Back to Front Page


Share This Article!
Share
የለውጡ ፍሬዎች

የለውጡ ፍሬዎች

አዲስ ቶልቻ 08-28-18

ኢህአዴግ 5ኛውን ዙር የመንግስት የስልጣን ዘመኑን ጀምሮ ወራት እንኳን ሳያስቆጥር ነበር 2008 ዓ/ም መግቢያ ላይ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ የገጠመው። ይህ ህዝባዊ ተቃውሞ ኢህአዴግ ራሱን ወደውስጥ በጥልቀት እንዲመለከት አስገድዶታል። በዚህ የውስጥ ምልከታ የከፋ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር እንዳለበት ገምግሟል። እንዲሁም እጅግ በፍጥነት እያደገ የሚሄውን የህዝቡን የልማት ፍላጎትና የዴሞክራሲ ጥማት ማርካት እንዳልቻለም ገምግሟል። በዚሁ መነሻነት ራሱን በጥልቀት ለማደስ ወስኗል። ይህ ብጥለቅት የመታደስ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ በሚያስተዳድራቸው ክልሎችና በፌደራል መንግስት ውስጥ አዲስ የተሃድሶ ወይም የለውጥ አመራር ወደሃላፊነት እንዲመጣ አድርጓል። ወደሃላፊነት የመጣው አዲሱ የለውጥ አመራር ህዝቡን አስከፍተው ለተቃውሞ ያነሳሱ ችግሮችን ለማቃላል ሲፍጨረጨር ቆይቷል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነሃሴ 14 እስከ 16፣ 2010 ዓ/ም ባካሄደው ስብሰባ ያለፉት ሶስት ወራትን በልቀት የመታደስ የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውሳኔዎች አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገምግሟል። ቀጣይ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል። በዚህ ጽሁፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የገመገማቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ወሳኔዎች አፈጻጸም ግምገማ እንዲሁም ያስቀመጣቸውን ቀጣይ አቅጣጫዎች በተጨባጭ ካለው እውነታ አንጻር ለመመልከት እሞክራለሁ።

Videos From Around The World

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የሚተላለፉ ውሳኔዎች የአፈጻጸም ድክመት ይታይባቸው እንደነበረ፣ አሁን ግን የአመራር ፈጠራ ታክሎባቸው ፈጣንና ውጤታማ አፈጻጸም መመዝገቡን ገምግሟል። በፖለቲካው መስክ በተለይ ባለፉ ሶስት ወራት የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን የሚያሻሽሉ እርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወቃል። የስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ በግምገማው ካነሳቸው መሃከል ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ወንጀሎች የተከሰሱና የተፈረደባቸው እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸው ተጠቃሽ ነው። በውጭ ሃገራት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ ለነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች የተላለፈው ጥሪና በዚህ መሰረት በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅሰቀሴ ውስጥ ለመሳተፍ በርካታ የፖለቲካ ቡድኖችና ግለሰቦች ወደሃገር ቤት መመለሳቸውንም ስራ አስፈጻሚው በስኬትነት ጠቅሶታል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚያውቀው፣ ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ወንጀሎች ተከሰው የነበሩና የተፈረደባቸው በበዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ከእስር ተፈትተዋል። ከእነዚህ መሃከል ቀድሞ ወደነበሩበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተመለሱ በርካቶች ናቸው። ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ በቀለ ገረባን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች አሁን በንቃት ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳሰትፎ እያደጉ ነው። እንቅስቃሴያቸው በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ በመፎካከር የተገደበ አይደለም። አሁን የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ለለውጡ ቀጣይነት አስፈላጊ የሆነው ሰላም እንዲረጋገጥ ከደጋፊዎቻቸው ጋር እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ ሁሉንም ነገር በመቃወም ታጥሮ ከቆየው የተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ባህል የተለየ አካሄድ እንደ አንድ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነው።

ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ወንጀሎች ታስረው የነበሩ ዜጎችን ከመፍታት በተጨማሪ በውጭ ሃገራት የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ያካሂዱ ለነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ ተላልፏል። በረዚህ ጥሪ መሰረት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደሃገር ቤት ገብተዋል። ከእነዚህ መሃከል በአንጋፋ የኦሮሞ ነጻነት ታጋዮች ሌንጮ ለታና ዲማ ነገዎ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ቀዳሚው ነው። በኤርትራና በግብጽ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮችም ወደሃገር ቤት ከተመለሱ ወራት እየተቆጠሩ ነው። በአሜሪካ ይንቀሳቀሱ የነበሩት አምባሳደር ካሳ ከበደ፣ ጃዋር መሃመድ ወዘተ የመሳሰሉ የፖለቲካ አክቲቪስቶችም ወደሃገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል።

