Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሰንደቅ ዓላማ የማንነት አርማ

 

ሰንደቅ ዓላማ  የማንነት አርማ 

ይቤ ከደጃች·ውቤ 10-13-18

    

     ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሉዓላዊ ሀገር  ብሔራዊ ኩራትና የማንነት መለያ አርማ ነው። በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሲጠየቁ “ባንዲራን ጨርቅ ነው” ብለው ነበር። አባባላቸው ግን በብዙ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ሲብጠለጠል ቆይቷል።በርግጥም ባንዲራ ጨርቅ ነው። ብረት ወይም እንጨት አይደለም።ባንዲራ ጨርቅ ስለሆነ ግን ሲያረጅ ወይም ሲቀደድ የትም ቦታ እንደ አሮጌ ጨርቅ ሊጣል አይችልም።ክብር ስላለው፣ ሀገርን ስለሚወክልና የሉዓላዊት ሀገር መለያ አርማ ስለሆነ ማለት ነው።  

     ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዥ ወራሪዎች ድንበርዋን ተከላክላ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች የጥቁር ሀገሮች መመኪያ ነች። ከአፍሪካ አገሮች አልፎ እንደ ጀማይካና ሀይቲን የመሳሰሉ የካሪቢያን ሀገሮችም  በቅኝ ግዛት በሚማቅቁበት ጊዜ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንደ ነጻነት አርማ ይመለከቱት ነበር።  ለዚህም  ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ ሀገሮች መካከል ሃያ የሚሆኑ አፍሪካውያን እህት ሀገራት ሰንደቅ ዓላማቸውን የቀረፁት ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ነው።ሰንደቅ ዓላማችን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች እና  የኢፌዴሪ መንግሥት ኤምባሲ ባለባቸው ሀገራት እንደ መለያ አርማ ይውለበለባል።

     ዘመናዊ የጦር መሣርያ ያልነበራቸው ዜጎቻችን የብዙ ኮሎኒያሊስት ሀገሮችን ወረራ በመከላከል እና አሳፍሮ በመመለስ ይታወቁ ነበር። ከአድዋ ድል በፊት የጣልያንን ቅኝ ገዥ ጦር ለመመከትና ድል አድርጎ አሳፍሮ ለመመለስ ከአዲስ አበባ ዘመቻው የተጀመረው በመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።በመስከረም መጨረሻ ሳምንት  በእግርና በፈረስ ተጉዘው በየካቲት 23 ቀን 1988ዓ·ም በአድዋን ድልን ተቀዳጅተው በቅኝ ግዛት ለሚማቅቁ ሀገሮች የነጭ ወራሪዎችን አሳፍሮና አሸንፎ መመለስ እንደሚቻል በማሳየት ምሳሌና ኩራት ሆነዋል።

Videos From Around The World

     ታዋቂው ገጣሚና ሰዐሊ ገብረክርስቶስ ደስታ “ሀገሬ” በሚል ርዕስ በ19 50ዎቹ ከገጠመው ረጅም ግጥም ስለ ሰንደቅ ዓላማ የሚከተለውን ቀንጭበነዋል

“··· መቅደስ ነው ሀገሬ፣አድባር ነው ሀገሬ፣

እናትና አባት ድኸው ያደጉበት፣

 ካያት ከቅድመ ሀያት የተረካከቡት፣

አፈር የፈጩበት፣ጥርስ የነቀሉበት።

ሀገሬ አርማ ነው የነፃነት ዋንጫ፣

                                  በቀይ የተጌጠ ባረንጓዴ ቢጫ፣

                 እሾህ ነው ሀገሬ በጀግናው ልጅ አጥንት የተከሰከሰ፣

ጠላት ያሳፈረ አጥቂን የመለሰ፣···”

 

    ሀገራችን ቀደም ሲል በሊግ ኦፍ ኔሽን ኋላም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሀገራችን አባል መሆን የቻለችው አፍሪካውያን ገና በቅኝ ግዛት በሚማቅቁበት ወቅት ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በነበራት ዕውቅና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽህፈት ቤቱንና የስብሰባ አዳራሹን አዲስ አበባ ከተማ አድርጓል። ቆይቶም ነፃ የወጡ የአፍሪካ ሀገሮች አሁን አፍሪካ ኅብረት የሚባለውን የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ ላይ እንዲቋቋም አድርገዋል። ይህም እኛ በቅኝ ግዛት ሳንገዛ በነፃነት በመኖራችን የሰጡን ትልቅ ዋጋና ዕውቅና ነው።

     የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለዜጎቻችን ከብሔራዊ ኩራትም አልፎ ለአፍሪካ ሀገሮች የነፃነት አርማ ሆኖ ከማገልገሉ በተጨማሪ ሀገራችንም በቅኝ ግዛት ውስጥ ሲማቅቁ ለነበሩ ሀገሮች የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ እንደነበር የሚታወቅ ነው። የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታጋይና በኋላም የሀገሪቱ መሪ የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግሉን አፋፍመው እንዲመሩ በወቅቱ መጥተው ኮልፌ በሚገኘው ፖሊስ ማሰልጠኛ እንዲሰለጥኑ ተደርጓል።ወደ ሀገራቸው ሲገቡ በአፓርታይድ መንግሥት ወደ እስር ቤት ቢወረወሩም ከእስር ነፃ ሲወጡ የሀገሪቱ መሪ መሆን ችለዋል።በመሪነት ከተመረጡ በኋላ መጀመሪያ ከጎበኟቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። ዚምባብዌንም ነፃ ለማውጣት በተደረገው ትግልም ሀገራችን የቁሳቁስና የስነ ልቦና ድጋፍ በመድረግ ውጤታማ ፍሬ አፍርታለች።       

     

     በስፖርት መድረኮች በእግር ኳስ በአትሌቲክስ በመሳሰሉት የአሸናፊ ሀገሮች ተወዳደሪዎችና ደጋፊዎች ደስታቸውንና ለሀገራቸው ያላቸውን አክብሮት የሚገልፁት ሰንደቅ ዓላማቸውን በመያዝና በማውለብለብ ነው። በአትሌቲክስ ሩጫ ስሟ በተደጋጋሚ የሚጠራው ኢትዮጵያ እንደ ኦሎምፒክ በመሳሰሉ ትልልቅ የስፖርት መድረኮች እነ ሻምበል አበበ ቢቂላና ምሩፅ ይፍጠርን የመሳሰሉ ብሔራዊ ጀግኖች የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል። በተለይ ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ለኢትዮጵያ ያስገኘው ድል ፋና ወጊ ነው። በአምስቱ ዓመታት የጣልያን ጦርነት ቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ ብላ  በዱር በገደሉ ተዋግታ ነፃ ከወጣች በኋላ በሮም አደባባይ ባንዲራችን እንዲውለበለብ ብሔራዊ መዝሙራችን እንዲውለበለብ ያስቻለ የምንኮራበት ብሔራዊ ጀግናችን ሲሆን የርሱን ፈለግ ተከትለው በዘመናችንም እነ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ የመሳሰሉ ሯጮች ባንዲራችንን በስፖርቱ ሜዳ ከፍ አድርገው በማውለብለብ የሀገር ክብርና ኩራት ሆነዋል።

   በሴቶችም ከነ ደራርቱ ቱሉ ፋጡማ ሮባ ጀምሮ በትልቁ ኦሎምፒክ የስፖርት አደባባይ ድላቸውንና ደስታቸውን  የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ብሔራዊ መዝሙራችንን በማዘመር አሳይተዋል። እነ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ (ጆሌ ዲባባ) መሠረት ደፋርን  የመሳሰሉ ወጣት ስፖርተኞችም ቀደም የስፖርት ጀግኖችን ፈለግ ተከትለው ተመሳሳይ አኩሪ ታሪክ ሠርተዋል።  

   በትምህርት ቤቶችም ጠዋት ተማሪዎች ወደ የክፍላቸው ከመግባታቸው በፊት በብሔራዊ መዝሙር ታጅበው ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ሉዓላዊ በሆኑ ሀገሮች ሁሉ የሚሠራበት ነው።ምንም እንኳን በሀገራችን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ቢከበርም በትምህርት ቤተች ደረጃ ተማሪዎች ብሔራዊ መዝሙር እየዘመሩ ሰንደቅ ዓላማ የማውጣትና የማውረድ ስነ ሥርዓት የለም ማለት ይቻላል።በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተማሪዎች የሪፑብሊኩ ዓርማ ያለበት ሰንደቅ ዓላማን በብሔራዊ ታጅበው ማውጣትና ማውረድ መተግበር አለባቸው።

     ሰንደቅ ዓላማችን መደበኛ ቀለሙ እንዳለ ሆኖ ዓርማዎቹ ግን በየመንግሥታቱ ሲቀያየሩ ነበር። በንጉሡ ዘመን የአንበሳ አርማ ፣ በወታደራዊው ደርግ ዘመንም የራሱ አርማ የነበረው ሲሆን የኢፌዴሪ መንግሥትም የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች እኩልነት መሀሉ ላይ የሚወክል አርማ ተደርጓል።

     በዘውዳዊውም ሆነ በወታደራዊው አገዛዝ ዘመናት የነበሩት መንግሥታት በትምህርት ቤቶች ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል መደበኛ ቀለም ያለው ባንዲራ ይሰቀል እንደነበር ይታወሳል።በኢፌዴሪ መንግሥት የምንገለገልበት ሰንደቅ ዓላማ ዓርማው ላይ ያለው ቀለም አንዳንዴ ደማቅ ሰማያዊ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ ፈዛዛ ሰማያዊ ነው።ለዚህም መፍትሔ መሰጠት አለበት።  በየመሥሪያ ቤቱ ያሉትን ሰንደቅ ዓላማዎች አርማ ቀለም በማየት ልዩነታቸውን መታዘብ ይቻላል። አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት በኦፊሻል የሚጠቀምበትን ወይም በሕግ የተደነገገውን ሰንደቅ ዓላማ  እየተጠቀመ ዜጎች መደበኛ ቀለም ያላቸውን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም ቢችሉ ጥሩ ነው የሚል ግምት አለኝ።

