት ስለሚያስብ፣ የነዚህ ጥናቶች መደምደምያዎችም እንደዚያው የለተለያዩ ናቸው። አንደኛው በጎ ጎኑን ብቻ ስለጻፈው ክስተት ሌላኛው ደግሞ ስለ ሰይጣናዊ ጎኑ ይነግረናል። ስለአንድ የግጭት ታሪክ ሲያወሱ፣ አንደኛው ጀግና ብሎ ስለጻፈው መሪ ሌላው ደግሞ ፈሪና አጥፊ አድርጎ ይስለዋል። አንደኛው፣ ላገር አሳቢ፣ የሥልጣኔ ጮራ፣ የአንድነት ምልክት ብሎ ስለሚጽፈው አንድ ንጉሥ፣ ሌላው ደግሞ ለመከፋፈላችን መንስዔና ለዕድገታችን ጠንቅ አድርጎ ያቀርብልናል። እነዚህን በተለያይ ጨርቅ ተጠቅልለው ይቀርቡልን የነበሩትን የሕዝባችንና ያገራችንን ታሪክ እያንዳንዳችንም እንደሚጥመን ሸምተናቸው እንደ ግል ዕቃችን (አቋማችን) በኪሳችን ይዘን መዞር ከጀመርን ይኸው አንድ ምዕተ ዓመት አሳልፈናል።

 

ስለክስተቶች የነበረን ድምዳሜ የሚለያየውን ያህል ደግሞ፣ ላለፉት መቶ ዓመታት ባገራችን ስለነበረው ፖሊቲካዊ ሥርዓት ግን ሁላችንም ለማለት በሚያስችል አኳኋን ባንድ ጭንቅላት ስናስብ ነበር ማለት ይቻላል። ከዓጼው ዘመን ጀምሮ የደርግንና የኢህዴግን መንግሥታት ያላንዳች ማቋረጥና መዛነፍ ከሞላ ጎደል ባንድ ድምጽ ባንድ ላይ ሆነን ስንቃወም ነበር። ተቃዉሟችን ደግሞ ከወረቀትና ዲስኩር ዘልቆ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩትን ዜጎቻችንን ውድ ሕይወት አስከፍሎ ነበር። አርሶ አደሩ፣የርሻ መሬቱ በንጉሡ ባለሟሎችና ጋሻ ጃግሬዎች ሲነጥቁበት ሸፍቶ፣ አንድ ቀን ተሳክቶልኝ እበቀል ይሆናል በሚል ተስፋ ከዘመድ አዝማድ ተለይቶ ከዱር እንስሳት ጋር ተለምዶ ሲኖር፣ እኛ ፊደል የቆጠርነው ደግሞ፣ ደሃውን ሕዝባችንን ከችግርና ስቃይ የሚያላቅቅ የሕዝብ መንግሥት ለማቋቋም ይረዱናል የምንላቸውን ማህበረሰባዊ ጽንሰ ሃሳቦችን ከዓለም ዙርያ አሰባስበን መርሆአችን በማድረግ፣ መጀመርያ የዓጼውን፣ ከዚያም የደርግን፣ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ደግሞ የኢህአዴግን መንግሥት ስንቃወም ኖርን። በሌላ አነጋገር፣ ላንድ መቶ ዓመት ያህል ያለማቋረጥ ስንቃወም ኖርን ማለት ነው። መቶ ዓመት የሶሶት ትውልድ ዘመን ነው። የዚህ ጽሁፌ ዓላማም፣ ይህንን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ስላለው የተቃውሞ ኑሮ በመጠኑም አስረድቼ፣ ይህንን ባህላችን እየሆነ የመጣውን የተቃውሞ ሕይወት እንዴት አድርገን ወደ አመራር/አስተዳደር ሕይወትለመቀየር ኃላፊነት አለባቸው ብዬ በማስባቸው የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ያነጣጠረ አስተያየቴን ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ ላንባቢዎቼ ለማጋራት ፈለግሁ።

Videos From Around The World

 

