Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጂኦ ፖለቲካዊ ፍጥጫና የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ

ጂኦ ፖለቲካዊ ፍጥጫና የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ

ገብረግዚኣብሄር ሃይሉ 11-16-18

 

እ.አ.አ 1991 የሶቬት ህብረት መፈረካከስ ተከትሎ ለ18 ዓመታት የዓለማችን ልዕለ ሃያልነት ጨብጦ የቆየው አክራሪ የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም መሆኑ ሁላችንን ያግባባናል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የርእዮተ- ዓለም አሸናፊ ነኝ በማለት የተገነባው ስነ ልቦናዊ ጫና አሁን በዓለማችን ለተፈጠሩ አዳዲስ እድገቶች ለመቀበል አዳጋች ሆኖባቸው ይገኛል፡፡

እስከ 1983 ዓ.ም ኢትዮጵያን ያስተዳደር የነበረው የደርግ ሰርዓት የዓለማችን ርእዮተ ዓለም አስቸጋሪ በሆነበት ሰዓት በህዝቦች የተደራጀ ትግል መገርሰሱን ተከትሎ በሃገራችን ከፍተኛ ጫና መከሰቱን ይታወቃል፡፡ ፍፁም አስቸጋሪ በሆነበት ወቅት ኢትዮጵያን በአዲስ መልኩ ማስተዳደር የጀመረው ኢህአዴግ ከዓለማዊ ርእዮ-ተዓለም ይልቅ የህዝቡን ጥያቄ እንዴት ልመልስ የሚል ህዝባዊ ውሳኔ መከተሉን ይታያል፡፡ ኢህአዴግ ከመነሻውም ጀምሮ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተደራጀ ሃይል እንደ መሆኑ መጠን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለህዝብ ጥቅም ከሚሰሩ ማናቸውም ሃይሎች በትብብር ለመስራት ራሱን ማስማማት ችሏል፡፡

Videos From Around The World

ባለፉት 27 ዓመታት የተለያዩ የምዕራቡ ዓለም ርእዮተ- ዓለም አቀንቃኝ ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ጫና ተግባራዊ ለማድረግ ያልሞከሩበት ጊዜ ነበረ ለማለት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ጫናዎችን ተጋፍጦ መሄድ የቻለ አመራር በመሆኑ ሃገሪቷ ተስፋ ሰጪ ጎዳና ላይ መግባት ችላለች፡፡ ፈጣንና ተከታታይ የባለ-ሁለት አሃዝ እድገት ባለ ቤት በሆነች ሃገር ውስጥ በርካታ ዜጎች ከድህነት ወለል ወጥተዋል፡፡ የከተማና የገጠር መሰረተ ልማት፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተስፋፍተዋል፡፡ በእኛ መንገድ ካልሆነ ማደግ አይቻልም እያሉ ሲማፀኑ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ የዚህ ሃገር ተስፋ እያጓጓቸው መጥቶ ነበረ፡፡

አሁን በሃገራችን እየሆነ ያለው ጉዳይ ግን የዚህ ፈጣን ጉዞ ሌላ መአዘን የያዘ ይመስላል፡፡ በሃገሪቷ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዳይ ከኢኮኖሚያዊ እድገቱ በተጓዳኝ ማደግ ተስኖት መቆየቱ ግልፅ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ፈጣን ቢሆንም በበርካታ ማነቆዎች የተተበተበ ነበረ፡፡ ከግብር ሰርዓቱ አንስቶ የተለያዩ ማነቆዎች እና ጣልቀ ገብነቶች እንዲሁም አሻጥሮች የበዙበት ሁኔታም ታይተዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ዜጎች አሁንም በድህነት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ተደማምረው በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ መቀስቀሳቸው ይታወቃል፡፡ ለአሁኑ ለውጥ መነሻነትም ከፍተኛ ድረሻ ተጫውተዋል፡፡ ለውጡ የስርዓት ለውጥ ነው ባይባልም እስከ አሁን ተወዝፈው በቆዩ በርካታ ጉዳዮች ላይ ፈጣን ውሳኔ በመስጠት የህዝቡ ቅሬታ ቀስ በቀስ ማርገብ አስችሏል፡፡

የሰው ልጅ ሁሌም ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ከለውጥ ያመለጠ አካልም አይገኝም፡፡ በሃገራችን የታየውን ግን እንዲሁ በቀላሉ ሊታይ የሚገባ አይደለም፡፡ በርካታ ጂኦ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እየታየበት ነው፡፡ ለውጡን ኢህአዴግ በፈለገው ሳይሆን እነሱ በፈለጉት መሰረት እንዲሁን ሲጠባበቁና ከፍተኛ በጀት መድበው ሲያስተባብሩ የነበሩ አካላት መኖራቸው አሁን የሚታየው ጂኦ ፖለቲካዊ ፍጥጫ እውነተኛ ምልክት ነው፡፡

የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩ ሄርማን ኮሆን ሕዳር 6 ቀን 2011ዓ.ም ባስተላለፉት የትዊተር መልእክት እንዲህ ይላል ቻይና በጅቡቲ ያላትን ከፍተኛ ተፅዕኖ ለመቋቋም አሜሪካ ከኤርትራ ጋር እንድትተባበር ሴናተር ሮቢዮ እና ኩን የወዱት እርምጃ መስተዋል የተሞላበት ነው ይላል፡፡ በእኔ እምነት ኢትዮጵያም ከዚህ ያመለጠች አይመስለኝም፡፡ አዲሱ አመራር ከኤርትራ መሪው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሙጥኝ ማለት ከኤርትራና ከኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት አንፃር እንዴት እንደተመዘነ ለኔ ጥያቄ ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ስምምነቱ እጅግ ጥሩ ቢሆንም በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ማስታረቅ ሰበብ በዚህ ቀጠና ያለው የጣልቃ ገብነት እሽቅድምድም ግን እጅግ አስጊ ይመስላል፡፡

እንደ ሄርማን ኮሆን አባባል በቀይ ባህር ሊያጡት የነበረ የበላይነት ለማስመለስ በኤርትራ ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ ማንሳት የሴናተሮቻቸው ጉትጎታ አድንቀዋል፡፡ ፕረዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ሳዉዲ ዓረብያ እና የተበባሩት አረብ ኤሜት ድረስ በመሄድ ዳጎስ ያለ ሽልማት እንደተበረከተላቸው በሚዲያዎች የተላለፈ ጉዳይ ነው፡፡ አሜሪካ በእነዚህ አራት ሃገራት ሁለት (የምስራቃዊ ቀይ ባህር እና ሁለት ምዕራባዊ ቀይባህር) አማካኝነት የበላይነቷን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ነው፡፡ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ በየመን የሁቲ አማፂዎች ላንዴና ለመጨረሻ በማጥፋት የሳውዲ ኢምፓየር ማስፋፋት ትልቁ ዓላማ ያደረገው ዘመቻ አሁን በአሜሪካዊያን የተደገፈ ይመስላል፡፡

አሜሪካ በሰሜንና በምዕራቡ የቀይ ባህር ዳርቻዎች የራሷን ተላላኪ መንግስታት በማስቀመጥ የማይቀረውንና ጡንቻውን እያሳበጣ ለሚገኘውን የምስራቁ የኢኮኖሚ እድገት መግታት በአማራጭ ያስቀመጠች ይመስላል፡፡

በዚህ የሁለት አስተሳሰብ መካከል ግን በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ህዝብ ያላት ሃገረ-ኢትዮጵያ ትገኛለች፡፡ ሃገራችን የመዕራቡ ጡንቻ ባበጠ ቁጥር ለምዕራቡ፣ የምስራቁ ጡንቻ በፈረጠመ ጊዜ ደግሞ ለምስራቁ እየተንበረከከች መኖር አለባት የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዋነኝነት የኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎት ማዕከል ያደረገ እንዲሁም ከማንም ተባብሮ መስራት የሚያስችል አቋም ሲኖረን ብቻ የዚህ ሃገር ሰላም ተጠብቆ ይኖራል፡፡

የምዕራቡ አስተሳሰብ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የበላይነቱን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት ከሚያደርግባቸው አከባቢዎች በዋናነት ምስራቅ አቅዎፓ፣ የኮሪያ ልሳነ ምድር፣ ላቲን አሜሪካ እና አፍሪካ (ምስራቅ አፍሪካ) ይጠቀሳሉ፡፡ በምስራቅ አውሮፓ በርካታ ሃገሮች እንዲበታተኑ ያደረገው ይህ አስተሳሰብ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህ አንድ ምሳሌ ጠቅሼ ፅሁፌን ላገባድድ፡፡

ከሶቪዮት ህብረት መፍረስ ጋር ተያይዘው ከተመሰረቱት ነፃ ሃገሮች መካከል ዩክረይን አንዷ ነች፡፡ ሃገሪቷ በህዝብ ብዛቷ እና በጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታዋ ቀዳሚ ሃገር ነች፡፡ የሃገሪቷ ምስራቃዊ እና ደቡብ ምስራቅ ክፍል የሪስኪ (ሩስያ) ቋንቋ ቤተሰብ ያላቸው ሲሆኑ ፤ በእምነታቸውም ከምስራቅ ኦርቶዶክስ (የራሺያ ኦርቶዶክስ) አማኞች ናቸው፡፡ የምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ ራሺያን ለማምበርከክ ካስቀመጣቸው ስትራቴጂዎች አንዱ ዩክሬይን የአስተሳሰቡ ሰለባ ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም እ.አ.አ 2004 በሃገሪቷ የተካሄደውን ምርጫ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የቀለም አብዮት እንደ አማራጭ ተጠቅሞበታል፡፡ በወቅቱ የሃገሪቷ ዜጎች መሪያቸውን መርጠው ለፕረዝደንትነት ያበቃቸው ቪክተር ያንኮቪች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የምዕራቡ አስተሳሰብ ያላካተተ ምርጫ በመሆኑ ምርጫው በብርቱካናማ ልብስ ለባሾች እንዲሰረዝ ተደረገ፡፡

