Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሴራን እንታገል!

ሴራን እንታገል!

                                                         ታዬ ከበደ 06-26-18

ሰሞኑን በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በተለይ ከዚህ በፊት ሁከትና ግጭት ባልነበረባቸው አካባቢዎች ግጭት ተከስቷል። የግጭቱ እሳት ጫሪዎች ጥቅማቸው የተነካባቸው አካሎች የዘረጉትን ኔትዎርኮች ተጠቅመው አገራችን የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ አስበውና አቅደው ያደረጉት ነገር ነው።

የአገራችን ህገ መንግስት ከሰማይ በታች ህዝቦች ማንኛውንም ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ እንዲችሉ መብት አጎናፅፏቸዋል። አንዳንድ ሃይሎች ግን የግል ፍላጎታቸውን  ለማሳከት በህዝቦች ትክክለኛ ጥያቄ ከለላ ለማድረግ በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም ጥቅመኛ ፖለቲከኞች የትላንት ኢ-ፍትሃዊነትን ለማስቀጠል ወይም እስካሁን ላደረጓቸው ወንጀሎች ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ አገራችንን ወደ ቀውስ እንድታመራ ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ናቸው።

እነዚህ ሃይሎች የህዝብ አብሮነትና የአገር አንድነት የማይገዳቸው በመሆናቸው ነገን አሻግረው መመልከት የሚችሉ አይደሉም። በመሆኑም ህዝቡ ሴራቸውን በመገንዘብ ሰላሙን ራሱ በመጠበቅ ከፖለቲካ ነጋዴዎች ጋር መታገል ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አያሌ የአገራችን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉለት፣ አካላቸውን ያጡለትና ለተግባራዊነቱም የተረባረቡለት ነው። ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስማምተው ያፀደቁትና የሉዓላዊ ስልጣናቸው ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት ማናቸውንም ዓይነት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሰጠ ነው።

Videos From Around The World

የአገራችን ህዝቦች በሙሉ ፈቃደኝነታቸው ያፀደቁት ህገ መንግስት፤ በሀገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች ከመፍታት በላይ ዴሞክራሲን በአስተማማኝ ሁኔታ መተግበር ያስችላል።

ይህም የሀገራችን ህዝቦች ከሳይ በታች ማናቸውንም ህጎች መቃወም እንዲችሉ ያደረገ ነው። የህገ መንግስቱ አንድ ሶስተኛው ክፍል ስለ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያትት በመሆኑ ዜጎች ይህን መብቶቻቸውን መጠቀም እየቻሉ ሁከትና ብጥብጥ የሚሹ ሴረኞችን በመከተል ሰላማቸው እንዳይደፈርስ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አገራችን ውስጥ መቃወም ህገ መንግስታዊ መብት ነው። ይህ መብት ለዜጎች ትክክለኛ ፍላጎት እንጂ ለሴረኞች የፖለቲካ ንግድ መዋል የለበትም። እናም መብታችን የፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ እንዳይውል በንቃት መከታተል ይገባል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ችግር ዴሞክራሲ ብቻ አይደለም። ከሰላምና ከልማት አኳያ የተገኙት ውጤቶች አበረታች ቢሆኑም፣ አሁንም በህብረተሰቡ ውስጥ በሚሽሎከሎኩ ሴረኞች ሳቢያ በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች እየተፈጠሩ ነው።

ይህ ሁኔታም አንድም ኮሽታ ታይቶባቸው በማይታወቁ አካባቢዎች እንኳን ሳይቀር ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በሁሉም መስኮች የሚከሰቱ ችግሮችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ አድርጎ መፍታት እየተቻለ ሴረኞች መብቶቻችንን ነጥቀው ጥገኛቸው እንዲያደርጉንና እንድንጨራረስ በር እንዲከፍቱልን መፍቀድ የለብንም። ልንታገላቸው ይገባል።

ዴሞክራሲያዊ መብታችንን የመብቱ ባለቤት ከሆነው ህዝብ በስተቀር ጥቅማቸው የተነካባቸው ሴረኞች እንዲቀሙን በር መክፈት የለብንም። ምክንያቱም መብቱን ዜጎች ታግለው ያመጡት እንጂ ማንም የሰጣቸው ስላልሆነ ነው።