በኔ ግምት፣ ፍትህ ሲጓደልና መሰረታዊ ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ሲጣሱ ተቃውሞ አለማሰማት ወንጀሉን ከሚፈጽሙት ጋር ተባባሪ መሆን ነውና፣ ባገራችን ውስጥ በፊውዳሉ ዘመንና በደርግ እንዲሁም በኢህአዴግ ዘመን የነበሩትን ግፎች ተቃውሞ ድምጹን ያላሰማ ኢትዮጵያዊ የጥሰቱ ወንጀል ተባባሪ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ይህንን በየቤቱ ተከማችቶ የነበረውን የብሶት ክምርን ነው ተቃዋሚ ድርጅቶች አሰባስበው ከሕዝቡ ጋር በመሆን ግፈኛ ሥርዓቱን ለመገርሰስ የተቃውሞ እንቅስቃሴያቸውን ሲመሩ የነበሩት። የግፉና የጭቆናው መጠን ከአዕምሮ ግምት በላይ ቢሆንም፣ ይነሱከነበሩጥያቄዎችከፊሉ፣ የታሰሩት እንዲፈቱ፣ የመናገር፣ የመጻፍና እና የመሰብሰብ መብት እንዲከበር፣ ወዘተ ይሆንና መቋጫው፣ የሕዝቡን መብት የሚያከብር ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ማቋቋም ነው የሚል የፖሊቲካ ሥልጣን ሆኖ ያርፋል። በሌላ አነጋገር፣ ባገራችን በተለይም ላለፉት ሃያ ስባት ዓመታት የተቃዋሚ ድርጅቶች ሲያካሄዱ የነበረው እንቅስቃሴ መቋጫው፣ ወያኔ-መራሹን ኢህአዴግን ከሥልጣን አውርዶ በቦታው ዲሞክራሲ በሆነ መንገድ በተመረጠ ሕዝባዊ መንግሥት መተካት ነበር። በጣም ትክክል ናቸው። የመብት ጥሰቶች የሚወገዱት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ብቻ በመሆኑ እንቅስቃሴውም አንቀሳቃሾቹም ሙሉ የሕዝብ ድጋፍ ነበራቸው።

 

ላለፉት አራት ዓመታት በቄሮና ቀጥሎም በፋኖ እንዲሁም በዘርማና ሌሎችምበተናጠል የተመራው ሕዝባዊ ዓመጽ ያልታሰበና ተቃዋሚ ድርጅቶችም ያልተዘጋጁበትን ክስተት ይዞ ብቅ አለ። መጀመርያ ጠቅላይ ሚኒስትር ደሳለኝ ካቅሜ በላይ ሆኖብኛል ብለው በፈቃደኝነት ራሳቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትርነትና የኢህአዴግ መሪነት አገለሉ። ቀጥሎ ደግሞ፣ ባልተጠበቀ መልኩ ዶ/ር ዓቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ። የለማ ቡድን በአሸናፊነት ወጣ! ኦቦ ለማም ድርጅቱን ወክሎ ኢህአዴግ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ስላልሆነ ሕዝቡ ለሚያነሳው ጥያቄ መልስ ሊሰጥ አይችልም ብሎ በይፋ ዓቀጀ። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ኢህአዴግ ሕዝቡን፣ በጨለማ ቤት ሲያስር፣ ሲያሰቃይና ሲገድል የነበር አሸባሪ ድርጅት ነው ብለው በአደባባይ ተናግረው ሕዝቡን ይቅርታ ጠየቁ። መስማትና ማመን ከብዶን ባለንበት ቀልጠን ቀረን። ትንሽ ሳይቆይ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ፣ የፖሊቲካ እስረኞች በሙሉ ተፈቱ፣ ማዕከላዊ ተዘጋ፣ ያስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ተነሳ፣ የጸረ ሽብር ዓዋጁ መሻሻል ተደርጎበት በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከወንጀሉ ነጻ ሆኑ፣ ውጭ አገር ያሉት ተቃዋሚ ድርጅቶች ወዳገር ቤት እንዲመለሱ ተጋበዙ። ከሁለት ዓመት በኋላ በሚደረገው ሕዝባዊ ምርጫ ውስጥ የተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ ያላንዳች መሰናክል እንደሚወዳደሩናየፉክክሩ ሜዳውም ለሁሉም በእኩልነት መደላደሉን በቤተ መንግሥት ተጠርተው ማስተማማኛ ተሰጣቸው። ሌላም ሌላም!