ዘ-ጋርዲያን የተባለ የእንግሊዝ ጋዜጣ በወቅቱ ባቀረበው ዘገባ መሰረት ያንኮቪች ከስልጣን ወርዶ ዩልያ ቲሚ ሾንኮ ስልጣን እንዲይዙ ለማድረግ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይን ጨምሮ ዩኤስ ኤይድ፣ ዓለም አቀፍ የሪፖብሊካን ኢንስቲትዩት፣ ፍሪዶም ሃውስ፣ በጆርጅ ሶሮስ የሚመራ ኦፕን ሶሳይቲ ኢንስቲትዩት፣ ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ የተባሉ 6 ግዙፍ ተቋማት ሁሉን ዓቅማቸው ተጠቅሞ በዩክሬይን ላይ ዘምተዋል፡፡ በዜጎቹ የተመረጠውን መንግስት በሃይል ለመገልበጥ ሰልፍ ለወጡ የዩክሬይን ዓመፀኞች ብርቱካናማ ጃኬት፣ ብርድ ልብስ፣ ምግብና ውሃ እንዲሁም ተሰላችተው ከጎዳናው እንዳይለቁ ተንቀሳቃሽ መፀዳጃዎች ከጀርመን ተገዝተው እንዲጓጓዙላቸው ተደርገዋል፡፡

በዚህ መልኩ ለስልጣን የበቁ ቲሞ ሾንኮቭም ለአሜረካ ድርጅቶች ውለታ ሲባል ሃገራቸውን ለምዕራቡ ዓለም አሳልፈው ከመስጠት በተጨማሪ ቤተሰባዊ ትስስር ፈጥረው የዩክሬይን አንጥሮ ሃብት እንዲባክን አድርጓል፡፡ በሃገሬው ህዝብም ከፍተኛ ቁጣ እንዲነሳባቸው ሆኗል፡፡ በውጤቱም በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ያንኮቪች ከ5 ዓመት በዓመፅ ያጡትን ቤተመንግስት ተረከቡ፡፡ ህዝበ ውሳኔ በማድረግ ለምዕራቡ ዓለም የተሰጠቺው ሃገራቸው ወደ ራሳቸው መመለስ ቻሉ፡፡ በዚህ ሂደት በዩክሬይናዊያን ተወዳጅ በሆኑበት ሰዓት ላይ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ውድድር ለማድረግ 4 ወራት ሲቀራቸው በአፍቃሬ አውሮፓ ዓመፀኞች በአውሮፓ ህብረት እና በኔቶ ተደግፈው ቤተ ምንግስታቸውን ተቆጣጠሩ፡፡ ፕረዝዳንቱ የሰው ደም በከንቱ ከሚጠፋ በማለት ወደ ምስራቃዊ የሃገራቸው ክፍል ለመሸሽ ተገደዱ፡፡ የኪሬሚያ እና ሉሃንስክ ህዝቦች ከፕረዝዳንታቸው ጋር ወግነው ፀረ የተቀረው ዩክሬይን ደም አፋሳሽ ጦርነት ገጠሙ፡፡ ሃገሪቷም በአውሮፓ አፍቃሪ እና በሩስያ አፍቃሪ መካከል ለሁለት ተከፍላ እናገኛታለን፡፡

የሃገራችን ዕጣ ፋንታ ስመለከትም ይህንን ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ በዙርያችን ያሉ ሃገሮች ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ የተረጋጋ መንግስታቸው በመያዝ የዓረብ-አሜሪካ የበላይነት ለመቀበል ዝግጁ እንዳልሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች እያንፀባረቁ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሁለት የተዳከሙ (የሶማልያ እና የኤርትራ) መንግስታት በመያዝ ለዚህ አስተሳሰብ ተገዢ እየሆነች ትገኛለች፡፡ በዚህ ሁኔታ በሃገራችን የልማታዊ ዴመከራሲያዊ መንግስት ህልውና አደጋ ላይ እየወደቀ ብአንፃሩ አክራሪ ካፒታሊዝም ሊስፋፋ የሚችልበት አጋጣሚ እንዲፈጠር ዕድል እየሰጠን ያለን ይመስለኛል፡፡

በ11ኛው ኢህአዴግ ጉባኤ የተላለፈው ውሴኔ መግለጫ መሰረት ከአዴፓ ውጪ ሌሎቹ እህት ፓርቲዎች ልማታዊ ዴመክራሲያዊ እና የመደመር ፍልስፍና የበለጠ ተጠንተው ለፖሊሲ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉበት አግባብ እንዲጠኑ የወሰኑ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ይዘነው የመጣነው አስተሳሰብ እስካልተቀየረ ድረስ እንዴት ነው ለአክራሪ ኒዮ ሊበራል ሐይሎች ምሽግ መሆን የምንችለው? ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር የዚህ ሃገር ብቸኛ ኣማራጭ አይደለም ወይ?

 

Back to Front Page