በተለይም ሴረኞች በአጎራባች ክልሎች ውስጥ መካከል ያለውን የወሰን መካከል ጉዳይ እንደ የግጭት መንስኤ አድርገው በመጠቀም በህገ መንግስቱ መሰረት የሚፈታውን የወሰን ችግር እያጦዙ ለሴራ ፖለቲካቸው እንዲጠቀሙበት እድል መስጠት አይኖርብንም።

እርግጥ ማህበረሰብ እስካለ ድረስ ግጭት መቼም ቢሆን ሊጠፋ አይችልም። እንኳንስ የህዝቦች ንቃተ ህሊና እየተገነባና ይበል የሚያሰኝ ደረጃ ላይ እየደረሰ ባለበት፣ መደመርና አንድነት እንዲሁም ፍቅርና ይቅርታ እየነገሰ በሚገኝበት ብሎም ኢትዮጵያዊነት በአንድ ጥላ ስር እያሰባሰበን ባለበት በአሁኑ ወቅት ቀርቶ እንዲህ የተካረረ ግጭት ኖሮ አያውቅም።

ይህ እውነታ የችግሩ መንስኤ ምንም ይሁን የሚያሳየን ነገር ቢኖር የከሰሩ ፖለቲከኞች ሴራቸውን ቀምረው ህዝቡን ለማጋጨት እየሰሩ መሆናቸውነ ነው። ሆኖም ሴራቸው ትናንት ያልሰራ በመሆኑ ዛሬም ሊሰራ አይችልም።

እርግጥ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መዋቀሩ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተመቸ ይመስለኛል። የአገራችን ህዝቦች የጋራ ማንነቶችንና እሴቶች ያሏቸው ናቸው። በሴረኞች የሚከሰቱ ችግሮች የስርዓቱ አሊያም የህዝቦች የዘመናት የተንሰላሰሉ እሴቶችን የሚወክሉ አይደሉም።

የአገራችን ህዝቦች ባለፉት ዓመታት ከመልካም አስተዳደር እጦት ውስጥ ነበሩ። ይህ ሁኔታ በጥቂት ወራቶች ውስጥ እየተቀየረ ነው። ችግር ሲፈጠር በአግባቡ መፍታት ያልቻሉ አመራሮች ራሳቸው በፈቃዳቸው የስራ ሃላፊነታቸውን እየለቀቁ ነው። ይህም የግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ጥቂት ግለሰቦች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች እንዳይኖሩ እያደረገ ነው።

ይህ ሀኔታም በመላ አገሪቱ ሰላሙ የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር የሚያስች ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና መንግሥት መላ አቅማቸውን አቀናጅተው በድህነትና በኋላ ቀርነት ላይ ይበልጥ እንዲዘምቱ የሚያደርጋቸው ነው።

ሕዝቦች በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን አገራዊ መግባባት ተመርኩዘው ኢትዮጵያን ለመለወጥ እንደ አንድ ማህበረሰብ በልማት አጀንዳዎች ላይ እንዲረባበረቡ ያችችላቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት አገራችን የምትከተለው ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ በአዲስ መልክ እየተሰራ ይገኛል።

የአገራችን ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር የጋራ አገራቸው የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማልማት አዲስ መንገድ ተከፍቶላቸዋል። ይህ መንገድ የሴረኞች ስግብግብ ፍላጎት የገታ ነው። ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና እኩልነትን ወደ መሬት አውርዶ ህዝቡ ጋ የሚያደርስ ነው።

በዶክተር አብይ የሚመራው አዲስ አመራር ህዝቡ ጥላቻንና ቂም በቀልን አሽቀንጥሮ እንዲጥል እያደረገ ነው። አገር በቁርሾ ስለማይመራ እንዲሁም ህዝብም በጥላቻ ስሜት የሚወዳትን አገሩን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ስለማይችል የተቀየሰው የፍቅርና የመደመር ስሜት ሴረኞችን ማስደንገጡ የሚገርም አይደለም።

ይሁን እንጂ ህገ መንግስቱ ከሰማይ በታች ሁሉንም ችግሮች የመፍታት አቅም ስላለው ዜጎች ጥያቄ ቢኖራቸውም በህገ መንግስቱ አግባብ ማቅረብ እንጂ የከሰሩ ፖለቲከኛ ሴረኞች መፈንጫ መሆን አይኖርበትም። ሰሴረኞችን የመታገያው ወቅት አሁን ነው።     

 

Back to Front Page