ከጎረቤት አገራት በተለይም ከኤርትራ ጋር ለማመን በሚከብድ ፍጥነት የወዳጅነት ግንኙነት ተጀመረ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አስመራ በረረ፣ ለሩብ ምዕተ ዓመት ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኙ፣ የኢትዮጵያ ቱሪስቶች የምጽዋን ባሕር ዙርያ አጥለቀለቁ፣ ኤኮኖሚው እንዲንሰራራ ይረዳል ተብለው የተገመቱ ትላልቅ ፕሮጄክቶች ውል ከሃብታም አገሮች ጋር ተፈረመ። ባጭሩ ዶ/ር ዓቢይ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ቀውስ ለማከም በመቶ ቀናት ውስጥ የወሰዷቸው ተጨባጭ እርምጃዎች በታሪካችን ውስጥ ተወዳዳሪ አይገኝለትም ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ይህ እንግዲህ እሳቸው የሚመሩት ኢህአዴግ ድሮም በተግባር ለማዋል አስቦ አጋጣሚን እየጠበቀ ይሁን ወይም አዲሱ የለውጥ ቡድን ያቀደው አዲስ ጎዳና ነው የሚለውን ጥያቄ ወደ ጎን ትተን፣ ድርጊቱ አሌ የማይባልና አንዳችም ተቃውሞን የማያስተናግድ አዎንታዊ ጎን ብቻ ያለው የሕዝቡን የዓመታት ጥያቄ ከሞላ ጎደል የመለሰ ነው ብለን እንለፈው።

 

እኚህን የኢህአዴግ መሪ ማለትም የዶ/ር ዓቢይን የመቶ ቀናትአስገራሚ ሥራዎችና ውጤታቸውን እንዲሁም፣ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ያሳለፍነውንየተቃውሞ ሕይወት ደግሞ ባጭሩ ብንገመግም ዛሬ የት ላይ ነን ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ይረዳን ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። አዎ! ከዓጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ እስካለፈው አምስት ወር ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላላ ሲበላና ሲጠጣ፣ እንዲሁም ሲተነፍስ የኖረው የተቃውሞ አየርን ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም። የኔ ትውልድ ራሳችንን ካወቅንበት ቀን ጀምሮ፣ የፊውዳሉ ሥርዓትና ቁንጮው ኃይለ ሥላሴ ላገሪቷ ዕድገት ጠንቅ ስለሆኑ መወገድ አለባቸው ብለው ተቃውሞ ከሚያሰሙ አንጋፋ ተማሪዎች ጋር ተደምረን አቅማችን በፈቀደው ሁሉ የተቃውሞ ድምጻችንን ስናሰማ ነበር። የዓመታት የተቃውሞ ትግላችንም ፍሬ አፍሮቶ ንጉሡም ከሥልጣን ወረዱ። ባላሰብነው መንገድ ደርግ ሥልጣን ወስዶና ጸረ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መሆኑን ስናረጋግጥ፣ ላገሪቷ ዕድገት ጠንቅ ስለሆነ ይወገድ ብለን የለመድነውን ተቃውሞ በተሻለ መልኩ ቀጠልንበት። ከአሥራ ሰባት ዓመት ያላቋረጠ ትግል በኋላ ደርግም ወርዶ ወያኔ-መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት አራት ኪሎ ገባ፣ የሙሽርነት ጊዜው ገና ሳያልቅ አካሄዱ አላምር አለንና ተቃውሞ ማሰማታችንን ቀጠልንበት። ላገሪቷ ዕድገት ጠንቅ ነውና ኢህአዴግ መወገድ አለበት ብለን በታሪካችን ታይቶ ተሰምቶ በማይታውቅ አኳኋን ባገር ቤትና በዓለም አቀፍ ዙሪያ ዘመናዊ በሆነ መልክ ተደራጅተን ለሃያ ሰባት ዓመት ተቃውሞአችንን አፋፋምነው። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ግን ስንቃወመውና ሞቱን ስንመኝ ከነበረው ግፈኛ ድርጅት እንደዚህ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለዘመናት አንግበን ለተቃውሞ የተሰለፍንባቸውን የመብት ጥያቄዎች የሚመልስ አዲስ ብቅል መውጣቱ ከማስገረሙም በላይ፣ ልዩ መታወቂያችን የሆነውን የተቃውሞ አጄንዳችንንና የኛ ብቻ ይመስለን የነበረውን ጩኸታችንን በነዚህ የለውጥ ቡድን ተቀምተን ባዶ እጃችንን ቀረን።