ከዚህ በተጨማሪ በሃገሪቱ ጸረሽብርተኝነት ህግ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) እና ግንቦት 7 የሽብርተኝነት ፍረጃቸው እንዲነሳ መደረጉ ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ ለእነዚህና ሌሎችም በትጥቅ ትግል ላይ ለነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦች በሙሉ ምህረት ተደርጓል። የሽብርተኝነት ፍረጃን የመነሳትና የምህረቱ ዓላማ የፖለቲካ ቡድኖቹና ግለሰቦቹ ወደሃገር ቤት ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። በዚህ መሰረት በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራውና የነጻ አውጪ ሰራዊት አሰልፎ በኤርትራ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወደሃገር ቤት ለመመለስ ከመንግስት ጋር ድርድር አካሂዶ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የተወሰኑ አመራሮቹም ወደሃገር ቤት ገብተዋል። ግንቦት 7 የተባለውም ድርጅት በቅርቡ ወደሃገር ቤት እንደሚገባ አሳውቋል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ የተሃድሶው/የለውጡ አመራር በወሰዳቸው እርምጃዎች የተገኙ ውጤቶች በሃገሪቱ የነበረውን አግላይ የፖለቲካ አካሄድ በመድፈቅ አካታችና ሰላማዊ አካሄድን አጎልብቷል። ይህ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ከዚሁ ከፖለቲካው ሳንወጣ በዲፕሎማሲው መስክም ውጤታማ አፈጻጸም መከናወኑን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገምግሟል። በተለይ ከኤርትራ ጋር ለሃያ ዓመታት ያህል የቆየው ጠላትነት ተሽሮ፣ በጠንካራ የህዝብ ለህዝብና የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት ተተክቷል። ይህ ከሶስት ወራት በፊት ይሆናል ተብሎ ያልተጠበቀ ፈጣንና ትልቅ ስኬት ነው። ስራ አስፈጻሚ የሰብአዊ መብት አያያዝን ማሻሻል የስቻለ እርምጃ መወሰዱን ገምግሟል። በዚህ ረገድ በተለይ በማረሚያ ቤቶች የነበረውን አሰከፊ የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያሻሽል ተጨባጭ ስራ ተከናወኗል። በጸጥታና ህግ አስከባሪ ተቋማት ውስጥም የሰብአዊ መብት አያያዝን ማሻሻል የሚያስችል የሪፎርም ሰራ ተሰርቷል። እነዚህ ሁኔታዎች በሃገሪቱ ያለውንና የሃገሪቱን ገጽታ ያበላሸውን አስከፊ የሰብአዊ መብት አያያዝ በማሻሻል ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በመደበኛ ስብሰባው የገመገመው ሌላው ጉዳይ ኢኮኖሚን የሚመለከት ነው። ግምገማው በተለይ ሃገሪቱ ገጥሟት የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር በማስተካካል የተከናወኑ ወጤታማ ስራዎች ላይ አተኩሯል። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ሃገሪቱ ለዜጎች መሰረታዊ የሆኑ የመድሃኒት ፈላጎቶችን እንኳን ማሟላት እስኪያቅት ደረስ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገጥሟት ነበር። ይህ ችግር ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ መንቀሳቀስ የማይችልበት፣ ዜጎች በመድሃኒትና ሌሎች መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች እጥረት ለአስከፊ አደጋ ይጋለጡ የነበረበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀሬ ነበር። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ከዚህ አጣዳፊ ችግር ለመውጣት በወሰዳቸው የአመራር ብልህነት የታከለባቸው እርምጃዎች አሁን ችግሩ በጉልህ መቃለል ችሏል።

በማህበራዊ መስክ የተወሰዱ እርምጃዎችና የተገኙ ወጤቶችንም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገምግሟል። በዚህ ረገድ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን መከፋፈል በእርቅ እንዲፈታ ለማድረግ የተወሰደውን እርምጃና የተገኘውን ውጤት ስራ አስፈጻሚው በመግለጫው ላይ እንደ አብነት ጠቅሶታል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመገለጫው ላይ አይጥቀሰው እንጂ በኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን መከፋፈል በእርቅ የመፍታት እርምጃ መወሰዱንም እናስታውሳለን።

