Back to Front Page


Share This Article!
Share
የተጀመረው ለውጥና በትግራይ ያለው ሁኔታከትግራይ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ግንባር

የተጀመረው ለውጥና በትግራይ ያለው ሁኔታ

ከትግራይ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ግንባር

በአገራችን ውስጥ ባንድ በኩል የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በመፍታት፣ አስችኳይ ጊዜያዊ አዋጁን በማንሳት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደ ጠላት ሳይታዩ ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂዱ በመጋበዝ፣ ከኤርትራ ጋር የሰላም ውይይት በመጀመር ወዘተ.. አፋኙ ስርዓት እየተወገደ እንዳለ የሚያመለክቱ እርምጃዎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስለተወሰዱ ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመሸጋገር ግን ነጻና ገለልተኛ የሆኑ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች መገንባት ያስፈልጋል። በተቋሞቹ ግምባታም ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና በአጠቃላይ ህብረተ ሰቡ ሊሳተፍ ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ግን በማንነት ላይ የተመሰረቱ ደም አፋሳሽ፣ ሃብት አውዳሚና አለመተማመንን የሚያሰፉና የአገራችን አንድነትን የሚያላሉ ክስተቶች እየተባባሱ በመሄድ ላይ ስላሉ በህዝባችን ላይ አደጋ ያንዣብባል፡፡

የክልሎች ያስተዳደርና የፖሊስ ተቋሞች በአቅም ማነስ ይሁን በቸልተኝነት ወይም በእቅድ ወጣቶች በጥላቻ ተቀስቅሰውና በስሜት ተነሳስተው በዜጎች ላይ የሚወስዷቸውን አስቃቂና አሳፋሪ ድርጊቶች በተሟላ መንገድ ሲገቱ አይታይም፡፡ የዚህ ችግር መቀጠልና አለመቀጠል በዋናነት በተወሰኑ የክልል አስተዳደሮችና በፌደራል መንግስቱ እጅ ነው፡፡

Videos From Around The World

በዚህ በኢትዮጵያ ደረጃ ተስፋና አደጋ ጎን ለጎን ባሉበት ሁኔታ በትግራይ ውስጥ ከተስፋው ጋር ከሚሄዱት ለውጦች፣ ተከልክለው የነበሩ ተቃዋሚዎች መመለሳቸውና ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ በጋራ መድረክ መወያየታቸው እንደ አብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ግብታዊ የሆኑ ዜጎችን የሚያሸማቅቁ በወጣቶች የሚፈጻሙ ድርጊቶች ባይኖሩም ገዢው ፓርቲ በህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የግፍ እርምጃዎች መፈጸም አላቆመም፡፡ ለምሳሌ በነሓሴ 2 ቀን 2010 ዓ/ም የዓረና የማ/ኮ አባልና የዓብይ ዓዲ ጽህፈት ቤት ሓላፊ፣ አቶ ዜናዊ አስመላሽን ለማፈንና በሳቸው ላይ አደጋ ለማድረስ በሰላም ጣብያ አቃቤ ህግ፣ በአቶ ተፈራ ትእዛዝ መሰረት ሃለቃ ፀጋዘኣብ ሃይሉ የሚባል ሰው ተልኮ ነበር፡፡ ሃላቃ ፀጋዛአብ የአቶ ዜናዊ ወንድም አቶ ገብረዋህድ አስመላሽን በስፍራው ስላገኘ የአቶ ገ/ዋህድን እግር በፋስ በመደብደብ ከባድ ጉዳት አድርሷል፤ ከዛም አልፎ የተጠቂውን እንስሳት በፋስ ደብድበዋል፡፡ አቶ ገ/ዋህድ ህክምና ከተደረገላቸው በሁዋላም ያገዛዙ ፖሊስ ተረኛ ነርሷን በማስፈራራት ጉዳቱን የሚመለከት የፅሑፍ ማስረጃ እንዳይሰጥ ከልክለዋል፡፡

ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት የለውጡን ተስፋ የሚያጭልም ነው፡፡ የህወሓት አመራርም ቢያንስ በከፊሉ የለውጡን ማዕበል የተቀበለ በመምሰል በለመደው የአፈና አሰራር ለመቀጠል የፈለገ ስለሚመስል በትግራይ ውስጥ ለለውጡ ከፍተኛ ትግል እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በትግራይ ክልል የለውጡ ተስፋ ለመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ ከተቀነባበረ በሁዋላ በተግባር የቆየው ግፍ መቀጠሉ ያሳስባል። ከዚህ በባሰ ደግሞ ከለውጡ ጋር እንደመጣ የሚገለጽ አደጋ አለ፡፡ በዚህ መሰረት ይህ አደጋ ከትግራይ ህዝብ ህልውናና ደህንነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ስለሚገለፅ የትግራይ ህዝብን ህልውናንና ደህንነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ፓርቲዎች ያሉት ልዩነቶች በሁለተኛ ደረጃ እንዲታዩና በመካከላቸው ለአንድነት ቅድሚያ እንዲሰጠው በመገለጽ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጥያቄ ግን በእርግጥ በትግራይ ህዝብ ህልውናና ደህንነት ላይ የተጋረጠ አደጋ አለ ወይ? የሚለው ነው።