 

አዎ! የለውጡ ቡድን የሕዝቡን ጥያቄ ከሞላ ጎደል መመለሱ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ግራ አጋብቷል። ላለፈው አንድ ምዕተ ዓመት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የነበረው የመቃወም ልምድ ወደ ባሕል ተቀይሮብን፣ ተቃውሞን ወደ አመራር/አስተዳደር መቀየር የቸገራቸው ይመስለኛል። ከመቃወም ሌላ ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብን የማስተዳደር ልምዱ ደግሞ ስለሌላቸው፣ ያልሄዱበት መንገድ ሆኖባቸው ከሩቁ አስፈራርቷቸው ነው መሰለኝ ተቃዋሚ ኃይላት በሙሉ የታገሉትና ያታገሉት የፖሊቲካ ሥልጣን ለመጨበጥና የሕዝቡን የመብት ጥያቄ ከመመለስ ባሻገር፣ እንዴት ተደርጎ ዛሬ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ ለሆነው ትውልድ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት፣ ሰባ አምስት በመቶ ለሆነው አርሶ አደር ሕዝባችንን እንዴት ተደርጎ በቀን ሶስቴ ሳይሆን አንድ ጊዜ እንኳ በልቶ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችል የረጅም ጊዜ የኤኮኖሚ መርሃ ግብር፣ ወይም መሰረታዊ ሕክምና አገልግሎት አጥቶ በየቦታው ሕይወቱ የሚቀጠፍበትን ዜጋ ችግር ለመቅረፍ፣ ወይም ደግሞ ተተኪው ትውልድ ብቁና ብሩህ ሆኖ አድጎ አገሪቷን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚያስችል አገራዊ ዕቅድ አውጥተው የማህበረሰቡን አባላት ሲያወያዩ አይታዩም። ዝም! እንዲያው ዝም ብቻ! ጆሮ የሚያደነቁር ዝምታ!

 

እኔን እጅግ የሚይሳስበኝ ይህ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ብሎም የሕዝቦች ዝምታ ነው። አዎ! ለዓመታት የታገሉለትና ያታገሉበት የኢሕአዴግን መንግሥት ገርሶስ በቦታው ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋሙ በታሪክ አጋጣሚ ምክንያት አላስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከኢሕአዴግ የፈለቀው ወጣቱ የለውጥ ቡድን የሕዝቡን የዲሞክራሲ ጥያቄ ከሞላ ጎደል ስለመለሰው ይህንን ቡድን ከሥልጣን ይወገድ ብሎ ሕዝቡን ለተቃውሞ ለማሰለፍ መሞከር ደግሞ ለግል ሥልጣንን ከመፈለግ ሌላ ትርጉም አይኖረውም። የተቃዋሚ ድርጅቶች አሁንም ዓላማቸው የፖሊቲካ ሥልጣንን ለመጨበጥ ከሆነ ደግሞ፣ ያን የሥልጣን ምኞት ዕውን ለማድረግ የቀረችው ጊዜ ሁለት ዓመት ብቻ ናትና ለዚያ መዘጋጀቱ የሚያዋጣቸው ይመስለኛል።ማን ያውቃል፣ በሚቀጥለው ምርጫ ሕዝቡ ከኦቦ ለማ የለውጥ ቡድን ይልቅ ተቃዋሚዎችን ሊመርጥ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ያ ዕውን እንዲሆንላቸው ከፈለጉ ደግሞ፣ ተቃዋሚ ኃይሎቹ በዚች በቀረችው ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ፤ ያላቸውን የኤኮኖሚና ማሕበራዊ፣ የጤናና የትምሕርት፣ የመከላከያና የውጪ ጉዳይ ረቂቅ ፖሊሲያቸውን በአደባባይ ለሕዝብ አቅርበው እያወያዩ የዝምታ ድባቡን ማስወገድ አለባቸው። ድሮ የመናገር፣ የመጻፍና የመሰብሰብ መብት በማይፈቀድበት በዚያ በጨለማው ዘመን ሕዝብን ሕገ ወጥ በሆነ ዘዴ ለተቃውሞ ሲያነሳሱ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ዛሬ ያላንዳች ችገር በፈለጉበት ቦታና ሰዓት ሕዝብን አሰባስበው ማወያየት ሲችሉ፣ ዝምታቸው ወይ ያልለመዱት ሆኖባቸው ተቸግረዋል ወይም ደግሞ ድሮውንም ከፖሊቲካ ሥልጣን ባሻገር ያገሪቷን ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቅረፍ የሚያስችል መርሃ ግብር አልነበራቸውም ያሰኛል።