እንግዲህ መንግስትና ሃይማኖት በህገመንግስት እንዲለያዩ መደረጉ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥና በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል ግን ከሃይማኖቶቹ አመራሮች አልፎ ህዝቡንም ከፋፍሎት ነበር። ይህ እስከ ህዘቡ የዘለቀ መከፋፈል የብሄርና የፖለቲካ አቋም ቅርጽ የያዘበትን ሁኔታም ታዝበናል። በዚህ ምክንያት በመንግስትና በህዝብ መሃከል ያለው መተማመን ላይ ጉልህ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቷል። እንዲሁም የሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተዕእኖ የማሳደር አቅም ፈጥሮ ነበር። በመሆኑም መንስት ይህን ታሳቢ በማድረግ በተመጠነ ጣልቃ ገብነት በሁለቱ ሃይማኖቶች ውስጥ የተፈጠረውን መከፋፈል በእርቅ ለመፍታት የወሰደው እርምጃ እጅግ አስፈላጊ ነበር።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በቀጣይ ግንባሩ የሚያከናውናቸው ተግባሮችን የሚመለከት  አቅጣጫም አስቀምጧል። አንደኛው ቀጣይ አቅጣጫ ባለፉት ሶስት ወራት የተከናወነውን ለኢትዮጵያዊነት ተገቢውን ክብርና ቦታ እንዲያገኝ የማድረግ ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ነው። ይሁን እንጂ ይህ የኢትዮጵያዊነትን ሰሜት የማጠናከር ተግባር ከብሄራዊ ማንነት ጋር አየተሰናሰነ መቅረብ እንደሚገባው ነው ኮሚቴው አቅጣጫ ያስቀመጠው።

በመሰረቱ የኢፌዴሪ ህገመንግስት ዋነኛ ተኩረት አንድነት ያላትን ኢትዮጵያ መፍጠር መሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አንድነት ልዩነቶችን የሚጨፈልቅ ሳይሆን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን እንደጠበቁ፣ ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ  በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት ያላት ኢትዮጵያ መገንባት የሚመለከት ነው። ህገመንግስቱ ስራ ላይ በዋለባቸው ያለፉ ሁለት አስርት ዓመታት ከብሄራዊ ጭቆና ወጥተው ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የጀመሩ የሃገሪቱ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ማንነታቸው ላይ ያተኮሩበት ሁኔታ ተስተውሏል። ይህ የኢትዮጵያዊነት እሴት እንዲደበዝዝ የማድረግ አዝማሚያ አምጥቷል። ይህን ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል።

በዚህ መሰረት ባለፉት አራት ወራት የኢትዮጲያዊነት ስሜት እንዲያንሰራራ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተሰርቷል። በተለይ የለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ባገኙት አጋጣሚ በሙሉ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን ለመገንባት ጥረት አድርገዋል። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የኢህአዴግ ስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ የወሰነው። ይሁን እንጂ ይህ እጅግ ከተለጠጠ በሃገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዘቦች ዘንድ ማንነታችው የመጨፍለቅ ስጋት የተጋረጠበት አድርገው እንዲወስዱ የሚያደርግ ሁኔታ መፈሩ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያዊ አንድነትና ብሄራዊ አንድነት እየተሰናሰነ እንዲጎለብት ማድረግ አስፈላጊ ነው። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ይህነኑ ነው የወሰነው።

በአጠቃላይ፣ ባለፉት ሶስትና አራት ወራት ወደሃላፊነት የመጣው የኢህአዴግ የለውጥ አመራር የሰላምና መረጋጋት ፈተናዎች የገጠሙት መሆኑ ባይካድም፣ ከላይ እንደተገለጸው በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ወጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተገኙ ስኬቶች በህዝቡ የእለት ተዕለት ቁሳዊና መንፈሳዊ ህይወት ላይ ለውጥ እንዲያመጡና እርካታ እንዲፈጥሩ ማድረግ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ወሬ ሆኖ ነው የሚቀረው። ይህ የዕለት የእለቱን ከመመልከት አልፎ አርቆ መመልከትን በተለይ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ ይፈልጋል። በየወቅቱ የሚገጥሙ ትኩሳቶችን በማብረድ እፎይታ ለማግኘት ብቻ የሚደረግ ሩጫ አድሮ ውሎ ጎልቶ የሚበቅል ውስብስብ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው። እናም የተሃድሶውን ፍሬዎች የህዝቡ ገበታ ላይ ለማቀረብ ኢህአዴግ በስትራቴጂ የሚመራ መሆን ይጠበቅበታል።

Back to Front Page