      በንጉሡም ሆነ በደርግ አገዛዝ  ዜጎችና ተማሪዎች አርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማ ያዛችሁ ተብሎ የተከሰሱ መኖራቸውን አላነበብኩም። በሀገራችንም የፌዴራሉ አርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማ መያዝ ሕገ መንግሥቱን መቃወም ነው የሚል ሃሳብ የተነሳው ከ19 97 ዓ·ም በኋላ ነው።ስለዚህ ሁለቱንም ጎን ለጎን አጣጥሞ መጓዝ ይቻላል የሚል አመለካከት አለኝ።

      የክልል ሰንደቅ ዓላማዎችና የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችም የየራሳቸው አርማ ይኖራቸዋል።ይህ ማለት ግን አርማቸው ሲውለበለብ የሉዓላዊት ሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማም ቢይዙ ለነርሱ ክብርና ኩራት ነው። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የእናት ሀገራቸው መለያ ዓርማ መሆኑን ማስተዋል፣ አንድ ጣት የማይሞሉ ሰዎች ጡት ቆርጠዋል ተብሎ በሚናፈስ አሉባልታ ሉዓላዊት ሀገርን መጥላት ተገቢ አይደለም።         

            በኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መስከረም በገባ ሁለተኛ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር ቆይቷል።የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ ሦስትን መነሾ በማድረግ የወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 በየዓመቱ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን እንዲከበር ተደንግጓል ። በዚህም መሠረት ለአምስት ዓመታት ከተከበረ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ·ም  በዓሉ በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ሰኞ እንዲከበር ወስኗል።

     በዚህም መሠረት የ2011 ዓ·ም ለ11ኛ ጊዜ መስከረም 5 ቀን የሚከበረው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች በመከለከያና በፖሊስ ሠራዊት ማዕከላት  በተመሳሳይ 4፡30 ላይ በብሔራዊ መዝሙር ታጅቦ የፌዴራሉን መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል የሰንደቅ ዓላማ ቀን ይከበራል።የሰንደቅ ዓላማ ቀን መከበሩ የመደመርን መንፈስ ለማጎልበት የሚያስችል ትልቅ መሣርያ ነው።በመሆኑም በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በብሔራዊ መዝመር ታጅበው ለትምህርት ሲወጡና ሲገቡ ሰንደቅ ዓላማ እንዲያወጡና እንዲያወርዱ ቢደረግ የበለጠ ዋጋ ይኖረዋል።   

     በተለይ በኢፌዴሪ የተወካዮች ምክር ቤት በሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የሚከበር ሲሆን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንዶች ይገኛሉ።

      በ2011 ዓ·ም ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረው  ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ከተመረጡ ወዲህ  ለመጀመሪያው ሰኞ ጥቅምት አምስት ቀን ይከበራል  ። በሀገራችን በየቦታው ሲታዩ ቀውስ ተወግዶ የኢፌዴሪ መንግሥት የለውጥ ርምጃዎች በወሰደ መንፈቀ ዓመት እና  ኢህአዴግ ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና”በሚል መሪ ቃል  ካካሄደው  ጉባዔ  እና ዶክተር ዐቢይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀ መንበር እንዲሆኑ በተመረጡ ሰሞን የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

     በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ሦስት መሠረት“ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ፣ከታች ቀይ ሆኖ ብሔራዊ አርማ ይኖረዋል ።ሦስቱም ቀለማት ዕኩል አግድም የሚቀመጡ ሲሆን ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ አርማ ኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች በእኩልነት እና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል” ብሎ ይደነግጋል ።

     ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የወጣው የሰንደቅ ‘ላማ አዋጅ ቁጥር 654/ 2001 ሰንደቅ ዓላማ የሪፑብሊኩ ሉዓላዊነት እና የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የመሠረቱት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑን ይገልፃል።የቀለማቱ ትርጓሜው

    አረንጓዴው የሥራ የዕድገት እና ልምላሜ

    ቢጫው የተስፋ የፍትሕ እና ዕኩልነት

    ቀዩ  ለፃነት እና ለእኩልነት የሚደረግ መስዋዕትነት ምልክት በመሆን ያገለግላሉ። 

     የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የሀገሪቱን የማንነት ጥያቄዎችም በሕግ አግባብ እንዲፈቱ ማድረግ፤የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠናከር ፣የተሃድሶ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ማስቀጠልና ሀገራዊ ለውጡን ወደፊት ማስኬድ መቻል በተጀመረበት  የመደመር መንፈስን በሚያጎለብት መልኩ የሚከበር በመሆኑ ብሩህ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።

    

 

 

    

 

Back to Front Page