በዶ/ር ዓቢይ የሚመራው የለውጥ ቡድን ግን ለዚያ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው። ያገሪቷን ኤኮኖሚያዊ ማህበረሰባዊ ችግር ለሕዝብ በግልጽ እየተናገረ ችግሩን ለመቅረፍ ይረዳሉ የሚላቸውን ሃሳቦች ደግሞ እያካፈለ ነው። ላገሪቷ ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊ ናቸው በማለት ከጎረቤት አገራት ጋር ስምምነት ፈጥሯል፣ ወዳጅነትን አጠናክሮአል። ብድር የሚገኝበትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ ኤኮኖሚያዊ ችግሩን በተቻለ መጠን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ነው። የውጪ ባለሃብቶች መጥተው ኢንቬስት የሚያደርጉበትን ዕቅድ አውጥቶ እየጋበዛቸው ነው። ሌላም ሌላም! ከሁሉም በላይ ግን፣ አገሪቷ ያጋጠማትን የማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ በግልጽ ለሕዝብ እየተናገሩ በጋራ እንወጣውበሚል መፈክር ሥር ለረጅሙና ፈታኙ የዕድገት ጉዞ ሕዝቡን እያሰባሰቡ ነው። ይህ አካሄድ ላለፈው ሃያ ሰባት ዓመታት ኤኮኖሚያችን በያመቱ በ 11% እያደገ ነበር እያለ ኢህአዴግ ያደነቁረን ከነበረው ባዶ ፕሮፓጋንዳ የተለየና ያገሪቷን የኤኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ በግልጽ ያስቀመጠ ስለሆነ፣ ሕዝቡ ደፍሮ ዛሬውኑ ዳቦ ካልተሰጠኝ ብሎ እንዳይጠይቅና ቁርጡን አውቆ ለረጅሙ ጉዞ እንዲዘጋጅ የታለመ ነው። ግልጽነት ማለት እንደዚህ ነው!

 

ለመደምደም ያህል፣

 

ይህ የተቃዋሚዎች ዝምታያስከተለው የሕዝቦች ዝምታአደገኛነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየታየኝ ነው።ችግሬ ለምን ዝም አሉ አይደለም፣ ዝምታው በፍላጎት ላይ የተመሰረተና የርካታ ምልክት ሳይሆን ከምርጫ ማጣት የተነሳ ስለመስለኝ ነው። እኔን የሚያስፈራኝ ዝምታን ያልለመደ ሕዝብ በድንገት ዝም ለማለት ሲገደድ፣ ከዚህ ካልለመደው የዝምታ ድባብ ለመውጣት ሊወስድ ስለሚችለው እርምጃ ነው። የተቃዋሚ ድርጅቶች የተለመደውን አመራር መስጠት ስላቃታቸው፣ ሕዝቡ በራሱ ጥረት የራሱን መሪ (የጎበዝ አለቃ) መርጦ ወደ ለመደው የተቃውሞ ሕይወት ይመለሳል የሚል ስጋት አለኝ። የተለመደው የተቃውሞ ጥያቄ ደግሞ በለውጥ ቡድኑ አጥጋቢ መልስ ስላገኘ፣ አዲሶቹ የሕዝብ መሪዎች ከመብት ጥያቄ ውጪ አዲስ የሆነና ከወትሮው የተለየ የተቃውሞ ጥያቄ መፈለግ አለባቸው ማለት ነው። ይህንን ከመብት ጥያቄ ውጪ የሆነ የተቃውሞ ጥያቄን ለማግኘት ደግሞ ሕዝቡ ሩቅ መሄድ አያስፈልገውም። እዚያው ባካባቢው ያገኘዋልና! አዎ በዚህ የዝምታ ጊዜ ነው ለዘመናት፣ እንኳን ለግጭት ምክንያት መሆን ይቅርና ሰበብ ሊሆኑ የማይችሉትን ጥቃቂን ጉዳዮች ዛሬ በድንገት ያገር ጉዳይ ተደርገው ይታዩና የተቃውሞ ጥያቄ ሆነው ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ። ዓመታትን ያስቆጠሩና ለወትሮው ለደቂቃ እንኳ የሕዝብን ቀልብ ያልሳቡ ሓውልቶች ዛሬውኑ ፈርሰው በሌላ ካልተተኩ፣ ወይም ደግሞ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል በባንዲራው ላይ ያለው ኮከብ አገሪቷ እያስተናገደች ላለው ቀውስ አስተዋጽዎ እንደሌለው እየታወቀ፣ ዛሬውኑ ካልተነሳ እያሉ ትልቅ አታካራ መፍጠር፣ ወይም ደግሞ ለዘመናት በመዋደድና በመከባበር አብረው የኖሩ የተለያዩ ብሄር አባላትን ዛሬ እንደጠላት ፈርጆ ዛሬውኑ ከክልላችን ይውጡየሚል የተቃውሞ ጥያቄለማንሳትና አላስፈላጊ የሆነ ግን ደግሞ ውድ ዋጋ የሚያስከፍል ግጭት ለመፍጠር የተቃውሞ ጥያቄ ሆነው መንሳፈፍ ይጀምራሉ።