በእርግጥ በትግራይ ተወላጆች ላይ በተለያዩ ክልሎች ጥቃትና ግድያ እንደሚፈጸም የታወቀ ነው። ለአብነት በቅርቡ ሁለት የትግራይ ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል፣ በወለጋ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። በአማራ ክልልም በጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ አካባቢ 3 የትግራይ ተወላጆች ተገድለዋል። እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የትግራይ ተወላጆች እየተፈናቀሉ ወደ ትግራይ እንደሚሄዱ ብዙ መረጃዎች አሉ። ይህ በብሄር ምክንያት የሚደረግ ግድያ፣ እንግልትና መፈናቀል ግን በትግራይ ተወላጆች ብቻ የተወሰነ አይደለም። የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣የወላይታ፣ የሶማሌ ወዘተ ተወላጆችም በተለያዩ ክልሎች ተገድለዋል፣ ተፈናቅለዋል። ስለሆነም ይህ ችግር አጠቃላይ የአገሪቱ ችግር ነው። የዚህ ችግር መንስኤ ደግሞ በመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነው የብሄር ፌደራሊዝምና የህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ነው።

በኛ እምነት የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ በሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ግድያና መፈናቀል አስነዋሪ ድርጊትና ወንጀልም ስለሆነ መወገዝ አለበት። ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና ለአገራችን አንድነትም ትልቅ አደጋ

 

ነው። ስለሆነም ይህን ችግር ለመፍታት ሁሉም አገር ወዳድና ዴሞክራሲያውያን የሆኑ ዜጎችና ድርጅቶች ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

የህወሓት አገዛዝ ግን የትግራይ ተወላጆችን እንግልት፣ ግድያና መፈናቀል በትግራይ ህዝብ ህልውና ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው እያለ ፍጹም የዲሞክራሲ መብት የሌለውን የትግራይ ህዝብ ፍርሃት እንዲያድረበትና ከጎኑ እንዲሰለፍ እየጣረ ነው። የህወሓት መሪዎች ይህንን የሚያደርጉት የትግራይን ህዝብ እንደ መሳሪያ በመጠቀም በሚካሄደው ለውጥ ምክንያት ስልጣንና ጥቅም እንዳያጡ ለመከላከል ነው።

በህወሓት የሚሳለው ምናባዊ አደጋ በአንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዋችም ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል። ምናባዊ አደጋ መሳል አንጻራዊ ሰላም ባለበት ሁኔታ ነፃነትን የማጥበብ አደጋን ያስከትላል፤ ልዩነትን በመደበቅ ያስተሳሰብ ጥራት በህብረተሰቡ እንዳይሰራጭና ህዝብ ነፃ ሆኖ በመወያየትና በመደራጀት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዳያደርግ ይገታል፡፡ ባጭሩ ዴሞክራሲ በትግራይ እንዳይሰፍን የሚደረግ መሰሪ ድርጊት ነው።

ስለዚህ በምናባዊ አደጋ በማሳበብ ለለውጡ ወሳኝ የሆነውን የዴሞክራሲና የነፃነት መንፈስ እንዳይሰፍን መግታት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለም በትግራይ ማሰቀጠል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የህወሓት መሪዎች እና ተካተዮቻቸው የኢህአዴግ አሰራር እና ደምብ እየተጣሰ ነው እያሉ በየጊዜው የሚለፍፉት እንዲሁም በቅርቡ የህወሓት ም/ሊቀመንበር ወደ ነበርንበት አሰራር መመለስ አለብን ብለው የተናገሩት ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አሰራር እንመለስ ማለታቸው ነው ። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ግን ከሃቀኛው ዴሞክራሲ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያን ህዘብ ለ27 ዓመት ያንገሸገሸው የአፈና፣ የግፍና የድንቁርና አስተሳሰብና አደረጃጀት ማለት ነው፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይወገዳል!

የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በዴሞክራሲያዊ ስርአት ይኖራል!

(Forwarded by Tesfay 08-28-18)

Back to Front Page