 

ወድዳ አይደለም ለካ ዘፋኟ እህታችን ጭር ሲል አልወድም ያለችው! መጽሃፉም የሚለው እኮ ሥራ የፈታ ጭንቅላት የሰይጣን የግልቢያ ሜዳ ይሆናል ይላል። በኔ ግምት፣ ይህንን የዝምታ ወረርሽኝ በአዎንታዊነት ለመጠቀምና ለበጎ ዓላማ ለማዋል፣ ብሎም በዝምታው ሰበብሕዝቡ ለውጡን በማይደግፉ አካላት እኩይ ተግባርሰለባ እንዳይሆን፣ተቃዋሚ ኃይሎች ሁለትባስቸኳይ መውሰድ ያለባቸውእርምጃዎች ያሉ ይመስለኛል። የመጀመርያው፣ ድሮውንም የኢሕአዴግን መግሥት ለመጣልና የፖሊቲካ ሥልጣን ለመጨበጥ እንጂ ያገሪቷን የማህበራዊና ኤኮኦሚያዊ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል መርሃ ግብር አልነበረንምና በዶር/ ዓቢይ የሚመራው የለውጥ ቡድን የዘረጋውን አገራዊ መርሃ ግብር በሙሉ ተቀብለንበአፈጻጸሙም ላይ ሕዝቡ በሙሉ ልቡ እንዲደግፋቸው እንጥራለን ብሎ በግልጽ ማሳወቅሲሆን፣ሁለተኛው ደግሞ፣ አይ! የለውጥ ቡድኑ ከዘረጋው አገራዊ የኤኮኖሚና ማህበራዊ መርሃ ግብር የተሻለ መርሃ ግብር አለን ካሉደግሞ ይህን አጄንዳቸውን አምጥተው በአደባባይ ሕዝቡን ማወያየት አለባቸው። ልክ የለውጥ ቡድኑ እያደረገ እንዳለው ማለት ነው። አለበለዚያ ግን፣ ይህ ባህላችን ያልሆነውና ያልለመድነው ዝምታ፣ ለዘመናት ተንቀሳቃሽ የነበረውን የተቃውሞ ትውልድ ባለህበት እርጋ ብሎ ለረጅም ጊዜያት ማስቆም ስለማይቻል፣ ጥቃቂን የሆኑና በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ጎጣዊ ችግሮችን አጉልቶ በማቅረብና አላሳፈላጊ የሆኑ ግጭቶችን በማስነሳትውድ ዋጋ ከፍለን የተጎናጸፍነውን ሰላምና መረጋጋትን፣ እንዲሁም በለውጥ ቡድኑ ቃል የተገባልንን ፈታኝ ግን ደግሞ ተስፋ ሰጪ ለሆነው ረጅም የዕድገት ጉዞ ትልቅ እንቅፋት ይሆናልና በጥብቅ አስቡበት ባይ ነኝ።

 

ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛልን።

 

****

 

ጄኔቫ 30 ጁላይ 2018 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com

 

 

 

 

Back to Front Page